አምልኮና የአምልኮ መልክ

በገዛኸኝ ሙሴ

[የመጨረሻው ክፍል]

_____________________________________

የግል አምልኮ ማለት ሰው አየኝ አላየኝ እኔ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ነኝ የሚል እምነት ይዞ መመላለስ ነው። እንዲህ ሲሆን ሕይወት አንድ ረዥም አምልኮ ሆነች ማለት ነው፡፡

አምልኮ ምንድነው?አምልኮን በቅጡ ለመረዳት ከሁለት ከፍሎ ማየቱ ይመረጣል፡፡ አምልኮ ቢያንስ ከሁለት ትልልቅ ምድቦች ይከፈላል፡፡ የግል አምልኮና የጉባኤ አምልኮ ተብሎ፡፡ እስቲ የሁለቱን ብያኔ እንመልከት፡፡

የግል አምልኮ። በቀን 24 ሰዓት፣ በሳምንት 7 ቀናት፣ በዓመት 365/366 ቀናት በሁሉም ቦታ በእግዚአብሔር ፊት እንዳለን በማወቅና በመረዳት የምንኖረው ኑሮ ነው፡፡ ይህን ስናሳጥረው፡- የግል አምልኮ ሁል ጊዜ በሁሉም ቦታ በእግዚአብሔር ፊት እንዳለን በማወቅና በመረዳት የምንኖረው ኑሮ ነው፡፡ ለግል አምልኮ ጥሩ ግንዛቤ ካላቸው የብሉይ ኪዳን ወጣቶች መካከል ዮሴፍ አንዱ ነው፡፡ የጲጢፋራ ሚስት ላቀረበችለት የነውር ግብዣ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢዓት እሠራለሁ›› (ዘፍ 399)? የሚል ቆፍጣና ምላሽ ነው የሰጣት፡፡ ዮሴፍ ከእስራኤል ምድር ርቆ፣የእስራኤል አምላክና የእስራኤላውያን አምልኮ በማይታወቅበትና ከእርሱ በስተቀር ማንም ዕብራዊ በሌለበት በግብፅ ምድር ቢገኝም እንኳን ያህዌ በአንድ ጊዜ በሁሉ ቦታ እንደሚገኝ እርሱም በዚህ ቅዱስ አምላክ ፊት ሁል ጊዜ እንዳለ ያምን ነበር፡፡ እናም የግል አምልኮ ማለት ሰው አየኝ አላየኝ እኔ ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ነኝ የሚል እምነት ይዞ መመላለስ ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ሕይወት አንድ ረዥም አምልኮ ሆነች ማለት ነው፡፡

የጉባኤ አምልኮ። የጉባኤ አምልኮ አማኞች በሳምንት ለተወሰኑ ቀናት፣ ለተወሰኑ ሰዓታት፣ በተወሰኑ ቦታዎች (እንደ ቤተ ክርስቲያን ባሉ) በአንድነት በመሆን እግዚአብሔርን የሚያከብሩበት፣ እርስ በርሳቸው የሚተናነጹበትና ለዓለም ምስክርነታቸውን የሚሰጡበት አገልግሎት ነው፡፡

የግል አምልኮ የጉባኤ አምልኮ መሠረት ነው፡፡ የግል አምልኮ ከሌለ የጉባኤ አምልኮ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የግል አምልኮ የጉባኤ አምልኮን አይተካም፡፡ የጉባኤ አምልኮም የግል አምልኮን አይተካም፡፡ ለጤናማ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁለቱንም በሚዛናዊነት መያዝ ያስፈልጋል፡፡

የብዙ መሪዎችና አገልጋዮች ትልቁ ትኩረት የጉባኤ አምልኮው ነው፡፡ ምእመናን ልብሳቸውንና ጸባያቸውን አሳምረው ለሰንበቱ አምልኮ ብቅ ካሉ፣ ዝማሬውንና ስብከቱን ከተከታተሉ፣ ዐሥራታቸውን፣ መባቸውንና የፍቅርና የሌላም ስጦታቸውን ከሰጡ ምእምናንም አገልጋዮችም ትልቁን ኃላፊነታቸውን የተወጡ ይመስላቸው ይሆናል፡፡ በእርግጥ በእሑዱ የጉባኤ አምልኮ ወቅት በብዙ መቶ ወይም በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አምልኮ አዳራሽ ሲገቡ ሲያይ ልቡ የማይሞቅ መጋቢ አለ ለማለት ያዳግታል፡፡ መጠየቅ ያለበት ትልቅ ጥያቄ ግን ይህ ብዙ ሕዝብ በአዘቦቱ ቀናት በግልና በሥራ ሕይወቱ፣ በቤቱ፣ በጎረቤቱ፣ በመሥሪያ ቤቱ፣ በንግዱ ሥራ እንዴት  ከርሞ ነው የመጣው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አገልጋዮች የምዕመናናቸውን የአዘቦት ሕይወት ምን ያህል ያውቃሉ? ወይስ ዘመኑ የዲሞክራሲ ስለሆነ ምእመናን እሑድ ብቅ ይበሉ እንጂ የግል፣ የቤት፣ የመስሪያ ቤት ሕይወት የራሳቸው ጉዳይ ነው? ከቶ እንዲህ ሊሆን አይገባም፡፡

baganaመጀመሪያ የመጠቀስ መርሆ/ሕግ። ቃለ እግዚአብሔር የሁሉ መፈተኛ ነውና ከላይ ያነሳነውን ነገር ቃሉ ይደግፈዋል? በእርግጥ! መጀመሪያ በመጠቀስ መርሆ መሠረት እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ በአቤልና በቃየን የቀረበለትን መሥዋዕት አስመልክቶ የሰጠው ምላሽ ዛሬም እግዚአብሔር የሚቀበለውን አምልኮ አስመልክቶ ትልቅ መሠረታዊ መርሆ ይሰጠናል፡፡ በዚያ ስፍራ ላይ ለእግዚአብሔር የቀረበለትን (የጉባኤ?) አምልኮ በሚመለከት ቃለ አግዚአብሔር የሰጠው አስተያየት የሚከተለው ነው፡- ‹‹እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም›› (ዘፍ 44)፡፡

በዚህ ቦታ ላይ አምልኮን አስመልክቶ ቃለ እግዚአብሔር የሚሰጠንን መሠረታዊ መርሆ የምናገኘው ‹‹እግዚአብሔር የአቤልን መሥዋዕት ተቀብሎ የቃየንን መሥዋዕት ያልተቀበለበት ምክንያት ምንድነው?›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ስናገኝ ነው፡፡ አንዳንዶች ትኩረታቸውን መሥዋዕቱ ላይ ያደርጋሉ፡፡ እንዲያውም የቃየን መሥዋዕት የደም መሥዋዕት ስላልነበረ ነው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘው የሚል መልስ ያቀርባሉ፡፡ የሆነ ሆኖ እግዚአብሔር በቅድሚያ የተመለከተው ያቀረቡትን መሥዋዕት ሳይሆን ሕይወታቸውን ነበር፡፡ ቃሉ ይህን ይላል? አዎ! ‹‹እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም›› ይላል፡፡ ይህን ኃይለ ቃል ስናነብ ብዙ ጊዜ ልብ የማንለው አንድ ወሳኝ መስተጻምር አለ፡፡ ይህም ‹‹እና›› የሚለው ነው፡- ወደ አቤል እና ወደ መሥዋዕቱወደ ቃየን እና ወደ መሥዋዕቱ፡፡ እናም እግዚአብሔር የአቤልን መሥዋዕት የተቀበለው በቅድሚያ የአቤልን ሕይወት ስለ ተቀበለ ነው፡፡ እግዚአብሔር የቃየንን መሥዋዕት ያልተቀበለው በቅድሚያ የቃየንን ሕይወት ስላልተቀበለ ነው፡፡ ከዚህ የምናወጣው መርሆ እነሆ፡- ‹‹እግዚአብሔር መሥዋዕትን የሚቀበለው መሥዋዕት አቅራቢውን ሲቀበል ነው፤ መሥዋዕት አቅራቢውን ካልተቀበለ እግዚአብሔር መሥዋዕቱን አይቀበልም፡፡›› እግዚአብሔር አምልኮን የሚቀበለው አምላኪውን ሲቀበል ነው፡፡ አምላኪውን ካልተቀበለ እግዚአብሔር አምልኮውን አይቀበልም፡፡ እግዚአብሔር ዝማሬን የሚቀበለው ዘማሪውን ሲቀበል ነው፤ ዘማሪውን ካልተቀበለ እግዚአብሔር ዝማሬውን አይቀበልም፡፡

ይህ መርሆ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ ያለው ነው፡፡ ጥቂት ጥቅሶችን ለአብነት እንጥቀስ፡፡ 1 ሳሙኤል 1517 ላይ ሳሙኤል ለሳዖል ‹‹እግዚአብሔር ቃሉን በሚሰሙት ሰዎች የሚደሰተውን ያህል በሚታረድና በሚቃጠል መሥዋዕት ደስ ይለዋልን?›› መልሱ አይለውም ነው፡፡ እንዲሁም በኢሳይያስ 110 ላይ የየዕለቱ ኑሯቸውና የሰንበቱ አምልኳቸው ለየቅል የሆነውን ሕዝቡን እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፡- ‹‹የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምኔ ነው?...መባቻችሁን፣ ሰንበታችሁን፣ በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድምመባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፤ ልታገሳቸውም ደክሜያለሁ…›› ምናልባት ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ትጠይቁ ይሆናል፡፡ መልሱ ቁጥር 16 ላይ ይገኛል፡- ‹‹እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል፡፡ ታጠቡ፤ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፤ መልካም መሥራትን ተማሩ…›› ወደ ሌላ ጥቅስ እንሸጋገር፡፡ ሆሴዕ 66 ‹‹ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠል መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለሁና›› ይላል፡፡ እንዲሁም በአሞፅ 521 ላይ ‹‹ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ፤ ተጸይፌውማለሁ፤ የተቀደሰውም ጉባኤያችሁ ደስ አያሰኘኝም፡፡የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም፡፡ ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፤ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ›› ይላል፡፡ በሚልክያስ ዘመንም የቤተ መቅደሱ የሰንበት አምልኳቸውና የአዘቦቱ ኑሯቸው ፈጽሞ ተቃራኒ ስለ ነበረ እግዚአብሔር ‹‹ምርር ብሎት›› ይመስላል እንዲህ ይላቸዋል፡- ‹‹በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ (የቤተ መቅደሱን) ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፤ ቁርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም›› (ሚል 110)፡፡

ጌታ ስለ እኛ ዘመን አምልኮ እንዲናገር ዕድል ብንሰጠው ምን ይል ይሆን? የመነቃቂያ ኮንፍረንሶቻችሁን፣ ራሳችሁን የምታዝናኑባቸውን የሙዚቃ ኮንሰርቶቻችሁን፣ የኪቦርዳችሁንና የጊታራችሁን፣ የሳክስፎናችሁንና የድረማችሁን ድምፅ አላደምጥም፡፡ ባዶ ጩኸትና ጭፈራችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፡፡ ይልቁን በሳምንቱ ኑሯችሁ በጽድቅ፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በይቅርታና በፍቅር፣ በመካከላችሁ ላሉት ችግረኞች በመቁረስና በመቆረስ አገልግሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ዝማሬያችሁን፣ ሽብሸባችሁን፣ የሞቀ የደመቀ ሙዚቃችሁን አቅርቡልኝየሚለን መስለኛል፡፡ በሳምንት ስድስት ቀን በዓለም ውስጥ እንደ ዓለማውያን ስንኖር ሰንብተን፣ እግዚአብሔር ተለዩ ካለን ነገር ሳንለይ፣ እግዚአብሔር አድርጉ ያለንን ሳናደርግ ቆይተን በሳምንት አንድ ቀን በምናደርገው አምልኮ ብለን በምንጠራው ፐርፎርማንስ/ ኢንተርቴይመንት እግዚአብሔርን ልንሸነግለው አንችልም፡፡ እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን አምላኪዎችን ከሕይወትና ከኑሮ የተፋታ አምልኮ አልቀበልም ካለ የእኛን የአዲስ ኪዳን አምላኪዎችን ከቶ እንዴት የሚቀበል ይመስለናል?

የአምልኮ መልክ ምንድነው? 

የአምልኮ መልክ ማለት አምልኮ የሚመስል ግን ያልሆነ ማለት ነው፡፡ የአምልኮ መልክ የሚለውን ቃል የምናገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ የመጨረሻውን ዘመን ምልክቶች በሚዘረዝርበት 2 ጢሞቲዎስ 36 ላይ ነው፡፡ በዚያ ስፍራ ጳውሎስ የመጨረሻውን ዘመን ክፉ የሚያደርጉ ምልክቶችን መዘርዘር ይጀምራል፡- ‹‹ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ፤ ይሆናሉ›› ካለ በኋለ ‹‹የአምልኮ መልክ አላቸው፣ ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ›› ይላል፡፡ ሰው ራሱን፣ ገንዘብንና ተድላን ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚወድ ከሆነ የሚያመልከው እግዚአብሔርን ሳይሆን ራሱን ነው፡፡ ታላቁ ትእዛዝ እግዚአብሔርን በፍጹም ሁለንተናህ አምልክ/ ውደድ የሚል ነው፤ ሰይጣን 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰው የሚሰብከው ስብከት ራስህን በፍጹም ሁለንተናህ ውደድ የሚል ነው፡፡

እግዚአብሔር በዘፍጥረት 4 በአቤልና በቃየን ከቀረበለት መሥዕት ጀምሮ የአምልኮን መልክ እንደ ተቃወመ አለ፡፡ የአምልኮ መልክ ማለት ይዘት የሌለው ሜዳዊ እንቅሥቃሴ ብቻ ማለት ነው፡፡ ይዘት ስንል ሌላ ሳይሆን የአምላኪው ሁለንተና ማለት ነው፡፡ አምልኮን አምልኮ የሚያደርገው የአምላኪው ሁለንተና ነው፡፡ እግዚአብሔር አምልኮን የሚቀበለው ከሰው ውስጣዊ ማንነት እንጂ ከሜዳዊው ፐርፎርማንስ አይደለም፡፡ የአምልኮ መልክ ኃይል አልባ የሆነበት ምክንያት ይሄ ነው፡፡ ‹‹የአምልኮ መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ክደዋል፡፡››

አንዳንድ ሰዎች ‹‹በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ ሞልቷል፤ የጠፋው ቅድስና ነው›› ሲሉ ይሰማሉ፡፡ አባባሉ ትክክል ባይሆንም ምን ለማለት እንደ ፈለጉ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ቦታ አምልኮ የተባለው ውዳሴ፣ ማለትም ዝማሬ፣ ሽብሸባ፣ ሙዚቃነው፡፡ በእርግጥ እያሸበሸቡ፣ እየሞዘቁ፣ እየዘመሩ አለመቀደስ ይቻላል፤ እያመለኩ ግን አለመቀደስ አይቻልም፡፡ ማምለክ ማለት ወደ ቅዱስ አምላክ መቅረብ ማለት ከሆነ ቅዱሱን አምላክ እያመለኩ አለመቀደስ አይቻልም፡፡ አምልኳችን ወደ ቅድስና የማያመጣን ከሆነ አምልኮ ብለን ልንጠራው አንችልም፡፡ ወይም እያመለክን ያለነው ቅዱሳን ፍጥረታት በቅዱስነቱ ፊት መቆም ፈርተው በሁለት ክንፎቻቸው፣ ፊታቸውን፣ በሁለት ክንፎቻቸው እግሮቻቸውን ሸፍነው በሁለት ክንፎቻቸው እየበረሩ ያለ ማቋረጥ ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ! በሚሉት ቅዱስ ነበልባል በሆነ አምላክ ፊት መሆኑን እጠራጠራለሁ፡፡ ሰዎች የሚያመልኩትን ነገር ይመስላሉና እያመለኩ ነኝ እያሉ በእርኩሰት የሚመላለሱ ካሉ የሚያመልኩት የሚቀድሰውን ሳይሆን የሚያረክሰውን ርኩስ መንፈስ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እናም እውነተኛው ክርስቲያናዊ አምልኮ ኃይል አለው፡- ከኃጢአትና ከኃጢአተኝነት፣ ከዓለምና ከዓለማዊነት ሕይወት የሚያወጣ ኃይል አለው፡፡ አምልኳችን ኃይል ከሌለው አምልኮ ሳይሆን የአምልኮ መልክ ነው፡፡ ከቃሉ እንዳየነው የአምልኮ መልክ ውስጥ ኃይል የለም፤ እውነተኛ አምልኮ ውስጥ ግን ኃይል አለ፡፡

ይህን ሰፊ ርእስ እንዲህ በአንድ መጣጥፍ አንጨርሰውም፤ ሐሳቦችን እናጭራለን  እንጂ፡፡ በዚህ ዘመን ስለ ቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ብዙ ሲባል እንሰማለን፡፡ የችግሩ ሥር እታች ድረስ ተሂዶ ቢመዘዝ የእውነተኛ አምልኮ መጓደል መሆኑን ማወቅ ይቻላል፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ሲያመልክ ከሰው ሁሉ ጋር በፍቅር ይኖራል፤ ታጋሽ ይሆናል፣ ለጋስ ይሆናል፣ ይቅር ባይ ይሆናል፣ ትጉ ይሆናል፣ ከዓለምና ከዓለማዊነት ይወጣል፤ በጽድቅና በቅድስና ሕይወት ይመላለሳል፡፡ ወደ እውነተኛ አምልኮ መመለስ ማለት ሁለንተናዊ በረከትና ሙላት ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር መመለስ ማለት ነው፡፡ እስቲ ከኢያሱ ጋር ይህን ውሳኔ እንወስን፡- ‹‹…የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፡፡ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› (ኢያሱ 2415)፡፡

ሕያው  አምልኮ ለሕያው አምላክ!