ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ!

ስሜ ወንጌላዊ ዳንኤል አፎጫ ይባላል። የተወለድኩበትን ቀን በውል ባላውቅም በ1936 ዓ.ም. የሆኑ ክስተቶችን አስታውሳለሁ። በዚሁ ስሌት ዕድሜዬ ቢያንስ ሰባ አምስት እንደሆነ እገምታለሁ። የትውልድ አካባቢዬ በቀድሞው ከንባታና ሃዲያ አውራጃ ሻሸጎ ቢድቃ ቀበሌ ሊጣና ምክትል ወረዳ ተብሎ ይታወቃል።

በ1950 ዓ.ም. ኡርበጫ በሚባልና ከእኛ መንደር አቅራቢያ በሚገኝ ቀበሌ ወንጌላዊ ኬዳሞ ፊደል ማስቆጠር እንደጀመሩ ሰማሁና ከእረኝነት ጠፍቼ ወደዚያው አመራሁ። ከግማሽ ሰዓት የእግር ጉዞ በኋላ እዚያው ደርሼ ተማሪዎቹን ተቀላቀልሁ። የዚህ ትምህርት ዓላማ በቀለም ትምህርት ልጆችን በመሳብ ጎን ለጎን ወንጌልን ወደ ልባቸው ማስረጽ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል?” እንደሚል ሲነገረኝ ልቤ ተነካ። ጌታን የተቀበልኩትም ያኔ ነው። ከዚያ በኋላ ቤተሰቦቼ በሙሉ አገለሉኝ። አጎቴ ግን ጌታን ተቀብሎ ስለነበረ ምርጫዬ እርሱን መጠጋት ብቻ ነበር። እርሱም ለመጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዱራሜ በማምራቱ ተከትዬው ሄድኩ። እስከ 1953 ዓ.ም. ድረስ ዱራሜ በነበረው የሚሲዮን ጣቢያ ውስጥ የቀለም ትምህርቴን ስከታተል ቆየሁ። አጎቴ ከሁለት ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ቆይታው በኋላ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ቤቱ ሲመለስ እኔ ግን ወደ ሆሳዕና አመራሁ። በ1955 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ የቀድሞው ራስ አባተ የዛሬው የካቲት ትምህርት ቤት ውስጥ የአራተኛና የአምስተኛ ክፍል ትምህርቴን በአንድ ዓመት አጠናቀቅኩ። የትምህርት አቀባበሌ ጥሩ ስለነበር ወደ መምህራን በመጠጋት የአራት መምህራን ልብስ ወደ ባቴና ወንዝ ወስጄ ዘወትር ቅዳሜ ቀኑን ሙሉ እያጠብኩ በመዋል ተኩሼና አጣጥፌ አስረክባቸው ነበር። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሆሳዕና ከርሜ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ወደ ሁርበጫ በመሄድ በኬዳሞ ምትክ ፊደል እያስቆጠርኩ ቆይቼ ወደ ሆሳዕና እመለስ ነበር።

በ1957 ዓ.ም. ወንጌላዊ ኬዳሞ ወደ ሲዳማ ሲያመሩ እኔ በሙሉ ጊዜ አስተማሪነት በእርሳቸው ምትክ ተቀጠርኩ። ያኔ ደመወዜ ሰባት ብር ነበር። ከዚያ ላይ ሰባ ሳንቲም የጌታ አሥራት እዚያው ተቆርጦ ስድስት ብር ከሠላሳ ሳንቲም በእጅ ይደርሰኝ ነበር። በ1960 ዓ.ም. በወንጌል አስተማሪነት ወደ ሻሸጎ ተላኩኝ። ይሁንና ያኔ ትዳር ያልመሠረተ ለወንጌላዊነት ስለማይታጭ በአሥራዘጠኝ ብር ደመወዜ [ጭማሪ አግኝቼ ነበርና] የጥሎሽና የልብስ ጣጣ ጨርሼ የዛሬዋን ባለቤቴን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቀለልኳት። የሠርግ ስነ ስርዓቱ የተፈጸመው ህዳር 27/1960 ዓ.ም. ነበር።

ከ1961 እስከ 1962 ዓ.ም. በአርባ ብር ደመወዝ ወደ ቦቢቾ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተልኬ ትምህርቴን ቀጠልኩ። ሐምሌ 1961 ዓ.ም. እዚያው ትምህርት ቤት ሳለሁ የመጀመሪያ ልጄ ተወለደ። ከ1962 እስከ 1966 ዓ.ም. ያሳለፍኩት በማረቆ ቤተክርስቲያን እያገለገልኩ ነበር።

ከዚህ በኋላ ቤተክርስቲያን ወንጌል ከልማት ጋር ተቀናጅቶ እንዲሠራ አዲስ ስልት በመንደፏ በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ላኪነት ወደ ጅማ አምርቼ ለሦስት ወራት ከተማርኩ በኋላ የቤተክርስቲያን የልማት ሠራተኛ ሆኜ ተመደብኩ። ከአሥር ዓመታት በኋላ ቤተክርስቲያን ይህንን የልማት ፕሮጀክት ለወርልድ ቪዥን በማስረከቧ እኔና አንድ ወንድም አብረን ወደዚያው ተዛወርን። ሸንቆላ በተባለ ስፍራ ላይ አሥር ዓመታት በልማት ሥራ ከወርልድ ቪዥን ጋር ስሠራ ቆየሁ። ከቤተክርስቲያንና ከዚህ ድርጅት ጋር በልማት ዘርፍ ላይ ያገለገልኩባቸው ሃያ ዓመታት ከወንጌል አገልግሎት ስላራቁኝ ውስጤ እጅግ ያዝን ነበር። በወርልድ ቪዥን ውስጥ በነበረን የህብረት ጸሎት ላይ የየግል ጥያቄዎቻችንን ስንነጋገር የእኔ የጸሎት ርዕስ በአላባ፣ በስልጤና በሳንኩራ አካባቢዎች በወንጌል ያልተደረሱ ወገኖችን አገለግል ዘንድ ጌታ እንዲረዳኝ ነበር።

በ1989 ዓ.ም. ወርልድ ቪዥን የልማት ሠራተኞችን ከሥራ ሲቀንስ በፌስታል አንዲት ጋቢ ብቻ ይዤ በመውጣት በሸኖ፣ ቆንቻ፣ አላጌ እና ሚቶ ለአራት ዓመታት በእግሬ እየዞርኩ አገለገልኩ። ቤተሰቤ ከእርሻችን እየተደጎመ እኔ ደግሞ በደረስኩበት ሁሉ በቅዱሳን እርዳታና በኪሴ በነበረ ገንዘብ ማገልገል ቀጠልኩ። ምንም እንኳን ቤተክርስቲያን ባትቀጥረኝም የሻሸጎን ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ጸልዩ እያልኩኝ ወጥቼ፣ አመስግኑ ብዬ እየገባሁ፣ የአገልግሎቴን ሪፖርት አቀርብላቸው ነበር። ከአራት ዓመታት በኋላ በተሰጠኝ የስብከት መድረክ ላይ ያካፈልኩት “ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ” የሚለውን ቃል ነበር።

በ1992 ዓ.ም. እኔን ጨምሮ ሁለት ወንጌላውያንን ቤተክርስቲያን በሁለት መቶ ብር ደመወዝ ቀጠረችን። ከስድስት ዓመታት በኋላ ይኸው ቅጥር ተቋረጠና ክፍያውም ቀረ። የእንሠት ማሳዬን በጥቅምት ኮትኩቼ የእርሻ መሬቴን ደግሞ የእኩል ለሚያርስ ሰው በመስጠት ለአገልግሎት እወጣ ነበር። በዚህ መልኩ እስከዚች ዕለት በማገልገል ላይ እገኛለሁ። ይህ ለእኔ የደስታዬ ከፍታ ነው። በእርግጥ ይህ አገልግሎት አልጋ በአልጋ አይደለም። በጉዞው ወቅት ዛቻ፣ ማስፈራራት፣ ዳገት ቁልቁለት፣ ረሃብ ጥም ወዘተ፣ የለመድኩት ነገር ነው።

በዚህ አገልግሎት ጌታ በርካታ ተኣምራትንም አሳይቶኛል። የምጓጓዝባትን ብስክሌት እንዲሠርቅ የተቀጠረ አንድ ወጣት ብስክሌቷን ይዞ እንዲመለስ ሲጠበቅ እርሱ ግን ጌታን አግኝቶ ለዘላለሙ ድኖ ቀርቷል። ዛሬ የዚህ ወጣት ቤተሰብ በአጋንንት የተያዙ ሳይቀሩ በመፈታት ላይ ይገኛሉ። ይህ ወጣት ጌታን ተቀብሎ ፍጹም ሌላ ሰው በመሆኑ “ያበላሸኸው አንተ ነህ” ተብዬ ለሃያ አራት ሰዓታት ተከብቤ ከቆየሁ በኋላ የአካባቢው ማህብረሰብ ምን እናድርገው ብሎ ሲማከር ቆይቶ አንድ ሃሳብ ላይ ለመድረስ ባለመቻሉ ደም አታምጡብን የሚሉ ወገኖች ከመካከላቸው ተነስተው እርስ በርስ ሲጋጩ እኔን ጌታ አስመልጦኛል።

በብስክሌት እየተዘዋወርኩ ማገልገል የጀመርኩት ከዓመታት በኋላ ነበር። በመጀመሪያ ብስክሌት እንገዛልሃለን በማለት ጌታ ያነሳሳቸው ወንድሞች ሲያበረታቱኝ፣ እኔ “ብስኪሌት መንዳት አልችልም” ነበር ያልኳቸው። እንዲያውም አንዲት እህት እንዴት መክራኝ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። ግለሰቦች ብስክሌት ከገዙልኝ በኋላ ሰው ወደማያየኝ ሩቅ ጫካ ወስደው መንዳት አለማመዱኝ። ከዚህ በኋላ ነበር በአደባባይ ለመንዳት የደፈርኩት።

በአንዲት ወቅት “አብሲኒያ ሚሽኔሪ” የሚባል አገልግሎት ለወንጌላውያን ስልጠና ሊሰጥ ፈልጎ እኔን እንዲያሠለጥኑ ለሻሸጎ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን፣ ወንድም ደገፋ ሶደሮ ስሜን ይጠቁማቸዋል። ለአንድ ወንጌላዊ ስልጠና ስምንት መቶ ብር ያስፈልግ ስለነበር ቤተክርስቲያን አንድ ወንጌላዊ ብቻ ላከች። ወንድም ደገፋ ከኪሱ አራት መቶ ብር ከፍሎ ሲጠራኝ እኔ ደግሞ ሰባት መቶ ብር የገዛሁትን ብስክሌት አምስት መቶ ብር ሽጬ ለስልጠና ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። የሚገርመው ያቺን የሸጥኳትን ብስክሌት እያሰላሰልኩ በቁጭት ወደ ኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ዋና ጽሕፈት ቤት አመራሁ። ለዶ/ር ተስፋዬ ያዕቆብና ለአቶ ኩርሲ ሸፈኖ ስለ አገልግሎት ሳጫውት ልባቸው ተነክቶ ኖሮ አዲስ ብስክሌት ከመጋዘን ወጪ ሆኖ እንዲሰጠኝ ታዘዘልኝ። የጌታ በረከት በዚህ ብቻ አላበቃም። ወደ ክፍለ ሃገር ተመልሼ አላባ ከተማ ላይ አንድ ካፌ ተቀምጬ ሳለ አንድ ወንድም መጣና አገኘኝ። የቤተሰቤንና የአገልግሎቴን ሁኔታ ከጠየቀኝ በኋላ ከሻሸመኔ ከተማ አላባ እስክደርስ “10 ማውንቴን” ብስክሌት የያዙ ሰዎች የኔን የቻይና ብስክሌት እየቀደሙኝ ማለፋቸውን በቁጭት ነገርኩት፤ እርሱም የአፌ ቃል እንዳለቀ አንድ ሺ ሦስት መቶ ብር ከኪሱ አውጥቶ ብስክሌት ግዙ ብሎ ሰጠኝ። ዛሬ በዚህ ብስክሌት አገለግላለሁ።

ምንጭ፦ ኤፍታህ መጽሔት፣ 2003 - ቁጥር 8፣ ገጽ 20-21 “የአዛውንቱ ብስክሌተኛ አስደናቂ ገድል” በሚል ርዕስ ካተመው የተወሰደ። [ጽሑፉ በመጠኑ ታርሞ አጥሮአል]

ከታች በተመለከቱት ነጥቦች ላይ እናሰላስል፦

  1. ወንጌላዊ ዳንኤል ለትምህርትና ለሥልጠና የሰጡት ከፍተኛ ሥፍራ
  2. የወንጌላዊው እምነት ትጋትና ታማኝነት
  3. በጥሪአቸው ሥፍራ ላይ ለመቆም እየከፈሉ ያሉት መስዋእትነት
  4. ተጠሪነታቸው ለቤተክርስቲያን ስለመሆኑ
  5. የጌታ ጸጋና ታማኝነት
  6. ለቤተክርስቲያን ተጠሪ ያልሆኑና የቤተክርስቲያንን አቋም የሚሻሙ አገልጋዮችንና አገልግሎቶችን ማስተናገድ ቢቆም ምን ለውጥ ያስከትል ይሆን?
  7. ለትምህርትና ለሥልጠና ጊዜ የሌላቸው አገልጋዮች የሚያስተምሩትን ትምህርት [በተለይ ከሰበኩ በኋላ] አንድ ባንድ በጉባኤ መመርመር ቢጀመር ምን ውጤት ያስከትል ይሆን? [“መርምሩ” 1ኛ ዮሐንስ 4፡1፤ “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን?” የሐዋርያት ሥራ 16፡11]
  8. ለዓመት ያህል አብያተክርስቲያናት ከውጭ ሰባኪዎችን መጋበዝ ቢያቆሙ፣ ስንቶች በአገልግሎት ላይ ይሰነብቱ ይሆን? የስንቶቹስ ስብከት ይዘት ይለወጥ ይሆን?
  9. የቤተክርስቲያን የበጀትና የወጪ አቅጣጫ ቢመረመር ስለ አመራሩ ምን ያስረዳን ይሆን?