ውጤታማ ጸሎት

ተድላ ሲማ

“እግዚአብሔር በከንቱ ፈልጉኝ አላልኩም” ብሏል (ኢሳይያስ 45፡19)። በምንጸልይበት ጊዜ በከንቱ አይደለም የምንጮኸው፤ ጊዜያችንን በከንቱ አይደለም የምናጠፋው። ይልቁን ጸሎትን ወደሚሰማና ወደሚመልስ አምላክ ነው የምንጸልየው። ምን ዓይነት ጸሎት ነው ውጤታማ የሚሆነው? ከዚህ በታች ጸሎትን ውጤታማ የሚያደርጉ ስምንት ነጥቦችን እናያለን።

1. በቅን ልብ የሚጸለይ ጸሎት ውጤታማ ነው። በንጹሕ ልብ የሚጸለይ ጸሎት ኃይል አለው። “ቅንነት ግን ፊቱን ታየዋለች” ይላል ቃሉ (መዝሙር 11፡7)። እግዚአብሔር በባሕሪው ቅን አምላክ ነው፤ ቅን የሆነው እርሱ ጸሎታቸውን በመመለስ የቅኖችን መንገድ ያቀናል (ዘዳግም 32፤4፤ ኢሳ 26፡7)። ዳዊት ቅን ሰው ነበር፤ ጸሎቱም የሚሰማለት ሰው ነበር። “አቤቱ የኢኮጦፌልን ምክር ስንፍና አድርገህ እንድትለውጠው እለምንሃለሁ” ብሎ ጸለየ (2ኛ ሳሙኤል 15፡31)። እግዚአብሔርም ጸሎቱን እንደመለሰለት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። “እግዚአብሔርም በአሴሰሎም ላይ ክፉ ያመጣ ዘንድ እግዚአብሔር መልካሚቱን የኢኮጤፌል ምክር እንዲበትን አዘዘ” (2ኛ ሳሙ 17፡14)። ዳዊት ለጠላቱ ለሳኦል የነበረው አመለካከት በቅንነት የተሞላ ነበር፤ የሳኦል ሞት በተነገረው ጊዜ “እስራኤል ሆይ ክብርህ በኮረብቶች ላይ ተወግቶ ሞቶአል” በማለት ሳኦልን “የእስራኤል ክብር” እያለ ያቆላምጠዋል (2ኛ ሳሙ 1፡19)። ስለ ሳኦልና ዮናታን ሲናገር ደግሞ “ከንሥርም ይልቅ ፈጣኖች፣ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ” ብሏል (2ኛ ሳሙ 1፡23)። ስለ ሰዎች ያለን አመለካከት በቅንነት የተሞላ ሊሆን ይገባል። ጠማማ አስተሳሰብ ሊኖረን አይገባም። ሌሎች ሰዎች መልካም ነገር ሲሆንላቸው ልንደሰት፤ ችግር ሲገጥማቸው ደግሞ የሚያዝን ልብ ሊኖረን ይገባል፤ ያን ጊዜ ጸሎታችን የሚሰማልን ሰዎች እንሆናለን። “እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው … ጠማማው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነው። ወዳጅነቱ ግን ከቅኖችጋር ነው” (ምሳሌ 2፡7፤3፡32)።

2. እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ጸሎት ውጤታማ ነው። “እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል” (1ኛ ዮሐንስ 5፡14)። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የእግዚአብሔርን ቃል ልናነብና ልንሰማ ይገባል። የእግዚአብሔር ፈቃድ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ተገልጾአል። የጌታን ፈቃድ ለተለያዩ የግል ጉዳዮቻችን ለማወቅ ስንሻ ነገሮቹን አስመልክቶ የጌታ ሰላም እንዳለበት ማረጋገጥ አለብን። የእግዚአብሔር ፈቃድ በሆነ ጉዳይ ላይ ልባችን በእግዚአብሔር ሰላም ይሞላል። ጭንቀት የሚሰማን ከሆነ፥ ጥድፍድፍ የሚያደርግ ውክቢያና ነውጥ የበዛበት ከሆነ ልናደርግ ባሰብነው ነገር ላይ ጊዜ ወስደን መጸለይ አለብን። የጌታን ፍጹም ፈቃድ ለማወቅ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ የጸሎት ጊዜ ልንወስድ ይገባል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ዘለቄታዊ ጥቅማችንን የሚፈልግ ነው። “ለእናንተ የማስባትን ሀሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም” (ኤርምያስ 29፡11)። እንዲሁም የእግዚአብሔር ቃል “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው” (ምሳሌ 14፡12) ይላል። እግዚአብሔር ብቻ ነው የነገሮችን ፍጻሜ በውል የሚያውቀው። ባይገባንም እንኳ የእርሱን ምክርና ፈቃድ መቀበል መልካም ነው። ስለዚህ እርግጠኛ ባልሆንበት ጉዳይ ላይ ስንጸልይ ፈቃድህ ከሆነ ይሁን፤ ፈቃድህ ካልሆነ ግን ይቅር እንበል።

3. ትኩረትን በችግሮቻችን ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ማንነት ላይ በማድረግ መጸለይ ውጤታማ ነው። ስለ ችግሮቻችን ብቻ የምናስብ ከሆነ እምነት እናጣለን። ያለ እምነት የሚጸለይ ጸሎት ደግሞ ውጤታማ አይሆንም። ቃሉ “በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በንፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባህር ማዕበል ይመስላልና፤ ሁለት ሃሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች የሚያገኝ አይምሰለው” ይላል (ያዕቆብ1፡6-8)። ኢያሱ ለስለላ ከላካቸው መካከል አስሩ የተግዳሮቱን ብዛት አግዝፈው በማየታቸው ምድሪቱን እግዚአብሔር ሊያወርሳቸው እንደሚችል እምነት አጡ። ችግሮቻቸውን በእግዚአብሔር ዓይን ማየት ሲገባቸው እግዚአብሔርን በችግሮቻቸው ዓይን አዩት፤ ኢያሱና ካሌብ ግን ችግሮቻቸውንና ተግዳሮቱን በእግዚአብሔር ዓይን ሲያዩት እንደ እንጀራ ሆኖ ታያቸው። እምነትም አገኙ። እንዲህ በማለትም ተናገሩ “…እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና፣ የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፎአልና፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው አትፍሯቸው” (ዘኁልቁ 14፤9)። በተጨማሪም ካሌብ “ማሸነፍ እንችላለንና እንውጣ እንውረሰው” በማለት እምነቱን ገለጸ (ዘኅልቁ 13፤30)። አስሩ ሰላዮች ባመጡት ወሬ ውስጥ የጠላትን ትልቅነትና ግዝፈት አጉልተው ሲናገሩ አንዴ እንኳን የእግዚአብሔርን ስም በአዎንታዊ መልኩ አልጠቀሱትም። ኢያሱና ካሌብ ግን ሦስት ጊዜ የእግዚአብሔርን ስም ጠቅሰው ተናግረዋል (ዘኁ 13:26-33፤14:7-9)። ስለዚህ በምንጸልይበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ታላቅነትና ሁሉን ቻይነት እያሰብን ሊሆን ይገባል። ጆርጅ ሙለር የተባለው የ19ኛው ክፍለ ዘመን የእምነት ሐዋሪያ በአንድ ወቅት ወደ ካናዳ ለአገልግሎት በመርከብ ይጓዝ ነበር። በባህር ላይ ሲጓዙ መንገዳቸው በጭጋግ ስለ ተሸፈነ መርከቡ መጓዝ ተስኖት ነበር። ጆርጅ ሙለር ካናዳ አገልግሎት ስለ ነበረው ሁኔታው አልተመቸውም። ወደ መርከብ ነጂው ሄዶ በፍጥነት እንዲያደርሰው ጠየቀው፤ የመርከቡም ነጂ “ይህ ሰው ጤነኛ ነው?” በማለት ካሰበ በኋላ ከፊታቸው የተደቀነውን ጭጋግ በጣቱ እየጠቆመ “አይታይህም እንዴ? መሄድ እንችላለን በዚህ ሁኔታ?” አለው። ጆርጅ ሙለር የተደቀነውን ጭጋግ ሳያይ “የሕይወቴን የእያንዳንዱን ሁኔታ የሚቆጣጠረውን አምላኬን ነው የማየው፤ አንተ ልትረዳኝ ካልቻልክ ሌላ የሚረዳኝ አለ” ብሎ ወደ መርከቡ የታችኛው ክፍል ለጸሎት ወረደ። የመርከቡ ነጂም ክርስቲያን ስለነበረ ይሉኝታ ተሰምቶት ለመጸለይ ጆርጅ ሙለርን ተከትሎ ሄደ። ጆርጅ ሙለር አጭር ጸሎት ጸለየና ከጸሎቱ በመነሳት ሊጸልይ የነበረውን የመርከቡን ነጂ እንዲህ አለው፤ “አየህ፣ አንተ መጸለይ አያስፈልግህም፤ በመጀመሪያ ደረጃ አንተ እምነት የለህም፤ ሁለተኛ ደግሞ እኔ ስለ ጸለይኩ አንተ መጸለይ አያስፈልግህም። አየህ ካፒቴን፣ ከጌታ ጋር ላለፉት አምሳ ሰባት ዓመታት ስኖር አንድም ቀን አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ሂድ ወጥተህ እይ አለው” መርከብ ነጂው ወጥቶ ሲያይ ጉሙ ተበትኗል፤ ሕይወቱ በዚህ የአምነት ተዓምር በጣም ተነቃቃ፤ ጆርጅ ሙለርም ባሰበው ሰዓት ለአገልግሎት ካናዳ ደረሰ። በእግዚአብሔር እመኑ። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር ይህን ተራራ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል፤ ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የጸለያችሁትን የለመናችሁትን ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፣ ይሆንላችሁማል” (ማርቆስ 11፡23-24)።

4. ጌታን በመታዘዝ የሚደረግ ጸሎት ውጤታማ ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦ “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆናላችሁማል” (ዮሐንስ 15፡7)። በተጨማሪም እንዲህ ይላል፦ “ትዕዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን” (1ኛ ዮሐንስ 3፡22)። ከእነዚህ ጥቅሶች ጌታን መታዘዝ ለጸሎታችን መመለስ ወሳኝ መሆኑን ልንገነዘብ እንችላለን። የእግዚአብሔርን ቃል እንታዘዝ፤ እግዚአብሔርም ጸሎታችንን ይሰማል። ዓመጸኞች ከሆንን ግን ጸሎታችንን አይሰማም። አለመታዘዝ በደል ነው፤ በደል ደግሞ ጸሎት እንዳይመለስ እንቅፋት ይሆናል። “እነሆ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤ ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም። ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና አምላካችሁ መካከል ለይታለች፤ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል” (ኢሳ 54፡1-2)። ስለዚህ ራሳችንን በጸሎት በጌታ ፊት በመፈተሸ ያልታዘዝነው ነገር ካለ በመናዘዝ ንስሐ እንግባ፤ ከዚያም ጌታ ጸሎታችንን ይሰማል።

5. በኢየሱስ ስም የሚጸለይ ጸሎት ውጤታማ ነው። በራሳችን ስም ወደ እግዚአብሔር አብ የመቅረብ ብቃት የለንም፤ ጽድቃችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በልጁ ስምና ደም በኩል ወደ አብ መግባት አግኝተናል። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፦ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል …ማንኛውን ነገር በስሜ ብትለምኑት እኔ አደርገዋለሁ” ብሏል ጌታ ኢየሱስ (ዮሐ 16፡24፤ 14፡14)። ሁል ጊዜ ወደ እግዚአብሔር አብ ስንቀርብ ጽድቃችን ክርስቶስ እንደሆነ ማወቅ አለብን፦ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብ፣ ጽድቅ፤ ቅድስናም፣ ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 1፡31)።

6. ሁለት ሆኖ በመስማማት የሚደረግ ጸሎት ውጤታማ ነው። “ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማይ ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል” (ማቴዎስ 18፤19)። የልብ አንድነት ትልቅ ሥራ ይሰራል። ስለዚህ ቢያንስ አንድ የልብ የሆነ የጸሎት ጓደኛ ያስፈልገናል። ልባችን የሚቀባበልና የማይገፋፋ የጸሎት ወዳጅ ያስፈልገናል። ሁለትና ሶስት ከተገኙ መታደል ነው። ቢያንስ ግን አንድ የጸሎት ወዳጅ ያስፈልገናል። በልብ አንድነት የማይጸለይ ጸሎት ከጣራ አያልፍም፤ ከንቱ ልፍለፋ ነው።

7. ከልብ የሚደረግ ጸሎት ውጤታማ ነው። “ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ (ጴጥሮስ) ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር” (የሐዋርያት ሥራ 12፡5)። “አጥብቆ” የሚለው ቃል በሙሉ ልብ የሚደረግ ጸሎት እንደነበር ያሳያል። እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ መልአኩን ላከ፤ ጴጥሮስንም ከእስር ቤት አስወጣው፤ከተቀጠረለትም ሞት አዳነው። ጴጥሮስን ወደ ጸሎቱ ስፍራ ላከው፦ “ባስተዋለም ጊዜ (ጴጥሮስ) እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ” (የሐዋ ሥ12፤12)። ስለዚህ ስንጸልይ ከልባችን ልንጸልይ ይገባል፤ በግማሽ ልብ የሚጸለይ ጸሎት ኃይል የለውም። በሙሉ ልባችን ልንጸልይ ይገባል።

8. በጾም የሚጸለይ ጸሎት ውጤታማ ነው። በምንጾምበት ጊዜ ከምግብ ይልቅ ለጌታ ነገር ቅድሚያ መስጠታችንን ያሳያል፤ ጾም ራሳችንን ለማዋረድ ይረዳናል። ልባችንንም ለእግዚአብሔር ነገር ለማዘጋጀት በጣም ጠቃሚ ነው። በምንጾምበት ጊዜ መንፈሳችን ለመጸለይ የበለጠ ይዘጋጃል። የተለያዩ የጾም ዓይነቶች አሉ፦ ሀ/ የአጭር ጊዜ ጾም፦ ቁርስን ብቻ መጾም (የ6 ሰዓት ጾም)። ቁርስንና ምሳን መጾም (የ12 ሰዓት ጾም)። ቁርስ፣ ምሳና እራት መጾም (የ24 ሰዓት ጾም)። የ3 ቀን ጾም (ብዙ ውሃ መጠጣት አለብን፤ አካላችን ውሃ በማጣቱ የተነሳ የጤና ቀውስ ውስጥ እንዳንገባ)። ለ/ የረጅም ጊዜ ጾም፦ የ7 ቀን ጾም። የ21 ቀን ጾም። የ40 ቀን ጾም። ረዘም ላለ ጊዜ የምንወስደው ጾም (የ7 ቀን፣ የ21 ቀንና የ40 ቀን ጾም) በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሊሆን ይገባል። በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከሆነ የምንጾመው መንፈስ ቅዱስ ለሚሞተው ሰውነታችን ኃይልና ሕይወት ይሰጣል። በእነዚህ የጾም ቀናት ብዙ ፈሳሽ መውሰድ አለብን። ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት ረዘም ያለ ጾም መጾም የለብንም፤ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት ረዘም ያለ ጾም መጾም ለአጋንንቱ ዓለም ሊያጋልጠን ይችላል። ከክርስቶስ እምነት ውጪ የሆኑ ኃይማኖቶችም ጾም እንደሚጾሙ ማስተዋል አለብን። ጾም በራሱ የሚፈይደው ነገር የለም፤ ከጌታ ጋር ያለን ግንኙነት ወሳኝ ነው። ግልጽ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ማነሳሳትና ምሪት ካገኘን ረዘም ያለ የጾም ጊዜ መውሰድ ለብዙ ድል ያበቃናል። ቀንበር ይሰበርልናል፤ መለኮታዊ ምሪት እናገኛለን፤ የጠላት ሥራ ይፈርሳል፤ ጥሰት/ ጥርመሳ እናገኛለን። የ3 ቀን፣ የ7 ቀን፣ የ21 ቀን፣ የ40 ቀን ጾም ስንጾም ማታ ላይ ለስለስ ያሉ ምግቦችና ፈሳሽ በመውሰድም መጾም ይቻላል። በተለይ ያለ ምግብ ከሦስት ቀናት በላይ የምንቆይበት ጾም ከያዝን ስንፈስክ በጣም መጠንቀቅ ይኖርብናል። ቀጠን ያሉ ፈሳሾችን በመውሰድ ቀስ በቀስ ወደ ጠንካራው ካልተሸጋገገርን ትልቅ የጤና ችግር ሊያስከትልብን ይችላል። የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች (ለምሳሌ እንደ ስኳር በሽታ ዓይነት) ረዘም ያለ ጾም ከመያዛቸው በፊት ሐኪም ቢያማክሩ መልካም ነው። በታሪክ ውስጥ የተነሱትን ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች ታሪክ ስናነብ በሳምንት አንድ ቀን በተለይ ዓርብ፣ ዓርብ የጾም ጸሎት ቀን እንደሚያደርጉት አግኝተናል። ስለዚህ ቢቻል በሳምንት አንድ ቀን በጌታ ፊት እራሳችንን የምናዋርድበት፣ ሕይወታችንን በቅዱስ ብርሃኑ የምናስፈትሽበት፣ የምንታደስበት፣ የአምላካችን ፊት የምንፈልግበት የጾም ቀን ቢኖረን መልካም ነው። የሕይወት ቀንበር ሲከብድብን፥ ጨለማ መንገዳችንን ሸፍኖት ምንም ተስፋ አልታይ ሲለን፥ ሰፋ ያለ የጾም ጸሎት ጊዜ መውሰድ መልካም ነው። ቢቻል ምቹ ቦታ ሄደን ሰብሰብ ባለ አእምሮ ብንጸልይ ብዙ በረከት ልንቀበል እንችላለን፡፡ ለሕይወታችን ጌታ አዲስ አቅጣጫ ይሰጠናል፤ በመንገዳችንም ላይ መለኮታዊው ብርሃኑን ስለሚፈነጥቅልን የከበበን ጨለማ ይበተናል። በመንፈሱም ይሞላናል፤ የመታደስ ጊዜ ይሆንልናል። በየአብያተ ክርስቲያናቱ በሚታወጁት ጾም ጸሎቶች ላይ መሳተፍ ለሕይወት ልምላሜና ተሃድሶ እጅግ ጠቃሚ ነው፤ ከቅዱሳን ጋር ስንከማች የበለጠ ኃይል ይለቀቃል። የጌታ ዓላማ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ስለሆነ ለአካሉ በሚለቀቀው ኃይልና ቅባት እንሞላለን።

ስለ ጾም የተጠቀሱ ጥቅሶች። “አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም፣ በለቅሶ፣ በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፤ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሓሪ፣ ቁጣው የዘገየ፣ ምሕረቱም የበዛ፣ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ … በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሕዝቡንም አከማቹ፤ማኅበሩንም ቀድሱ ሽማግሌዎችንም ሰብስቡ፤ ሕጻናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፣ሙሽሪቱም ከጫጉላ ይውጡ” (ኢዩኤል 2፡12-13፤15-16)። “ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል። በዚያን ወራት ይጦማሉ …ይህ ወገን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም አላቸው (ማርቆስ 2፡20፤ 9፡29)። “እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን ለጠሯኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ” (የሐዋ ሥ13፤2)። ከምግብ ይልቅ የጌታን ፊት በመናፈቅ አስኪ ራሳችንን እናዋርድ፤ በመጾም ስንጸልይ የብዙዎች ቀንበር ይሰበራል፤ እስራት ይበጣጠሳል፤ ተሐድሶ ወደ ሕይወታችንና ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣል፤ ብዙዎችም ከጨለማው መንግሥት ፈልሰው ወደ ጌታ መንግሥት ይመጣሉ።