ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም መኖር
ተድላ ሲማ
በ ክፍል አንድ፣ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር፥- 1. ሰዎችና ድርጊታቸውን በቅንነት እንረዳ 2. ስላደረግነው ነገር ሙሉ መግለጫ እንስጥ፤ ወዘተ፣ ብለን ነበር። የሚቀጥለው የመጨረሻው ክፍል ነው።
ከሰዎች ፍጹምነትን አንጠብቅ
ሰዎች ልንሳሳት የምንችል ፍጡራን በመሆናችን ከሰዎች ፍጹምነትን መጠበቅ አይገባም። እግዚአብሔር ብቻ ነው ፍጹም። ከሰዎች ፍጹምነትን የምንጠብቅ ከሆነ፥ ሰዎች ሲሳሳቱ ይቅር ማለት ይከብደናል። በአንጻሩ ሰዎች ፍጹም እንዳልሆኑ ከተረዳን ስህተት ሲፈጽሙ አይደንቀንም። በቀላሉ ይቅር ማለትም እንችላለን። እኛም እንሳሳታለን። ለምንድን ነው ታዲያ ከሰዎች ፍጹምነትን የምንጠብቀው? እኛ እንደምንሳሳተው ሁሉ እነርሱም ሊሳሳቱ እንደሚችሉ ለምን እንዘነጋለን?
በዋተርጌት ቅሌት ክስ ምክንያት ጊዜያቸው ሳይደርስ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የተገደዱት ፕሬዚደንት ኒክሰን ተከስሰው እያለ ታመው ወደ ሆስፒታል ገብተው ነበር። በዚህ ጊዜ ምክትላቸው የነበሩት ጄራልድ ፎርድ መንበረ ሥልጣኑን ይዘው ነበር። እርሳቸው ለኒክሰን ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን ነበራቸው። ይቅርታ ባደርግለት ከበሽታው ሊያገግም ይችላል ብለው በማሰብ ይቅር አሏቸው። ከዚህም የተነሣ ክሳቸው ተቋርጦ ነፃ ሆኑ። ይቅርታው ያላስደሰተው ሕዝብ ነበር። በፕሬዚደንት ጄራልድ ፎርድ ላይ ቂም የያዘው ሕዝብ በሚቀጥለው ምርጫ ላይ ጄራልድ ፎርድ ለፕሬዚደንትነት ሲወዳደሩ ድምጹን ነፍጓቸው ተሸንፈዋል። ከዚህ የምንማረው ምንድነው? ያ ሕዝብ እንዴት ይሳሳታሉ ብሎ የተበሳጨ ሕዝብ ነበር። ፍጹምነትን ከሰው ስንጠብቅ፥ ያ ሰው ሲሳሳት ይቅር ማለት እንቸገራለን። መሪዎቻችን ሲሳሳቱ በቀላሉ ይቅር ማለት የምንችለው፥ፍጹምነትን የማንጠብቅ ከሆነ ነው።
እኛም በየዕለቱ ብዙ ስህተት እንደምንሠራ መገንዘብ አለብን። ስለዚህ ሌሎችም ሲሳሳቱ ይቅር ልንላቸው የተዘጋጀን መሆን አለብን።
ችግር ሲከሰት የችግሩ ምክንያት እኔ እሆንን? ብለን እንጠይቅ
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ችግር ሲከሰት፥ ጣታችንን በሌላው ላይ ከመቀሰራችን በፊት ለተከሠተው ችግር የእኔ እስተዋጽዖ ምን ነበር? ብለን መጠየቁ ጥበብ ነው። ያን የምናደርግ ከሆነ ሃላፊነት ለመውሰድ የተዘጋጀን መሆናችንን እናሳያለን። ሰው በተፈጥሮው ስህተቱን በሌሎች ላይ የማላከክ ዝንባሌ ስላለው፥ እንዲህ ያለውን ጥያቄ አስቀድሞ በመጠየቅ ራስን ለማየት መሞከሩ ችግሩን ለመፍታትና ከሌሎች ጋር ለሚኖረን ጤናማ ግንኙነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የችግሩ መንስዔ እኛ ከሆንም ቶሎ ይቅርታ በመጠየቅ በመበላሸት ላይ ያለውን ግንኙነት ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመለስ ማድረግ እንችላለን። ለችግሩ መከሰት የእኔ ድርሻ ምን ያህል ነው? ብሎ መጠየቁ መልካም ነው። ይህን የምናደርግ ከሆነ ላጠፋነው ጥፋት ኃላፊነት እንድንወስድና ችግሩንም ለመፍታት አስፈላጊውን እርምት እንድናደርግ ይረዳናል።
ግጭቶችንና ቅሬታዎችን ሳናከማች ደረጃ በደረጃ እንቅረፍ
ሰዎች ሲበድሉን ቢቻል ወዲያው ተነጋግሮ መፍታት መልካም ነው። ቁርሾ ይዞ መቀመጡ ጥሩ አይደለም። ቅሬታዎችን በልባችን የምናከማች ከሆነ ግን ከልክ በላይ ይሆንና ድንገት በሚያስቀይም መልኩ ይገለጻል። ያን ጊዜ ቁጣችን ስለሚገነፍል ቃላት መምረጥ እንቸገራለን። ከዚህም የተነሣ በንግግራችን ሰዎችን እንጎዳለን። ለዚህ መፍትሔው ችግሮች ሳይከማቹ በጊዜ መፍታት ነው።
አንድ ጊዜ በሁለት እህቶች መካከል የተከሰተውን እዚህ ላይ ማንሳት ይጠቅማል። እነዚህ እህቶች ጎረቤታሞች ሆነው ሲኖሩ አንደኛዋ እህት በምትናገረው ነገር ሌላኛዋን እህት ትጎዳታለች። የተጎዳችውም እህት ምንም ሳትናገር ዝም ብላ ትኖራለች። በሌላ ቀን ሲገናኙ ያቺ እህት መጉዳቷን ሳታውቅ አሁንም በንግግሯ ታስቀይማታለች። ያቺም እህት በውስጧ "ህ ህ" እያለች ኑሮዋን ትቀጥላለች። አንድ ቀን ግን ጽዋው ሞላና እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ ያቺን እህት ልክ ልኳን ነገረቻት። ልክ ልኳን የተነገራት እህት ምን መጣብኝ ብላ በጣም ደነገጠች። እንባዋም ዱብ ዱብ ይል ጀመር። ልክ ልክ የነገረችው እህት ውስጧ የሞላውን ብስጭቷን ስለተናገረች እፎይ አለች። ያቺኛዋ ግን ተጎዳች። አምቀን የምንይዘው ነገር በኋላ በሚያስቀይምና በሚጎዳ መልኩ ይገለጻል። ስለዚህ ምንድ ነው መደረግ ያለበት?በነዚህ ሁለት እህቶች መካከል ምን መሆን ነበረበት? መጀመሪያ በንግግሯ ስታስቀይማት “ለምን እንደዚህ ትያለሽ? ያልሽው ነገር አሳዝኖኛል፤ በንግግርሽ ተጎድቻለው። ሁለተኛ እንዲህ ያለ ነገር አትበዪ” ብትላት ኖሮ ያቺ እህት ለመታረም ዕድል ታገኝ ነበር። ይቅርታም የመጠየቅ ዕድል ይኖራት ነበር። ያ ባለመደረጉ ግን ተጎዳዱ። ቁስላቸው እስኪሽርና ግንኙነታቸው እስኪታደስ ጊዜ ፈጀ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግንኙነታቸው እንደታደሰ አስታውሳለሁ። ስለዚህ ቅሬታዎችን ሳናከማች በጊዜው መናገር መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል፤ የባሰ መጎዳዳት እንዳይመጣም መከላከል ያስችላል። አቂመን የምንቆይ ከሆነ በኋላ በሚያስቀይም መልኩ መገለጹ አይቀርም።
ሰዎች ሲያሳዝኑን ተነጋግረን መፍታት ካልቻልን በጌታ ፊት በጸሎት አቅርበን ይቅር ልንላቸውና ልንባርካቸው ይገባል። በምንጸልይላቸውና በምንባርካቸው ጊዜ ጥላቻ ከልባችን ላይ ይወገዳል። የምንጸልይለትን ሰው ልንጠላው አንችልም። ጸሎት የፍቅር ቋንቋ ነውና።
ሰዎችን ማድነቅን እንማር
ሰዎች ላይ የምናደንቀው ነገር ካለ ያን የምንገልጽበት ሁኔታ ከገጠመን ማድነቅ ጥሩ ነው። ይህም ሰዎች ያላቸውን መልካም ነገር እንዲያውቁትና እንዲበረታቱበት ያደርጋቸዋል። በሰዎች ላይ የምናየውን መልካም ነገር በመናገር ልናበረታታቸው ይገባል። በልተን ”ሆድ ይመርቅ” ማለት የለብንም። ምግቡ ከጣፈጠ አፍ ነው መመረቅ ያለበት። የበላው እሱ ነውና። ልመርቅ ቢልም ሆድ መናገር መች ይችልና። ስናመነፈሰው ደግሞ ”እንዳይታበይ አልነግረውም ” እንላለን። መልካም ነገሩን ለወንድማችን ከነገርነው ይታበያል የሚል እሳቤ መሆኑ ነው። እንዳይታበይ እንጸልይለት። መልካም ነገሩን ግን እንዲበረታታበት እንንገረው ወይም እንንገራት።
የሰዎችን ድካም ስናይ ለመተቸት የምንፈጥን፥ መልካም ነገር ስናይ ግን ማድነቅ የማንችል ስንቶች ነን? ጳውሎስ በጢሞቴዎስ ላይ ያየሁን መልካም ነገር እንዲህ በማለት ይነግረዋል፥ “እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ። በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤(2ኛ ጢሞ.1:4-5) እምነቱ ግብዝነት እንደሌለበት ለጢሞቴዎስ ይነግረዋል። እኛም በሰዎች ላይ የምናየውን መልካም ነገር በመንገር እናበረታታቸው።
ለተደረገልን ነገር ሰዎችን ማመስገን እንማር
“ለተደረገልን ነገር ማመስገን ድንቅ ባይባልም አለማመስገን ግን ከመጥፎ ነገሮች ውስጥ ከላይኛው ተርታ የሚመደብ ነው” ሲል አንድ ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ተናግሯል። በመሆኑም ከሰዎች ለሚደረግልን ነገር ለማመስገን ፈጣን መሆን አለብን። የዘገየ ምሥጋና እንደ ውለታ ቢስነት ሊቆጠር ይችላልና።
ፍቅርን መስጠትና መቀበልን እንማር
ለሰዎች ፍቅርን እንስጥ ማለት የምንችለውን ነገር ለሌሎች ማድረግን እንማር ማለት ነው። ያ የፍቅራችን መገለጫ ሊሆን ይችላልና። ለምሳሌ ለሰዎች የእንኳን አደረሳችው መልዕክት ስንልክ እናስባችኋለን ማለታችን ነው። ፍቅራችንን መግለጻችን ነው። አንድ ሰው ለአዲስ ዓመት 50 ፖስት ካርድ ከሰዎች ተላከልኝ ካለ እሱ ግን ለማንም ምንም ካርድ ካላከ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ፍቅርን የሚቀበል ግን ፍቅር የማይሰጥ ሰው ነው ማለት እንችላለን። የፍቅር ደሃ ሊባል ይችላል ወይም እንደ ቤርሙዳ ትሪያንግል ሁሉን የሚውጥ ግን ምንም የማይወጣው ማለት ነው። ስለዚህ ፍቅርን መስጠትንና ሰዎች ፍቅር ሲያሳዩን ደግሞ አመስግነን ፍቅራቸውን መቀበል የምንችል ሰዎች ልንሆን ይገባል። እንደዚያ የምናደርግ ከሆነ ከሰዎች ጋር ጤናማ ግንኙነት ይኖረናል።
ሰዎችን አንሸንግል
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት እውነተኞች መሆን አለብን። ሰዎችን መሸንገል የለብንም። ለምሳሌ ከአንድ ከማውቀው ሰው ገንዘብ መበደር ፈልጌ ያን ሰው ለብድሩ ለማዘጋጀት ከወትሮ የተለየ ሞቅ ያለ ሰላምታ ብጀምር ያ ሽንገላ ነው። ብሩን ከተበደርኩ በኋላ ሞቅ ያለው ሰላምታዬ ከጠፋ ያ ገንዘብ ያበደረኝ ሰው ግብዝነቴ ያበሳጨዋል። በግኑኘነታችንም ላይ ጥላ ያጠላል። በመሆኑም ለሰዎች ያለን አቀራረብ እውነተኛ ሊሆን ይገባል። ገንዘብ ካስፈለገኝ ምንም ከወትሮ የተለየ አቀራረብ ሳይኖረኝ በእውነተኛ ማንነቴ ሰዎችን ቀርቤ ልጠይቅ ይገባል። ከሰጡኝ መልካም ካልሰጡኝም በፀጋ መቀበል ነው እንጂ ያልሆንኩትን ሆኜ ልቀርብ አይገባም። እውነተኛ ስንሆን ሰዎች ያምኑናል። ካመኑን ደግሞ ግንኙነታችን ይሰምራል።
ሰዎችን ለመቆጣጠር አንሞክር
ይህን ነጥብ ለማስረዳት በትዳር ጓደኛሞች መካከል ያለውን ምሳሌ መጠቀሙ መልካም ነው። ባል ሚስትን የት ወጣሽ? የት ገባሽ? የሚል ያልተቋረጠ ቁጥጥር ማድረግ ጤናማ አይደለም። ወይም ሚስት ባሏን የት ወጣ? የት ገባ? የሚል የማያቋርጥ ክትትል ማድረግ ባሏን ለመቆጣጠር መፈለጓን ያመላክታል። በርግጥ ሚስት ለባል፥ ባል ለሚስት ተጠያቂነት አለባቸው። የት እንደ ሄደ ምን እንዳደረገ ባል ለሚስቱ በግልጽ ማስረዳት ይገባዋል፤ ሚስትም እንዲሁ ለባሏ ያን ማድረግ አለባት። ከዚያ ባለፈ ግን የትዳር ጓደኛን እግር እግር እይተከታተሉ ለመቆጣጠር መሞከር ጤናማ አይደለም። መተማመን ሊኖር ይገባል። የሰውን ነፃነት መግፈፍ ተገቢ አይደለም። ነፃ ፈቃድ የተሰጣቸውን የሰው ልጆች ከልክ ባለፈ መልኩ በመቆጣጠር ለመግዛት መሞከር የለብንም። ሌሎች ሰዎችንም እንዲሁ ለመቆጣጠር መሞከር የለብንም። የመቆጣጠር ዝንባሌ ካለን ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነታችን ይበላሻል።
ከእኛ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ነገሮች ላይ ዕቅድ ማውጣት የለብንም
ዕቅድ ማውጣት ያለብን በቁጥጥራችን ሥር ባለ ጉዳይ ላይ ብቻ ሊሆን ይገባል። ለምሳሌ የሠርግ ዝግጅት ኖሮብኝ ለሠርጌ እቅድ ሳወጣ በእጄ ባለው ገንዘብ ልክ ሊሆን ይገባል። ወንድሜን ሳላማክር እሱ ገንዘብ ሊሠጠኝ ይችላል በሚል እሳቤ እቅድ ባወጣ ችግር ውስጥ ልገባ እችላለሁ። እቅድ ካወጣው በኋላ ወንድሜ ያሰብኩትን ገንዘብ ባይሠጠኝ ከወንድሜ ጋር ያለኝ ግንኙነት ሳንካ ሊገጥመው ይችላል፤ ከራሴም ጋር ልጣላ እችላለሁ፤ ምናልባትም ከእግዚአብሔር ጋር ልጣላ እችል ይሆናል። በነገራችን ላይ እቅድና እምነት ይለያያል። እኔ እየተናገርኩት ያለው ስለ እቅድ ነው እንጂ ስለ እምነት አይደለም። አንዳንድ ሰዎች አምኜ ማቀድ አልችልም እንዴ? ሲሉ ይጠይቃሉ። በርግጥ አምነን ማቀድ እንችላለን። ሆኖም ግን እምነታችን ሊመሠረት የሚገባው እግዚአብሔር በጉዳዩ ላይ በተናገረን ቃል ላይ ሊሆን ይገባል። ከጌታ ቃል ተቀብለን ከሆነ እቅዳችንን የሚያሳካበትን ሁኔታዎች ጌታ ያመቻቻል። ጌታ ግን በጉዳዩ ላይ በግልጽ ባልተናገረን ሁኔታ ግን እምነት ነው ብለን ብናቅድ የእምነት ኪሳራ ሊደርስብን ይችላል። ብዙ ጊዜ እምነት የምንለው ነገር አጉል ድፍረት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መጠንቀቅ አለብን።
ሌላ ምሳሌ በመስጠት ይህን አሳብ እንመልከት። “በየዕለቱ 4 ምዕራፎች በማንበብ መጽሐፍ ቅዱሴን በአንድ ዓመት ውስጥ እጨርሳለሁ” ብዬ ባቅድ፥ ይህ እቅድ በቁጥጥሬ ስር ባለ ነገር ላይ የታቀደ ስለሆነ የመሳካት ዕድሉ ሰፊ ነው። ነገር ግን ከቁጥጥሬ ውጪ በሆነ ሰው ላይ ይህን እቅድ ባወጣ የመሳካት ዕድሉ የመነመነ ነው። ለምሳሌ “ጓደኛዬን በየቀኑ 5 ምዕራፎች እንዲያነብ አድርጌ መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ዓመት እንዲጨርስ አደርገዋለው” ብዬ ባቅድ የዚህ እቅድ መሳካት አጠራጣሪ ነው። አንድ ቀን አንብቦ በሁለተኛው ቀን “ደክሞኛል ዛሬ አላነብም” ቢለኝ ምን ማድረግ እችላለሁ? በግድ አንብብ ብዬ ልጋጭ ነው? እቅድ ስናወጣ ሁልጊዜ ልንቆጣጠረው በምንችለው ሁኔታ ላይ ብቻ ሊሆን ይገባል። ከኛ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እቅድ አይወጣም። መመኘት ይቻላል። እቅድ ግን አይወጣም። ይህን በቅጡ ከተረዳን ክብዙ ራስ ምታትና ከሰዎች ጋር አላስፈላጊ ከሆነ እሰጥ አገባ ውስጥ ከመግባት እንጠበቃለን።
በመልካም ጊዜ የተነገረንን ምስጢር በጠብ ጊዜ አንናገር
ሰዎች በመልካም ጊዜ የነገሩንን ምስጢር ከነሱ ጋር ስንጋጭ ሚስጥራቸውን መዘርገፍ የለብንም። ያን ማድረጋችንን ካወቁ ግንኙነታችን በፍጹም መታደስ በማይችልበት ሁኔታ ለዘለቄታው ሊበላሽ ይችላል። የሰውን ገመና መደበቅ አለብን። የእኛን ገመና ቢዘረግፉት ምንድ ነው የሚሠማን? አለመግባባቶችና ግጭቶች ቢከሰቱም ሊፈቱ በሚችልበት ሁኔታ እንተወው እንጂ ከናካቴው ዳግም በማንታረቅበት ደረጃ እንዳይደርስ ልንጠነቀቅ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ዋናው አስፈላጊ ነገር ሰዎች እንዲያምኑን ማድረግ ነው። ካላመኑን ምንም ብንናገር የምናመጣው ለውጥ አይኖርም። አሜኔታን በጣም ከሚሸረሽሩ ነገሮች አንዱ የሰዎችን ምስጢር መዘርገፍ ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ይመክረናል፦ "ክርክርህን ከባልንጀራህ ጋር ተከራከር፤ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ፥” (ምሳሌ25:9)
ሁለታችንም የምንጠቀምበትን አካሄድ ሁልጊዜ እንከተል
ማንኛውንም ነገር ስናቅድ ራሳችንን ብቻ ያማከለ መሆን የለበትም። ለምሳሌ ከባለቤቴ ጋር ለእረፍት አንድ ሥፍራ ለመሄድ ካሰብኩ ወደዚያ ሥፍራ መሄድ የባለቤቴ ፍላጎት መሆን አለመሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብኝ። በእኔ ተጽዕኖ የማትወደው ሥፍራ ለእረፍት ከምወስዳት እኔም እሷም እኩል ልንወደው የምንችለውን ሥፍራ መምረጤን ማረጋገጥ አለብኝ። ይህን በመመካከር ማቀድ ይቻላል። ያን ስናደርግ ሁለታችንም የምንጠቀምበትን መንገድ ተከተልን ማለት ነው። ይህ አካሄድ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሁሉ ልንጠቀመው ይገባል። ከራስ ወዳድነት ጸድተን የሌሎችንም ፍላጎት ግምት ውስጥ የምናስገባ ከሆነ ከሌሎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ጤናማ ይሆናል።
ሌላ ምሳሌ እንውሰድ:- ከጓደኛዬ ጋር ለመጫወት ስንቀጣጠር የምንገናኝበት ቦታ ለሁለታችንም አማካይ የሆነ መሆኑን ማረጋገጥ አለብኝ። ለኔ ቅርብ የሆነውን ለሱ ግን ሩቅ የሆነ ቦታ የምመርጥ ከሆነ ራስ ወዳድ ሆኛለሁ ማለት ነው። ደጋግሜ ያን የማደርግ ከሆነ ደግሞ በግንኙነታችን ላይ ጥላ ያጠላል። ወዳጄ ይሉኝታ ይዞት ባይነግረኝም በውስጡ እንደሚያዝን ማወቅ አለብኝ። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ጥቃቅን በሚመስሉ ጉዳይች ሳይቀር ሁለታችንንም እኩል አሸናፊ የሚያደርግ ወይም እኩል የሚጠቅም ነገር ማሰብና ማድረግ ነው ያለብን። ቃሉ “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” ይላል። (ፊልጵስዩስ 2:4)
አንዳንድ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያነሱት ጥያቄ አለ:- "ለሌሎች ብለን እልፍ ብንል ምን ችግር አለው? ክርስቲያናዊ ባህሪ አይደለም እንዴ?" ይላሉ። ሌሎችን ለመጥቀም እልፍ ብንል ችግር ላይኖረው ይችላል፤ እንደሁም እልፍ ማለታችን በጣም ሊጠቅም የሚችልባቸው ጊዜያት ይኖራል። ሆኖም ግን እዚህ ነጥብ ላይ ለማለት የተፈለገው ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሌሎች እልፍ እንዲሉልን በማድረግ ለራሳችን የሚጠቅመውን ብቻ አናድርግ የሚል ነው። ጓደኛዬ "ምንም ችግር የለውም። እኔ ላንተ የሚቀርበው ቦታ ድረስ እመጣለው" ይበለኝ እንጂ እኔ ራስ ወዳድ መሆን የለብኝም። ወዳጆቻችን ለኛ አስበው የሚከፍሉትን ዋጋ በመገንዘብ በሌላ ጊዜ ለመገናኘት ስንቀጣጠር ደግሞ ለነሱ የሚቀርበውን ሥፍራ መምረጥ አለብን። ያን ጊዜ ለሁለታችንም የሚጠቅመውን አካሄድ ተከተልን ማለት ነው።በራስ ወዳድነት ላይ ያልተመረኮዘ አካሄድ ስለሆነ ለጤናማና ዘላቂነት ላለው ግንኙነት ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት መንገድ ነው።
ሌላ ልናስተውለው የሚገባ ነገር አለ። ለሌሎች እልፍ እንበል ብለን የምናደርጋቸው ነገሮች በጥበብና በሚዛናዊነት ሊሆን ይገባል። ካልተጠነቀቅን ራስ ወዳድ ሰዎች ካገኙን ሁልጊዜ ይጠቀሙብናል። እየተደጋገመ ሲሄድ ውስጣችን መታመም ይጀምራል፤ እንጎዳለን። ለእንደዚህ ዓይነት ራስ ወዳድ ሰዎች ገደብ ልናበጅላቸው ይገባል። ሁልጊዜ የሚፈልጉትን ብንሆንላቸውም ወይም ብናደርግላቸውም እንኳን ራስ ወዳድነታቸውን ከማጠናከር ውጪ አንጠቅማቸውም። እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልህ እንድንሆን የታዘዝነውን እዚህጋም ማጤኑ ጠቃሚ ነው፤ ሚዛናዊ ልንሆን ይገባል።
የወንድሞቻችን/የእህቶቻችን ጠባቂ መሆናችንን እንወቅ
ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ጌታ የሰጠን ልንጠብቃቸውና ልንጠነቀቅላቸው ነው እንጂ እንድንጎዳቸው አይደለም። ቃየን “የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” (ዘፍጥረት 4:9) ብሎ ለእግዚአብሔር እንደ መለሰ እኛም እንደዚያ ልንሆን አይገባም። ፍቅር ማለት ለሌሎች መጠንቀቅ ማለት ነው። የሰው ትልቁ ችግር ራስ ተኮር መሆኑ ነው። ለሌሎች ስሜት ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ያ ሲሆን ከሌሎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ጤናማ ይሆናል።
ከላይ የተጠቀሱት በኛ በኩል ልናደርጋቸው የሚገቡ 20 ነጥቦች በኛና በሌሎች ሰዎች መካከል የሚኖረውን አሜኔታ በማጠናከር ግንኙነታችንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ልንገነዘብ ይገባል። ሰዎች በእኛ ላይ ያላቸው አመኔታ እንዳይሸረሸር መጠንቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። አመኔታ እየተጠናከረ ሲሄድ ልክ በባንክ ውስጥ እንዳለ ተቀማጭ ገንዘብ ጠቃሚ ነው። ገንዘቡን በሚያስፈልገን ጊዜ እንጠቀምበታለን። ሰዎችም ሲያምኑን በምንፈልጋቸውና በሚያስፈልጉን ጊዜ ይገኙልናል። ይህ ማለት በሰው ላይ እንታመን ለማለት አይደለም። የምንታመነው በእግዚአብሔር ላይ ነው። ሆኖም ግን የጤናማ ግንኙነት መሠረቱ መተማመን መሆኑን ለማሳየት ነው። ለምሳሌ አንድ የማያውቀን ሰው አለ እንበል። ይህ ሰው አንድ ነገር እንዲያውሰን ፈለግን። በቀጥታ ሄደን ብንጠይቀው ስለማያውቀን ሊያምነን ይቸገራል። ስለዚህ ዕቃውን ለማዋስ ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው? እኛ የምናውቀው ወዳጃችን ከዚህ ሰው ጋር ወዳጅ ከሆነ በሱ በኩል ያንን ሰው መቅረቡ ችግሩን ሊፈታው ይችላል። ሁለቱ ስለሚተዋወቁና ስለሚተማመኑ በዚያ በኩል ብንመጣ አሳባችንን ማሳካት እንችላለን። የግኑኝነት መሠረቱና ድምድማቱ አመኔታ መሆኑን ላንዳፍታም ልንዘነጋ አይገባም።
አመኔታ እንዳያሽቆለቁል የተቻለንን ሁሉ ልናደርግ ይገባል። ሰዎች የሚሰሙን ባመኑን መጠን ነው እንጂ ብዙ ስለ ተናገርን አይደለም። በሰዎች መካከል መተማመን ሲጠናከር በመተያየት ብቻ መግባባት የሚቻልበት ደረጃ ሊደረስ ይችላል። ይህ ትልቅ የግንኙንት ስኬት ነው። ሰዎች በኛ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጠናከር ማድረግ የሚገባንን ማድረግ፥ ማድረግ የማይገባንን ደግሞ አለማድረግ የኛ አላፊነት ነው። መናገር የሚገባንን መናገር፥ መናገር የማይገባንን ደግሞ አለመናገር ኃላፊነቱ በኛ ላይ ይወድቃል። ለምሳሌ ወዳጆቻችን መታመማቸውን ስንሰማ መጠየቅ ያስፈልጋል። ችግር ሲገጥማቸው በጊዜው ባጠገባቸው በመሆን መርዳት አመኔታን ያጠናክራል። ሃዘን ሲገጥማቸው ማጽናናት ይጠበቀብናል። በጸሎት መደገፍ ያስፈልጋል። እነዚህን ነገሮች የማናደርግ ከሆነ በኛና በወዳጆቻችን መካከል ያለው ግንኙነት እየተበላሸ ይሄዳል። ለዚህም ምክንያቱ በልባቸው ውስጥ ለኛ የሚሰጡት ሥፍራ ወይም አመኔታ ስለሚሸረሸር ነው። ተራ የሚመስሉ ነገሮች እንኳን ሳይቀር ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙንት ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። ስለዚህ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙንት ግድ የለሾች ልንሆን አይገባም። የገነባነውን ድልድይ እያፈረስን መሄድ የለብንም። ተመልሰን ልንሻገርበት የሚያስፈልግበት ወቅት ሊመጣ ይችላል። ልክ የቆጠብነው ገንዘብ ለችግር ጊዜ እንደሚጠቅመን ሁሉ ማለት ነው።
ማድረግ የሚገባንን ነገር ባለማድረግ ወይም ማድረግ የማይገባንን ነገር በማድረጋችን የተፈጠረ የግንኙነት ችግር ካለ ፈጥነን የእርምት እርምጃ መውሰድ አለብን። የእርምት እርምጃው ይቅርታ መጠየቅ ሊሆን ይችላል። ወይም እንደ ችግሩ ክብደት መጠን ተመጣጣኝ ማስተካከያ ወይም ማካካሻ ማድረግ ሊሆን ይችላል።
ከላይ የተዘረዘሩትን የጤናማ ግንኙነት አካሄዶችን በመከተል ሁልጊዜ የተፈለገውን ሰላም ልናመጣ እንችላለን? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል” ነው ቃሉ የሚለው። በእኛ በኩል ማድረግ የሚገባንና መሆን የሚገባንን ሁሉ ከሆንን በኋላ ከሌሎች ጋር ጤናማ ግንኙነት ባይኖረን ምን እናድርግ? ለሰላማዊና ጤናማ ግንኙነት የራሳችንን ድርሻ ከተወጣን በኋላ ሰላም ካልመጣ መጨነቅ የለብንም። ከላይ የተዘረዘሩትን ጤናማ የግንኙነት አካሄዶች ከተከተልን ለሰላማዊ ግንኙነት ድርሻችንን ተወጥተናል ማለት እንችላለን። የተቀረው ኃላፊነት ከኛ ጋር በሰላም ለመኖር በሚሹት ላይ ይወድቃል። የቱንም ያህል መንገድ ሄደንላቸው ከኛ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለማድረግ የማይፈልጉ ወይም የማይችሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ላይ ገደብ ልናበጅ ይገባል። ግንኙነቱን ለመቀጠል ብንፈልግም እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ይጎዱናል እንጂ አንጠቅማቸውም። በመሆኑም እንዳይጎዱን ገደብ ልናበጅላቸው ይገባል። ያን ጊዜ ከነሱ ጋር ሰላም ማምጣት ባንችልም የራሳችንን ሰላም መጠበቅ ግን እንችላለን። ልንጸልይላቸው እንጂ ልንጠላቸው አይገባም። እግዚአብሔር ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንዲኖሩ እንዲረዳቸው ልንማልድላቸው ይገባል። እኛ ልንረዳቸው ስላልቻልን ሊረዳቸው ወደሚችለው አምላክ በጸሎት ልናቀርባቸው ይገባል።
ቋንቋን በቋንቋ | ሞት እና ፕሮፌሰር | መንበርና እርካብ | Land of the Shy, Home of the Brave | በመዝሙር ብቻ የምናውቀው ደረጀ ከበደ | አዲስ አዲስ ራእይ (ያሬድ ጥላሁን | ከፒኤችዲ እስከ ጠቅላይ | እሳት ነው፣ በእሳት ነው