muluwongel54

እሳት ነው፣ በእሳት ነው

የሙሉ ወንጌል “ሀ” መዘምራን የተቋቋመበት 54ኛ ዓመት በያዝነው ዓመት ተከብሯል። የክብረ በዓሉን ቪዲዮ “ወንጌል በዝማሬ ዩቱብ” ኖቬምበር 12/2023 ለጥፎ በጥሞና ተመልክቻለሁ። ጽሑፌ፣ ያየሁትና የሰማሁት የቀሰቀሰውን ትዝታ ለማሰባሰብና ለማጋራት ያለመ ነው።

የሙሉ ወንጌልን ቤተ ክርስቲያን ጅማሬ (1959 ዓም) እና ዛሬ የደረሰችበትን ለተመለከተ፣ ያመነ ይሁን ያላመነ፣ በእግዚአብሔር ኃይል ሥራ ከመገረም ወዲያ አማራጭ አይቀርለትም። የተሰደዱ ጥቂቶች፣ እዚህ ግቡ የማይባሉ የትናንት ወጣቶች የዛሬ አዛውንት፣ ያመለኩትን አምላክ ምሥጋናውንም ለልጅ ልጅ አድርሰው በእግዚአብሔር ዐይን ሞልተው ታይተዋል። የሥራው ባለቤት ይመስገን።

የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የማደጓና የመስፋቷ ምክንያት የእግዚአብሔርን ቃል እንደ እግዚአብሔር ቃል መቀበሏ ነው። በእሳት ውስጥ ማለፏ ደግሞ የእድገቷ ሌላኛው ገጽታ ነው። እሳቱ ከውስጥ ይምጣ ከውጭ፣ ያው እሳት ነው። እሳት፣ የቤቱ ባለቤት ሕዝቡን ሊያጠራ፣ ለታመነ ምስክርነት ሊያበቃ፣ ስሙን ሊያገንን የሚጠቀምበት መንገዱ ነው። ቁጥቋጦውን ያነደዋል፣ ቁጥቋጦው ግን አይቃጠልም። ያመነታሉ፣ ተስፋ አይቆርጡም። ይሰደዳሉ፣ አይጣ-ሉም። ይወድቃሉ፣ አይጠፉም። ከእነዚህም አንዳንዶች “የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁ” ለማለት በቅተዋል። ይህንን ሁሉ ቀድሞ ማን አወቀ? ማን አሰበው? ሁሉን የሚያውቅ የሕዝቡ አምላክ ይመስገን።

“ሙሉ ወንጌል” ማለት ምን እንደ ሆነ ከማወቄ አስቀድሞ፣ እህቱ ዘማሪ የሆነች ሰው ጋብዞኝ ዘማሪዎቹን ላያቸው ሄጄ ነበር። ስንደርስ፣ ነጭ እና አረንጓዴ ቀሚስ አጥልቀው እንደ ኢየሩሳሌም ግንብ ተገጥግጠው ቆመዋል። የሆነ ሰው የሆነ ነገር ተናግሮ፣ በኮረብታ ላይ እንደሚወርድ ጠል ዝማሬው መውረድ ጀመረ፣

ክንድህ ይበርታ በጠላትህ በር | ሥራቸው ይፍረስ ይድቀቅ ይሰበር፣ ሃሌ ሉያ... | አምላክ እረኛዬ ነው፣ አምላኬ እረኛዬ ነው...

እንዲህ እንደሚዘመር አይቼም አስቤም አላውቅም ነበርና ከተቀመጥኩበት ጥግ ትኵር ብዬ አየኋቸው። ሰዎች ይመስላሉ፤ ደግሞ ሰዎች አይመስሉም፤ ምናልባት ግማሽ መላእክት ይሆናሉ። ቀልዴን አይደለም። ጸጋ ስለሚሉት ነገር የነገረኝ የለማ! ኋላ ነፍስ ሳውቅ፣ በጥንት ግሪኮች መጽሐፍ፦ አማልክት በሰው ተመስለው ይቀላቀላሉ የሚል እምነት እንደ ነበራቸው አንብቤአለሁ። የአይሁድ፦ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት ይላል። ባጭሩ፣ የዘማሪያኑ ቅኔ ቅላፄና አቋቋም ነፍስ የሚያሸፍት ነበር፤ ከምድረኛነት የሚያላቅቅ። ወደ እግዚአብሔር ክልል የሚያከንፍ። ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነትና አሠራር ገና አላወቅሁም ነበር! ዝማሬው እንደ ባሕር ተመመ፤ ነፋስ እንደሚወዘውዘው ዛፍ መሰለ፣

በሸለቆ ብታልፍ በጨለማ ዐይንህ ቢጋረድ | ሰጥመህ አትጠፋም አትደንግጥ ቢመታህም ሞገድ | ልብህ እየባባ ወደ ኋላ ሃሳብህ ቢረታ | ለጥቂት ደስታ አትጣለው የፍቅሩን ትዝታ | ነፋስ አያርድህ | ከንቱ ወሬ አይፍታህ | ልብህ ጥቂቱን ወዶ | አይኑር በኃጥያት ተዋርዶ

አዳዲስ ነገር መሞከር የሚደፍር ሌላኛው ጓደኛዬ ሳይነግረኝ ለካንስ ሙሉ ወንጌል በድብቅ ይመላለስ ኖሯል። እንዲህና እንዲያዎቹ ዘማሪያን ጋ እንዴት መሄድ ይቻላል አልኩት። ቀላል ነው፤ እኔ እወስድሃለሁ አለኝ። መኖሪያ ቤት ነው፤ የቆርቆሮ አጥር አለው፤ በሩ አንዱ ሲገባ ሌላው ሲወጣ፣ ቡና እንደ ጠማው ሰው ማዛጋት የበዛበት በር ነበር። ገባን። ትርምስ ነው፤ ጩኸት ነው፤ ያዙኝ ልቀቁኝ። ንግግሩ አይ-ገባ፤ ንግግር አይሉት ነገር። እንሂድ እንሂድ አልኩት፤ ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ቦታ ላልደርስ ወሰንኩ። ምን ያህል መንፈሳዊ ቢመስል፣ አእምሮን ካስካደ፣ ኃይማኖት እስከ ወዲያኛው ይቅርብኝ ብዬ ማልኩ። ማልኩ። ዛሬም እንኳ ዘመን አልፎ ዘመን ተተክቶ መሓላዬን አልሻርኩም። አእምሮን ካስካደ ... (ሮሜ 12:1-2፤ ኤፌሶን 4:13-15፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 14:20፤ ሉቃስ 2:52)። ዛሬም፣ ዘመን አልፎ ትምህርት በዝቶ፣ ሕፃን የነበረው አዳድጎ፣ ተተኪው ትውልድ ካለፈው ስህተት ሳይማር፣ በእውቀት ጠልነት “መንፈሳዊ” በሚመስል መጤ ልማድ ተተብትቧል!

መንፈስ ቅዱስ መኖሩን ሰምቼ አላውቅም ነበር ብያችኋለሁ፤ አለመብሰል ምን እንደሚመስል ግን የነገረኝ የለም! ኋላ እኔንም ደርሶብኝ፤ በእሳትና በደመና ዓምድ፣ በምድረ በዳ ቁመት ልክ ተመላልሼበት፣ የአጋንንት ጦርነት በበዛበት እስር ዳርቻ አድርሶ፣ ግራ እና ቀኝ አትበል፤ ቀጥ ብለህ ተከተለኝ ብሎኛል።

ወዳጄ፣ የእነዚያን ዘማሪያን መዝሙር በካሴት ሲያደምጥ ደረስኩበት። አውሰኝ ብለው፣ ነገ ጧት መመለስ አለብኝ አለ። ሌቱን ሳደምጥ አደርኩኝ (የያን ዘመን ቴፕ ሪኮርደር፣ አንድ ቃል እንጂ እንደ ዛሬዎቹ ሁለት ቃል ድግግሞሽ እንደማያውቅ አንርሳ!)፤

ጌታ የሱስ ና መርምረኝ፣ በደሌንም ይቅር በለኝ | ባንተ መንፈስ ተመርቼ፣ እኖር ይሆን ሁሉን ትቼ...

ለዚህ ዓለም ባእድ ሆነን፣ የሱስን እንጠብቃለን | እዚህ ዘላቂ ቤት የለንም፣ ርስታችን በሰማይ ቤት ነው፤

ማለዳ፣ ማን ማንን ማስታወስ እንደ ረሳ ሳይታወቅ፣ ቴፑን ሳይይዝ ተነሥቶ ወጥቶ ሄዷል። መሄዱን ሳውቅ፣ ከዐረብ ቤት አዳዲስ ባትሪ ድንጋዮችን ገዥቼ ቀኑን ሙሉ ሳደምጥ ዋልኳ!

ሌላ ቀን፣ መንፈስ ቅዱስ ተሞልቻለሁ፣ በልሳን እጸልያለሁ አለኝ። ይህን ያገኘው ከዚያው ከሙሉ ወንጌል ነው። ሲጸልይ ሰማሁት። በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ምልክቱ በልሳን መጸለይ ነው አለኝ። ረጂም ቀናት ስለ መፆም ስለ ቅድስና እና ከመፆም ብዛት ኢየሱስን ስለ ማየት፣ ሌላም ሌላም ነግሮኝ ነበር፤ ለሌላ ቀን ይደር? እርግጥ ነው፣ ልሳን ከጸጋ ስጦታዎች አንዱ ነው፤ ሁሉ በልሳን ይጸልያል ማለት ግን አይደለም። አተረጓጎሙ የሳተ እንደ ሆነ የገባኝ ቆይቶ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ማነው? በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ፦ የኢየሱስ ስም ከአፉ የማይለይ፣ መንፈስን የሚ-ለይ፣ በቃሉ እውቀት ያደገ፣ ሰውን ሁሉ የሚወድድ የሚያከብር፣ ጥቂት ልከኛ ቃል የሚናገር፣ እውነት እና ፍትኅን ወገኑ ያደረገ፣ ከዓለም ያልተለዋወሰ፣ እርሱ ነው!

እከሌ ቢጸልይልህ አለኝ። ከአንድ እከሌና እከሊት ከሁለትም ሦስት ጸለዩልኝ። ቋንቋዬ ከአማርኛ ሊያልፍ ግን አልቻለም። መንፈስ ቅዱስ የለኝም ማለት ነው? እንዲያ ማለት እንዳልሆነ ያኔም እንኳ አውቄ ነበር። እንዴት አወቅሁ? በዚያው በመንፈስ ቅዱስ ነዋ! እኔም ወዳጄም እስከ ዛሬ አጽንቶን በጌታ አለን፤ በጸጋው ኃይል ተደግፈን ያዳነንን ያፀናንን እናመልካለን፣ እናገለግላለን! ክብር ለጌታ ይሁን!

ልሳን፣ የጸጋ ሁሉ ባለቤት እና ሰጭ ከሆነው ይልቅ ተፈላጊ ሆነ። በኢየሱስ አምኖ መዳን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ያህል፣ ልሳን መደረቢያ፣ የቅድስና፣ የመብሰል ማእረግና መለኪያ ተደረገ። በጉባኤ በልሳን መጸለይ፣ ተርታ ምእመንን ከዋነኞቹ “መንፈሳውያን፣ ቅዱሳውያን” ለየ። በግ በግ እንደ ሆነ፣ ጸጋ እና የጸጋ አሠራር ልዩ ልዩ እንደ ሆኑ፣ ሰጭው አንድ እንደ ሆነ ለማሰብ ያኔ አቅም አልነበረኝም። በልሳን ያልጸለይከው እምነት ስለ ጎደለህ ነው ተባልኩ፦ አማጥኩ፤ ላብ፣ ግራ መጋባት እና እንቅልፍ እንጂ እምነት ጠብ አልልልህ አለ።

ባልበሰለ ትምህርት የተሰናከለውን፣ እንግዲህ ቤቱ ይቊጠረው! ደግነቱ፣ ጌታ መሓሪ ነው፤ የእርሱ የሆኑትን፣ የሚሹትን የሚጠብቅበትና የሚመራበትን ብልኃት አጥቶ አያውቅም።

ሳይቆይ፣ ሙሉ ወንጌል፣ በአስተምህሮ ዓይነቶች፤ በጸጋ ስጦታዎች አጠቃቀም ታመሠች። እሳቱ ከውስጥ ነበርና የማኅበሩን አንድነት ተፈታተነ። ቆይቶ፣ በሌላ በረት ከነበሩት አማንያን ጋር “ቃል ብቻ” “መንፈስ ብቻ” መባባል ተጀመረ። በ “መንፈስ ብቻዎች” ዘንድ ስለ ዶክትሪን ማንሳት ቀርቶ ማሰብ ሥጋዊነት መሰለ። ነገር በራእይ ነው፤ በትንቢት ነው፤ በእውቀት ቃል ነው፤ በህልም ነው። ይህም መልካም ነው። የፍቅርን ህግ፣ ቃሉን እና እውነታን ይገነዘባል ወይ? የሚለው ግን አብሮ አልታሰበም። የጸጋዬ ገብረ መድህንን ቴአትር መመልከት፣ በሬዲዮ ዜና ማድመጥ (የዓለም ወሬ ነዋ!)፣ ፖለቲካ እና ማሲንቆ ጋ መድረስ (የዛሬን ማን አለመ?)፤ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከ “መንፈሳዊ” መጻሕፍት ውጭ ሌሎች መጽሐፍትን ማንበብ የማይደገፍ ሆነ። እውነትን ከቅርብና ከሩቅ እንዳናያት ተሸብበን በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውስጥ ብቻ ፈላለግናት! ነፍስን ከአእምሮና ከእውቀት ነጠልናት! አምላክ ፈጥሮ ባኖረን ምድር ላይ፣ በማኅበረ ሰብ ውስጥ መገኘታችንን ክደን አሁን ድረስ ብዙ ዋጋ ከፈልንባት!

ከላይ እንዳሰማኋችሁ፣ ባለመድኃኒቱ የእሳት መድኃኒት ላከ። የአብዮት እሳት ሰደደ። ኬላ ክልሉን ናደ አነደደ። ወዲያ ወዲህ ቆሞ በጎሪጥ ሲተያይ የኖረ ሳያስበው ባንድነት አደረ። ጠላት የጋራ ጠላት ነበረና፣ ከኢየሱስ ጋር የወገነ ሁሉ፣ አንድነቱን መሰከረ።

ዛሬ ስለ መንፈስ ቅዱስ መሪነት፣ ስለ ቃሉ እውቀት እና መካከለኛነት ጥያቄ የሚያነሳ ብዙ ሰው ያለ አይመስለኝም። የዛሬ ጥያቄ እንደ ጥንቱ፦ የጌታን እና የቤተ ክርስቲያኑን ሥልጣን አውቆ ስለ መታዘዝ እና አለመታዘዝ ነው፤ በቅድስና ስለ መኖር አለመኖር፤ መንፈስን ስለ መለ-የት፤ ስለ ግለኛ ክርስትና እና ስለ ማኅበራዊ ክርስትና ነው። ዛሬ በአተረጓጎም ነው፦ ብልጽግና ከፍታ ስኬት እንዲል ቃሉን ስለ ማስገደድ ነው። መረጃ ስለማይሻ እውቀት ጠልነት ነው። ከስነ ምግባር የጎደሉ አቋራጮችን ስለ መቀየስ ነው። የዓለምን ማእረግ፣ እንደ መቊጠሪያና መቆጠሪያ ስለ መፈላለግ ነው።

የያኔዋ ሙሉ ወንጌል እንደ ወጣትነቷ ሳይሆን፣ መንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎችን እንዳደላት፣ ሌሎችን የክርስቲያን ማኅበራትን አበልጽጋለች፤ ይኸ አጠያያቂ ሆኖ አያውቅም። በትጋቷ የመንግሥቱን ድንበር አስፍታለች፤ መንግሥታትን ድል ነሥታለች፣ የባዕድ ጭፍሮችን አባርራለች። ኦርቶዶክስ አማኝ አባቴም እንኳ ከብዙ ዓመት ትዝብት በኋላ፦ እነዚህ ሙሉ ወንጌሎች ባይኖሩ አዲሳባ ትወረር ነበር ብለውኛል።

ሙሉ ወንጌል በአጋንንት ለታሠሩ ነፃነትን አውጃለች (ያኔ ትርምስ የመሰለኝ አንዱ ይኸ ኖሯል)። ነፍሳትን ከጥግ ጥግ ማርካለች። ሥርዓተ አምልኮአቸው ለየት ያለ አብያተ ክርስቲያናት ያለመንፈስ ነበሩ ማለት ግን አይደለም። እነዚህኞቹም፣ ያው መንፈስ እንዳደላቸው ቃሉን ከመሠረቱ የማጥናትን ልማድ፣ የቤተ ክርስቲያንን ማኅበራዊ ግዴታዎችና ተቋማዊ አሠራሮችን በማጋራት ድርሻቸውን ተወጥተዋል።

በሕይወት ጒዞ ላይ ለውጥና ሂደትን ከአንድ ወገን ብቻ መጠበቅ ስህተት ነው፤ ለውጥ ሁሌ ዘርፈ ብዙ፣ ከሁለት አቅጣጫ ነው፦ በመስጠት እና በመቀበል ነው። በመቀባበል ነው። መቀባበል እና መከባበር መንትዮች ናቸው። አምላካችን በጥበቡ ሲፈጥረን ልዩ ልዩ አድርጎ ነው። አንዱ ያለሌላኛው እንዳይኖር፣ ከሌላኛው የሚቀበለውና ለሌላኛው የሚያቀብለው ጸጋ እንዲኖረው አድርጎ ነው። የአንድ አባት ልጆች ናቸው፤ ሁለት ሦስት አይደሉም፤ አንድ ናቸው። መካነ ኢየሱስ ሙሉ ወንጌል ቃለ ሕይወት መሠረተ ክርስቶስ ስም እንኳ አይለያቸውም፤ ሊለያቸው አይገባም። እዚህም እዚያም ኢየሱስ፣ ትናንት ነገ ለዘላላም ኢየሱስ ነው! እረኛው አንድ እንደ ሆነ መዘንጋት፣ በሌላ በረት ውስጥ ያሉትን እንደ ቤተ ሰብ ሳይሆን እንደ ሌላዎች መቍጠር፣ ከክልል ፖለቲካ አስተሳሰብ ብዙ አይርቅም!

ሙሉ ወንጌል እንደ ሌሎቹ ሁሉ እዚህ የደረሰችው በሚታዩና በማይታዩ በዓለም ዙሪያ በተበተኑ፣ ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ፣ በሰማያዊ ሥፍራ በተከማቹ ቅዱሳን ፀሎት ነው። ከሁሉ በላይ፣ ፀሎት ወደ እርሱ በሚያርገው፣ በአብ ቀኝ በተሰየመው፣ ዘወትር ሊያማልድ በሚኖረው፣ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር በተሰጠው፣ ሊፈርድ እና ሊታደግ፣ ሁሉን አዲስ ለማድረግ ተመልሶ በሚመጣው በኢየሱስ ምልጃ ነው። በሰጠው ጸጋ፣ ባመኑት ልጆቹ ሥራውን ቢሠራም፤ ኢየሱስ እና መንፈሱ በሠሩት ሰው አይሞገስ! (ሉቃስ 17:10)

የሙሉ ወንጌል ሕንፃዋ ለአብዮት ጥይት ምዝገባ ጣቢያ በዋለበት ዘመን፣ በኢየሱስ ስም በደጇ ፈክሮ ዝቶ የአጋንንትን ሠራዊት አራውጦ ያላለፈ አማኝ አልነበረም። መጽሐፍ እንደሚል፦ አንድ ብልት ቢሠቃይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሠቃያሉ። ያ ያኔ ነው። ዛሬ፣ ለጌታ ክብር ይግባውና፣ በህንፃ ላይ ህንፃ ገንብታ የ57 ዓመት በረከቶቿን በዝማሬ የምትቆጥርበት ሁኔታ ላይ ትገኛለች፤ ደግሞ መጽሐፍ እንደሚል፦ አንድ ብልት ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እንኳን ደስ አለን!

መቀባበል ሲጠፋ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ትታመሳለች፤ ቤተ ክርስቲያን ከታመሰች አገርም ይታመሳል። ቤተ ክርስቲያን ከበረታች፣ አገር እና ሕዝብ ይበረታል። ዛሬ ውዥንብር የበዛብን ለምን ይመስለናል?

ሃምሳ አራት ዓመት በሰው አቅም ሲሠላ ረጂም ዘመን ነው፤ ይህን ያህል ዘመን በጌታ ቤት ቆሞ መዘመር ምንኛ መታደል ነው። ግማሽ ምዕተ ዓመት ቀላል ያይደለ ጒዞ ነው። ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ለሆነለት ለጌታ ግን ምኑም አይደለም! ገና ከእልፍ አእላፋት መላእክት ጋር ለዘላለም እንዘምራለን። ሃሌ ሉያ!

ዘመን ሲለዋወጥ የሰውም ቃና ቁመና አሳብና ልማድ መለወጡ አይቀርም። ዘማሪያኑ ለብሰውት ያየሁት ነጭና አረንጓዴ ቀሚስ፣ ዛሬ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ተተክቷል። መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተተክሏል። እነዚህ ልማዶች በአፄውም በደርግም ዘመናት አይታሰቡም ነበር። “ቤቴ በሰማይ ነው፣ ከዚህ ምንም የለኝ” ብሏላ! አንደኛውን ስህተት ለማቅናት ሌላ ስህተት ፈጽመን ይሆን?

ሙሉ ወንጌል ዛሬ ከዋነኞቹ አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ነች፤ ዛሬ ነገረ መለኮትን ታስተምራለች። እግዚአብሔር ይመስገን። በአገር ደረጃ በተዋቀረው “ካውንስል” አባል ነች። አገሪቱን የሚመሩት ጠቅላይ ሚንስትር እና ከፍተኛ ሹማምንት ከምእመኖቿ መሓል የወጡ ናቸው። ጠ/ሚሩ በንጉሥ ቊስጠንጢኖስ አምሳያ ቤተ እምነቶችን በመላ በመንግሥታቸው ሥር አሰባስበዋል። በ “ሃይማኖት አይለያየንም” ቤተ እምነቶችን ቀድሞ ያሰባሰበ የ6/66ቱ ደርግ መንግሥት ነበረ፤ ያኔ ዶሮን ሲያታልሏት ነበረ፣ ከመነሻው አላማረም ነበረ።

የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት (አማንያንን አይደለም) ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነትና መልክ የመንግሥት አካል ተደርገዋል። የተደላደሉ ይመስላል፣ አንዳንዶችም በክርስቲያናዊ ሹክሹክታ አንዳንዴም ባደባባይ አምልጧቸው “አሁን ገና የክርስቲያን መንግሥት አገኘን” ብለው ሲፈክሩ ይሰማል። ትክክለኛውና የኖረ ጥያቄ ግን ይህ ነው፦ የቤተ ክርስቲያን ጌታዋና መታመኛዋ ማነው ነው? ምስክርነቷስ በእግዚአብሔር እና በዓለም ፊት ምን ይመስላል? በእውነት እና በፍትኅ ጉዳይ ከደኃው ጋር ወግና በደልን ተቃውማ ድምጿን አሰምታለች? ወይስ ተመሳስላ ድምጿን አጥፍታለች?

ትናንት ቤተ መንግሥት ቀርቶ ኪራይ ቤት ውስጥ መገኘት መከራ ያስከትል ነበር። ዛሬ ከቤተ መንግሥት ደጅ ለግብር፣ ለሹመት፣ ለፀሎት፣ ለትንቢት ወጣ ገባ ማለት በዝቷል። በዚህ ልማድ ውስጥ፣ እውነትን የሚቀናቀን ስውር ወጥመድ አይኖርበትም ማለት አለማስተዋል ነው። የእግዚአብሔር ታላቅነት በትንሽነት ውስጥ የሚገለጠውን ያህል፣ ሕዝብና ንብረት ሲበዛ ራስን በማተለቅ አይተካም ማለት ሰውን አለማወቅ ነው (ራእይ 3:17-18)።

የጥንቷ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን፣ ከሮም ንጉሥ ጋር ተደምራ፣ በሥልጣን ቅርምት ክብሯን ጥላ ራቊቷን ቀርታ ነበር። ዛሬስ ካለፈው ተምራለች? የቤተ ክርስቲያን ምስክርነቷ ካልታመነ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ከዓለማዊነት ካልተላቀቁ፣ ጌታ ስለ ስሙ ሲል የሚያደርገው አለ ማለት ነው! አንድ ነገር ግልጽ ነው፤ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ስደት የሚያጠራትና የሚያፀናት፣ እንደ ምቾትና እንደ ብልጽግና የሚፈታተናት የለም።

ደቀ መዝሙር የጌታውን ፈለግ የሚከተል ነው። ኢየሱስን መከተልና ወደ እርሱ መጠጋጋት መንትዮች ናቸው። ፖለቲከኞች ምን ያህል ወንጌል አማኝ ቢሆኑ፣ መ-መ-ዘን ያለባቸው በብቃታቸው እና በቅን ቆራጥ ፖለቲካቸው ብቻ ነው። የመንግሥት እና የቤተ ክርስቲያን መጣመርና መደራደር የሚያጎድፈው ቤተ ክርስቲያንን ነው። ይኸ ብዙ ጥበብና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው። በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ያለው ለዚሁ ነው። የዛሬ ፈተና ስደት የሌለበት የ “ከፍታ” ምኞት ፈተና ነው። የብልጽግና ምኞት ፈተና ነው። የስኬት “ማይንድሴት” ፈተና ነው። ጒዞአችን አደጋ የሌለበት ከመሰለን ተታልለናል። “ታላቅ ታላቅ በረከት” ይላሉ፤ ከሠጭው ላይ ዐይናቸውን ይነቅላሉ። ደቀ መዝሙርነትን ያቃልላሉ። ያን ጊዜ ወድቀዋል።

ሃምሳ አራት ዓመት። ዝማሬ በልብ ዝማሬ በጉባኤ። በወጣትነት እድሜ ልባቸውን የሰጡትን ኢየሱስን፣ እስከ ሽበት ይዞ መዝለቅ እንዴት መታደል ነው! የሕዝቡ እረኛ በለመለመ መስክ፣ በእረፍት ውሃ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሸለቆ ጠብቆ ማዝለቅ የተቻለው ነው። አንዳንዶች በክብረ በዓሉ ሳይሳተፉ ቀድመው ወደ ጌታ አገር ተሻግረዋል። ምንም አልቀረ-ባቸውም!

በቪዲዮው ላይ፣ ለስድሳኛው ዝግጅት እየታሰበ መሆኑ ተነግሮናል። ዝግጅቱ፣ ስለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እና ስለ ሕዝቡ ታሪክ ሐውልት እንደ መሆኑ፣ ሳይዝረከረክ በተሻለ ሁኔታ መቀናበር ይኖርበታል። የዚያ ሰው ይበለን።

~ ምትኩ አዲሱ

© 2024 by Mitiku Adisu. All rights are reserved.

ኅብር ሕይወቴ | የማርያም ታላቅ አእምሮከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | መንበርና እርካብ | Land of the Shy, Home of the Brave | የማለዳ ድባብ