rainbow

አ ገ ር   እ ና   እ ው ነ ት

ፍቅር ሲጠራ ከሩቅ፥
ሰው እና ሰው እንዳይተላለቅ፥
በአንድ ባንዲራ - በአንድ ሰንደቅ፥
ሁሉም ክብሩን ነጻነቱን እንዲያውቅ።
ምክር - ፖለቲካ፥ ትግል - እስከ ሥር ነቀል ጦርነት፥
በከንቱ አይደለም ይሔ - የእውነት እና የውሸት ትንንቅ።
ሰው ቢያልቅም፥ ሰልፉ ይቀጥላል፤
እውነት እስኪያሸንፍ፥
ውሸት ድቅቅ እስኪል።
ስለዚህ በመሰለህ ግባበት፥
አማራ ነኝ ትግሬ፥ ኦሮሞ ነኝ ሲዳማ ሳትል፤
ኢትዮጵያችን እውነት ከሆነች አድናት፤
ውሸት ከሆነችም ገድለህ ቅበራት።
ሁለት ልብ ያላቸው - ተጠራጣሪ ቢያደርጉህ፥
በአንድ ልብ ውሸት፥
በሌላም ልብ እውነት ይዘው፤
መስሏቸውም ይሆናል - ሁለት ነፍስ ያላቸው፤
እኛ ግን ያለን አንድ ናት ነፍሳችን፥
አንድ እርሷ ብቻ ናት አገራችን፤
በእውነት ለኛ አንድ ናት - ለኛ እውነት ለሆነችልን፤
ስለዚህ እናድናት ለእውነት ብለን።
ዝም ቢልም - ዝም ማለት ለማይችል፥
አንድ ናት አገሬ ለሚል፥
ቀና ብሎ ለሚያስተውል፥
ያውና አርማው - ሰማይ ላይ ይውለበለባል፤
ቀስተ ደመና ነው፤ ሌላም አይደል።
ቀኑም ቢጨለም - እጅግ ቢበዛ ስቃይ፥
መጪውን ጊዜ ለሚያስተውል - ተስፋችን ተዘርግቷል ከሰማይ።

© መዝ ኃይሌ 2014 ዓ.ም. | 2021 Mez Haile