ስለ ሐዋርያት

ዶ/ር ፒተር ኮትረል በእንጦጦ መካነ ኢየሱስ ቤ/ክ እንዳስተማሩት፣ ዶ/ር ሽመልስ አድማሱ እንዳቀናበሩት።

[አዲስ ኪዳን በተፃፈበት] በግሪክ ቋንቋ “አፖሰቶሎስ” ማለት የተላከ ሰው ማለት ነው። በአማርኛ ደግሞ “ሐዋርያ” ከግእዝ የተገኘ ነው። “ሆረ” በግእዝ ቋንቋ ይሄዳል ማለት ነው። “ሐዋርያ” እንግዲህ የተላከ ሰው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ [ውስጥ] ሁለት ዓይነት ሐዋርያት እንደነበሩ እናውቃለን። በመጀመሪያ 12ቱ ብቻ፤

“በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም፥ ጴጥሮስ ብሎ እንደ ገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብም፣ ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ይሁዳም፥ አሳልፎ የሰጠውም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው።” (ሉቃ. 6፥12-16)

ደቀ መዛሙርት ብዙ ነበሩ። አሥራ ሁለት ብቻ አልነበሩም። ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ፣ አሥራ ሶስት፣ አሥራ አራት፣ አሥር አይደለም። ኢየሱስ የመረጠው አሥራ ሁለት ብቻ ነበር። እነርሱም የተመረጡት በኢየሱስ ነው፣ ራሱ ኢየሱስ ነበር የመረጣቸው። እንደ ምናውቀው ይሁዳ አስቆሮቱ ኢየሱስን አሳልፎ ሰጠ። ስለዚህም አሥራ ሁለት የነበሩት አሥራ አንድ ሆኑ። በሐዋርያት ሥራ እንደምናገኘው ደቀ መዛሙርት ተሰብስበው አሥራ አንድ የነበሩት እንደገና አሥራ ሁለት እንዲሆኑ ቆረጡ።

“በዚህም ወራት ጴጥሮስ መቶ ሀያ በሚያህል በሰዎች ማኅበር አብረው በነበሩ በወንድሞቹ መካከል ተነሥቶ አለ። ወንድሞች ሆይ፥ ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባ ነበር፤ ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበርና፥ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበርና። ….ስለዚህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ሰዎች፥ ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል። እዮስጦስም የሚሉትን በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን አቆሙ። ሲጸልዩም። የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ፥ ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው አሉ።” (የሐዋ ሥ. 1፥15-17፤ 21-26)

ሐዋርያት እንግዲህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ክርስቶስ እስካረገበት ድረስ ካዩት አንዱን መረጡ። አንደኛው ዓይነት ሐዋርያት ማለት ከደቀ መዛሙርት ጋር ከሌሎች ደቀ መዛሙርት ጋር ከነበሩት ሰዎች ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ክርስቶስ እስካረገበት ድረስ ከእነርሱ ጋር የነበረ ነበር። ሌላ አይደለም። እኔም ያን ወቅት አልነበርኩም። በዮሐንስ ጥምቀት ጊዜ ከክርስቶስ ጋር አልነበርኩም። እናንተም አልነበራችሁም። ኢየሱስ ሲገባ ሲወጣ ከእርሱም ጋር አልነበርኩም፥ እናንተም አልነበራችሁም። ስለዚህ ሐዋርያ አይደለሁም፣ እናንተም ሐዋርያት አይደላችሁም። ሐዋርያት አሥራ ሁለት ብቻ እንደነበሩ ማወቅ አለብን። ግን ከእነዚህ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሌላ ሌሎች ሐዋርያት እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል።

“ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥” (የሐዋ ሥ. 14፥14) በርናባስና ጳውሎስ ሐዋርያት ነበሩ። ይሁን እንጂ በርናባስና ጳውሎስ ከአሥራ ሁለቱ ውጪ ነበሩ። ለምን? እነርሱ ከአሥራ ሁለቱ ውጪ የነበሩት ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ኢየሱስ እስካረገበት ቀን ድረስ ከሌሎቹ ጋር ስላልነበሩ ነው። በዚህ ምክንያት እንግዲህ እንደ አሥራ ሁለቱ አልነበሩም። ይሁን እንጂ ሐዋርያት ነበሩ። ከአሥራ ሁለቱ በላይ የተጨመሩት እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ደግሞ ነበሩ። ለምሳሌ አንዲራኒቆና ዩልያን ፤ “በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ፥ ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ፥ አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንዲራኒቆንና ለዩልያን ሰላምታ አቅርቡልኝ።” (ሮሜ 16፥7) በሮሜ እንግዲህ እዚህ እንደተጻፈው ብዙ ነበሩ፣ ሁለት ብቻ አልነበሩም ብዙ ነበሩ። ነገር ግን እንደ አሥራ ሁለቱ አይደሉም። በርናባስና ጳውሎስ የተጠሩት በማን ነበር? “በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምኦንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ።” (የሐዋ ሥ. 13፥1-4) በመንፈስ ቅዱስ የተመረጡት ግን በክርስቶስ ኢየሱስ የተመረጡት አልነበሩም። ኢየሱስ አሥራ ሁለት መረጠ፤ አሥራ ሦስት አይደለም፤ አሥራ አራት አይደለም፤ ከአሥራ ሁለት በላይ አልነበሩም። ጳውሎስና በርናባስ የተላኩት በቤተ ክርስቲያን ነበር፤ የተመረጡት ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ነበር። እንግዲህ ሁለተኛው አይነት ሐዋርያ እንዴት ያለ ሰው መሆን አለበት? “እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን? የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ።” (1ቆሮ. 9፥1)

በዚያን ወቅት አሥራ ሁለት ሐዋርያት ነበሩ። ግን ከእነርሱም [ሌላ] ሌሎች አማኞች ክርስቶስን አይተውት ነበር። ከእነርሱ ክርስቶስን ካዩት ሰዎች መንፈስ ቅዱስ አንዳንድ መረጠ። ሁለተኛው ዓይነት ሐዋርያት እንዲሆኑ ነው። አንደኛው ዓይነት ሐዋርያ [ማነው]? አሥራ ሁለቱ ብቻ! ሁለተኛው ዓይነት ሐዋርያ [ማነው]? ከእነዚህ ከአሥራ ሁለቱ በላይ (የተጨመሩት) የሆኑት ሐዋርያት ናቸው። ግን አሥራ ሁለቱ ለብቻ ናቸው። በእነርሱ [ላይ] የተጨመረ ማንም የለም። ኢየሱስ እንግዲህ አሥራ ሁለት የመረጠው በምን ምክንያት ነው ብለን ልንጠራጠር እንችላለን። መልሱ ግን ቀላል ነው። በመጀመሪያ እንዳልኩአችሁ ኪዳኖች ስንት ናቸው? ሁለት፥ አይደሉም? ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን። በብሉይ ኪዳን ዘመን ስንት ወገኖች ነበሩ? አሥራ ሁለት! በአዲስ ኪዳን ስንት ሐዋርያት አሉ? አሥራ ሁለት! በብሉይ ኪዳን ዘመን የህዝቡ መሪዎች አሥራ ሁለት ነበሩ በአዲስ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔር ህዝብ መሪዎች እንደዚሁ ደግሞ አሥራ ሁለት ናቸው። የያዕቆብ ልጆች አሥራ ሁለት ብቻ ነበሩ (ዘፍ. 35፥22)። በዘፍ 49 ቡራኬ አለ፥ ይህ ቡራኬ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች ነበረ። ኢያሱ ምዕራፍ 4 ውስጥ አምስት ጊዜ አሥራ ሁለት ተጽፎአል። በብሉይ ኪዳን ወገኖች አሥራ ሁለት ነበሩ። በአዲስ ኪዳን ዘመን ደግሞ አሥራ ሁለት መሪዎች አሉልን።

“ከዚያ በኋላም አየሁ፥ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ። ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ። ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም፥ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፤ ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን እንቍ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ። በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።” (ራእይ 4፥1-4) ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ። ሃያ አራት የተባለው በምን ምክንያት ነው? እነዚያ ዙፋኖች አሥራ ሁለት ስለ ብሉይ ኪዳን፤ አሥራ ሁለት ስለ አዲስ ኪዳን፤ አሥራ ሁለት፣ ስለ አሥራ ሁለቱ የአይሁድ ወገኖች፤ አሥራ ሁለት፣ ደግሞ ስለ አዲስ ኪዳን ሐዋርያት፤ በጠቅላላው 24 ናቸው። ማንኛውም ሰው ከብሉይ ኪዳን [ሥር] ከነበሩት ወይም ከአዲስ ኪዳን [ሥር] ከነበሩት ሰዎች ሁሉም ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡት ህጉን ስለጠበቁ አይደለም። አይደለም። ለምን? ህጉን ስላልጠበቁ ነው። በብሉይ ኪዳን [ሥር] የነበሩት ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት የገቡት በእምነታቸው ምክንያት ነበር። በአዲስ ኪዳን በታች ያሉት ሰዎች ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡት ስለምንድነው? በእምነታቸው ምክንያት። ሁለቱም ወገኖች አንድ ናቸው። እንደ ምሳሌ ሆኖ ሁሉም አንድ ላይ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ። በመንግሥተ ሰማያት በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት 24 ዙፋኖች አሉ። በአንድ በኩል አሥራ ሁለት የብሉይ ኪዳን ወገኖች፣ በአንድ በኩል ደግሞ የአዲስ ኪዳን አሥራ ሁለት ሐዋርያት። ስለዚህ አሥራ ሦስት ሐዋርያት ሊኖሩ አይችልም፥ 14 ሊሆን አይችልም፥ 20 ሊሆን አይችልም። እንደ ዛሬው እኔም ሐዋርያ ነኝ፣ እኔም ሐዋርያ ነኝ፣ እንደ ሐዋርያት አንዱ ነኝ የሚሉት ሞኞች ናቸው።

አሥራ ሁለቱ ደግሞ እንዴት ያሉ ሰዎች ናቸው? አማኞች ብቻ አይደሉም። አሥራ ሁለቱ ከዮሐንስ ጥምቀት ጊዜ ጀምሮ ክርስቶስ እስካረገበት ቀን ድረስ ከክርስቶስ ጋር የነበሩት ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ነበሩ? [አልነበሩም]! በመጥምቁ ዮሐንስ ጊዜ ነበሩ? አልነበሩም! አሥራ ሁለት ብቻ ናቸው። ጠቅላላ እንግዲህ አሥራ ሁለት፣ አሥራ ሁለት፣ 24 ናቸው። ብሉይ ኪዳን እንደ አዲስ ኪዳንም ሁለቱም አንድ ላይ መንግሥተ ሰማይ ሊገቡ ይችላሉ። በእነርሱ [ላይ] ልንጨምር አንችልም። “ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።” (ራእይ 21፥14) አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት። መሠረት ስንት ነው? አሥራ ሁለት! በዚያም በእያንዳንዱ የተጻፈው ምንድነው? የአሥራ ሁለቱ ስሞች ነው። ከአሥራ ሁለት በላይ ሊሆን አይችልም። ሐዋርያነት እንግዲህ ሊተላለፍ ይችላል ዎይ? ለምሳሌ ሐዋርያው ዮሐንስ ምናልባት እጁን በሌላ ሰው ላይ ጫነ [እንበል]፣ እንግዲህ ሐዋርያነት ከእርሱ ወደ ሌላ ተላለፈ? [አልተላለፈም]። ለምን? ሐዋርያ ማለት ከዮሐንስ ጥምቀት ጊዜ ጀምሮ ክርስቶስ እስካረገበት ቀን ድረስ ከክርስቶስ ጋር ለነበሩት ሰዎች ብቻ ነው። ሌላ በዚያን ዓይነት ሐዋርያ ሊሆን አይችልም።

“ሐዋርያ” በፊት እንዳልኩት “ሄደ” ማለት ነው። የሄዱት ሰዎች፣ የተላኩት ሰዎች በእኔ አስተያየት እንጃ ምናልባት ሚሲዮናውያን ሐዋርያት ናቸው። እነርሱም ይሄዳሉ። የእግዚአብሔርን ቃል ይሰብካሉ ያስተምራሉ። ፈረንጅ [ይሁን] ኢትዮጵያዊ፣ ከሀገሩ ወደ ሌላ ሀገር፣ እዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ገጠር ሲላክ እርሱ ምናልባት ሐዋርያ ሊባል ይችላል። ነገር ግን እንደ አሥራ ሁለቱ አይደለም። አሥራ ሁለቱ የተለዩ ሰዎች ናቸው። ዛሬም እንግዲህ ሐዋርያት አሉ ዎይ? ለሚለው ጥያቄ እኔ በበኩሌ የሉም እላለሁ፣ በፍጹም የሉም። አንደኛው ወይም ሁለተኛውም አይነት የሉም እላለሁ። ለምን? ኢየሱሰ በተጠመቀ ጊዜ [ሐዋርያ የሆነ ሰው] አልነበረም። ኢየሱስ ባረገ ጊዜ[ም] አልነበረም። ስለዚህ እኛ ሐዋርያት አይደለንም። በተለይም በአሥራ ሁለቱ ላይ አንድም ልንጨምር [አንችልም]። ይሁን እንጂ መሪዎች በቤተ ክርስቲያን አሉ። እነርሱ ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጡ መሪዎች ናቸው። ለእነርሱ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሃላፊነት እንደተሰጠ እናውቃለን። እነርሱ እንግዲህ እንደ መሪዎች ሆነው የእግዚአብሔርን ቃል እያጠኑ፣ የእግዚአብሔር[ን] ቃል እያስተማሩ እንዲመሩ ይገባቸዋል። እነርሱን ደግሞ መስማት አለብን። የእነርሱን [ትምህርት] ልንቀበል ይገባል። ይሁን እንጂ ያንን ቃል ሰምተን እውነት መሆኑን አለመሆኑን ልናው[ቅ] የምንችለው የእግዚአብሔርን ቃል ስንመረምር ብቻ ነው። በመጀመርያ የእኔ ቃል ምንም ጥቅም የለውም። የእነርሱም ቃል ምንም ጥቅም የለውም። ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተስማሚ የሆነ እንደሆነ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እንደ ቤርያ [ሰዎች] እናንተም ደግሞ ወደ ቤት ስትሄዱ እለምናችኋለሁ፣ መጽሐፍ ቅዱስ [መርምሩ]። እነዚህን ጥቅሶች አንብቡ። ይህ [ሰው] የተናገረው ቃል እውነት ነዎይ ብላችሁ ጠይቁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተስማሚ ከሆነ [ትምህርቱ] ከእግዚአብሔር መሆኑን ልታውቁ ትችላላችሁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ከሆነ ዋጋ የለውም፣ [ይህንንም] ልታውቁ ትችላላችሁ። እግዚአብሔር ይባርካችሁ!

ይህን ጽሑፍ በ2009 አትመነው ነበር፤ በዚያን ወቅት እንዳደረግነው ዛሬም “ሐዋርያዊ አገልግሎት” የሚሰጡ ሁሉ፣ ያላቸውን መረዳት በዚሁ መድረክ እንዲያስረዱና፣ ዝምታቸው “አንጠየቅም” የሚሉ እንዳያስመስልባቸው፣ ይህን ጥሪ በድጋሚ እናስተላለፋለን። “ሁሉ ለማነጽ ይሁን።” ማስታወሻ፦ በ [ቅንፍ] የተመለከቱት የተናጋሪውን አሳብ ግልጽ ለማድረግ የተጨመሩ ናቸው።