ቅዱሱና የተቀደሱ ሥፍራዎች

debreLibanos2

ስለ እግዚአብሔር ያለን መረዳት ስለ ራሳችን፣ ስለ ሌሎች እና ስለ ተቀደሱ ሥፍራዎች ያለንን አስተሳሰብ ይወስነዋል። እግዚአብሔር ማነው? ቅዱስ እና የሚቀድስ ነው? ሰውን በአምሳሉ የፈጠረ ከሰው የተለየ ወይስ ሰው የፈጠረው ነው? ሁለቱም አስተሳሰቦች በግንኙነቶቻችን ላይ ወሳኝ ናቸው።

ቅዱስ ይቀድሳል፤ በኅልውናው ያሰግዳል። እግዚአብሔርን የሚፈራ ልብ በአምሳሉ በፈጠራቸው፣ በእጁ ሥራዎች፣ በስሙ በተቀደሱት ሥፍራዎች ይደሰታል። “ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው”[ዘፍ 28፡17]። “በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው… በፊታቸው ወደቁ”[ማቴዎስ 17:1-8]

ሰው ሁሉ፣ ትውልድ ሁሉ ለቅዱሳን ነገሮች እኩል ግንዛቤ ይኖረዋል ማለት አይደለም። ቅዱሱን ለይተው የሚያውቁት፣ ቅዱሱን የሚወዱና አብረውት የኖሩ ናቸው። ቅዱሱን ማወቅ በመቅረብ ነው። ቅዱሱን አጥብቀው የሚሹ ቅድስናን የተጠሙ ናቸው፤ እግዚአብሔር ሰው እንዳልሆነ፣ ሰውም እግዚአብሔር እንዳይደለ የተገነዘቡ ናቸው። ፈሪኃ እግዚአብሔር የሚያድን እንጂ የሚያጠፋ እንዳልሆነ ያስተዋሉ ናቸው። “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው። ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው” [ምሳሌ 9፡10]።

ቅዱሱና ለራሱ የቀደሳቸው ሰዎች እቃዎችና ሥፍራዎች ከሌላው ሁሉ የተለዩ ናቸው። የተለዩ ስለሆኑም የሚያስቧቸውና የሚቀርቧቸው የተለዩ ናቸው። ተለይተው የወጡ፣ የተሰጡ ስለሆነ ያስፈራሉ፣ ያሰግዳሉ፤ አሳብን ወደ አምላክ ያቀናሉ።

ቤተመቅደስ አጠገብ ዝግታና ጸጥታ፣ ኮፊያ ማውለቅ፣ አንገት ዝቅ ማድረግ፣ መጸለይና አቅንቶ መሳለም ለባለቤቱ አክብሮትን ያሳያል። የእግዚአብሔር ኅልውና በሚታሰብበት በዚያ ረብሻ ይሁን ጸያፍ ነገር አይገባም። ወደዚያ ሮጦ የሸሸ ያመልጣል፤ ነፍስ አጥፍቶ የሸሸ ወደ አምላክ ጉያ ሸሽቷልና አሳዳጅ አይነካውም። ሰውን ማደሪያው ያደረገ። ከሕያዋን ድንጋዮች ቤቱን የሠራ እንዲህ ይላል፦ “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ[ም] ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና … በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ … ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ። እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል … ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” [2ኛ ቆሮ 6: 16-18። 1 ቆሮ 6:20]

በስድሳ ስድስቱ አብዮት የተቀደሰውን ለማርከስ ያልተደረገ ጥረት አልነበረም። ወጣቱን ለመሳብ የወንጌል ዜማዎች በአብዮታዊ መፈክሮችና ግጥሞች ተለዋውሰው ነበር። ወጣቱ ከሶሻሊስት ስነ ምግባር እንዳይጎድልና የኢምፔሪያሊስቶች ሰለባ እንዳይሆን አንደኛው ስልት ከጫት ከሰዶማዊነት ከሐሺሽ መከልከል ነበር፤ ዛሬ ስልቱ መረን መልቀቅ ሆኗል። በ“ሃይማኖት አይለያየንም” አገራዊ ጥሪ አሳብቦ የእምነትን ድንበር ማደብዘዝ። “እግዚአብሔር የለም” ገሃድ ሲወጣ ለእግዚአብሔር የተከለሉ ሥፍራዎች ለአብዮታዊ ተግባራት ይዋሉ መጣ። ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን የጸሎት ጥይት የሚተኮስበት፣ የቃሉ ሰይፍ የሚመዘዝበት መሆኑ ቀርቶ፣ የጥፋት መሳሪያ ፈቃድ መስጫ ጣቢያ ሆኖ ነበር። ሰይጣን መኮረጅና ቀናውን ማጣመም ምግባሩ ነው። የቤተክርስቲያን መሪዎች ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን ለማስከበር ዋጋ ከፈሉ። ከእነዚህ አንዳንዶች ተሻግረዋል፣ አንዳንዶች በሕይወት አሉ።

አብዮት፣ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ተተካ። ስለ ተቀደሱ አሳቦችና ልምዶች ግን ጉልህ ለውጥ አልታየም። እምነትና ስነ ምግባር ከታሪካዊ ማቴሪያሊዝም ወደ ጎሰኛ ግለኛነት ተሻገረ። አንድ ዐይናው አብዮት በሚቀላምድ ቅንዝረኛ አሥር ዐይናው ተተካ። እንደ ቀድሞው ዛሬም የገዥው ክፍል ካድሬዎች በየእምነት ተቋማት ውስጥ ተሰግስገዋል። ዛሬም ወደ ቤተክርስቲያን ሸሽቶ ማምለጥ አያድንም። አዳራሾች ለዳንኪራም ለአምልኮም ይከራያሉ። ሁሉም የየራሱን ማኅበርና ጀማ ስላቋቋመ ማንም ምንም እንዳይል ታቅቧል።

የግለሰብን፣ የቤተሰብና የማኅበረሰብን የስነ ምግባር አቅም ለቅዱሱና ለተቀደሱ ሥፍራዎች ካላቸው አመለካከት አኳያ መገምገም ይቻላል። የሞራል ውድቀት ሲበራከት፣ ሸፍጥና ክህደት አለመተማመን ይበዛል፤ ሰው ለራሱ እንጂ ለባልንጀራው የማይገደው ይሆናል። ሰው ባልንጀራውን በጊዜአዊ ምቾቱ ሲለውጥ፣ ያኔ ቅዱሱን ረስቶአል፣ ፈጣሪውን ንቆአል። ለዚህ ነው ትውልድ ትውልድን ማስተማርና ማቅናት የሚኖርበት። እንደ እህል ዘር ቅዱሱን ማወቅ ሊበዛ ወይም ሊቀጭጭና እስከነአንካቴውም ሊጠፋ ይችላል።

“ትውልድ ሁሉ ደግሞ ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ፤ ከእነዚያም በኋላ እግዚአብሔርን ለእስራኤልም ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ …ከእናንተም ሰው ሁሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቁጥር በጫንቃው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ይሸከም። ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይሆናል፣ ልጆቻችሁም በሚመጣው ዘመን፦ የእነዚህ ድንጋዮች ነገር ምንድነው? ብለው ሲጠይቋችሁ፣ እናንተ፦ “በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለ ተቋረጠ ነው …ትሉአቸዋላችሁ …ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ፣ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ዘመን ሁሉ ለእስራኤልም ያደረገውን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ” [መሳፍንት 2፡10፤ ኢያሱ 4፡4-7፤24፡31]

ለእህል ዘር እንደሚደረግ ሁሉ፣ የቅዱሳን አሳቦች ማረፊያና ማፍርያ አፈሩ ሊለሰልሰ፣ ውሃ ሊጠጣ፣ ሊኮተኮት እና ከአራዊትና ከተባይ ሊጠበቅ ይገባል። አፈር የትውልድ ልብና አሳብ ነው። አራዊትና ተባይም እግዚአብሔርን የማይገነዘብ ባህል፣ ሥልጣኔ፣ መንግሥታዊ አመራርና የትምህርት ዘርፍ ነው።

የአውሮጳ ልብ ደንዝዞአል፤ የአሜሪካ ተቀያይጧል። የኢትዮጵያ ግራ ተጋብቶ ይሆን? እስቲ እነዚህን ምልክቶች እናስተውላቸው፦
1/ በአምልኮ ሰዓት የእጅ ስልክ አውጥቶ ለማይታይ፣ ድምጽ ለማያሰማ፣ በጣት እየጠቀሰ ያወራል፣ ፎቶ ይሠራል።
2/ ቱሪስቶችና ውጭ አገር የኖሩ አበሾች እንደ ፍየል ማስቲካ እያመነዠጉና እያቁለጨለጩ፣ ያንጠለጠሉትን ካሜራ ታቦት ላይ ያብረቀርቃሉ፤ ከቋጥኝ ቋጥኝ ይዘላሉ፤ በሲና ተራራ ለሙሴ የታየውን ነጎድጓድና መብረቅ ያስታውሳሉ፤
3/ ጫማ አውልቆ ቤተክርስቲያን መግባት ድሮ ቀረ። ጫማ ማውለቅ፣ በእግዚአብሔርና በሰው መሓል ያልተቀደሰ ነገር አይግባ ማለት ነበር። ሙሴን “የቆምክበት መሬት ከኔ መገኘት የተነሣ የተቀደሰ ነውና ጫማህን አውልቅ” ብሎታልና። አገር ቤት ጫማ አውልቆ ስግደት፣ ባዶ እግር መቅረት ነው። ውጭ አገር በጫማ ላይ ኪስ ላስቲክ ሆኗል። እነሆ፣ አለመታዘዝን በመንፈሳዊ ላስቲክ ሸፋፈንን።
4/ ወንጌል ሲሰበክ ባርኔጣ አይወልቅም። እግዚአብሔር ከራሴ እንጂ ከባርኔጣዬ ወይም ከጭንቅላቴ ምን አለው፤ ቤቱ መምጣቴ መቸ አነሰና ነው? ለዚያውም እኔ ሆኜ ነው ይላል። ከገንዘቤ ቆንጥሬ ያደረግሁትን ውለታ ባርኔጣ መድፋት ያሳንስብኛል ብዬ አላምንም፣ ይላል። ንስሓ ገብቼለት የአገልግሎት መድረክ ይነሳኛል ብዬ አላስብም። የባሰ ጉድ ይዘው የሚያገለግሉትን ምነው ዝም አላችሁ? አድልዎ ቢቀር አይሻልም፣ ይላሉ፤ 
5/ ውጭ አገር ልብስ ሳይቸግር ምላስ የምታክል ምላሰኛ ካናቴራ ለብሶ ብቅ ይላል። ካናቴራዋ “ፔፕሲ” “ኢትዮጵያ” “ያንኪስ” “ኪስ ሚ” “ሎስ አንጀሊስ” ትላለች። እግዚአብሔር ከልቤ እንጂ ከልብሴ ምን አለው ብሎ ይሞግታል። ቀጣሪ ፊት በጥብቆ ይቅረብና እስቲ ይቀጠራታል! ፈጣሪስ ፊት?
6/ ለእግዚአብሔር የተለየውን መንካት፣ የሰው አማና መብላት ያስፈራ ነበር። ዛሬ ቅዱሳን ንዋያትን ለመሸጥ ሽሚያው ተጧጡፏል። በወንጌላውያን ቤት፣ በቸርነትና በባርኮት ስም የጌታ ገንዘብ ይመዘበራል። የራሳቸውን መቆንጠር የሚያማቸው፣ የጌታን አፍሰው ይበትናሉ፣ ወዳጅ ያፈሩበታል፣ ቸር ተብለው ይመሰገኑበታል።
7/ ለቤተክርስቲያን ሕንጻ ገንዘብ ለማሰባሰብ ዘፋኝ ይጋበዛል፤
8/ በጽሞና ማምለክ ተረስቷል፤ በእግዚአብሔር ፊት የግማሽ ሰዓት ጸጥታ እንኳ ጠፍቷል። አምልኮ ዐይን የሚስብ ግርግር መስሏል፤

ቅዱሱንና የተቀደሱ ሥፍራዎችን አለመለየት ይህን ይመስላል። “ቅዱስ በሆነና ቅዱስ ባልሆነ መካከል አልለዩም፤ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም …በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኩላዎች ናቸው” [ሕዝቅኤል 22፡26]። ቅዱሱን መገንዘብና አለመገንዘብ ውጤት ያስከትላል። አንደኛው ውጤት የማስተዋል፣ የሰላምና የጽድቅ ነው፤ ሌላኛው የስህተት፣ የሁከትና የጣዖት አምልኮ ነው። የትኛውን መረጥን?

© ምትኩ አዲሱ / ከ “ዘንድሮስ አልዋሽም፣ ተመስጦአዊ ድርሰቶች” / 2002 ዓ.ም፤ ገጽ 122-126። ለዚህ እትም በመጠኑ ታርሟል / 2008 ዓ.ም.