jesus on the cross tissot

መስቀል ሠላጢን
መ ለ ስ ተ ኛ  ን ዛ ዜ፣  መ ስ ቀ ል ኛ  ነ ገ ር

ምትኩ አዲሱ

መስቀል እና ሠላጢን እንዴትና መቸ በማን እንደ ተጋጠሙ እቅጩን ማወቅ ያዳግታል። ሁለቱ የሚያበስሩት ፍልስፍና ግን የተድበሰበሰ ነገር የለውም። ወይ ሰላም ወይ ፀብ። ሰላም እና ፀብ። በሰላም ከመጣ አሳልመው፤ በጠብ ከመጣ ጎኑን ወግተህ ጣለው ...

ከጅምሩ የጠበኛና የጠርጣራ ሰው ሥራ ይመስላል፤ ጨርሶ ኢትዮጵያዊ ነገር። ጸሎት ያዘወትራል፤ ጠብ ይወድዳል፤ ያሤራል፣ ቅንነቴ አስጠቃኝ ብሎ ይበሳጫል። ትሑት ነህ እስኪባል እንኳ አይታገሥም፣ “ትሑት ልሁን ብዬ እንጂ ...” ይላል። ትሕትናና ጥጋብ፣ እርቅና ቂም፤ ውዳሴና እርግማን አብረው መታየታቸው ትንሽም አይቆረቊረው። መስቀል በእጅ፣ ጠብ በልብ ይዞ ሰላም እንደማይሆን አይታየውም። መንደር ዘሩን ሲያገንን፣ አገሬን እወዳለሁ ማለት መቃረኑ አያሳፍረውም! የዜግነት መሥፈርቱ እኔው ራሴ ነኝ፤ ውልፍች ካልክ ጽንፈኛ ባዳ ነህ ብሏል!

መስቀል ተሠላጢኑን የያዘው እጅ የማን ነው? በሠላጢን አስታክኮ የመስቀል ሥራ መሥራት አግባብ ነው? ወግቶ ካጋደመ በኋላ ጠብ አለመሆኑን ሲያውቅስ? ሳሚና አሳላሚ በባህልና በቋንቋ ባይግባባስ? ከተወጋ በኋላ ቊስሉ ቂም እንዳይዪዝ እንዳይመረቅዝ እንዴት ማስጣል ይቻላል? መስቀል ተሠላጢንን በሚዛን መያዝ እንዴት ይቻላል?

መስቀል ተሠላጢን። ሠለጠ፣ ሾለ ነው። አንካሴ ነው። ከላይ ሰላም፣ ከታች ፀብ፤ ከላይ ለሌሎች መሠ--ዋት፤ ከታች ሌሎችን መሠዋት! አንካሴም ምርኲዝም ነው። ምርኲዝ አዳልጦት እንዳይወድቅ፣ እባብና (የሰው) አውሬ ቢገጥመው መከላከያ ጭምር። “መስቀል ባናቱ” አንካሴ ግን ደባ ይመስላል። እንደ ሰላምታው፣ እንደ ፈገግታው አይምሰልህ! በሰላምታ አዘናግቶ፤ የሚደግፍ መስሎ የሚወጋ። መቋሚያው በትር ነው፤ ጥምጥምና ቀሚስ ሥለት ሠላጢን ሸሽጓል። ወደ ቤት ገብቶ እጁን ግድግዳ ላይ እንዳስደገፈውና እባብ እንደ ነደፈው ሰው።

መስቀል በእጅ ከያዘ፣ በፀብ የመጣውን ለምን በሰላም አይመልስም? ብዙዎች በመስቀል አዘናግተው ተዘናግተው፣ ወግተውና ተወግተው ከመንገድ ዳር ወድቀዋል፤ ላሞራ ለጅብ እራት ተሠርተዋል። ቊጥራቸው ስንት ይሆን? በኢትዮጵያ ወርድና ስፋት የየዋሃን አፅም ተዘርቶበታል። ዛሬ አፅም ቆፋሪ በዝቶ ግማቱ ከዚች እዚች አላራምድ ብሏል።

መስቀል ተሠላጢን። ትሳለማታለህ ወይ ትጋደማታለህ። ምርጫው ሁለት ብቻ ለምን ሆነ? በአመፅ የመጣውን በሰላም መስቀል መመከት ሳይቻል ቀርቶ ነው? እንደ በጎች በተኵላዎች መሓል ሲሰድ ብልሃቱና ኃይሉ የኔ እንጂ የናንተ አይደለም ማለቱ አልነበር? ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተት ሲል፣ ሰይፍ ሰላምን ያመክናል፣ ሰይፍ ሰይፍን ይወልዳል ማለቱ አልነበር? ምድርን የሚወርሷት ብፁዓን፣ የዋሆች፣ ጽድቅን የሚራቡ የሚጠሙና የሚያስተራርቊ አይደሉም?

እንደ በግ በተኲላ መሓል ለመገኘት እንደ እባብ ልባም፣ እንደ ርግብ የዋህ መሆን ይጠይቃል። አንባቢ ያስተውል። የዋህ ሳይኾን ልባም መሆን ዘበት ነው! ልባም፣ አስተዋዩ ሩቅ አሳቢው እንጂ ክፉ ተንኰለኛ ድንክ ህልመኛው አይደለም! ተንኰለኞች፣ ሰላም ማውረድ ቀርቶ ራሳቸውም ሰላም የላቸው! እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ይሉ ዘንድ አይችሉ፣ ጭቃና ጕድፍ ይተፋሉ!

መስቀል፣ ሰላምን ለማውረድ ነበር፤ ነው። በሰውና በእግዚሐር መሃል፤ በሰውና በሰው መሃል፤ በራሱ በሰው ልብ ውስጥ የተዘፈዘፈውን ፀብና በደል ጠርጎ አስወግዶ በምትኩ እርቅና ሰላም ለማውረድ ነበር፤ ነው። መስቀል የፍቅር መግለጫ ነበር፤ ነው። ወይ ተሳለም ወይ ተጋደም፣ እንኳን ፍቅር ጠረኑም የለው! በግዴታ ከሆነ፣ ጥላቻ ከሆነ፤ ፍርኃት ከሆነ፤ ፍርኃቱ ለሚያሳልመውና ለሚሳለመው ከሆነ፤ መተማመን፣ አለመተማመን፣ መካካድ ሆነ ማለት ነው!

መስቀል ተሠላጢን። እነሆ፣ ሠላጢን ሚዛን ሲደፋ! አወይ ኢትዮጵያዊነት! ከመስቀሉ? ከሠላጢኑ? ምረጥ መባሉ! ወደ (ተሰቀለው) ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ... ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያው ደምና ውኃ ወጣ። ማንም ተወግቶ ከመንገድ ዳር እንዳይጣል አንዱ ስለ ሁሉ ተወጋ። ፍቅሩ ይህ ነው፤ ሰላምና ይቅርታ በደምና በውኃ ነው። አንባቢ ያስተውል።

*

ይህ ህግ ስለማስከበር ስላለማስከበር አይደለም፤ ህገ ወጡን ለፍርድ ስለማቅረብ ስላለማቅረብም አይደለም። ህግ ያፈረሰ ምንጊዜም አያምልጥ፤ በህግ ይቀጣ። ይህ ሤረኛነትን፣ ፀበኛነትን ስለማብረድ ነው፤ በሚዛን ሊያዙ ስለሚገባቸው ነገሮች ነው። ስለ ሰው ልብ ነው፤ ስለ ተንኰለኛነቱ። ስለ አስተሳሰብ ነው፤ ስለ ጨለምተኝነቱ፣ ስለ እውቀት ጠልነቱ። የፀብ የጠባብነት እስረኛ ስላለመሆን ነው። ስለ ርኅራኄ ነው፤ ስለ ፍትኅ ነው፤ ስለ እግዚአብሔር ፍርኃትና ፍቅር፣ ለሰው ሁሉ ፍቅርና አክብሮት ስለማሳየት ነው።

መስቀልኛ ነገር፦ ጠፍር ያነገቱ የማይተዋወቁ ሁለት፣ ቆዳ ለብሰው፣ መስቀል ተሠላጢን ይዘው ከየመንደራቸው ተነሥተው ጒዞ ጀመሩ። ዱር ገደል ወንዝ ምድረበዳ አቋርጠው፣ ድንገት ተገናኙ። በመስቀል ወይስ በሠላጢን ይሳለሙ? በሠላጢን እንጂ ካሉ፣ ሰላም ላያተርፉ፣ ሊጎዳዱ፤ ሁለቱም የጅብ ቀለብ ሊሆኑ ነው። እኔ ልጎዳ ቢሉ፣ መስቀል ቢያስቀድሙ፣ ያኔ ብቻ ሰላምና ተስፋ ነው!

Painting by Tissot, c.1886--1904