ስለ አንድ ጫማ ሰፊ

cobbler1አንድ ጫማ ሰፊ ከጧት እስከ ማታ በእጁ ጫማ ሲሰፋ፤ ባፉ ሲዘፍን ይውል ነበር። በጐረቤቱም አንድ ባለጠጋ ነበረና አንድ ቀን ወደ እርሱ መጥቶ፣ ወዳጄ ሆይ፣ እንዲህ ሌት ቀን ስትደክም ባመት ምን ያህል ታተርፋለህ አለው። ጫማ ሰፊውም እየሳቀ መለሰ፣ ጌታ ሆይ፣ እኔ ያመት ትርፍን አላስብም። ነገር ግን አሳቤ ሁሉ እጄ ወደ አፌ የሚያቀርበው የዕለት ምግብ ብቻ እንዳልቸገር ነው አለው። ባንድ ቀን ምን ያህል ታተርፋለህ አለው። ጌታዬ ሆይ፣ አንድ ቀን ብዙ አንድ ቀን ጥቂት እሠራለሁ። ትርፉ በምን ይታወቃል አለው።

ባለጠጋውም እንግዲህ ወዲህ እኔ ያለችግር አኖርሃለሁና ከኔ ዘንድ መቶ ምዝምዝ ወርቅ ውሰድና በጥንቃቄ ጠብቀህ አኑር። በቸገረህም ጊዜ የሚበቃህን ያህል እንጂ በከንቱ አታባክን ብሎ ሰጠው። እርሱም ይህን ያህል ገንዘብ ባይኑ ስንኳ አይቶ አያውቅም ነበረና ደስ እያለው ተቀብሎ ወደ ቤት ሔደ። ነገር ግን ይጠፋብኛል ብሎ ሲጨነቅ ሌሊቱን ሁሉ ካይኑ እንቅልፍ ሸሸ። በሌሊትም የሰው ድምጽ በሰማ ጊዜ ገንዘቡን የሚቀማ ወምበዴ የመጣ ይመስለዋል። ነፋስም ቤቱን ባነቃነቀው ጊዜ ገንዘቡን የሚሰርቅ ሌባ የመጣ እየመሰለው ይጨነቅ ጀመረ። እንዲህ እየሆነ ብዙ ቀን ተቀመጠ። ነገር ግን ልቡ የዚህን አሳብ የማይችለው ሆነ። ከእለታት አንድ ቀን እንዲህ ሲጨነቅ አደረና በማግሥቱ በማለዳ ተነሥቶ ወደዚያ ባለጠጋ ቤት እየሮጠ ሔዶ፣ ለኔስ የቀድሞ ኑሮዬ እጅግ ይሻለኛል። አሁንም ይህን የሰጠኸኝን መቶ ምዝምዝ ወርቅ ተቀበለኝ። ቀን ስሠራ እየዋልሁ ሌሊት እንቅልፍ ቢወስደኝ ለኔ እጅግ መልካም ነው ብሎ በትኖለት ሔደ።

ወዳጄ ልቤና ሌሎችም፣ ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ አ.አ.ዩ ፕሬስ፣ 2000 ዓ.ም. ገጽ 110-111 / photo credit: postcardman.net