አምልኮና የአምልኮ መልክ

በገዛኸኝ ሙሴ

________________________________

"መልካሙን ዝማሬያችሁን ሰምተው፣ ማራኪ ሽብሸባችሁን አይተው፣ በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያከብሩት ዘንድ

ዝማሬያችሁና ሽብሸባችሁ በሰው ፊት ያማረ ይሁን" አለማለቱን እርግጠኛ ሁኑ።

የተሳሳቱ የአምልኮ ግንዛቤዎች

አምልኮ ምንድነው? የሚለውን ከማየታችን በፊት በቅድሚያ አምልኮ ምን እንዳልሆነ ወይም ደግሞ የተሳሳቱ የአምልኮ ግንዛቤዎችን እንመልከት። አምልኮ የሚለው ቃል በጣም የምናውቀው የሚመስለን ሆኖም የምናውቀው የሚመስለንን ያህል የማናውቀው የከበረና ጥልቅ ትርጉም ያለው ቃል ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹አምልኮ›› ወይም ‹‹ማምለክ›› የሚለው ቃል በብዙ ወንጌላዊያን አማኞች ዘንድ እጅግ የጠበበ ትርጉም እየያዘ መጥቷል። በመሆኑም እግዚአብሔርን ማምለክ ማለት ሞቅ ደመቅና ፈጠን ባለ ሙዚቃና ሽብሸባ የታጀበ ሞቅ ደመቅ ያለ ዝማሬ በጉባኤ ማቅረብ ማለት ብቻ ነው ለብዙዎች።

ከዚህ ትንሽ ብናሰፋው ማምለክ ማለት መዘመር ማለት ነው፤ የምናመልከውም ስንዘምር ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ በጉባኤ ውስጥ ‹‹እግዚአብሔርን እናምልክ›› ብዬ ብናገር ምእመኑ በሙሉ የሚረዳው እንዘምር ማለቴ እንደሆነ ነው። ከዚህ ትንሽ ብናሰፋው ደግሞ ማምለክ ማለት ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተን የምናደርገው ነገር ብቻ ነው። ለምሳሌ ‹‹የቤተ ክርስቲያናችን የአምልኮ ሰዓት ዘወትር እሑድ ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 6፡30 ነው›› የሚለው ማስታወቂያ በሰሌዳ ላይም ይለጠፍ ወይም ከመድረክ ይነገር ትርጉሙ ከላይ ከተጠቀሱት ከሁለቱ ግንዛቤዎች ይሰፋል፡-ዝግ ያለውንም ሆነ ፈጣኑን ዝማሬ መዘመርን ጨምሮ፣ ቃሉን መስማት፣ መጸለይ፣ የጌታን ራት መውሰድ፣ ለጌታ ሥራ መስጠትና፣ መልካምን ማድረግ…አምልኮ ነው የሚል ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ነገሮች በጉባኤ አምልኳችንን ከምንገልጽባቸው መንገዶች ዋነኞቹ ናቸው።

ያም ሆነ ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹አምልኮ››ማለት ‹‹ዝማሬ››፣ ‹‹ማምለክ›› ማለት ደግሞ ‹‹መዘመር›› ማለት ሆኗል ብል ከእውነት የራቀ አባባል አይመስለኝም። ‹‹ታዲያ ምን ችግር አለው?›› ችግርማ አለው። ችግሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የአምልኮ ትርጓሜ ወዲያ መጣላችን ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ለአሁኑም ለሚቀጥለውም ትውልድ አጅግ የጠበበ የአምልኮ ትርጉም አወረስነው ማለት ነው። ‹‹ትርጉሙ ቢጠብ ምን ችግር አለው?›› እንዴታ! አለው እንጂ! የጠበበ የአምልኮ ትርጉም የጠበበ የአምልኮ ልምምድን ያስከትላል፡፡ ይህ እንዴት እንደሚሆን ትንሽ ቆይተን እንመለስበታለን።

cymbal2‹‹ማምለክ ማለት መዘመር ነው›› ማለት ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ የራቀ የሚሆነው እንዴት ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይም ሆነ በአዲስ ‹‹ዘምሩ›› ለማለት ‹‹አምልኩ›› ስለማይል ነው። ዘምሩ ለማለት ዘምሩ ነው የሚለው፡፡ አጨብጭቡ ለማለትም ‹‹ለእግዚአብሔር ክብር ስጡ!›› አይልም፤ አጨብጭቡ ነው የሚለው። መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ለእግዚአብሔር ክብር ስጡ!›› በሚልባቸው ቦታዎች ትርጉሙ ‹‹አጨብጭቡ!›› ከሚለው የራቀ ነው። አምልኩ ሲልም መላ ሁለንተናን ለእግዚአብሔር ብቻ ማስገዛትን የሚመለከት ትእዛዝ እንጂ ዘምሩ ማለቱ አይደለም።

ከዚሁ ሐሳብ ሳንወጣ ለቅዱሱ እግዚአብሔርና ለቅዱስ አምልኮ ፈጽሞ የማይመጥን በቅርቡ የተፈጠረ ቃል ‹‹አስመላኪ›› የሚለው ነው። ይህ ቃል ክርስቲያናዊውን አምልኮ የመግለጽ ዐቅም ፈጽሞ የለውም። የሚያስተላልፈውም መልእክት ክርስቲያናዊ አይደለም። ማንም ሥጋ ለባሽ ሌላውን ሥጋ ለባሽ ‹‹ሊያስመልከው›› አይችልም፡፡ ሰዎች ሊያስዘምሩን ይችላሉ፤ ሊያስሸበሽቡን ይችላሉ፤ ሊያስጨበጭቡን ይችላሉ፤ ሊያስቆሙን፣ ሊያስጎነብሱን ወይም ሊያሰግዱን ይችላሉ። ‹‹ሊያስመልኩን›› ግን አይችሉም፡፡ ማምለክ ከላይ በተጠቀሱት ሜዳዊ እንቅስቃሴዎች ወይም ድርጊቶች ብቻ የሚገለጥ ነገር አይደለም፡፡ አምላክ በመሆኑ ‹‹አስመላኪ›› የሚለው አይመጥነውም እንጂ ምናልባት ቃሉን መጠቀም የግድ ካስፈለገን እንኳ ስያሜውን ለመንፈስ ቅዱስ መስጠት እንችል ይሆናል፤ ወልድ አብን እንደ ተረከ ሁሉ ለኢየሱስ ያለውን ለእኛ አምጥቶ የሚያካፍለን መንፈስ ቅዱስ ነውና፡- ‹‹ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል›› (ዮሐ 16፡14)።

በተለይ በጉባኤ ዐውድ እውነተኛ አምልኮ ውስጣዊነቱ ይጎላል። ንጉሥ ዳዊት ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ‹‹መሥዋዕትን ብትወድስ በሰጠሁህ ነበር፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም፤ የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም›› (መዝ 51፡17) ሲል ይህን የአምልኮን ውስጣዊነት መግለጹ ነው። ጌታችንም ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት አምልኮን በተወሰነ ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ ለወሰነችው ሳምራዊት ሴት ‹‹እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል፤ አብ እንዲህ ዐይነት ሰጋጆችን ይሻልና›› (ዮሐ 4፡24) በማለት ትክክለኛው አምልኮ በሰው መንፈስ ውስጥና በእውነተኛ ግንዛቤ የሚከናወን እንደሆነ አስተምሯታል። እንዲሁም አምልኮን ከሜዳዊ ሥርዓት፣ ልምምድና ወግ ጋር ያያዙትን ፈሪሳዊያን ጌታ ከኢሳይያስ መጽሐፍ እየጠቀሰ ሲገስፅ ‹‹ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያመልከኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው፤ የሰው ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል›› (ማቴ 15፡7-9) ብሏል።

አሁንም ቢሆን ‹‹የዘመረ ሁሉ፣ ያሸበሸበ ሁሉ፣ ያጨበጨበ ሁሉ እግዚአብሔርን አምልኳል›› የሚለው ጠባቡ መረዳታችን ሜዳዊና ውሱን ለሆነው የአምልኮ ጎን ብቻ ከፍተኛ ትኩረት እየሰጠ በመሆኑ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኪሳራ እያደረሰብን ይገኛል። ቶሎ ባንነን ወደ ትክክለኛው የቋንቋ አጠቃቀምና ወደ ተሟላ የአምልኮ ግንዛቤና ልምምድ በፍጥነት ካልተመለስን፣የመዓት ነቢይ አትበሉኝና፣ ስብራታችን ፈውስ የሌለው ይሆናል።
ቀደም ብለን ወዳነሳነው ሐሳብ ስንመለስ፣ የአምልኮ ትርጉም መጥበቡ የአምልኮ ልምምዳችንን የሚያጠበው እንዴት ነው? ሰፊው ምእመን እግዚአብሔር የሚመለከው በጉባኤ አምልኮ ወቅት ብቻ ለዚያውም ሞቅ ደመቅ ያለ ዝማሬ ሲዘመር ብቻ ነው የሚል ግንዛቤ ከያዘ፣ ከእሑድ አምልኮ በኋላ ወደ ቤቱና ወደ ጎረቤቱ ሲሄድ፣ ሰኞ ወደ ቢሮው፣ ወደ ንግዱ፣ ወደ እርሻው… ሲመለስ በዚያ የሚሠራውና የሚሆነው ነገር ሁሉ እንደ አምልኮ ተግባር አይቆጠርም ማለት ነው። ይሄ ከትክክለኛው ክርስቲያናዊ የአምልኮ አስተምህሮ ያፈነገጠ አመለካከት ነው። ጌታችን ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ‹‹መልካሙን ዝማሬያችሁን ሰምተው፣ ማራኪ ሽብሸባችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያከብሩት ዘንድ ዝማሬያችሁና ሽብሸባችሁ በሰው ፊት ያማረ ይሁን›› አለማለቱን እርግጠኛ ሁኑ። ይልቁን ጌታ ያስተማረው ‹‹መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ›› (ማቴ 5፡16)ነው። ዓለማውያን ወደ ጉባኤ አምልኳችን መጥተው ዝማሬና ሽብሸባችንን ሊሰሙና ሊያዩ የሚችሉበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው። በአዘቦቱ ቀናት በየተሰማራንበት መስክ በዕለት ተዕለት ምልልሳችን የምናሳያቸውን ‹‹መልካሙን ሥራችንን›› አሌ ማለት ወይም አልሰማም! አላይም! ማለት አይችሉም፡- ምስክርነቱ የንግግር ሳይሆን የሕይወት ዘዬ፣ የኑሮ ነውና።

ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት ባሮች በታማኝነት ጌቶቻቸውን እንዲያገለግሉ የመከራቸው ምክር ዛሬ ባሮች ባይኖሩም መርሆው ግን ለሁላችንም ተግባራዊነት አለው፡- ‹‹…ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ›› (ኤፌ 6፡7)። እንዲሁም በቆላ 3፡23 ላይ ‹‹ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት›› ይላል። በዚሁ በቆላስይስ 4፡5 እና 6 ላይ ደግሞ ‹‹ዘመኑን እየዋጃችሁ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁል ጊዜ በጨው እንደ ተቀመመ በጸጋ ይሁን›› ይላል።

ከላይ ለአብነት በጠቀስናቸው ጥቅሶች ውስጥ የምንገነዘበው ነገር ‹‹አምልኮ በአራት ግድግዳና በአንድ ጣራ ሥር ጀምረን የምንፈጽመው የተወሰነ ድርጊት ነው›› የሚለው የብዙ የወንጌላዊያን አማኞች አመለካከት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑን ነው። እንዲያውም ዋናው የአምልኮ ቦታችን አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናጠፋበት ቦታ ነው። ነጋዴ ከሆንኩ የንግድ ሥራዬ የአምልኮ ተግባር ነው። ቃለ እግዚአብሔር ‹‹…ማናቸውንም ነገር ብታደርጉ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት›› (1ኛ ቆሮ 10፡31) ይላል። የንግድ ሥራዬ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰዎች ጥቅም የሚያመጣ ካልሆነ እንደ ማንኛውም ራስ ወዳድ ነጋዴ ሁለት ዐይነት መስፈሪያና ሚዛን የምጠቀም፣ ደንበኞቼን እጅግ ተመጣጣኝ ባልሆነ ትርፍ የምበዘብዝ፣ ግብርና ታክስ የማጭበረብር፣ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን የማልሰጥ ከሆነ በሳምንት አንድ ቀን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማደርገው ‹‹ፐርፎርማንስ›› እግዚአብሔርን ‹‹ሸውጄው›› አምላኪ ልሆን የምችልበት ምንም ዕድል የለም።

በፊርማዬ በብዙ ነገሮችና በሰዎች ሕይወት ላይ የምወስን ቢሮክራት ወይም ባለ ሥልጣን ከሆንኩ እስክሪፕቶዬን ለፊርማ ከማንሣቴ በፊት የምፈርምበት ጉዳይ ትክክለኛና ፍትሓዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብኛል። እናም ቢሮክራት ከሆንኩ እስክሪፕቶዬና ወረቀቴ ለእግዚአብሔር አምልኮን የማቀርብበት መሠዊያ ይሆናል ማለት ነው። መሐንዲስ ከሆንኩም ብዙ ገንዘብ ለማጋበስ ወይም ያለ አግባብ ለመበልጸግ ስል ደረጃና ጥራቱ የወረደ ሥራ በመሥራት የሐገርንና የሕዝብን ሐብት መበዝበዝ የለብኝም። ወንጀሌን መንግሥት ባይደርስበት እንኳ ሁሉ ነገር ሁል ጊዜ በፊቱ ዕርቃኑን ሆኖ ለሚታየው ለነገሥታት ንጉሥ ግን አይሰወርም። በእርሱ እጅ መውደቅ ከየትኛውም ምድራዊ ሥልጣን እጅ ከመውደቅ የከፋ ነው። ማምለክ ማለት መዘመር ማለት ብቻ ነው የሚለው ግንዛቤ አደገኛና በጣም አሳሳች የሚሆነው ከዚህ የተነሣ ነው።                      ይ ቀ ጥ ላ ል ...