"የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ነው"

ከእለታት አንድ ቀን፥ ቀኑ መሸና ድንኳን የምንጥልበት ማደሪያ ሥፍራ ስንፈልግ፥ አንድ በዛፍ የተከበበ ገላጣ ሜዳ አገኘን። ከሜዳው ዳርቻ (መቼም ትግራይ፥ እንደ ሕዝቡ ደግነት፥ ገዳምና ቤተ ክርስቲያንም የበዛበት ነውና)፥ አንድ እጹብ ድንቅ የሆነ ቤተ ክርስቲያን አየን። ድንኳናችንን ከቤተ ክርስቲያኑ ራቅ አድርገን ከሜዳው ካይ ተከልን። ሦስታችንም በአንድ ድንኳን ውስጥ ተጠቃለን ተኛን። ሞቃት ሥፍራ ስለነበር፥ የድንኳኑን በር (ዚፕ) ሙሉ ለሙሉ አልዘጋነውም ነበር። ሌሊት በእንቅልፍ ልቤ፥ ደረጀና ኃይሉን ከእንቅልፋቸው የሚቀሰቅስ፥ ጥርት ባለ አማርኛ ንግግር አደረግሁ፤ ለፈለፍኩ። ምን እንዳልኩ የሚያውቅ የለም፤ ግን ያካባቢውን ጭቁን ሕዝብ የሚመለከት ንግግር ይመስላል። ምናልባትም ከመምሸቱ በፊት ስላጋጠመን ስለ አንድ ጭቁን ገበሬ ኑሮ፥ በቀን የታሰበኝ ይሆናል፤ በሌላ መልኩ (በቅዠት) መልክ የመጣብኝ። አንድ ጭቁን የትግራይ ገበሬ ድንጋይ ለድንጋይ እያማታ ያርሳል፣ በእርሻው ላይ ከአፈሩ ብዛት የድንጋዩ ብዛት ሳይበልጥ አይቀርም። ከሩቅ ሲያየን ሥራውን አቋርጦ እጅ ነሳን፤ ወዲያው ሊረዳን ፈለገና እኛ መንገድ ስንጠይቀው፤ እርሱ ደግሞ “እባካችሁ ኑ፥ ወደኔ ቤት እንሂድ፤ ሚስቴ ከእንጨት ለቀማ ስትመለስ ወጥ ትሠራልናለች። ቶሎ ካልተመለሰችና እናንተም ከቸኮላችሁ “ጣይታ ብበርበሬ ጌርና ክንበልእ፤ በጀኻትኩም ገዛ ንእትው፤” (እንጀራ በበርበሬ እንበላለን እባካችሁ፥ ወደ ቤት እንግባ) እያለ ተማጸነ። የሕዝቦች ደግነት፥ የአስተዳደር መዛባት፥ የእኛም ሕዝቦች ያሉበትን ሁኔታ በደንብ አለመረዳትና ዘላቂ መፍትሔ አለመፈለግ፥ ይህ ሁሉ ታስቦኝ ይሆናል ሌሊት የቃዠሁት።

ሊነጋጋ ሲል ደግሞ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያኑ ካለበት አቅጣጫ ተነስቶ በተከፈተው የድንኳን በር በኩል ሲያልፍ ተመለከትኩ። ጧት፥ ገና ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ሳትወጣ፥ ከእንቅልፋችን እንደተነሳን፥ ሲያቀብጠኝ ይህንኑ አስገራሚ ትእይንት ለጓደኞቼ ተናገርኩና፥ መሳቂያ - መቀለጃ ሆኜ ቀረሁ። ያየሁት የሰው ቅርጽ በሰው ቀለም ሳይሆን፥ ሰማያዊና ነጭ ሆኖ ነበር የታየኝ። ነገር ግን ልክ “ይህ የተመለከትከው መልክ የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ነው፤” የሚል ሃሳብ፥ ልክ እንደማይታበል ሃቅ በመሆን፥ እስካሁን በጭንቅላቴ ተቀርጾ አልጠፋ ብሏል።

ግለሰብና አብዮታዊ ውዝግቦች ጓደኞቼ ግን “ቤተ ክርስቲያን አጠገብ በማደራችን በአይምሮህ የምታሰላስለው ተከሰተብህ፤ አንተ አሁንም አይዲያሊስትነት (በእግዚአብሔር አማኝነት) ያልተላቀቀህ መሆንክን ተረዳን፤” ብለው አዘኑብኝ። እኔም የበኩሌን እውነተኛነት ከጓደኞቼ አስተሳሰብ ጋር እያነጻጸርኩ በነገሩ ብዙ አሰብኩበት። “መቼም በቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሥጋም ሆነ በመንፈስ የሚንጎራደድ ሰው አይታጣም። መቼም ሳይንቲስትና ኮሙኒስት ሲደመር አይዲአሊስት ሊሆን አይችልም። የቀን ተቀን ተግባሬ ሳይንሳዊ ምርምር ሆኖ ሳለ፥ ይህን የማይመስል ነገር የሚያጉላላ ጭንቅላቴ እውነቱን ማመሳከር እንዴት ያቅተዋል?” ብዬ እራሴን በትዝብት ጠየቅሁ። ከሰማዩ ብርሃን ጋር የሰው ቅርጽ እንዲፈጠር የሚያደርግ አካላዊ ክስተት ሊኖር ስለመቻሉ ጉዳይ ሳይንሳዊ ገለጻ ለማግኘት ባለመቻሌ፥ እራሴኑ ባለ ቅዠታዊ አስተሳሰብ ከማድረግ በስተቀር ሌላ አማራጭ በማጣቴ እስካሁን ድረስ ዝም አልኩ። [ምንጭ፦ መ. ኃ/መስቀል፤ ከምድራዊነታችን ባሻገር፣ አንደኛ መጽሐፍ፣ 2011 ዓ.ም.፤ ገጽ 4—5። ደማቅ ፊደላት ከአታሚው ናቸው]

ጒዞዬዝብርቅርቁ ሕይወቴ እና መለኮታዊው ጸጋ

ሞት እና ፕሮፌሰር