የመጨረሻው ዘመን ስህተት አሠራሮችና ጥንቃቄ1

በሰለሞን ከበደ 

መጻሕፍትንና የእግዚአብሔር ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ” (ማቴዎስ 2229)

ያለንበት ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የተለያዩ የፀጋ ስጦታዎች የሚታዩበት ነው፤ በአንጻሩ በተመሳሳይ መንገድ የቀደመው እባብ ራሱን እንደ ብርሃን መልአክ በመለወጥ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳት የተነሳበት ጊዜ ነው፤ ቃሉ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” እንደሚል በማስተዋል በጥንቃቄ ልንመላለስ ይገባል (ማቴዎስ 24፡4)። ሃሰት በዙሪያዋ፣ በአጠገቧና በመካከልዋ እየበቀለ ቢያውካትም፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን “የእውነት ዓምድና መሠረት” ናት (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15፣ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡14)። ብዙዎቻችን የመንፈሳዊ እንቅስቃሴን ትምህርትና ትክክለኛነት ከራሳችን ስሜት፣ ልምድ፣ የግል ጥቅም፣ ምቾት፣ ክብር፣ የባህርይ ዝንባሌ ውጪ የምንለካበት ሚዛን ይኖረን ይሆን? አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ቃል አኳያ የመፈተሽ ባሕል አዳብረን ይሆን?

ልብ መባል የሚገባው በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እንቅስቃሴን መመዘን እንቅስቃሴን ለማንኳሰስ ሳይሆን የጠራውን ለመያዝና በዚህም ለመገልገል ከሚፈልግ እውነተኛና ቅን ልብ የተነሳ መሆን አለበት። አንዳንዶች ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ (በፀጋ ስጦታዎች መገለጥ) ስለማያምኑ ለማጣጣል መቃወሚያ ምክንያቶችን ይፈልጋሉ፣ ለድንዛዜም ሰበብ ይሆናሉ። “መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ ፈልጉ” የሚለውን ሃሳብ ገሸሽ ያደርጉታል (1ኛ ቆሮንቶስ 14፡1)። ሌሎች ደግሞ መንፈሳዊ እንቅስቃሴን ስለሚናፍቁ ብቻ የኃይልን መገለጥ ለማድነቅ ስለሚጓጉ ብቻ ያለ ምንም ምርመራ አንዱም እንዳይነካ ከጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ይከላከላሉ፣ ይጋርዳሉ፣ ለሰይጣን ስውርና አሳሳች አሠራር ከለላ ተገን ይሆናሉ። “ሁሉ ለማነጽ ይሁን፣ ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን” የሚለውን የጌታን ትዕዛዝ ሲረግጡ ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆኑ ይመስላቸዋል (1ኛ ቆሮንቶስ 14፡ 37-40)። እነኚህ ሁለቱም አካሄዶች ሊታረሙ የሚገባ ጐጂ አካሄዶች ናቸው።

አንዳንዶች በቃሉ ከመኖር ይልቅ የቃሉ ጠበቆች፣ በመንፈስ ቅዱስ ከመመላለስ ይልቅ ለመንፈስ ቅዱስ የፀጋ ስጦታዎች ነገረ ፈጆችና ተሟጋቾች ለመሆን ይታጠቃሉ። በአንደበት ጠበቃ ለመሆን ከመነሳት ይልቅ በቃልና በተግባር ምስክር መሆኑ ዋናና ተፈላጊ ነገር ነው። "ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አኗኗሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ይሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አመጸኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ አትመኩ፣ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፣ ነገር ግን ከምድር ነው የሥጋም ነው የአጋንንት ነው፣ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ሥፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት። በኋላ ታራቂ ገር እሺ ባይ ምሕረትና በጐ ፍሬ የሞላባት ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል (ያዕቆብ 3፡ 13-18)።

“ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል” እንዲል ቃሉ (ምሳሌ 2፡11) በዚህ ጽሑፍ ዓይነተኛ የሐሰት አሠራር መልኰች ምን እንደሆኑና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ምን መሆን እንዳለባቸው የሚጠቁሙ አሳቦች ተሰንዝረዋል። የ”አዲስ ዘመን” እንቅስቃሴ (“ኒው ኤጅ”) ዘመናዊነትን የሥነ ልቡና ሳይንስን የጥንቆላ አሠራርን የሩቅ ምሥራቃውያንን አስተሳሰብና ፍልስፍናን በማጣመር አዲስ የዓለም ሥርዓት ለመመስረት የሚጥር ሲሆን ለሐሰተኛው ክርስቶስ መምጣት ጥርጊያውን የሚያመቻች ሴራ ነው። ከመንፈስ ሙትነት እንዲሁም በራስ ከተዋጠ ግልብ መንፈሳዊ ሕይወት እግዚአብሔር ይጠብቀን! በጠራና በነጠረ የክርስትና ሕይወት ያመላልሰን፤ አሜን!!

የመጨረሻው ዘመን ወንጌል በዓለም ሁሉ የሚሰበክበት ሰይጣን የመጨረሻው ጊዜ መሆኑን አውቆ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ዓለምን ለጥፋት የሚያስከትትበት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማሳት በከፍተኛ ደረጃ በረቀቀ መንገድ የሚፈታተንበት ነው። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 እንደምንመለከተው ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርበው የመምጣቱንና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምን እንደሆነ ንገረን ብለው ጠየቁት። እርሱም ሲመልስላቸው “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ” አላቸው። ጦርንም የጦርንም ወሬ እንደሚሰሙ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እንደሚነሳ፣ ራብም ቸነፈርም የምድር መናወጥም በልዩ ልዩ ሥፍራ እንደሚሆን እነዚህም እንደ ምጥ ጣር መጀመሪያ እንደሚሆኑ ነገራቸው። ለመከራ አልፎ መሰጠት፣ መገደል፣ ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መጠላት፣ ብዙዎችም እንደሚሰናከሉና እርስ በርስ አልፎ እንደሚሰጣጡ፣ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት እንደሚነሱና ብዙዎችንም እንደሚያስቱ፣ ከዓመፃ ብዛት የተነሳ የብዙ ሰዎች ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ፣ ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ እንደሚሰበክ፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው እንደሚመጣ ገለጸላቸው። ስለ ዘመኑ መጨረሻ ተጠይቆ ጌታ ኢየሱስ ከሰጠው መልስ ውስጥ፦ የመጀመሪያውና አሳሳቢው ምልክት የሐሰተኞችን መነሳት አስመልክቶ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” የሚለው ብርቱ ማስጠንቀቂያ ነው። በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 24-25፣ “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና ቢቻላቸውም የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ” የሚል ተጨማሪ ማስገንዘቢያ እናገኛለን።

እንግዲህ ጌታ ኢየሱስ ሰለ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ነቢያት መነሳት አስቀድሞ ነግሮናል፣ እንዳያስቱንም አስጠንቅቆናል። የትንቢት መነገር የድንቅና የተአምራትም መደረግ አድራጊው የክርስቶስ ወገን ነው፤ የተደረገውም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው ለማለት አያስችለንም። “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም ከቶ አላውቃችሁም እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።”

ከዚህም የምንረዳው ቁም ነገር ጌታ ኢየሱስ ከቶ ሳያውቃቸው፣ ምንም ሕብረት ከእርሱ ጋር ሳይኖራቸው ብዙዎች በስሙ ትንቢት እንደተናገሩ አጋንንትን እንዳወጡ ብዙ ተአምራት እንዳደረጉ የሚቆጥሩና የሚቆጠሩ እንደሚኖሩ ነው። እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ከጌታ ኢየሱስ ጋር በአንድ ወቅት ሕብረት ኖሯቸው በኋላ የተውትን አይደለም። ይህን በማስተዋል እንዳንስት መጠንቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝበናል። “የመንፈስ ቅዱስ ዘመን ነው” የሚለው አነጋገር ተአምራት ሁሉ፣ እየነፈሰ ያለ የመንፈስ እንቅስቃሴ ሁሉ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ነው የሚል ትርጉም እንድንወስድ ተፅዕኖ እያደረገ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ከበዓለ ኅምሳ ጀምሮ የመንፈስ ቅዱስ ዘመን ነው። የ”አዲስ ዘመን” እንቅስቃሴን በየመልኩ የሚያራምዱ ሰዎች ይህ የመንፈስ ዘመን ነው፣ አሁን ወደ መንፈስ ዘመን “አኳርየስ” ዘመን ገብተናል ይላሉ። የ”አዲስ ዘመን” እንቅስቃሴ ስያሜውን ያገኘው ከዚሁ አዲሱ የመንፈስ ዘመን የ”አኳርየስ” ዘመን ከሚል አሳብ ነው።

የውይይት ጥያቄዎች 

  1. ስሕተት በቅድሚያ የሚመጣው ከምን ጉድለት ነው?
  2. የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከሥጋ ወይም ከሰይጣን ሥራ በምን መንገድ ይለያል?
  3. የመንፈሳዊ እንቅስቃሴን ትክክለኛነት እንዳንለይ የሚያግዱንን ነገሮች ዘርዝር፤
  4. የመንፈስ ቅዱስን እንቅስቃሴ በሚመለከት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያቀረባቸውን ሁለት አክራሪና የተሳሳቱ አመለካከቶችን ግለጽ።
  5. መንፈሳዊ እንቅስቃሴን የምንፈልገው ለምንድነው? የኃይልን መገለጥ ለማድነቅ ነው? ለመስማት የምንፈልገው እንዲነገርልን ነው?
  6. የጠራ መንፈሳዊነት እንዲታይብን ልናደርጋቸው የሚገቡን ነገሮች ምንድናቸው?
  7. የዚህ ጽሑፍ አቅራቢመንፈስ፣ መንፈስስለተባለና ትንቢትና ተአምራት ስለታየ ብቻ ከመንፈስ ቅዱስ ነው ማለት አይደለም ይላል፤ የተጠቀሰው የወንጌል ክፍል የትኛው ነው? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሊከሰት መቻሉ ምን ያመለክተናል?            [ክፍል 2 ይቀጥላል]