እግዚአብሔር ከእኛ ምን ይፈልጋል?

በመለሰ ወጉ

እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ብዙ አስደናቂ የሆኑ ስጦዎችን ሰጥቶናል። ከስጦታዎቹ መካከል አንደኛው ጥሩ የሚያስብ አእምሮ ነው። ጥበብና ዕውቀት ሰው ከእግዚአብሔር የሚሰጠው መሆኑን ብዙ ቦታ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል። “ጥበብን ለጠቢባን፣ ዕውቀትንም ለአስተዋዮች የሚሰጥ እርሱ ነው” ይላል [ዳንኤል 2፡21] እንዲሁም ሰለሞን “በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ጠቢባን መሆን ይገባቸዋል፤ ምክንያቱም ጥበብን ማግኘት ርስትን የመውረስ ያህል ነው” ይላል [መክብብ 7፡11]።

በዘመኑ ያለነው አማኞች እግዚአብሔር የሰጠንን መልካም አእምሮ ምን ያህል እንጠቀምበት ይሆን? እርግጥ ነው እግዚአብሔር የዓለም ጠቢባንን ሊያሳፍር የመረጠው ተራ ሰዎችን ነው። ይሁን እንጂ “ተራ ሰዎች” በእግዚአብሔር እጅ ሲገቡ አዋቂዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም። አልፎ አልፎ የምንሰማው አስተያየት እግዚአብሔር በሰጠን አእምሮ መጠቀም መንፈሳዊነት እንደ ጎደለው ነው። “በእግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በሰው ዕውቀትና ጥበብ አልመራም” የሚለው አነጋገር የተለመደ ሆኗል። “ጥበብን አልፈልግም” ማለት “የእግዚአብሔርን ስጦታ አልቀበልም” ማለት ይሆናል። ጥበብ አስፈላጊ ባይሆን ኖሮ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ቢኖር እግዚአብሔርን ይለምን፣ እግዚአብሔርም ይሰጠዋል፤ ምክንያቱም እርሱ ምንም ሳይከለከል ለሁሉም በልግስና የሚሰጥ ቸር አምላክ ነው” [ያዕቆብ 1፡5] በማለት እንድንጸልይ ባልተናገረን ነበር። መንፈስ ቅዱስ ለአማኞች ጥበብን በመስጠት የማይታየውን፣ የተደበቀውን ምስጢር ይገልጻል። “ዕውቀትን ወይም ጥበብን አልፈልግም” ማለት “መብራት አጥፍቼ ጨለማ ውስጥ መቀመጥ እፈልጋለሁ” ማለት ይመስላል። ይኼም ሞኝነት ነው።

እግዚአብሔር አሻንጉሊት አድርጎ አልሠራንም። እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ሕይወት ብዙ አስደናቂ ስጦታዎች ሰጥቶናል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቻችን በባትሪ የሚሠራ አሻንጉሊት እንመስላለን። ሲያስቀምጡን የምንቀመጥ፣ ሲያንቀሳቅሱን ብቻ የምንንቀሳቀስ፣ “ተናገሩ” የተባልነውን ብቻ ምንም ሳንጨምር ወይንም ሳንቀንስ የምንናገር ነን። ማንንም ቅር ማሰኘት አንፈልግም። በራሳችን አእምሮ ሳይሆን በሌሎች አእምሮ የምናስብ፣ እንመስላለን። ሕይወታችን ወዴት እንደሚያመራ ወሳኞቹ ሌሎች እንዲሆኑ የፈቀድንላቸው ይመስላል። ከፈቃዳቸው ውጪ መውጣት ድጋፋቸውን የሚያሳጣን ስለሚመስለን እነርሱ ከደነገጉትና ካወጡት ሕግ አንወጣም። የራሳቸው አቋም የሌላቸው ሰዎች ደካሞች ናቸው። የኑሮ ጓደኛ የምትፈልግ ወጣት የሕይወቱ አቅጣጫ ወዴት እንደሚያዘነብል የሚያውቀውን፣ አደጋ ያለበትም እንኳን ቢሆን ሳይፈራ በድፍረት እርምጃ የሚወስደውን፣ “ምን እያሰበ ይሆን?” እያለች የማትጠራጠረውን ወንድ ባል እንዲሆናት ትመርጣለች እንጂ፣ “አንቺ እንዳልሽ ብቻ ይሁን” እያለ የሚኖረውን፣ የራሱ የሆነ መመሪያ ራእይ የሌለውን ወንድ አትፈልግም።

ዕውቀት ይቀርጸናል። ነገር ጨልሞ የሚታያቸው ሰዎች በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጡ፣ የሚበሳጩ፣ የተስፋ ማጣት ስሜት የሚያጠቃቸው ናቸው። በራሳቸውና እንዲሁም በሌሎች ሰዎች እምነት የላቸውም። የሚያዩት ከፊት ለፊታቸው ያለውን፣ ግልጽ ሆኖ የሚታያቸውን ብቻ ነው። ነገር ብሩህ ሆኖ የሚታያቸው ሰዎች ግን የሚያዩት ከፊት ለፊታቸው ያለውን፣ ጨለማውንና ጉሙን ብቻ ሳይሆን በአሻገር ራቅ አድርገው የመመልከት ችሎታ ስላላቸው የጠራ ሰማዩን፣ ከዋክብቱን፣ ፀሐዩንና ጨረቃውን ያያሉ። እነዚህ ከላይ የገለጽናቸው ሁለት ዓይነት ሰዎች ሁለቱም ያሉበት ሕይወትና አካባቢ አንድ ዓይነት ቢሆንም አስተያየታቸውና አመለካከታቸው ፍፁም የተለያየ ነው። ያላቸው አመለካከት የሕይወታቸውን እድገትና እርምጃ ወሳኝ ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ኢየሱስ ስለ ሦስቱ አገልጋዮች በምሳሌ የተናገረውን ታሪክ እናስታውሳለን። አንድ ሰው አገልጋዮቹን ጠርቶ እንደ ችሎታቸው ለአንዱ አምስት ሺህ ብር፣ ለአንዱ ሁለት ሺህ ብር፣ ለአንዱ ደግሞ አንድ ሺህ ብር እንዲነግዱበት ሰጥቶ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። ከብዙ ጊዜ በኋላ መጣን ከአገልጋዮቹ ጋር ሂሳብ መተሳሰብ ጀመረ። አምስት ሺህ ብር የተሰጠው ሌላ አምስት ሺህ ብር አተረፈ። ሁለት ሺህ ብር የተሰጠው ሌላ ሁለት ሺህ ብር አተረፈ። አንድ ሺህ ብር የተሰጠው ግን ምንም ሳያተርፍ ዋናውን ይዞ ቀረበ። ለምን እንዳላተረፈ ምክንያቱን ሲገልጽ፣ “ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁና ሄጄ ገንዘብህን በመሬት ውስጥ ቀበርሁት፤ ይኸውልህ ገንዘብህ አለው” [ማቴዎስ 25፡ 24-25]። በተሰጣቸው መክሊት የተጠቀሙበት ጌታቸውን ደስ ያሰኙት ከመሆናቸውም ሌላ፣ ሽልማታቸው ትልቅ ነበር። በመክሊቱ ያልተጠቀመበት ጌታውን ከማሳዘኑም በላይ ፍርዱ ከባድ ሆነ።

የተሰጠውን መክሊት እንዴት መጠቀም እንደሚችል ራእይ ያልነበረው ያ ሰው ሁሉ ነገር ጨልሞ ታየው። በራሱና በጌታው ላይ እምነት አልነበረውም። ሁሉ ነገር አስፈራው። የራሱን ድክመት ወደ ሌላው ማስተላለፍ ጥሩ ምክንያት ይሆነኛል ብሎ ስላሰበ ጌታው የሌለውን ባህርይ መስጠት ጀመረ። “…ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ…” አለ። በራሱ እምነት የሌለው፣ የራሱ የሆነ መመሪያ ወይንም ራእይ የሌለው ሰው እጁን አጣምሮ መቀመጡ ብቻ ሳይሆን የሚሠሩትን፣ የሚንቀሳቀሱትን መንቀፍ፣ ልዩ መልክና ቅርጽ ማውጣት እንዲሁም ልዩ ልዩ የቅጽል ስም መስጠት ይጀምራል። በራሱ ሕይወት መልካም ነገር ማየት የማይችል መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሰዎች ሕይወትም በጎ ነገር አለ ብሎ አይገምትም። ሁልጊዜ ተጠራጣሪና ፈሪ ነው።

ጥበብንና ዕውቀትን መፈለግ ኃጢአት ይሆን?። ሰው በተፈጥሮ “የዕውቀት፣ የጥበብ” ፍላጎትና ጥማት በውስጡ አለ። ይኼም በመጀመሪያዋ ሴት በሔዋን ሕይወት ታይቷል። “ሴቲቱ ዛፉ … ጥበብን የሚያስገኝ እንደ ሆነ በተመለከተች ጊዜ…” ይላል [ዘፍጥረት 3፡6]። የሔዋን ችግሯ “ጥበብን” መፈለጓ ሳይሆን “ጥበብን” ለማግኘት የሞከረችው ከመስመር በወጣ መንገድ በመሆኑ ነው። “እግዚአብሔር ለሰለሞን እጅግ አስደናቂ የሆነ ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሁም ወሰን የማይገኝለትን ዕውቀት ሰጠው” [1ኛ ነገሥት 4፡29] ይላል። “ጥበብ” አስፈላጊ ባይሆን፣ የማይጠቅም ቢሆን ኖሮ ለሰለሞን እግዚአብሔር ጥበብን ባልሰጠውም ነበር። ሰለሞንም የጥበብን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ባይጠይቅ ኖሮ መቀበል ባልቻለም ነበር። “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?”[2ኛ ዜና 1፡7] የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት፣ ሰለሞን “ሕዝብህን በትክክል ለመምራት የሚያስችለኝን ጥበብና ዕውቀት ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ግን ታላቅ ሕዝብህን እንዴት ልመራ እችላለሁ?” [2ኛ ዜና 1፡10] ሲል ጥበብ እንዲሰጠው ጠየቀ። እግዚአብሔርም “… ጥበብና ዕውቀትን መጠየቅህ ትክክል ነው፤ ስለዚህ እነሆ የጠየቅኸውን ጥበብና ዕውቀት እሰጥሃለሁ …” [2ኛ ዜና 1፡11-12] አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቀድሞ መንፈሳዊ አባቶች ጥበብንና ዕውቀትን በጣም ከተመኙ፣ በዘመኑ ያለን አማኞች ጥበብና ዕውቀት አያስፈልገንም ለምን እንላለን? “ጥበብና ዕውቀት” ለመንፈሳዊ ዕድገታችንና አገልግሎታችን ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም። “በጥበብ እንራመድ” የሚለውን አማኝ፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች “የደረቀ ክርስቲያን ነው፣ መንፈስ ቅዱስ የለበትም” ይሉታል። ለምን ይሆን?

  1. በማስተዋል ሕይወቱን ለመምራት የሚፈልግ ሰው፣ ብዙ ጊዜ “ስሜቱን” ብቻ ተከትሎ የሚሄድ ስላልሆነ፣ በቀላሉ በስሜት ሲከንፍ አይታይም። “ስሜት” የለውም ማለት ሳይሆን ስሜቱን መስመር ማስያዝ ስለሚችል ለሰዎች አይታይም። ሌሎች ስለ አደረጉት ብቻ እኔም ማድረግ አለብኝ አይልም። ውጪያዊ የሆነ እንቅስቃሴ እንደ አንዳንዶቹ ባለማሳየቱ “የታሠረ ነው፣ መንፈስ የለበትም” ይባል ይሆናል። ይህን ዓይነት አስተያየት እንዲሰጥበት ካልፈለገ፣ የግድ አካባቢውን መስሎ መገኘት አለበት። ይሁን እንጂ በአእምሮው የበሰለ ስለሆነ፣ እነርሱን ለመምሰል ብቻ ምንም ነገር አያደርግም።
  2. በጥበብና በማስተዋል ሕይወቱን የሚመራ፣ ለአእምሮው ነጻነት አይከለከልም። በአእምሮው ውስጥ ጥያቄ ቢፈጠር፣ ያልገባውን ቢጠይቅ “ኃጢአት ነው” ብሎ መቀበል አይሆንለትም። ይህን የሚያዩ አንዳንድ አማኞች “አንተ በአንጎልህ ነው የምትመራው” ሲሉ ወቀሳ ያሰሙታል። “ጥሩ ክርስቲያን ነው” ብሎ የሚያስጠጋው ሰው ስለማይኖር ብቸኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ ያለው ዕውቀትና ጥበብ ይኸውም በማስተማርና በአስተዳደር ሊጠቅም ሲችል ያለ አገልግሎት ተገፍቶ ከዳር መቀመጡ ነው። ቤተክርስቲያንን በተለያየ የአገልግሎት ዘርፍ ሊጠቅሙ ሲችሉ “በዝምተኛነታቸው” ብቻ ዕውቀታቸውና ጥበባቸው የሻገተባቸው ስንት ይሆኑ?
  3. በጥበብና በማስተዋል ሕይወቱን የሚመራ የነገሩትን ሁሉ “እሺ እንዳልክህ” ብሎ የሚቀበል፣ “ተቀመጥ” ሲሉት የሚቀመጥ፣ “ተናገር” ሲሉት ብቻ የሚናገር፣ “አድርግ” የሚሉትን ብቻ የሚያምን አይደለም። ይህን ማለት ትሕትና የጎደለውና የማይታዘዝ አስቸጋሪ ሰው ነው ማለት አይደለም። ካልገባው የሚጠይቅ፣ ካልተስማማው “አልተስማማኝም” የሚል ነው። የማይጥምና የማይዋጥለት ነገር ሲያጋጥመው እየመረረው ዝም ብሎ የሚውጥ አይደለም። ስለዚህ “ስሜታዊ” ለሆኑት አንዳንድ ሰዎች፣ የእንዲህ ዓይነቱ ሰው አቋም እንግዳ ስለሚሆንባቸውና እነርሱን ስለማይመስል ብቻ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሌለበት፣ በጥበብና በዕውቀት ብቻ የሚመራ አድርገው ይገምቱታል።

አእምሮአችንን እንቅረጽ። የእግዚአብሔርን ሥራ በተቀላጠፈና በአማረ መልክ ለመሥራት ጥበብና ዕውቀት ያስፈልገናል። ያለ ጥበብ ለመሥራት መሞከር በደነዘ መጥረቢያ እንጨትን ለመቁረጥ እንደ መሞከር ይሆናል። “የደነዘ መጥረቢያውን የማይስል ሰው ኃይሉን በከንቱ ይጨርሳል፤ ስለዚህ ጥሩ ውጤት ለማግኘት በጥበብ መሥራት ያስፈልጋል” ይላል [መክብብ 10፡10]።

ዶ/ር መለሰ ወጉ የኢትዮጵያውያን የወንጌል አገልግሎት መሥራችና መሪ ናቸው። እዚህ ይመልከቱ፦ http://www.eomusa.org/ ይህ ጽሑፍ ከብርሃን መጽሔት/ገጽ 17-18፣ ቁ.22/1988 ዓ.ም. የተወሰደ ነው።                                                           3/31/2010 | 4/22/12