truck

በ ብ ብ ት  የ ገ ባ

ከሃራምባ ወደ ቆቦ ዚታዎ

ሲያንከባልል ውሎ

ቀትር ላይ በጣም ወበቀው

ከላቦት የተሠራ ገንቦ እስኪመስል

ላብ አጠመቀው

እንዲነፍስበት የጋቢናውን

መስኮት ትንሽ ከፈት

አርጎ ተወ

ረባዳውን ተሻግሮ ጋራውን

ሲያያዝ ብርድ ብርድ

አለው አስነጠሰው!

ሁለቴ አከታትሎ

አስነጠሰው!!

እጁን መሪው ላይ እያፈራረቀ

ከለበሰው ጃኬት ሥር

ለመደረብ ቀስ ብሎ ጃኬቱን

አወለቀና ተንጠራርቶ በዳበሳ

ከጋቢናው አልጋ ላይ

የፈታት ሚስቱ የሠራችለትን

ባለ ሽንትር ሹራብ አወረደ

ሹራቢቱን አውርዶ

ዐይኑን ከመንገዱ ላይ

ሳይነቅል መጀመሪያ ግራ እጁን

አስገባ ቀጥሎ መሪውን በግራ እጁ ይዞ

ቀኝ እጁን አስገባ

አሁን የቀረው ጭንቅላቱን

በአንገትጌው ማውጣት ነው

አንገትጌው በየት ይገኝ?

ስቅ

ስቅ

ላት

እንደ ተፈረደበት ሰው

የፈታት ሚስቱ የሠራችለትን

የሚወዳትን ሽንትር ሹራብ

ተከናንቦ ትንፋሽ

እያጠረው

ታገለ

ዚታዎ፣

ከ-መ-ን-ገ-ድ-ል-ወ-ጣ-

እ-ኰ-ነ-ው

እያለ የድረስልኝ ያጓራል

ኋላ መጥተው ሲያዩት

ቀኝ እጁን ያስገባው

በግራ ብብቱ ቀዳዳ

ሆኖ ተገኘ …

© ምትኩ አዲሱ፣ ከ "ኩኩሉ በምሽት" | ገጽ 42፣ 2010 ዓ.ም.