አምልኮ

በነቢዩ ኢሳይያስ

በዓለም ላይ ብዙ ኃይማኖቶች አሉ። ሁሉም እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት የየራሳቸው መንገድ አላቸው። ብዙዎች የአምልኮ መለኪያውን የራሳቸው አምልኮ በማድረግ በእነርሱ አምልኮ እግዚአብሔር ደስ እንደሚሰኝ፣ በሌሎች ግን ደስ እንደማይሰኝ በድፍረት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ከአምልኮ ጋር በተያያዘ የብሉያትን መጽሓፍ ስንመረምር በቀደመው ኪዳን ይኖሩ የነበሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች አምልኮአቸው በአጠቃላይ በሕጉ መጽሓፍ ከተቀመጠው ሓሳብ በወጣ ጊዜ ያህዌ በነቢያቱ በኩል እንዲህ ይላቸውና ይገስጻቸው ነበር፣ “ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ ተጸይፌውማለሁ፤የተቀደሰውም ጉባኤአችሁ ደስ አያሰኘኝም። የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁና የእህሉን ቍርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም። የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም” (አሞጽ 5፡ 21-23)።

እግዚአብሔርን ከማወቅ መንገድ ርቀው በሚያቀርቡት መስዋዕት ብቻ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ይጥሩ ለነበሩት ለእነዚሁ የእስራኤል ልጆች በሌላ ጊዜ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንዲህ የሚል መልዕክት መጥቶላቸው ነበር፤ “እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ።  የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው? ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም። መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ። እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል” (ኢሳ 1፡10-15)። ከእነዚህ ሁለት የመጽሓፍ ቅዱስ ክፍሎች እግዚአብሔር አንዳንድ አምልኮዎችን እንደሚቀበል፣ አንዳንዶችን ደግሞ እንደማይቀበል እንረዳለን።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አስመልክቶ ስለ “አምልኮ” ይህንን መልዕክት ስጽፍ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማው፣ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንዳለብን አቅጣጫን ከማሳየት ይልቅ፣ አምልኮን በሰው ሕይወት የሚፈጥረው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ማሳየት ነው (ፊል 2፡13)፤ ወይም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቤተክርስቲያን ተሓድሶአውያን አገላለጽ፣ “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው አምልኮ የሚወሰነው እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ በገለጠውና ባደረገው ነገር ላይ እንጂ በእኛ ኃይማኖታዊ ስሜት ወይም አሳብ አይደለም። እግዚአብሔርን የሚያስደስተው አምልኮ የሚመነጨውም ሆነ የሚካሄደው በራሱ በእግዚአብሔር  ነው።” ይህንን በወንጌላት ከተገለጸው እውነት ማስተዋል እንደምንችል አስባለሁ። እኛም በዚህ ዘመን የምንገኝ የእግዚአብሔር ሕዝቦች አምልኮን በተመለከተ ከወንጌላት ልንማረው የምንችለው በርካታ ነገር ስላለ  ወደዚያው ሓሳብ እንሄዳለን፦

1. አምልኮ በእረኞቹ ሕይወት። የአምልኮአቸው ምክንያት የምሥራቹ ቃል ነበረ። በሰው ሕይወት ውስጥ አምልኮን የሚፈጥር እግዚአብሔር አምላክ መሆኑ በግልጽ ተቀምጦ ከምናይባቸው የወንጌላት ክፍሎች ውስጥ አንዱ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡8-14 ያለው ታሪክ ነው። በዚህ ክፍል የምሥራቹ ቃል የተበሠረላቸው እረኞች ሲሆኑ፣ እግዚአብሔር መድህን እንደ ተወለደ ያበስሩላቸው ዘንድ መላእክቱን ወደ እነርሱ ላከ። እረኞቹም በመልእክቱ የታወጀውን የምሥራች ቃል እንደ ሰሙ፣ “ስለ ሰሙትና ስላዩት ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ።” እነዚህ እረኞች በመላእክቱ አማካይነት የመጣውን ይህን የምሥራች ቃል ባይሰሙ ኖሮ፣ እግዚአብሔርን በማምለክ ደስታ አይጥለቀለቁም ነበር። ስለዚህም ከሰሙት የምሥራች ቃል የተነሳ አዳኙን ለማየት ወደ ቤተ ልሔም ተጣደፉ፣ እግዚአብሔርም በመላእክቱ በተነገረው የምሥራች ቃል አማካይነት እረኞቹን  እንዲያመልኩት አደረገ። ሉቃስ ስለዚህ ሁኔታ ሲተርክልን “ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ” ይለናል (ሉቃስ 2፡20)። እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚያነሳሳው አምልኮ እውነተኛ ከመሆኑም በላይ እርሱ ደስ የሚሰኝበትና ትክክለኛ አምልኮ ነው። እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት አምልኮ ሁሉ ከወንጌሉ ቃል ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በዚሁ የወንጌል ቃል እንዲህ ዓይነቱንም አምልኮ በሰው ሕይወት ውስጥ እንዲፈጠር የሚያደርገው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ከዚህ እውነት ስንነሳ በሰው ሕይወት የሚፈጠር የእውነተኛ አምልኮ ምንጭና መገኛ እግዚአብሔር ነው ማለት እንችላለን። መልአኩ “ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና … ዛሬ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ተወልዶላችኋልና” ሲል ባበሠረላቸው የወንጌል ኃይል ምክንያት እረኞቹ እግዚአብሔርን አመሰገኑት (ሉቃስ 2፡10-11)። ሰዎችን በሰማያዊ ደስታ እንዲጥለቀለቁ የሚያደርግና እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑት (እንዲያመልኩት) የሚያስችለው ብቸኛ ኃይል የማዳኑ ወንጌል ነው። ሕያው ቃሉ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ቦታ ሲያገኝና ሲሠራ ሰዎች በደስታ ሊጥለቀለቁ፣ እግዚአብሔርንም ሊያመልኩት ይችላሉ።

2. መግደላዊት ማርያም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የአምልኮ ምሳሌ ነች (ሉቃስ 7፡38፤48-50)። የዚች ሴት ታሪክ የሚገኝበትን ዐውደ ምንባብ በጥልቀት ካልመረመርነው ምናልባትም ድርጊቷ ሊያሳስተን እንደሚችል አስባለሁ። ከእኛ እይታ አንፃር ምንም እንኳ ይህች ሴት ጌታን አንድ ነገር በማድረግ እያመለከችው ያለች ቢመስለንም፣ “ኃጢአትሽ ተሠረዬልሽ… እምነትሽ አድኖሻል… በሰላም ሂጂ’’ የሚለው የኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር ግን፣ ከእርሷ ድርጊት ፈጽሞ የተለየ ነበር። ይህች ሴት ወደ ኢየሱስ የመጣቸው የኃጢአት ይቅርታ በእርሱ እንደሚገኝ በማመን ነው። ይህ እግዚአብሔርን የማምለክ ከፍተኛ ደረጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የወንጌል አማኞች እንደ ተነሳንበት የእምነት አቋም፣ አምልኮ ማለት እኛ በራሳችን ተነሳሽነት ለእግዚአብሔር የምናደርገው ነገር ሳይሆን፣ ይልቁንም እርሱ በሕያው ቃሉ አማካይነት በእኛ  ሕይወት ውስጥ የሚፈጥረው ነገር ነው። መግደላዊት ማርያም ወደ ኢየሱስ የመጣቸው የኃጢአት ይቅርታን ሽታ ነበር። ጌታም ይህን ሊሰጣት እንደሚችል ስለ እርሱ ቀድማ ከሰማችው ነገር አምናለች። ይህች ሴት ስለ ኢየሱስ መሲህነቱን ከመቀበልና የኃጢአትን ይቅርታ እንደሚሠጣት ከማመን ውጭ ስለ እርሱ ልታውቀው የምትችለው ነገር አልነበረም። ለእኛም ቢሆን ከዚህ የተለየ ነገር የለም። ጌታ ኢየሱስ እርሱ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚሰጥ በማመን በእምነት ወደ እርሱ መጠጋት የአምልኮ ከፍተኛው ደረጃ ነው። መግደላዊት ማርያም ኢየሱስን ሽቱ በመቀባቷና በማልቀሷ እርሱ ድርጊቷን አድንቆታል፤ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ በእርሱ ላይ ያላት የእምነት ምልክትና መግለጫ እንዲሁም ከእርሱ የኃጢአት ይቅርታ ለመቀበል ያደረገችው አንድ ዓይነት ኑዛዜ ነበር። ወደ እርሱ ከመምጣቷ በፊት ስለ እርሱ ዝና ሰምታለች (ሉቃስ 7፡17)። ወደ እርሱም የመጣችውና እርሱን ማምለክ የጀመረችው የእርሱ ምህረቱና የኃይሉ ዝና በመውጣቱ ምክንያት በሰማችው የምሥራች እንጂ እንዲሁ ከሜዳ በመነሳት አልነበረም። የወንጌሉን ክፍል ልብ ብለን እንመልከት። ኢየሱስ መግደላዊት ማርያም ባሳየችው የፍቅር ሥራ የኃጢአት ይቅርታን እንዳገኘች መናገር አልፈለገም፤ ስለዚህ “እምነትሽ አድኖሻል” በማለት መለሰላት። ከዚህ እውነት ስንነሳ የኃጢአት ይቅርታን እንደምናገኝ በማመን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት፣ የአምልኮአችን ከፍተኛው ደረጃ ነው። ይህም እርሱን በማመን የሚጀመር ይሆናል። ሰው የኃጢአትን ሥርየት የሚያገኘው በእምነት እንጂ በአምልኮው ወይም በድርጊቱ ብዛት አይደለም። የአምልኮአችን መነሻ በእምነት ያገኘነው የኃጢአት ይቅርታ ነው። ከዚህ እውነት ስንነሳ አምልኮን በውስጣችን የሚፈጥረው ስለ እርሱ የምንሰማው ሕያው እውነት እንደሆነ እንረዳለን።  

አምልኮ ከመስጠት ይልቅ መቀበል ላይ ያመዝናል። በወንጌላት የተገለጸው የአምልኮ የመጀመሪያው ምዕራፍ በእምነት አማካይነት በሰው ሁኔታ ላይ ባልተመረኮዘው የእግዚአብሔር ጸጋ የኃጢአት ይቅርታንና ያለ ሥራ የሚገኝን ጽድቅ ለመቀበል መዘጋጀት ይሆናል። እዚህ ላይ ታዲያ አንድ ጥያቄ ይነሳል። ይኸውም በዚህ የወንጌል ክፍል ተገልጻ የምናገኛት የዚህች ሴት ድርጊት፣ ዛሬ ለእኛ ምን ፋይዳ አለው? የሚለው ነው። እንደ እኔ አመለካከት የዚች ሴት ድርጊት ለእኛ አንድ ጥሩ ፋይዳ እንዳለው አስባለሁ። ይህም ስለ አምልኮ ሊኖረን የሚገባውን  አሳብና አመለካከት ለማስተካከል እንደ መስተዋት የሚሆን ምሳሌ የሚሰጠን መሆኑ ነው። እኛ ዛሬ እንደ ሴትዬዋ በኢየሱስ ክርስቶስ እግር ላይ እንባችንን እያፈሰስን እግሩን ማጠብ ባንችልም፣ነገር ግን ለማምለክ የተለያዩ ነገሮችን እናደርግ ይሆናል። እግዚአብሔርን በማምለክ ሂደት ውስጥ የዚች ሴት ድርጊት የሚያሳየን ዋናው ትኩረት፣ አምልኮ እርሱ ለእኛ ካደረገልን ነገር የሚመነጭ እንጂ እኛ በራሳችን ለእግዚአብሔር የምናደርገው ነገር እንዳልሆነ ነው። የእኛ የአምልኮ ተግባር እግዚአብሔር በእኛ ላይ ምህረቱን፣ ፍቅሩንና ጸጋውን ከማፍሰሱ የተነሳ የሚመጣ ነው። በአምልኮአችን ውስጥ ዋናው ነገር የኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ሲሆን፣ ይህም በመስቀል ሞቱ ያስገኘልንና እኛ በእርሱ በማመን የተቀበልነውን የኃጢአት ይቅርታ ነው (1ዮሐ 4፡19)። እግዚአብሔርን እንድናመልከው የሚያነሳሳን ነገር ቢኖር ይኽ ነው። አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁና ይህንን ሓሳብ ላጠቃልለው፣ እግዚአብሔርን ስናመልክ በጣም ግድ የሚለን እኛ ለእርሱ የምናደርግለት ነገር ነው? ወይስ እርሱ ለእኛ ያደረገልን ነገር? ይህንን ሓሳብ መለየት በጣም ጠቃሚ ነገር እንደ ሆነ አስባለሁ። የዚች ሴት ታሪክ ስለ አምልኮ ያለንን አመለካከት እንዲያስተካክልልን እንፍቀድ፤ ከዚያም አምልኮአችን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። ኢየሱስን ያስደስተዋል ብለን አንድ ነገር በመያዝ ወደ ፊቱ ከመምጣት ይልቅ  ይህች ሴት የኃጢአትን ይቅርታ ለመቀበል በእምነት ወደ ኢየሱስ እንደ መጣች፣ እኛም ምህረትንና ጸጋውን ለመቀበል እለት እለት በእምነት ወደ ፊቱ እንምጣ። ይህ እርሱን ያስደንቀዋል። የአምልኮአችን ጅማሬ የሚመነጨው ከዚህ ውስጥ ነው። 

3. አምልኮ በማርያምና ማርታ ሕይወት (ሉቃስ 10፡42)። አምልኮ ማለት ኢየሱስን መስማት እንጂ ለኢየሱስ አንድ ነገር ማድረግ አይደለም። እ. ኤ. እ ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም በኮፕን  ሃገን ዴንማርክ አንድ ትልቅ የሙዚቃ ትርዒት ቀርቦ ነበር። ትርዒቱን የተከታተሉ ሰዎች በቀረበው የሲንፎኒ ሙዚቃ ትርዒት ተመስጠው እንደ ነበር ተናግረዋል። አሁን አሁን አንዳንድ ኃይማኖታዊ ፕሮግራሞች እንዲህ ዓይነት ይዘት አላቸው። በዚህ ዘመን በትልልቅ ካቴድራሎችና የስብሰባ አዳራሾች የሚቀርቡ እንዲህ ዓይነት ረቂቅ ሙዚቃዎች፣ የሰውን ቀልብ የመጎተትና ነፍስን በማባበል ወደ ውስጡ እንዲያዘነብል የማድረግ ባህርይ አላቸው። እንዲህ ዓይነቶቹ ረቂቅ የሙዚቃ ቅንብሮሽ በቤተ ክርስቲያን በሚከናወን አምልኮ ውስጥ እየተለመደ መጥቷል። በተለይም እንዲህ ዓይነቱ ኃይማኖታዊ የሙዚቃ ኮንሰርትና ፌስቲቫል በአሁኑ ወቅት በአውስትራሊያ፣በሰሜን አሜሪካና በአፍሪካ አንዳንድ አገሮች ውስጥ እየተከናወነ ያለ ነገር በመሆኑ በትንንሽ ቤተ ክርስቲያን ከሚካሄዱ የአምልኮ ፕሮግራሞች ይልቅ ሰዎችን የሚመስጡ እየሆኑ መጥተዋል። ወደ ወንጌል ትምህርት ስንመጣ ግን፣ የምንመለከተው የዚህን ድርጊት ተቃራኒ ነገር ነው። በሉቃስ ወንጌል ላይ የተገለጸውን የማርያምንና የማርታን ታሪክ ልብ እንበል። ማርያም ከኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ በማለት እርሱ የሚያስተምረውን በአንክሮ ትከታተላለች። የማርያምን ሕይወትና ድርጊት ወደ እዚህ ዘመን ድርጊትና ልምምድ ብናመጣው ብዙዎቻችን መነቃቃት የምንለውን የአምልኮ ሕይወት አይገልጽም፤ ይሁን እንጂ ከማርታ ድርጊት ይልቅ ኢየሱስ ደስ ተሰኝቶበታል። ኢየሱስ ማርያምንና ማርታን ለመጎብኘት ወደ ቤታቸው በመጣ ጊዜ፣ ማርታ ኢየሱስን ለማስደሰት ስትል ራሷን አባተለች፤ ማርያም ግን ሕይወት ሰጭ በሆነው ጌታ እግር ሥር በመቀመጥ ነፍሷን ትመግብ ነበር። ፈቃዷንም ለዚህ ነገር አስገዛች። በዚህ የማርያም ድርጊት ማርታ በማጉረምረሟ ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላት፣ “ማርታ ማርታ በብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም እድልን መርጣለች፣ ከእርስዋም አይወሰድባትም” (ሉቃስ 10፡41-42)።

አምልኮ የሚጀምረው በመቀበል እንጂ በመስጠት አይደለም። ማርታ ለመስጠት ስትነሳ ማርያም ግን ለመቀበል ተቀምጣለች። ኢየሱስ እየተናገረ እያለ ማርታ ለኢየሱስ የሚሰጥ ነገር ለማቅረብና እርሱን ለማስደሰት ደፋ ቀና ትላለች። ማርያም ግን የአምልኮ መገኛና ሕይወት ሰጭ የሆነውን ሕያው ቃሉን ዝም ብላ ትመገብ ነበር። ምንም እንኳ እርሱን የምናምን እኛ በአምልኮ ለእርሱ በርካታ ነገሮችን የምንሰጥበት ጊዜ ቢኖረንም፣ ይህንን ምላሽ ከመስጠታችን በፊት ግን በእርሱ ሕይወት ሰጭ ቃል እለት እለት አዲስና የተለወጠ ሕይወት ልንቀበል ይገባል (ዮሐ 6፡63)። በዚህ ዘመን ብዙዎች ስለ አምልኮ ያላቸው መረዳት ከመቀበል ይልቅ መስጠት ላይ ያተኩራል፤ ስለዚህ ሕይወታቸው የማርያም ሳይሆን የማርታ፣ ጸጋ አደር ሳይሆን ወዝ አደር ነው። እግዚአብሔርን በአምልኮ ለማስደሰት ሞቅ ባለ ሁኔታ መዘመር ወይም እንቅስቃቄ ማድረግ ብቻ አለብህ የሚለው አስተሳሰብ ለሕዝብ ስሜት የሚመችና በአንድ በኩል ብቻ ረዝሞ የጸነፈ አመለካከት ነው። እንዲያውም የተሳሳተ አመለካከት እንዳይሆን ያስፈራል። በአምልኮ ጊዜ ከእግዚአብሔር ከምንቀበለው በረከት ይልቅ ለእርሱ በምንሰጠው ነገር ፈተና ውስጥ መውደቅ አዲስ ነገር አይደለም። እንደ ተሓድሶአውያን አባባል፣ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውና “ለሰው ልጅ ታላቅ መጽናናት የሚያመጣው ከፍተኛ አምልኮ፣ በወንጌል ውስጥ ከተቀመጠልን የኃጢአት ይቅርታና የጸጋ ትምህርት የሚነሳ ነው።” ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ስንነሳ የሚታሰበን እግዚአብሔርን ለማምለክ ያለብን ግዴታ ነው? ወይስ እርሱ ነፍሳችንን ሊመግባት ያዘጋጀልን ግብዣ? በእርግጥ በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ አምልኮን በይበልጥ እኛ ለእርሱ የምናደርግለት ነገር መሆኑን የሚያስመስሉ ሓሳቦች አሉ። ለምሳሌ ሮሜ 12፡1-2 አንዱ ነው። ይህ ጥቅስ ከአጠቃላይ የሮሜ መልእክት ዐውድ አኳያ ሲታይ ምዕራፉ “እንግዲህ” ብሎ በመጀመሩ አምልኮ እግዚአብሔር ለእኛ ካደረገልን ነገር የሚጀምር መሆኑን አመልካች ሲሆን፣ ይኸውም እኛን ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ማምጣቱ ነው። ብዙ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት መሄድን ስናስብ እርሱ ለእኛ የሚያደርግልን ሳይሆን፣ እኛ ለእርሱ የምናደርግለት ነገር አእምሮአችንን የሚገዛ ከሆነ፣ አሁንም ደግሜ እላችኋለሁ፣ ሕይወታችን የሚሆነው ጸጋ አደር ሳይሆን ወዝ አደር ነው። እኛ ለእርሱ የምናቀርብለት አምልኮ ከእኛ እንዲወጣ አስቀድሞ እርሱ በሕያው ቃሉና በጸጋው ወደ እኛ መምጣት አለበት። በኃጢአተኛው ሰው ሕይወት መፈለግንና ማድረግን የሚሠራ እርሱ ነው (ፊል 2፡13)። 

የአምልኮ ዋና ነጥብ ጌታን መስማት ነው (ማቴ 17፡5)። ኢየሱስን በመስማትና ለኢየሱስ አንድ ነገር በማድረግ መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት ልብ ብለን ካላወቅን ሕግና ጸጋ ሊቀላቀልብን ይችላል። ከዚህ አኳያ የወንጌሉን አምልኮ ከሕግ አምልኮ መለየት መቻል አለብን። የወንጌል አምልኮ ኢየሱስን በመስማት መጀመር አለብህ ሲለን፣ በሰብዓዊ ጥረት ላይ የተመሠረተው (የሕጉ) አምልኮ ግን ለኢየሱስ አንድ ነገር በማድረግ ጀምር ይለናል። በዚህ ጊዜ አምልኮ ሥራ ይሆናል። የወንጌሉ አምልኮ ከእግዚአብሔር መልካም ነገሮችን መቀበል ሲሆን፣ የሕግ አምልኮ ግን የእኛን መልካም ነገሮች ለእግዚአብሔር ማቅረብ ነው። እግዚአብሔር አምልኮአችን ከወንጌሉ ቃል የወጣ እንዲሆን ይፈልግብናል። ይኸውም ኢየሱስን መስማት ነው። በዚህ መስማት ውስጥ ኃያልና ሕያው የሆነው የእግዚአብሔር ቃል በውስጣችን ታላቅ የሆነን ሥራ ይሠራል (1ተሰ 2፡13)። ከዚህ ውጭ ግን እንቅስቃሴያችንን የአምልኮአችን መጀመሪያ እንድናደርገው አይፈልግም። እግዚአብሔርን ለአምልኮ ወደ ፊቱ ስንመጣ፣ እንደ ማርታ ለኢየሱስ አንድ ነገር ለማድረግ ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ እንደ ማርያም ቃሉን በመስማት ላይ እና እርሱ ለእኛ ባደረገው ነገር ላይ ትኩረት እናድርግ። “እርሱን ስሙት” እንደ ተባለ፣ እርሱን ለመስማት እንዘጋጅ። ዛሬም ከዚህ ሓሳብ እግዚአብሔር አንድ ነገር እንድናውቅ ይፈልጋል። ይህም አንድ ነገር ቃሉን ከመስማትና ልብ ከማለት የበለጠ እርሱን የምናክበርበት ነገርና ፍቅራችንን ለእርሱ የምንገልጥበት እንዲሁም እርሱን ለማምለክ ከፍ ያለ ሁኔታና መንገድ ያለ መኖሩን ነው። ለእግዚአብሔር በመዝሙርና በመንፈሳዊ ቅኔ በልባችን የምንቀኘው የእግዚአብሔር ቃል በልባችን ሲኖር ብቻ ነው (ቆላ 3፡ 16)። ሕይወት ሰጭና አስተላላፊ ከሆነው የእግዚአብሔር ቃል ጋር እየተጣብቅን ስንመጣ ከኢየሱስ ጋር ያለን ሕይወት ሰጭ መያያዝ ውጤታማ ይሆናል (ዮሐ 6፡63)። በቃሉ የማይኖር ሕይወት ይቋረጥበታል (ዮሐ 15፡6)።

4. የአምልኮ ጽንሰ ሓሳብና ሳምራዊቷ ሴት (ዮሐ 4፡20)። እግዚአብሔርን የሚያስደስተው አምልኮ በቦታ የሚወሰን አይደለም። በዓለማችን ላይ የታወቁ የአምልኮ ሥፍራዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የነበረበት ሥፍራ፣ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ብሔራዊ ካቴድራል፣ በሎንደን የሚገኘው ዌስትሚንስተር ካቴድራል፣ በሜክሲኮ ከተማ የሚገኘው ጓዳሉፕ ሂዳልጎ፣ በሮም የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራልና እንዲሁም በአገራችን የሚገኙት የላሊበላና የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህን በምሳሌነት ጠቀስኩ እንጂ ዝርዝሩ ከዚህ በላይ ሊያልፍ እንደሚችል እውቅ ነው፤ ይሁን እንጂ በተለያየ አገር የሚኖሩ የሰው ልጆች ቢያንስ በሕይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ወደ እነዚህ የታወቁ የአምልኮ ሥፍራዎች መጓዝ ይናፍቃሉ። የዘመናችን ሰው በእነዚህ የተቀደሱ ሥፍራዎች በመገኘቱ ብቻ በጣም መንፈሳዊነት ሊሰማው እንደሚችል እገምታለሁ፤ ምክንያቱም ሥፍራዎቹ ለመንፈሳዊ ነገር ታስበው ስለተለዩና ተጓዡም ሰው ገንዘቡን ከፍሎ በሥፍራው ተገኝቷልና ነው። ኢየሱስ ግን ለሳምራዊቷ ሴት እግዚአብሔር በሰው አምልኮ ደስ ከተሰኘ ደስ የሚሰኘው በአምልኮው ይዘት እንጂ በሥፍራ እንዳልሆነ አስረዳት። ይህች ሴት እግዚአብሔርን ለማምለክ ሥፍራ ቁም ነገር ነው ብላ የምታምን ነበረች። ይህን የምታምን መሆኗ “አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፣ አንተ አይሁድ ግን ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” ከሚለው ንግግሯ መረዳት እንችላለን (ዮሐ 4፡20)። እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው አምልኮ ከሥፍራ ጋር የተያያዘ ሳይሆን፣ራሱን በልጁ በመግለጡ ላይ የሚያተኩር ነው። አምልኮአችን እግዚአብሔር አምላክ ራሱን በልጁ በኩል በመግለጡ ላይ ከመሠረተ፣ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው ብሔራዊ ካቴድራል እስከ ጦር ሜዳ ውስጥ እስካለች ትንሽ ድንኳን ሊከናወን ይችላል፤ እግዚአብሔርን ማምለክ ቦታ አይወስነውም። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህችን ሳምራዊ ሴት፣ “ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ፣ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም ሆኗአል፣ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና’’ በማለት ሲመልስላት በእርሱ መምጣት ወደ ፊት ሊከናወን ስላለው አምልኮ መናገሩ ነበር [ዮሐ 4፡23]። እግዚብሔርን የሚያስደስተው አምልኮ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ላይ ያተኩራል። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት እንዴት እንዳዳነንና ሥጦታውን በመስቀሉ በኩል በተከናወነው ነገር እንደለቀቀልን ብርሃን ስናገኝ፣ እግዚአብሔር በአምልኮአችን እጅግ ይደሰታል።

እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው አምልኮ በእውነት ላይ የተመሠረተ፣ በኢየሱስ ማንነት ዙሪያ የሚያተኩርና እርሱን ማዕከል የሚያደርግ ነው። ኢየሱስ እውነት ነው (ዮሐንስ 14፡6)። እንዲሁም ቃሉ ሕይወት ሰጭና እውነት ነው (ዮሐንስ 6፡63)። አምልኮአችን እውነት በሆነው በኢየሱስና እውነት በሆነው ሕያው ቃሉ ላይ ተመስርቶ ሲከናወን፣ ሰዎች ከጥማታቸው ይረኩበታል፤ እግዚአብሔርም ደስ ይሰኝበታል (ዮሐ 14፡4)። ሀልዎቱንም በቅርበት እንለማመዳለን። እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ አምልኮ ውስጥ በስብከትና በትምህርት አማካይነት ሕይወት ሰጭ የሆነው የቃሉ ውኃ በነፃ የሚፈስበት የእውነት ምንጭ አለ (ዮሐንስ 4፡14)።  የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ሰው ሁሉ በእውነትና በመንፈስ እንዲሰግዱለት ነው (ዮሐንስ 4፡23)። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አምልኮ ከሳምራዊቱ ሴት ጋር ያደረገው ንግግር በታወቁ ኃይማኖታዊ ቦታዎች ማምለክ እግዚአብሔርን ደስ ከሚያሰኘው አምልኮ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑን ያረጋግጥልናል። እግዚአብሔር የሚመለከው በእውነትና በመንፈስ ነው። ይህም እውነት ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰበት፣ የኃጢአት ሥርየት ያስገኘበት ሞትና ትንሳኤው ነው። ኢየሱስ ለሳምራዊቱ ሴት አብ ጥንታዊ የአምልኮ መንገዶችን ሁሉ የሚተውበት “ጊዜ ይመጣል” ሲል ገለጸላት። በመቀጠል “አሁንም ሆኗል” አላት። እግዚአብሔር በጥንቱ ፈንታ ኢየሱስን ለዓለም ሰጥቷል። እርሱንም ስሙት ተብለናል። እርሱን በሕያው ቃሉ በኩል ስንሰማው በአምልኮአችን እግዚአብሔር ይበልጥ ይደሰታል። ይህንን በማወቅና በመረዳት እናመልከው ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ጸጋውን ይስጠን። መልካም የልደት በዓል!!!

ወንድም ነቢዩ ኢሳይያስ በመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የመሐልና ምዕራብ አጥቢያ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪና የአዲስ አበባ ክልል የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ቨርጂንያ በምትገኘዋ አንጾኪያ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን አገልጋይ ናቸው። አድራሻቸው እነሆ፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.