በቤተክርስቲያን ውስጥ አራት ዓይነት ሰዎች አሉ:- ፍጥረታዊ ሰው። ህጻን ክርስቲያን። ሥጋዊ ክርስቲያን። መንፈሳዊ ክርስቲያን

የትኛው ነህ? የትኛው ነሽ?

ተድላ ሲማ

1. ፍጥረታዊ ሰው። ቤተክርስቲያን የሚመጡ ሰዎች ሁሉ በዳግም ልደት አዲስ ፍጥረት የሆኑ ናቸው ብሎ መደምደም ያስቸግራል። ቤተ ክርስቲያን የሚመላለሱ ነገር ግን ዳግም ያልተወለዱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ዳግም መወለድን አስመልክቶ አንድ ሰው ያለውን መጥቀስ እፈልጋለሁ፥ “አንዴ ብቻ ከተወለድክ ሁለቴ ትሞት ዘንድ አለህ፤ ሁለቴ ከተወለድክ ግን አንዴ ብቻ ነው የምትሞተው፤” የሚከተሉት ጥቅሶች ይህንን የሚያረጋግጡ ናቸው፤ (ዮሐንስ 3:3-5፣16-18፤ዕብራውያን 9:27-28፤ ራእይ 20:15)። ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው ያልተቀበሉ ነገር ግን ቤተክርስቲያን በዘልማድ የሚመላለሱ ሰዎች ሁሉ ፍጥረታዊ ሰው ብለን ልንጠራቸው እንችላለን። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች መንፈሳዊ ነገሮችን በፍጹም መረዳት የማይችሉ ናቸው። “ለፍጥረታዊው ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና። አይቀበለውም፤ በመንፈስ የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል፣ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም፤ (1ኛ ቆሮንቶስ 2:14-15)።” ጥሩ የትዳር ጓደኛ ፈልገው የሚመጡ ይኖራሉ፤ ቤተክርስቲያን መሄድ ጥሩ ሰው ለመሆን ይረዳል ብለው ቤተክርስቲያን መሄድን የሚያዘውትሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ወይም በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ አድገው ጌታን ግን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ሳይቀበሉ በዘልማድ ብቻ የሚመላለሱ ሊኖሩ ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች መንፈሳዊው ነገር በቅጡ ያልገባቸው እንደሁም ሞኝነት የሚመስላቸው ናቸው። ጌታ ኢየሱስን ወደ ልባቸው በመጋበዝና ንስሐ በመግባት በዳግም ልደት የእግዚአብሔር ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ። ያኔ ነው መንፈሳዊው ነገር የሚገባቸው።

2. ህጻን ክርስቲያን። ህጻን ክርስቲያን የሚባለው ኢየሱስን የግል መድኃኒቱ አድርጎ በቅርብ ጊዜ የተቀበለና ዳግም የተወለደ ሰው ነው። እንዲህ ዓይነቱ ክርስቲያን የቃሉን ወተት በመመገብ ማደግ ይገባዋል። ሳያቋርጥ የቃሉን ወተት ከተመገበና በጸሎት ከአምላኩ ጋር በየዕለቱ ህብረት የሚያደርግ ከሆነ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያድጋል። የሚማረውን የእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ በተግባር ሲፈጽም ሕይወቱ ጤናማ አስተዳደግ ይኖረዋል። ከቅዱሳን ጋር ንጹህ የሆነ መንፈሳዊ ህብረት እያደረገ የቅዱሳንን ጸጋ እየተካፈለ ሲሄድ ጊዜውን ጠብቆ መንፈሳዊ ክርስቲያን ይሆናል (1ኛ ጴጥ. 2:1-3፤ ዕብ. 5:12፤ 1ኛ ቆሮ. 3:1-2)።

3. ሥጋዊ ክርስቲያን። እንደዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች ጌታን ተቀብለው የዳኑ ነገር ግን አስተዳደጋቸው ሳንካ የገጠመው ሰዎች ናቸው። ይህም የሆነበት ምክንያት ቃሉን በመታዘዝ ጤናማ የክርስትና ሕይወት ስለማይመሩ ነው። ራሳቸውን ያልካዱና በሥጋቸው ምኞት የሚመሩ በመሆናቸው ህይወታቸው እየጫጨ ይሄዳል። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች አመታት በጌታ ቤት የቆዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙ ዓመት በጌታ ቤት መቆየት ጥሩ ቢሆንም ቆይታ ብቻውን ግን በራሱ የሚፈጥረው ነገር የለም። ጌታን መታዘዝና በቃሉ መኖር ነው መንፈሳዊ ክርስቲያኖች እንድንሆን ሊረዳን የሚችለው። ሥጋዊ ክርስቲያኖች ፈቃዳቸውን ለእግዚአብሔር ከማስገዛት ይልቅ የልቦናቸውን አሳብ ብቻ የሚፈጽሙ ናቸው። የሥጋ ሥራ የሠለጠነባቸው፥በመንፈስ የሰውነትን ሥራ ያልገደሉ፥ የሥጋቸውን ምኞት የሚፈጽሙ ናቸው። በጌታ ቤት እንዳሳለፉት ቆይታና እንደተዘራባቸው መጠን ፍሬ ያላፈሩ ናቸው። በሚያሳዝን መልኩ ቤተክርስቲያን በእንደዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች የተሞላች ነች (1ኛ ቆሮንቶስ 3:1-4፥ሮሜ 8:13፥ ገላትያ 5:19-21፥ ቆላስያስ 3:5)። ሥጋዊ ክርስቲያኖች የለብታን ሕይወት የሚወዱና መንፈሳዊ ግለትን የሚጠሉ ናቸው። አሳዛኙ ነገር ያሉበትን ሕይወት ተቀብለው ተስማምተው የሚኖሩ ስለሆኑ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ ሊረዷቸው የሚሞክሩትን ሰዎች እንደ አክራሪ የማየት ዝንባሌ አላቸው። ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነት ክርስቲያኖችን መርዳት ጭንቅ ነው። እንዲህ ሊሆኑ ከቻሉበት ምክንያት አንዱ ምናልባት የተንጋደዱ ሰዎች “ስላሳደጓቸው” ሊሆን ይችላል (ዕድገት ከተባለ ማለት ነው)። እግዚአብሔር ካሉበት ሁኔታ በምህረቱ ያውጣቸው። ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለራሳቸው ክብር የሚኖሩ ናቸው። ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ የሚያሳያቸው የማንቂያ ደወል ያስፈልጋቸዋል። ዓይናቸው ተከፍቶ ያሉበት ጉስቁልና ሲታያቸው ያን ጊዜ ከተዘፈቁበት ሥጋዊነት ለመውጣት ብድግ ማለት ይጀምራሉ። በፈቃዳቸው ተቀብለው ያስተናገዱትን ሥጋዊነት ማለትም ጥላቻ፥ ቅናት፥ ምቀኝነት፥ እኔነት፥ ክርክር፥ መከፋፈል፥ ዘማዊነት፥ ማመቻመች፥ ዓለምን መምሰል፥ ትዕቢትና የመሳሰሉትን በመካድ በንስሐ ወደ ጤናማ የክርስቲያን ሕይወት ቢመለሱ ማደግ ይችላሉ።

4. መንፈሳዊ ክርስቲያን። እንደዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች የክርስትናን የህጻንነትን ዘመን የቃሉን ወተት በመጋትና በመታዘዝ ያገባደዱ ወይም በማገባደድ ላይ የሚገኙ ናቸው። በትክክለኛው የዕድገት መስመር ላይ የሚገኙ ናቸው። ከሥጋቸው ምኞት ይልቅ ለመንፈስ ቅዱስ የተገዙ ናቸው። የሥጋን ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚገድሉ ሲሆኑ በመንፈስም የሚመላለሱ ናቸው። በውስጣቸው ሁለት የሚቀዋወሙ ወገኖች እንዳሉ በሚገባ የተረዱ ሲሆን፥በክርስቶስ ለተፈጠረው ለአዲሱ ማንነታቸው በማድላት በመንፈሳዊ ሕይወት የዕድገት ጎዳና የሚገሰግሱ ናቸው። ሆኖም ስህተት አይሰሩም ማለት አይደለም። ስህትት ሲሰሩ ወዲያው ንስሐ በመግባት ከስህተታቸው ተምረው እንደገና ወደ መንፈሳዊ እድገት መሠላል የሚወጡ ናቸው። መንፈሳዊ ክርስቲያኖች ጌታ ባሰመረላቸው ሕይወት የሚመላለሱና እግዚአብሔር የተለመላቸውን እቅድ እየኖሩ የሚገኙ ናቸው። ከዚህ በመቀጠል መንፈሳዊ ክርስቲያኖች የሚታይባቸው ሰባት ባህርያት ተዘርዝረዋል። እነዚህ ባህርያት ግን ሁሉንም የመንፈሳዊነት ባህርያትን ያጠቃለሉ ናቸው ማለት አይደለም። ለዚህ ጽሑፍ ግን እነዚህን አንኳር ባህርያት መዳሰሱ በቂ ነው። መንፈሳዊ ክርስቲያኖች፥

1. ሥጋን ከክፉ መሻቱ ጋር የሰቀሉ ናቸው(ገላትያ 5:24)። በየዕለቱ ልምምዳቸው ሥጋቸው መሰቀሉን እየተረዱ የሚመላለሱ ናቸው፤ በሥጋቸው ምኞት የማይነዱ ናቸው።
2. ስለ መንፈስ የሚያስቡ ናቸው (ሮሜ 8:5)። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት እንዳለበት ነገር ግን ስለ መንፈስ ማሰብ ሕይወትና ሠላም እንደሆነ የሚያውቁና የሚለማመዱ ናቸው። ሕይወታቸውን የገዛው ስለ ሥጋ ማሰብ አይደለም። የእግዚአብሔርን ቃል የሚያሰላስሉ ናቸው። የእግዚአብሔርን ቃል ማሰላሰል ስለ መንፈስ ማሰብ እንደሆነ ተረድተዋል:: ምክንያቱም የጌታ ቃል መንፈስ ነው፤ሕይወትም ነው (ዮሐንስ 6:63)። ስለ ሥጋ የሚያስቡ ሰዎች ጭንቀትና ውከት እንጂ ሠላም እንደ ወንዝ አይፈስላቸውም (ኢሳይያስ 48:22)። መንፈሳዊ ክርስቲያኖች ከሚያስቡት ንጹህ አሳብ የተነሣ ፊታቸው ያበራል።
3. በመንፈስ የሚኖሩና በመንፈስ የሚመላለሱ ናቸው (ገላትያ 5:25)። በከንቱ እርስ በርሳቸው ላይ የሚነሳሱ አይደሉም፤ አይቀናኑም። አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ናቸው። ወደውና ፈቅደው በመንፈስ የሚኖሩና የሚመላለሱ ናቸው። ከምድር ተኮር ሕይወት ወጥተው በንስር ከፍታ ከእግዚአብሔር ጋር የሚፈስሱ ናቸው (ቆላስይስ 3:1-3)። ለመንፈሳዊ ክርስቲያን ሁለት ተቃራኒ አማራጮች ሲቀርቡለት ለመንፈሳዊ ሕይወቱ የሚጠቅመውን በመምረጥ በመንፈስ ይመላለሳል።
4. ከዓይን አምሮት፥ከስጋ ምኞትና ስለ ገንዘብ ከመመካት ነጻ የወጡ ናቸው (1ኛ ዮሐ2:16)። የዓይን አምሮት የገዛው፥የሥጋ ምኞት የሠለጠነበትና በገንዘብ የሚመካ ክርስቲያን የአብ ፍቅር በውስጡ የለም። የሚያፈቅረው ምድራዊውን ነገር ነው። ልቡ ከምድር ጋር የተጣበቀ ነውና። መንፈሳዊ ክርስቲያን ግን ከነዚህ የጸዳ ልብ አለው። እግዚአብሔርን ይወዳል እንጂ በዓይን አምሮት፥ በሥጋ ምኞትና በገንዘብ ፍቅር የተዋጠ አይደለም።
5. እግዚአብሔርን የሚከተሉ ናቸው (ኤፌሶን 5:1)። እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የሚከተሉ ናቸው። ጌታ ኢየሱስን በማየት የእርሱን ምሳሌና ፈለግ የሚከተሉ ናቸው። የህይወታቸው መሪ ጌታ ኢየሱስ ነው። ሥጋዊ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም (ሮሜ 8:8)።
6. መንፈሳዊ ክርስቲያኖች በጤናማነት በማደግ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን የሚሠሩ ናቸው። 7. ሙሉ ሰው ወደ መሆን የክርስቶስ ሙላት ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስኪደርሱ ድረስ የሚያድጉ ናቸው (ኤፌሶን 4:12 -13)። ከካቻምና አምና፤ ከአምና ዘንድሮ፤ ከዘንድሮ መጪው ዓመት ሕይወታቸው እያደገ የሚሄድ ነው። ማደጋቸው በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ያስባሉ። ልንገነዘበው የሚገባ ነገር ቢኖር በማንኛውም አቅጣጫ ዕድገት ደስ የሚያሰኝ ነገር መሆኑን ነው። በመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደጋችን እግዚአብሔርን የሚያስከብርና ለእኛም ደስታን የሚያጎናጽፍ ነው። መንፈሳዊ ክርስቲያኖች ክርስቶስን እስኪመስሉ ድረስ ዕለት ዕለት እየተለወጡ የሚሄዱ ናቸው። የሕይወት ዓላማ ወይም የመኖር ዓላማ እግዚአብሔርን ለማክበር መሆኑን ፈጽሞ ልንዘነጋው አይገባም።

ማጠቃለያ፥ የራሳችንን ሕይወት ከላይ ከተዘረዘሩት አራት ዓይነት ሰዎች አኳያ ስንመዝነው የትኛው ዓይነት ሰው ነን? ፍጥረታዊ ሰው፥ ህጻን ክርስቲያን (በቅርቡ ወደ ጌታ የመጣ)፥ ሥጋዊ ክርስቲያን፥ ወይስ መንፈሳዊ ክርስቲያን? ፍጥረታዊ ሰው ከሆንን ጌታ ኢየሱስን በእምነት ወደ ልባችን እንጋብዝ፤ ኃጢአታችንን እንናዘዝ፤ የበደላችንን ስርየት በመቀበል በዳግም ልደት የእግዚአብሔር ልጆች እንሁን። አሁኑኑ ባለንበት ቦታ በእምነት ጌታ ኢየሱስን ወደ ልባችን ብንጋብዘው አዲስ ሕይወት ይሰጠናል። ልባችን ተለውጦ አዲስ ፍጥረት እንሆናለን (2ኛ ቆሮንቶስ 5:17)። ህጻን ክርስቲያን ከሆንን የቃሉን ወተት በመጠጣትና በመታዘዝ ዕድገታችንን እንቀጥል፤ የመንፈሳዊ ባህርያትን እየተላበስን በመሄድ በጊዜው መንፈሳዊ ክርስቲያን መሆናችን አይቀሬ ነው። ሥጋዊ ክርስቲያን ከሆንን ደግሞ ንስሐ እንግባ። የሕይወት ዘይቤያችንን ሙሉ በሙሉ እንቀይር፤ ራሳችንን እንካድ፤ ለእግዚአብሔር እንገዛ፤ በመንፈስ እንኑር፤ በመንፈስ እንመላለስ። ከሥጋዊነት ሕይወት ለመውጣት ከወሰንን የእግዚአብሔር ፀጋ ያግዘናል። ፈቃዳችንን ለፈቃዱ እናስገዛ። በጌታ ቤት ዘመንን ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊነት ለማደግ እንጠማ፤ እንደግ። ለመንፈሳዊ ዕድገታችን የሚረዱንን ስጦታዎች ሁሉ ጌታ አዘጋጅቷል (ኤፌሶን 4:11-14)። እነዚህን ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ስጦታዎች በሙሉ በመጠቀም እንደግ። መንፈሳዊ ክርስቲያን ከሆንን ደግሞ በጀመርነው ጤናማ የመታዘዝና በመንፈስ የመመላለስ ሕይወት እንቀጥል። ወደ ፍጹም ሙላት ገና አልደረስንም። በደረስንበት ሕይወት ሳንመጻደቅ ወደ ክርስቶስ ሙላት ልክ ለመድረስ በጌታና በኃይሉ ችሎት እንበርታ። አዲስ ክብር እንናፍቅ። ጌታ ታውቆ አይጨረስም። እንደ ጳውሎስ የኋላችንን እየረሳን ወደ ፊት እንዘርጋ (ፊልጵስዩስ 3:13-14)። ጌታ አብዝቶ ይባርካችሁ!

2008 ዓ.ም. / 2015 / Twitter @tedlasima / Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. / Facebook: Tedla Ashame