ተሐድሶ

የነህምያን መጽሐፍ መሠረት ያደረገ ትምህርት

በተድላ ሲማ

ተሐድሶ ማለት ሁኔታዎች እግዚአብሔር ወዳሰበው ወይም ወዳሰመረው መስመር ሲመጡ ማለት ነው። የዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ዘመን ከነበረችው በእጅጉ የተለየች ሆናለች። ይህም ከቅድስና፥ ከፍቅርና እግዚአብሔርን ከመፍራት አንጻር ሊታይ ይችላል። እንደ ቤተ ክርስቲያን የት ነው ያለነው? እንደ ክርስቲያን ተሐድሶ አያስፈልገንም? ቤተ ክርስቲያን ያለነቀፋ መሆኗ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ተሐድሶ እንዲመጣ ከተፈለገ ግን ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። እነዚህም፣ አንደኛ፣ የነገሮች ወይም ሁኔታዎች መበላሸት ወይም የቀድሞ ሁኔታቸውን ማጣት፤ ሁለተኛ፣ በሁኔታዎቹ መበላሸት የሚቆጭና የሚያዝን ሰው መኖር (ሸክም ያለው ሰው መኖር)፤ ሦስተኛ፣ የተበላሸው ሁኔታ እንዲቀየር እርምጃ የሚወስድ ሰው መኖር (ዋጋ የሚከፍል ሰው መገኘት) ናቸው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተሐድሶ ካመጡ ሰዎች አንዱ ነህምያ ነው። የነህምያን መጽሐፍ ስንቃኝ ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ሁኔታዎች ተሟልተው እናገኛለን። በመጀመሪያ፣ የኢየሩሳሌም የቀድሞ ሁኔታ ተበላሽቶ ነበር። ቅጥሮቿ ፈርሰው፥ በሮቿ ተቃጥለው፥ ሕዝቧ ተማርከውና ከምርኮ የተረፉትም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ ነበሩ (ነህምያ 1:3)። በአጠቃላይ የህዝቡ ውጫዊ እና መንፈሳዊ ሁኔታ የተበላሸ ነበር። ሁለተኛ፣ ሁኔታውን ሲያይ የተቆጨ፥ ያዘነና ትልቅ ሸክም የወደቀበት ሰው ነበር። ያም ሰው ነህምያ ነበር፦ “ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥አያሌ ቀንም አዝን ነበር። በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር” (1:5-11)። በመቀጠልም የተበላሸውን ሁኔታ ለማስተካከል እርምጃ የወሰደን ሰው [ነህምያን] እናገኛለን። የመጀመሪያው እርምጃ በጌታ ፊት መጾምና መጸለይ ነበር። ከዚያም እግዚአብሔር ሁኔታዎችን ሲያመቻችለት ለንጉሡ ጥያቄ አቀረበ። በመቀጠልም የምቾት ቀጠናውን በመተው ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስደውን ረጅም ጉዞ ተያያዘው።

bldgwalls

ዋጋ ሳይከፈል ተሐድሶ አይመጣም። የተሐድሶ ሰዎች ቁርጠኞች ናቸው። ሌላ የምናስተውለው፣ ተሐድሶ ለማምጣት አንድ ሰው በቂ መሆኑን ነው። ይህ ሰው የነቃ፥ የተነቃቃና የሚያነቃቃ ሲሆን ሁኔታዎች መለወጥ ይጀምራሉ። ነህምያ የተበላሸ ሁኔታ እንዳለ ሲያይ ይህ ልክ አይደለም ብሎ ነቃ። በመቀጠልም በጾምና በጸሎት ተነቃቃ። በመጨረሻም ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ሕዝቡን አነቃቃ። እንዲህ አላቸው፦ “እኛ ያለንበትን ጉስቁልና፥ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮቿም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ። አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ” (2:17)። ይህንን ሲሰሙ ሕዝቡ ተነቃቁ፦ “እንነሣና እንሥራ” አሉ (2:18)።

ተሐድሶና ተግዳሮቶች

ተሐድሶ ለማምጣት የሚንቀሳቀስ ሰው የተለያዩ ተግዳሮቶች ይገጥሙታል። ነህምያም በእስራኤላውያን መካከል ተሐድሶ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውታል። እርሱም ለእያንዳንዱ ተግዳሮት ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ወደ ተሐድሶ ሊደርስ ችሏል። ከዚህ በመቀጠል ነህምያ የገጠሙትን ስድስት ተግዳሮቶችና ለነዚህም ተግዳሮቶች የሠጠውን ምላሽ እናያለን። የመጀመሪያው ተግዳሮት የተቃዋሚዎች የንቀት ሳቅ ነበር፦ “በንቀት ሳቁብን” ሲል ይገልጸዋል (2፡19)። አላማውም ተስፋ ማስቆረጥ ነበር። ለዚህ ነህምያ የሠጠው ምላሽ የእምነት ቃል መናገር ነበር፦ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል። እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን” (2:20)። ለተሐድሶ ስንነሳ ሰይጣን ተስፋ ሊያስቆርጠን ይሞክራል። እኛም እንደ ነህምያ የእምነት ቃል በመናገር ወደሚቀጥለው ሥራ መሸጋገር አለብን። ይህ ባልተሳካ ጊዜ የነህምያ ጠላቶች በቁጣና በብስጭት በመነሳት በአይሁድ ላይ ማላገጥና መቀለድን ተያያዙ፦ “በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል” የሚል ፌዝ አፌዙ (4:3)። አሁንም አላማቸው ተስፋ ማስቆረጥና ልባቸውን ማድከም፣ ከተሐድሶው ሥራ መግታት ነበር። ነህምያ ለዚህ የሠጠው ምላሽ እየጸለየ ሥራውን ማቀላጠፍ ነበር (4:5-6)። ከዚህም የተነሣ የቅጥሩ ሥራ በዚህ ሰዓት እስከ እኩሌታው ተጋጠመ (4:6)።

በተሐድሶ የተግባር ሂደት ውስጥ የሚገጥሙንን የጠላት ፌዝና ልብ አድካሚ ተግዳሮቶችን ለጌታ በጸሎት በመንገር ሥራችንን ማቀላጠፍ አለብን። የትኩረት አቅጣችንን ለማግኘት ጠላት ደፋ ቀና ማለቱን አይተውም። ሁልጊዜ በጸሎት መንፈስ ውስጥ ልንሆን ይገባል። ሦስተኛ፣ ቀጣዩ የጠላት ስትራቴጂ እስራኤልን ለመውጋትና ለማሸበር መማማል ነበር (4:8)። ይህንንም የጠላት ሤራ ለማክሸፍ እነ ነህምያ ያደረጉት የሚከተለውን ነው፦ “ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን …ከቅጥሩም በስተኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን፥ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው” (4:9፣13)። ለተሐድሶ የሚነሱ ሰዎች የጠላት ኢላማ መሆናቸው የማይቀር ነው። በመሆኑም በጌታና በኃይሉ ችሎት በመበርታት ጠላትን በመዋጋት፥ዕቅዱንና አሳቡን ሊያፈርሱ ይገባል። ምሽግን ለማፍረስ ብርቱ የሆኑ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎች አሉን። የእግዚአብሔርን ቃል፥ እምነትን፥ የኢየሱስን ስም፥ የህብረት ጸሎትና የደሙን ኅይል በመጠቀም የጠላትን ውጊያ ሁሉ ልናፈርስ ይገባል። የምንዋጋው ከተሸነፈ ጠላት ጋር መሆኑን መዘንጋት የለብንም (ቆላስያስ 2:15፥ ዕብ 2:14፣15፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3:22)።   

ነህምያ የገጠመው ሌላው ተግዳሮት በእስራኤላውያን መሐከል የተነሣው የውስጥ ችግር ነበር። የነበረባቸው የኢኮኖሚ ችግር የተጀመረውን ተሐድሶ ተፈታትኗል። እስራኤላውያን የእስራኤላውያን ወገኖቻቸውን የእርሻ መሬቶች በብድር ምክንያት ይዘውባቸው ነበር። ሕዝቡ ተርቦ ነበር። ይህ የውስጥ ችግር ከሌሎቹ ተግዳሮቶች ይልቅ ነህምያን አስቆጥቶት ነበር። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደ ተሐድሶ ስንገሰግስና በተሐድሶ ውስጥ ስንሆን የሚገጥመን ትልቁ ተግዳሮት ከውጪ የሚመጣው የጠላት ሠልፍ ወይም ውጊያ ሳይሆን በቅዱሳን መካከል የሚነሳው ጠብና ሹክቻ ነው። ነህምያ የገጠመውን ችግር በጥበብ ሊፈታው ችሏል። እኛም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተሐድሶ ወቅት የሚገጥመንን ችግር በጠብ ሳይሆን በጥበብ ልንፈታው ይገባል። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የተነሡ ተሐድሶዎች ሊገቱ የቻሉት በቅዱሳን መካከል በተነሱ አለመግባባቶች፥ ፀቦች፥ ሹክቻዎችና ራስ ተኮር አካሄዶች እንጂ ከውጪ በሆነ ውጊያ አለመሆኑን እንገነዘባለን። እግዚአብሔርን ያላማከለ ሕይወትና የራስን ክብር መፈላለግ የመስቀሉ ጠላቶች ስለሆኑ የጌታን ሥራ ያበላሻሉ። ለዚህ መፍትሄው ራስን መካድና ለጌታ መኖር ነው።   

ሽንገላ ነህምያን የገጠመው ሌላኛው ተግዳሮት ነበር። ጠላቶቹ ከዚህ በፊት የሞከሩት አፍራሽ ስልት ሁሉ እንዳልተሳካና የማደሱ ሥራ ሳይገታ መቀጠሉን ሲያዩ ሽንገላ ጀመሩ። ለርሱ የተቆረቆሩ በመምሰል ነህምያን አምስት ጊዜ ለምክክር ስብሰባ ጠሩት፦ “እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር” የሚል ጥሪ ላኩ (6:2-9)። ለዚህም ነህምያ የሠጠው ምላሽ፣ “ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም” የሚል ነበር። ጠላት ሁልጊዜ የሚፈልገው የጀመርነውን የተሐድሶ ሥራ አቋርጠን ከከፍታችን እንድንወርድ ነው። በተሐድሶ ሥራ ውስጥ ያለ ሰው ለጠላት ሽንገላ አግባባዊ መልስ ሊሠጥ እንጂ የትኩረት አቅጣጫውን ሊስት አይገባም። የመጨረሻው የጠላት ሙከራ ሐሰተኛ ነቢይ በመላክ ነህምያ የማይገባውን እንዲያደርግና በደል እንዲፈጽም ለማሳሳት ነበር (6:10-14)። ሆኖም ነህምያ የጠላቶቹን ሤራ በማስተዋል ከስህተት ሊጠበቅ ችሏል። የዲያቢሎስን ሽንገላ እንድንቃወም የእግዚአብሔር ቃል ያሳስበናል (ኤፌሶን 6:11)። ዓለምን ያሳተው የቀደመው እባብና ዘንዶ (ሰይጣን ወይም ዲያቢሎስ) ዋና ሥራው መሸንገልና ማሳት ነው። በእግዚአብሔር ቃልና በጥበብ በመሞላት ሤራውን ልናስተውል ይገባል። “በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን አሳብ አንስተውምና” ይላል (2ኛ ቆሮ.2:11)። እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች በድል ከተወጣ በኋላ ነህምያ ለተሐድሶ መምጣት ምክንያት ለመሆን ችሏል። እልህ አስጨራሽ የነበረውን ውጣ ውረድና ፈተና ካለፉ በኋላ እነ ነህምያ የሚከተለውን ውጤት ለማየት በቅተዋል። በነህምያ መጽሐፍ የተጠቀሱ የተሐድሶ ውጤቶች 7 ናቸው፦ 1/ ቅጥሩን የማደስ ሥራ በ52 ቀናት ማጠናቀቅ ችለዋል (6:15)። 2/ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ማሳፈር ችለዋል (6:16)። ከዚህም የተነሳ 3/ መንፈሳዊ ተሐድሶ ሊመጣ ችሏል:- እስራኤላውያን ሁሉ በእግዚአብኤር ፊት ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዋል (9:3)። 4/ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰሙ ችለዋል (9:3)። 5/ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ሰገዱ (9:3)። 6/ በሕዝቡ መሐከል እጅግ ታላቅ ደስታ ሆነ (8:17)። 7/ ሕዝቡም ተቀደሰ (9:2)።   

መደምደሚያ። የተሐድሶ ግብ ቅዱሳን ኃጢአታቸውን በመናዘዝና በመተው በመንፈስና በእውነት እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ እንዲመጡ ነው። እግዚአብሔርን በመፍራት መቀደስ ሲችሉ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል በክብሩ ይመላለሳል። እግዚአብሔርም ይከብራል። የመኖራችን ግብ እግዚአብሔርን ማስከበር ከሆነ በተሐድሶ ሕይወት ውስጥ ለመገኘት መትጋት ይኖርብናል። ሁልጊዜ ስለራሳችን ጥቅም፥ ክብር እና ዝና የምናስብና በሥጋዊ ምኞት የተዋጥን ከሆነ ግን ተሐድሶ ያስፈልገናል፤ ለተፈጠርንለት አላማ እየኖርን አይደለም ማለት ነው። “ጌታ ሆይ በተሐድሶ ጎብኘን” ብለን ልንጸልይ ይገባል። ጥሪያችን እንደ ንስር እንድንኖር እንጂ እንደ ዶሮ ምድር ምድር እያየን ምድራዊ ሆነን እንድንቀር አይደለም። ቤተክርስቲያን ጌታን የምትወድና ነቀፋ የሌለባት እንድትሆን ተሐድሶ ዓይነተኛ ሚና አለው። እግዚአብሔር ያየልንን ሕይወት ኖረን እንድናልፍ ይርዳን።

ወንድም ተድላ ሲማ፣ አዲስ አበባ የካ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን አባልና አገልጋይ የነበረ ሲሆን አሁን ኗሪነቱ ሻርለት ኖርዝ ካሮላይና ነው። ከዚህ ቀደም “ቢሊ ግራሃም አንሰርስ ዩር ኴስችንስ” የተሰኘውን መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉሞ አሠራጭቷል።

Illustration Credit: The Rebuilding of the Temple by Gustave Dore, 1865.