ፔትራ ወይ ዳሞ?

[ሰው በራሱ ጥረት የሰማዩን መንግሥት መውረስ ይችላልን?]

petradamo

ፔትራ በግራ በኩል የሚታየው ነው። ፔትራ ጣርያ፣ ማገሩና መደምደሚያው የዓለት ምርግ፣ ሰማይ ጠቀስ የሰው እጅ ሥራ ተምሳሌት ነው። ፔትራ በመካከለኛው ምሥራቅ በዮርዳኖስ የሚገኝ ጥንታዊ ከተማ ነው። ከክርስቶስ ልደት በፊት ከስምንተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ የኤዶም ህዝብ መኖሪያ ሆነ። ኤዶም፣ የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ከርብቃ የወለደው፣ የዔሳው ዘር ነው። ዔሳው የያዕቆብ ታላቅና መንታ ነው። ዔሳው ብኲርናውን በቀይ ምስር ወጥ ለያዕቆብ የሸጠው ነው። ርቦት ነበርና፣ ርቦኝ ብኲርና ምን ያደርግልኛል ብሎ ዘላለማዊ ርስቱን በሥጋ አምሮት ለወጠ። ረሃቡ ሲያልፍለት ተጸጸተ፣ አምርሮም አለቀሰ። ርስቱን መልሶ ሊያገኛት ግን አልቻለም። (ዘፍጥረት 25:29-34። ዕብራውያን 12:14-17) የብኲርናን ክቡርነት ለይቶ ያወቀውን፣ አታላዩን ያዕቆብን እስከ ሞት አሳደደው። ዔሳው ለሆዱና ለዚች ምድር ብቻ የሚኖር ሰው ምሳሌ ነው። ዔሳው ኤዶምን ወለደ። ኤዶም የያዕቆብ ዘር [ሕዝበ እስራኤል] ወደ ተስፋዪቱ ምድር ሲጓዝ መተላለፊያ የከለከለው ነው። (ዘኁልቁ 20፡21) ኤዶም፣ ከፍታ ላይ ከቋጥኝ መኖሪያ ሠራ። ከዚያ ሆኖ ቁልቁል ተመለከተ። በዚህም የልቡን ዓይነት ገለጠ። ልብህና ልቤ ተገልጦ ቢታይ ምን ይመስላል?

የአብድዩ ራእይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶም[ያስ] እንዲህ ይላል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ወሬ ሰምተናል መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኮ። ተነሡ፥ በላይዋም በሰልፍ እንነሣ ብሎአል። እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ አንተ እጅግ ተንቀሃል። በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር፥ ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ፥ በልብህም። ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? የምትል አንተ ሆይ፥ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። (ትንቢተ አብድዩ 1፡1-4) እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። (ያዕቆብ 4፡6)

ትዕቢት አይሻሻልም። የሺህ ዓመት መንግሥት ሊመሠርት ዝቶ የተነሳው የጀርመኖች መሪ ሂትለር (በ1936 ዓ.ም. ራሱን ያጠፋ)፣ ኪልሽታየንሀውስ (የንስር ቤት) የተሰኘ ግዙፍ መኖሪያ ስድስት ሺህ ጫማ ከፍታ ዓለት ላይ አሠርቶ ነበር። ባጋጣሚ ነው? የሞተው ግን ከምድር በታች ምሽግ ውስጥ ነው!

ከላይ በቀኝ በኩል የሚታየው ምስል ከክርስቶስ ልደት በኋላ በስድስተኛው ምዕተ ዓመት የተቋቋመው የደብረ ዳሞ ገዳም ነው። ደብረ ዳሞ ከጠላት የማምለጫ ዋሻ ነው። የደብረ ዳሞ ድምጽ፦ ‘ማን ያወጣኛል? ማን ያድነኛል? ወደ ዓለቱ ንቃቃት ወደ ከፍታው ማን ያገባኛል?’ ነው። ያለ ገመድ፣ ያለ ጠንካራ ገመድ ከፍታው የማይሞከር ነውና። ጭው ያለ ሆኖ፣ ከታች የሚጣራ ሞት፣ ከላይ ደኅንነትና ሕይወት ዘብ ቆመዋል። ገመዱ የእምነት መንገድ ነው፤ የማያረጅ የማይበጠስ የፍቅር ገመድ ነው። የመታዘዝ ምሳሌ ነው። መንገዱ ቀጭንና ጠባብ ነው። የተጋበዙ ብዙኃን፣ የሚሄዱባት ግን ጥቂቶች ናቸው። ገመዱ፣ ለኃጢአተኛዋ ረዓብ እንደ ተዘጋጀው ቀይ የማምለጫ ፈትል ምሳሌ ነው። የደም ምልክት ነው። ደም በቀራንዮ ተራራ፣ በመስቀል ላይ የፈሰሰው የእግዚአብሔር በግ የሆነው የኢየሱስ ደም ነው፤ “ኢየሱስ” አዳኝ ማለት ነው። ማምለጫ ዓለት የሆናቸው ሁሉ ሞትን ቊልቊል እያዩ ፈጣሪአቸውን ያመሰግናሉ።

* * * *

ፔትራ ወይ ዳሞ። ሁለት መንገድ አለ። አንዱ ሰፊ የጥፋት መንገድ። ሌላኛው፣ ጠባብ ከሞት የማምለጫ መንገድ። ከሁለቱ ባንዱ ላይ ነህ። በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ መንገድ ላይ መሆን አትችልም። የቱ ላይ ነህ? በሕይወት ወይስ በሞት መንገድ ላይ ነህ? “በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን። ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም።” (2ቆሮንቶስ 3፡4-5)

ኢየሱስ፦ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” ይልሃል። “በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት [አለን]።" (ዕብራውያን 10፡19-20) ከእንግዲህ ሌላ መንገድ ፍለጋ መቅበዝበዝ አያሻም። የኃጢአት እስረኛ ሆነህ እስከ መቸ? ልታርፍ ስትችል በኅሊና ክስ ለምን ትማቅቃለህ? የትኛው መንገድ ላይ ነህ? አስተውልና ለይ። ስታመነታ ስታመካኝ ቀንህ እንዳይቆረጥ፣ የተዘረጋልህን የፍቅር ገመድ ያዝ። “እንደ ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ፥ እንደ ወፍም ከአጥማጅ እጅ ትድን ዘንድ” በኢየሱስ በኩል እጁን ወደ ዘረጋልህ፣ ወደሚያድነው ወደ እግዚአብሔር እጅህን ዘርጋ። ኢየሱስ ኃይል ይሰጥሃል። ሳታስበው ራስህን በሰንጣቃው ዓለት ውስጥ ሆነህ ታገኘዋለህ። የኃጢአት ይቅርታ፣ ሰላምና ደስታ ይሆንልሃል። ምኞት ወይም የሃይማኖት ተረት አይደለም። ብዙዎች ሚሊዮኖች በሕይወታቸው ሞክረው የመሰከሩት እውነት ነው!

የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? … ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ። (ሮሜ 8፡33-39)

እመን እንጂ አትፍራ። ኢየሱስ፣“ወደ እኔ የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም… በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 6፡37። ራእይ 3:20) ይህን ጥሪ ሰምተው ከሞት ካመለጡት መሓል አንዳንዶቹ በስም የምታውቃቸው ጓደኞችህና ዘመዶችህ ናቸው። የመዳን ቀን ዛሬ ነው፣ ቅጽበት የሚያመጣውን አታውቅም። “በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።" (2 ቆሮንቶስ 6፡2) "የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ፣" (መክብብ 12፡1)

* * * *

ፔትራ ወይ ዳሞ! ሁለት መንገድ አለ። ከሁለቱ ባንዱ ላይ ነህ። በሕይወት ወይስ በሞት መንገድ ላይ ነህ? እስካሁን ባነበብከው ልብህ ተነክቶ ከሆነ እንደዚህ ብለህ ጸልይ፦ ኢየሱስ ሆይ፣ ካንተ ሌላ አዳኝ የለም። ስለ ኃጢአቴ ሞተሃልና አመሰግንሃለሁ። ጽድቅህን ልታወርሰኝ ከሞት ተነሥተሃልና አመሰግንሃለሁ። እጄን ወዳንተ ዘርግቻለሁ፣ እጄን ያዘኝ። አድነኝ። በቀራንዮ መስቀል ላይ በፈሰሰው ደምህ ከበደሌ ፈጽሞ አንጻኝ፤ ይቅር በለኝ። የልቤን ደጅ ከፍቼልሃለሁና ወደ ሕይወቴ ግባ። ሰላምህን ስጠኝ። ስሜን በዘላለም መዝገብ ውስጥ ጻፍልኝ። አሜን።

ይህን ጸሎት ከልብ ከጸለይክ እግዚአብሔር ሰምቶሃል። ስለ ኢየሱስ የበለጠ ለማወቅ ወንጌላትን አንብብ። የማርቆስን ወንጌል አንብብ። ወንጌል ወደሚሰማበት ቤተክርስቲያን ሂድ።