ትዝብቶች ከ"አባቴ ያቺን ሰዓት"
ውብ ብዕር። ጭከናና ርኅራኄ። ሞትና ሕይወት። የማኅበራዊ ስነምግባር መዛባት። ለውጥ የሌለው ለውጥ።

abateeYachinsaatሜጀር ጄነራል ደምሴ ቡልቶ በ1981ዱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተገደሉት መሪዎች አንዱ ናቸው። "አባቴ ያቺን ሰዓት"፣ ጄነራል ደምሴ በሰሜንና በምሥራቅ ኢትዮጵያ ባሳለፉት የውትድርና ዘመንና በግንቦት 81 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የነበራቸውን ሚና የሚተርክ ታሪካዊ/ወታደራዊ ሰነድ ነው። ጠበቃ ልጃቸው ደረጀ ደምሴ "አባቴ ያቺን ሰዓት" ብሎ ከሃያ ዓመት በኋላ [በ2001] የወቅቱን ሁኔታ ተርኮልናል። ርእሱ የጸጋዬ ገብረመድህንን "ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት" እያስታወሰ፤ ግፍን መቃወምና መስዋእት መክፈል አብረው እንደሚጓዙ ያስገነዝበናል። መስዋእቱ ለቋሚው ነው። ቋሚው ግን ታሪኩን አድበስብሶ ወይም ለጊዜው እንዲመች ጨምሮበትና ቀንሶለት ማስታወስ የመረጠ ይመስላል። ደራሲው በርእሱ አመራረጥ የፋሺስት ኢጣሊያን ግፍ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ማያያዙ ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ያለፈውን አፍርሶና ረስቶ አዲስ ሥርዓት ለመፍጠር ለሚቻኮል ባህል እርምት ይሰጥ ይሆን?

"አባቴ ያቺን ሰዓት"ን ልዩ የሚያደርገው፣ አባትና ልጅ ከወዲህ፣ አባትና ልጅ ከወዲያ በመሪዎቻቸውና በባእዳን ቆስቋሽነት በሚፋለሙበት ዘመን መታቀፉ ነው። ጦርነትና አብዮት የብዙዎችን ግንኙነቶች ባሻከረበትና ባቆራረጠበት፣ ልጅ አባቱን ለማጋለጥ በማይመለስበት ወቅት ደራሲው ከአባቱ ጋር ያሳለፋቸው ውድ ግን አጭር ዓመታት ብዙዎች እድሜ ልክ ተመኝተው የማያገኙት ነው። አባቱ ለዓላማቸው እስከሞት ድረስ መጽናታቸው ኀዘን ቢያደርስም ውጤቱ ምንጊዜም ክብር ነው። ሁለት ምንባብ ከመጽሐፉ ቆንጽለን በሦስት ትዝብቶች እንደመድማለን።።

ውብ ብዕር - የአባትና ልጅ ፍቅር [ገጽ 6-10፣ 16]

"በእጄ የማሻትን ብርትኳን ውስጧ ሟሙቶ እንደተነፈሰ የላስቲክ ኳስ ቆዳዋን ሲነኩት ወደ ውስጥ ይጎረብጣል። አንዳንዴም ወደ ላይ ወርወር አደርጋትና እቀልባታለሁ። በአንድ እጄ ነበር የማሻት። ከአባቴ ጋር ከቦሌ አዲስ ባንክ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ አቅጣጫ በዝግታ እየተራመድን ነው። ከእህቴ ቤት ነበር የምንመለሰው። አባቴ በእግር መሄድ ደስ ይለዋል። በተለይ እሁድ ማምሻው አካባቢ፣ ቀጥ ብሎ አንገቱን ቀና አድርጎ ነው የሚራመደው።

"በጦርነት ላይ እንዴት ነው መድፍ የሚመታበትን ቦታ አስተካክሎ የሚመታው?" በማለት ጠየቅኩት።
"አስተኳሽ አለ፤ እሱ የርቀቱን መጠን ለክቶ በሚሠጠው ምልክት መሠረት ነው የሚተኮሰው" አለኝ፣ ለኔ ሊገባኝ በሚችል መልክ ለማስረዳት እየሞከረ።
"ርቀት ሳይለካ እንዴት ማወቅ ይችላል?" አልኩት።
"መንገድ አለው፣ ትምህርት ይሰጠዋል። አንዳንዴ ጊዜም ግምት መጠቀም የሚገደድበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል" ብሎ መለሰ።
"ርቀት መገመት አስቸጋሪ ነው። በተለይ በጦርነት መሃል" አልኩና "አሁን አንተ ከዚህ መብራት እስከዚያ ፎቅ ድረስ ያለውን ርቀት መገመት ትችላለህ?" ብዬ ጠየቅሁት ፊታችን ያለውን የመንገድ መብራትና እልፍ ብሎ የሚታየውን ባለ ሰማያዊ ቀለም ፎቅ እያመለከትኩ።
"በሚገባ!"
"ስንት ሜትር ይሆናል?"
"መቶ ሃምሳ"
"አይሆንም፣ መቶም ከሞላ ይገርመኛል።"
"ትወራረዳለህ?" አለኝ፣ ከመንገዱ መብራት ጎን ስንደርስ ቆም ብሎ በፈገግታ እየተመለከተኝ።
"እሺ እንወራረድ!" አልኩ እኔም በእርምጃ እንደምንለካ ስለገመትኩ ከምንጀምርበት ቦታ ቆም ብዬ።
"በምን ትወራረዳለህ?" አለኝ ሳቅ እያለ፣
"እ እ እ... በኩርኩም" አልኩ እየሳቅኩ።
"በፈለግኩት ሰዓት ጠርቼ ልኮረኩምህ ስችል ለምን በኩርኩም እወራረዳለሁ?"
"እሺ፣ በምን?"
እንግዳው ከተሸነፍክ የያዝካትን ብርትኳን እበላብሃለሁ፣ ካሸነፍክ ትኮረኩመኛለህ"
"እሺ!"
አባቴ እያንዳንዱ እርምጃ ወደ አንድ ሜትር እንዲደርስ ረዘም እያደረገ "ቁጠር!" ብሎ ከቆምንበት ቦታ ርምጃውን እየሳቀ ጀመረ ...
ቤታችን ለመድረስ ትንሽ ቀርቶናል። አባቴ ለብዙ ሰዓት ያሟሟሁዋትን ብርትኳን ከአንድ በኩል ቆዳውን ልጦ እየመጠጠ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በማብሸቅ መልክ ፈገግ ብሎ እየተመለከተኝ፣ መንገዱን ተሻግረን ወደ ቤታችን ገባን። ከአባቴ ጋር የማሳልፈው ጊዜ፣ የሳቅ፣ የደስታና፣ የትምህርት ነበር።

... ጊዜው ጦርነት እንደ ደራሽ ውሃ የሰሜኑን ግዛት አጥለቅልቆ፣ ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ግዛቶች ለመዛመት ማእበሉን ወድሮ የሚገሰግስበት ወቅት ነበር። የበጋ ወራቶች በደመና ጠለው ከተለዩን ትንሽ ጊዜ አልፏል። አዲስ አበባም ክረምት ክረምት መሽተት ጀምራለች። የበቆሎ እሸትና የትኩስ ቆሎ ንግድ ደርቷል። ሊስትሮዎችም የክረምት ጭቃ ያበላሸውን ጫማ ለመጥረግ ሣጥናቸውን እያንቋቁ የሰውን እግር በዓይናቸው ይከታተላሉ። ክረምቱ ለከተማዪቱ ዝናብ ብቻ ሳይሆን ልዩ ቀለምና ሽታን ጨምሮ ነው የመጣው። በየጥጉ የሚጠበሰው የበቆሎ እሸት አፍንጫን ሰንፍጦ ኪስ ያስዳብሳል። ለወትሮ በአቧራ የተሸፈኑ መንገዶች በዝናብ ታጥበው ያብረቀርቃሉ። የአላፊ አግዳሚው ፊት በክረምት ጨገግታ ገና አልተሞላም። የክረምት መጀመሪያ ፍካትንና ጥድፊያን ይዞ ነው ብቅ ያለው። ጥድፊያው ደግሞ የድካም ሳይሆን ደስ የሚያሰኝ የሥራ ጥድፊያ ይመስላል።

ዳሩ አዲስ አበባ ቆይቼ ክረምቱን ለማጣጣም አልነበረም ዓላማዬ። ወደ አስመራ ሄጄ አባቴን ለማየት ካሰብኩ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል። 12ኛ ክፍልን ጨርሼ ጊዜያዊ ሥራ ከጀመርኩ ብዙ ወራት አልሆኑም። በምን ምክንያት ልሄድ እንድምችል ሳሰላስል አንድ ነገር ተፈጠረ።

... ድሮ አባቴ ከበረሃ ሲመጣ የምናደርገው አሁንም ትዝ ይለኛል። ብዙ ጊዜ አባቴ ዛሬ ይመጣል እየተባለ ይነገረን ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አንድ ወይ ሁለት ቀን ዘግይቶ ስለሚመጣ ከት/ቤት ስንመለስ መጥቶ መሆኑን ለማወቅ ወደ ትልቁ መኝታ ቤት ሮጠን እንሄዳለን። በተለይ ከታናሽ እህቴ ከሄዋን ጋር ይዞት የመጣውን የተሰቀለ ልብሱን እያሸተትን "አባዬን አባዬን ይሸታል" እያልን መምጣቱን አረጋግጠን ከቢሮ እስኪመለስ በጉጉት እንጠብቀው ነበር።

ጭከናና ርኅራኄ ከአንድ ምንጭ? [ገጽ 37-38]

አባቴ ወጉን ቀጠለ። "ታዲያ ያቺ ሻምበል ከአራት ወታደሮች ጋር ጠፍተን ስንሄድ ማነው ስሙ? ስሙ ጠፋኝ - አዎ ሀብተሠላም ነው ያለኝ መሰለኝ - መንገድ ላይ ደከመንና አንድ ቦታ አረፍን አለ። ወታደሮቹ ጋደም እንዳሉ እንቅልፍ ወሰዳቸው፤ ቀን ሌሊት ስለተጓዙ ደክሟቸው ነበር። ሻምበሉ ግን አንድ ከፍታ ላይ ያለ ዛፍ ላይ ወጥቶ ተቀምጧል። ወዲያው ሳያስበው ጥቂት ወንበዴዎች እቦታው ደረሱ። ለመንቀሳቀስ አልቻሉም። ወንበዴዎቹ 'ወታደር! ወታደር!' ቢሉ ወታደሮቹ ሊነሱ ነው? ዝም። እንቅልፍ ይዟቸዋል ሄዷል። ደክመዋል። ትንሽ ተነጋገሩና አንደኛው ወንበዴ በመትረየስ ጨረሳቸው። ሻምበሉም ዝም ብዬ ቆይቼ ሲሄዱልኝ ጉዞዬን ቀጠልኩ አለ። መች በዚህ ይቆምና፤ መንገድ ላይ ሲሄድ ደግሞ አንድ ቤት ያገኝና ይገባል። ውሃ አግኝቶ ጠጣና በር ስር ትንሽ ደገፍ እንዳለ እሱም እንቅልፍ ይዞት ይሄዳል። ትንሽ ቆይቼ ከበደኝና ነቃሁ አለ። ሲነቃ አንድ ሽማግሌ ፊት ለፊቱ ቆመው በእጃቸው 'አይቼሃለሁ ተኛ' የማለት ዓይነት ምልክት ሰጡት። ትንሽም አልቆየ የመኪኖች ድምጽ ተሰማ፤ ሰውየው ወዲያው ወደ ውጭ ወጥተው ቤቱን ዘጉት። ወንበዴዎቹ ቆም ብለው 'ወታደሮች ወደዚህ አልፈዋል' ብለው ይጠይቋቸዋል። ሽማግሌውም 'አዎ ትንሽ ቆይተዋል እንጂ አልፈዋል' ብለው ይመልሳሉ። 'ውሃ አለ?' ይላል አንዱ ወንበዴ።
'ወታደሮቹ ጠጥተው ሄዱ። አሁን ምንም የለም። እኔም ባለቤቴ ቤቴን ዘግታ ሄዳ እየጠበቅኳት ነው'
'እሺ እንመለሳለን' ብለው ሄዱ ወንበዴዎቹ። ሻምበሉ ከዚያ የነበረኝን ሠላሳ ብር ለሽማግሌው አመስግኜ ሰጥቼ ወደ አክሱም ቀጠልኩ አለ።

ትዝብት 1፦ በሞትና ሕይወት ተከብበናል

በዓለም እስካለን ድረስ ጦርነት የማያቋርጥ ታሪካችን ነው። ሰው ራሱ ተንቀሳቃሽ ደማሚት ነው። እርግጥ ሰላምን እንመኛለን፤ ሰላም ሲርቀን በሶሻሊዝም፣ በዴሞክራሲና በሌሎች ሰው-ሠራሽ ርዕዮተ-ዓለማት ተተግነን ራሳችንን እናባብላለን፤ አንዳንዴም ራሳችንን እናታልላለን። የስድሳ ስድስቱ አብዮት በ "እኩልነት" "ያለምንም ደም" ብሎ ጀመረ፤ አድኃሪና ተራማጅ አሰኝቶ በደም ተጠመቀ። የሰማንያ ሦስቱ ለውጥ በ "ነፃነት" ጀመረ፤ እንደቀደመው፤ ሳይቆይ በሰሜንና በምሥራቅ ግንባሮች መቶ ሺህ ያህል ሕይወት ገበረ። ጦርነት አውዳሚ ነው፤ ድሉ ኀዘን የተላበሰ፤ ጥፋቱ ለሁሉም ነው። የሚገርመው፣ የጦርነት ጠባሳው እንዳይሽር ሲላላስ እንጂ ሲረሳ አይታይም። ይሆናል ያልነው እንደጠበቅነው አልሆነም።

ሌላኛው። የዕልቂት እሳት እየነደደ ሰው ለመኖር የሚያሳየው ጉጉትና ጥረት ነው። ይበላል፣ ይጋባል፣ ይወልዳል፣ ይስቃል። በነዚህ ድርጊቶቹ ሰብዓዊነቱን ያጸናል። በመንግሥት ተቃዋሚዎችም ሠፈር ከዚህ የተለየ ሆኖ አያውቅም። ሕይወት በሞት ተከብባለች፤ የሰው አንድ እግሩ ሁሌም መቃብር አፋፍ ላይ ተተክሏል። ከደጅ ፈንጂ ተቀብሯል ፣ ከጄነራል ቤት ደግሞ የዶሮ ብልትና እንቁላል "አንዳች በሚያህል አገልግል" ውስጥ ተቀብሯል [ገጽ 10]። በግለሰቦች ይሁን በሕዝብ መሃል፣ አለመደማመጥና አለመግባባት እንዳለ ሁሉ መነጋገርና መፋቀርም አለ። ይህን መጽሐፍ በዚህ ዐይን ማንበብ፤ ጭው ባለ ምድረበዳ ልምላሜ እንደከበበው የውኃ ምንጭ ያልታሰበ ሌላ ትርጉም ይሰጣል። ጦርነት ከቤት ይጀምራል። እርቅ መፈለግም። እግዚአብሔር ካልገባበት ግን ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሉት ነው። የስድሳ ስድስቱ አብዮት በቅድሚያ "የእግዚአብሔርን ነገር" ከአደባባይና ከአውራ መንገድ ላይ ጠርጎ ለማስወገድ የሞከረው የሻውን ለማድረግ እንዲያመች ነው። በሰማንያ ሦስት፣ ለሃይማኖት ድርጅቶች የወጣውን መመሪያ እስካልጣሰ ማንም በ"ነጻነት" ማምለክ ይችላል የተባለውም ለዚህ ነው።

ችግሩ ያለው የሰው ልብ ላይ ነው። የመሪዎች ልብ ላይ ነው፤ የተመሪ ልብ ላይ ነው። መፍትሔው በቅድሚያ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ ቀጥሎ በንስሃ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ ነው፣ "የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል? እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ። ትንቢተ ኤርምያስ 17፡9-10" "በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ፤ ያዕቆብ 4፡1-2"
ሰላምን ለማውረድ እግዚአብሔር የሚጠቀምባቸው ሰዎች አሉ። እግዚአብሔርን መፍራት ከሌለ ግን ሁሉ ድካም ነው። ብልጠት ስፍራውን ይይዛል፤ ቅንነት ጠፍቶ ሰላም አይገኝም። የእግዚአብሔር ፍርኃት ደግሞ በአምሳሉ ለፈጠረው ሰው አክብሮት ከማሳየት ጋር ይያያዛል።

ትዝብት 2፦ ማኅበራዊ ስነምግባር ሲዛባ [ገጽ 376-409]

በዚህ ክፍል በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የተገደሉ የ19 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ዜና እረፍት ተዘርዝሯል። የአገር መሪዎች ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚወስዷቸው እርምጃዎች ለትውልድ አሳር እንደሚያተርፍ እንደ መረጃ ሊታይ ይችላል። አብዛኛዎቹ መኮንኖች በአርባና በአምሳ ዓመት እድሜ ክልል መገኘታቸው ያካበቱት ልምድ ከንቱ መቅረቱንና ይልቁንም በቤተሰብና በማኅበረሰብ ላይ ያስከተለውን ጉዳት መገመት አያዳግትም። ሌላኛው፣ በአገር ላይ የደረሰው የሞራል ሚዛን መውረድ ጉዳይ ነው። የተገደሉት የጦር መሪዎች በወታደራዊ ሳይንስና በዘመናዊ ትምህርት ከፍተኛ ሥልጠና የተቀበሉና በግዳጅ ላይ የከረሙ ቢሆኑም፣ ከፖለቲካ ካድሬ ሥር ወይም ተጠሪነታቸው ዝቅተኛ ማእረግ ላላቸው መደረጉ የሥልጣንና የብቃት መለኪያ መፋለስን አስከትሏል። አንዳንዶችም ሥልጠናና ልምድ ሳይኖራቸው፣ ለገዢው ፓርቲ ታማኝ ስለሆኑ ብቻ ባጭር ጊዜ ከተራ ወታደርነት ጄነራልነት ማእረግ ተሰጥቷቸዋል [ገጽ 94፣ 204-5]። አመራራቸውም ለብዙዎች ሕይወት መጥፋትና ለጦርነት መባባስ ምክንያት ሆኗል። በጠብመንጃ አፈሙዝ እንጂ በምክክር ውጤት አይገኝም ብለዋልና።

ትዝብት 3፦ ለውጥ የሌለው ለውጥ አያዘልቅ

ያኔ "ወንበዴ" የተባሉ ዛሬ የአገር መሪዎች ናቸው። ያኔ "ወንበዴ" ይሉ የነበሩ "ፋሺስት" ተብለዋል። ሰውን በኃይል መግዛት ተቃውሞን ያስነሳል፤ ተቃውሞም ሲሰነብት ገዢውን ያዳክምና ያስወግዳል። ሁለቱም ወገን በወቅቱ የወሰዷቸውን እርምጃዎች የረጅም ጊዜ ውጤት በአጽንዖት ያሰቡበት አይመስልም። የነገሮች ያልታሰበ አቅጣጫ መያዝ የመንግሥታትና የሕዝቦች/የሰው ሁሉ ታሪክ ሂደቱ ነው። ይህ ሂደት አይደገምም ብሎ ማሰብ ከታሪክ አለመማር ነው። መሪዎች የጋራ ቅርስ እንዳያባክኑ/ቢያባክኑ እንዴት በጊዜ ማስቆም/መጠየቅ ይቻላል? "አባቴ ያቺን ሰዓት" ያለፈውን አፍርሶና ዘንግቶ አዲስ ሥርዓት ለመፍጠር ለሚቻኮል ባህል ምን እርምት ይሰጥ ይሆን?

[ምንጭ፦ አባቴ ያቺን ሰዓት - ሜጀር ጄነራል ደምሴ ቡልቶና የግንቦት 81 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፤ በደረጀ ደምሴ ቡልቶ። እ.አ.አ በ 2009 በአሜሪካ ታተመ፤ 431 ገጾች። 25 ዶላር Aesop Publishers, Tel: 202-386-3037]

ምትኩ አዲሱ
ጥቅምት 2006 ዓ.ም.

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave