Download Geez Unicode Font if unable to read Amharic text
የመንፈሳዊ ጤንነት ፍተሻ
በተስፋዬ ታደሰ
በሰለጠነው ዓለም ሰዎች ጤናማ መሆን ያለመሆናቸውን ለማወቅ በዓመት አንዴ ወይንም ሁለቴ የአካላቸውን ጤንነት በሐኪም ያስፈትሻሉ፤ የሚበረታታ ጥሩ ልምድ ነው። ለጊዜው ምልክትና ስሜት የሌላቸው ደዌዎች አቆጥቁጠው ቢሆን እንኳ ሥር ሳይሰዱ ከወዲሁ ለመቅጨት ይጠቅማል። ወደ አገራችን መለስ ስንል ደግሞ ጤናማ መሆን ያለመሆኑን ለማወቅ የጤንነት ፍተሻ የሚደረገው ግድ በሚል አጋጣሚ ነው። መኪና ለማሽከርከር የሚያስችል ፈቃድ ለማግኘት፣ በኰርሶች ለመሳተፍና ሥራ ለማግኘት፣ ወደ ባሕር ማዶ ለመሄድ ካልሆነ በስተቀር የጤንነት ፍተሻ በፍጹም አይታሰብም። ሌላው ቀርቶ የሕመም ስሜቶችና አካላዊ ለውጦች ችላ ስለሚባሉ በቀላሉ ሊወገድ በሚችሉ በሽታዎች ሕይወታቸውን የሚያጡ አያሌዎች ናቸው።
ምን ጊዜም ቢሆን ጤንነትን የመሰለ ሃብት የለም። ስለ ጤንነታችን እግዚአብሔርን ማመስገን፣ ጤንነትንም መጠበቅ፣ ጤንነታችንን የሚገዳደሩ ነገሮችን መቆጣጠርና ማራቅ ብልኅነት ነው። “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” ተብሎስ የለ? በእርግጥ ከጥንቃቄ የሚያልፍ ሕመም ሊከሰት ይችላል። ደግሞም በመታከም የሚዳን ወይም የማይዳን ቢሆን ሁሉን ለሚችል አምላክ ነግሮ ማረፍና ተመስገን ማለት ጤንነት ብቻ ሳይሆን በረከትም ነው።
የሥጋዊ አካላችን ጤንነት መፈተሽ እንዳለበት ሁሉ የመንፈሳዊ አካላችን ጤንነትም ፍተሻ ያስፈልገዋል። በየጊዜው ፍተሻ ካልተደረገለትና እንክብካቤ ካጣ ይታመምና ከሥጋዊ አካላችን ይልቅ ለበለጠ አደጋ ይጋለጣል። እንዲያውም ሕመሙ ሥጋዊ አካላችንን እስከ ማጥቃት ይደርሳል። ደግሞም ግለ ሰብን አቁስሎና ገድሎ የሚቆም አይደለም። ቤተ ሰብን አልፎም ማኅበረ ምዕመንን የሚጐዳ ይሆናል።
የመንፈሳዊ ጤንነት መታወክ ምክንያቶች ጥቂቶች ባይሆኑም አንዳንዶቹ በዋዛ የሚታለፉ አይደሉም። በተለይማ ፈጣኖቹና ተላላፊዎቹ በማር የተለወሰ መርዝ የሚባለውን ዓይነት መልክ የያዙ እጅግ መርዛሞች ናቸው። እንደ እነዚህ ያሉቱ ከጥንቃቄ ጉድለት ሊከሰቱ የሚችሉ ይሆናሉ፣ ወይንም ብስለት ከማጣት።
ከጥንቃቄ ጉድለት በሚባለው ምክንያት ለአጥቢያ ማኅበረ ምዕመን አገልጋዮች መቅረብ የሚገባው ጥያቄ አለ። ለስብከት፣ ለትምህርት፣ ለዝማሬና ለልዩ ልዩ ሥልጠናዎች መድረካችንን የምንፈቅድላቸው አገልጋዮችን ጤንነት ለማወቅ እንተጋለን? ወይስ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ይወቅ ብለን ኃላፊነታችንን ዘንግተን ይሆን? የውስጡን ገልጦ የሚያውቅ እግዚአብሔር መሆኑ እውነት ነው። ሆኖም ለአገልግሎት ስንጋብዝ የእውነተኛ አገልጋይነት ድርሻችንን መወጣት ግዴታችን ይሁን። ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት ማራመዳቸውንና ጤናማነታቸውን ኅብረት ካደረጉበት አጥቢያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በማጥናት ለመንጋው ጤንነት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።
ሌላው የመርዙ ቫይረስ ተሸካሚዎች ገዳይ መርዛቸውን የሚነሰንሱበት ምቹ ቦታዎችን ነቅቶ መጠበቅ ተገቢ ነው። የተለያዩ ሕብረቶችን ቤተ ክርስቲያን በበላይ መጠበቅ ብትችል መልካም ነው። በነጻነት ስም ኑፋቄና አጋንንታዊ ትምህርቶች የክርስትናን ካባ እየለበሱ የምዕመኑን ጤንነት በመርዛቸው እንዳይበክሉ ጥንቃቄ የሚደረግባቸውን አካባቢዎች ለማስታወስ ብዬ ነው (ዮሐንስ 21፡ 15-17)።
በመሠረቱ በክርስትና ስም የሚደረጉ ሆኖም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጣጣሙ ትምህርቶችን በግልጽ የምናይበት ዘመን ላይ እንዳለን ማወቅ አለብን። እንደዚህ በመሳሰሉ በሽታዎች ተለክፈው ዓይኖቻቸውን የተያዙ የበሽታቸውንም ምልክት ያስተዋልንባቸው ጥቂቶች አይደሉም። ነገር ግን ልንገነዘበው የሚገባ ዋነኛው ነገር ቢኖር መንፈሳዊ የጤንነት ፍተሻ አድርጐ ሕመሙን መለየት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ነው። ዓላማችን መሆን ያለበት ከስህተት ተመልሰው በእግዚአብሔር ቃል መስዋዕትነት ራሳቸውን አይተው ያጐደሉብንን የአካል ክፍል መሆናቸውን እንደገና ሙሉ እንዲያደርጉት ነውና አበክረን ልንጸልይላቸው ይገባል።
የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለማወክና ተልዕኰዋን በብቃት እንዳትወጣ ሰይጣን በብዙ ዓይነት መንገድ ከመሞከር ቦዝኖ አያውቅም። ጭልጥ ያለውን ስህተት እውነት እያስመሰለና መንፈሳዊነትን እየቀባባ የሰዎችን ልብ ማማለሉ አያስደንቅም። “ሥራውን አንስተውም” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ከላይ የተገለጸው እንቅስቃሴ ስሜትን የሚማርክ በማይፈጸም ተስፋ የሚያነሆልል በመሆኑ አዳዲስ ነገርን ለመቅመስ፣ ለማየትና ለመዳሰስ የሚቻኰለው የኑፋቄ ትምህርት ሰለባ ወጣቱ ሆኗል። እነኚሁ ወጣቶች በትምህርቱ ላይ ምንም እንከን አላገኘንበትም፤ እንዲያውም ሕይወታችን ለመለመበት፣ የወደፊቱ ተስፋችን ብሩህ ሆነልን እያሉ ያልተረዱትን እውነት መሳይ ውሸት ቢያሞካሹትም የትምህርቱን መሠረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያለመሆኑን ያህል የሚፈጠረውን ኪሳራና የመጨረሻውን ግብ አሳዛኝ ፍጻሜ መሆኑን ከአስተምህሮታቸው ስንገነዘብ ልባችን በሐዘን ይደማል። “በሬ ሆይ፣ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ…” የሚለውን ተረት ልብ ይሏል።
እንግዲህ መንፈሳዊውን የጤንነት ፍተሻ አዘውትረን እናድርግ። ለዚህም የምንጠቀምበት መሣሪያችን ዘለዓለማዊ የሆነው የሕያው እግዚአብሔር ቃል ነው። “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፣ ራሳችሁን ፈትኑ” እንደተባለው (2ኛ ቆሮንቶስ 13፡ 5) በነገር ሁሉ ንቁ እንሁን። ከዚህ በታች የተዘረዘሩትም ነጥቦች ለፍተሻው ይረዱናል ብዬ አምናለሁ።
ሀ. የዓይኖቻችን ጤንነት ይፈተሽ
አምሮቱ ለሌሎቹ የአካል ክፍሎች እንቅፋት እንዳይሆን ይጥራ። ዓይን የሃሳብ መግቢያና የሰው ጠባይና ስሜት መግለጫ ስለሆነ ማስተዋል በጐደለው ስሜታዊ እንቅስቃሴ አይማረክ (ዘኁልቁ 15፡ 39፤ ማቴዎስ 5፡ 29፤ ሉቃስ 11፡ 34-36)።
ለ. የጆሮቻችን ጤንነት ይፈተሽ
ሁሉን የሚችለውን የእግዚአብሔርን ድምጽ ከእንግዳ ድምጽ ለመለየት አንቸገር። እንደ ዳዊት “እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ” የሚል ዝግጁነት ይኑረን (መዝሙር 84፡ 8)።
ሐ. የሆዳችን ጤንነት ይፈተሽ
ጌታ ኢየሱስ “በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ፣ የሕይወት ውሃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል” አለ (ዮሐንስ 7፡ 38)። ፈውስ የሚሆነው የሕይወት ውሃ ከሆዳችን እየፈለቀ መሆኑን እንፈትሽ። ቤተ ክርስቲያንን የሚያጐድፍ ነገር የምንናገር ከሆነ የውስጥ መታወክ ገጥሞን ይሆናልና በቶሎ እንታከም።
መ. ጉልበቶቻችን ይፈተሹ
ጉልበቶቻችን ለማን እየደከሙ እንደሆነ ልብ እንበል። ጉልበት ሁሉ ሊንበረከክለት ለሚገባው ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንበርከክ። በእግዚአብሔር የተመረጡ ሰዎች ጉልበታቸውን ሊያስገዙ የሚገባቸው ለእንግዳ ትምህርትና ሐሳብ ሳይሆን ለእግዚአብሔር መሆን አለበት።
“ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፣ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው። እንግዶች ጉልበቱን በሉት፤ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፤ እርሱም አላወቀም” ስለሚል (ሆሴዕ 7፡ 8) ጉልበታችንን ሳናውቀው ለማይገቡና ለሚያፈርሱ ነገሮች እንዳናስበላ ራሳችንን እንመርምር።
(ብርሃን መጽሔት፣ ቁጥር 28፣ 1989፣ ገጽ 26-27። ጽሑፋ በመጠኑ አጥሯል) ለመጀመሪያ ጊዜ በ2006 ተለጠፈ፤ 7/2/2009
ልመናና ምልጃ
እንደሚታየው፦ ደክመናል/ ለዛችን ተሟጧል / የሕይወት ኃይል እርቆን /ቀሰስተኛ ሆነናል።
አሻፈረኝ ለፍርስራሽ አሻፈረኝ ለሽንፈት/የሚል ወኔ ከእኛ ተወስዷል
የዕለት ጉዳያችን፣ የሃሳባችንን አድማስ/ገድግዶ ይዞታል /ከግል ጉዳያችን ተሻግረን ማየት ተስኖናል።
በዕለት ነገራችን ተወጥረን /እርስ በርስም ተፎካክረን/በመነቃቀፍ በመናናቅ መጠላለፍን
ሥራችን አድርገን ተያይዘነዋል /በዚህ ነፍሳችን ተይዛ ትንፋሿ የሲቃ ሆኖአል።
በዚህ ጉስቁልና፣ ቀኖች /ለጥቅም ከመዋል አፈትልከው/እየነጎዱ የዕድሜም ድውር እየሞላብን [ነው]
ምን ይባላል ተስፋው ምኞቱ ታላቅ ሥራ/አከናውኖ የማለፍ ጉጉ ናፍቆቱ ሟሾብናል
ተጠልፎ ተወስዶብናል።
እንግዲህ ሁሉም ከአንተ ነውና /ማዳኑም፣ ጽድቁም ከአንተ ነውና/የበጎነት ምንጭ
ምን ጊዜም /አንተና አንተ ብቻ ነህና/በምሕረትህ ተነሥ፣ ታደገንም /ተሐድሶንም ስጠን
በመካከላችንም በውስጣችንም /ስምህን አክብረው/እኛም አይተን ተገንዝበን
በሁለንተናችን እንገዛልህና/እርስታችን ሁነን/ስምህም ትምክሕታችን ይሁን
በሕይወት ኑሩ ብለህ ብርሃንህ /ጨለማችንን ያስወግድ/ዐይናችንም ተከፍቶ
የዐይን መስታወታችንም አጥርቶ ይይ/ይሁን በል፣ ከአንተ ዘንድ ድንጋጌ ይውጣ።
የሳቱና ገለባ የሆኑ ትንቢቶች፣ ሟርቶች /ከክብርህ መገለጥ የተነሣ/ወድቀው ይንኰታኰቱ
ተቃጥለው ይብነኑ/የተሸነገሉ የሕዝብህ እስረኞችም ይፈቱ/ነጻ ወጥተው በእውነትህ ኪዳን ተሐድሶ
እንደ ገና ይታነጹ/የከበረውን ከተዋረደው/ዘላለማዊውን ከጊዜያዊው/ከኃላፊው፣ ከጠፊው ይለዩ
ክብር ለአንተ፣ ክብር ለአንተ ብለው /ለሕያውነትህ ለአምላክነትህ ይስገዱ።
ሁላችንም ሐሰቱን እውነት ነው ብለን/ራሳችንን ካማተብንበት ከበባ /ከፍ ከፍ ብለን
ምንጥቅ ብለን እንውጣ/የብርሃኑ ሙላትም /ሁሉን ፍንትው አድርጎ ያሳየን
የሸነገልንበትና የተሸነገልንበት /ትብታብ ትባንትብ /ይበጣጠስ፣ ከእጅ ከእግራችን ላይ ይርገፍ።
እባክህ ጌታ ሆይ እባክህ/ዘመናችንን እንደ ቀደሞው አድስ/መልሰህ በአንተ መሥርተን
መቆሚያ ዐለት ሁነን/ከአሸዋ መሠረት ከእንሽርት /አውጣን፤ በከፍታ ላይ አቁመን
ሞታችንን በትንሣኤ ሕይወት ተክተህ ሙላን።
አንዛል፣ ይልቁንም/እንላቅ፣ እንደርጅ፣ እንለምልም፣ እናብብ/ፍሬ እንያዝ፣ እንብዛ፣ እንትረፍረፍ
ሕይወት ይፍለቅ ይጉረፍም/የደረቁ አጥንቶች ይሰባሰቡ/በጅማት ይያያዙ፣ ሥጋም ይልበሱ
በቆዳም ይሸፈኑ፣ በኃይለ ሕይወትም ይሞሉ/ይንቀሳቀሱ ይጎልብቱና/ታላቅ ሠራዊት ሆነው ይቁሙ። ከዚያም
ለአንተ ይጎንበሱ፣ ጠላትን ግን ያስጎንብሱ/የጠላትን ሠፈር ሁሉ ይውረሱ።
እንግዲያስ፣ ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም/ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ ያበጀ
ለሕዝቧ እስትንፋስን/ለሚኖሩባትም ሕይወትን የሚሰጥ /እግዚአብሔር እንደ ገና ያበጃጀን
ከእርሱ በሚመነጭ በእስትንፋሱ/ሕይወት ይሙላን፣ በድል ያመላልሰን።
ክብር ለእግዚአብሔር አብ/ ክብር ለእግዚአብሔር ወልድ/ ክብር ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፤
አንድ አምላክ ይሁን፣ አሜን።
የአዲስ ኪዳን ኅብረተ ሰብ [ተልእኮውና ተግባሩ በተቃውሞ መካከል] ከተሰኘው መጽሐፍ በፈቃድ የተወሰደ። ገጽ 282-284። ታህሳስ 1999 ዓ.ም. በብራና ማተሚያ፣ አዲስ አበባ፣ ታተመ። ደራሲ፦ ሰለሞን ከበደ ወ/ጻዲቅ። መጽሐፉን ለመግዛት (323)731-8721 ይደውሉ። 6/13/2009
================================================================================================================
አሠራርም እኰ ዓላማ ነው
በምትኩ አዲሱ
መግቢያ
አንድ አቅጣጫ ይዞ ለመጓዝ መነሻና መድረሻን ብቻ ሳይሆን መሸጋገርያንም ማወቅ አስፈላጊ ነው። የብዙ ድርጅቶች ፍጻሜ እንደ ጅማሬአቸው የማያምረው በአብዛኛው የመሸጋገርያውን አስፈላጊነት ካለማጤናቸው የተነሣ ነው። በብዙ ድምቀት ይጀምሩና ከተነሡበት ዓላማ ጋር በማይታረቅ አኳኋን ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። እንግዲህ ዓላማን ተግባራዊ ለማድረግ የመሪ ሚና ምንድነው? አሠራርስ ዓላማን እንዴት ይተረጉመዋል?
መሪ ማነው?
መሪ ሁሉን ጠቅልሎ በቁጥጥሩ ሥር ያደረገ፣ መሪነት ለርሱ ብቻ እንደ ተገባው የቆጠረ አይደለም። መሪ የሚጋራ ዓላማ ያለው፣ ዓላማውን ጠንቅቆ ያወቀና በዓላማ የሚመራ፤ ምድር በመላ የእግዚአብሔር እንደ ሆነች የተገነዘበና በጠባብ አስተሳሰብ ያልታጠረ ነው። ተግባሩም ሰዎችን ማሳተፍና፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በተወሰነ ሥፍራና ጊዜ ውስጥ አቀናጅቶ ወደ ታለመው አቅጣጫ መምራት ይሆናል። ሰዎችን ማሳተፍ ማለት እንቅስቃሴ መፍጠር ወይም ዓላማን ማስፈጸም ብቻ ሳይሆን ብቃታቸውን ለይቶ ማጎልበት፣ የተቃረኑ አሳቦችንና አሠራሮችን በሥጋትና በጥርጣሬ ከማየት ይልቅ ለጋራ ጥቅም ማዋል፣ ኃላፊነትን ማከፋፈልና መተማመንን መፍጠር ነው። የአንድ መሪ ብቃት አብረውት እንዲያገለግሉ በሚመርጣቸው ግለሰቦች ማንነት ይለ-ካል። በተጨማሪ፣ እርሱ በሌለበት ሥራው መንቀሳቀስ መቻሉ ብቃቱን ይገልጻል። ስሕተት በአብዛኛው የሚመነጨው ከአስተያየት እጥረት ሳይሆን ከአፈጻጸምና ከአሠራር ነው። የሰዎችን ችሎታ አለመለየትና ሰዎችን አለማሳተፍ ነው። ባጭሩ፣ የምዕመንን ስብዕና ካለማክበርና የተሰጠ ሕይወት እንዲጎለብት ካለማድረግ ነው።
የሚያረጋጋና የሚያስተማምን መሪ
መሪ መነሻውንና መድረሻውን አጥርቶ የሚያይ ነው። የራሱን ደካማ ጎን ጠንቅቆ የተረዳና ለዚህም የሌሎችን ድጋፍ ለመሻት የማይሰንፍና ሲሳሳት ይቅርታን ለመጠየቅ የማያፍር ነው። ይኸው ግለ ሰብ በብዙ ግርግር መካከል መረጋጋት የሚታይበት፤ አሳቡን በቃል፣ በጽሑፍና በድርጊት መግለጽና ማስረዳት የሚችል ነው። ከዚህም የተነሳ ሰዎች በአመራሩ ተማምነውና ተረጋግተው ይከተሉታል ማለት ነው። ተከታዮቹን ከሚያረጋጉ ወይም ከሚያነሳሱ ነጥቦች ዋነኛው ታማኝነቱና እውነተኛነቱ ነው። ሕይወቱ ግልጽና የተሰጠ ነው? ተፈትኖ ያለፈ ነው?
ሌላኛው ነጥብ፣ ከማንም የተለየ እንዳልሆነ ማወቁ ነው። ምናልባት ከሌላው የሚለይበት ነገር ቢኖር ስሕተቱ እንደ ማንም በቀላሉ የማይታለፍለት መሆኑና ንግግሩ፣ አኗኗሩና ውሳኔዎቹ በተከታዮቹና በተመልካቹ ፊት ሁሌ መገምገማቸው ነው። በመጨረሻም፣ የሚያረጋጋ መሪ የተቀናበረ እቅድ ያለው ነው። ይህንንም እቅድ ተግቶ በወቅቱ ማስረዳት፣ የሚከሰቱ ችግሮችን ሳይዘገይ ማረምና ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል ማለት ነው።
ሳይከናወኑ በውጥን ስለቀሩ ጉዳዮች ደግሞ ሳያድበሰብስ ማስረዳትና መፍትሔአቸውን መግለጽ ይኖርበታል። እነዚህ የዘረዝረናቸው ሁሉ አስፈላጊ ነጥቦች ናቸው። አለዚያ ማን ምን እንዳከናወነ፣ ለክንውኖቹ መሳካት ሆነ አለመሳካት ተጠያቂ ማን መሆን እንዳለበት ማስረዳት አዳጋች ይሆናል።
ሁሉም በየፈርጁ
በንግድ ድርጅቶች የምርት ከፍ ማለት ይታያል፤ የሰው ኃይል በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉ ይገናዘባል፤ የበለጠ ምርት እንዲኖር የሠራተኛውን ሞራል መገንባት ይታቀዳል። ወዘተ። በትምህርት ተቋማት የተማሪው ውጤት ከሌሎች ተቋማት ጋር ሲነጻጸር በልጦ መገኘቱ፤ የመምህራን ሞራል መገንባቱ፤ ተማሪው የዜግነትን መልካም ሥነ ምግባር ከቀለምና ዕደ ጥበብ ሙያ ጋር መቅሰሙ፤ ለቁም ነገር የበቁ ምሩቃን ቁጥር በዛ ማለቱ ይታያል።
በቤተ ክርስቲያን ደግሞ ስንቶች የክርስቶስን ፈለግ ለመከተል እንደቆረጡ፣ ስንቶች ተረጋግተውና የጌታ ቤት ጉዳይ ግድ ብሏቸው በቁም ነገር ሥፍራ ላይ እንደዋሉ፣ እነዚህንም በእምነት መንገድ ላይ ለማጽናት የተሰጠው የቃሉ መመሪያ፤ ምን ያህል ገንዘብ ተሰብስቦ ምን ላይ እንደ ዋለ ይመሳከራል። በተጨማሪ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ ምን እንደተከናወነ ይመረመራል።
ሰዎችን ማሳደግ ወይስ እንቅስቃሴ ብቻ?
እስካሁን የጠቀስነው አሠራር የሚያስቀድመው ድርጊትን ነው። እንቅስቃሴን ነው። ብዙ እንቅስቃሴ ከትንሽ እንቅስቃሴ እንደሚሻል ተደርጎ ይታሰባል። ግቡ ከአሠራር እንደሚሻልና እንደሚቀድም ተደርጎ ይቆጠራል። ሰዎች ከቁሳቁስ ጋር ተደምረው የተዘረጋውን እቅድ ከግብ ለማድረስ መሠለፍ እንደሚገባቸው ይታሰባል።
በአንጻሩ፣ ሰዎችን በግል ሆነ በማኅበር ማነጽ ቅድሚያ ቢሰጠው ምን ውጤት ያስገኝ ይሆን ብሎ ማሰብ አስፈላጊና ተገቢ አማራጭ ነው። በአመራር ላይ ያሉትን ለመተካት ምን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው? ሰዎች በነፍስም በሥጋም መጎልመሳቸው ምን ዓይነት የአሠራር ለውጥ ያስከትል ይሆን? በመሪነት ሥፍራ ላይ የተቀመጠ ሁሉ ለዚህ ጥያቄ መልስ መሻት ይኖርበታል።
ሰዎች እንደ ተፈለጉ ከማወቃቸው የተሻለ ሞራላቸውን የሚገነባና ራሳቸውን እንዳይቆጥቡ የሚያደርጋቸው ነገር አይገኝም። ገንዘቡም ቁሳቁሱም ጊዜም በእግዚአብሔር ጸጋ ሰውን ሊያገለግሉና ማኅበራዊ አስተሳሰብን ሊያጎለብቱ ይገባል።
ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ አውጥቶ ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንዲያገባ እግዚአብሔር ያስነሳው መሪ ነበር። ጊዜ ቢፈጅበትም፣ የራሱን ዓላማ ወደ ጎን ትቶ የእግዚአብሔርን ዓላማ ዓላማው ማድረግ ነበረበት። ሕዝቡ ከባርነት ውስጥ ገና መውጣቱ ስለሆነ ስለራሱ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነበር፤ ኅልውናው የላሸቀ ሕዝብ ነበር። በእግዚአብሔርና በራሱ መተማመን ያልተለማመደ ሕዝብ ነበር።
በዚህ ሁኔታው ወደ ተስፋዪቱ ምድር ቢገባ ኖሮ በመንፈሱ የበረከቱን ክቡርነት አይገነዘብም ነበር። የአምላኩን ሥራ ኃይል መዝኖ ለአምላክነቱ የሚገባውን ምስጋና ማቅረብ አይቻለውም ነበር። ሙሴም ቢሆን ገና ይቀረው ነበር፤ እንደ እኛው ሰው ነበረና።
እንግዲህ የአንድ እቅድ መነሻውና መድረሻው ብቻ ሳይሆን መንገዱና ጉዞው አስፈላጊ እንደ ሆነ ከእስራኤል ሕዝብ ታሪክ እንገነዘባለን። በዚህ ጉዞ ውስጥ እስራኤል በአስተሳሰቡ ተፈወሰ። ባሪያ የነበረ ባለ ርስት ሆነ። ተስፋ ያልነበረው ባለ ብዙ ተስፋ ሆነ። ደካማና ሥጉ የነበረ ኃያልና የሚያስፈራ ሆነ። እንግዳ የነበረ በመካከሉ ላሉት እንግዶች ቸርነትን አሳየ። ተነጣጥሎ ሲጠቃ የኖረው፣ ተያይዞ ተቻችሎ መጓዝን ተማረ፤ ተረባርቦ ጠላቶቹን ድል ማድረግ ለመደ። ማንም ይንቀው የነበረ፣ ወንድሞችን እህቶችን አባቶችን እናቶችን ማክበር ተማረ። እርዛትና ረሐብ ያወቀ መልበስና መጋራት ተማረ። እርስ በርሱ እንዳይተማመን በፍርሃትና በጥርጥር እሥራት የኖረ ዛሬ ተደጋግፎና ተማምኖ መጓዝ ጀመረ።
ጉዞው በምድረ በዳ በኩል ነበር። ያለ መሪ መጓዝ የማይቻልበት መንገድ ነበር። የምድረ በዳው ስፋትና ጭውታ በራሳቸው ብርታት በቁጥራቸው ብዛት መታመን የማይችሉበትን ሁኔታ ፈጥሮ ነበር። በምድረ በዳ ውስጥ ሆነው ዕለት ዕለት የራሳቸውን ውሱንነት እየተረዱ፣ የሚጠብቃቸውን ርስት ማሰብ ነበረባቸው። ለከነዓን ምድር ኑሮ ወደሚያበቃ የእድገት ደረጃ መሸጋገር ነበረባቸው። በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ መታመን ነበረባቸው፤ እርስ በርስ መጠባበቅ ነበረባቸው።
የመሪ ዋነኛ ተግባር እቅድን ማስፈጸም ሳይሆን ሰዎችን ማያያዝ በነፍስና በሥጋ የሚጎለብቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ቀዳሚ ሊሆን የሚገባው ሲቀድም ሌላው ሁሉ ይከተላል። እቅድ ሲወጣ በዚህ ዋነኛ ዓላማ ላይ ማተኮር ይኖርበታል ማለት ነው።
በዓይነ ቁራኛ መጠባበቅ
በአብዛኛው ግን ጊዜና ጉልበት የሚጠፋው ችግር እንዳይፈጠር በዓይነ ቁራኛ በመጠባበቅ ነው። የዚህም መንስዔዎች የሚከተሉት ይሆናሉ፦
· ዓላማን አጥርቶ አለማወቅ፣ አለማሳወቅ · አንዱ ለሌላው የሥጋት ምንጭ መሆን
· ልበ ሙሉነት ሲጠፋ፤ ይህም በእግዚአብሔር ላይ ካለመታመንና ቃሉን ለሰሚው በማመቻቸት ውስጥ ሥልጣንን ከመጣል የተነሳ
· ጸጋ ለማትረፊያና ለመወዳጃ ሲውል · በሰማያዊ ጥበብ ፈንታ ምድራዊ ብልሃት ሲያይል
· የእግዚአብሔርና የሰው ነገር ሲደበላለቅ · መሪው ብቃቱን ሳያሳድግ ሲቀር (ለምሳሌ፣ በቃሉ እውቀት አለማደግ፣ የዘመኑን ባሕላዊ አስተሳሰብ በቃሉ መርምሮ አለመረዳት፣ ከራሱ ባሕል ጋር አለማመሳከርና አለማዋሃድ፣ የሚጠቅመውን መርጦ መውሰድ አለመቻል፤ ዘመናዊነት ሲያሸንፈው)
ወንጌልና ሰው
ወንጌል የታወጀው ለሰዎች እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም። ወንጌል የገባው ሰው ለእግዚአብሔር ይመቻል፣ ለሰዎችም ይተርፋል። የኢየሱስም ሰው መሆን ለሰዎች ነው፤ ለራሱ አይደለም።
ሰብዓዊነትን የሚዘነጋ እቅድ ትክክለኛ እቅድ ሊሆን አይችልም። በእቅድና በአስተዳደር መዋቅር ላይ ብቻ የሚያተኩር አሠራር ዓላማውን የሳተ ነው። እቅድን ተግባራዊ ለማድረግ ሰው ቢያስፈልግም፣ የእቅዱ ግብ መልሶ በሰው ላይ ማተኮር ይኖርበታል ማለት ነው። ትክክለኛ እቅድ ሰዎችን እንደ ገቢ ምንጭ ወይም እንደ ቁጥር ማሟያ አድርጎ አያስብም። ትክክለኛ እቅድ ሰውን ያከብራል። በአምላክ አምሳል ስለ ተፈጠረ ክቡርነቱን ይገነዘባል። እግዚአብሔር ሲፈጥረው የለገሰውን ጸጋ ይለ-ያል፣ ያሳድጋል። ሌሎችን ለከበረ ኃላፊነት ለማብቃት ይተጋል። በሌላ አነጋገር፣ በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ የሚታዩት የእንቅስቃሴና የእድገት ሚዛኖች በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲሠለጥኑ አያሻም ማለት ነው። ሰው ማኅበራዊ ፍጡር ነው። ማኅበራዊነቱ ግላዊነቱን ሳይሽር የሚያብብበትን እቅድ መተለም ያሻል ማለት ነው።
እርስ በርስ መያያዙና መተሳሰቡ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ይሆናል። ጥቂቶች የሚያይሉበት ወይም ሌላው የማይታይበትና የሚጣበብበት መሆን የለበትም። ሁሉም አብሮ የሚያድግበት እንጂ። እያንዳንዱ የሚተናነጽበትና የሚጠባበቅበት እንጂ። እያንዳንዱ አስተዋጽዖ እንዳለው ወደ መገንዘብ የሚደርስበት እንጂ። ከማኅበራዊነት ጋር የማይስማማ ግለኝነትን መቅረፍ እንጂ። ከሁሉም በላይ መተማመንን መፍጠር። እግዚአብሔርን እንዲተማመን እየተነገረው እርስ በርሱ የማይተማመን ከሆነ ዓላማውን ከጅምሩ ስቷል ማለት ነው። የኅብረት አስፈላጊነት እየተነገረው ለየብቻ መካለል እንደዚሁ ትርጉም አይኖረውም።
ዛሬ የሚታየው ሁኔታ
በዚህ ዘመን ጎልቶ የሚታየው ሁሉም የየራሱን ክልል ማበጀቱ ነው። በዚህም ሰፊ ልብና ሰፊ አእምሮ እንደጎደለ ያስታውቃል። “አትድረሱብኝ፣ አልደርስባችሁም” የተባለ ያህል ማለት ነው። ነገሩ ኅብረት ይመስላል። የሚያያዝበትን ሳይሆን ከሌላኛው የሚለይበትን እስካሰበ ድረስ ግን ገና ይቀረዋል ማለት ነው። የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ከአብዮት በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ እየተመለሰ እንዳይሆን እንስጋ።
እግዚአብሔር አዋቂ ነው። የፊተኛውን ዘመን ሁኔታ ለማቃናት አስቦ ስደትን ፈቀደ። የሙሉ ወንጌል አማኞች ከመካነ ኢየሱስ ሠፈር ተገኙ። ቃለ ሕይወት ከሙሉ ወንጌል ሠፈር። ወዘተ።
መሪ መተማመንን መፍጠር የሚችለው የወንጌል እውነት ከራሱ ክልል ያለፈና የሰፋ መሆኑን ሲገነዘብና ሌሎችን ለማስጠጋትና ለመጠጋት ሲፈቅድ ነው። የሚመራው ጉባዔ የሰፋ ልብና አእምሮ እንዲኖረው ተግቶ ሲያመቻች ነው። አለመተማመን ደግሞ የሚባባሰው ይኸው መሪ ሰዎችን፣ ድርጅቶችንና መዋቅሮችን ላጭር ዓላማው ሊያውላቸው ሲጥር ነው።
በተጨማሪ፣ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ ከኑሮው ለይቶ ማየት ሲያቀተው ነው። ከተገኘበት ክልል አርቆ ማየት ሲሳነው ወይም ሳይፈቅድ ሲቀር ነው። የሚመራውን ማኅበር እድገት ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ሲወስነው ነው። እንደ በርናባስ የጌታን ጸጋ እያየ ደስ የሚሰኝና ሌሎችን ለማስቀደምና ካስፈለገም ሥፍራውን ለመልቀቅ የሚፈቅድ ልብና ፈቃድ ሲያጣ ነው። ይልቅ ለራሱ የወሰነውን ክብርና ሚዛን የሚሻማ ከሆነ፣ ላቀደው ዓላማ ካልተስማማ ግንኙነት አይፈጥርም ማለት ነው።
ይህን ሁኔታ ለማገድ ከጥቃቅኑ ጉዳይ በላይ ማሰብና ከጊዜአዊውና ከሚታየው ያለፈ የከበረ ዓላማ እንዳለ መረዳትን ይጠይቃል። ብቃት ባለው መልኩ ትምህርትና አመራር መስጠትን ይመለከታል።
ይህም በእግዚአብሔርና በራስ መተማመንን ይጠይቃል። ዓይነተኛ አመራር በሌሎች ሙገሳና ትችት የሚንቀሳቀስ ሳይሆን ልኩን በማወቁ፣ በማድረጉና የወደፊቱን በማሰብ ውስጥ የሚከሰት ነው።
ለመሆኑ፣ የሚደመጡና የሚፈሩ መሪዎች ዛሬ የጠፉት ለምን ይሆን? በመሪዎች መካከል ልበ ሰፊነትና ማስተዋል በመጥፋቱ መፍትሔ ያልተፈለጉላቸው ጉዳዮች ዛሬም ውይይት ሳይደረግባቸው በእንጥልጥል ተትተዋል። ገልጾ መወያየት ካስፈራ ወይም ከደረስንበት መረዳት ጋር የማይጣጣም ሁሉ ውጉዝ ከሆነ ጥያቄና እያደረ የሚመረቅዝ ችግር ይዘን ለመጓዝ መርጠናል ማለት ነው። ከነዚህ ጥቂቱን ለምሳሌ ያህል እንመልከት፦
· የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በመጋቢ ወይስ በሽማግሌ ይሁን? ይህ ጥያቄ በዚህ መልኩ መጋቢንና ሽማግሌዎችን ነጣጥሎ የሚያቃርን ብቻ ሳይሆን ክርስትና በመሠረቱ ማኅበራዊ እንደ ሆነ ይዘነጋል። አንዱ የሌላኛው ጠባቂ እንደ ሆነ በመዘንጋቱ ተጠሪነትንና ተጠያቂነትን ያዛባል። አመለካከት ስለ ተዛባ አንድ ጎን ይዞ መሮጥ ይጀምራል። ምዕመንም ማኅበራዊነትን ሳይሆን አንጀኛነትን ልክ እንደ ሆነ አድርጎ ይቆጥራል። አሠራር ልዩ ልዩ ቢሆንም ጌታ አንድ ነው። ልዩ ልዩ ብልቶች ቢኖሩም አካል ግን ያው አንድ ነው። አሠራሩ በዓላማው ትይዩ መጓዝ ይኖርበታል ማለት ነው።
· ውጭ አገር የተደራጁት ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በሚሲዮናውያን የታየውን ስሕተት እንዳይደግሙ ምን ይደረግ? ሚሲዮናውያን ወንጌልን በማስፋፋት ረገድ ብዙ የደከሙ ቢሆንም፣ የአገሬውን መሪዎች ባለማሠልጠናቸው፣ የአማንያንን መያያዝ ከማጎልበት ይልቅ አካልለው በአምሳላቸውና በስማቸው ርስተ ጉልት መፍጠራቸው፣ የአብያተ ክርስቲያናት የበጀት አቅም ከድጎማ እንዳይወጣ በማድረጋቸው፤ ከአገሬው ባሕልና አመራር ጋር ያልተጣጣመ ትልም በመተለማቸው፣ የስነ-መለኮት ግንዛቤ ያላቸውን ምሑራን ባለማፍራታቸው፣ ይልቁን የምድራዊውን እውቀትና ማኅበራዊ ተሳትፎን የሚዘነጋ አመለካከት በማጽናታቸው ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ልትላቀቅ ያልቻለችበትን ሰንካላ የአሠራር ባሕል አጎናጽፈዋታል።
በአንጻሩ፣ ውጭ አገር ያሉት የቤተክርስቲያን መሪዎች አገር ውስጥ ያለውን አሠራር በማጠናከር ፈንታ የየራሳቸውን ክልል ሲያበጁና የምዕራባውያንን ባሕላዊ ክርስትና በማስተናገድ የሚሲዮናውያኑን ስሕተት ከሞላ ጎደል እየደገሙት ይገኛሉ። ይህም የአማንያንና ከክርስቶስ ማኅበር በስተውጭ ያሉቱ ስለ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን አመለካከት እያዛባው መጥቷል። የዓለማውያን መሳለቂያ መሆናችን ሳያንስ መሪዎች እርስ በርስ የሚያደርጉትን ፍልሚያ ተራው ምዕመን ሳይቀር እየኰረጀ ገና የሚተርፍ አሣር እያከማቸን ነው። ከዚህ የተነሳ የቤተክርስቲያን መሪዎችም በዓለማውያን መሪዎቻችን ላይ ከሚታየው አይለዩም ወይ ወደ ማለቱ ደርሰናል።
የመሪ ድርሻው እንግዲህ መተማመንን መፍጠር እንዴት ይቻላል የሚለው ይሆናል። ለዚህም እነዚህን አሳቦች ማሰብ ይጠቅማል።
· በቅድሚያ፦ እግዚአብሔር ያለ እኔም መሥራት ይቻለዋል፣ እግዚአብሔር በማንም መሥራት ይችላል፤ እኔስ ማን ነበርኩና ነው ብሎ ማሰብን ይጠይቃል።
· እኔ አረጃለሁ፣ አልፋለሁ፤ የእግዚአብሔር ሥራ ግን አያረጅም፣ አያልፍም፤
· የጥንቱን ሃይማኖት ማጽናት ይጠይቃል። ይኸውም፦
o የቃሉን መካከለኛነት ማጽናት o የጸሎትን ፍቱንነት መለማመድ o አብሮ ማዕድ መቁረስ
o ኃላፊነትን ማጋራት o ለቤተክርስቲያን መገዛት o ትውልድን አለመነጣጠል፤ ይህም አደገኛ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። መንፈስ ቅዱስ ሲሠራ “የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል” ይላልና። (የሐዋርያት ሥራ 6፡1-6። ሚልክያስ 4፡6)
ማጠቃለያ
በቤተክርስቲያን የሚታየው እንቅስቃሴ ተግባራዊነቱ በሰዎች ተሳትፎ ቢሆንም ያው እንቅስቃሴ ደግሞ መልሶ ሰዎችን ዓላማው ካላደረገ መነሻ ትርጉሙን ስቷል ማለት ነው። ምእመን በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እድገት ካላሳየ፣ ማንኛውም ነፋስ ይዞት የሚሄድ ከሆነ፤ የቃሉን አተረጓጐም በሚመለከት “እኔ ለራሴ የምተረጉመው እንዲህ ነው” ከማለት ያላለፈ ከሆነ፤ መንፈሳዊነትን ከማኅበራዊ ኑሮ ካልለየ፤ የግል ልምምዱ የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ከመሰለ፣ የአገልግሎት ዘርፎች መብዛት እንቅስቃሴ ከማብዛት በቀር ሌላ ትርጉም አይኖራቸውም?
ምእመን የገበያን ባሕል ከክርስቲያናዊ ባሕል የማይለይ ከሆነ፤ ከጸጋ ይልቅ ዝናን የሚሻ ከሆነ፣ የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ሥልጣን ሆነ ሥርዓት ከራሱና ከግለሰቦች ፈቃድና ልማድ የማይለይ ከሆነ፣ እውነቱን ከሐሰቱ ለመለየት ከራሱ ስሜትና እውነቱን ከማይነግሩት ማረጋገጫ የሚሻ ከሆነ፤ “የግል አገልግሎት” ለቤተክርስቲያን ላለመገዛት ሰበብ የሚሆን ከሆነ እንቅስቃሴ እንጂ ሌላ ትርጉም አይኖረውም።
እንዲህ ዓይነቱ አመራር ሰዎች እርስ በርስ የሚሞጋገሱበትና የሚወዳጁበት እንቅስቃሴ እንጂ ማኅበርንና ማኅበርተኛን የሚያንጽና የሚያጸና አይሆንም። ከሁሉ ይልቅ ደግሞ መሪው ራሱ በአመራር ብቃቱና በመልካም ሥነ ምግባሩ፣ በታማኝነቱና በቃሉ እውቀት፣ በወሳኝነቱና ዋጋ ለመክፈል ባለው ቁርጠኛነቱ አንሶ ከተገኘ የሚያቀናብራቸው እንቅስቃሴዎች መዝናኛና መተዳደሪያ ብቻ ይሆናሉ፤ ምዕመኑን በማባበል እድገቱን ይገታሉ ማለት ነው። ባጭሩ የሰው ሥራ ከመሆን አያልፉም።
በመጨረሻም፣ መሪ ዓላማውንና የአሠራሩን ዘርፍ ከማጠናከሩ የተነሳ እርሱ በሌለበት ሥራው የሚካሄድ መሆን ይኖርበታል።
የተከታይስ ተግባርና ድርሻ ምንድነው? ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን።
Revised 6/2009/ Copyright Ó January 2008 by Mitiku Adisu /All rights reserved
ትላንት ዛሬ ቢሆን፣ ዛሬ ደግሞ ትላንት
በፀሐይ ዓለሙ
ትላንት ከሆነው ነገር ጋር አልፏል፤ የቀደሙት ጊዜአትና ድርጊቶች ሁሉ ዕድሎቹም ሁሉ ሄደዋል። ሰው ሁሉ አሁን ያወቅሁትንና የተረዳሁትን ያህል ያኔ ባስተውል ኖሮ ይህንና ያንን አደርግ ነበር ይላል። የዛሬው ዕድልና ሁኔታ ያኔ ቢኖር የታሰበውን ሁሉ ለመሥራት ይቀል ነበር እንላለን።
ማስተዋል ከዕድሜ ጋር እየተደጋገፈ ይመጣል። የመረዳታችን ሁኔታ በጨቅላነትና በወጣትነት እንዲሁም በጎልማሳነት ወራት የተለያየ ነው። ሁሉም ደረጃውን ጠብቆ የሚሄድ የሕይወት ሂደት ነው።
እርግጥ በዝግታ አስተውለን ልናደርግ የተገባውን ነገር በጊዜው ሳንረዳ ቀርተን ብናልፈው ዕድሉን ለአንዴም ለመጨረሻም ልናጣው እንችላለን። ለምሳሌ ትዳር የመመሥረቻው ዘመን ክልል፣ ልጆችን ወልዶ የማሳደጊያው ዕድሜ ገደብ ዳርቻው እየታወቀ ችላ ቢባል ወደ ኋላ ተመልሶ ማስተካከል የማይሆን ነገር ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ። /ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ [መክብብ 3፡10-11]
ሁሉ በጊዜውና በሰዓቱ ሲደረግ እጅግ ያምራል። ሆኖም በቆይታም ውስጥ ተዘግተን ኖረን ዘመኑ እኛን እንዲያየንና እንዲጎበኘን ሆኖ የተመደበልንን ያህል ጊዜው ረድቶን ያልጠበቅናቸው ነገሮች እየተከታተሉ መጥተው ሲሆኑልን ስናይ የሕይወታችን ዘመን ክልል ከእግዚአብሔር በታቀደልን እቅድ ተከፋፍሎ የተፈጠረ፣ የተወሰነለትን እንዲቀበል ሆኖ የተሠራ መሆኑን እንገነዘባለን።
የኛ ማስተዋልና ጥረት ሳይታከልበት ራሱን ችሎ የሚሆን እግዚአብሔር ብቻውን የሚያደርገው ልዩ ልዩ ነገር አለ። ያም የኛን ብቃት ወይንም ማንነት ሳይጠይቅ እንዲሁ እርሱ እንደ ወሰነልን የሚሆን ነው። ሕይወት ራሱ ስፋቱ እንደ ውቅያኖስ የሚመስል፣ እንደ ባሕር ጥልቀት የሆነ የረቀቀ ምሥጢር ያለው ውስብስብ ነው። ይህን ጥልቅ ሕይወት በዝርዝር የሚያውቀውና ሊያነብበው የሚችል ሠሪው እግዚአብሔር ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦
ሁለንተናዬን የፈጠርህ አንተ ነህ። በእናቴ ማሕፀን አገጣጥመህ የሠራኸኝ አንተ ነህ፤/ክብር የሚገባህ ስለሆነም አመሰግንሃለሁ።/ሥራህ ሁሉ ግሩምና ድንቅ ነው፤ ጠንቅቄም አውቀዋለሁ።/አጥንቶቼ በመሠራት ላይ እንዳሉ በእናቴም ማሕፀን በጥንቃቄ በመገጣጠም እንዳሉ፣ እዚያም በስውር በማድግበት ጊዜ በዚያ መሆኔን አንተ ታውቅ ነበር። ከመወለዴ በፊት አየኸኝ ለእኔ የተወሰኑልኝ ቀኖቼ ገና ከመጀመራቸው በፊት በመዝገብህ ሰፍረዋል፤ አምላክ ሆይ! አሳብህ እጅግ የከበረና የሰፋ ስለሆነ እኔ ልረዳው አልችልም። [መዝሙረ ዳዊት 139፡13-17። 1980 ትርጉም]
ዝርዝር አድርጎ የሚያውቀን እግዚአብሔር ብቻ ነው። የአካላችንም ክፍሎች በእርሱ ዘንድ የታወቁና የተመዘገቡ ናቸው። እኛ ግን ራሳችንን በከፊል እንጂ በሙላት አናውቀውም። ሁኔታዎችንና ጊዜአትንም አጠናቅቀን አንረዳም። ስለዚህም የሰው ሁሉ ሕይወት ብዙ ጥያቄ አለው። ሆኖም ሠሪውን አምላክ ካወቅነው፣ መሪያችንም ካደረግነው እርሱ ራሱ ለነፍሳችንና ለመንፈሳችን እረፍትን በመስጠት መልስ ይሆነናል። ቢገባን ባይገባንም ስለ ሕይወት ያለን አመለካከት የረጋና የተደላደለ ሊሆን የሚችለው ለፈጠረን አምላክ አክብሮትና ፍርሃት ሲኖረን ነው።
ትላንት ወይም ያለፈው ዘመን አሁን ያለሁበትን ጊዜ ቢሆን እያልን ወደ ኋላ ተመልሰን እናስባለን? እንፀፀትስ ይሆን? የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ይላል፦
በዙፋንም የተቀመጠው። እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። [ዮሐንስ ራእይ 21፡5]
እንዴት ነው ሁሉን አዲስ የሚያደርገው? ከሁሉም በላይ የኛን የውስጥ አመለካከትና አስተሳሰብ በመለወጥና አዲስ በማድረግ ነው። አምላክ እንደሚያየው እንድናይ፣ እርሱ የሚያስበውን እንድናስብ በማድረግ ያሳርፈናል።
እርሱ ተቀማጭነቱ ዙፋን ላይ ነው። በሥልጣንና በኃይል የሚሠራ ጌታ ስለሆነ የእርሱ ሃሳብና መንገድ የጸና ነው፤ ተፈጻሚነትም አለው። ስለ ብዙ እንጨነቃለን፤ የሚያስፈልገው ግን ብዙ ነገር አይደለም፤
ኢየሱስም መልሶ። ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ፣ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፣/ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች፣ ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት። [ሉቃስ 10፡41-42]
ያሁኑንም ያለፈውንም ለዚህ ታላቅ ጌታ አስረክቦ ሰጥቶ በእርሱ ፈቃድና ሃሳብ ለመመራት መወሰናችን ብቻ ያሳርፈናል። ከዚህ ውጭ ላለው ነገር ሁሉ ውስጣችን ከተከፈተ ግን ማብቂያ የሌለው መዋለል ይሠለጥንብናል።
በሕይወት ሩጫ ውስጥ ማንም አሸናፊ የለም፤ ለምን ቢባል ሁሉም የራሱን ድርሻ ለራሱ ነው የሚሮጠውና። ተሸናፊም የለም፤ ሁሉም የራሱን የሕይወት ትግል ነው የሚጋፈጠውና። እግዚአብሔርም ሕይወታችንን ለውድድር አልሠራትም። ከድካማችን ግን ሊያሳርፈን ተስፋ ስጥቶ ከጥረት ጋር ፈጥሮናል።
ስለዚህ በክርስቶስ የምናርፈው ከብዙ ጥያቄአችን ጋር ሆነን ነው። ይኼ ጌታ ምንጊዜም ልክ እንደ ሆነ እየተረዳን የምንጓዘው የሰላም መንገድ ነው። ስለ ብዙ ነገር እንዳንገረም አድርጎ በጸጥታና በሰላሙ በመሙላት ይመራናል። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦
አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሰነፎችንም ቸልተኛ መሆን ያጠፋቸዋልና። /የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል። [ምሳሌ 1፡32-33]
በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ። /ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ። [ኢሳይያስ 26፡ 3-4]
ያለፉት ቅዱሳን እንዲሁ እንደ እኛው ሰዎች ነበሩ። እንዲሁ እንደ እኛው የሚመስል ሕይወት ነበራቸው። እጅግ ብዙ ጥያቄም ነበራቸው። ነገር ግን በእግዚአብሔር ማመናቸውና መደገፋቸው ጠቀማቸው። አእምሮንም የሚያልፈው የእግዚአብሔር ሰላም ሁለንተናቸውን በክርስቶስ ኢየሱስ ገዛላቸው።
የፍጥረት ሁሉ ሁኔታ ለእግዚአብሔር አይደንቀውም። እኛም የኛ ሁኔታ ሊያስደንቀን አይገባም። እንደ ሰው ማሰብና መኖር ስላለ እንደዚያ ሆነናል። በጌታ ሰላም ግን እረፍታችን የተጠበቀ ነው።
5/16/2009 Copyright ©by Ethiopianchurch.org
All rights reserved
የተከበራችሁ የ Ethiopianchurch.org አንባቢዎቻችን፣
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።
Ethiopianchurch.org አገልግሎት መስጠት ከጀመረ እነሆ፣ አራተኛ ዓመቱን ይዟል። ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅና ማሳወቅ፣ ክርስቲያናዊ ተግባራትን ማሳሰብና ማጽናት ተቀዳሚ ዓላማችን እንደ መሆኑ በነዚሁ ዓመታት በተለያዩ ርዕሶች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን አዘጋጅተን አቅርበንላችኋል። የተጠቃሚውም ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ከመረጃ ማጠናቀሪያችን ተረድተናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለእንግሊዝኛ ብቻ ተናጋሪዎች Ethiopianchurch Blog ጀምረናል፤ [ከላይ በስተ ቀኝ ጥግ ይመልከቱ]
አሁን የቀረው የናንተ የአንባቢዎቻችን ድርሻ ነው።
1. በጸሎት እርዱን፤ እግዚአብሔር የረጋ አእምሮና ብርታት እንዲጨምርልን፤ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ የሚያነጋግርና መፍትሔ የሚያመጣ ጽሑፍ ለማቅረብ የሚችሉ ሰዎችን እንዲያነሳሳ፤
2. የተዘጋጀውን አንብቡ፣ አስተያየታችሁን በ Info@Ethiopianchurch.org መላክ አትርሱ፤
3. ግጥም ይሁን ሌላ፣ ከሁለት እስከ አራት ገጽ የሆነ በቀላል አማርኛ የተዘጋጀ ጽሑፍ በ Word አትማችሁ ላኩልን፤
4. ቢያንስ ለአምስት ወዳጆቻችሁ በኢ-ሜይል ይሁን በስልክ Ethiopianchurch.orgን ያስተዋውቁ፤
5. በአገር ቤት ሆነ በውጭ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ መረጃ ጽሑፎችና ሰነዶችን ላኩልን ወይም ጠቁሙን፤
6. እንዲገመገሙ የምትፈልጉት መጽሐፍ ካለ ወይም ለመገምገም የምትፈቅዱ በአድራሻችን አስታውቁን፤
ከዚህ ወዲያ ሌላ አንጭንባችሁም። በሰላም ቆዩን።
5/5/2009
በዘመናት መካከል የሚጠበቁ ሰዎች አሉ
በፀሐይ ዓለሙ
ሁሉም ልዩ ታሪክ እንዲሠራ አልተፈጠረም። ለዚያ ተለክተው የተሠሩና ለወቅቱና ለቦታው የተመደቡ ልዩ ሰዎች አሉ። እንደነዚህ ዓይነቶቹን ሰዎች ሰማይና ምድር ፍጥረትም ሁሉ በመቃተት እስኪከሰቱ ድረስ ይጠብቋቸዋል። ሊሆን ያለው ነገር እነዚህ ልዩ ሰዎች እስከሚገለጡ ድረስ አይሠራም፤ አይፈጸምም። ሕይወታቸው የተሰጠ ስለሆነ ለድርጊቱ የተመረጡ ናቸው። የሚያሠራቸውም እግዚአብሔር ከበስተጀርባቸው ነው።
እነዚሁ በዘመናት ውስጥ ሳይዘገዩና ሳይፈጥኑ በጊዜውና በቦታው ይታወቃሉ። ስማቸው ለመታወቅ ጊዜ አይፈጅበትም። ዝናቸው ከሚያሠራቸው ኃይል እንጂ ከራሳቸው የሚፈልቅ አይደለም። ድርጊታቸውና ቃላቸው አያዳግምም። ተቀባይነታቸውና ተሰሚነታቸው የተለየ ነው። የራሳቸው የግል ዓላማና ሥራ የላቸውም። አስቀድሞ ከተወሰነውና ከተደነገገው ውስጥ ብቅ ይላሉ። ጊዜአትና ሁኔታዎችም ይረዷቸዋል። ምድርና ሰማይ ይቀበሏቸዋል። በቁጥር ብዙ አይደሉም፤ ነገር ግን ከአእላፋት የበለጠ ሥራ ያከናውናሉ።
ሰማይና ምድር ፍጥረታትም ሁሉ ቀን ለሌት፣ ሌትም ለቀን በመንገር ይቃትታሉ። ሊሆን ያለው ፈጥኖ እንዲሆን ይቃትታሉ።
ጌታ ኢየሱስም ከመወለዱ በፊት ይጠበቅ ነበር። በሰዓቱ መጣ፤ ለየት ያለውን ድርጊት በሕይወቱ በታሪክ ውስጥ አከናውኖ ሄደ። ዮሐንስ መጥምቁም በሕይወቱ፣ በአኗኗሩ፣ በአመጋገቡ፣ በአለባበሱና በአነጋገሩ በዘመኑ ባሉት መካከል በጊዜውና በቦታው ተከሰተ፤ የማይደገመውን ሥራ በፍጥነት ሠርቶ አለፈ። በየዘመናቱ ልዩውን መልእክት ለማስተላለፍ ነቢያት መጡ፤ የማይለወጠውን ድርጊት ፈጽመው ተሻገሩ። ልዩ አስተማሪዎች፣ ሰባኪዎች፣ ተአምራት አድራጊዎች፣ ደራሲዎች፣ የጦርና የአገር መሪዎች ተጠብቀው ተከስተው ሥራቸውን ፈጽመው ሄደዋል።
አሁንም ለተለየው ዓላማና ሥራው ልዩ መልእክት በሥራቸውና በሕይወታቸው እንዲያሳዩ ከጥንት ከዘለዓለሙ ሥፍራ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የተሰየሙቱ እነርሱ እንዲመጡ ፍጥረት በማይታወቅ መቃተት ይጮሃል። እነዚህ ልዩ ሰዎች ለምድር ወገን ሁሉ ስለሚያስፈልጉ ይፈለጋሉ። ደግሞም በጊዜውና በሰዓቱ ይመጡ ዘንድ ግድ ስለሆነ ይመጣሉ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ባለፉት ድርጊቶች አትመኩ፤ ከዚህ በፊት የሆነውንም ነገር በማሰላሰል ጊዜ አታጥፉ።/ይልቅስ እኔ ወደ ፊት የማደርገውን አዲስ ነገር ጠብቁ፤/እርሱም በመፈጸም ላይ ስለሆነ አሁን ማየት ትችላላችሁ።” [ትንቢተ ኢሳይያስ 43፡ 18-19። 1980 ዓ.ም ትርጉም]
እንደ ቃሉ እንዲሁ ይሆናል። እኛስ በሕይወታችን እንዲሆን ከጥንት ከጌታ ዘንድ የተወሰነ ልዩ የታሪክ ወቅት ይኖር ይሆን? ከነዚዎቹስ ሰዎች አንዱ እንሆን ይሆንን? ማን ያውቃል! የእኛም የውስጥ መንፈስ ቢሆን በመቃተት ላይ ይገኛል፤ ታላቅ የልብ መንጠልጠል፣ ያለማረፍ ሃሳብ በውስጣችን ይኖራል፤ ሊሆን ያለው ሊሆን ሰዓቱ እስከሚደርስ ነው። ደግሞም ይሆናል!
“ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። /እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?” [ዘኅልቁ 23፡19]
5/3/2009
አቤቱ፣ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ።
አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። እርሱም። ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም። አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን። አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።
አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ። እነሆ፥ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው። በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም። አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው።
አቤቱ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን። ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ። ሰውን ወደ ኅሳር አትመልስም፤ የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ ትላለህ፤ ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና። ዘመኖች የተናቁ ይሆናሉ፥ በማለዳም እንደ ሣር ያልፋል። ማልዶ ያብባል ያልፋልም፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል። እኛ በቍጣህ አልቀናልና፥ በመዓትህም ደንግጠናልና። የተሰወረውን ኃጢአታችንን በፊትህ ብርሃን፥ በደላችንንም በፊትህ አስቀመጥህ። ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመዓትህ አልቀናልና፤ ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ። የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንገሠጻለንና።
ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው …
እኔ በልቤ። ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ መልካምንም ቅመስ አልሁ፤ ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ። ሳቅን። ዕብድ ነህ፤ ደስታንም። ምን ታደርጋለህ? አልሁት። የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ። ትልቅ ሥራን ሠራሁ፥ ቤቶችንም አደረግሁ፥ ወይንም ተከልሁ፤ አትክልትንና ገነትን አደረግሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፤ በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ አደረግሁ …ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ። ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፤ አዝማሪዎችንና አርሆዎችን የሰዎች ልጆችንም ተድላ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ። ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፤ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸንታ ቀረች። ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻችን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም።
እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፤ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከስንፍና እንዲበልጥ አየሁ። የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ ሰነፍ ግን በጨለማ ይሄዳል፤ ደግሞ ለሁለቱ መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ። እኔም በልቤ። ለሰነፍ የሚደርሰው ለእኔም ይደርሳል፤ ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ? አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ። ይህ ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘላለም የሚሆን የጠቢብና የሰነፍ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከሰነፍ ጋር እንዴት ይሞታል! ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ ከብዶብኛልና ሕይወትን ጠላሁ፤ ሁሉም ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች የደከምሁበትን ሁሉ ጠላሁት። ጠቢብ ወይም ሰነፍ እንዲሆን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ከፀሐይ በታች በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ላይ ጌታ ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። እኔም ተመልሼ ልቤን ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተስፋ አስቈረጥሁት። ሰው በጥበብና በእውቀት በብልሃትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ያወርሰዋልና፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም መከራ ነው። ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ አሳብ የሰው ጥቅም ምንድር ነው? ዘመኑ ሁሉ ኀዘን፥ ጥረትም ትካዜ ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም፤ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ። ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው? እርሱም ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል፤ ለኃጢአተኛ ግን እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ጥረትን ይሰጠዋል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።
አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቍጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።
[ሉቃስ 12፡ 13-21። መዝሙር 39፡ 4-7፤ 90፡ 1-17። መክብብ 3፡1-8፤ 2፡ 1-26። ኢሳይያስ 55፡1-2፣6-7። ኢዩኤል 2፡12-13።]
4/28/2009
ርዕሰ አንቀጽ
እርካታን ለማግኘት
አንዳንድ ወቅቶች ከሌላው ይልቅ ስለ ሞትና ስለ ሕይወት አብዝተን እንድናስብ ያስገድዱናል። አብዛኛው የአገራችን ሕዝብ ከሕጻንነት እስከ ጎልማሳነት እስከ ሽበት ጥላሁን ገሠሠ ከደረደራቸው ቅኔአዊ ዜማዎች ጋር ተላምዶ ያደገ ስለሆነ ሞቱ ባሁኑ ወቅት ብሔራዊ ገጽታን ተቀዳጅቷል። ባሕላችን የምንለው፣ የሚያስተሳስረንና ከሌላው ልዩ የሚያደርገን እንግዲህ ይህም ጭምር ነው ማለት ነው።
ጥላሁን በግልና በጋራ ምኞታችንን፣ ሐዘናችንን፣ ደስታችንን በጣዕመ ዜማና በቅኔ ሲያስደምጠን ቆይቶ ተለይቶናል። “መለያየት ሞት ነው” ይለናል፤ ባንለያይና አብረን ብንኖር ምን ነበረ? እንድንል ያስገድደናል። “ዋይ ዋይ ሲሉ፣ የረሐብን ጉንፋን ሲስሉ” ይለናል፤ ረጋፊ መሆናችንን፣ እርስ በርስ እንድንራራ ያሳስበናል። ቀጠሮ እናክብር፤ ቃላችንን እንጠብቅ፤ ትዳራችን ባይፈርስ፣ ፍቅራችን ባይቀዘቅዝ እያለ ይመክረናል። ለአፍታ ችግራችንን ያረሳሳናል፤ የዘመናችንንና የመልክዐ ምድራችንን ትዝታ ይቀሰቅስብናል። በስሜታችን መስኰት ዘው ብሎ በኛ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት የአገራችን ሕዝብ በያለበት በአንድ ድምጽና በአንድ ልብ የሐዘኑ ተካፋይ ሊሆን የበቃው። ሁላችንም እኰ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን ነን።
በየድረ ገጹ የሚታየው የሐዘን መግለጫ ሁሉን አቀፍ እንደ ሆነ እንገነዘባለን። ለካንስ በአሳብና በአመለካከት የተራራቀ የሚመስለው ሕዝብ በስሜቱ የተቀራረበ ነውና! ሰውን መማረክ በስሜቱ በኩል ነው ብንል አንሳሳትም። በቅንዓትና በጥላቻ ሳይሆን በቅን መንፈስ ሕዝብን ለበጎ ማነሣሣት ምን ያህል ዘላቂነት እንዳለው እንገነዘባለን። ለዚህስ ሳይሆን ይቀራል መንግሥታት የቁጥጥር ዒላማቸውን በቅድሚያ በኪነ ጥበብ ሰዎች ላይ የሚያነጣጥሩት? ለዚህ ነው የመናገርና አሳብን የመግለጽ መብት ከሰብአዊ መብቶች ውስጥ ቀዳሚ ሥፍራ የተሰጠው!
ረሐብ ዛሬም ከኛ አልተለየም። ቀጠሮ ማክበር ነውር ሆኖብናል። ትዳርም በየቀኑ በየምክንያቱ ይፈራርሳል። ወላጅና ልጅ፣ ወዳጅና ወዳጅ ይካካዳል፣ ተለያይቷል። ገሚሱ በስደት፣ ገሚሱ በእሥራት፣ ሌላው ቅርብ እያለ በቂም ተራርቆ ይኖራል። የምንኖርባት ዓለም ሥርዓቷና የሰውም ባሕሪ ለዚህ የተመቻቸ ነው። በዚሁ ሁኔታም ውስጥ ሆኖ ሰው እንደ አቅሙ ወዳጅነት በመፍጠር፣ ኑሮውን በማደራጀት ለምድራዊ ኑሮው ትርጉም ለማግኘት ራሱንም ለማስደሰት ይጣጣራል።
ከፈጣሪው ጋር ግን ባይስማማ ብዙ ያጎድላል።
የጥላሁን ሕይወትና ሞት ያልደረስንባቸው የምንጠማቸው እውነቶች እንዳሉ ጠቋሚ ናቸው። ዘመን አላፊ ነው፤ ያለፈውን ማምጣት፣ የወደ ፊቱን ማፍጠን አንችልም። ገንዘብ ጠፊ ነው። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ማዳን አይቻለውም። ሕይወት አጭር ናት። መመኘትና ወደ እርካታ ዳርቻ መድረስ ለየቅል ናቸው። ምድራዊ ኑሮ አድካሚና ብርቱ ሰልፍ ነው። ሰው ሟች ነው፤ ሆኖም ይህን ማሰብ አይፈቅድም። ምክንያት መደርደር ይቀናዋል። የሚያረሳሳውን ይሻል። ራሱን መሸንገል፣ መሸነጋገል ያበዛል። የሞትን ቅጽበታዊነት ቢገነዘብ ግን የሕይወትን ጉዳይ አጥብቆ በፈለጋት። እንደ እርሱ ሰው ለሆነ፣ ለእንስሣውና ለዕጽዋቱ ሳይቀር ርህራሄና እንክብካቤን ባሳየ።
ረሐብ ደግሞ ምግብ መኖሩን ጠቋሚ ነው። መለያየት፣ አለመለያየትን። እሥራት፣ ነጻነትን። ሞት፣ ሕይወትን። አገሬ፣ ምድሬ የምንለው ሰማያዊ አገር መኖሩን አመልካች ነው። ተስፋ ደግሞ ምድራዊ ቢሆን ምን ይረባል? የሚታየውን ተስፋ ቢያደርግ ሰው ይሞኛል። ነፍስ ከሥጋ ይበልጣል፤ የነፍስ ረሐብ ከሥጋ ረሐብ ይበረታል። የማይታየው ዘላለማዊ ነው። ጥም መቀስቀሱ ጥሩ ጅማሬ ነው። ከጠጡ በኋላ ግን ሌላ ጥም የሚያስከትል ከሆነ ምን ፋይዳ አለው? ድካም ነው። እንደ ባዘኑ መኖር ነው፤ እንደ ባከኑ መቅረት ነው። የምድሩ ያረሳሳል እንጂ ዘላቂ እርካታና ሰላም ለማቀዳጀት አይበቃም።
አሁን ሞት አሳባችንን ይዞታል። በሌላ ጉዳይ እስኪያዝና የሚያረሳሳ እስኪመጣ። አሁን እንባ በየቤቱ ሞልቷል።
ታዲያ ሞትና ስቃይን እግዚአብሔር ወደ ራሱ እኛን ለመጥሪያ ይጠቀምባቸዋል። ሟች መሆናችንን እያወቅን፣ አብረውን የኖሩ ከአጠገባችን ሲወሰዱ እንደነግጣለን፣ እናዝናለን፣ አኳኋኑን ለመረዳት እንሞክራለን። የተወሰነ አቅም፣ የተወሰነ እውቀት እንደ ተሰጠን እንገነዘባለን። ተራው ሲደርሰን ግን ፋታ አናገኝም፤ ወረፋው መቸ እንደሚደርሰን በኛ ዘንድ የሚያውቅ የለም። ይኸ አስፈሪ ነው፤ አሳሳቢም ነው። መዘጋጀት አይቻልም ማለት ግን አይደለም። መዘጋጃውም ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። ሲቻልህ፣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ የሚለው ለዚሁ ነው። ምንም ማድረግ የማይቻልበት ሰዓትና ሁኔታ አለ ማለቱ ነው። ለአንዳንዶቻችን እንዲህ የመሰለ ብዙ እድል አይቀርልንም። ቀንህ፣ ቀንሽ ዛሬ ቢሆን በምድርና በሰማይ ምን መታሰቢያ አለህ፣ አለሽ?
ስለ ወደ ፊቱ ግን ይህ ተስፋ አለ። እርካታን ለማግኘት መፍትሔው ሰማያዊ ነውና። ተስፋ የሰጠውም ሰሞኑን ያሰብነውና ያከበርነው ሞትን ድል ነሥቶ የተነሳው ተመልሶም ለፍርድ የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የኢየሱስ ሥጋ የተቆረሰው፣ ደሙም የፈሰሰው ሰውና አምላኩን፣ ሰውና ሰውን፣ ሰውና ፍጥረትን፣ ሰውን ከራሱ ጋር ሳይቀር ለማስታረቅ ነው። በኃጢአት ምክንያት የተገነባውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ሰላምን ለማምጣት ነው። እርሱ ራሱ በወንድማቸው ሞት ላዘኑት ለማርያምና ለማርታ፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” ብሏልና።
“ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።
አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። በዙፋንም የተቀመጠው። እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም። እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ። አለኝም። ተፈጽሞአል። አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ። ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል። [ዮሐንስ 11፡ 25-26። ራእይ 20፡11-21፡ 1-7]
ላዘኑ ሁሉ እግዚአብሔር ጽናቱን ይስጣቸው።
ኢየሱስ ተነሥቶአል! ሞት ድል ተነሥቶአል!
ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ። ኢየሱስም። አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኳንንቱም ደግሞ። ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን እያሉ ያፌዙበት ነበር። ጭፍሮችም ደግሞ ወደ እርሱ ቀርበው ሆምጣጤም አምጥተው። አንተስ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን እያሉ ይዘብቱበት ነበር። ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው ተብሎ በግሪክና በሮማይስጥ በዕብራይስጥም ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ። ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ። አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ። አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም። ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው። ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ። አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ይህንም ለማየት ተከማችተው የነበሩ ሕዝብ ሁሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። የሚያውቁቱ ግን ሁሉ ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ይህን እያዩ በሩቅ ቆመው ነበር። እነሆም፥ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ አውርዶም በተልባ እግር ልብስ ከፈነው፥ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም ሊጀምር ነበረ። ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ። ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።
ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ። ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በኋላ ወደ መቃብር መጡ። እርስ በርሳቸውም። ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል? ይባባሉ ነበር፤ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ። ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን። አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም። ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው። መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ፤ ይፈሩ ነበርና ለማንም አንዳች አልነገሩም። እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው። ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ አስቀድሞ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ። እርስዋ ሄዳ ከእርሱ ጋር ሆነው ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ አወራችላቸው፤ እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም። ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ባላገር ሲሄዱ በመንገድ በሌላ መልክ ተገለጠ፤ እነርሱም ሄደው ለሌሎቹ አወሩ፤ እነዚያንም ደግሞ አላመኑአቸውም። ኋላም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ተገለጠ፥ ተነሥቶም ያዩትን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ። እንዲህም አላቸው። ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።
ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል። አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፥ የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው፥ የእንስሳም ሥጋ ሌላ ነው፥ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፥ የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው። ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፥ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው። የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና። የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። እንዲሁ ደግሞ። ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።
ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ። ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ። [ሉቃስ 23፡33-56፤ 24፡1-5፤ ማርቆስ 16፡1-15፤ 1ቆሮንቶስ 15፡ 35-58]
የሕይወት ትንሣኤ!
በፀሐይ ዓለሙ [4/15/2009]
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን ገና ሲጀምር ያደረገው ነገር ቢኖር ቤተ መቅደሱን ማጽዳት ነበር፦
ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና። ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። [ማቴዎስ 21፡12-13]
አገልግሎት ከመስጠታችን በፊት ጌታ ከኛ ሕይወት ጋር ነው መጨረስ የሚፈልገው፤ ብዙ አለመታመን፣ እጅግ ብዙ ነውር ከውስጣችን ተነቅሎ እንዲወጣ መጀመሪያ አጥርቶ ያሳየናል። እንድንገነዘበውም ያደርጋል። ከጌታው ጋር ያልታረቀ አገልጋይ ማንንም ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ወይም ማገናኘት አይችልም። ራሱ ነፃ ሳይወጣ የወንጌልን ነፃነት ማወጅ ውሸት ይሆናል። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጅራፍ አንስቶ ገሠጻቸው፤ ተቆጣ፤ ክፉ ሥራቸውንም ነቀፈ፤ ከመሠረቱም ገለባበጠው።
አንዳንዴ እኰ ስናበዛው ሕይወታችንን ለብዙ ከንቱ ነገር ስንለቀው የእግዚአብሔር መንፈስ እኛን ለማስተካከል እርምጃ ይወስዳል። ብዙ ነገር እንዲናጋብን ይፈቅዳል። ቆም ብለን እንድናስብም ያደርገናል።
የጌታን ሞትና ትንሣኤ ለምን እንደሆነ ብናስብ ለኃጢአት የሚከፈል ዋጋ ነበር። ሞትም በትንሣኤ ድል መሆን ነበረበት። ይህም ማለት ለሰው ሁሉ አዲስ የሕይወት ለውጥ እንዲሆን ለሚያምኑ ሁሉ እንዲሆንላቸው እርሱ ራሱ ሁሉን ፈጽሞ በሕይወቱ ከከፈለ በኋላ ድል አድርጎ ከሞት ተነሳ።
ሆኖም ግን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ብዙ ዘመን ኖረውም ያው የድሮው ሕይወትና ባሕሪ የሚታይባቸው ሰዎች አሉ። እንደዚያው ሆነው ይቀጥላሉ። ሳይለወጡ ከጌታም መንፈስ ጋር ሳይስማሙ ዘመናቸውን ያጨልማሉ። ለእግዚአብሔር የክብር ዕቃው ሳይሆኑለት እንደሚገባም ሳይሠራባቸው ጊዜው ያልፋል።
ዕድሜ ልክ አለመታመን ከቀጠለ ያ ሰው መቸ ነው በጌታ ተለውጦ ትንሣኤ በሕይወቱ የሚሆነው? እንዲያው እኰ ሰው ራሱን ባይገነዘብ ራሱን ያታልላል። ሁሉ ድካም ይሆንበታል። ለምንስ ይረባል?
ጌታ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ካጸዳ በኋላ “በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው” ይላል። [ማቴዎስ 21፡14] ሁልጊዜ የሕይወት ጽዳት በመንፈስ ቅዱስ በኩል በሰው ውስጥ ከተከናወነ በኋላ ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል መሥራት ይጀምራል። ለብዙዎች መዳን ምክንያት ሊያደርገን ስለሚሻ የሕይወት ትንሣኤ ሊሰጠን ፈቃዳችንን ይጠይቃል።
ለሰው ተስፋው ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ ሕይወቱን ማስማማቱ ብቻ ነው።
ለሁለት ጌታ መገዛት ከባድ ነው። ከሁለቱም አንዱን መምረጥ አስፈላጊ ነው። ሙልጭ ያለ ዓለማዊ ወይም የለየለት እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ግድ ነው። ምርጫው የባለቤቱ ነው። ጥቅሙ ለእኛ እንጂ ጌታ በራሱ የከበረ ከሆነ ምንም አንጨምርለትም። ሆኖም ወደ እርሱ ሰላምና እውነት በመመለሳችን ደስ ይለዋል፦
አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፤ በዚያም በጎነት ታገኛለህ። /ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤ /ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ /ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥ የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥ /የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥ /ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል። /የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ /ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ። /ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ /ስእለትህንም ትሰጣለህ። ነገርንም ትመክራለህ፥ እርሱም ይሳካልሃል፤ /ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል። [ኢዮብ 22፡ 22-28]
አዎ፣ እግዚአብሔር የሚሠራው እንደዚህ ነው። ሞትና ትንሣኤውም የሆነው ለእኛ ሕይወት አዲስ ልደት አዲስ ጅማሬ ለመስጠት ነው።
እኔ ሰምቼዋለሁ
ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፤/እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሩን ይሰድዳል።
ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፥ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል።
ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፤ ከእህሉም የተነሣ ይጠግባሉ፤
እንደ ወይንም አረግ ያብባሉ፤ መታሰቢያውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል።
ከእንግዲህ ወዲያ ጣዖት ለኤፍሬም ምንድር ነው? እኔ ሰምቼዋለሁ፥ /ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ /እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፤ /ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል። /ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ፥ የሚያውቃትም አስተዋይ ማን ነው? /የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው፥ ጻድቃንም ይሄዱበታል፤ /ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታል። [ሆሴዕ 14፡ 5-9]
የመጽሐፍ ግምገማ 3/30/09
ዓላማ መር ሕይወት
የመጽሐፍት ወዳጅ ለሆኑትና የክርስቶስን ወንጌል አገልግለው ወደ ጌታ ዕረፍት ለሄዱት ለወንድማችን አቶ መስፍን ተስፋዬ መታሰቢያ ይሁን።
መግቢያ
ስለ መጽሐፍት ግምገማና ትርጉም በዚሁ ድረ-ገጽ ላይ “የወንጌል ስርጭትና እስካሁን የተጓዝነው ጉዞ” በሚል ርዕስ በመጠኑ እንዲህ ብለን ጠቃቅሰን ነበር፦
ምንም እንኳ የትችት ባሕል በቤተ ክህነት ሊቃውንት ዘንድ የተለመደ ቢሆንም፣ በተለይ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ክልል የጽሑፎች ግምገማና ትችት ልምድ ይጐድላል። ትችት ሲባል ነቀፌታ እንጂ ክርስቲያናዊ ምግባር እንደሆነ አይታሰብም። ይህ ስህተት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የስነ-ጽሑፍ ትችት ለደራሲ እድገት፣ ለአንባቢ ጥቅምና ለስነ-ጽሑፍ ልማት አማራጭ የሌለውና ሊዳብር የሚገባ አገልግሎት ነው …
በመሠረቱ፣ የአንድ ጽሑፍ ግምገማ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይኖርበታል። የጽሑፉ መነሻ አላማና ዋነኛ መልእክት ባጭሩ ምንድነው? የደራሲውስ ብቃት? ጸሐፊው የተነሳበትን አላማ በሚገባ አስረድቷል? ዓይነተኛና ትክክለኛ መረጃዎችንና ምሳሌዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሟል? በዚህ ጉዳይ ላይ የማናውቀውን አዲስ መረጃ አቅርቦልናል? ሊታከል ወይም ሊታረም የሚያስፈልግ ነገር አለ? የተራ አንባቢውን የመረዳትና የባሕል አቅም እንደሚገባ ተገንዝቧል? ባጠቃላይ የጽሑፉ ጠንካራና ደካማ ጐን የቱ ላይ ነው? [በፈረንጅ አቆጣጠር ኦክቶበር 2006]
የ “ዳቪንቺ ኮድ” የተሰኘው መጽሐፍ በክርስቶስና በወንጌሉ ላይ የነዛውን መሠረተ-ቢስ ሃሳብ በማብራራትም ጽፈን ነበር። ዛሬ ደግሞ በእንግሊዝኛ ተጽፎ ወደ አማርኛ በተተረጎመ “ዓላማ መር ሕይወት” ላይ የመጀመሪያውን ግምገማችንን እንጀምራለን።
ግምገማና ገምጋሚ
ግምገማ ስንል በተሠነዘረው አሳብ ላይ ማወያየትን፣ የተዘነጋ ወይም የተዛባ ትምህርት ካለ ማከልን፣ ያልተጠቀሱ ነገር ግን የተቀራረቡ አሳቦችን ማሰባሰብን ይጨምራል። ዞሮ ዞሮ ዓላማው ማነጽ ነው:: የአንድ መጽሐፍ ደራሲ ለሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ጥንቃቄ እንዲወስድ ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን ደራሲው ራሱ ከተጠያቂነት በላይ እንዳልሆነ ማስረዳትን ይጨምራል።
ገምጋሚውም በተራው እንደ ግምገማው ጥራት መልሶ ስለሚገመገም ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል። መጠባበቅና መደጋገፍ አንደኛው ጥሪአችን ነው። ባጭሩ፣ ማኅበረ ምዕመንን የሚመለከት ጉዳይ በአንድ ሰው ወይም በጥቂቶች እጅ መተው የለበትም ለማለት ነው።
የዛሬው ግምገማችን ተራዝሞ ሌላ መጽሐፍ እንዳይወጣው በ “ዓላማ መር ሕይወት” ትርጉም ጥራት ላይ ብዙ አናተኩርም።
የመጽሐፉ ርዕስ፦ ዓላማ መር ሕይወት (በእንግሊዝኛ፦ The Purpose Driven Life) ደራሲ፦ ሪክ ዋረን:: ተርጓሚ፦ ኤቫንጄሊካል ቴዎሎጂካል ኮሌጅ፤ አዲስ አበባ። የታተመበት ዘመን፦ 1994 (በኢትዮጵያ)፤ 2002 (በፈረንጅ)። የተተረጎመበት ዘመን፦ 1997 (በኢትዮጵያ)፣ 2005 (በፈረንጅ) በአማርኛ ሦስተኛ እትም። የገጽ ብዛት 340። ገምጋሚ፦ ምትኩ አዲሱ
“ዓላማ መር ሕይወት” ‘ሳድልባክ’ በተሰኘ በካሊፎርንያ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ቤተክርስቲያን መጋቢ ሪክ ዋረን የተጻፈ መጽሐፍ ነው። እኝሁ ሰው ቀደም ሲል “በዓላማ የሚመራ ቤተክርስቲያን” የሚል ጽፈው ያስነበቡ ሲሆን ሁለቱም ከሃያ አምስት ሚሊዮን ኮፒ በላይ ተባዝተው ተሽጠዋል፤ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል። “በዓላማ የሚመራ ማኅበረሰብ” ሦስተኛውና የመጨረሻው ክፍል በቅርቡ ይታተማል ተብሎ ይጠበቃል።
“ዓላማ መር ሕይወት” የሚከተሉትን መሠረታዊ አሳቦች ያዘለ ነው፦
በምድር ላይ የተገኘህበትን ምክንያት በራስህ ጥረት መረዳት አትችልም
ፈጣሪህን እግዚአብሔርን ማወቅ ይኖርብሃል
እግዚአብሔር በዓላማ ለዓላማ ፈጥሮሃል
ዓላማ የሌለው ሕይወት ከሞት ይብሳል (ገጽ 32)
በዚህ መጽሐፍ የተካተቱትን 40 አጫጭር ምዕራፎች አንዳንድ በየቀኑ እያሰላሰልህ ብታነብ ዓላማ ያለው ደስተኛ ሕይወት ይኖረሃል የሚል ነው፤
ብዙ ሰዎች በግልና በቡድን ይህን የአርባ ቀን ጥናት ተከታትለዋል። በሩዋንዳ ደግሞ የሃይማኖትና የአገር መሪዎች ሳይቀሩ ተሳትፈውበታል። ውጤቱም እያደር መከሰቱ አይቀርም።
የትርጉም ሥራ ክብደትና ኃላፊነት
የትርጉም ሥራ ፈተናው ብዙ ነው። በመጀመሪያ፣ ተርጓሚው ቢያንስ ሁለቱን ቋንቋዎች (ለዚህኛው እንግሊዝኛና አማርኛን) አጥርቶ ማወቅ ይኖርበታል። የሁለቱን ቋንቋዎች ዘይቤ፣ ያልተገለጡ ነገር ግን የታሰቡ አሳቦችን፣ የሚተረጎምለትን ትውልድ ቋንቋና አስተሳሰብ፣ የደራሲውን ባሕል፣ ማንነትና መነሻ አሳብ፣ የአንባቢውን ዓይነትና የመረዳት አቅም፣ ዘመን የለወጠውንና ያጸናውን ባሕል፣ ወዘተ፣ ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪ፣ በአእምሮው ውስጥ አንዱ ቋንቋ ሌላኛውን እንዳይበርዝ፣ እንዳይቆጣጠር መጠንቀቅ ይኖርበታል። አለበለዚያ ትርጉሙ የደራሲውን አሳብ በታማኝነት ሳያቀርብ ይቀራል፤ ሲብስም ለአንባቢው የፈረንጅ አማርኛ ይሆንበታል።
በመጨረሻም፣ ተርጓሚው አሜሪካዊ ክርስትና በአብዛኛው ባሕላዊ ክርስትና እንደሆነ ማስታወስ ይኖርበታል። ባሕላዊ ስንል ዲሞክራሲያዊ ባሕልና አስተሳሰብ የሠረጸበት ማለታችን ነው፤ የገበያ ኃይላት የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ማለታችን ነው። ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ደግሞ ሁሉም እኩል እንደ ሆነ አድርጎ ማየትን የሚያገንን ነው። ይህ በአንድ ፊቱ መልካም ቢመስልም “እውነት እንደ አመለካከት ነው” ስለሚል በጥርጣሬ ሊታይ ይገባል። “ይኸ ስሕተት ነው፣ ይኸ ትክክል ነው” ብሎ ማለት የሰውን መብት መጋፋት ነው ስለሚል ልኩንና ስሕተቱን መለየት ያዳግተዋል፤ መድፈር ያቅተዋል። ፈተናው ብዙ ነው ያልነው ለዚህ ነው። ሌላ ሊዘነጋ የማይገባ ነገር ባሕላችን ከምዕራቡ ባሕል ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ለተጻፈበት ቋንቋና ባሕል የቀረበ መሆኑን ነው። ታዲያ ከሌሎች አንማርም አንልም። መማር ደግሞ የሌሎችን ልምድና አስተሳሰብ መዝኖ ከራስ ሁኔታ ጋር ማዛመድን ይጠይቃል። የትርጉም ሥራ ፈተናው ብዙ ነው፤ ጥቅሙም እንደዚሁ። የትርጉምን ሥራ ጥቅም መገንዘብ የምንችለው በተለይ ተተርጉሞ በእጃችን ያለውን ዘላለማዊውን ወንጌል ስናስብ ነው።
የ”ዓላማ መር ሕይወት” ተርጓሚዎች ስላደረጉት ጥረት ሊመሰገኑና ሊበረታቱ ይገባል። ጥረታቸው ግን በተተረጎመለት አንባቢ አስተያየት ካልታገዘ የታሰበለትን ግብ እንደሚገባ አይመታም፤ ወደ ፊት የሚያደርጉትን የትርጉም ሥራ ጥራት ያጓድላል። ማወያየትና ማሳሰብ የአንድ መጽሐፍ አንዱና ዋነኛ ተግባር ነውና።
ተርጓሚዎቹ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ደራሲው ከተጠቀሙባቸው ትርጉሞች ይልቅ ከተተረጎመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለመቅዳት መወሰናቸው ተገቢና ትክክለኛ ቅድመ ውሳኔ ነው። ይህን ያደረጉበት ምክንያት ምናልባት እንደ እንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን የአማርኛ ትርጉሞች ከሦስት ያልበለጡ ስለሆነም ሊሆን ይችላል።
ሪክ ዋረን “ዓላማ” የምትለዋን ቃልና ሐረግ ለሚጠቀሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቅድሚያ ሰጥተዋል። ደራሲው የመረጧቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአብዛኛው ማብራርያ እንጂ መሠረተ ቃሉን የሚገነዘቡ ትርጉሞች አይደሉም። ጥሬ ቃሎችን እንዳሉ ከመተው ይልቅ ለአንባቢያን ባሕል በሚስማሙ አባባሎች ላይ አተኩረዋል። ስለሆነም፣ ቃሎቹ በቀደመው አገባባቸው የያዙትን የእውነት ክብደት ሲያሳሱና ሲበርዙ ይታያሉ።
ደራሲው ከሺህ በላይ ጥቅሶችን ተጠቅመዋል። ለምሳሌ፦ ሮሜ ምዕራፍ 8ቁጥር 6 ላይ የተጠቀሰውን ደራሲው ከተጠቀሙበትና ከመደበኛው አማርኛ ትርጉም ጋር እናስተያይ፤
በአዲሱ መደበኛ ትርጉም፦
“የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው” (ገጽ 18)።
ደራሲው መደበኛና ብዙ ሊቃናት የተረጎሟቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን “ዘ ሜሴጅ” የሚለውን የአንድ አሜሪካዊ ግለሰብ የማብራርያ ትርጉም ተጠቅመዋል፤ ጥቅሱ ሲተረጎም እንደዚህ ይላል፦
“በገዛ ራስ ላይ ማተኮር አያዘልቅም፤ እግዚአብሔርን ማሰብ ግን ወደ ሰፊ ሥፍራና ወደ ነጻ ሕይወት ይመራል፤” [ትርጉም የኔ]
የደራሲው ትኩረት “ሕይወት ይመራል” የሚለው ሐረግ ላይ እንደ ሆነ እንረዳለን። ከዚህም የተነሳ ሥጋዊነትና ሥጋዊ ክርስትና ሞትና የሞትን ሥራ እንደሚያተርፍ ሳያስታውቀን እንደቀረ እንመለከታለን።
ቃል በቃል ወይስ አሳብ በአሳብ?
ተርጓሚዎቹ ለደራሲው ሥራ ታማኝ ለመሆን ከመፈለጋቸው የተነሳ ይመስላል “አሳብን በአሳብ” ሳይሆን ቃልን በቃል ተርጉመዋል። ይህ ዘዴ የራሱ የሆነ ችግር አለው።
1. ከርዕሱ እንጀምር፦
Purpose = ዓላማ። Driven = መር። Life = ሕይወት። Purpose Driven Life= ዓላማ መር ሕይወት ተብሏል። [“በዓላማ የሚመራ ሕይወት” ወይም “ዓላማ ያለው ሕይወት” ወይም “እግዚአብሔር የሚመራው ሕይወት” ለምን እንዳላሉ ግልጽ አይደለም]
2. በመጽሐፉ ሽፋንና ገጾች ላይ “ኦክ” የሚሉት ዛፍ ምስል ተመልክቷል። “ኦክ” በሰሜን አውሮጳና በሰሜን አሜሪካ ብቻ የሚበቅል ዛፍ ነው። ለአገራችን አንባቢ ምን ትርጉም ይሰጣል? ወይስ ትርጉም መስጠቱ አላስፈለገም? አንድን አሳብ ካለው እውነታ ጋር ሳናገናዝብ እንዳለ ስለ መቀበል ይህ ምን ያስተምረናል? ደራሲው ወይም አሳታሚው ምንም ሳይለወጥ ይተርጎም ብለው ከሆነ ትልቅ ስህተት ብቻ ሳይሆን ያልተገባ ተጽዕኖ ነው እንላለን።
የመጽሐፉ መግነን
መጽሐፉ የማናውቀውን እውነት አይነግረንም። ስለ ደረስንበት እውነትና ልምምድ ስናወራ የቀደሙን ሊኖሩ እንደሚችሉም ማሰብ ከብዙ ድካም ያድናል። አንዳንዴ አንድን ሁኔታ ወይም አሳብ ልዩ የሚያስመስለው አገላለጽ እንጂ መሠረተ አሳብ እንዳልሆነ ሳንገነዘብ አንቀርም።
ሰው ሆኖ የተፈጠረ ሁሉ ‘ለምን ምድር ላይ ተገኘሁ?’ ማለቱ አይቀርም። በመሰለው መንገድ ለዚህ ፍለጋው መልስ ይሻል። መልሱ ግን ለየግለሰቡና ለየማኅበራቱ ተመሳሳይ ውጤት ይኖረዋል ማለት አይደለም።
ታዲያ መጽሐፉ እንዴት እንዲህ ሊገንን ቻለ? ብለን ልንጠይቅ ይገባል።
አንደኛው፦ ወቅቱ የሚፈልገው በመሆኑ ነው። መጽሐፉ የታተመው አልቃይዳ በአሜሪካ ላይ ጥቃት አድርሶ ብዙ ንብረትና ሦስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ሕይወት ባጠፋበት ሰሞን ነው። የአሜሪካን ሕዝብና መንግሥት ከርቀት በሌሎች ላይ ሲደርስ እንጂ እቤት ድረስ ይህን መሳይ መዓት ይመጣል ብለው አልጠበቁም። እግዚአብሔር ለዓላማው የመረጠን ቸርና መልካም ሕዝብ ነን የሚል አስተሳሰብ ሠርጾ የኖረ ስለሆነ፣ እግዚአብሔር እንዴት በኛ ላይ ይህን ፈቀደ? የታመንበት የጦር ኃይላችንና ብልጽግናችን እንዲህ የሚፈራርስ ከሆነ፣ ኃይላችን የማይመክተው ሌላ ኃይል ካለ፣ እንግዲህ የሚያስተማምን ምን ይኖራል? ሕይወት ይኸው ነው ማለት ነው? አደጋው በወቅቱ ይህን መሰል ጥያቄ አስከትሎ ነበር። ወደ ቤተ አምልኮ የሚጎርፈውም ሰው ብዛት በጣም የጨመረበት ሰዓት ነበረ። የአልቃይዳስ ጥቃት ባይከሰት መጻሕፍቱ ይህን ያህል ይገንኑ ነበር?
ሁለተኛው፦ አቀራረቡ አንባቢን ሳይለይ በማግባባት ላይ ያተኮረ ስለሆነ ነው። ጌታ በድካማችን እንጂ በብቃታችን ሥራውን ሠርቶ አያውቅምና በዚህም እንኳ ወደ መንግሥቱ የሚገቡ አሉ።
የመጽሐፉ አቀራረብ እንግዲህ፦ ሀ) ለሚያምኑ፣ ለ) በእምነታቸው ገና ለሆኑ፣ ሐ) ለማያምኑም ጭምር ታስቦ እንደ ተጻፈ እንመለከታለን። ታዲያ ችግሩ ሁሉን ለማቀፍ መሞከሩ ላይ ነው። አግባብቶ ቤተክርስቲያን ደጅ ለማድረስ መጣሩ ላይ ነው። ያደፋፍራል እንጂ ደፍሮ በቀጥታ አያስተምርም። ለምሳሌ፦ ጌታ ኢየሱስ በወንጌላት ውስጥ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ” ብሎ ያዘዛቸው “የመካከለኛው ምሥራቅ ደቀመዛሙርት” ተብለዋል፣ (ገጽ 313)። እስከምናውቀው ደቀመዛሙርት ከመካከለኛው ምሥራቅ ይሁኑ እንጂ ያው “አይሁድ” ናቸው። እንግዲህ ደራሲው “አይሁድ” ላለማለት የወሰኑት ይህን የማይፈቅዱ ስላሉ እነርሱን ለማግባባት እንደ ሆነ እንገነዘባለን። ኢየሱስ ለሰማርያዊቱ ሴት (ዮሐንስ 4፡ 22) “እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፣ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን” ማለቱ እንዴት ይተርጎም? ሰዎችን ወንጌል እንዲሰሙ ማግባባት መልካም ነው። ግን ስንቱን እውነት ሸንሽኖ ይዘልቃል?!
ሦስተኛ፦ የአታሚ ድርጅቶች፣ የማስታወቂያ ድርጅቶች፣ አሻሻጮች ሁሉም በየፊናቸው ገበያው ከሚያመነጨው ለመቋደስ መሯሯጣቸው ነው። ይህን ያልነው እውነት በሺያጭ ብዛትና በዝና አይለካም የሚለውን ለማጽናት ነው።
አራተኛ፦ ያለፉትን ስምንት ዓመታት በአሜሪካ የገዛው የረፐብሊካን ፓርቲ አስተዳደርና የ “ኤቫንጄሊካልስ” በዓላማ መሰባጠር የቤተክርስቲያንና የቤተ መንግሥትን ድንበር ኩታ ገጠም ከማድረግ አልፎ አደብዝዞታል። ይህን የመሰለ አጋጣሚ መጠቀም ያወቁበት የመጽሐፍትን መደርደርያዎች በመላ ምታቸውና ልብ በሚሠርቁ፣ ጆሮ በሚስቡ ውለው ሲያድሩ ግን በሚረሱ ቁም ነገር አልባ ታሪኮች ሲያጣብቡ ሰንብተዋል። ለምሳሌ ያህል ሦስት ጻሕፍትን እንጥራ።
የመጀመሪያው በ ቲም ላሃይ የተደረሱ ተከታታይ “ሌፍት ቢሃይንድ” መጻሕፍት ናቸው። እነዚህም ጌታ ሲመጣ ያመኑቱ ይነጠቃሉ የሚለውን አስተምህሮ በልበ ወለድ መልክ ይተርካሉ። መጽሐፍቱ ተወዳጅነት ያተረፉበት ዋነኛው ምክንያት ፈተና ቢኖርም እኛን አያገኘንም ጥለነው እናመልጣለን የሚለውን በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጀመረ ትምህርት ስለሚያገንን ነው። በእምነት ምክንያት መሰደድንና የክርስቶስ ቤተክርስቲያን የምታልፍበትን መከራ በወሬ እንጂ በልምድ የማያውቅ ስለሆነ አብዛኛው ምድራዊ ምቾቱን ጭኖ ቤተክርስቲያን ገብቷል።
የአሜሪካን ሕዝብ ክርስቲያን ነኝ ይላል። ለምሳሌ፦ “ባርና ግሩፕ” የተሰኘ የሕዝብ አስተያየት አጠናቃሪ ድርጅት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2006 ባደረገው ጥናት ከአሜሪካ ሕዝብ መካከል ከመቶ እጅ ሠላሳ ስምንቱ ወንጌል አማኝ ነኝ ይላል። አማኝ ነኝ ከሚለው ውስጥ ደግሞ ሩቡ የጌታ አዳኝነት እንኳ ያልገባው ነው። ታዲያ ከዚሁ ውስጥ ዘጠኙ እጅ ብቻ ነው የወንጌልን መሠረተ እምነት የሚቀበል። የወንጌል መሠረተ እምነት ስንል ኢየሱስ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው መሆኑን፤ ከቅድስትና ድንግል ማርያም መወለዱን፤ በመስቀል ላይ በመሞቱ የኃጢአት ዕዳ መከፈሉን፤ ትንሣኤው ለሚያምኑት ጽድቅ ማጎናጸፉን፣ የእግዚአብሔር ቃል እውነተኛ፣ ሕያውና ፍጹም መሆኑን፣ ወዘተ፣ ማለታችን ነው።
ሁለተኛው መጽሐፍ፦ “ዘ ፕሬየር ኦፍ ጄቤዝ” የተሰኘ በብሩስ ዊልክንሰን የተደረሰ ትንሽ መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ ትኩረት ያቤጽ በአንደኛ ዜና 4፡10 ላይ “እባክህ መባረክን ባርከኝ” ብሎ የጸለየውንና ባርኮቱን ይመለከታል። ደራሲውም ሲያስረዳን ይህንን ጸሎት በየቀኑ ደጋግሞ የሚጸልይ ደስታና ብልጽግናን ያገኛል ይለናል።
ሦስተኛው ይኸው የምንገመግመው የሪክ ዋረን “ዓላማ መር ሕይወት” ነው። ሦስቱም ዓለም አቀፋዊ ራእይ አላቸው። ሦስቱም እጅግ ባለ ጸጎችና ተናግረው የሚደመጡ ሆነዋል፤ ከመን