የማለዳ ድባብ
ሐ ተ ታ ና ግ ም ገ ማ
[የአዳዲስ ግጥሞች መድብል]፤ 2009ዓ.ም፤ አ/አ፤ አታሚ አልተገለጸም፤ 10ዶላር፣ 100 ገጽ
የማለዳ ድባብ፣ ለ በዕውቀቱ ሥዩም አራተኛ የግጥም ሥራው ነው። መጽሐፉ ሦስት ክፍሎች አሉት፤ “ግጥምና የዘመን መንፈስ” [ገጽ 5-9]። ግጥሞች [ገጽ 17-91]። “ጉደኛ ስንኞች” እና “ሙሾና ባለቅኔ” [ገጽ 93-100]። መድብሉ፣ ቀድሞ ካስነበባቸው ላይ አዳዲሶች ተጨምረውበት የተዘጋጀ ነው [ገጽ 9]። የትኞቹ አዳዲሶች እንደሆኑ አልተገለጸም።
ግጥም ከስድ ንባብ ይልቅ የግል እይታዎችን፣ ማህበራዊ ትረካዎችን ለመቋጠርና ለማስታወስ ይረዳል፤ ቅኝቱና አወራረዱ ለጆሮና ለዐይን ይጥማል። ግጥም ማህበራዊ እሴት አለው፤ በሥልጣን ለሚባልጉ እርምት ለመስጠት [“ይድረስ ለጥም ሚኒስትር”፣ ቁ.71]፣ የሕይወትን አጭርነት ለማሳሰብ፣ ከሚታየው ውጭ የላቀ ተስፋ እንዳለ ለማወጅ፣ የግለሰብ ህልውና በማህበራዊ ኃይላት እንዳይደፈር ለማስከበር፣ ወዘተ።
[1] የመጀመሪያውና ሦስተኛው ክፍል፣ ማለትም፣ “ግጥምና የዘመን መንፈስ፣” “ጉደኛ ስንኞች፤” እና “ሙሾና ባለቅኔ” ጠለቅ ያለ ጉዳይ አዝለዋል፤ ግን ምን ያህል ተብራርተዋል? ምን ያህል አሳማኝ ናቸው? ዋና ዋናዎቹን እንመልከት፦
[ገጽ 5] “ኢትዮጵያ የአንባቢና የጣፊ አገር ሳትሆን የተናጋሪና የአድማጭ አገር” ነች። ማንበብ መጻፍ የሚችሉ ሁሉ ያነብባሉ፣ ይጽፋሉ ማለት አይደለም። ስንቶቻችን ከአገራችን ዋነኛ ቋንቋዎች ስንቶቹን እንሰማለን እንናገራለን? ወይም ለመማር ምን ጥረት አደረግን? ግንዛቤአችን የተሟላ እንዲሆን፣ የግል እይታችን ሁሉ-አቀፍ እንዳይመስለን፣ የምንናቆርበትን ወንዝ ለመሻገርና እርስበርስ ለመያያዝ ይህ ወሳኝ ነው።
[ገጽ 8] “አንድን አሪፍ ገጣሚ አሪፍ የሚያደርገው ትልቅ ሀሳብ ማንሳቱ [ሳይሆን] ሀሳቡን አሳምሮ የሚገልጥለትን ምስል ከቃሎቹ ሁሉ መርጦ መጠቀሙ” ነው? “ትልቅ ሀሳብ” ምንድነው? ሃሳብና ቃላት የሚነጣጠሉበት ሁኔታ አለ?
[ገጽ 9] “ገጽታው በተረበሸ፣ እንደ ዝግመተ ለውጥ በድንብር በሚመራ አገር ውስጥ እየኖሩ በሰከነ ቋንቋ፣ ወግ ያለው ሥነጽሑፍ የሚያቀርቡ ደራሲዎች ካሉ ከዘመናቸው የመነኑ መሆን አለባቸው።” “የሰከነ ቋንቋ” ምን ማለት ነው? በማን መስፈርት? “ወግ ያለው” ሥነጽሑፍስ? አብዮት [ረብሻ፣ ዝግመተ ለውጥና ድንብር አመራር] የተካሄደባቸውን አገራት [ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ ኢትዮጵያ፣ ጀርመን፣ ግብጽ፣ እሥራኤል፣ ኢራቅ፣ ዚምባብዌ፣ ወዘተ] ያበረከቱትን ጥልቅና ዘመን ተሻጋሪ ቅኔዎችን መቃኘት ይህን ድምዳሜ አጠያያቂ ያደርገዋል። አካባቢአችን በእኛ ላይ፣ እኛም በአካባቢአችን ላይ ተጽእኖ ማሳደራችን እርግጥ ነው። ባለቅኔ ደግሞ ጥሪው፣ የሚታየው ዘላለማዊ እንዳይደለ፣ ዘመን እንደሚሽረው ማስታወስ ነው፤ አድሮ እውን የሚሆን ህልም መዝራት ነው። ባለቅኔን ከሌላው የሚለየው በሚታየው አለመነዳቱ፤ የንስር ዐይን መታደሉ ነው። ፐርሲ ሼሊ የባለቅኔዎችን ማህበራዊ ድርሻና ኃያልነት ሲያጎላ፣ “ማንም ያላወቀላቸው ህግ ደንጋጊዎች ናቸው” ብሎ ነበር።
[ገጽ 98] “ሰውን ከሌሎች እንስሳት የሚለየው፣ ሞት እንደማይቀርለት ማወቁ ነው። እና ለመቀበል አሻፈረኝ ይላል፤ ምናቡን የሙጥኝ ብሎ ሞት የሌለበትን አገር ይፈጥራል፤ ሞት ሆይ መውጊያህ ወዴት ነው ብሎ ይፎክራል፤ መታሰቢያውን ሞት ለጊዜው ወደማይደርስበት ቦታ ያሻግራል።” እንደዚያ ነው ነገሩ? ወይስ ጭፍን ግለኛ ድምዳሜ ነው? በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ ሰውን ከእንስሳ እንደሚለየው ብንክድ እንኳ፣ ኢየሱስ ከሙታን ለመነሳቱ የታሪክ መረጃና የዐይን ምስክሮችን ወደ ጎን ብናደርግ እንኳ። የማክስ ፕላንክ ኢንስቲትዩትና ሌሎችም፣ ከሞት ወዲያ ስለ ነፍስ ህያውነት ያቀረቡትን ሳይንሳዊ መረጃ መመልከት ብቻ ቢያንስ ከዚህ ዓይነቱ ድምዳሜ ያግደናል! ዘመን የከሓዲያን ሆኖ አያውቅም፤ የዛሬዪቱ ሩስያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ወዘተ፣ የጠንቋይና የኮከብ ቆጣሪ መነኻሪያ መሆናቸው ምን ይጠቁመናል? ከኃይማኖት ላይ ሳይተከል ያበበ ማህበራዊ ስነምግባር [አባት እናትህን አክብር፣ በሐሰት አትመስክር፣ ሌላውን ሰው እንደራስህ ውደድ፣ ወዘተ] የለም።
[ገጽ 97] “ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ‘ጎሕ ጽባሕ’ በተባለ መጽሐፋቸው፣ ‘ይህ ዓለም የተድላና የደስታ ብቻ ሳይሆን፣ የመከራና የሐዘንም ስለሆነ ብዙ ዘመን ቢኖሩ ጥቅሙ ምንድነው? ጥቂት ዘመን ቢኖሩስ ጉዳቱ ምንድነው?’ ብለው ሰብከዋል። ይቺን ከሰበኩ ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ ጣልያን ሞት ጭኖ ሲመጣ ብላታ ረጅም ዘመን መኖርን መርጠው ወደ ኢየሩሳሌም ሸሽተዋል” ይለናል። ይኸም የቸኮለ፣ ጥልቀት የሌለው ጅምላ ድምዳሜ ነው። ደስታና ሐዘን በሰው ሕይወት ውስጥ መፈራረቃቸው አጠያያቂ አይደለም። የኅሩይ ጽሑፍ መነሻ አሳብ፣ የእድሜ መርዘምና ማጠር ሳይሆን ቁምነገር ሠርቶ ስለ ማለፍ ነው። ኅሩይ የንጉሠ ነገሥቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ነበሩና፤ ሞታቸው ለምን ወይም ለማን እንደሚጠቅም ግልጽ አይደለም። እኝህ ሰው በፖለቲካ፣ በስነጽሑፍና በዲፕሎማሲ ለአገር ምን ቁምነገር ሠርተው እንዳለፉ የምናውቅ ስንቶች ነን? እውን ኅሩይ “ረጅም ዘመን መኖርን መርጠው” ሸሹ? እውን ፈሪና ከዳተኛ ናቸው? የአንድ የከበረን ሰው ታሪክ በአንድ ሐረግ ማጉደፍ ለምን አስፈለገ? [ስለ ኅሩይና ሌሎች ቀደምት መሪዎች፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በዚህ ዓመት ያሳተሙትን “የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮጳና መካከለኛው ምሥራቅ” መመልከት ተጨማሪ መረጃ ይሰጠናል።
[2] የማለዳ ድባብ 59 ግጥሞችን አካትቷል። የመድብሉ መክፈቻ፣ መተላለፍያና መዝጊያ በተስፋ ማጣት የተቀለመ ይመስላል፤ “ሲፈርድባት ኢትዮጵያ” [ገጽ 5]፤ “የኔ ዘመን ቃናው የጠፋበት ቅኝቱ የተበላሸበት ዘመን” ይለናል [ቁ.9] ወይም “የተካደ ትውልድ” [ቁ.28]፤ “ሕይወቴ ሲጨመቅ ይሄ ነው ምስሉ / ... የቢራ ጠርሙዞች ... ንዋያተ ሱሶች ... የሚያርጉ ጭሶች ... ባመድ የተሞሉ ገጣባ ሳህኖች። [ቁ.17] “በምን ይገለጻል፣ የትውልዴ አበሳ፣ በመንበርከክ ብዛት፣ መራመድ የረሳ” [ቁ.72]። “መከራን በበርሜል፣ መጽናናትን በፍኝ፣ ከዘመን ያተረፍሁ” [ቁ.76]። “ከጥቁር አፈር ጋራ እድሜአችንን እየፈጨን... ለብሳናው ለግራሩ ላለቀው በመጋዝ ታርዶ ... ምነው ደረት የማንመታ” [ቁ.90]። በሌላ ሥፍራ፣ ዮሐንስ መኮንን የተሰኘ፣ “የኔ ትውልድ እድለኛ አይደለም። በሽግግር ጊዜ የተገኘ ስለሆነ ይመስለኛል፤ ከቀደምቶቹ በወጉ የተረከበው እሴት የለውም። ወይም በተረከብነው ላይ መስማማት አልሆነልንም። አንዳችን የምናከብረውን ሌሎቻችን እንዘረጥጠዋለን” ብሏል። ይኸ አስተሳሰብ በትውልዱ መሓል የተንሠራፋ ይመስላል። አደጋ ከፊቱ ተጋርጦ እንኳ ወደ ውጭ እየጎረፈ ነው! እውነታው ይህን ቢመስልም፣ መፍትሔው ምንድነው? የባለቅኔስ [የኪን] ድርሻ ምንድነው? አንድ ነገር ግልጽ እናድርግ፤ ሁኔታዎች እንዲህ ይቀጥላሉ ብሎ ማሰብ የሕዝቦችን ታሪክ ሂደት አለማወቅ ነው። ራስ ላይ ማተኮርና ወደ ውስጥ ማየት ሲበዛ፣ ራስን ወደ መጥላት ያመራል። ሰው ራሱን ሲያቆላምጥ፣ ራሱን ከሌላው ነጥሎ ማየት ሲያበዛ ያኔ የራሱ እስረኛ ሆኗል። ራስን የማተለቅ፣ የውዳሴ፣ የመኮራረጅና አማራጭ አስተያየት የማይታገስ ባህል እንዲህ መንሠራፋት ለምን ይመስለናል? በአንጻሩ፣ ዓላማውን አውቆ መስዋእት የሚከፍል ራሱንና ሌሎችን ነጻ ያወጣል።
ለነገሩ፣ በአፄ ኃይለሥላሴም ዘመን፣ በደርግም የነበረው ትውልድ እንደዚሁ “ቃናው የጠፋበት ቅኝቱ የተበላሸበት” ነበር። መልክና መጠኑ ይለዋወጥ እንጂ ለየዘመኑ የተመደበ ግራ መጋባት ምንጊዜም አይጠፋም። ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነው፤ ተስፋ በሌለበት ወደ ፊት መጓዝ ግን ታሪክና አብሮነትን መገንዘብ፣ በእግዚአብሔር ላይ መታመንና መተማመንን ይጠይቃል። አብዮተኛውን ትውልድ ከዚህኛው የሚያመሳስላቸው፣ በሁለቱም፣ የአገር መሪዎች ከሕዝቡ ተነጥለው ፈሪሃ እግዚአብሔርን መጣላቸው ነው፤ ውጤቱም ለሰው ሕይወት አክብሮት በማጣት፣ ባለመደማመጥ፣ በጠባብነት፣ በግፍ ብዛትና በፍጻሜ ላይ በእግዚአብሔርና በታሪክ ፍርድ ተተርጉሞ አይተናል።
[3] ለውይይት እንዲያመቸን ግጥሞቹን በሦስት እንክፈላቸው? ሀ/ ከምናቡ “ያፈለቃቸው” ለ/ ከእንግሊዝኛ የመለሳቸው እና የሌሎች ገጣሚያንን መነሻ በማድረግ የጻፋቸው ሐ/ [አፈ]ታሪክን በስንኝ የቋጠረባቸው [ቁ.18፣ ቁ.34]። ያፈለቃቸውን ደግሞ እንዲሁ በሦስት እንክፈል? የመጀመሪያው፣ መዳረሻው ላይ በማነጣጠር፣ በከበደ ሚካኤል ስልት “ለማስተማሪያነት” የተጻፈ፦ [ቁ.3] “ሰው ፀሐይን አምኖ፣ ፋኖሱን አይሰብርም” መዳረሻ ነው፤ “ጎሕ ገስግሶ ደርሶ/ ጽልመት ቢያባርርም/ የማለዳ ድባብ ህብሩ ገጹ ቢያምርም” መገስገሻ ነው። [ቁ.17] “ኖሮ ማለፍ ብቻ፣ ጀግንነት ነውና” መዳረሻ ነው። “መርዝም መድኃኒት ነው ሲሆን በጠብታ / እንዲሁም ለተንኮል አለው ቦታ ቦታ” [ከበደ ሚካኤል]። ሁለተኛው፣ የሚወተውት የሚፈልቅ፦ “ላባቴ” ቁ.23፤ [ለእህቱ] “በሞቷ ፊትለፊት” [ቁ.44]። ሦስተኛው፣ በተመስጦ ልቦና የተጻፈ [ቁ.22፣42፤56]።
ግጥሞቹ እርስበርስ የሚጋጩም ይመስላል። ለምሳሌ፣ “ጠብና ጥበብ” [ቁ.53]፦ “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ፣ ጠብን መፍራት፣ ጦርን መግራት፣ ከጋሻ የእበት ማፈሻ መሥራት” ይላል። ጠብ ገፍቶ ሲመጣ መመከት ላይኖር ነው? “ሰቆቃወ በውቄ” ደግሞ፣ “ያኔ ጌቶች ቦርጫቸውን እንደ ጉማሬ ሲያደልቡ / ምመናን ሆይ ንስሓ ሳይሆን ጫካ ግቡ” [ቁ.84 መስመር 32-34] ይለናል። በመጀመሪያው፣ “ጋሻን የእበት ማፈሻ” [ኢሳይያስ “ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ” ብሏል] አድርጉ ነው፤ በሁለተኛው፣ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንስሓ መግባት አቁማችሁ ጦር አንሱ ነው። ለፍልሚያ ሆነ ሰላም ለመፍጠር ጊዜ አለው ማለቱ ይሆን? ንስሓ ለምመናን ብቻ ለምን አስፈለገ? ምመናን ለአገር አልተዋደቁም? በበደል ላይ አልሸፈቱም [ምኒሊክንና አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ]? ጅምላ ድምዳሜ ነው የምለው ለዚህ ነው።
ከመድብሉ አሥራ አንድ ያህሉ ከእንግሊዝኛ የተመለሱና የሌሎች ገጣሚያንን መነሻ ያደረጉ ናቸው። የትርጉሞቹን ጥራት እዚህ አናነሳም፤ ለምሳሌ ያህል፣ የሼክስፒር “መኖር ወይስ አለመኖር” በምን መስፈርት ትርጉም ሊሰኝ እንደሚችል ግልጽ አይደለም። እስቲ ትርጉሙን ከዋና ቅጂው ጎን ለጎን እናስተያይ፤
ለግጥሞቹ መነሻ ካደረጋቸው መሓል ደግሞ፣ እስራኤላዊው አሚኻይ “አልጋዬ ላይ ልሙት” ያለው፣ “አንሶላየ ውስጥ ልሙት” [ቁ.40] ተሰኝቷል። አሚኻይ ግጥሙን ከቀመረበት 5 አንቀጾች ውስጥ የመጀመሪያውና ሦስተኛው ስንኞች ብቻ ተወስደው ሌሎቹ ተትተዋል። “አንሶላየ ውስጥ ልሙት” ሬሳ በነጭ አንሶላ እንደሚጠቀለል ለመግለጽ፣ ወይም የአገራችን ድሃ አልጋ የለውም ለማለት ታስቦ ከሆነ ተገቢና ጥሩ ጥረት ነው። በነገራችን ላይ፣ አሚኻይ ባለቅኔ ብቻ ሳይሆን ጦረኛም ነው። ጀግና ጦረኛ ከምባል፣ ጦርነት ሰልችቶኛል፣ አልጋዬ ላይ ልሙት ማለቱ ለቅኔው የማይረሳ ኅልውና አጎናጽፎታል።
[3] [ሀ] የተመለሱ ግጥሞች፦ ከዬይትስ “ሂ ዊሽስ ፎር ዘ ክሎዝስ ኦፍ ሄቨን = “ህልሜን አደራ” [ቁ.36]። ከሼክስፒር ሐምሌት “መኖር ወይስ አለመኖር” [ቁ.68]።
[3] [ለ] መነሻ የሆኑ፦ ከዬይትስ “ዌን ዩ አር ኦልድ” = “ግን አንድ ሰው አለ” [ቁ.48]። ከአሚኻይ “አልጋዬ ላይ ልሙት” = “አንሶላዬ ውስጥ ልሙት” [ቁ.40]። ከኦማር ኻያም “ሩባያት ክፍል 1፣ ስንኝ 1” = “የምድረበዳ በረከት” [ቁ.51]። ከፓብሎ ኔሩዳ “ቱናይት አይ ካን ራይት ዘ ሳደስት ላይንስ” [በከፊል] = “ከዚህ ወዲያ አልወድሽም” [ቁ.87]። ከገሞራው “በረከተ መርገም” = “በረከተ መርገም 2” [ቁ.56]። የጸጋዬ ገብረመድኅን፤ “የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ”/“የቴዎድሮስ ማመንታት በመቅደላ” [ቁ.34]፤ “ሰቆቃወ ጴጥሮስ”/“ሰቆቃወ በውቄ” [ቁ.84]፤ “ሕይወት ቢራቢሮ”/“ደስታ ቢራቢሮ” [25]። ከገብረክርስቶስ ደስታ “እኔ እወድሻለሁ” [ቁ.29]። “እንደምነሽ ሸገር” [ቁ.64] የመንግሥቱ ለማ “ጉድ ባይ” መነሻው ይሆን?፤ “ኬላ ነኝ” [ቁ.62] የሰለሞን ዴሬሣ “ክቡር ኢትዮጵያውያን” መነሻው ይሆን?
በመድብሉ ከተካተቱት ግጥሞች ሲሦው፣ ለሴትና ስለ ወሲብ ናቸው። በ “ኬላ ነኝ” [ቁ.62] እና በ “ታሪክ የሆነ ሌሊት” [ቁ. 69] ወሲብን በግልጽ አስፍሮታል። የአውሮጳውያኑ ፍሮይድ፣ [በኤሚል ዞላ አድርጎ] የስብሃት ገብረእግዚአብሔር እና የሚላን ኩንዴራ ተጽዕኖ እንዳለበት በዕውቀቱ በሌላ ሥፍራ ነግሮናል [አንድምታ፣ 1998 ዓ.ም፤ ከአሜን ባሻገር፣ 2009 ዓ.ም.፣ ወዘተ]። ሦስቱም ደራሲያን ለእንስት ያላቸው አስተያይ ከተለምዶው ያፈነገጠ ነው ብለን እንለፈው። “ግልጽነታቸው” በአንድ መልኩ እውነታን የካደን ዘመን ግብዝነት ለመውቀስና በግል ያሳለፉት ፆታዊ ምልከታ መነሻ እንደሆናቸው አንዘንጋ።
ቤተሰብ የማህበረሰብ ምሰሶ ነው ካልን፣ ወሲብ ከተከለለት [በወንድና በሴት መሓል በፍቅርና በመከባበር ላይ ከተመሠረተ ትዳር] ሲያፈነግጥ ዝሙትና ፍትወት ይሆናል፤ ፍትወት፣ ስለራስ እንጂ ስለሌላው አይገደውም፣ ሕይወትን ካመለጠች ዳግመኛ አላያትም ብሏልና የቅጽበት ስሜቱን ማርካት እንጂ መግታት አያውቅበትም [ኩንዴራ ከኒቸ ተቀብሎ፣ በዕውቀቱ ከኩንዴራ ተውሶ]፦ “መስጠማችን ላይቀር በየውቅያኖሱ፣ ተነሱ ደንሱ!” [ቁ.59፣ መስመር 21፣22] ሲለን በደስታ ሳይሆን ተስፋ በቆረጠ ድምጽ ነው። ግልጽ እንሁን። ወሲብ የተፈጥሮ ሂደት ነው። እንደ መጸዳዳት እንደ መብላትና መተኛት ተፈጥሮአዊ ሥርአት ነው። ተፈጥሮአዊ ነውና አውራ መንገድ ላይ መጸዳዳት ግን የጤና ጠንቅ ከመሆን አልፎ ለተመልካች ኃፍረት፣ ለሚጸዳዳው ክብር የለሽ አድራጎት ነው። እንደ “ቢግ ብራዘር” ሕዝብ እያየ ግብረሥጋ መፈጸም፣ ግለሰቦቹን ደስ እስካሰኘ [ገንዘብ እስካስገኘ] ምንም አይደለም? የሮምን መንግሥት ካፈረሰ ዋነኛው ምክንያት ማህበረሰቡ በስነምግባሩ መረን መውጣቱ፣ ስለ ብዙኃኑ ደኅንነት ፍትወቱን መግታት አለመማሩና አለመቻሉ፣ ያም እያደር ልኩ መደረጉ ነው። ባጭሩ፣ የሞራል ድንበሩን ለይቶ ባለማወቁና አውቆ ግዴታውን ባለመወጣቱ ስብእናው ያልተዋረደ፣ ያልፈረሰ ግለሰብና ማህበረሰብ የለም።
ማህበረሰብ እንዳይፈርስ ከሚያያይዙት ኃይላት መሓል ማህበራዊ ኃፍረት አንደኛው ነው። ከምሥራቅ ምዕራብ፣ ከጥንት እስከዛሬ በዘመናዊነት ይሁን በልማድ፣ ኃፍረት ያልገዛው፣ ማህበራዊ ኃፍረት ያላያያዘው ሕዝብ የለም። እርግጥ፣ አኳኋኑና መጠኑ ይለያያል። ከዕውቀት ማነስ የሚመጣ አጉል ልማድ እንዳለ አንክድም። ቤተሰባዊነትን የሚያጸኑ፣ ሰውን በሰውነቱ የሚያከብሩ ስነምግባሮች ሁሉ ግን ሊከበሩና በጥንቃቄ ሊያዙ ያስፈልጋል። ከዚህ በመነሳት ሌላ ጥያቄ እንጠይቅ፦ ወጣቱ ቤተሰብን አፍራሽ በሆኑ ድርጊቶች በተሠማራባት አገር የደራሲ ማህበራዊ ግዴታ እስከምን ድረስ ነው? ወይንስ ደራሲ፣ የፖለቲካና የኃይማኖት ሥልጣናት ያፈቀዳቸውን ማድረግ ይችላሉ? የሰባ አምስት ዓመት አዛውንት ከአስራ አራት ዓመት ልጃገረድ ጋር ቢዳራ ምንም አይደለም? የግል ምርጫ ስለሆነ ማንም አያገባውም? ናትዚዎችና ፋሺስቶችን ማወደስስ? በግልጽነትና በአሳብ ነጻነት አሳብቦ የጓዳውን አደባባይ ማውጣትስ? ለማህበረሰቡ ተጠሪነት ሳይኖርበት፣ እያንዳንዱ እንዳሻው ይሁን?
ቤተክርስቲያንና አማንያንን የሚወርፉ ግጥሞች ደግሞ አሉ [ቁ.59፣ 66፣ 75፣ 78]። አንዳንዱ ውረፋ ተገቢ ነው። አንዳንዱ እግዚአብሔርን ክጃለሁ ማለቱን ተከትሎ የመጣ ነው። ያም ሆኖ ከውስጥ ሆኖ ለውጥ ለማምጣት ከመሞከር፣ ቀላሉን ከውጭ ሆኖ መውቀስን የመረጠ ይመስላል። በዕውቀቱ ግን እውነት ከሓዲ ነው ወይስ እውነትን ጠያቂና ፈላጊ? አገር ወዳድ ወይስ እንደ ብዙዎቻችን ገና ፈር ያልለየ የዳበሳ ጉዞ ላይ የሚገኝ? ቀጥሎ [በአፅንዖት] የተመለከቱትን ስናጤን ግን፣ እንዳሰበውና እንዳሳሰበን ከክርስቲያናዊ ስነምግባር የራቀ አእምሮና ስብዕና እንደሌለው እንገነዘባለን። ሆድ ያባውን ቅኔ ያወጣዋላ!
[ሀ] ቁ.23፣ “ላባቴ”፦ የማትንበረከክ፣ የማትርመጠመጥ / ከባለጌ ዙፋን፣ በርጩማ የምትመርጥ / አወረስከኝ ትግል / የትም እንዳይጥለኝ ሕይወት እንደ ፈንግል፤
[ለ] ቁ.44፣ “ለእህቴ ለክብርት ሥዩም”፦ ሞትና ክስመት ነው የተፈጥሮ ግቡ ብዬ እንዳልጽናና / በሞቷ ፊት ለፊት ሀሳብ ሁሉ መና ምክር ሁሉ ኦና / እንባን አይገድብም የሰው ፍልስፍና
[ሐ] ቁ.66፣ “ወይ ገራምነቴ”፦ የክንፍ ድምጽ ይሰማል ተርገብጋቢ ነገር / የመላክ አይደለም ከመአት የሚያድን / ያሞራ ነው እንጂ የሚበላ በድን
[መ] ቁ.64፣ “እንደምነሽ ሸገር” [ሕይወት/ዓለም]፣ሥጋ ምታወፍር፣ ነፍስ ምታከሳ / ዘናጭ አልጋ ሰጥታ እንቅልፍ በምትነሳ [መስመር 51-53]
[ሠ] ቁ.72፣ “እንባዬን የት ላርገው”፦ እንባየን ዘግኜ ሽቅብ እየረጨሁ / ወደ አማልክት ብጮህ ጸሎቴን አይሰሙት / በየት በኩል ኖሬ በየት በኩል ልሙት [በጭንቅ ሰዓት ጸሎት፤ ከሚታየው በላይ አምላክ፤ ጸሎት የማይሰሙ አማልክት አሉ]
[ረ] ቁ.59፣ “ስብከት ደና ሰንብት፣ ወግድ አትሮኖሱ / ጭላንጭል የለውም፣ ቀፎ ነው ፋኖሱ …” [ቤተክርስቲያን ለጨለመ ዓለም/ሕይወት እውነት/ብርሃን የምትፈነጥቅ ነች፣ ዓላማዋን ዘንግታለች]፤ ይኸ ብቻውን ጳጳሱን ከመንበር የሚያስነሳ ግሣጼ ነው!
አንዳንዱ ውረፋ ተገቢ ነው ብለናል፤ “አባይን አዋሽን የሚያስንቅ ደም ሲፈስ … ልክ እንደ ጧፍ ሐውልት ምስኪኖች ሲጋዩ፣ ምድጃው ዳር ሆነው ይሄንን እያዩ፤ ገሃነም ከላይ ነው ብለው መሳትዎ፣ እስዎ እንደፈቱኝ እግዚሃር ይፍታዎ” [ቁ.75]። ከጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን ብዙ ጠብቆ ብዙ ያጣ ሰው ቁጣና ቅሬታ ይመስላል። ሌሎች አባባሎቹ ግን በጭፍኑ፣ ደስ ስለሚያሰኙ የተሰነዘሩ እንጂ ጥልቀት የላቸውም፦ ሀ/ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት” ነው የሚለውን “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ጠብን መፍራት ነው” ብሎታል [ቁ.53]። ጠብን መፍራት ጠብን ያስቀራል? ጠብ መፍራት ምን በጎ ለውጥ ያስከትላል? ጠብ የሚፈሩ ለምን ኃይል ይጠቀማሉ? ለ/ ኢትዮጵያ [እጆቿን ሳይሆን] ቀይ ምንጣፏን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤ ሰማዩን ሙጥኝ ስትል መሬቷን ትዘነጋለች” [ቁ.84]። በአገራችን ታሪክ ይህን ጥቅስ [መዝሙረ ዳዊት 68:31] የሚጠቅሱ ቤተ እምነትና ቤተመንግሥት እንደሆኑ አንርሳ። ወቅቱን ስንታዘብ ደግሞ፣ ቤተ እምነትና ቤተመንግሥት ሁለቱም ተደጋግፈው፣ የሰማዩን ችላ ብለውት እንመለከታለን። ለነፍስ ማደር ተመናምኗል። ለእምነት መሰደድ፣ ገንዘብ በማሳደድ፣ ለዶላር በመሰደድ፣ ዶላር ወደ ውጭ በመስደድ ተተክቷል። የቤተክርስቲያንና የአገር መሪዎች በጎሠኛነት፣ በፋሽን፣ በመካሰስ፣ በሥልጣን ሽኩቻና ሃይ የሚል የሚደመጥ የሚከበር እስኪጠፋ ድረስ በሙስና ተዘፍቀናል እያሉን ነው።
ኢትዮጵያ ምድር እየኖሩ ከሓዲ መሆን ከተዓምር የሚመደብ ነው። ለመሆኑ፣ [ወንጌል] አማኝ የኪነ ጥበብ ሰው መሆን አይችልም? ወይም የኪነጥበብ ሰው ከሓዲ መሆን አለበት? የሚገርመው፣ አማንያኑም ከሓዲውም በአብዛኛው ለዚህ ጥያቄ ምላሻቸው አሉታዊ መሆኑ ነው! የኪነ ጥበብ ሰው [በኢትዮጵያ ምድር ብቻ ነው] እምነቱን “በልቡ መደበቅ” ያለበት? [ቡዲስት፣ እስላም፣ አብዮተኛ፣ ኑኤጅ፣ ቃልቻና ዕብድ ብቻ እንደ ልቡ ይሁን?]
ይህ ትውልድ የዘመነ ቴክኖሎጂ ትውልድ እንደመሆኑ፣ ቋንቋችንን ከጊዜው ግኝት ጋር የማስማማትና ግኝቱ ያስከተለውን ተጽዕኖ አጸፋ የመመለስ ትልቅ አገራዊ ግዴታ ይጠብቀዋል። ብዙዎችን በማሳተፍ በዕውቀቱ [እና ኄኖክ ስጦታው፣ አንድምታ፣ አዲስ አድማስ እና ሌሎችም ትልቅ ሥራ እየሠሩ ነው]። ይኸ ብቻውን ዘመን ተሸጋጋሪ ራእይ ነው፤ ዛሬ ተስፋ የለሽ የሚመስለው ነገ ተስፋና ድል በውስጡ ቋጥሯል። በሰው ታሪክ ውስጥ ድል ለባለ ብዕር እንጂ ለባለ ብር ለባለ ጦር ሆኖ አያውቅም። ሁንጋሪያ፣ ቼኮዝሎቫክያ፣ እስራኤል፣ ኮሎምብያ፣ የስድሳዎቹና የሰባዎቹ አሜሪካና ኢትዮጵያ፣ አርጀንቲና፣ ሜክሲኮ፣ ወዘተ፣ የቅርብ ዘመን ምስክሮች ናቸው። ሌላ ተስፋ የሚሆነን፣ “ረብሻ፣ ዝግመተ ለውጥና ድንብር አመራር” በተንሠራፋበት፣ በአገራችን አብቦ ያፈራው የቅኔ አዝመራ ነው። አበባው መላኩ፣ አረጋሽ ሰይፉ፣ አበባየሁ ደበበ መኮንን፤ ፊርማዬ አለሙ፣ ኤፍሬም ስዩም፣ ምሥራቅ ተረፈ፣ በድሉ ዋቅጅራ፣ ኄኖክ ስጦታው፣ ሜሮን ጌትነት፣ ወዘተ። እነዚህ ባለቅኔዎች የዘመኑ መንፈስ መበጣጠቅና መቃቃር የወለዳቸው ናቸው።
[ቃል ልዋስና] በዕውቀቱ “አሪፍ” ገጣሚ ነው። አዝናኝም ነው፤ በዚህ ስንጠብቀው ባቋራጭ ደርሶብን ያስገርመናል፣ “የሞባይል ፈጣሪ የቴሌፎን ጌታ፣ በኖርክበት ዘመን ባለህበት ቦታ፣ አቡነ አረጋዊ ይጣሉህ በቴስታ…” [ቁ.57]። እያዝናና ግን ምን ራእይ አጋራን? ልንገልጸው ወድደን ያቃተንን ምን አንደበት አቀዳጀን? የትኛውን አብሮነታችንን እንዳይረሳ አድርጎ አነጸልን፣ አጸናልን? ራእዩንና ሥራውን በመሞገታችን ስለ ስብእናችን ምን ግንዛቤ አተረፍን? ወይስ መጠየቁን ትተን ዝም ብለን እንደሰት? ደግሞ፣ ስለ አገሩና ስለ ሕዝቦቿ ታሪክ ለማወቅ ያሳየው ጥረት የሚደነቅ ነው። ይኸ ቢጋባብን ከምንሟገትባቸው ጉዳዮች ገሚሱ በተቃለለልን ነበር፤ የሌለ ታሪክ እየፈጠርንና ያለውን እያጣመምን ጊዜና ጉልበት ባላጠፋን! እግዚአብሔርን መፍራት፣ ራሳችንን ማክበርና መከባበር ባወቅንበት! ድባብ በማለዳ፣ ድባብ በቀትር፣ ድባብ በምሽት ይዘን አብረን በተሰለፍን!
ምትኩ አዲሱ
መስከረም 2010 ዓ.ም.
ቀላሉን መንገድ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave