ዓላማ መር ሕይወት

የክርስቶስን ወንጌል አገልግለው ወደ ጌታ ለሄዱት ለወንድማችን ለአቶ መስፍን ተስፋዬ መታሰቢያ ይሁን 

purpose-cov-crስለ መጽሐፍት ግምገማና ትርጉም በዚሁ ድረ-ገጽ ላይ “የወንጌል ስርጭትና እስካሁን የተጓዝነው ጉዞ” በሚል ርዕስ በመጠኑ እንዲህ ብለን ጠቃቅሰን ነበር፦ “ምንም እንኳ የትችት ባሕል በቤተ ክህነት ሊቃውንት ዘንድ የተለመደ ቢሆንም፣ በተለይ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ክልል የጽሑፎች ግምገማና ትችት ልምድ ይጐድላል። ትችት ሲባል ነቀፌታ እንጂ ክርስቲያናዊ ምግባር እንደሆነ አይታሰብም። ይህ ስህተት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የስነ-ጽሑፍ ትችት ለደራሲ እድገት፣ ለአንባቢ ጥቅምና ለስነ-ጽሑፍ ልማት አማራጭ የሌለውና ሊዳብር የሚገባ አገልግሎት ነው … በመሠረቱ፣ የአንድ ጽሑፍ ግምገማ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይኖርበታል። የጽሑፉ መነሻ አላማና ዋነኛ መልእክት ባጭሩ ምንድነው? የደራሲውስ ብቃት? ጸሐፊው የተነሳበትን አላማ በሚገባ አስረድቷል? ዓይነተኛና ትክክለኛ መረጃዎችንና ምሳሌዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሟል? በዚህ ጉዳይ ላይ የማናውቀውን አዲስ መረጃ አቅርቦልናል? ሊታከል ወይም ሊታረም የሚያስፈልግ ነገር አለ? የተራ አንባቢውን የመረዳትና የባሕል አቅም እንደሚገባ ተገንዝቧል? ባጠቃላይ የጽሑፉ ጠንካራና ደካማ ጐን የቱ ላይ ነው?” [በፈረንጅ አቆጣጠር ኦክቶበር 2006]

የ “ዳቪንቺ ኮድ” የተሰኘው መጽሐፍ በክርስቶስና በወንጌሉ ላይ የነዛውን መሠረተ-ቢስ ሃሳብ በማብራራትም ጽፈን ነበር። ዛሬ ደግሞ በእንግሊዝኛ ተጽፎ ወደ አማርኛ በተተረጎመ “ዓላማ መር ሕይወት” ላይ የመጀመሪያውን ግምገማችንን እንጀምራለን።

ግምገማና ገምጋሚ፦ ግምገማ ስንል በተሠነዘረው አሳብ ላይ ማወያየትን፣ የተዘነጋ ወይም የተዛባ ትምህርት ካለ ማከልን፣ ያልተጠቀሱ ነገር ግን የተቀራረቡ አሳቦችን ማሰባሰብን ይጨምራል። ዞሮ ዞሮ ዓላማው ማነጽ ነው። የአንድ መጽሐፍ ደራሲ ለሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ጥንቃቄ እንዲወስድ ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን ደራሲው ራሱ ከተጠያቂነት በላይ እንዳልሆነ ማስረዳትን ይጨምራል። ገምጋሚውም በተራው እንደ ግምገማው ጥራት መልሶ ስለሚገመገም ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል። መጠባበቅና መደጋገፍ አንደኛው ጥሪአችን ነው። ባጭሩ፣ ማኅበረ ምዕመንን የሚመለከት ጉዳይ በአንድ ሰው ወይም በጥቂቶች እጅ መተው የለበትም። የዛሬው ግምገማችን ተራዝሞ ሌላ መጽሐፍ እንዳይወጣው በማሰብ በ “ዓላማ መር ሕይወት” ትርጉም ጥራት ላይ ብዙ አናተኩርም።

የመጽሐፉ ርዕስ፦ ዓላማ መር ሕይወት (በእንግሊዝኛ፦ The Purpose Driven Life) | ደራሲ፦ ሪክ ዋረን። ተርጓሚ፦ ኤቫንጄሊካል ቴዎሎጂካል ኮሌጅ፤ አዲስ አበባ | የታተመበት ዘመን፦ 1994 (በኢትዮጵያ)፤ 2002 (በፈረንጅ)።|    የተተረጎመበት ዘመን፦ 1997 (በኢትዮጵያ)፣ 2005 (በፈረንጅ) | በአማርኛ ሦስተኛ እትም። የገጽ ብዛት 340። ገምጋሚ፦ ምትኩ አዲሱ 

“ዓላማ መር ሕይወት” ‘ሳድልባክ’ በተሰኘ በካሊፎርንያ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ቤተክርስቲያን መጋቢ ሪክ ዋረን የተጻፈ መጽሐፍ ነው። እኝሁ ሰው ቀደም ሲል “በዓላማ የሚመራ ቤተክርስቲያን”ን ያስነበቡ ሲሆን ሁለቱም ከሃያ አምስት ሚሊዮን ኮፒ በላይ ተሽጠዋል፤ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል። “በዓላማ የሚመራ ማኅበረሰብ” ሦስተኛውና የመጨረሻው ክፍል በቅርቡ ይታተማል ተብሎአል። “ዓላማ መር ሕይወት” የሚከተሉትን መሠረታዊ አሳቦች ያዘለ ነው፦

በምድር ላይ የተገኘህበትን ምክንያት በራስህ ጥረት መረዳት አትችልም፤ ፈጣሪህን እግዚአብሔርን ማወቅ ይኖርብሃል | እግዚአብሔር በዓላማ ለዓላማ ፈጥሮሃል | ዓላማ የሌለው ሕይወት ከሞት ይብሳል(ገጽ32) | በዚህ መጽሐፍ የተካተቱትን 40 አጫጭር ምዕራፎች አንዳንድ በየቀኑ እያሰላሰልህ| ብታነብባቸው ዓላማ ያለው ደስተኛ ሕይወት ይኖረሃል፣ የሚል ነው። ብዙ ሰዎች በግልና በቡድን ይህን የአርባ ቀን ጥናት ተከታትለዋል። በሩዋንዳ ደግሞ የሃይማኖትና የአገር መሪዎች ሳይቀሩ ተሳትፈውበታል። ውጤቱም እያደር መከሰቱ አይቀርም። 

የትርጉም ሥራ ክብደትና ኃላፊነት፦ የትርጉም ሥራ ፈተናው ብዙ ነው። በመጀመሪያ፣ ተርጓሚው ቢያንስ ሁለቱን ቋንቋዎች (ለዚህኛው እንግሊዝኛና አማርኛን) አጥርቶ ማወቅ ይኖርበታል። የሁለቱን ቋንቋዎች ዘይቤ፣ ያልተገለጡ ነገር ግን የታሰቡ አሳቦችን፣ የሚተረጎምለትን ትውልድ ቋንቋና አስተሳሰብ፣ የደራሲውን ባሕል፣ ማንነትና መነሻ አሳብ፣ የአንባቢውን ዓይነትና የመረዳት አቅም፣ ዘመን የለወጠውንና ያጸናውን ባሕል፣ ወዘተ፣ ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪ፣ በአእምሮው ውስጥ አንዱ ቋንቋ ሌላኛውን እንዳይበርዝ፣ እንዳይቆጣጠር መጠንቀቅ ይኖርበታል። አለበለዚያ ትርጉሙ የደራሲውን አሳብ በታማኝነት ሳያቀርብ ይቀራል፤ ሲብስም ለአንባቢው የፈረንጅ አማርኛ ይሆንበታል።

በመጨረሻም፣ ተርጓሚው አሜሪካዊ ክርስትና በአብዛኛው ባሕላዊ ክርስትና እንደሆነ ማስታወስ ይኖርበታል። ባሕላዊ ስንል ዲሞክራሲያዊ ባሕልና አስተሳሰብ የሠረጸበት ማለታችን ነው፤ የገበያ ኃይላት የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ማለታችን ነው። ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ደግሞ ሁሉም እኩል እንደ ሆነ አድርጎ ማየትን የሚያገንን ነው። ይህ በአንድ ፊቱ መልካም ቢመስልም “እውነት እንደ አመለካከት ነው” ስለሚል በጥርጣሬ ሊታይ ይገባል። “ይኸ ስሕተት ነው፣ ይኸ ትክክል ነው” ማለት የሰውን መብት መጋፋት ስለሚሆንበት ልኩንና ስሕተቱን መለየት ያዳግተዋል፤ መድፈር ያቅተዋል። ፈተናው ብዙ ነው ያልነው ለዚህ ነው። ሌላ ሊዘነጋ የማይገባ ነገር ባሕላችን ከምዕራቡ ባሕል ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ለተጻፈበት ቋንቋና ባሕል የቀረበ መሆኑን ነው። ታዲያ ከሌሎች አንማርም አንልም። መማር ደግሞ የሌሎችን ልምድና አስተሳሰብ መዝኖ ከራስ ሁኔታ ጋር ማዛመድን ይጠይቃል። የትርጉም ሥራ ፈተናው ብዙ ነው፤ ጥቅሙም እንደዚሁ። የትርጉምን ሥራ ጥቅም መገንዘብ የምንችለው በተለይ ተተርጉሞ በእጃችን ያለውን ዘላለማዊውን ወንጌል ስናስብ ነው።

የ”ዓላማ መር ሕይወት” ተርጓሚዎች ስላደረጉት ጥረት ሊመሰገኑና ሊበረታቱ ይገባል። ጥረታቸው ግን በተተረጎመለት አንባቢ አስተያየት ካልታገዘ የታሰበለትን ግብ እንደሚገባ አይመታም፤ ወደ ፊት የሚያደርጉትን የትርጉም ሥራ ጥራት ያጓድላል። ማወያየትና ማሳሰብ የአንድ መጽሐፍ አንዱና ዋነኛ ተግባር ነውና። ተርጓሚዎቹ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ደራሲው ከተጠቀሙባቸው ትርጉሞች ይልቅ ከተተረጎመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለመቅዳት መወሰናቸው ተገቢና ትክክለኛ ቅድመ ውሳኔ ነው። ይህን ያደረጉበት ምክንያት ምናልባት እንደ እንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን የአማርኛ ትርጉሞች ከሦስት ያልበለጡ ስለሆነም ሊሆን ይችላል።

ሪክ ዋረን “ዓላማ” የምትለዋን ቃልና ሐረግ ለሚጠቀሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቅድሚያ ሰጥተዋል። ደራሲው የመረጧቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአብዛኛው ማብራርያ እንጂ መሠረተ ቃሉን የሚገነዘቡ ትርጉሞች አይደሉም። ጥሬ ቃሎችን እንዳሉ ከመተው ይልቅ ለአንባቢያን ባሕል በሚስማሙ አባባሎች ላይ አተኩረዋል። ስለሆነም፣ ቃሎቹ በቀደመው አገባባቸው የያዙትን የእውነት ክብደት ሲያሳሱና ሲበርዙ ይታያሉ።

ደራሲው ከሺህ በላይ ጥቅሶችን ተጠቅመዋል። ለምሳሌ፦ ሮሜ ምዕራፍ 8ቁጥር 6 ላይ የተጠቀሰውን ደራሲው ከተጠቀሙበትና ከመደበኛው አማርኛ ትርጉም ጋር እናስተያይ፤

በአዲሱ መደበኛ ትርጉም፦ “የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው” (ገጽ 18)፤ ደራሲው መደበኛና ብዙ ሊቃናት የተረጎሟቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን “ዘ ሜሴጅ” የሚለውን የአንድ አሜሪካዊ ግለሰብ የማብራርያ ትርጉም ተጠቅመዋል፤ ጥቅሱ ሲተረጎም እንደዚህ ይላል፦ “በገዛ ራስ ላይ ማተኮር አያዘልቅም፤ እግዚአብሔርን ማሰብ ግን ወደ ሰፊ ሥፍራና ወደ ነጻ ሕይወት ይመራል፤” [ትርጉም የኔ] የደራሲው ትኩረት “ሕይወት ይመራል” የሚለው ሐረግ ላይ እንደ ሆነ እንረዳለን። ከዚህም የተነሳ ሥጋዊነትና ሥጋዊ ክርስትና ሞትና የሞትን ሥራ እንደሚያተርፍ ሳያስታውቀን እንደቀረ እንመለከታለን።

ቃል በቃል ወይስ አሳብበ አሳብ? ተርጓሚዎቹ ለደራሲው ሥራ ታማኝ ለመሆን ከመፈለጋቸው የተነሳ ይመስላል “አሳብን በአሳብ” ሳይሆን ቃልን በቃል ተርጉመዋል። ይህ ዘዴ የራሱ የሆነ ችግር አለው።

1. ከርዕሱ እንጀምር፦ Purpose = ዓላማ፤ Driven = መር፤ Life = ሕይወት Purpose Driven Life= ዓላማ መር ሕይወት ተብሏል። [“በዓላማ የሚመራ ሕይወት” ወይም “ዓላማ ያለው ሕይወት” ወይም “እግዚአብሔር የሚመራው ሕይወት” ለምን እንዳላሉ ግልጽ አይደለም]

2. በመጽሐፉ ሽፋንና ገጾች ላይ “ኦክ” የሚሉት ዛፍ ምስል ተመልክቷል። የተመለከተው “ኦክ” በሰሜን አውሮጳና በሰሜን አሜሪካ ብቻ የሚበቅል ዛፍ ነው። ለአገራችን አንባቢ ምን ትርጉም ይሰጣል? ወይስ ትርጉም መስጠቱ አላስፈለገም? አንድን አሳብ ካለው እውነታ ጋር ሳናገናዝብ እንዳለ ስለ መቀበል ይህ ምን ያስተምረናል? ደራሲው ወይም አሳታሚው ምንም ሳይለወጥ ይተርጎም ብለው ከሆነ ትልቅ ስህተት ብቻ ሳይሆን ያልተገባ ተጽዕኖ ነው እንላለን። 

የመጽሐፉ መግነን፦ መጽሐፉ የማናውቀውን እውነት አይነግረንም። ስለ ደረስንበት እውነትና ልምምድ ስናወራ የቀደሙን ሊኖሩ እንደሚችሉም ማሰብ ከብዙ ድካም ያድናል። አንዳንዴ አንድን ሁኔታ ወይም አሳብ ልዩ የሚያስመስለው አገላለጽ እንጂ መሠረተ አሳብ እንዳልሆነ ሳንገነዘብ አንቀርም። ሰው ሆኖ የተፈጠረ ሁሉ ‘ለምን ምድር ላይ ተገኘሁ?’ ማለቱ አይቀርም። በመሰለው መንገድ ለዚህ ፍለጋው መልስ ይሻል። መልሱ ግን ለየግለሰቡና ለየማኅበራቱ ተመሳሳይ ውጤት ይኖረዋል ማለት አይደለም።

ታዲያ መጽሐፉ እንዴት እንዲህ ሊገንን ቻለ? ብለን ልንጠይቅ ይገባል። አንደኛው፦ ወቅቱ የሚፈልገው በመሆኑ ነው። መጽሐፉ የታተመው አልቃይዳ በአሜሪካ ላይ ጥቃት አድርሶ ብዙ ንብረትና ሦስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ሕይወት ባጠፋበት ሰሞን ነው። የአሜሪካን ሕዝብና መንግሥት ከርቀት በሌሎች ላይ ሲደርስ እንጂ እቤት ድረስ ይህን መሳይ መዓት ይመጣል ብለው አልጠበቁም። እግዚአብሔር ለዓላማው የመረጠን ቸርና መልካም ሕዝብ ነን የሚል አስተሳሰብ ሠርጾ የኖረ ስለሆነ፣ እግዚአብሔር እንዴት በኛ ላይ ይህን ፈቀደ? የታመንበት የጦር ኃይላችንና ብልጽግናችን እንዲህ የሚፈራርስ ከሆነ፣ ኃይላችን የማይመክተው ሌላ ኃይል ካለ፣ እንግዲህ የሚያስተማምን ምን ይኖራል? ሕይወት ይኸው ነው ማለት ነው? አደጋው በወቅቱ ይህን መሰል ጥያቄ አስከትሎ ነበር። ወደ ቤተ አምልኮ የሚጎርፈውም ሰው ብዛት በጣም የጨመረበት ሰዓት ነበረ። የአልቃይዳስ ጥቃት ባይከሰት መጻሕፍቱ ይህን ያህል ይገንኑ ነበር? ሁለተኛው፦ አቀራረቡ አንባቢን ሳይለይ በማግባባት ላይ ያተኮረ ስለሆነ ነው። ጌታ በድካማችን እንጂ በብቃታችን ሥራውን ሠርቶ አያውቅምና በዚህም እንኳ ወደ መንግሥቱ የሚገቡ አሉ። 

የመጽሐፉ አቀራረብ እንግዲህ፦ ሀ) ለሚያምኑ፣ ለ) በእምነታቸው ገና ለሆኑ፣ ሐ) ለማያምኑም ጭምር ታስቦ እንደ ተጻፈ እንመለከታለን። ታዲያ ችግሩ ሁሉን ለማቀፍ መሞከሩ ላይ ነው። አግባብቶ ቤተክርስቲያን ደጅ ለማድረስ መጣሩ ላይ ነው። ያደፋፍራል እንጂ ደፍሮ በቀጥታ አያስተምርም። ለምሳሌ፦ ጌታ ኢየሱስ በወንጌላት ውስጥ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ” ብሎ ያዘዛቸው “የመካከለኛው ምሥራቅ ደቀመዛሙርት” ተብለዋል፣ (ገጽ 313)። እስከምናውቀው ደቀመዛሙርት ከመካከለኛው ምሥራቅ ይሁኑ እንጂ ያው “አይሁድ” ናቸው። እንግዲህ ደራሲው “አይሁድ” ላለማለት የወሰኑት ይህን የማይፈቅዱ ስላሉ እነርሱን ለማግባባት እንደ ሆነ እንገነዘባለን። ኢየሱስ ለሰማርያዊቱ ሴት (ዮሐንስ 4፡ 22) “እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፣ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን” ማለቱ እንዴት ይተርጎም? ሰዎችን ወንጌል እንዲሰሙ ማግባባት መልካም ነው። ግን ስንቱን እውነት ሸንሽኖ ይዘልቃል?! ሦስተኛ፦ የአታሚ ድርጅቶች፣ የማስታወቂያ ድርጅቶች፣ አሻሻጮች ሁሉም በየፊናቸው ገበያው ከሚያመነጨው ለመቋደስ መሯሯጣቸው ነው። ይህን ያልነው እውነት በሺያጭ ብዛትና በዝና አይለካም የሚለውን ለማጽናት ነው። አራተኛ፦ ያለፉትን ስምንት ዓመታት በአሜሪካ የገዛው የረፐብሊካን ፓርቲ አስተዳደርና የ “ኤቫንጄሊካልስ” በዓላማ መሰባጠር የቤተክርስቲያንና የቤተ መንግሥትን ድንበር ኩታ ገጠም ከማድረግ አልፎ አደብዝዞታል። ይህን የመሰለ አጋጣሚ መጠቀም ያወቁበት የመጽሐፍትን መደርደርያዎች በመላ ምታቸውና ልብ በሚሠርቁ፣ ጆሮ በሚስቡ ውለው ሲያድሩ ግን በሚረሱ ቁም ነገር አልባ ታሪኮች ሲያጣብቡ ሰንብተዋል። ለምሳሌ ያህል ሦስት ጻሕፍትን እንጥራ።

የመጀመሪያው በ ቲም ላሄይ የተደረሱ ተከታታይ “ሌፍት ቢሃይንድ” መጻሕፍት ናቸው። እነዚህም ጌታ ሲመጣ ያመኑቱ ይነጠቃሉ የሚለውን አስተምህሮ በልበ ወለድ መልክ ይተርካሉ። መጽሐፍቱ ተወዳጅነት ያተረፉበት ዋነኛው ምክንያት ፈተና ቢኖርም እኛን አያገኘንም ጥለነው እናመልጣለን የሚለውን በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጀመረ ትምህርት ስለሚያገንን ነው። በእምነት ምክንያት መሰደድንና የክርስቶስ ቤተክርስቲያን የምታልፍበትን መከራ በወሬ እንጂ በልምድ የማያውቅ ስለሆነ አብዛኛው ምድራዊ ምቾቱን ጭኖ ቤተክርስቲያን ገብቷል።

የአሜሪካን ሕዝብ ክርስቲያን ነኝ ይላል። ለምሳሌ፦ “ባርና ግሩፕ” የተሰኘ የሕዝብ አስተያየት አጠናቃሪ ድርጅት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2006 ባደረገው ጥናት ከአሜሪካ ሕዝብ መካከል ከመቶ እጅ ሠላሳ ስምንቱ ወንጌል አማኝ ነኝ ይላል። አማኝ ነኝ ከሚለው ውስጥ ደግሞ ሩቡ የጌታ አዳኝነት እንኳ ያልገባው ነው። ታዲያ ከዚሁ ውስጥ ዘጠኙ እጅ ብቻ ነው የወንጌልን መሠረተ እምነት የሚቀበል።  የወንጌል መሠረተ እምነት ስንል ኢየሱስ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው መሆኑን፤ ከቅድስትና ድንግል ማርያም መወለዱን፤ በመስቀል ላይ በመሞቱ የኃጢአት ዕዳ መከፈሉን፤ ትንሣኤው ለሚያምኑት ጽድቅ ማጎናጸፉን፣ የእግዚአብሔር ቃል እውነተኛ፣ ሕያውና ፍጹም መሆኑን፣ ወዘተ፣ ማለታችን ነው።

ሁለተኛው መጽሐፍ፦ “ዘ ፕሬየር ኦፍ ጄቤዝ” የተሰኘ በብሩስ ዊልክንሰን የተደረሰ ትንሽ መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ ትኩረት ያቤጽ በአንደኛ ዜና 4፡10 ላይ “እባክህ መባረክን ባርከኝ” ብሎ የጸለየውንና ባርኮቱን ይመለከታል። ደራሲውም ሲያስረዳን ይህንን ጸሎት በየቀኑ ደጋግሞ የሚጸልይ ደስታና ብልጽግናን ያገኛል ይለናል። ሦስተኛው ይኸው የምንገመግመው የሪክ ዋረን “ዓላማ መር ሕይወት” ነው። ሦስቱም ዓለም አቀፋዊ ራእይ አላቸው። ሦስቱም እጅግ ባለ ጸጎችና ተናግረው የሚደመጡ ሆነዋል፤ ከመንግሥታት መሪዎች ጋር ወዳጅነት ገጥመዋል። በባሕላቸውና በማኅበረሰባቸው ውስጥ የተረዱትን በወጠኑት መሠረት ለዓለም ሁሉ ማዳረስ ይሻሉ። ብሩስ ዊልክንስ በአፍሪካ ግዛት ቦትስዋና ውስጥ ለ 10 ሺህ ሕጻናት የሕጻናት መንደር ለመቆርቆርና አውሮፕላን ማረፊያ የቱሪስት ማዕከልና የአራዊት ክልል ያለው ይዞታ አስቦ ነበር። የቦትስዋና መሪዎች ግን ጉዳይ አስፈጻሚዎቹ ሊያደርጋቸው እንዳሰበ ስለመሰላቸው ምን ያህል ሚሊዮን ዶላር አዘጋጅቻለሁ ቢልም ሳይስማሙ ቀርተዋል። ድሮውንም ባለቤቱ የማይጋራው ራእይ ሌላ ቦታ ተቀምሞ ቢመጣ ከቁም ነገር አይውልም።

የሪክ ዋረንም ራእይ በየአገሩ እርሱ በተረዳው መሠረት “በዓላማ የሚመሩ” አብያተ ክርስቲያናትንና ማኅበረሰቦችን ማዋቀር ነው። የራእዩ መሠረተ አሳብ ከንግድ ሥራ አደረጃጀትና አፈጻጸም ጋር የተያያዘ ነው። ይህንንም ፒተር ድረከር ከተሰኘ የአመራር ሳይንስ ምሑር እንደ ተቀበለ ደራሲው ራሱ መስክሯል። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሪክ ዋረን ራእይ ውስጥ ለመታቀፍ ባትፈቅድ “በዓላማ አትመራም” ሊባል ነው? በመንፈስ ቅዱስ ብትመራ ያንስና ነው? ራእይ እንደሌላትና አሁን ገና እንደ ተገለጣላት ሊታሰብም አይገባም። ከአገራችንም ክርስቲያን መሪዎችን ጋብዞ ይህንኑ ራእይ ለማሠራጨት አቅዷል። የወንጌላውያን አብያተ ክርስርቲያናት መሪዎች ራሳቸው ያልጀመሩትንና ያልተሳተፉበትን ገንዘብ ስለ ተገኘ ብቻ ሲያስፈጽሙ እንዳይገኙ ጥንቃቄ ሊወስዱ ይገባል። በአሶሳ አካባቢ ለምሳሌ “ኢቫንጂ ኪዩብ” የተሰኘ የወንጌል ማሠራጫ ብልሃት ሲጠቀም ይታያል። በባሕላችን እርስ በርስ የምናወራውና የምንግባባው በእንዴት ያለ አኳኋን ነው? ከባሕል ጋር መጣጣሙም ሊታሰብ ይገባል ማለት ነው። 

ከላይ የጠቀስናቸው ደራሲያን ቢበለጽጉ፣ ስማቸው ገንኖ ቢወጣ ታዲያ ምን በደል አለበት? እንል ይሆናል። ምንም በደል የለበትም። ችግሩ ያለው የተኮረጀ ባሕል መዛመት ሲጀምር ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ከማጥናትና አዘውትሮ ከማንበብ ሊያዘናጋን ሰበብ ሲሆነን ነው። እርግጥ ለአንዳንዶች የሥራ ዕድል መፍጠሩ አይቀርም። ገንዘብና ሥልጠና ይዞ የመጣ ገንዘብና ሥልጠና ከጎደለው ክፍል ጋር እኩል ይተያያል ማለት ግን ራስን ማታለል ነው። በዚህ ረገድ ፈረንጅና አበሻ መሆን ልዩነት አያመጣም። አንደኛው ረጂ፣ ሌላኛው ተረጂ፣ አንደኛው ሰጭ፣ ሌላኛው ተቀባይ በሆነበት እኩልነት አይኖርም። ከመቶ ዓመት የሚሲዮናዊ እንቅስቃሴ በኋላ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ገና በአገር ደረጃና ከአገር ውጭ የሚደመጡ መሪዎች አለማፍራት፣ ዛሬም በውጭ ድጎማ መተዳደር እጅጉን ሊያሳስበን ይገባል።

ማጠቃለያ

አንድ የትርጉም ሥራ በቅድሚያ መልስ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች አሉ፦ አንደኛ፣ የታሰበውን መጽሐፍ መተርጎም አስፈላጊ ነበር ወይ? የሚል ነው። ለማንስ ነው የሚተረጎመው? ሁለተኛ፣ የማናውቀውን ምን አዲስ እውነት ያስታውቀናል? ወይስ ያንኑ የምናውቀውን በቃል ብዛት አዲስ ስያሜ ሰጥቶ ያደናግረናል? ሦስተኛ፣ ከመተርጎም ይልቅ ዋነኛ አሳቦቹን አስማምቶ ማቅረብ ይሻል ነበር? አራተኛ፣ መጽሐፉ ያልተለመደ አሠራርና የተዛነፈ ስነ መለኮታዊ አመለካከት ያራምዳል?

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን ጥንካሬና እድገት ያጸኑ የተፈተኑ ቅዱሳት ተግባራት አሉ፦ ከእነዚህም፣ የቤት ለቤት ጸሎት፣ የቃሉ ጥናት፣ ስደት፣ የመንፈስ ቅዱስ ምሪትና የእግዚአብሔር ፍርሓት ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ ግለኛነት፣ የግለሰቦች መግነነ፣ ለብዛት ብቻ እንጂ ለጥራትም ትኩረት አለመስጠት ውሎ ሲያድር ጉድለት ማምጣቱ አይቀርም። በመጨረሻም፣ ተርጓሚዎቹ አንባቢውን ለማዘጋጀት ሆነ በትርጉሙ ሥራ ላይ ስላጋጠሟቸው ችግሮችና ስለ ወሰዷቸው እርምጃዎች፣ በቡድን ተርጉመው እንደ ሆነ ለምን መግቢያ ወይንም ማብራሪያ እንዳላስቀደሙ አልገባንም። አራተኛው እትም ላይ የሚብራሩና የሚታረሙ ክፍሎች ይኖራሉ ብለን እንገምታለን። ጊዜ ለመቆጠብ ለምሳሌ ያህል እነዚህን ብቻ እንጥቀስ፦ 

“There’s nothing quite like it.” (ገጽ 12) የሚለው፦ “ይህን የመሰለ መልካም ልምምድ የለም” ተብሏል።| “ዓላማ መር”፣ “ራስ ተኮር” ወዘተ፣ የሚሉ አባባሎች ቢዘረዘሩ ምን ይጎዳሉ? | “አንተ ለእግዚአብሔር ተፈጠርህ እንጂ፣ ተገላቢጦሹ አይደለም የሆነው” (ገጽ 18)፤ [ለተርጓሚዎቹ ግልጽ ስለሆነ ለአንባቢውም ግልጽ ይሆናል ማለት አይደለም፤ ለዚህም ነው የተለያየ የመረዳት ደረጃ ባላቸው ግለሰቦች ላይ አስቀድሞ የትርጉሙን ጥራት መሞከር የሚያሻው] | “በተራራዎች ላይ በመጓዝ ላይ ሳለሁ…”(ገጽ18) “ተራራ ስወጣ” ወይም “ተራራ ወጥቼ” ቢል ምን ያጎድላል?

የጽሑፍ አገልግሎት ቀላል እንዳልሆነ እንመለከታለን። የራስን አሳብ ለሌሎች ማስረዳት አንዳንዴ ምን ያህል እንደሚያስቸግር እናውቃለን። የሌሎችን አሳብ ወደ ሌላ ቋንቋ መመለስ ደግሞ ምን ያህል ይከብድ? አገልግሎት ብዙ ጸሎትና ብዙ ምክክር ይጠይቃል፤ እንደ ተርጓሚው አንባቢውም የሥራ ድርሻ ይኖረዋል ማለት ነው። እንግዲያውስ በዚህ አገልግሎት ለተሠማሩ መጸለይና ጊዜ ወስዶ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል። እኛም ከርቀትም ቢሆን ይህን ለማድረግ ሞክረናል። መጽሐፉም ታትሞ እሰው እጅ የገባ ስለሆነ ተርጓሚዎቹን አፋልገን በግል ማሳሰብ ጥቅም እንደማይኖረውና በአደባባይ መነጋገሩ እንደሚሻል ተገንዝበናል። የሥራው ባለቤት የሆነ ጌታ ሁላችንን ይባርክ።                                                   2008/2009 (መጀመሪያ በ2000 ዓ.ም ታተመ)