አልጋነሽ ወልዳ

አልጋነሽ ወልዳ ጋንዲ የተኛች ሰሞን የዘመድ ያህል ሦስቴ ተመላልሰው ጠይቀዋታል። ሦስቱንም ጊዜ ባዶ እጃቸውን አልሄዱም፤ ምን የመሰለ አጥሚት የጃንሆይ ቅልብ በመሰለ ፔርሙዝ እያንገደገዳቸው ወስደዋል። አጥሚቱን ሌላው ጠያቂ "እንዴት ግሩም ነው" እያለ ይፈራረቅበታል። የርሷን እንጃ እንጂ እርሳቸውስ በጣም ይወዷታል። ጥየቃዋን በመጡ ቁጥር ታዲያ መግቢያው አጠገብ ከቀጨሞው ጀርባ የቆሙትን ዘበኛ፣ ነጠላቸውን ከራሳቸው ላይ ገለጥ አርገው ሳይሳለሙ አይገቡም። አንዱን ቀን ረፍዶባቸው ምሽት ላይ ደረሱ። ከቀጨሞው ወዲህ ቆመው፣ "እባክዎ በማርያም ይሁንብዎ፣ እዚህ ደርሼ አይመልሱኝም መቸም፤ መንገድ ተቆፍሮ ታክሲ መንደር ለመንደር ሲያንከራትተን ነው የዘገየሁት" አሉ። ከቀጨሞው እልፍ ብለው ሲጠጉ፤ የቆሙት ጋንዲ ናቸው፤ በወላቃ መነጽራቸው አጮልቀው እያዩዋቸው፣ በወላቃ ጥርሳቸው ፈገግ ብለውባቸው።  አበስገበርኩ!

 

© ምትኩ አዲሱ / 2007