ጽ ላ ተ  ሙ ሴ እና  እ ኛ

wodajepic

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ከወንጌላውያን መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት በአምስት ቀን ውስጥ ከ200ሺህ ጊዜ በላይ ታይቷል። የአድማጭን ቀልብ ከሳቡት መሓል የዶ/ር ወዳጀነህ መሐረነ አስተያየት አንደኛው ነው (ከ40፡06—47:23 ደቂቃ)። የዶ/ር ወዳጀነህ አስተያየት ስነ መለኮታዊ/ማህበራዊ እይታዎችን ያንጸባረቀ ነው። ወንጌላውያን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ ግን ጎረቤታቸው ያለውን እምነት ችላ ብለዋል፣ ፍላጎቱም የላቸው። በሌላ እምነት ውስጥ በጎ ነገር አለ ማለት የሚያስወነጅል ሆኗል ብሏል። ይኸ ተገቢ ውረፋ ነው! ለውረፋው የወንጌላውያንን የአጭር ዘመን ታሪክ ማየት ጠቃሚ ነው። የአስተምህሮ ትኲረቱ በ “መንፈሳዊነት” (ነፍሳትን ከሲኦል ማዳን፣ ዛሬ ደግሞ ትንቢት) ላይ በመነበሩ፣ የአማኝ (የቤተክርስቲያን) ማህበራዊ ድርሻ ችላ መባሉ። ዶክትሪን/ስነ መለኮት ሰይጣናዊና ሥጋዊ እንደ ሆነ መታሰቡ (ዛሬ እንዲህ ልንለቀቅበት!)። “መንፈሳዊነት” በአእምሮ ማደግን አለመጨመሩ (1ኛ ቆሮንቶስ 14:20። ኤፌሶን 4:12-13፣23)።

ሥጋና መንፈስን የለየ አስተምህሮ ፍትህን አይገነዘብም፣ ከተገነዘበም ሥጋና ዓለም ጠፊ ናቸው ስለሚል ማህበራዊ በደል አፍጥጦ እያየ ያፈገፍጋል እንጂ በማቃናቱ አይሳተፍም። ወንጌላውያን በሃያ ሰባት ዓመት ውስጥ እርስ በእርስ ከመናቆር አልፈው በማህበራዊ ፍትህ ዙሪያ የወሰዱትን ጒልህ እርምጃ ማሰብ ያዳግታል። ይባስ የመንግሥትን ውለታ የሚቆጥሩ፣ “ሰላምና ከፍታ”ን የሚወዱና የሚተነብዩ “ነቢያት” በዙ! እስከ ዛሬ ለምንታመስባቸው ችግሮች መንስኤው፣ ማህበረ ምእመን ሊቀበለው የተገባ መሠረታዊ ትምህርት (ዶክትሪን) መፋለሱ ነው። ልኩን ሳያውቅ በእውነት መኖር፣ ስህተቱን መለየትና ማረም ያዳግታልና። የቤተክርስቲያንን ትምህርትና ተልእኮ ጠንቅቆ ማወቅ ቢኖር፣ ጠ/ሚሩ የጠሩት ስብሰባ ባላስፈለገ፤ ግለኛና በዝባዥ “መንፈሳዊነት” መሓል ላይ ተደላድሎ ባልተቀመጠ። እርግጥ፣ ሁሉም ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት አንድ ላይ ሊደመሩ አይችሉም። መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ለምሳሌ፣ የስነ መለኮት ትምህርት በማደራጀት፣ መኃይምነትን በመዋጋት፣ የወንጌልን ማህበራዊ ድርሻ በመገንዘብና በመተግበር ቀዳሚነት አላት። ሰፊ አእምሮና ልምድ ያላቸው መሪዎች መኖር፣ የረጋ አደረጃጀት መበጀትና የሚሲዮናውያንን አሠራር እንዳለ ከመቅዳት ከአገሬው ጋር ማስማማት ለዚህ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።

ዶ/ር ወዳጀነህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከ “ጠባብ” አመለካከት እንውጣ እያለን ነው፤ አንዱ እምነት ጋ የሌለ ብዙ መልካም ሌላው ጋ ስለሚኖር እንቀባበል፣ እንማማር፣ “ኤኪዩሜኒካል” እንሁን እያለን ነው። አባባሉ ምን ያህል አሳማኝ ነው? ለምሳሌ፣ ከሞት በኋላ (የዘላለምን) ሕይወት ለመረዳት፣ ውቅያኖስ ውስጥ ጣቱን ለነከረ፣ ከጣቱ ላይ የሚወርደው ጠብታ ምድራዊ ሕይወትን ሲወክል፣ ውቅያኖሱ ደግሞ ዘላለማዊ ሕይወትን ይወክላል የሚል አገላለጽ ቅርብ ጊዜ እንዳነበበና እንደ ወደደው ነግሮናል። አስተምህሮው ቡዲስት ይመስላል። ከቡዲስት አንማርም ባንልም፤ ወንጌል ምድራዊውንና ሰማያዊውን፣ ጊዜአዊውንና ዘላለማዊውን እንዴት ይገልጸዋል ብለን ልንጠይቅ ይገባል። በሌላ አነጋገር፣ ሌላው ሁሉ (ቡዲስት ሆነ አይሁድ) ሊመጣ ላለው ጥላ ነው (ቆላስይስ 1:15፤2:9፣17። ዕብራውያን 1:3። ዮሐንስ 1:1-5)።

በአገራችን የፖለቲካና የሃይማኖት ባህል፣ ወይ ረሓብ ወይ ጥጋብ የመሰለ አክራሪነት ይታያል። ዶ/ር ወዳጀነህ አክራሪነቱን ለማለዘብ ይመስላል እንድንቻቻልና እንድንቀባበል መክሮናል። ከራሳችን ወጣ ብለን የሌሎችን “አፕሪሼት” እናድርግ ይለናል። “ጠባብነት” እና “መቀባበል” ግን በማን አተረጓጎም ይሁን? ወንጌል፣ “መቀባበልን” የሚያንጸውና የሚዳኘው በመስቀሉ ትይዩ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስንና መስቀሉን ያላማከለ አስተሳሰብና አኗኗር ድካም ብቻ ሳይሆን ከንቱ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 1:23፣ 2:1-2)።

ዶ/ር ወዳጀነህ በመቀጠል፣ የአክሱም ጽዮንን ጽላት አስመልክቶ ጠ/ሚ ዐቢይ ወንጌላውያንን እንዲመክሩ አሳስቧል፦ እንጠቅሳለን፦ “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን [ ] ከእግዚአብሔር ተቀብለናል ብዬ የማምነው አንድ አደራ አለ። ይኸም ትልቅ አደራ፣ እግዚአብሔር ለሙሴ ተናግሮት በቀጥታ በትእዛዝ የተሠራ የእግዚአብሔር ታቦት አለ ... በኋላ ይኸ ታቦት “ዲሳፒር” አደረገ [የሄደበት ጠፋ] ከቤተመቅደስ። ጠፍቶ የት ነው ያለው ተብሎ ሲፈለግ፣ ሲጠና፣ ማስረጃዎች ሁሉ የሚያሳዩት፣ ይኸ ታቦት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ነው። እሱም አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ውስጥ ይኸ ታቦት አለ፣ እኔ በግሌ እርግጠኛ ሆኜ አምናለሁ። እንዳጠናሁት፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት መውደቅና መነሳት፣ የኢትዮጵያም ሕዝብ ብልጽግናና ጒስቊልና ቀጥታ ከዚህ ታቦት ጋር ይያያዛል። እና የርስዎን መንግሥት እግዚአብሔር ታቦቱን ያንን “ስፔሲፊክ” የሆነውን “ኦሪጅናሉን” ታቦት ነው የምለው፣ እርሱን ያከበሩ ነገሥታት ከብረዋል። ኃ/ሥላሴን እስከ ዛሬ ድረስ “ሂስ ማጀስቲ” ነው የምንላቸው። ከአርባ ዓመት በኋላ። “ስቲል ሪስፔክትድ” [የተከበሩ] ናቸው። እና እርስዎ በግልዎም በተከበሩ “ፈርስት ሌዲዋም” አማካኝነት ቢሆን ያ ቦታ ቢጎበኝ፣ እኛንም ይመለከተናል። እኛም ያንን “ኦሪጅናሉን” ታቦት እንወደዋለን፣ እናከብረዋለን። ይህን ቢያረጉ ነው ...”

ከዶ/ር ወዳጀነህ ንግግር ምን እንረዳለን?

1/ ዶ/ር ወዳጀነህ አገሩን እና የቀድሞውን “ንጉሠ ነገሥት” በጣም ይወድዳል፤ ከእግዚአብሔር ቃልና ታሪክ ጋር የአገሩን ታሪክ ማያያዝ ይሻል። በዚህ አድራጎቱ፣ አሐዳዊ መንግሥትና በተቀጽላ ባህላዊ የበላይነትን ማራመድ ይሻል። ይህ አይደንቅም፤ በአገራትና በነገሥታት ታሪክ ከእስራኤል አምላክ ጋር ወይም ከሌሎች አማልክትና ኃይላት ጋር ምድራዊ ሥልጣናትን ማያያዝ የተለመደ ነውና፤ እንግሊዞች (እና ሰሜን አውሮጳውያን) እንደ እስራኤል መሆን ከጅሏቸው ራሳቸውን “ብሪቲሽ ኢዝራኤላይትስ” አሰኝተው ያውቃሉ፤ ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከጠፉት አስሩ የእስራኤል ነገዶች የወጣን ነን ይሉ ነበር። ብቸኛውና አሜሪካኖች የፈጠሩት ሞርመን ሃይማኖት ከ19ኝኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይህንኑ ትረካ ደግሞታል። የግብጽ ፈረዖኖች ሥዩመ አማልክት ነን አሰኝተው ነበር፣ ወዘተ።

2/ በቂ መረጃ ባይኖርም፣ መረጃውን ማመሳከር ባይቻልም፣ አገሩንና ሃይማኖቱን ይወድዳል። ኃ/ሥላሴ "ቀዳማዊ" የተባሉት፣ "ሂስ ማጀስቲ" የተባሉት ታቦት ስላከበሩ ነው ማለት ከሚመልሰው ይልቅ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል! በውርደት ከሥልጣን መውረዳቸው ከዚህ አባባል ጋር እንዴት ይታረቃል?  ታቦት እያከበሩ ለምን ሕዝብ በረሓብና በጭቆና ረገፈ? ይልቅ "ሂስ ማጀስቲ" የትም አገር ላሉ፣ ታቦት ለሌላቸው (እንግሊዝ፣ ስፓኛ፣ ኢራን፣ ግብጽ፣ ወዘተ) ነገሥታት የተሰጠ ስም ነው ብሎ ዝም አይሻልም? ባጭሩ፣ ኢትዮጵያ እስራኤል አይደለችም፤ ነገሥታቶቻችንም ዳዊትና ሰለሞን አይደሉም!

3/ የወንጌላውያንን ጠባብነት አስቀድሞ ማንሳቱ ይህን የአክሱም ጽዮንን ጽላት ጒዳይ ለመግለጽ መሆኑ ግልጽ ነው።

4/ ጠ/ሚ ዐቢይ እንደ አገር መሪ ሁሉን የሃይማኖት ክፍሎች እኲል መመልከታቸውና ለማግባባት መጣራቸው፣ ከቀደሟቸው ሁሉ ልዩ ቢያደርጋቸውም፣ ሊደንቀን አይገባም። ይልቅ የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው፣ የሃይማኖት መሪዎች አደራቸውን መወጣት አቅቶአቸው ከመንግሥት (ከዓለም) ምሪት መጠየቃቸው ነው! የማህበረሰብ ሞራል ግንባታና የሰማያዊ እውቀት መነኻሪያ የሆነችዋ ቤተክርስቲያን የዓለም ብርሃን፣ ሰላም፣ አዳኝና ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታዋን መስማትና መታዘዝ ችላ ብላ፣ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ፣ ረዳቴ ከቤተ መንግሥት ይምጣ ማለቷ አሳፋሪና አሳዛኝ ነው!

5/ እንደ አንድ የጤና ባለሙያ፣ ዶ/ር ዐቢይና ሚንስትሮቻቸው ከሥራ ብዛት በቂ እረፍት አለማግኘት አንስቷል። በተለይ ያልተረጋጋች አገራችንን መምራት ቀላል እንዳልሆነ ብንረዳም፣ ችሎታ ያላቸውን (በጎሳ ኮታ ሳይሆን ብቊ ዜጋ በመሆናቸው ብቻ) መልምሎ ኃላፊነት የማያጋራ መሪ፣ የጀመረው መልካም ሥራ እርሱ በሌለበት ይበተናል፤ አካሉና አእምሮው ሳያርፍ የሚወስዳቸው እርምጃዎች የባሰ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ። አማንያን ለመሪዎቻችሁ ጸልዩ ተብለዋል፤ ከሰው ብቻ ያይደሉ፣ ከሰው በስተጀርባ የቆሙ የጭለማ ኃይላት ምድራችንን ለማወክና በመበተን ላይ ተሠማርተዋል። ቊልፉ የተሰጣት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ ቊልፉን ያኖረችበት ጠፍቷታል ወይም ልዩ በር ለመክፈት እየታገለች ነው!

6/ ዶ/ር ወዳጀነህ ለጠ/ሚ ዐቢይና ባለቤታቸው አክሱም ጽዮንን እንዲጎበኙ ያቀረበው ጥሪ እንዴት ይተርጎም? ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ጽ/ቤት ተገኝተው ስለ አከናወኑት የማስታረቅ ሥራ ቀደም ሲል ተሸልመዋል። በአንዋር መስጊድ ተገኝተዋል። “በግልዎም በተከበሩ 'ፈርስት ሌዲዋም' [ባለቤታቸው] አማካኝነት ቢሆን ያ ቦታ ቢጎበኝ፣ እኛንም ይመለከተናል። እኛም ያንን 'ኦሪጅናሉን' ታቦት እንወደዋለን፣ እናከብረዋለን።”

7/ “እኛ” እነ ማን ናቸው? ዶ/ር ወዳጀነህ ስለ ጽላቱ ካስረዳው ብንነሳ፣ የጠቀሳቸው የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ታሪካዊነት ትክክል ቢሆኑም፣ ከሐዲስ ኪዳን አስተምህሮ ጋር ሳናስተያይ መተርጎም ትልቅ ስህተት ነው። ሐዲስ፣ “ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለው … እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው … በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራል … ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤” ሲል ዘግቶታል፡፡ ዘግቶታል፡፡ (ዕብራውያን 10:1። ቆላስይስ 2:9፣17። ዕብራውያን 1:1-3)። ኢየሱስ፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ። ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር” (ዮሐንስ ወንጌል 2:19-21)። የቤተመቅደስና የመሠዊያው ዘመን አብቅቷል፤ አብቅቷል ያለው ሥርዓቱን በሙሴ እጅ ያዘዘው ሕያው እግዚአብሔር ራሱ ነው! “ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ (ማቴዎስ ወንጌል 27:50-51)። ቀድሞ ከመጋረጃው ኋላ ገብቶ እግዚአብሔር ፊት ሊቀርብ ያልተፈቀደና አስፈሪ ነበር፤ አንድ ሊቀ ካህኑ ብቻ፣ ለዚያውም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ፣ ለዚያውም ለራሱና ለሕዝቡ ኃጢአት ደም ሳይይዝ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አይገባም!! በየጊዜው ሞት ስለሚያግዳቸው ብዙ ሊቀ ካህናት ይፈራረቁ ነበር። እግዚአብሔር ያዘጋጀው ፍጹምና ንጹሕ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሠዋቱ ከእንግዲህ ሌላ መሥዋእት አልቀረም! ቤተመቅደስ አሁን በክርስቶስ ያመኑ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆኑት ናቸው እንጂ ድንጋይና በወርቅ የተለበጡ ዕቃዎች አይደሉም። ይህን ያለው እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ በላከው በልጁና፣ ልጁ በላካቸው በሐዋርያትና በነቢያት እጅ ያዘዘው ነው (ኤርምያስ 31:33፤ ዕብራውያን 8:10፤ 10:15-16። 1ኛ ቆሮንቶስ 3:9፣ 11፣ 16-17፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2:4-6፣ 9)። የበጎ ነገር እውነተኛው አምሳል ተገልጦ፣ ጥላውን መፈለግ፣ ከብርሃን ወደ ጭለማ መጓዝ ነው!! 'ኦሪጅናሉን ታቦት እንወደዋለን፣ እናከብረዋለን' ሲል፣ አስቦበት ይሁን ሳያስበው፣ ከኢየሱስ ላይ ዐይናችሁን አንሡ እያለን ነው!

“አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና። እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ” (ኤፌሶን 2:13-22)

የወንጌል ብርሃን ከበራልን በኋላ ወደ ኋላ አንመለስም!!

የማርያም ታላቅ አእምሮ

ፖለቲከኛ ቀስ በቀስ

የነጋሶ መንገድ