ይድረስ ለቴዲ አፍሮ
ሰላም ላንተ ይሁን፣
ራቅህ እንጂ እንደ አገሬ ወግ አገላብጬ እስምህ ነበር። ምን ይደረግ፣ ድንበርና ዘመን አራራቀን።
ካገር ስወጣ ባልሳሳት ገና የአስርና የአስራ አንድ ዓመት ልጅ ነበርክ። ዛሬማ ፊትህ እንደ ካፊያ ፀሐይ ደምቆ አምሮብህ ፎቶህን ሲያሳዩኝ ማመን ነው ያቃተኝ።
ግራ ተከሻዬ፦ “ይመስለዋል እንጂ እሱ አይደለም” ቢለኝ፣ ቀኝ ተከሻዬ ተቀብሎ፦ “እርሱ እራሱ ነው፣ አታየውም?” አለኝ። ግራ ቀኝ፣ ግራ ቀኝ ስል ያቺ የምትወዳትን እስክስታ ልወርድ ምንም አልቀረኝም እልሃለሁ፤
ቴዲ መባልክን የሰማሁት ገና ዛሬ ነው። አፄው ቴዎድሮስ በፈረንጅኛ አፄ ቴዲ ይባል እንዳትለኝና የእንግሊዝ ሳቄን እንዳልለቀው ብቻ? አፍሮውን እንኳ የዛሬን አያድርግና እኛም ስንባባል ነው የኖርነው። ያንተዋ ግን ጨዋ ቁርጥ የምንላት ነች። ለአፍሮ ገና ይቀራታል ማለቴ ነው።
አያ ካሣሁንን … አፍሮነቱ ተስማማህ ወይ? በልልኝ። እንዳትረሣ።
ይገርማል፣ የጊዜው መገሥገሥ። የአብዮት መዝሙር እንዳልዘመርክ ሁላ ዛሬ ደግሞ “ጃንሆይ፣ ጃንሆይ” ማለትህ። የምትጠራቸው “ግርማዊነታቸው” በዙፋናቸው ላይ ሳሉ እንኳን ልትወለድ ቀርቶ አልታሰብክም ነበር።
የገረመኝ፣ የአብዮቱን ፍሬ ልጅ ሳይቀር አንቅሮ የተፋው ምንኛ መራራ ቢሆን ነው?
እንግዲህ ወሬ አላበዛብህም። አውቃለሁ አውሮፕላን እየተሳፈርክ ስለሆነ ቸኩለሃል። ከአውሮፕላን ወርደህ ያቺ መኪናህ ውስጥ ገብተህ በርረህ ሳታመልጠኝ አየር ላይ ልቅለብህ ብዬ ነው።
ቴዲ። ኧረ ይኸ የምሰማብህ ነገር ምንድነው?
“ጃህ” ትላለህ አሉ። እንጃ ማለትህ ነው? ጐረበቴን ብጠይቀው የምን እንጃ ነው? እርስዎ ደግሞ አበዙት። ጃህ ይበሉ፤ ሁለት ቃል ነው ብሎ ጣል ጣል አረገብኝ።
እሽ፣ ጃስ ይሁን፤ ፍቺው ምን ይሆን? ብለው፦ ጃማ ጃንሆይን ነው፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ነው፤ አይለኝ መሰለህ?
እንዴት ተደርጐ፣ በምን ሂሳብ ጃህ ጃንሆይን ይሆናል? ብለው፤ በጃማይካዎች እንደርሱ ነው፤ ጃማይካ ማለት እነዚህ ጃንሆይ አምጥተው ሻሸመኔ ያሠፈሯቸው ናቸው፣ ብሎ አብራራልኝ። እግዚአብሔር ይስጠው።
ታዲያ ጃንሆይ እኝህ የምናውቃቸው ጃንሆይ አይደሉም? እንዴት ያስተሠርያሉ ትላለህ? ከመቸ ወዲህ ነው አምላክ የሆኑት? ከሞቱ በኋላ ነው ወይስ በሕይወት እያሉ? ደግሞስ ጃማይካው ቢል ተቀበልከው? በሐሺሽ ፍላት ግርማዊነታቸውን አምላክ ነው ቢል ጭሱ ጋርዶበት ይሆናል ብለህ እንዴት አልጠረጠርክም? ሀበሻ መሆንህ ቀረና ነው? ያንተው ይባስ፤ የለም የለም አብዮቱ አልለቀቀህም ማለት ነው።
ቴዲ። ይህ ሳያንስ ሌላም ወሬ ሰማሁብህ።
ደግሞ ምን ይሆን? ትላለህ አውቃለሁ። የሠራኸውን አሁን አጣኸውና ነው? ክርስቲያንና እስላም ማለት ምን ያስፈልጋል፣ ቢጋባ ምንም አይደለም ትላለህ አሉ።
ፍቅርን ሃይማኖት አያግደው ማለትህ እንደ ሆነ ገብቶኛል። እርግጥ ሊጋባ ያሰበን ምን ይመልሰዋል ብለህ ነው? ልንበላት ያሰብናትን አሞራ ዥግራ እንላት የለ? የሃይማኖት ምሥጢርና ኃይል ለገባቸው ግን አንተ እንዳቀለልከው መቸ ሆነና?
ስታስበው ድንበር አይኑር ነው የምትለው? ሁሉ እንዳፈቀደ ይሁን ነው የምትለው? ይኸ አባባልማ ለነጮቹም አልበጃቸው። ይኸውልህ፣ ወንዱ ሴት፣ ሴቱም ወንድ ቢሆን መብትና ነጻነት እንጂ ኃጢአት አይደለም፣ የፈጣሪን ሥርዓት መዳፈርና ማፍረስ አይደለም እያሉን ነው።
ያለ ክርስቶስና ያለ ወንጌሉም ክርስቲያን መሆን ይቻላል እያሉ ነው። ስንቱን ዘርዝሬ እጨርሳለሁ።
አንዳንዶችም ክርስቲያን ነን፣ ከሃዲም ነን፤ ማለት ጀምረዋል። በአንድ ጊዜ ሁሉንም መሆን እንችላለን ነው ነገሩ።
ልክና ስሕተት ብሎ ነገር የለም፤ እያንዳንዱ በመሰለው የሚያደርገው ነው ልኩ እያሉን ነው።
ያውልህ፣ እምቢ ብለናቸው ነው እንጂ፦ ሰው ራሱ አምላክ ነው እያሉን ነው። ስታስበኝ እኔ አሁን ምኔ ነው አምላክ? አንተስ ምንህ ነው አምላክ? እንደ ሞኝ ያደርጋቸዋል ልበል?! ይኸውልህ፣ የሚሉት አንዱም አልጠቀማቸውም። እንደ መበልጸጋቸው እንዳይመስልህ። እውነት በብልጽግና ብዛት መች ተገኘና! የሕይወትን ውል ስተውታል፣ እልሃለሁ።
ቴዲ። አገር ወዳድነት እንዳለብህ አውቃለሁ። ክርስቲያኑና እስላሙ በጋብቻ ይጣመር ያልከው፦ መስጊድ ይቀድስ፣ ቤተ ክርስቲያን ሰላት ያድርግ እያልክ እንዳይሆን ብቻ። አይመስለኝም።
ከመ … ለያየቱ
ከመ … ነታረኩ
መድኃኒቱ
መ … ከባበሩ
መ … ተሳሰቡና
መፋቀሩ
ነው ማለትህ ይመስለኛል። በጐ አሳብ ነው። ግን የጀመርከው በጐ የሚመስል ሃሳብ መጨረሻው ወዴት እንደሚያመራ አስበህበታል? እንጃ የሰውን ባሕርይና የሃይማኖትን ታሪክ እንደሚገባ ያጤንኸው አልመሰለኝም።
ለመሆኑ፣ ሁሉ ይቀላቀል ድንበር ይደብዝዝ የምትለዋን ሃሳብ ከወዴት አገኘሃት? መቻቻሉን ስላጣንበት፣ ሁሉ አንድ ወጥ ይሁን ማለት ፍርደ ገምድልነት አይሆንም ወይ? ገደብና ሥርዓት እኰ እሥራት ሳይሆን ነጻነት ነው። ልዩ ልዩ መሆን ፀጋና ውበት አለው። የሕልውናም መጠበቂያ ነው። አንድ ወጥነት አያምርም፤ አንድነትንም አያስገኝም። ይልቅ እሥራት ነው። አብዮቱ ትዝ ይበልህ …
ኢትዮጵያ ምድር መወለዳችን ከፈረንጁና ከኬንያው ለይቶናል። መለያና ክብር አቀዳጅቶናል። ያም ኢትዮጵያዊነታችን ነው። የሁሉ ሰው ስም አበበና አበበች ቢሆን ምን ያምራል? ፈረንጁን ካልሆንኩ ብንል ፈረንጁንም ኢትዮጵያዊውንም ሳንሆን ዋልለን እንቀራታለን። በገደብና በየመልኩ ይሁን ማለት እሥራት አይደለም ያልኩህ ለዚህ ነው።
ቴዲ። የለም፣ የለም ይኸ የምሰማብህ ነገር አላማረኝም።
ይህንኑ ጉዳይ ለጐረቤቴ ባጫውተው፦ ገና ኖትና፣ ወዲህ ጠጋ ጠጋ ይበሉ እንጂ አይለኝ መሰለህ?
ወዴት ጠጋ ጠጋ ልበል? ብለው
ከዘመኑ ጋር ይሠለፉ እንጂ፣ ገና የስብስቴውን ነው የሚያወሩትሳ?
ዘመን አልፎ ቢያልፍብኝ፣ ቀኝና ግራዬን አጣሁት? ልለው አሰብኩና ሌላ እንዳልናገር ራሴን ያዝኩት እልሃለሁ።
ቴዲ አፍሮ። ቴዲ ልበልህ እንጂ ምን ምርጫ አለኝ። ይኸ የምሰማብህ ነገር አላማረኝም።
እረፍት ነስቶኛልና አደራህን ቶሎ ቁርጡን አስታውቀኝ። ስ-ሜ እንዳልሰናበትህ ድንበር ከለለን። ምን ይደረግ?
በዓይነ ሥጋ ለመገናኘት ያብቃን።
በል ስትነዳ ቀስ በል።
ያንተው
ኬኔዲ በራራስ
Copyright© 2006 እ አ አ