መሪ ስትሆን... ሁል ጊዜ፣
ከአሸብር ሰይፉ

ስለመሪነት ብዙ ተብሏል ደግሞም ገና ብዙ ይባላል፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ ከአንድም ሁለት የሚደርሱ ስለ አገልጋይ መሪነት ተጽፈው አነበብኩኝ፡፡ የብዙዎች ጥማቱና ረሐብ የሆነው መሪነት የቱንም ያህል ቢባልበት ብዙ ቢወራበትም የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት "ብዙ የተጠናና ብዙ የተባለበት ግን ጥቂት የታወቀ" እስከማለት ደርሰዋል:: እኔም የበኩሌን ለመወጣት ይህችን አነስተኛ መጣጥፍ ሞነጫጨርኩኝ፡፡ የእግዚአብሔር ህዝብን ለመምራት የሚረዱ ነጥቦችን እንደሚከተለው አቅርቢያለሁ፡፡
+ የጸሎት ጊዜ ይኑርህ፡፡ ጸሎት ሰማያዊው የእግዚአብሔር እቅድን የምንረዳበት፤ የፍቅሩን ጽናት የምናውቅበት፤ ማንነታችንን በአምላካችን ፊት የምንገልጥበት መሳሪያችን ነው፡፡ ጸሎት ምድራዊ የሆነን ተግዳሮት የምናሸንፍበት ትልቅ የጦር እቃ ነውና በእየለቱ በተገቢው ሁኔታ ልንታጠቅ ይገባል፡፡ የተሰወረ የሚገለጥበት ሀይለኛ መሳሪያ ነውና በጸሎት ትጋ፡፡
+ የፍቅር ሰው ሁን፡፡ ፍቅር ባለበት ነፃነት እንዳለ አትርሳ፡፡ ሸክም ለከበደው ሰው ቀንበር የሚሰበረው በፍቅር ነው፡፡ ጆሮዎችህ አጥርተው የሚሰሙት፤ የተነገረህን ሳይሆን እውነታውን የምትረዳው በፍቅር ነው፡፡ ፍቅር የደረቀን ነፍስ የሚያለሰልስ ቅባት፣ ሀጢያተኛውን ከሀጢያቱ የሚመልስ ጉልበት አለውና ዘወትር ፈልገው፡፡ ቅን ፍርድን መፍረድ የምትችለው የወንድምህና የእህትህን ድካም የምትቀበልበት መሳሪያህ ፍቅር ነው፡፡
+ ትህትናን ተላበስ፡፡ ክርስቲያን አገልጋይ መለያው ትህትናው ስለሆነ በትህትና ተመላለስ፡፡ የትዕቢት መጨረሻው ውድቀትና ውርደት ስለሆነ ተጠንቀቅ፡፡
+ የተናገርከውን ኑር ፤ የኖርከውንም ተናገር፡፡ ከምታውቀው ውጭ ማንንም ልትመራ እንደማትችል ተረዳ፤ ስለዚህ የምታውቀውንና ያደረከውንና የፈጸምከውን ብቻ ስበክ እንዲሁም ኑረው፡፡ በዚህ የተነሳ የምታጣው ነገር ወይም ክብር የለም፡፡ ሰዎችም ስላንተ ሲመሰክሩ እውነቱን ነው እንዳለው ነው የሚኖረው ይሉሀል፡፡ በዚህ የምትጨምረው ደግሞ ታማኝነትን ነው፡፡ እርሱ ደግሞ ውድ ሀብት በመሆኑ ጠብቀው፤ እንዳይባክን በደንብ ያዘው፡፡
+ ለውጥን በተገቢው ሁኔታ አስተናግድ፡፡ ለውጥን ሁሉ በጥላቻ አትመልከት የማይቀር ነውና፡፡ ሁሉ ነገር በቋሚ ለውጥ ውስጥ እያለፈ ስለሆነ አንተም በአካባቢህ የሚከናውነውን ነገር በደንብ ተመልከት፤ አጥናው ጉዳትና ጥቅሙን መዝን (የእግዚአብሔር ቃል የመለኪያ መሰረትህ
ይሁን) ከዚያም የሚመጣው ለውጥ ጋር በተገቢው መንገድ መሄድ ትችላለህ፡፡
+ ሀቀኛ እና ታማኝ ሁን፡፡ ማንም ሰው አምኖ የሚከተልህ ታማኝና ሀቀኛ ስትሆን ነው፡፡ ስለዚህ በሰው ፊትም በእግዚአብሔርም ፊት ወጥ የሆነ ማንነት ይኑርህ፡፡ ከጥቂቱ ነገር ጀምረህ ራስህን ወጥ በሆነ አቋም ቅረጽ፤ ለጥቅም ብለህ ሀሳብህን አትለውጥ፡፡ ሰዎች ሁልጊዜ ለመከተል ከመሰናቸው በፊትም ይሁን በኋላ ነገሮችን መመዘናቸው ስለማይቀር ተለዋዋጭ ባሕሪን አታሳይ፡፡
+ ልበ ሩህሩህ ሁን፡፡ በቡድኑ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሀዘን የምትካፈል ሁን፡፡ የሰው ልጆች በችግር ቀን ወዳጅ እንዳለቸው ማወቅ የሚፈልጉት በዚህ ጊዜ በመሆኑ ከጎናቸው አትለይ፡፡ በተቻለህ መጠን እርዳቸው፡፡ ለዐዘነ ልብ የፍቅር ቃል በደመና መሀል እንደወጣች ጸሐይ ልብን ያሞቃልና በተገቢው መንገድ አጽናና፡፡ ለደከመው ሰውም የብርታት ቃልን አስታጥቅ፡፡
+ ሚዛን የጠበቀ ሕይወት ይኑርህ፡፡ አገልግሎትህ መጀመር ያለበት ራስህ በተገቢው ትጥቅ ካደራጀህ በኋላ ቤተሰብህን በማገልገል መሆን ይገባዋል፡፡ በውጭ የምትሰጠው አገልግሎት ፍሬያማ መሆኑ በቤትህ ካልተደገመ የኋላ የኋላ ሀዘንና ብስጭት ታተርፋለህ ስለዚህ ልዩ ትኩረት ለቤተሰብህ ልትሰጥ ይገባል፡፡
+ መጸሐፍትን መርምር፡፡ ካንተ ቀደም የነበሩ ሰዎችን ልምድ፣ ድካም፣ ብርታት፣ የገጠማቸውን ተግዳሮት፣ የህይወታቸውን ግብ እንዲት እንዳስቀመጡ ሁሉ ታገኛለህ፡፡ መልካም ከሆኑ ተሞክሯቸው ተጠቃሚ ትሆናለህ፤ ከስህተታቸው ትማራለህ፡፡ የህይወትህን አቅጣጫ የሚያጣፍጡ ቅመሞችን ታገኛለህ፡፡
+ የእግዚአብሔር ቃል የምታጠናበት ጊዜ ለይ፡፡ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን ቃሉን ማጥናትህን አታቋርጥ፡፡ የመኖርህ ምስጢር ቃሉ ነውና በፍጹም ልብህ ፈልገው፣ አሰላስለው፡፡ ይህ አለም እንዲሁ አይሸነፍምና በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተደገፍ፡፡ ለብርታትህ ምንጩ እርሱ ነውና ሁልጊዜ ከርሱ ፈቅ አትበል፡፡ እንደመልካም ዛፍ ብዙ ፍሬ የምታፈራው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ስትመሰረት ነውና፤ ከቃሉ ፈቅ አትበል፡፡
+ የጥሞና ጊዜ ይኑርህ፡፡ ብዙ በመሮጥ አትራፊ የምትሆን ከመሰለህ ተሳስተሀል፡፡ ብዙ በመሮጥ ሣይሆን በማስተዋል ውስጥ ነው ውጤታማነት ያለው፤ ስለዚህ ራስህን መፈተሸ አታቋርጥ፤ ድካምህንና ብርታትህን ለይተህ እወቅ፡፡ ይህንን በማድረግህ ደግሞ ያለህን ጠንካራ ጎን ማሳደግን ተለማመድ፡፡ ድካምህን ለማሻሻል ራስህን አስለምድ፡፡ በትምህርት ላይ መሆንህን ተገንዘብ ያንተ ድካም የሚከብደው ላንተ እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም፤ ለእርሱ ቀላል ስለሆነ ይለውጠዋል ብለህ እመን፤ በዚህም ወደማደግና ወደ መሻሻል ትመጣለህ፡፡ ሁሉ በእግዚአብሔር ይቻላልና ነው፡፡
+ ጊዜ የምድራዊው ኑሮ መለኪያ ነውና ይህንን ውድ ሐብት በአግባቡ ተጠቀመው፡፡ የህይወትህ ሽርፍራፊ በጊዜ እየተቆጠረ እንደሚያልፍ ልብ በል፡፡ ስለዚህ ይህንን መተኪያ የሌለውን ነገ ልታገኘው የማትችለውን ክቡር ሀብት ተንከባከበው፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጡትን ሐያ አራት ሰዓታት እንዲት እንደምታሳልፋቸው እቅድ አውጣ፤ ብዙ ጊዜህን የሚወስድብህን ነገር ለይተህ እወቅ፣ አትራፊ ሆኖ ካላገኘህው አስወግደው፡፡ ጊዜን አላግባብ ከሚበሉብህ ነገሮች ራቅ፡፡ በየቀኑ መጨረሻ የጊዜ አጠቃቀምህን ፈትሽ፡፡
+ የቡድን አጋሮችህን ማንነት ጠንቅቀህ እወቅ፡፡ ድካማቸውን፣ ጥንካሬያቸውን፣ የህይወታቸው ግብ፣ ደስታ የሚሰጣቸውን የሚያሳዝናቸውን ነገሮች ለይተህ እወቅ፡፡ በብርታታቸው ተጠቀም አበርታቸውም፡፡ በድካማቸውም ከጎናቸው አትለይ የሚሻሻሉበትን መንገድ አሳያቸው፤ ነቀፋ አታድርስባቸው፤ በሰው መሀልም አትውቀሳቸው፡፡ ወደተሻለው ከፍታ እንዲደርሱ መንገዱን ቀና አድርግላቸው፡፡
+ ውሳኔ ስትወስን መሰረቱ የእግዚአብሔር ቃል ይሁን፡፡ የሰው ልጅ ስለሆንክ ስህተትን ልትሰራ ትችላለህ ስለዚህ ስትሳሳት ተሳሳትኩኝ ለማለት አትፈር፡፡ ካንተም በፊት የነበሩት ካንተም በኋላ የሚመጡ መሪዎች መሳሳታቸው የማይቀር ነውና በራስህ አትፈር፡፡ የሚሰራ ሰው መሳሳቱ ስለማይቀር ብዙ አትጨነቅ፡፡ ይቅርታ በመጠየቅህ የሚደርስብህ የተለየ ችግር አይኖርም፤ ቢኖርም እንኳን ከአእምሮ ወቀሳና ከእግዚአብሔር ቅጣት ታመልጣለህና ቅር አይበልህ፡፡ በመሪነትህ ዘመን ሁሉ አገልጋይ መሆንህን አትዘንጋ፤ የክብር መገለጫ፤ የጥቅም ማግኛ አይደለምና መሪ ስትሆን ዘወትር የተሻለውን አገልግሎት አበርክት፡፡ እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይርዳን!!!