ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው - 1

በመጋቢ ገ/እግዚአብሄር ካሕሳይ

“ደቀ መዝሙር” ማለት ተማሪ ወይም ተከታይ ማለት ነው። ደቀ መዝሙር የሚማረው ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ያወቀውን በተግባር ለማዋል ነው። በየዘመኑ ይኖሩ የነበሩ ታላላቅ አስተማሪዎች ደቀ መዛሙርት ነበሩዋቸው። ለምሳሌ፦ ኢያሱ የሙሴ ደቀ መዝሙር ነበረ። የግሪኰች ፈላስፋ ፕሌቶ የሶክራጥስ፤ አሪስቶትል ደግሞ የፕሌቶ ደቀ መዛሙርት እንደ ነበሩ ከታሪክ እንረዳለን።

  • ደቀ መዛሙርት ማፍራት የጌታ የኢየሱስ ትዕዛዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
  • ደቀ መዛሙርት ለማፍራት የጌታ ደቀ መዛሙርት ልንሆን ያስፈልጋል።
  • ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ወደ አሕዛብ ሁሉ መሄድ ያስፈልጋል።
  • ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ያመኑትን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅ ያስፈልጋል።
  • ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ጌታ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቁ ያመኑትን ማስተማር ያስፈልጋል።

ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ስንሰማራ ጌታ ሁልጊዜ በመጀመሪያ ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ደግሞ መጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት እንደ ነበሩትና ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ የጌታ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆኑ ከአዲስ ኪዳን ጽሑፎች እንገነዘባለን። (ዮሐንስ 1፡35-40)

ኢየሱስ ዓለም አቀፍ የሆነውን የማዳን ዓላማውን ለማዳረስ ሕዝቡን ከማስተማር ሌላ አስራ አንድ ደቀ መዛሙርት አሠልጥኗል። አስራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና ረድኤት የወንጌል መልእክት ዛሬ የደረሰበት ሁኔታ ላይ አድረሰዋል።

ወንጌልን ወደ ዓለም ሁሉ የማድረስ ተግባር ዛሬም ገና አላበቃም፤ ወንጌል ያልሰሙ፣ ሰምተውም ያልገባቸው፣ ገብቷቸው ተገቢ ምላሽ ያልሰጡ ገና ብዙ ሰዎች አሉ። ወንጌልን ወደ ዓለም ሁሉ ለማድረስ ዋነኛ መንገድ በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና ረድኤት ደቀ መዛሙርት ማፍራት ነው። ጌታ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28 ከቁጥር 16-20 ከሰጠው ትዕዛዝ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት የሚረዱንን ስድስት ነጥቦች እንመለከታለን። ከእኛ ጋር መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። እስቲ እነዚህን ነጥቦች በዝርዝር እንመልከታቸው፤

1.     ደቀ መዛሙርት ማፍራት የጌታ ትዕዛዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። “አስራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” (ማቴዎስ 28፡ 16-28)። ጌታ ይህን ቃል ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው የኃጢአታችንን ዕዳ ለመክፈል በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በኋላ ወደ አብ ከማረጉ በፊት ነበር። ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በክብሩና በታላቅነቱ ታያቸው፤ እነርሱም በአክብሮት፣ በአድናቆት፣ በአምልኰ፦ አምላካችን፣ ጌታችን አንተ ታላቅ ነህ፣ አንተ ኃያል ነህ፣ ሁሉን ቻይ ነህ ብለው ሰገዱለት። እርሱም ስግደታቸውንና አምልኰአቸውን ተቀበለ። “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” ብሎ ደቀ መዛሙርት እንዲያፈሩ ትዕዛዝ ሰጣቸው። ጌታ የሰጣቸው ምክር ሳይሆን ትዕዛዝ ነው። ደቀ መዛሙርት ማፍራት ትዕዛዝ ነው። ትዕዛዙ የድርጅት ወይም የቤተ ክርስቲያን ወይም የሃይማኖት መሪዎች ትዕዛዝ አይደለም። የምድራዊ ባለሥልጣንም ትዕዛዝ አይደለም። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር የእርሱ የሆነ የጌታ ኢየሱስ ትዕዛዝ ነው።

የምድራዊ ባለሥልጣንን ትዕዛዝ የምናከብር ከሆነ፣ ሥልጣን ሁሉ በምድርና በሰማይ የእርሱ የሆነውን የጌታ ኢየሱስን ትዕዛዝ እንዴት ማክበር አይገባንም? የማናከብርበትስ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? “ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለው ትዕዛዝ ያኔ የተሰጠው ለአስራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ነበር። ዛሬ ይህ ትዕዛዝ ለእኛ መሆኑን እናውቃለን? አውቀንስ እየታዘዝን ነው ወይ?

2.     ደቀ መዛሙርት ለማፍራት የጌታ ደቀ መዛሙርት መሆን ያስፈልጋል። ለአስራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ቀረበና እንዲህ ተናገራቸው፦ “ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴዎስ 28፡ 16-18)። ጌታ “ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሎ ያዘዘው ይከተሉት ለነበሩ ለብዙ ሕዝብ አይደለም። ይህንን ትዕዛዝ የሰጠው ለአስራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ነው። እነዚህን አስቀድሞ ጠራቸው፣ ጸልዮም መረጣቸው፤ ጊዜ ወስዶ አስተማራቸውና አሰለጠናቸው። የጌታ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እኛ ራሳችን በእውነት የጌታ ደቀ መዛሙርት መሆን ያስፈልገናል።

በዚህ ዘመን የሚያሳዝነው ግን የጌታ ደቀ መዛሙርት ሳንሆን ለተለያዩ ግለሰቦች ደቀ መዛሙርት መሆናችን ነው። በእውነት የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ብንሆንማ እርስ በርሳችን ጌታ እንደ ወደደን በተዋደድን ነበር። በተለያዩ ሰዎች ስም እንደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ባልተከፋፈልን ነበር (1ኛ ቆሮንቶስ 1፡ 11-13፤ 3፡ 3-4)። በዘመናችን ብዙ የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሲያፈሩ ማየት ያልተቻለበት ምክንያት ብዙዎቻችን ራሳችን በእውነት የጌታ ደቀ መዛሙርት ባለ መሆናችን ሊሆን ይችላል። ብዙዎቻችን ያለጥርጥር አማኞች ልንሆን እንችላለን፤ ክርስቲያኖችም ልንሆን እንችላለን፤ ግን በእውነት የጌታ ደቀ መዛሙርት ነን ወይ?

ዓለማችን “ክርስቲያኖች ነን” “የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ነን” በምንል ሰዎች ተሞልታለች። የብዙዎቻችን ሥራና ሁኔታ ግን እውነተኛ ደቀ መዛሙርት አለመሆናችንን እያስመሰከረ ነው። ምክንያቱም በመካከላችን መለያየት፣ ጥላቻና ቅንዓት ሞልቶአል። ነገር ግን ዋና ምልክታችን የሆነው ተግባራዊ ፍቅር ጠፍቷል። የጌታ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት በእውነት የጌታ ደቀ መዛሙርት እንሁን። የጌታ ደቀ መዝሙር የሚያፈራ የጌታ ደቀ መዝሙር የሆነ ነው።

3.     ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ወደ አሕዛብ ሁሉ መሄድ ያስፈልጋል። “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ … ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው … “ (ማቴዎስ 28፡ 19-20) ጌታ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ደቀ መዝሙር መሆን ብቻ ሳይሆን ወደ አሕዛብ ሁሉ መሄድ ያስፈልጋል። ሰዎች ወደ እኛ እንዲመጡ መጠበቅ ብቻ በቂ አይደለም። የጌታ ደቀ መዛሙርት ወደ አልሆኑ ሰዎች መሄድ ያስፈልጋል። ትዕዛዙ “ሂዱ” ነው። ጌታ ሰዎች ወዳሉበት ሄዶ “ወደ እኔ ኑ” ካለ በኋላ ወደ እርሱ የመጡትን አስተማራቸው፣ አሰለጠናቸው፣ ወደ ሌሎች “ሂዱ” አላቸው። ሰዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን “ኑ” ማለት መጥፎ ባይሆንም ዋናው ትዕዛዝ ግን “ሂዱ” መሆኑን እንገንዘብ።

“መሄድ” ሲባል የግድ ሩቅ አገር መሆን የለበትም። ቁም ነገሩ ታዝዞ መሄዱ ላይ ነው። ወደ ጐረቤቶቻችን ሊሆን ይችላል፤ ወደ ሠፈራችን ሊሆን ይችላል። ጌታ ካዘዘ ደግሞ ወደ ሩቅም ሊሆን ይችላል። ሩቅ የሚሄደውም ቅርብ የሚሄደውም ለጌታ ፈቃድ ታዝዞ እስከ ሄደ ድረስ መልካም ይሆናል። ሩቅ የሄደው ቅርብ ከሄደው አይበልጥም። አንዳንዶቻችን ወደ ሩቅ አገር የወንጌል አገልግሎት አለ ስንባል የምንሄድ፣ ነገር ግን ወደ ሠፈራችን እሑድ ከሰዓት በኋላ ወንጌል ለመስበክ እንሂድ ሲባል ለመሄድ የማንፈቅድ አለን። በሩቅም በቅርብም ያሉ ሰዎች ናቸው። ሁሉም ወንጌል ያስፈልጋቸዋል። ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ነው። ያለ አንዳች አድልዎ ልንሰብክና ሰዎችን የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ልናደርግ ይገባናል። ሁላችን የጌታ ደቀ መዛሙርት የሆንነው ወደ አሕዛብም ሁሉ የምንሄደው በመጀመሪያ ስለ ሁሉ በመጸለይ ነው። ወደ አሕዛብ ሁሉ የሚሄዱትን በጸሎትና በመስጠት በመደገፍ እንሄዳለን። ጌታ በከፈተልን በር ደግሞ ራሳችን በመሄድ እንሳተፋለን። ስለዚህ በጸሎት፣ በመስጠትና በመሄድ ሁላችንም ማገልገል ይኖርብናል።

ዛሬ በዓለም ያለነው ሦስት ቢሊዮን የምንሆን ክርስቲያኖች በእውነት የጌታ ደቀ መዛሙርት ብንሆን፣ እያንዳንዳችን በዓመት ለአንድ ሰው ብንመሰክርና የጌታ ደቀ መዝሙር ብናደርጋቸው የዓለምን ሕዝብ ሁሉ በወንጌል ለመድረስ የሚፈጀው ከሦስት ዓመት አይበልጥም ነበር። እንግዲህ አለመታዘዛችንና ስንፍናችን ምን ያህል እንደ ሆነ እንመልከት። በዓመት አንድ ሰው ደቀ መዝሙር ማድረግ ነው ያቃተን። ምናልባት ራሳችን እውነተኛ የጌታ ደቀ መዛሙርት መሆን ነው የተሳነን። ጌታ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ያድርገን። 

የውይይት ጥያቄዎች

1. የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ፣ ደቀ መዝሙርነት በመጀመሪያ ለጌታ መታዘዝን ቀጥሎም እርስ በርስ መታዘዝን ይጠይቃል፣ ይላል። ራሳችን ለጌታ ሳንታዘዝ ሌሎች እንዲታዘዙን እየጠበቅን ይሆን?

2. ደቀ መዝሙርነት ዋጋ የሚያስከፍል ሕይወት ነው። ዋጋውን ተምነን እናውቃለን? ለመክፈል ፈቃደኞች ነን?

3. ድብቅ አኗኗርና የጐደለ የሕይወት ምስክርነት ደቀ መዝሙር ለመሆን ሆነ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት አያስችለንም። ለሚያዩን ፈለግ የሚሆን ሕይወት አልተገኘብን ይሆን?

4. እነ ጴጥሮስ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። ራሳችንን ከነርሱ ተራ ለመመደብ ምን መብት አለን?

5. የሰው ቁጥር በየቤተ ክርስቲያኑ መብዛት ስለ ደቀ መዝሙርነት ምን ያስረዳናል? የዮሐንስ ወንጌል 6፡66 ይመልከቱ። 

6. ሌሎች ጌታን ታዝዘው የምሥራቹን ወንጌል እንዳመጡልን ማስታወስ ለምን ይጠቅማል?

7. እውነተኞች ደቀ መዛሙርት ለመሆን አኗኗራችንን እንዴት ልናስተካክል ይገባል? 

ክፍል 2 ይቀጥላል