ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት

በ ባየህ ኃይሉ ተሰማ

በዓሉ ግርማ በመስከረም ወር 1962 ዓ.ም ታትሞ ለሚወጣው መነን መፅሔት አንጋፋውን የአማርኛ ቋንቋ ጠቢብ እንግዳ ለማድረግ ቀጠሮ ተቀብሏል፡፡ ልክ በሰዓቱ በቀጠሮው ስፍራ ሲደርስ የ68 አመቱን አዛውንት ያገኛቸው አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ካለው ቢሯቸው ውስጥ በስራ ተጠምደው ነበር፡፡አዛውንቱ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ናቸው፤ የ29 ዓመት ጐልማሳ ሳሉ የጀመሩትንና 30 አመት የለፉበትን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ለማሳተም በመዘጋጀት ላይ የነበሩበት ጊዜ ሲሆን ቃለ ምልልሱ በተደረገበት ወቅት የረቂቁ መፅሐፍ ገፅ 2978 ላይ ደርሷል፡፡በዓሉ ግርማ አለቃ ደስታ ተክለወልድን ሲያነጋግራቸው፤ ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ ባገለገሉበት የአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት የሙሉ ጊዜ የእርማት ሠራተኛ ነበሩ፡፡

የአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ባለቤት የነበሩት ሙሴ ጆርጅ ጄራህያን በጊዜው ስለ አለቃ ደስታ ሲናገሩ፤ ከምድብ ሥራቸው አንዲት ደቂቃ እንኳን ዝንፍ የማይሉ ብርቱ፣ ታታሪና ኃይለኛ ሠራተኛ መሆናቸውን ገልፀው የእርማቱን ሥራ ጨርሰው ትተው ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት አዲስ በሚያዘጋጁት መዝገበ ቃላት ላይ እንደሆነ ገልጠው ነበር፡፡ ሙሴ ጆርጅ፤ አለቃ ደስታ በእርምት ሥራቸው ችላ ብለው የሚያልፉት ቃላት ቀርቶ ፊደል ስለሌለ “የአለቃ እርምት ከባድ ነው፤ የእርሳቸውን እርምት የተከተልን እንደሆን በሳምንት የሚያልቀው ሥራ በወር እንኳ አይገባደድም፤ በዚህ የተነሳ እርምት እንዳይሰሩ ከልክለናል” ብለው ነበር፡፡ አለቃ ደስታ ለሙሴ ጆርጅ አስተያየት መልስ ሲሰጡ፤ “ማንም ሰው ግዕዝን ጠንቅቆ ካላወቀ አማርኛን ሊያውቅ አይችልም፤ ፊደሉንም አነጋገሩንም ስህተት ያደርጋል፡፡ የኔ አረም ለዘመኑ ሰው ሁሉ አይስማማም፡፡ ከግዕዝና ካማርኛ ህግ ውጪ ተፅፎ የመጣውን ሁሉ አልቀበልም፡፡ ቋንቋዬን ስለማውቀው ማክበር አለብኝ፡፡ እንደኔ ከሆነ “ዦሮ” ነው እንጂ “ጆሮ” አይባልም፡፡ እንዲሁም ባንድ “ሀ” “ዐ” “አ” እንጠቀም ከሚሉ ሰዎች ጋር አልስማማም፡፡ ያማርኛ አባት ማን ሆነና! ይህ ሁሉ ስህተት የሚመጣው ግዕዝን ጠንቅቆ ካለማወቅ ነው” በማለት ተናግረው ነበር፡፡

በአለቃ ደስታ የቢሮ ጠረጴዛ ላይ ቀይና ጥቁር ቀለም የያዙ ልዩ ልዩ ቅርፅ ያላቸው ብልቃጦች ተደርድረው ይታያሉ፡፡ ልዩ ልዩ የብረት ብርዖች የመስቀል ችቦ መስለው ተከምረዋል፡፡ የሚፅፉት በእጃቸው ሲሆን አንዴ ቀይ አንዴ ጥቁር እያጠቀሱ ያዘጋጁት መዝገበ ቃላት ላይ ይወርዱበታል፡፡ በቀይ የሚፅፉት አውራ ቃል ሲሆን በጥቁር የሚፅፉት ደግሞ ትርጓሜው ይሆናል፡፡ በዓሉ በመጣጥፉ የአለቃ ደስታ ተክለወልድን ፅናት በማድነቅ “ውቅያኖሰን በማንኪያ እየጨለፈ ለመጨረስ ታጥቆ የተነሳ ሰው ይመስላሉ፤ ትዕግስታቸው ትዕግስት ያሳጣል” በማለት አትቷል፡፡ “ከዘመዶቼ የወረስኩት መሬት ብቻ ነው” በማለት የተናገሩት አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ፤ የተወለዱት በሸዋ ክፍለ ሀገር፤ በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ፤ በወግዳ ወረዳ ልዩ ስሙ ጐሽ ውሃ ጊዮርጊስ ከተባለ ስፍራ ሐምሌ 19 ቀን 1893 ዓ.ም ነበር፡፡ ሰባት ዓመት ሲሆናቸው አባታቸው በተውት ኑዛዜ መሰረት ትምህርት ጀምረው እንደዘመኑ ተማሪ ከወግዳ ደብረ ሊባኖስ” ከደብረ ሊባኖስ አዲስ አበባ በመዘዋወር ንባብ፣ ቅኔና ዜማ ለመማር ቻሉ፡፡ ለአስራ አምስት ዓመታት ያህል ከወዲያ ወዲህ እያሉ የቅኔ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በሁዋላ በ1916 ዓ.ም በያኔው ተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት (ዛሬ ብርሃንና ሰላም) በአራሚነትና በሃይማኖት መፃህፍት አማካሪነት በሰባት ብር ደሞዝ ተቀጠሩ፡፡ አለቃ ደስታ በተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት በሚሰሩበት ጊዜ ከአንጋፋው የግዕዝ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ጋር ለመተዋወቅ ቻሉ፡፡ በተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት የተወጠነው ምሁራዊ ጓደኝነት” ድሬዳዋ በሚገኘው በቅዱስ ዐልአዛር የላዛሪስት ማተማያ ቤትም ቀጥሎ ሁለቱ በእውቀት ሰንሰለት የተሳሰሩት ሰዎች ለአስራ ስድስት አመት አብረው ሰርተዋል፡፡ አለቃ ደስታ ስለ የእድሜና የእውቀት ታላቃቸው ሲመሰክሩ፤ “የግዕዝን መሰረት ያወቅሁት ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ነው፤ አሁን ያዘጋጀሁትን ሰፊ ያማርኛ መዝገበ ቃላት ለመፃፍ የበቃሁት ከርሳቸው ባገኘሁት ትምህርትና እውቀት ነው” ብለው ነበር፡፡

ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ጋር:: አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የተወለዱት በ1862 ዓ.ም ሲሆን የ20 ዓመት ወጣት ሳሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ግእዝ፣ እብራይስጥና ዐረብኛ ያጠኑ፤ በትምህርትና በምርምር ላይ የቆዩና ከቀደምት የኢትዮጵያ የቋንቋ ሊቃውንት አንዱ ናቸው፡፡ በዘመኑ ኢትዮጵያ አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ የነበሩት ልዑል ራስ ተፈሪ፤ “ትችል እንደሆነ መጥተህ ሕዝቅኤልን ተርጉምልኝ” ብለው በፃፉላቸው ደብዳቤ መሰረት፣ በ1912 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ በታዘዙት መሰረትም ሕዝቅኤልን ንባቡን ከምሉ ትርጓሜው ጋር አሳትመው ካስረከቡ በኋላ፣ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ከተባለ አንጋፋ የግዕዝ ሊቅ በኑዛዜ የአንድ ትልቅ የመዝገበ ቃላት ሥራ ይተላለፍላቸዋል፡፡ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በዘመናቸው የግዕዝ - አማርኛ መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም ጅምራቸውን ከዳር ሳያደርሱት ሞት እንደሚቀድማቸው ስላወቁት ይህንን ኑዛዜ ለአለቃ ኪዳነ ወልድ ትተውላቸው አለፉ፡፡ ኑዛዜውም “ልጄ ሆይ! ይህንን ግሥ ለማሳተም ብትፈልግ እንደገና ጥቂት ዕብራይስጥ ተምረህ ማፍረስና ማደስ አለብህ፡፡ መጀመሪያ አበገደን ጥፈህ የፊደሉን ተራ በዚያው አስኪደው፡፡ አንባቦችም እንዳይቸገሩ ከፊል ቀጥለህ አጭር ስዋስው አግባበት፡፡ የጐደውና የጠበበው ሞልቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው፡፡ ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን አንድ መክሊት ለማብዛትና ለማበርከት ትጋ፡፡ ዘር ሁን፤ ዘር ያድርግህ” የሚል ነበር፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የተፃፈውን ጅምር መዝገበ ቃላት ቀን ከሌት ሳይሉ ይሰሩ ጀመር፡፡ ይህንን ትጋታቸውን አለቃ ደስታ ሲያስታውሱ፤ “በሥራ ውለው ማታ ንፋስ በመቀበል ጊዜ አንድ ሃሳብ ቢያገኙ በማስታወሻ ለመፃፍ ከውጭ ወደ ቤት ይመለሳሉ፡፡ በምሳ ወይም በራት ጊዜ አንድ ትርጓሜ ቢታሰባቸው ምግቡን ትተው ብድግ ይላሉ፡፡ ሌሊትም ተኝተው ሳሉ አንድ ምስጢር ቢገጥማቸው ከመኝታቸው ተነስተው መብራት አብርተው ይፅፋሉ” በማለት ተናግረዋል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ለበርካታ ዓመታት በዚህ ሁኔታ ቢሰሩም መዝገበ ቃላቱን ከፍፃሜ ለማድረስ እድሜ እንደሚገድባቸው ስለተረዱት አለቃ ደስታን ለደቀ መዝሙርነት መረጡ፡፡ ጊዜ ሞታቸው ሲቃረብም ከመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በጅምር የተቀበሉትንና እርሳቸው ያስፋፉትን የግእዝ መዝገበ ቃላት ሥራ በተራቸው ለአለቃ ደስታ ተክለወልድ አስተላልፈው አረፉ፡፡ አለቃ ደስታ በበኩላቸው፤ መዝገበ ቃላቱን አድሰውና አርመው “መፅሐፈ ስዋስወ ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” በሚል ርዕስ በ1948 እንዲታተም አደረጉ፡፡ ይህ 908 ገፆች ያሉት የግእዝ - አማርኛ መዝገበ ቃላት ደራሲ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መሆናቸው በመፃሀፉ የተገለፀ ሲሆን ደስታ ተክለወልድ በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ማሳተማቸውም ተጠቁሞበታል፡፡ በመሆኑም የሁለት ቀደምት ሊቃውንት ልፋትና ድካም በአለቃ ደስታ ተክለወልድ ፍፃሜ አግኝቶ ለመገለጥ በቃ፡፡

ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት:: የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንዲዘጋጅ ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት ዐልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ የነበሩት ንጉሥ ተፈሪ የካቲት 27 ቀን 1921 ዓ.ም ለአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የፃፉት ንጉሳዊ ማዘዣ ነ፡፡ ማዘዣው ይሄ ነበር፡፡

ይድረስ ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ
እንደምን ሰንብተሃል፡፡ እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ፡፡ ያገራችንን የቋንቋ ድህነት የምታውቀው ነው፡፡ ስለዚህ ዲክሲዎኔር እንዲገለበጥ አዝዣለሁና፤ ለዚሁ ሥራ ላቶ ብሩ ረዳት ኾነህ የተቻለህን ያህል አብራችሁ እንድትሰሩ ይሁን፡፡

ንጉሡ ያዘዙት ላሩስ የተባለውን ትልቁን የፈረንሳይ መዝገበ ቃላት ወደ አማርኛ ተርጉሞ ዐማርኛን ከዚያ ለመልቀምና ለመሰብሰብ ነበር፤ ነገር ግን ይህ አደራረግ አስቸጋሪ ስለሆነ በውጥን መቅረቱን አለቃ ደስታ ያስታውሳሉ፡፡ ትዕዛዙ የተፃፈላቸው አለቃ ኪደነ ወልድ ክፍሌ በበኩላቸው፤ ግዕዝን ትቼ አማርኛን ልፅፍ አይገባኝም፤ በአበገደ ተራ አንተ (አለቃ ደስታን) አማርኛውን ሰብሥብ በማለታቸው ንጉሳዊ ማዘዣውንና፤ የአማርኛ ቃላት የመሰብሰብ፣ የመፍታትና መዝገበ ቃላት የማደራጀቱ ግዙፍ ተግባርን አለቃ ደስታ በታላቅ አደራ ሊረከቡ በቁ፡፡ በመሆኑም አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ከ1921 ዓ.ም ጀምሮ ከሥራ መልስ በነበራቸው የእረፍት ጊዜ የአማርኛ ቃላትን የመሰብሰብ፤ የመመርመር፤ የማጥናትና የመተርጐምን ታላቅ ሥራ አንድ ራሳቸውን ሆነው ጀመሩ፡፡ ያለረዳትና ያለመተየቢያ መሳሪያ የተጀመረው ይኸው ግዙፍ ሥራ ለመጠናቀቅ ሰላሳ ዓመታት ያህል አስፈልጐታል፡፡ መዝገበ ቃላቱ በተለያዩ ምክንያቶች የሕትመትን ብርሐን ሳያይ ተጨማሪ አሥር ዓመታት መቆየት የነበረበት ሲሆን በመጨረሻም በ1962 ዓ.ም ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት የሚል ሱያሜ ይዞ በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ታተመ፡፡ አለቃ ደስታ ያዘጋጁት መዝገበ ቃላት የተደራጀው እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሁሉ በአበገደ ፊደል ተራ መሰረት ነው፡፡ ይህም ማለት መዝገበ ቃላቱ የሚጀምረው በ”ሀ” ፊደል ሳይሆን በ”አ” ፊደል ይሆናል ማለት ነው፡፡ የተለመደውን የፊደል ተራ ትተው በ”አ” የጀመሩበትን ምክንያት አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ሲያስረዱ፤ “በኢትዮጵያችን የፊደል መጀመሪያ “አ” መሆኑ ቀርቶ “ሀ” የሆነው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፤ ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡ የጥንቱ ፊደል ተራ አበገደ ነበር፡፡ የዓለም ፊደል ሁሉ የሚጀምረው በ”አ” ነው፡፡ እኔ በአበገደ ፅፌዋለሁ፤ አለቃ ኪዳነ ወልድን ተከትዬ” ይላሉ፡፡ በዚህ አካሄድ “ሀ” አምስተኛ ፊደል እንዲሁም “ለ” ሠላሳኛ ፊደል ሲሆን የመጨረሻው ፊደል ደግሞ “ተ” ይሆናል ማለት ነው፡ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት የመጀመሪያ ገፁ ያደረገው ከላይ የተጠቀሰውን ንጉሳዊ ማዘዣ ትክክለኛ ግልባጭ ሲሆን በመቀጠል የንጉሠ ነገሥቱ፣ የአልጋ ወራሹ፣ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌንና የደራሲውን ምስሎች በተከታታይ ገፆቹ አስፍሯል፡፡ ከገፅ 2 እስከ ገፅ 66 ያለው የመዝገበ ቃላቱ ክፍል መነቃቂያ፣ ማውጫ፣ መግለጫ፣ መቅድምና ግጥም፣ አገባብ፣ ነጥቦች፣ ቅፅል፣ ምዕላድና ስዋስው እና የመሳሰሉትን ርእሶች በዝርዝር የያዙ ምዕራፎችን አዝሏል፡፡ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት “አ”ን አጋፋሪ አድርጐ ገፅ 69 ላይ ይጀምርና በ”ተ” ፊደል በገፅ 1284 ላይ ይፈፀማል፡፡ መዝገበ ቃላቱ በውስጡ 523 አስረጂ ሥዕሎች ይዟል፡፡ የመዝገበ ቃላቱን የቃላት አፈታት በጥቂት ምሳሌዎች እንመልከት፤

ክቡር - የከበረ፣ የተሾመ፣ የተሸለመ፣ ባለ ማዕርግ፣ ታላቅ ሰው፣ ጌታ፣ ባለ ጠጋ፣ ከውርደት ከድህነት የራቀ፣ ችግር ደህና ሰንብት ያለ፡፡ ነገር ግን ክቡር፤ በአእምሮ ለከበረ ጨዋ ሁሉ የስም ቅፅል ይሆናል፡፡ ይድረስ ለክቡር አቶ እከሌ እንዲል ፃፊ፡፡ በቅሎ (ዎች)፤ በቅል አብቅልት፤ በቁሙ አጋሰሥ ከፈረስ ከአህያ የሚደቀል፤ አባቱ አህያ እናቱ ፈረስ፡፡ ባላገሮች ከጥንት ከፍጥረት ስላልነበረ አህያና ፈረስን በማራከብ በሰው ዘዴ ስለተገኘ፤ በምድራችን እንዲህ ያለ በቅሎ አያውቅም ተባለ ይላሉ፤ የስሙም ምክንያት ይህ እንደሆነ ይተርካሉ፡፡ (የጭን በቅሎ)፤ መቀመጫ ሰጋር፡፡ ግራጫን፣ ዋርዳን፣ ጨበርን፣ ሸክላን፣ ሳሙናን እይ፡፡ (ተረት)፤ በቅሎ አባትህ ማነው ቢሉት እናቴ ፈረስ ነች አለ፡፡ ብልሃተኛ: ኞች - ብልህ የእጅ ጥበብ የናላ እውቀትና ማስተዋል ያለው ሰው፤ ባለአእምሮ ፈላስፋ ሀኪም ወጌሻ፤ ሞፈር ቀንበር ጉርዳ በሺ፤ እርፍ አራቂ ድግር ጠራቢ፤ ወይፈን ወጠጤ ወቃጭ፤ መዝጊያና መስኮት ገጣሚ፤ ጣራ አዋቃሪ ከዳኝ፤ ሱሪ በርኖስ ልብስ ድንኳን ሰፊ፤ የዘርን ጊዜ አዋቂ፤ ወለምታና ውልቃት ስብራት ጠጋኝ፤ ገራዥ እንጥል ቆራጭ፤ ዐይን አብራ (ዳን 1፤4፡፡ ማቴ 25፤2 ፡ 8 ፡ 9):: በመጨረሻው ምሳሌ (ብልሃተኛ) ግርጌ እንደተፃፈው ያለ ጥቅስ በመዝገበ ቃላቱ የሚገኝ ሲሆን በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅሱን ስንመለከት የአውራውን ቃል ፍቺ በምሳሌ የሚያስረዳ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ መዝገበ ቃላት ማደራጀትን የመሰለ ግዙፍ ተግባር ያለረዳት ለብቻ ያውም በእጅ እየፃፉ ማዘጋጀትን እንደ አለቃ ደስታ ተክለወልድ ያለ መንፈሰ ጠንካራ ሰው ካልሆነ በስተቀር ተራ ተርታው ሰው የሚደፍረው ተግባር አይሆንም ነበር፡፡ ይሄው መዝገበ ቃላት በታተመበት ተመሳሳይ ጊዜ የታተመውና 1390 ገፆች ያሉት (The Collins Dictionary of the English Language) ለማዘጋጀት 13 የእንግሊዝኛ ምሁራን የተሳተፉበት ሲሆን ቃላት ለመሰብሰብና ለመተየብ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እንደተጠቀሙ ሲታወስ የአለቃ ደስታን ድካም አጉልቶ ለማሳየት ይረዳል፡፡

አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ይህ ድካማቸው በዘመኑ እውቅና አግኝቶ "በኢትዮጵያ ጥናት ዘርፍ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተመራጭ" በመሆን የብር 15 ሺህ ሽልማት አሸናፊ አድርጓቸዋል፡፡ በዓሉ ግርማ በሽልማቱ ገንዘብ ምን ሊያደርጉበት እንዳሰቡ ጠይቋቸው ሲመልሱለት፤ “ገንዘቡ እጄ ከገባ በኋላ ጠይቀኝ፤ አለዚያማ አንበሳ ገድዬ ለምዱን ሸጬ - የሚለውን ተረት ይሆናል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በመፃፍ ላይ ያለሁትን ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት አሳትምበታለሁ እላለሁ” ብለውታል፡፡ አለቃ ደስታ ከዚህ መዝገበ ቃላት መታተም አስቀድሞ ዘጠኝ ሃይማኖታዊ መፃህፍትን አዘጋጅተው አሳትመዋል፡፡ እርጅና መጥቶ አዳከማቸው እንጂ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላትን እንደገና አርሞ፣ አስፋፍቶና አሻሽሎ የማሳተም ውጥን ነበራቸው፡፡ በመጨረሻም እኒህ አንጋፋ ምሁር በተወለዱ በ84 ዓመታቸው፤ ጳጉሜ 1 ቀን 1977 ዓ.ም አርፈው የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈፀመ ሲሆን የማይሞት ሥራቸው ግን ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡

ምንጭ፦ አዲስ አድማስ:: 9/18/2004