የዛሬው ጥናታዊ ጽሑፍ ስለ አሥራትና በኩራት ዶ/ር ቶለሳ ጉዲና በዋሽንግተን ዲሲ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ባስተማሩትና በ "ዲቪዲ" እና በ “ዩቱብ” በተሠራጨው ትምህርት  ላይ ይሆናል።  የጽሑፉ ደራሲ እሙዬ ሜጫ የተሰኙ የቨርጂንያ “ኢማኑኤል ባይብል ቸርች” አባል ናቸው። ጽሑፉን ከመለጠፋችን በፊት ዶ/ር ቶለሳ አንብበው ምላሽ እንዲሰጡበት በስልክና በኢሜል ልናገኛቸው ሞክረን አልተሳካልንም። አንባቢው ሁለቱንም ምልልሶች ጎን ለጎን ቢያነባቸው ይበልጥ ይጠቀማል ብለን አስበን ነበርና። እንደ ደረሰን የዶ/ር ቶለሳን ምላሽ እናትማለን። ማሳሰቢያ፦ ይህ ጽሑፍ ላለመስጠት ሰበብ ሊሆነን አይገባም። ስጦታና በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው … ያልተቀበልነው አለን የምንለው ምንም የለም … ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው፣ ብሏልና [ያዕ 1፡17፤ 1ቆሮ 4፡7፣ የሐዋ ሥራ 20፡35]። በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ፣ ስለ አሥራት የተለያዩ ልምዶችና መረዳቶች እንዳሉም አንርሳ። ጥያቄው፣ የቱ በዘልማድ ነው? የቱ ገንዘብ ለመሰብሰቢያ? ቃሉስ ምን ይላል? የሚለው ነው። በመጨረሻ፣ ብሉይና ሐዲስን እንዳንነጣጥል እንጠንቀቅ። ኢትዮፕያንቸርች። 7/16/12

በውኑ አዲስ ኪዳን ስለ መስጠት እንጂ ስለ በኩራትና አሥራት ያስተምራል?

በእሙዬ ሜጫ

በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አጥቢያዎች ውስጥ ከምስባኮች ላይ የሚተላለፉ የስብከትና የትምህርቶችን መጽሓፍ ቅዱሳዊ ይዘት በጥንቃቄ ፈትነንና መርምረን እንቀበል ዘንድ የግድ የሚለን ነገር አለ። መጽሓፍ ቅዱስስ ስለ እንደነዚህ ዓይነት ትምህርቶችና ስብከቶች ምን ይላል? ብሉያትና ሐዲሳት በየራሳቸው የነገረ-መለኮት ዐውድ ምን ይላሉ? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። አብዛኛዎቻችን ፓስተሮቻችንና ቄሶቻችን ስላስተማሩትና ስለሰበኩት ያልገባንን ነገር መጠየቅ እንዳለብን አናስብም። ምናልባትም ብንጠይቃቸው እንደ አለማመንና እንደመጠራጠር ስለሚቆጥሩብን ጥያቄዎችን አንስተን ለመጠየቅ አንደፍርም፤ ልቡም የለንም። ወንጌላዊው ሉቃስ በቤርያ ይገኙ ስለ ነበሩ ሰዎች ሲተርክልን ግን «ዕለት ዕለት መጽሓፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ልብ ተቀበሉ» ይለናል (የሐዋ ሥራ17፡11)። የዚህ ምክንያቱ ልበ ሠፊነታቸው እንደ ነበር በዚሁ ክፍል ፍንትው ብሎ ተቀምጧል። ቃሉን በሙሉ ልብ ለመቀበልና በሕይወት ለመለማመድ ቃሉን በልበ ሠፊነት በቅድሚያ መመርመር ያስፈልገናል። ቃሉን በጥልቀትና በልበ ሰፊነት መርመር ቃሉን በሙሉ ልብ ለመቀበልና በሕይወታችን ለመተርጎም ብቻ ሳይሆን፣ እርስ በርስ ለመተራረምም ይረዳል። ቃሉን የማያውቅ በቃሉ ላይ ተንተርሶ የሚሰጥን ኑፋቄን ወይም የስህተትን ትምህርት ማረም እንደማይችል እውቅ ነው። እድሉም የለውም።

የቃሉን ሥልጣንና ማዕከላዊነት ጠብቀን እርስ በእርስ መተራረም ለመማማር፣ ለመተናነጽና ለመንፈሳዊ እድገት ይጠቅማል። ደግሞም መሠረት እንደሆነ አምናለሁ። ይህ ካልሆነ ግን ክፋት፣ መለያየትና መከፋፈል ከፊት ይልቅ እያደገ ይመጣል። በመጨረሻም አትራፊው እግዚአብሔር ሳይሆን ሰይጣን ይሆናል። እንግዲህ ይህንን እውነት በመንተራስና ዓላማ በማድረግ ነው ይህንን አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ የተነሳሳሁት። በተጨማሪ፣ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አባል የሆኑ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ አሥራትና በኩራት ዶ/ር ቶለሳ ጉዲና ጁን 3/2011 ያቀረቡት ስብከታዊ ትምህርት ጥያቄ እንደፈጠረባቸው በማየቴ ነው። እዚህ ላይ አንድ ነገር በቅጡ ልብ እንዲባልበትና አጽንዖት እንዲሰጥበት እፈልጋለሁ። ይኸውም የጽሑፉ ትኩረት ግለሰብ ላይ አለመሆኑን ነው። አንባቢውም በዚህ ረገድ የራሱን ጥንቃቄ ያድርግ። ትምህርቱ ባጭሩ፦ በኩራትህን በዓመት አንድ ጊዜ ሙሉ ደሞዝህን ስጥ፤ አሥራትህን በወር አንድ ጊዜ፤ መባህን በየሳምንቱ፤ የፍቅር ስጦታህን ምን ጊዜም ወደ ካህኑ ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያን በማምጣት ለእግዚአብሔር ቀድስ የሚል ሲሆን፣ በመጨረሻም ዘላለማዊ መዋለ ነዋይ (ማትረፊያ “ኢንቬስትመንት”) የሚል ነበር። ከትምህርቱ መግቢያ እስከ መደምደሚያ ድረስ ከእግዚአብሔር ቃል የተወሰዱትና የተነበቡት ክፍሎች (ዘዳ 26፡1፣11፤ዘጸ 3፡11፤23፡16፤1 ነገ17፡8፤ምሳሌ 3፤ማቴ 6፡25) ናቸው።

ብሉያት ስለ አሥራትና በኩራት ምን ያስተምራሉ?

በቅዱሳት መጽሓፍት ከ600 በላይ ሕግጋት፣ ትዕዛዛትና ሥርዐቶች በሙሴ በኩል ለቀደመው የኪዳን ሕዝቦች ለእስራኤላውያን ተሰጥቶ ነበር። እነዚህን ሕግጋት ከነገረ-መለኮት አኳያ በጥቅሉ የሞራል፣ የልዩ ልዩ ሥርዓቶችና የማህበረሰብ ሕግ ብለን ልናስቀምጣቸው እንችላለን። በዚያ ኪዳን ውስጥ እንደ ሌዊ ክህነት በሆነው የአገልግሎትና የመቅደስ ሥርዓት መሠረት እስራኤላውያን ከማንኛውም ከሚያገኙት ገቢ በሕጉ በተደነገገው መሠረት ወደ አሮን በማምጣት ለእግዚአብሔር እንዲቀድሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር (ዘሌ 22፡30)። ይህ የመቅደስ አገልግሎትና ክህነትም ኢየሱስ ክርስቶስ በነበረበት ዘመን ቀጥሎ እንደ ነበር ወንጌላቱ ያስነብቡናል (ሉቃ 5፡14)። በዚህ ክፍል «እርሱም ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፥ ነገር ግን። ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ አለው።» ይላል። ይህ ክፍል በቀጥታ የሚመራን በዘሌዋውያን 13 ላይ ወደ ተመለከተው የሙሴ  ትዕዛዝ ነው። አይሁዶች በእዚሁ በቀደመው ኪዳን የሕግ ትዕዛዝ መሠረት፣ ከሚያገኙት ሁሉ አሥራት ይከፍሉና መባና መስዋዕትንም ያቀርቡ እንደ ነበር፣ ነገር ግን ፍርድንና ምህረትን እንደተው በሚያስገነዝበው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የወዮታ ንግግር ላይ እንዲህ ተመልክቷል፦ «እናንተ ግብዞች  ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና  ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።» (ማቴ 23፡23)

ከጌታችን ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በኋላ፣ ለአዲስ ኪዳን ማህበረሰብ (አማኞች) የቀደመውን ኪዳን የመቅደስ አገልግሎት ማለትም አሥራትና በኩራት እንደ መስዋዕት በማቅረብ እንዲቀደስ ትዕዛዝ አልቆመለትም። በዚህ ጉዳይ የአዲስ ኪዳን ጸሓፍትም ምንም ያሉት ነገር የለም። ምክንያቱም «የክህነት አገልግሎቱ ሲለወጥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ ግድ ነውና» (ዕብ 7፡11፣12)። የአሮን ሹመት ወይም የሌዊ ክህነት ጊዜያዊ ነበር፤ እንደመልከ ጼዴቅ ሹመት የተመሰለው የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት ግን የዘላለም ነው (ዕብ 5፡5-10፤7፡11-12)። የሙሴ ሕግ ለአንድ ማህበረሰብ ይኸውም ለእስራኤል ሕዝብ ሲሰጥ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕግ ግን የተሰጠው ለዓለም ሁሉ ሕዝብ ነው (ሉቃ 22፡20፤ ማር 14፡24፤ 2ቆሮ 5፡19)። ስለዚህ በገንዘብ ጉዳይ ያለው የኢየሱስ ክርስቶስና የአዲስ ኪዳን መመሪያ «መስጠት» እንጂ በኩራት፣ አሥራት፣ መባና መስዋዕት የሚል አይደለም። ከኢየሱስ ክርስቶስ መመሪያ በመነሳት፣ አዲሱ የእግዚአብሔር ማህበረሰብ በወንጌል አማካይነት በሚደረገው የእግዚአብሔርን መንግሥት የማስፋፋት ተልዕኮ፣ ሠርተን ካገኘነው መስጠት ይጠበቅብናል። ነገር ግን አሥራት መስጠት በማቆማችን ርግማንና መቅሰፍት እንደሚያገኘን ማስተማር አዲስ ኪዳናዊ መሠረት የለውም። ከብሉያት በመጥቀስ በእስራኤል ካህናትና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የበረከትና የመርገምን ትምህርት በማስተማር አማንያንን ግራ ማጋባት፣ ማስጨነቅና ሥነ ልቦናዊ  ውዥንብርን መፍጠር፣ እንዲሁም አሥራት ባለ መስጠቱ እንደሚቀሰፍ አድርጎ ማቅረብ መታረም ያለበት አካሄድ ነው።

በአንድ በኩል ጸንፎ በመሄድ እንደ ጉም ያለ ተስፋ ለማስጨበጥ መሞከር ትልቅ ስህተት ነው። ይህ ዓይነቱ ስህተት ለመምህራኑ ብቻ ሳይሆን ሳያጣራ እንደወረደ ለሚሰማውም ሕዝበ ክርስቲያን ጭምር ነው። ቅዱስ ቃሉ «ስለምትሰሙት ተጠንቀቁ » ይለናልና ነው (ማቴ 12፡37)። የቃሉ አስተማሪዎች የሚያስተምሩት፣ ምዕመኑም የሚሰማው፣ ሙሉ ሥልጣን ባለው በቃሉ ሊፈተሽ ይገባዋል። ከመድረኮች የሚነገረውና የሚሰማው ሁሉ መመርመር አለበት። ቃሉ ከመድረክ ሲተላለፍ በማስተዋልና በጽሞና ልናደምጥ ይገባናል (ነህምያ 8፤2፡9-10)። በነህምያ ዘመን ሕዝቡ ቃሉን በማስተዋል ስለ ሰሙ በመጨረሻ ልባቸው ተነካ፣ አለቀሱም። በቃሉ ስንነካ ያለ ማንም ቀስቃሽ “አሜን” እንላለን። ሕዝቡ አስተውሎ እንዳይሰማ “አሜን በል እባክህ! አሜን የማይል ጉባኤ የታሰረ ነው፣ አሜንታችሁ እስኪ ይገፍትረኝ” የመሳሰሉት የሰባኪዎች ተጽዕኖ የሚመቸው ለግርግር ነው። ግርግር ባለበት ሰው ባልገባው ነገር “አሜን፣ አሜን፣ አሜን” እንጂ በጥንቃቄ ማድመጥ አይኖርም።

ብሉይና አዲስ ኪዳናት በየዐውዳቸው ሲነጻጸሩ፦

emuyetblአዲስ ኪዳን ስለ መስጠት ያለው መርህ ይህን ይመስላል።

1. ማንኛውም አማኝ ገንዘቡን ለእግዚአብሔር ሥራ ከመስጠቱ በፊት ራሱን መስጠት አለበት (2ቆሮ 8፡5)። 2. ገንዘቡን መስጠት ያለበት በግድ ሳይሆን በሙሉ ፈቃደኝነት ነው (2ቆሮ 9፡7)። 3. ሲሰጥም በደስታ (ከልቡ) መስጠት አለበት (2ቆሮ 8፡12፤ 9፡7)። 4. በአቅሙ መስጠት፤ የእግዚአብሔር ጸጋ ከበዛለት ደግሞ ከዚያ በላይ መስጠት ይችላል (2ቆሮ 8፡3፣12፤ የሐዋ ሥራ 11፡29)።

የመስጠት አስፈላጊነት፤

1. ትክክለኛውን ወንጌል ለሚያስተምሩና ለሚሰብኩ ደመወዝ ለመክፈል ወይም ኑሮአቸውን ለመደገፍ (1ቆሮ 9፡14፤ 1ጢሞ 5፡1-8)። 2. የተራቡትን ለመመገብ (የሐዋ ሥ11፡29)። 3. መበለቶችንና ባል የሞተባቸውን ሴቶች ኑሮ ለመደገፍ (ያዕ1፡27)። 4. የተቸገሩትን ለመርዳት (1ቆሮ 16፡2)። አዲስ ኪዳን ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያን የመስጠታችን ዋና ዓላማ የሚያደርገው እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ነው። ከዚህ ውጭ ያለው ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ መታየት እንዳለበት አስባለሁ። በተጨማሪ አዲስ ኪዳን አሥራትን፣ መባን፣ በኩራትንና መስዋዕትን ለእግዚአብሔር መቀደስ የሚል ትምህርት የለውም።