የመጽሐፍ ቅዱስ አፈታት መርሆዎች+

በዘላለም መንግሥቱ

illuminatedGospel

የስሕተት አስተማሪዎች ሐሰተኛ ትምህርት የሚያስተምሩት ወይም አንዳንድ ክርስቲያን አስተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ አፈታት የሚጋጩትና በተሳሳተ ሁኔታ ቃሉን የሚፈቱት ለቃሉ  አፈታት በጣም ጠቃሚ  የሆኑ መሠረታዊ መርሆችን ባለመረዳትና ትኩረት ባለመስጠት ነው። ትክክለኛ መርሆችን የሚከተል የቃሉ አፈታት በስነ መለኮት ቋንቋ ስነ አፈታት  ወይም ጥበበ አፈታት ይባላል።  ይህ ማለት፥ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉው ምስጢራዊ ነው ማለት አይደለም። በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ግልጽ በሆኑና ምንም ፍቺ በማይፈልጉ ምንባቦች የተሞላ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለመረዳት ጥረት የሚጠይቁ ክፍሎች ደግሞ ያሉበት መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ጥረት ክፍሉ በየትኛው ኪዳን ውስጥ ከመገኘቱ ጀምሮ እስከ መጽሐፉ ዓይነት፥ ከቋንቋው እስከ ዳራው፥ ከዐውደ ምንባቡ እስከ ቀጥተኛ ወይም ምሳሌያዊ አገላለጡ፥ ወዘተ፥ ፍተሻ የሚጠይቅ ነው። ቃሉን የሚያስተምር ማንም ሰው መሠረታዊ የሆኑ የአፈታት ሥርዓቶችን ማወቅ እንደሚጠበቅበት አጠያያቂ መሆን የለበትም።

ይህ ካልሆነ ሰባኪው ወይም አስተማሪው ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ነገር ከማስተማር ጀምሮ ሌላ ወንጌልና ሌላ ክርስቶስ እስከ ማስተማር ሊደርስ ይችላል (1ጢሞ. 6፥3፤ 2ቆሮ.11፥4፤ ገላ. 1፥6-7)። ከዚህ የተነሣ የተሳሳቱ ትምህርቶች ብቻ ሳይሆኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተደላድለውና ተመቻችተው የሚቀመጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ልምምዶችም ይበዛሉ። እነዚህ ስሕተቶችና ችግሮች የሚፈጠሩበትን ሂደት ቃሉን መግመድና መቋጠር ልንላቸው እንችላለን። መግመድና መቋጠር የሐሰት አስተማሪዎች ብቻ ስራ ሳይሆኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን እሁድ እሁድ ወይም በአዘቦቱ ቀን የሚያስተምሩን ሰዎችም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሊያደርጓቸው የሚችሉአቸው የተሳሳቱ የአፈታት ሕጸጾች ናቸው። እነዚህ አገማመዶች ለሐሰተኛ ሃይማኖች ብቻ ሳይሆን ለተሳሳቱ ልምምዶች፥ ድምዳሜዎችና፥ እርምጃዎችም ሊያጋልጡን ይችላሉ። በጣም በጉልህ ሁኔታ ለተሳሳተ የአፈታት ግድፈት የሚያጋልጡንን ጥቂቱን በዚህ አጭር ጽሑፍ ላነሣ እፈልጋለሁ። እነዚህ ነጥቦች ጥቂቶች ብቻ ናቸው እንጂ ሁሉም አይደሉም።

የተባለውን ትቶ ያልተባለውን ማለት። ትክክለኛ ያልሆነ አጠቃቀስ እና አንድን ጥቅስ በቃል ብቻ ማለት እንጂ ከመጽሐፉ አለማንበብ የስሕተት አንድ መንደርደሪያ ነው። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ጥቅስ ሳናነብበው በቃል ስንለውና ደግሞ በትክክል እንደተጻፈው ሳይሆን በግርድፉ የምናስታውሰውን እንደተጻፈ አድርገን ስንል ነው። በቃላችን በትክክል ያልያዝነውን ቃል በመሰለኝ መጥቀስ ራስንም ሌሎችንም ለመሳትና ለማሳሳት ይዳርጋል። ይህ ብዙ ጊዜ የሚሆነው ያልተዘጋጁበት አሳብ ሲሰነዘር ነው። ለማስተማርና ለመስበክ ያለመዘጋጀትን ከመንፈሳዊነት ጋር የሚያቆራኙ ሰነፎች ይህ መንፈሳዊነት ሳይሆን ያገጠጠ ስንፍና መሆኑን ቢያስተውሉት ምንኛ መልካም ነበር! ተሰናድተውበት የጌታ መንፈስ አሳብን ቢያስለውጥ መታዘዝ አንድ ነገር ነው። ሳይዘጋጁ ቀርቶ ማሳበብ ደግሞ ሌላ ነው።

አንድ ሰባኪ ሊሰብክ ወጥቶ የሚያካፍለው ያልተዘጋጀበትን መሆኑን ተናግሮ ላለመሰናዳቱ ያቀረበው ጥቅስ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና አለ። ቃሉ ከማር. 13፥11 የተወሰደ ቢሆንም ከጥቅሱ የተወው ወይም ያስቀረው ክፍል፥ ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ የሚለው ነው። የዚህ ሰው ችግሮች ሁለት ናቸው፤ አንዱ አለመሰናዳቱ ራሱ ሲሆን ሌላው ከታች የምንመለከተው የጥቅሱን ዐውድ አለማጤን ነው። ምዕራፉ በሙሉ (ማር. 13) ሲጤን ከዚህ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑ ይስተዋላል። ቃሉን ለክርስቲያኖች መስበክና በአሳዳጆች ሸንጎ ስለ እምነት መልስ መስጠት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ጥቅሱን ከሞላ ጎደል አውቀነው ቦታውን ስለማናውቀው፥ ፈልገንም ለማግኘት ጊዜና ቦታው ስለማይፈቅድልን፥ አላዋቂ መስለንም ላለመታየት ስንል በነሲብ እንጠቅሰዋለን። አንዱ ያለውን ደግሞ ሌላው እንደ ማሚቶ እየደገመ  ነገሩ ይባዛል። ጌታ፥ “አንድ ወይም ሁለት  ሆናችሁ በተሰበሰባችሁበት እኔ እገኛለሁ” ማለቱ ሲጠቀስ ደጋግሜ ሰምቻለሁ። ወይም ጌታ ሐዋርያቱን ያስተማረው ጸሎት ሲጨረስ፥ “ኃይልም ክብርም ምስጋናም ለዘላለሙ አሜን” ማለት የተለመደ ነው። አንዳንዴ ስናነብበውም እንኳ ጥንቃቄ ባለማድረግ ያልተጻፈውን የምናነብብበት ወይም የተጻፈውን የማናነብበት ሁኔታ ይስተዋላል። በማቴ. 7፥23 ጌታ፥ “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” ማለቱን ሲያገለግሉ የቆዩቱ እንኳ “አላውቃችሁም” ብለው ሲያነብቡት ብዙ ጊዜ አድምጫለሁ። እንዲህ ሲያነብቡትም፥ በቃል ሲሉትም ስሕተት ካለ ጠንቃቃ የቃሉ ተማሪ መሆን የተገባ ነው።

ዐውዱን ትቶ ጥቅስን መጥቀስ። ዐውድ ማለት የጥቅስ ወይም የክፍለ ምንባብ ሰፊ ከባቢ ነው። ይህን ሰፊ የጥቅስ መገኛ ወይም መስክ ካላስተዋልን በአንድ ጥቅስ ትልቅ ትምህርት የመገንባት ችግር ውስጥ እንገባለን። የዚህ ነገር ችግር የትምህርቱ መሠረት ትምህርቱን መሸከም የሚችል አቅም ስለሌለው በማይቀር ሁኔታ ስለሚወድቅ እንዳይወድቅ የሚደረገው ርብርብ ሌላ የሰፋ ስሕተት ስለሚሆን ነው። ዐውድ ወይም ዳራ የመጀመሪያ ተቀባዮቹን እንድናጤን ያስገድደናል። እንደሚታወቀው እኛ የመጀመሪያ ተደራሲዎች አይደለንም። የፊልጵስዩስ መልእክት ለኛ ቤተ ክርስቲያን አልተላከም፤ ወይም የፊልሞና መልእክት ለኔ አልተላከም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲጻፍ ዋና አስጻፊ የሆነው መንፈስ ቅዱስ  ይህ ቃል  ለእኛም የሚደርስ ዘመንና ድንበር ዘለል የሆነ ቃል እያስጻፈ እንደሆነ ያውቃል። ቃሉ ደግሞ በአፊዎተ መለኮት የተጻፈ ከመሆኑ የተነሣ ዘላለማዊነትን የተቀዳጀ ቃል ነው። “አፊዎተ ቃል” ትልቅ  ስነ መለኮታዊ ቃል ቢሆንም ትርጉሙ ቃሉ ከእግዚአብሔር የመነጨ፥ ቅዱሳን በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የተናገሩት፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መሆኑን የሚያሳይ ቃል ነው (2ጴጥ. 1፥21፤ 2ጢሞ. 3፥16-17፤ ዮሐ. 6፥63)። ስለዚህ ለነዚያ በቀጥታ ለተጻፈላቸው እንዳለው ያለ ሥልጣን ለእኛም አለው። ሆኖም ለእኛም የተጻፈ ቢሆንም በቀጥታ ለእኛ የተነገረ ስላልሆነ ወይም የመጀመሪያዎቹ የመልእክቱ ተቀባዮች እኛ ባለመሆናችን ጠቅላላ መርሆዎችን ስንወስድ በግንዛቤ ደረጃ እንጂ የግል አድርገን የማንወስዳቸው ክፍሎችም ይኖራሉ ማለት ነው። ለምሳሌ፥ ዘፍ. 18፥14 የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ ሣራም ልጅን ታገኛለች የሚለው ለአብርሃም ብቻ የተነገረ እንጂ ለሌላ ለማናችንም አይደለም። ያንን ጥቅስ ከፊቱ ከተጻፈው ጋር ወስዶ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ያለመኖሩን ማስተማርና ራሱኑ ያንኑ ጥቅስ ልጅ ለሌለው ሰው በዓመት እንደሚፈጸም ተስፋ አድርጎ መቀባት የተለያዩ ናቸው። ዐውድን ስናጤን ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ቃሉ በሙሉው ስለዚያ ስለሚነገረው ነገር ምን ይላል የሚለው ነው። በቃሉ አፈታት ዓይነተኛ ሚና ያላቸው ሁለት አሉ። እነዚህም መንፈስ ቅዱስና ቅዱስ ቃሉ ራሱ ናቸው። በስነ አፈታት ሊቃውንት ዘንድ የሚነገር፥ ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ተርጓሚና ማብራሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ነው’ የሚባል መርህ አለ።የቃሉ ፈቺ ቃሉ ነው።ይህንን ቀጥሎ እመለስበታለሁ፤ቀድሜ ግን መንፈስ ቅዱስ አብሪነት እንይ።

የመንፈስ ቅዱስ ሚና። እርሱ ባይገልጠው ኖሮ በምንም መንገድ ሊታወቅ የማይችል ቃሉን የገለጠው፥ ገሐድ ያደረገው መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ ቃሉን በማስጻፍ ረገድ ወይም እንዲጻፍ በመግለጥ የተደረገው የመንፈስ ቅዱስ የግሒዶት ሥራ የተጠናቀቀ ነው። አዲስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚቀጠልና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩያ ሥልጣን ያለው ቃል የለም፤ አይኖርምም። ነገር ግን ቀጣይ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ የአብርሆት ተግባር አለ። ይህንን እንዲጻፍ ያደረገውን ቃል የገለጠው መንፈስ ቅዱስ በዚህ ቃል ላይ ብርሃኑን የማብራት፥ የማስረዳት፥ የመፍታት ድርሻ አለውና በእርሱ ጥበብ መደገፍ ቃሉን ለመረዳትና ለማስረዳት ይጠቅማል። የሰው አእምሮ ብቻውን መንፈሳዊውን ወይም መለኮታዊውን ነገር መረዳት ይሳነዋል። ለፍጥረታዊ አእምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነው። ለዚህ ነው ጳውሎስ ይህንን እውነት በ1ቆሮ. 2 በሰፊው ያስተማረው። ያለ መንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት የተጻፈውን ቃል በትክክል መፍታት ወይም ማስረዳት አይቻልም። ማንም የቃሉ ተማሪና አስተማሪ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሳይደገፍ ቃሉን ሊፈታ ቢጥር የሳይንስና የጂዖግራፊያ መሳይ ትምህርት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሊያቀርብ ይችል እንደሆን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ሊፈታ አይቻለውም። ቃሉን ስናጠና ምንም እንኳ አእምሮአችንን ሙሉ በሙሉ በተግባር ላይ ማዋል ቢኖርብንም በቃሉ ገጾች ውስጥ የፈሰሰውን ሙሉው አእምሮአችን ሊረዳው የማይችለውን እውነት ወደ ልባችን ሊያስገባልንና ሊያስረዳን የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው።

የቃሉ ፈቺ ቃሉ ነው። የቃሉ ፈቺ ቃሉ ወደመሆኑ ልመለስ። ምንም እንኳ የጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ዋና አሳብ ግልጽ ቢሆንም በጣም ግልጽ ያልሆኑ ወይም አሻሚ የሆኑ ጥቅሶችና ምንባቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖራቸው የታወቀ ነው። እነዚህ ሲገጥሙን ማድረግ ያለብን ነገሮች አሉ። ሌሎች ነጥቦች በእርግጥ ሊኖሩ ቢችሉም እነዚህ ሦስቱ በጣም ጠቃሚ ናቸው ብዬ አምናለሁ፤

1. ግልጽ ያልሆነው ጥቅስ ወይም ክፍል ያንን ጉዳይ በተመለከተ ግልጽ ሆነው በተጻፉት ጥቅሶች መብራራት አለበት። ይህንን ለመረዳት የአሻሚውን ቃል ትርጉም ለማግኘት ዐውዱን ከመፈተሽና ከምንጩ ቋንቋ ከመረዳት ባሻገር በዚያ የሚገኘውን ጠቅላላ አስተምህሮ ዋና ጥያቄ ማንሳትና ያንን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ በጠቅላላው የሚያስተምረው ምን መሆኑን ማወቅ ተገቢ ይሆናል። ለምሳሌ፥ በ1ጢሞ. 2፥1፣ ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች። በሚለው ውስጥ በመውለድ ድነት ይገኛል የሚል ይመስላል። ወይም በ1ቆሮ. 15፥29 እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? የሚለው ለሞቱ ሰዎች መጠመቅ አንዳች የሚፈይድላቸው ይመስላል። እንዲህ ያሉ ሞጋች ጥቅሶች ሲገጥሙን ነው ከላይ ያልኩት የጠቅላላው አስተምህሮ ጥያቄ መነሣት ያለበትና ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ያንን ለመመለስ የሚሰጠውን ምላሽ መውሰድ ያለብን። ለነዚህ ሁለት ናሙና ጥቅሶች ጠቅላላ ጥያቄዎቹ ለፊተኛው፦ ድነት ምንድርነው? የሚገኘውና የምንቀበለውስ እንዴት ነው? ለሁለተኛው፦ ሞትና ትንሣኤ ምንድርናቸው? ጥምቀትና ዓላማው ምንድርነው? የሚሉት ሊጠየቁ ይችላሉ።

2. ታሪካዊ የሆኑት የማይደጋገሙ ክስተቶች ያንን በሚመለከቱ ትምህርታዊ በሆኑ ክፍሎች መፈታት አለባቸው። ለምሳሌ፥ በሐዋ. ሥ 19፥6 ጳውሎስም እጁን  በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ የሚል ጥቅስ እናገኛለን። ይህ የሆነ፥ የተፈጸመ ታሪካዊ ክስተት ነው። ይህን ጥቅስ በልሳኖች ስለመናገርና ትንቢት ስለመናገር እንደ መተግበሪያ አድርገን ወስደን እጅ በተጫነ ቁጥር ይህ እንዲሆንና ሁሌም እንዲሆን ልንጠብቅ ይዳዳን ወይም ልባችን ይከጅል ይሆናል። አንዳንዶች ይህን ያደርጋሉ። ይሁንና፥ በዚህ በሁለተኛው ነጥብ መሠረት በጉባኤ ልሳኖችን ስለመናገር እና ትንቢትን ስለመናገር፥ ስለ ግቡና ስለ ሥርዓቱ የተብራራና በትምህርት ደረጃና መልክ የተሰጠ ክፍል አለ ወይስ የለም ብለን እንድንጠይቅና ከኖረ ያንን ክፍል ማጤንና ማጥናት ተገቢ ይሆናል ማለት ነው። ከላይ ለተጠቀሰው ናሙና ጥቅስ 1ቆሮ.14 ትምህርታዊና ተግባራዊ የማብራሪያና የአፈታት ምንባብ ነው።

3. አዲስ ኪዳን በብሉይ ሳይሆን ብሉይ ኪዳን በአዲስ ማብራሪያነት መፈታት አለበት። ይህ ጠቃሚ የአፈታት እውነት ነው። በመጀመሪያ የኪዳኑን ተሳታፊዎች ስናስተውል ቤተ ክርስቲያንን ወይም አሕዛብ የሆንን እኛን በቀደመው ኪዳን ውስጥ አናገኝም። ምንም እንኳ ወደ ኪዳኑ ሕዝብ በተለያዩ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ራሳቸውን አስገብተው የተገኙ ሰዎች ቢኖሩም ያ ኪዳን የእግዚአብሔርና የአንድ ሕዝብ ቃል ኪዳን ነው። ሁለተኛው ነጥብ የቀደመው ኪዳን ነቀፋ የኖረበት መሆኑና ገና በብሉይ ኪዳንም እንኳ ያ ኪዳን እንደሚታደስ ተስፋ መገባቱ ነው፤ ዕብ. 8 እና 9። ነቀፋው ሕጉ ስሕተት ወይም እንከን ያለበት መሆኑ አይደለም፤ ሮሜ 7፥12 ስለዚህ “ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት” ይላል። ነቀፋው ኪዳኑ ውጪያዊና ድርጊታዊ እንጂ ውስጣዊና ግንኙነታዊ ያለመሆኑ  ነው። ሕጉ በድንጋይ ተጽፎአል፤ በልባቸው ግን አልተጻፈም። አፈጻጸሙም በትእዛዛት እንጂ በመንፈስና በጸጋ አልነበረም። ጌታ አዲሱን ኪዳን በመስቀሉ ደም ካተመው ወዲህ ግን እኛን መኖሪያው አድርጎ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የራሱን ኑሮ ገንዘቡ ባደረገው ሕዝቡ መኖር ጀመረ። በሮሜ.  15፥4 “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና” እንማርበት ዘንድ ቃሉ ተሰጥቶናል። ሕጉም፥ ታሪኩም፥ ሥርዓቱም፥ አምልኮውም፥ ትንቢቱም እንማርባቸው ዘንድ ተሰጥተውናል። አሮጌ አዋጅ ኃይልና ሥልጣን ቢኖረውም አዲስ አዋጅ ሲኖር በዚያ ይሻራል ወይም ይተረጎማል። እንዲሁ የቀደመውን ኪዳን ሕግና ትምህርት በአዲሱ ኪዳን እንፈታዋለን ወይም እናገናዝበዋለን እንጂ አዲሱን ኪዳን በቀደመው አንፈታውም።

ፖለቲካዊ ትክክለኝነት። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንዳንድ ጉዳዮች የሚናገራቸው ነገሮች አድማጮችን የሚያስቆጡና የሚረብሹ ከሆኑ አለማንሳትና አለማውሳት ዘዬ ሆኖአል። የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በመጀመሪያው ምርጫ ወቅት እንደ ‘ክርስቲያንነታቸው’ መጠን ስለ ግብረ ሰዶማውያን ምን እንደሚሉ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ግልጽ ካልሆኑት የጳውሎስ መልእክቶች ይልቅ ግልጽ የሆነውንና ጌታ ስለ ፍቅር የተናገረውን እንደሚቀበሉ ተናግረው ነበር። የተጠየቀው ጥያቄ ግልጽ ነው። በጥያቄው ላይ ጳውሎስ በሮሜ 1 በግልጽ ጽፎአል። ጌታ ስለዚህ በግልጽ ያስተማረበት ቦታ የለም። ፕሬዚደንቱ ይህን ጥያቄ የሸሹት ለፖለቲካዊ ትክክልነት ነው። ፖለቲካዊ ትክክልነት ሰዎችን ላለማስቆጣትና ላለማበሳጨት ወይም ለዘለቄታው ላለማስቀየም እውነቱ በአንድ ስፍራ ቢኖርም ያንን እውነት አለመናገርና መመሳሰል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱስ እግዚአብሔርን ባህርይ ስለሚገልጥና ሰውን በዚያ መስፈሪያ ስለሚለካ የሚያስቆጣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ፥ በማያሻማ ሁኔታ የሚገልጣቸው ነገሮች የመኖራቸውን ያህል ዘመናችንና ዓለማችን በርዕዮታዊ ቀውስ ውስጥም ትገኛለች። መጽሐፍ ቅዱስ በአመዛኙ በአንድ ባሕላዊ፥ ሕዝባዊ፥ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መዋቅር ውስጥ የተጻፈ ነው። ዘላለማዊ እውነቱ በምንም ድንበር የማይከለል ይሁን እንጂ የተጻፈበት ከባቢ ካለንበት በጊዜ ብቻ ሳይሆን በስነ ልቡናም የራቀ ነው። ስለዚህም ቃሉን እንደ መጽሐፋቸው አድርገው ከሚቆጥሩቱ እንኳ ይዘቱን ለዘመናዊው አንባቢና አእምሮ ምቹና ለስላሳ ለማድረግ ተብሎ ጠቅላላው ይዘቱ መፋለስ እንዳለበት የሚመስላቸው አሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ባልለሰለሰበት ስፍራ የሚያለሰልሱትና ያላለውን እንዲል ከሚገምዱት መካከል ለፖለቲካዊ ትክክልነት ዘብ የሚቆሙ ሰዎችም ናቸው።

መዳን በክርስቶስ ብቻ በኩል መሆኑ የሚያስቀይማቸው አሉ። እነዚህ እንዳይቀየሙ መዳን ይቀየጥ? ጌታ ወይም ሐዋርያት ለፖለቲካዊ ትክክልነት ሲሉ፥ የነበረውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ወይም የአገዛዝ ተቋም ላለማስቀየም ሲሉ ራሳቸውን ደብቀው ወይም እነዚያን ሰዎች ላለማስቀየም ሸንግለውና ደልለው ነበር? አዲስ ኪዳንን ስናነብብ ጌታም ሐዋርያቱም ከነባሩ ሥርዓት ጋር ሲወዳጁና ሲመሳሰሉ ሳይሆን ቆፍጠን ብለው ሲጋፈጡት ነው የታዩት። ጆወል ኦስቲን በሲ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ ክርስቲያኖች ብቻ የሚድኑ ይመስልሃል? እስላሞችስ? አይሁድስ? ብሎ ሲጠይቀው፥ “እ … እኔ  እንጃ፥  እ… አላውቅም፥ ማለቴ …”  እያለ ሲናገር ሐዋርያው ጳውሎስ ወይም ዲያቆኑ ፊልጶስ ቢያዩት ምን ይሉት ነበር ይሆን?

ዐውዶችንና ጥቅሶችን ጨፍልቆ ማገናኘት። ይህ ሌላ የመግመድና የመቋጠር መሳሪያ ነው። በጥቅሶች ሰንሰለት ተመሳሳይ ቃል በውስጣቸው ስለተገኘ ብቻ ተመሳሳይ አሳብ የሌላቸው ጥቅሶችና ምንባቦች ተደጋግፈው መቆም ሲያቅታቸው ተጣብቀው እንዲቆሙ መደረግ የለባቸውም። አንድ ጓደኛዬ አንድ ጊዜ ስለ ኢያሱ ቃል ያካፍለን ነበር። ኢያሱ ሙሴን ያገለግል የነበረ፥ ሕዝቡን ወደ ተስፋዋ ምድር ያስገባ ድንቅ መሪ መሆኑን አወሳና ኋላ ግን እድፋም ልብስ ለብሶ በሰይጣን የተከሰሰ መሆኑን ከዘካ. 3 ቀጥሎ አያይዞ አስተማረን። ከጨረሰ በኋላ ሁለቱ ኢያሱዎች የተለያዩ መሆናቸውን ስነግረው ቢደነግጥም እርማቱን በደስታና በጸጋ ነበር የተቀበለው። “በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ” እና “ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” [ኤር. 1፥5ን፤ዮሐ. 1፥2] የሚለውን በግድ በማጣበቅ ሞርመኖች ሰው ቀድሞ ስለነበረው ኑባሬ የሚያስተምሩበት ጥቅሶች ናቸው። የመጀመሪያው እግዚአብሔር ኤርምያስን ከልደቱ በፊት ያወቀው መሆኑን የሚናገር ሲሆን፣ ሁለተኛው የእግዚአብሔር ወልድ ኅላዌ ቅድመ ዓለም መሆኑን የሚያስረዳ ነው። እነዚህ ሁለቱ እነርሱ እንዳሰቡት በአንድ ቀንበር ገብተው የማይጠመዱና የማይታረስባቸው ናቸው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለአፈታት ችግር የሚሆኑት ከሰዎች አለመረዳት ብቻ ሳይሆን መናኛ ትርጉሞች መኖራቸው ጭምር ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በራሳችን ቋንቋ ማግኘት መባረክ ነው። ትርጉሞች ሲበዙ ግን ከመጥቀማቸው ይልቅ ያለመጥቀማቸው ያይላል። አንድ የታመነ ትርጉም ከኖረ ያንን ከምንጭ ቋንቋዎች ጋር ባልተጣጣመባቸው ቦታዎች በማጣጣም መጠበቁ እንጂ አዳዲስ ትርጉሞችን ማብዛት ብዙ ጥቅም የለውም። ይህ ንዑስ ርእስ ራሱን የቻለ ስለሆነ በሌላ ጊዜና ቦታ እንመለስበታለን።

+መጽሐፍ ቅዱስና የአፈታት ስሕተቶችበሚል ርእስ ወንድም ዘላለም ጽፎ ካሳተመው መጽሐፍ የተወሰደ ነው። ሙሉውን መጽሐፍ ለማግኘት በዚህ አድራሻ ይጠይቁ፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.