ለጸሎት ምቹ ጊዜ

በፀሐይ ዓለሙ

jesusknockingእውነተኛ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ምልጃ ነው። ሆኖም ልብና አንደበት አንድ ሆኖ ሲናገር ነው የሚሠራው። የሰው መንፈሱ ሳይሰበሰብ የልቦናው ሁኔታ ሳይሰበር ፈጽሞ ወደ እግዚአብሔር ማቅናት አይቻልም። ቃሉ እንዲህ ይላል፦ እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል (መዝ 3418)።

በራሳችን ችግራችንን መፍታት የማንችል ፍጥረት ነን። ሁልጊዜ ከአቅማችን በላይ የሆነውን የምናቀርበው፣ ሁሉ ወደ ተቻለው አምላክ ነው። መንፈሳችን የሚቃትትበት ልባችንም ተሰብሮ እግዚአብሔርን የሚፈልግበት ሰዓት ለጸሎት ምቹ ጊዜ ያ ነው። ብዙ ሳንዘበዝብ ከእውነትና ከቅንነት ፈቃድ ተነሥተን ከልባችን ያለውን ሁሉ ለጌታ ገልጠን የምናሳየው፤ ያን ጊዜ ነው የእርሱ ጥገኛ እንደሆንን በጥልቁ የምንገነዘበው።

እግዚአብሔር በባህርዩ ትሑት ነው። በትሕትናም የሚቀርበውን ሁሉ ይቀርበዋል። መንፈሱ የተሰበረበትንም ሰው ያድነዋል። በገበያ መካከል እንሁን በቤተ መቅደስ የልባችንና የመንፈሳችን ሁኔታ ወሳኝ ነው። ልብና መንፈስ ሲሰበር፣ ራስን ሁሉን በሚችል ጌታ ፊት አምጥቶ ለመጣል አይከብድም። በዚያችም ሰዓት እግዚአብሔር ለመርዳት ቅርብ ነው። ጥልቅ የሆነ የውስጥ ልብ ልቅሶ አለ፤ ማንም የማይሰማው በነፍሳችን ውስጥ የሚፈስ ኀዘን አለ፤ ያንን በቃላት መግለጽ ሲሳን በደንብ ሊያየንና ሊረዳን የሚችል የምንጠራው አምላክ ነው። እርሱ ያለ ተስፋ አይተወንም። ቃሉ እንዲህ ይላል፦ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው፣እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ (መዝ 1053-4)። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፣ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፣ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፣ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፣እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና (ሮሜ 826-27)።

ወደ ጌታ ጸባዖት ከቀረብን በኋላ ጽናት አለ፤ ብርታት ይተካል፤ ፍርሃትና ድንጋጤም ይሸሻል፤ ጨለማው ርቆ ብርሃን ይቀርባል። ቃሉ እንደሚል፦ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፤ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃኗ ነው (መዝሙር 13911-12)። ልብ ተስፋ ሲያገኝ ይበረታል፤ ቀጥሎ ያለውን ሰዓት በመጽናናት መጠበቅ ይችላል። እግዚአብሔር እኰ የተሸነፈውንና የተርገደገደውን ልብ የሚያነሳ እንጂ የሚጥል አይደለም። ጌታ ልክ እንደ ቃሉ ነው፦የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስን ክር አያጠፋም፤ በእውነት ፍርድን ያወጣል፤ በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ይበራል እንጂ አይጠፋም፣ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ (ኢሳይያስ 423-4)። የተስፋ ሁሉ አምላክ በፍጥረቱ ላይ አይጨክንም፤ በተለይም በሰው ልጆች ላይ! ምክንያቱም እርሱ ተፈጥሮአችንን ያውቃል፣ ከአፈርም እንደ ሠራን ያስባል፣ ምንም እንደማንችል ዘመናችንም ፈጥኖ እንደሚያልፍ ይረዳል። ስለዚህ፦ ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፣ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል፦ የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፣ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፣ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘላለም አልጣላም፣ ሁልጊዜም አልቆጣም ይላል(ኢሳ. 5715-16)። እግዚአብሔር በመንፈሳቸው የቆዘሙትን ምስኪኖች ሁሉ የሚያስጠጋ አምላክ ነው፤ እርሱ ከእስትንፋሳችን ይልቅ ቅርብ ነው፤ ከልባችንም ይልቅ ታላቅ ነው። ስለዚህ የትም እንሁን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ልባችን በፊቱ ተሰብሮ እስከ ቀረበ ድረስ እግዚአብሔር ቀርቦ ይረዳናል፤ ሁኔታዎችንና እኛንም ይለውጣል።

ፓስተር ፀሐይ ዓለሙ በናሽቪል ጸጋ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን አገልጋይ ነች።                      1/30/2011