ግብዝ

pharisee-tax-collectorግብዝ ሰው "ያልሆነውን እንደሆነ፣ የማይችለውን እንደሚችል፣ ወይም ያላደረገውን እንዳደረገ አድርጎ የሚያስብና ያላግባብ ለራሱ ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ ሰው" ነው ይላል አንድ መዝገበ ቃላት። ሐዲስ ኪዳን በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ "ግብዝ" ሕልም ተርጓሚ፣ ተናጋሪ፣ ቅኔ አነብናቢ ወይም ተዋናይ የሚል ትርጉም የነበረው ቃል ነው። ኋላ፦ አስመሳይ፣ መሠሪ፣ ቅንነት የጎደለው የሚል ትርጉም እያገኘ ሄዶ የቀደመውን መሠረቱን ለቀቀ። እውነት ሲቀያየጥ እንግዲህ ንጹሕ ይመስላል፣ ግን እድፍ ነው። ቅን ይመስላል፤ ጽድቅ ይመስላል፤ አመጽ ነው። ቸርነት ይመስላል፤ ስርቆት ነው። ፍቅር ይመስላል፤ ወጥመድ ነው። እውነት ሲቀያየጥ አገልግሎት ይመስላል፣ መወዳጃና መረዳጃ ነው። ስብከት ይመስላል፤ "ንቃት" ነው። እንደ ተዋናይ፣ በጭንብል ተከልለው ያወራሉ፤ ድምጻቸውን ይለዋውጣሉ። ቃላት ይዥጎደጎዳሉ፤ እውነትን ወደማወቅ ግን አያደርሱም። በሰከነ አእምሮ ማሰብ እንዳይቻል ጩኸት ያበዛሉ፤ ፋታ ይነሳሉ። ስንፈታቸውን "መንፈስ መንፈስ" እያሉ ሰው ያካልባሉ። "በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ" ሲለን፣ ማሰብና መጠየቅን፣ ሥጋዊነት ነው ያሰኛሉ።

"ግብዝ" በዕብራይስጡ፦ ምግባረ ብልሹነትን፣ እግዚአብሔርን የሚጻረርና የሚዘነጋ ባሕርይን ለመግለጽ ይጠቀማል። ባጭሩ፣ ግብዝነት የሚመረጥ ክርስቲያናዊ ስነምግባር አይደለም። ይልቁን ቅንነት ይኑራችሁ ተብለናል። ቅኖች እግዚአብሔርን ያያሉ፤ እግዚአብሔርን ያሳያሉ። ኢየሱስ፣ "እናንተ ግብዞች" ያላቸው፣ በሰዎች ዘንድ ሊከበሩ፣ በምኩራብና በመንገድ፣ በፊታቸው መለከት የሚያስነፉትን ለመውቀስ ነው። ሲጸልዩና ሲመጸውቱ ለታይታ ስለሆነ ዋጋቸውን ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰው ተቀብላችኋል ይላቸዋል። በጓዳቸው አይጸልዩም፤ በምኩራብና በየማዕዘኑ መጸለይ ያበዛሉ። በረጅም ጸሎት እያመካኙ የማይጠረጥሩትን ይበዘብዛሉ። ስለጽድቅና ስለታማኝነት ሳይገዳቸው "መንፈሳዊ" ምክንያት እየፈጠሩ አሥራት ያ[ስ]ወጣሉ። በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ያጠራሉ። በአንደኛው እጃቸው የሰጡትን በሌላኛው መልሰው ይነጥቃሉ። ግብዞች መሆናቸው ሳያንስ ሌሎችን የባሰ ግብዝ ያደርጋሉ። ከውጭ አምረው ይታያሉ፤ ዳሩ ግን፣ የሙታን አጥንት፣ አመጽ፣ ርኩሰትም የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮች። በከንፈራቸው ያከብሩኛል ልባቸው ግን ከኔ የራቀ ነው ይላቸዋል። ስለ ፍቅር ያወራሉ፤ ልባቸውና ደጃቸው ግን ላልቦደናቸው ዝግ ነው። ራሳቸው የማይኖሩበትን ትምህርት ሌሎች እንዲከተሉ ይመክራሉ፣ ያዝዛሉ። ግብዝነት ባለበት የእውነት ቃል ይራከሳል፤ ክፋት፣ ተንኰል፣ ቅንዓትና ሐሜት ይወደዳል።

የዛሬይቱ ቤተክርስቲያን የምትገኝበትን ሁኔታ "በረከት"፣ "ሹመት"፣ "ጥበብ" በሚሉ ቃላት ዙሪያ መግለጽ ይቻላል። በረከት፣ ለገንዘብ ፍቅር መሸፈኛ ሆኗል። ሹመት ወይም ቅባት ለሥልጣን ጥማት፤ በሌላው ላይ ለመሠልጠን። ጥበብ፣ ለማግባቢያና ለማታለያ። "መንጋው እንዳይበተን" ገዷቸው ሳይሆን፣ መንጋው ከተበተነ የሚሰበሰበው ገንዘብ ሊያንስ ስለሆነ ነው! መንጋ እንዲበዛ [ገንዘብ እንዲበዛ] የወንጌልን እውነት ማላላት ይመረጣል። አንድነት የሚገኘው እውነትን በመነጋገር ውስጥ እንደሆነ እየታወቀ፣ እውነቱ ሳንሡር ይደረጋል። ጥበብ ይኸ ነው? ምእመን ከመተማመን ይተማማ? ጥበብ ይኸ ነው?

ጥበብ ምንጩ ልዩ ልዩ ነው። ዓለማዊ ምድራዊ ሥጋዊ ጥበብ አለ። የአጋንንት ጥበብ አለ። ሰማያዊ ጥበብ አለ። ወደ ዝርዝር ሳንገባ፣ በአብዛኛው የሚታየው ጥበብ ሰማያዊው አይደለም ብለን እንለፈው። ላይኛይቱማ "በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት [ያዕቆብ 3፡13-18]። ሰማያዊ ጥበብ ሲጎድል ቅንዓት፣ አድማ፣ ሁከትና ክፉ ሥራ ይንሠራፋሉ። ለቤተክርስቲያን ላለመገዛት ሰበብ ይፈጥራሉ። ከ"ጽዮን" ቤተክርስቲያን ተከፍለው ይወጣሉ፤ እልፍ ይሉና "አዲሲቱን ጽዮን" መሠረትን ይላሉ። ተላክን የሚሉ ሳያጣሩ፣ ሳያቅማሙ ከነአመጹ ያጸኑላቸዋል። "ጥበብ" በንስሃም ውስጥ ይከሰታል። ንስሃው ግን፣ መሸፈኛ እንጂ፣ እውነተኛ ንስሃ ሆኖ፣ ሕገወጥ አሠራሮች ተስተካክለው አይደለም። ጅራፍ እሱው ይገርፍ እሱው ይለፍ[ፍ] ማለት ይኸ አይደል?

ሥልጣን በሌላ መልኩ፦ ያልተጠሩ፣ ስለ ጥሪአቸው ጉባኤ ያልመከረበትና ያላመነበት፣ ከየት እንደመጡ ያልታወቁ በግርግር ሲሰየሙ ማለት ነው። ያልተሾሙ ሿሚ የሆኑበት ማለት ነው። ግርግር ለማን እንደሚመች እናውቃለን። በልባቸው ምኞት መጠን ይተነብያሉ። የራሳቸውን ቃል እግዚአብሔር አፍ ውስጥ ይጨምራሉ። ሥልጣን ግን በትህትናና በማስተዋል፣ ሌላው ከኔ ይሻላል ብሎ በማገልገል እንጂ በሌሎች ላይ በመሠልጠን አይደለም።

የገንዘብ አሰባሰብና ወጪ አደራረግ ተጨማሪ ግንዛቤ ይሰጣል። ጉባኤውን በስሜት አጋግለው አለማወቁንና ገርነቱን ይበዘብዛሉ። እያንዳንዱ በአጥቢያው እንጂ በየአጥቢያው የሚካሄደውን አለማወቁ ያለውን አሠራር አንድ ላይ ለማገናዘብ እንዳይቻል አድርጓል። ባለፉት አምስት ዓመታት በድረ-ገጾች፣ በመጽሔቶችና በመጽሐፎች የሚተላለፉትን ስብከቶች፣ ትምህርቶች፣ መዝሙሮችና "ሚኒስትሪዎች"ን፣ በተለይም የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናትን ሁናቴ ስንከታተል እንደቆየነው፣ ሁሉንም በአንድ ተርታ ማየት ቢቻል በጌታ ስም ንግድ እየተጧጧፈም እንደሆነ ማወቅ በተቻለ ነበር። ገንዘብ ወጥቶ ምእመን ጸጋውን ለይቶ እንዲያገለግል ቢያስችል ባልከፋ። ምእመን ተመልካች፣ የጌታ ቤት የጥቂቶች ጉዳይ ሲሆን። "ዘና በሉ። የተለያዩ ባለራእዮችን እያፈራረቅን እናዝናናችሁ" የሚባልበት። ትኩረቱ፣ የመስቀሉን የኃይል ሥራ መስማትና በጌታ ቁምነገር ውስጥ ማደግ ሳይሆን አዳዲስ ነገሮችን ማሳደድ ሲሆን። የእውነት ቃል ስለጎደለ ምእመን "ምን አነካካኝ፣ ተሳልሜ ልመለስ" ብሏል። ሚዛን ያጣ መንፈሳዊነት ሰብዓዊነትን ለመካድ ብቻ ሳይሆን ከተጠያቂነት ለመሸሽ ጥሩ ማምለጫ ዘዴ ፈጥሯል።

ሥልጣን ደግሞ፣ ራሳቸውን የሾሙ ራሳቸውን በሾሙ በሌሎች ሲሾሙ ነው። ግብዝነት ይኸ ነው። ያልሆነውን እንደሆነ፣ ያልተገባውን እንደተገባው፣ የማይችለውን እንደሚችል፣ ለራሱ ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ። የእግዚአብሔር ቀርቶ፣ ሰው ይታዘበኛልን የማያውቅ። ጌታ ግን በሐዋርያቱ አፍ እንዲህ ይላል፦ "ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ ...በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል ... የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው ... መንፈስ ግን በግልጥ። በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው ... ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ ... እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።" ለእውነት መቆም እውነቱን ሳያውቁ አይደለም። እውነቱን አውቆ መቆም መስዋእት ያስከፍላል። ልባቸው ለቆረጠ ግን የሰው ሙገሣና ነቀፌታ አይበግራቸውም፤ እግዚአብሔርን ይታመናሉና። ጌታ የሚሠራው እንደዚህ ካሉት ጋር ነው። [ሮሜ 12፥9። 2ኛ ቆሮንቶስ 6፥6። 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥5፤ 4፥1-2። 1ኛ ጴጥሮስ 1፥22፤ 2፥1-3]

ማንኛችንም ከግብዝነት የጠራን አይደለንም። እውነትን አውቀን ከእውነት ጋር ካልተጣበቅን፣ እውነትን ከመፍራት ይልቅ እውነትን ካልወደድን፣ ጸጋን ካልተለማመድን በስተቀር ከተገለጠልን እውነት ማፈግፈጋችን አይቀርም። ልንሰማ የምንፈልገውን የሚነግሩንን ብቻ መሰብሰብ እንጀምራለን። ግብዝነት በቅድሚያ ራስን ከማክበር ሰውን ከመፍራት ከሰዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ከመፈለግ የሚመጣ ነው። ቅንነትና ትኅትና ሲጎድል ነው። እግዚአብሔር አንዱን ዘር ባሕልና ቋንቋ ከሌላው እንደማያበላልጥ ጴጥሮስ ተረድቶ ነበር። "ነገር ግን፣" ይላል ጳውሎስ፣ "ኬፋ [ጴጥሮስ] ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና። አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን። አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት" [ወደ ገላትያ ሰዎች 2፥11-14]። ጴጥሮስ ትኁት ሰው ነበረ፤ ከዚህ ሁኔታ ተማረ። በመጀመሪያ መልእክቱ [1፡22]፦ "ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ" ሲል የቀደሙንንና እኛን መከረ።

ግብዝነት ይታገለናል። እጅ ልንሰጥ ወይም ስም ልንቀይርለት ግን አይገባም። ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማስተያየት እናቁም፤ ፊታችንን ወደ እግዚአብሔር እናቅና። ዓይናችንን በራሳችን ላይ እንዲገልጥ የእግዚአብሔርን መንፈስ እንማጠን። ማንም የሚያታልለን ሆነን እንዳንቀር፣ ብዙ ማስተዋል እንዲጨመርልን እንጸልይ። ቃሉ እንደሚነግረን፣ እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንኑር። እንዳንሳብ ከግብዞች እንጠንቀቅ። እውነትን ከሚወዱና ለእውነት ከሚታዘዙ ጋር እንያያዝ። ጌታ አንድ ነው፤ ትልቅ አንድ ብቻውን የሆነ ኃያል እግዚአብሔር ነው። መለዋወጥ በርሱ ዘንድ የለም፣ በመዞርም የተደረገ ጥላ በርሱ ዘንድ የለም፣ እርሱ የብርሃናት አባት ነው፤ ብርሃን ነው፣ ጨለማም በርሱ ዘንድ ከቶ የለም፣ ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን፣ እውነትንም አናደርግም፤ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፣ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል [ያዕ 1፡17፤1ኛ ዮሐ 1፡5-7] "በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፤ ምድር ሁሉ በፊቱ ትነዋወጥ፤" [መዝ 96፡9]