ሐተታ ግምገማ፦ ኅብር ሕይወቴ፤ ባሕሩ ዘውዴ (አዲስ አበባ፣ ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት፣ 2015 ዓም፣ 313 ገጽ)፤ ገምጋሚ፦ ምትኩ አዲሱ
ኅብር ሕይወቴ ግለ ታሪክ ነው፤ የግለ ሰብና የትውልድ ታሪክ ነው። ኅብሩ፣ ውስብስብና ሊበተን የነበረን ሕይወት ያያያዘ፣ ተርጒሞ የቀረፀ ነው። ታሪክ ያለተራኪ አይደለምና፣ ዓላማ የለሽ አይደለም፤ ያለ ዐውድም አይደለም። ግለ ታሪክን መፃፍ፣ ሌላው ከዳር ሆኖ እንደሚጽፈው አይቀልም። የታሪክ ነጋሪው ሕይወት ገና ስላልተጠናቀቀ፣ ኋላ የሚፀፅት ነገር እንዳይገኝ ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል። የቱን ምን ያህሉን በምን መልኩ፣ የቱን ማስቀደምና ማስቀረት እንደሚገባ ማወቅ ቀላል አይሆንም። ራሴን አለቅጥ አተለቅሁ ይሆን? የአንባቢን ስሜት ለረብ በዘበዝኩ ይሆን? ጠበሉን የቀመስኩለት ገብርኤል ቢታዘበኝስ? ማለት ይኖራል።
ደራሲው፣ ታሪክን አጋሩ አድርጓታልና፤ ታሪክም መረጃ የሚነሳትን አትምርምና፣ በአቀራረቡ ተገቢ ጥንቃቄ እንዳደረገ ያስታውቃል። ሚዛን መጠበቅ፣ ሓፍረትና የእግዚአብሔር ፍርሓት በተመናመነበት ዘመን፣ በጥንቃቄ፣ ሊመሳከር በሚችል መረጃና ምክክር፣ የሚብቃቃና የሚተርፍ ድግስ ቀርቦልናል። በተነባቢነቱ፣ በይዘቱ ስፋትና ጥራት፣ በቊጥብነቱ፣ ነገር ግን በጥልቀቱና በተሻጋሪነቱ፣ የጥሩ ግለ ታሪክ አፃፃፍ መለኪያ እነሆ!
ኅብር ሕይወቴን በጽሞና ላነበበ፣ አንድ ዋነኛ ጥያቄ አድብቶ ይጠብቀዋል። ይኸውም፣ ባለታሪኩ የዘመኑን ጋሬጣ አልፎ እንዴት ይህን የመሰለ ፍሬአማ ሕይወት ሊኖር ቻለ? ማመኻኘት፣ ማላከክ፣ ቂም በቀል እንደ ጧት ጸሎት በበዛበት ማኅበረ ሰብ ውስጥ እየኖረ፣ ከመነሻ ግብ እንዴት አልተሰናከለም? ከራሱ አልፎ ለብዙዎች የመትረፉ ምሥጢር ምንድነው? በአንፃሩ፣ ሕይወታቸው ያለምክንያት የተቀጠፈና የኅሊና ጠባሳ ያሽመደመዳቸውን ቊጥር ስናይ አገራችን ለምን ኋላ ቀር እንደ ሆነች ግልጽ ይሆንልናል። በዚህም፣ አንባቢ የራሱን ሕይወት ለመመርመር ይገደዳል፤ “አገሬ፣ አገሬ” የምንል ሁላችን ለአገራችን ምን የረባ ቊምነገር ሠራን?
በሌላ ሥፍራ እንዳመለከትኩት፣ የኢትዮጵያ ምሑራን ባብዛኛው ተርታውን ሕዝብ የናቁ፣ ከርሱ ይልቅ ያወቁ፣ በአስተሳሰብ የተራራቁ ናቸው (ገጽ 309 አንቀጽ 3፤ ገጽ 48 አንቀጽ 1)። ለሕዝብ ቆምን የሚሉትም እንኳ ትኲረታቸው እርስ በርስ ለመደናነቅ ለመተናነቅ ነው። ፊደል ቆጠርን ለምንል፣ ቋንቋችን ለሕዝብ ቀርቶ እርስ በርስም አላግባባንም። የእንግሊዝኛ ቃላትና ሐረጎች ሳንሸነቊር አናሳርግም። በእንዲህ የደፈረሰ አሳብ ለብዙሓኑ አድማጭ ይጠራል ማለት ጨርሶ መታወር ነው፤ አንጀኛነታችን ተጨምሮበት አለመግባባታችንን አባብሶበታል። ኅብር ሕይወቴ ለዚህ ዓይነተኛ እርምት ነው።
ከደራሲው ሕይወት ትምህርት የሚሆነን ዓይነተኛ ቁምነገር አለ፦ ይኸውም፣ የእውቀት ጥማትና ጥረት መልካም ፍሬ እንደሚያፈራ ነው። (መንግሥት ይህን ያን ለምን አላደረገም? ባጭሩ፣ የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ዓይነት ምክንያቶችን አለመደርደር ነው፣ ነው)። ምድረ በዳ ወይም ማእበል በበዛበት አካባቢም እንኳ ዙሪያ ገባውን ላስተዋለ ውኃና መሻገሪያ አይጠፋም። በሌላ አነጋገር፣ ከዝነኛው ዊንጌት ይሁን ከልዑል መኰንን መመረቅ የሚያመጡት ልዩነት ትንሽ ነው! ደራሲው ከየትምህርት ቤቱ መምህራን የሚጠቅመውን ተግቶ መቀበሉ፣ ርቆ ሳይሄድ፣ እዚያው አዲሳባ ካሉ የውጭ አገር ተቋማት ያለዋጋ (በጉጉቱና በጥረቱ ብቻ) ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛ፣ ጀርመንኛ መማሩ። እነዚህ “እድሎች” ለሁሉም ቅርብ ቢሆኑም፣ ጠቀሜታቸው፣ ቀድሞ ለተገነዘበ፣ ጊዜና ጒልበቱን ላፈሰሰባቸው ብቻ ነው። ደራሲው ለማመኻኘት ለማማረር ጊዜ እንዳልነበረው ግልጽ ነው! እንደ ሂሮዶተስ ተዘዋውሮ አካባቢውን ለመጎብኘት፣ ጠይቆ መልስ ለመሻት ስነ ልቡናውን አዳብሯል፦ “ከመዝናናቱም ባሻገር በዚህ የሽግግር ዘመን ብዬ በምጠራው ወቅት የሠራሁት አንድ ቁምነገርም ነበር። ይኸውም አገሬን እየተዘዋወርኩ መጎብኘት ነው” (ገጽ 83 አንቀጽ 1)። ይህን ያደረገው መጓጓዣና ቴክኖሎጂ እንደ ዛሬ ባልተስፋፋበት ዘመን መሆኑን አንርሳ። የኖረ አንድ ችግር፣ ለአገራችን መልክዐ ምድርና ለሕዝቡ ባህልና ኑሮ ባእዳን ሆነን መገኘታችን ያስከተለብን የተሳሳተ አመለካከት ነው። ወጣቱ ትውልድ (ወደ አድዋ፣ ካራማራ ዓመታዊ ጉዞ፣ ወዘተ) አገሩን ለማወቅ እያዳበራቸው ያሉ ልምዶች በዚህ ረገድ ተስፋ ይሰጡናል። ምሥጢሩ ይኸ ነው:- ለመማርና ለመታረም፣ የማያቋርጥ የማወቅ ጉጉት ማዳበር፣ ትሕትና እና መስዋእትነት ያስፈልጉናል።
ኅብር ሕይወቴ ግለ ታሪክ ነው፤ ደግሞ ግለ ታሪክ አይደለም። የግል የሚባል ታሪክ የለም፤ ማኅበራዊነትን ያጓደለ ማንነት ሊኖር አይችልምና። የኢትዮጵያ ታሪክ ያልሆነ የጉራጌ ታሪክ ብሎ የለም። የትግራዋይ የአማራ የኦሮሞ ታሪክ ተነጣጥሎ ብቸኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ሊሆን አይችልም። ጎሠኝነትን፣ ምሉእ ማኅበራዊነት ያሰኘ ሁሉ ሰብዓዊነቱን ሳያኮስስ አይቀርም። ደራሲው “ወዳጄ” “የልቤ ወዳጅ” “የቁርጥ ቀን ጓደኛዬ” ያላቸውን ግለ ሰቦች በስም ነቅሶ ያወጣ ጎሠኝነት ምንኛ እንዳልተጠናወተው ይታዘባል (መቅድም ገጽ ፱ አንቀጽ 4፤ ምስጋና ገጽ ፲፩)። የአገራችን ትውልድ ዘቅጦ ከገባበት መውጣት ያልቻለው፣ ማንነቱን ከኅብሩ ነጥሎ ለመያዝ በመሞከሩ ነው፤ እኔነቱ በእኛነት ባልታቀፈ መጠን እንደ ባዘነ ይቀራል። የኅብር ሕይወቴ እንደ ዜጋ እንደ ሕዝብ የሚጠቊመን ይህን የአመለካከት ለውጥ እንድናደርግ ነው። ለውጡ፣ ካለፈው ታሪካችን ሌላውን ለማንበርከክና ራሳችንን ለማግነን፣ የምንፈልጋትን መመራረጥ እንድናቆም ነው። ያለፈውን ታሪክ ያለመረጃ እንዳናስተናግድ ነው። እውነትን በቲፎዞና በጩኸት ብዛት ማጽናት እንደማንችል ነው። መረጃ ሲቀርብልን ከማንገራገር፣ የራሳችንን መረጃ ከመፈብረክ እንድንቆጠብ ነው። እውነት ብቻ ነፃ ያወጣል! የደራሲው መምህር፣ “በጥልቅ ሳንመረምር ቸኲለን አቋም መያዝ እንደሌለብን ያስጠነቅቀን ነበር” ያለውን ልብ ይሏል (ገጽ 61 አንቀጽ 3)። ይቺን የኋለኛዋን በጎ ምክር ተቀብለን ቢሆን ኖሮ፣ የኢሕአፓና የመኢሶን መተራረድ በቀረልን፤ ከእነርሱ ኋላ የተነሡት ወራሾቻቸው ስብእናችንን ባላመሳቀሉ ባላጎደፉብን ነበር። የሚያሳዝነው፣ ዛሬም እንደ ያኔው “ልዩ የማጋነን ችሎታ” ተንሠራፍቷል (ገጽ 65 አንቀጽ 3)፤ ጽንፈኛው ትምክህተኛው ነፍጠኛው ሌላኛውን በጅምላ ጽንፈኛ ትምክህተኛ ነፍጠኛ ብሏል (ገጽ 223 አንቀጽ 2 መስመር 7-9)!
ዛሬም፣ እያንዳንዱ የሚጋሩ እሴቶችን ጥሎ የየራሱን እውነት አንግቦ ተነስቷል። ይኸ ዓለም አቀፋዊ የአምባገነንነት ባሕርይ ነው። ደርግና ትውልዱ የአፄ ኃይለሥላሴን መታሰቢያ ለመደምሰስ ብዙ ጣሩ፤ መማሪያ መጻሕፍትን አቃጠሉ። ደርግ ዲሞክራሲያን (ጋዜጣ) አቃጠለ። ኢሕአፓ ከዲሞክራሲያ ሌላ ጽሑፍ ማንበብን በፀረ-ኢሕአፓነት ፈረጀ። በ66 የአፄ ኃይለሥላሴን ሐውልት ከሲኒማ አምፒር ፊት ፈንቅለው የጣሉ ተማሪዎች፣ ከአርባ ዓመት በኋላ ሥልጣን ሲይዙ፣ አዲሱ አፍሪካ ኅብረት ህንፃ ፊት መታሰቢያ ሐውልት እንዳይቆምላቸው ተከላከሉ! ታሪክን በመካድ የኢትዮጵያን ክብር አዋረዱ። ህወሓት-መራሹ መንግሥት ታሪክን በየክልሉ አጠረ፤ እያንዳንዱ ክልል የራሱን አሠማምሮ የሌላውን ያጣጣለ ትርክት ሞነጫጨረ። የየክልሉ ድንበር ሰፋ ጠፋ። መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ብዛት ባለባት ኢትዮጵያ፣ የኦሮምያና የአማራ ሕዝብ ብዛት በእልኽ ስድሳ፣ ስድሳ ሚሊዮን ደረሰ! በሳንትያና ቀመር፦ የታሪክን ምክር የናቊ፣ ታሪካቸውን እንዲህ ያስንቃሉ! ታሪክን ከአፈ ታሪክ ለይቶ ማወቅ፣ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ የሚሆነው ለዚህ ነው።
ጊዜ ቆሞ አይጠብቅም። ከሁሉ አስቀድሞ በዋነኛነት ትልቁን አገራዊ ኅልውናና ዓላማን ማወቅ ይበጃል። አገርን ለዘነጋ መንደር አይቀርለትም። ነገሮችን በስፋት ለሚያይ፣ ያን ጊዜ ብቻ፣ ዝርዝሩና ጥቃቅኑ ቦታ ቦታውን ይይዛል። ያን ጊዜ፣ የግብ ማእዘን የሌለበት እግር ኳስ መጫወት ይቆማል።
የአገራችን ተቋማዊ ኅልውና እና የመሪዎቻችን አገርን ያህል ለመምራት አለመዘጋጀት ሌላኛው አሳሳቢ ጒዳይ ነው። በተለይም ከደርግ ዘመን ወዲህ የተነሡ ባለሥልጣናት፣ የተሸከሙትን አገራዊ አደራ እንደሚገባ ሳያጤኑ፣ የታሪክም ግንዛቤ ሳይኖራቸው ብዙ ጒዳት እያስከተሉ ይገኛሉ። የሞት ዳኛ ይመስል የባለሥልጣን ሥራው “መከልከልና መፍቀድ” አድርገው በጠባቡ የሚያዩ ጥቂቶች አይደሉም (ገጽ 272 አንቀጽ 1)። በአንፃሩ፣ እነዚሁ ሹመኞች ሥፍራቸውን ሲለቊ፣ ተተኪያዎቻቸው የራሳቸውን ፈር መቅደዳቸው ለተቋማት አለመዳበር አሉታዊ አስተዋጽዖ አድርጓል። አድዋ ክብረ በዓል አዲስ አበባ እንጂ አድዋ መከበር የለበትም፤ አድዋ ስለሚደረገው የሚመለከተው ትግራይን ብቻ ነው አባባል፣ ከላይ ለተጠቀሰው ዓይነተኛ ምሳሌ ነው (ገጽ 220-227)። ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላም እስከ ዛሬ በልማት ስም ኗሪን ማስነሳት፣ አሮጌውን አፍርሶ አዲስ ሕንፃ መገንባት መደበኛ ተደርጓል። ለገሃርን ማፍረስ “ልማት” እንጂ ትውስታን ማፍረስ፣ ታሪክን መደምሰስ እንደ ሆነ ያላወቁ ውሳኔ ሰጭዎች መሰየማቸው ተዘግቧል (ገጽ 271 አንቀጽ 2)። ደግነቱ፣ እርምት ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆናቸው ውድመቱ በጊዜ ሊታቀብ ችሏል። ታሪክ ያለፈውን መዘገብ ብቻ ሳይሆን ያሁኑን ለትውልድ ለማቆየትና አገር ለመገንባት መሠረታዊ ድርሻ እንዳለው ግልጽ ነው።
እንደ ኻምሲን በሚገለጡ ለውጦች ሁሌ አዲስ ጅማሬ ቢያሰለቸንም፣ ያልተበገሩ፣ በአራት ትውልድ ያልተናወጡ ተቋማት እንዳሉ ማወቅ ተስፋ ይሰጠናል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምሳሌ፣ የደርግ መንግሥት ሲፈርስና ህወሓት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በፍጥነት ናይሮቢን ጊዜአዊ መቀመጫው አድርጎ ዓለም አቀፍ በረራውን አለማቋረጡ (ገጽ 205 አንቀጽ 3)፤ በኮቪድ ሰሞን ሕዝብ ማጓጓዝ አስቸጋሪ በሆነባቸው ጊዜአት፣ እቃ በማጓጓዝ የተወሰደው እርምጃ፣ የናይጄሪያን አየር መንገድና የከሠሩ ሌሎች ተቋማትን ተረክቦ ማስተዳደሩ ያስከተለውን እመርታ መጥቀስ ይቻላል።
የ ኅብር ሕይወቴ ጠንካራ ጎን ተነባቢነቱ ብቻ ሳይሆን ሠፋፊ አሳቦችን አዛምዶ ማቀራረቡ ጭምር ላይ ነው። እርግጥ ነው ደራሲው እንደነገረን “ታሪክን መጨለፍ እንጂ ሙሉውን ማወቅ አይቻልም” (ገጽ 268 አንቀጽ 2)። የተጨለፈውን ለአንባቢው አእምሮ መመጠን ግን በተለይ ለአገራችን ፀሐፍት ሁሉ የተሰጠ አይደለም። ተወዳጁ ቲቸር ክፍሌ ወደ ትምህርት ቤት ሲጓዙ፣ ከየሠፈሩ እየጠበቀ ከኋላ ከኋላ የሚከተላቸውን ተማሪ፣ አዋሽ ገባር ወንዞችን አስከትሎ እንደሚጓዝ ማሳየት (ገጽ 37 አንቀጽ 2)፤ ታሪካዊውን የግንቦት 7/1997 ዓም ሕዝባዊ ምርጫን ከመጀመሪያው የ1994 የደቡብ አፍሪካ ምርጫ ጋር ማስተያየት (ገጽ 273 አንቀጽ 2) አዝናኝ ትዝብት ብቻ ሳይሆን ምፀትም ነው።
የሰው ፍላጎት ሁሌ እንዳቀዱት አይሠምርም። አማራጮች በጠበቡባቸው አገራት፣ አማራጮች ሲገኙ ደግሞ ፍትሓዊነት በጎደለባቸው፣ የ“አጋጣሚዎች” ወሳኝነት ጎልተው ይወጣሉ። የ ኅብር ሕይወቴ ደራሲ የማቴማቲክስ ችሎታው ከክፍል ጓዶቹ የላቀ ቢሆንም በአንድ የታሪክ መምህር አቀራረብ ቀልቡ ተወስዶ አቅጣጫውን ሲቀይር እንመለከታለን። ተመሳሳይ “አጋጣሚዎች” በደራሲው ሕይወት ተደጋግመው ተከስተዋል (ገጽ 49፣ 55፣ 196 አንቀጽ 3፤ ወዘተ)።
“አጋጣሚዎቹ” የእግዚአብሔር እጅ እንደሆኑስ? “ባትታሠር ኖሮ በሕይወት አትቆይም ነበር” (ገጽ 122 አንቀጽ 1)። ደራሲው ስለ እምነቱ በግልጽ አይነግረንም። የአገራችን ምሑራን ምሑርነታቸው እንዳይበረዝ በመስጋት ይመስላል፣ የእግዚአብሔርን ኅልውና ጣልቃ የማስገባት ፍርሓት ይታይባቸዋል። ይህም ከምእራባውያን እውቀት ጋር ያለጥያቄ አብሮ የተወሰደ፣ ኃይማኖትን ከሳይንስ ነጣጥሎ ያቃረነ የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “ኢንላይትንመንት” ውጤት ነው። ችግሩ፣ የኃይማኖት እና የሳይንስን ምንነት ካለመረዳት ነው፦ ሳይንስ በመሠረቱ፣ ነጣጥሎ ካየ በኋላ እንዴት እንደሚገጣጠም እና እንደሚሠራ ለማወቅ ይጥራል። ኃይማኖት በአንፃሩ፣ የተለያዩትን አቀራርቦ የሚሠጡትን ትርጉም ለማወቅ ይሻል። በሌላ ሥፍራ እንደ ታዘብኩት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ መሓል ወጥቶ እግዚአብሔርን አለማሰብ ብቻውን ከተዓምር የሚመደብ ነው። “አጋጣሚዎቹ” ደራሲው ከሞት ተርፎ ከእስር በተለቀቀበት ሰዓት፣ ሳይስሙት ምሥጋናቸውን ለእግዚአብሔር በእልልታ ያቀለጡት የእናቱ ጸሎት ውጤት እንደሆኑስ (ገጽ 126 አንቀጽ 2)?
ኅብር ሕይወቴ፣ በተለይ በአገር መሪነት ላይ የተቀመጡ ሁሉ ሊያነብቡትና ሊወያዩበት የተገባ መጽሐፍ ነው። የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድን “መደመር” መጽሐፍ ገዝተው ያሠራጩ አገር ወዳድ ባለሃብቶች ይህን መጽሐፍ ለወጣቱ ትውልድ በማዳረስ ቢተባበሩ አይከሥሩም። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ተመሳሳይ መጽሐፎች ታትመው ለሕዝብ ቀርበዋል፦ አንዳፍታ ላውጋችሁ፣ በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፤ ከጒሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ፣ በፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፤ የሕይወቴ ትዝታ፣ በክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም፤ ሌሎችም። እነዚህ አራት መጻሕፍት በተለይ፣ የቅርብ ጊዜ ታሪኩን ለዘነጋና ግራ ለተጋባ ትውልድ ለዛና እውቀት ሰንቀዋል። በቴክኖሎጂና በመንደር ፖለቲካ ተጣብቦ በመርሳት የተዝረከረከን አእምሮ የማሰባሰብ ጥበብ ቋጥረዋል።
የፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ የብርሃነመስቀል ረዳ እና የኃይሌ ፊዳ ወዳጅ መሆን መቻል፣ ያን ዘመን የታጣ፣ ዛሬ በጣሙን የሚፈለግ እሴት ነው። ከኃይሌ ጋር መወዳጀት፣ ከብርሃነመስቀል ጋር ጠላትነት ሊሆን አይገባም። ከአንደኛቸው ጋር አለመወገን አቋም የለሽ፣ ዓላማ የለሽ አያደርግም። ሕይወት የሚፈካው በሞት ብቻ አይደለም። አጥብቆ ሕይወትን በመውደድ፣ ለመኖርና ሌላውን ለማኖር በመጣር ጭምር ነው። ደራሲው በኅብር ሕይወቱ እንዳመለከተን፣ የመኖር ነገረ ሥራዋ ውስብስብ ነው። የሕይወት ውበቷ፣ ልዩነት በኅብር መገኘቱ ላይ ነው። ሽብሩ ተድላ በሕይወት መኖራቸው ለቤተ ሰባቸው፣ ለሚወዷት አገራቸው ያስገኘውን ጥቅም አለመገንዘብ አይቻልም! መሞት ያልተገባቸው ብዙዎች እንደ ሞቱ ላፍታም አንዘነጋም፤ አሁን ድረስ። ማኅበራዊ ኑሮን በአንድ ፈር ብቻ መቋጨት የሚሹ አንዱንም ፈር ሳያገኙት ይቀራሉ። ከተካረረ ሁለት ብይን፣ ሦስተኛ ፈር መቅደድ እንደሚቻል መገንዘብ የተሻለ አብሮ ያኖራል። ለዚህ እሴት መጥፋት በዋነኛነት የእግዚአብሔር ፍርሓት መሸርሸር ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል። ከእግዚአብሔር ፍርሓት ውጭ ስለ ሰብዓዊ መብት (ዘር ፆታ ኃይማኖት ሃብት ሳይለይ፣ ስለ እያንዳንዱ ሰው ክቡርነት) ሙሉ ግንዛቤ ማግኘት አይቻልም፤ ሰውን (ወንድና ሴቱን) በመልኩ እንደ ምሳሌው ፈጥሯል ይላል (ዘፍጥረት 1፡26-27)። ዘውዳዊው፣ አብዮታዊውና ክልላዊው መንግሥታት ተራ በተራ የዘነጉት እውነት ነው። ሁለተኛ፣ የማኅበራዊ እሴቶች መባከን ምንጩ፣ የትምህርት ጥራት መውደቅና የታሪክ ብርሃን መና-ቅ ነው። ውጤቱ፣ እርስ በርስ መናናቅ፤ መረጃ በሳሳበት መሠረት ላይ ህንፃ መገንባት፤ ለራስና ለሌላው የተሳሳተ ትርክት መፍጠር ነው። ውጤቱ፣ ማእበል ሲነሳ መናጋትና መፍረስ ነው። በተወሳሰበ፣ ፈጥኖ በሚፈረካከስ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ኅብር አስተሳሰቦችን አለማጠናከር ከኪሳራም ኪሳራ ነው።
≈∞≈
ለሁለተኛ እትም ቢረዳ፦ ገጽ 28 እና ገጽ 36 ፎቶግራፍ ከግርጌ “ከግራ ወደ ቀኝ” ይታከልበት። ገጽ 74 ግርጌ ማስታወሻ “አንፊሎ” ወረዳ እንጂ አውራጃ አይደለም። ገጽ 86 ከአናቱ መስመር 10 “በተለመደው ዳተኝነታቸው እግራቸውን ሲጎትቱ” እንግሊዝኛውን “dragging their feet” አባባል ለማይረዱ በ “ሲወለጋገዱ/ሲጓተቱ/ሰበብ ሲያበዙ/ሲለግሙ”? ይተካ። ገጽ 105 አንቀጽ 2 መስመር 5 “የአንድ አብዮታዊ ሕይወት በሺ ፀረ-አብዮተኞች ሕይወት ይመነዘራል” “የአንድ አብዮተኛ/አብዮታዊ ጓድ ሕይወት?” ይተካ። ገጽ 110 አንቀጽ 3 መስመር 7 “አንጻራዊ የግል ነፃነት (privacy) ለማግኘት ቻለ” እንግሊዝኛውን አሳብ ለማይዙ ቀለል ይደረግ (መጋረጃ/አጎበር ለማግኘት በቃ/ቻለ?)። ገጽ 121 አንቀጽ 1 መስመር 7 “በልቶ የማይጠግበው የደርግ የግድያ መኪና ዋጣቸው” “killing machine” እንግሊዝኛውን አባባል ለማያውቁ ግልጽ ይደረግ። ገጽ 139 አንቀጽ 1፣ መስመር 2 ላይ “ታደሰ” የትኛው ታደሰ እንደ ሆነ ይጠቀስ። ገጽ 162 አንቀጽ 1 መስመር 8 “የቤቶች ኪራይ አስተዳደር” በ “ኪራይ ቤቶች አስተዳደር” ይተካ። ገጽ 249 አንቀጽ 4፣ መስመር 7 “ነገሩ የዶሮውንና የዕንቁላሉን አዙሪት ዓይነት ነው” የእንግሊዝኛውን አባባል ለማያውቁ ግልጽ ይደረግ (ከዶሮና ከእንቁላል የቱ ይቀድማል ዓይነት ነው?)። ገጽ 265 አንቀጽ 1፣ መስመር 6 “ድማዳሜውን” በ “ድምዳሜው” ይተካ። ገጽ 268 አንቀጽ 3፣ መስመር 10 “በማበረታቱ” በ “ማበርታቱ” ወይም “በማበረታታቱ” ይተካ። ከገጽ 276 አናት፣ መስመር 3፣ “የፕሮፌሰር ኤፍሬም እንቅስቃሴ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደ ተቋጨ ሁሉም የሚያውቀው ነው” የሚለው ሁሉም የሚያውቀው ስላልሆነ ግልጽ ይደረግ። ገጽ 309 አንቀጽ 3 መስመር 12 “ቁልፍ ንግግሬ” (keynote speech/speaker/presentation በ “መክፈቻ ንግግሬ” ቢተካ?)። 7/27/2023
የማርያም ታላቅ አእምሮ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | መንበርና እርካብ | Land of the Shy, Home of the Brave | የማለዳ ድባብ