የልማት መሠረቱ መታመን ነው

ክፍል አንድ

መታመን እንደ አለመታመን በቃልና በድርጊት ይገለጻል። መታመንና አለመታመን ወዳጅነትና አገርን ያለማል ወይም ያናጋል። እምነት እንዲጣልበት ከፈለገ ሰው፦ በስውር የሚያየውን እግዚአብሔርን መፍራት። ሕግ የሚያስከትለውን ቅጣት መፍራት። ኃፍረትን ማወቅ። የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገን ማሰብ ይኖርበታል። ሕግ ግን ለሁሉም እኩል ካልሠራ፣ በሁሉም ላይ እኩል ተጽእኖ ካላሳደረ የማኅበረሰብን ደጅ ምስጥ አንክቶ ሊበረግደው ነው። እምነት ማጉደልና ቀምቶ ማደር ሲለመድ፣ እምነት ያጎደሉ አደባባይ መውጣት ሳያስፈራቸውና ሳያሳፍራቸው ሲቀር፤ እምነት ያጎደሉ መልሰው መካሪ ሲሆኑ። ያልታመኑ ተሹመው የታመኑ ሲከሥሩ። መታመን ብርቅና መሳለቂያ ሲሆን። የአምላክ ፍርዱ በደጅ ነው። ፍርኃትና ኃፍረትን ሲጥል ክቡር ሰው እንደ እንስሳ ይሆናል። ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል፤ ከፍተኛ ዕውቀት ሊገበይ ይችላል፤ ባለሥልጣን ሊሆን ይችላል። ፍርኃትና ኃፍረትን ስለጣለ ግን ሰብአዊነቱን ተቀምቷል፤ ክብር የለውም።

እሙን ሰው ቃል ይገባል፣ ቃሉን ይጠብቃል። ዋጋ ቢያስከፍልም ቃሉን ይጠብቃል። እምነት ያጎደለ ኃላፊነቱን አልተወጣምና አያስተማምንም፣ አይታመንም፤ እንዲያውም እምነተ ቢስ ይባላል። አማና። አማና በአደራ የተሰጠን መጠበቅ፣ የተጠየቀውን ግዳጅ መፈጸም ነው። እንዲህ ዓይነት ሰው አደራ የማይበላ ይባላል። የቀኙን በግራ አይለውጥም። ይህን በማድረጉ መታመንን ገንዘቡ ያደርጋታል።

መተማመን የአንድ ወገን ብቻ ኃላፊነት ሊሆን አይችልም። ለመተማመን ሁሉም ወገን የአንደኛቸው ድርጊት ሁላቸውን እንደሚጠቅም ወይም እንደሚጎዳ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፤ የመጀመሪያውን እርምጃ ለመውሰድ መፍቀድና መድፈር ይኖርባቸዋል። የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድ ሌላኛውን ወገን ለማደፋፈርና ለመተማመን መነሻ ይሆናል፤ የአንዱ እርምጃ ለሌላኛው ሥጋት አይፈጥርም፣ ያረጋጋዋል። እንዲህ ሲሆን ብቻ እውነተኛ ማኅበራዊና ፍትሃዊ ልማት ይከሰታል። የሰው ጤና፣ መንፈስና ኑሮ ከበዛ ኪሳራ ይድናል።

ማኅበረሰብ የሚጸናውና የሚበለጽገው የሚያያይዙትን ኃይላት ጠንቅቆ ሲያውቅና ሲያጠናክራቸው፤ የሚፈረካከሰው ደግሞ እነዚሁኑ ሲዘነጋቸው ነው። የሚያያይዙ ኃይላት በሁለት ይከፈላሉ። አንደኛው፣ በቤተሰብ ብቻ፣ በጎሣ ብቻ፣ በጾታ ብቻ፣ በሃይማኖት ብቻና በመሳሰሉት ሲያያዝ። ሁለተኛው፣ በቤተሰብ፣ በቋንቋ፣ በጎሣ፣ በጾታ፣ በሃይማኖት ሳይገደብ ድንበር ዘልሎ ግንኙነት ሲመሠርት ነው። ዙሪያችንን እንቃኝ። ስንት ድንበር ያላገደው ወዳጆች አፍርተናል? ዘመን ቢለዋወጥም ያልተለወጠ ስንት ወዳጅ አትርፈናል? ወዳጅነት ደግሞ እንዲሁ የሚገኝ አይደለም፤ ብዙ ጥረት፣ ፈቃደኛነትና መስዋዕት ይጠይቃል። ሁለቱም ኃይላት በአንድነት ሲገኙ ማኅበረሰብ ጤናማ ይሆናል። ቅርበት በመፍጠሩ ይተማመናል፤ በመተማመኑ ቅርበት ይፈጥራል። የወንጀል ቁጥር ይቀንሳል፤ ጦርነትና የጦርነት መንፈስ ይከስማል። አባካኝ ማኅበራዊ ወጪዎች ይቀንሳሉ። ዜጎችን ለመቆጣጠር የሚባክነው ጊዜና ንብረት፣ ወህኒ ለማሠራት የሚወጣው ወጪ ለትምህርት ቤቶች፣ ለጤና ጥበቃ ጉዳዮችና ለልማት ይውላል ማለት ነው።

መተማመንን በማጠናከር ረገድ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ዓይነተኛ ድርሻ አላት። የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በተናጠልና በጋራ ሊሠሩት የማይችሉትን ሥራ ለመሥራት ቁልፉን ይዛለች። በክርስቶስ ደም ተዋጅታ የተመሠረተች ማኅበር እንደ መሆኗ የሥነ ምግባር መሠረቱና መፍትሔ ከርሷ ዘንድ ይገኛል። የኃጢአትን ምንነትና ውጤት ታውቃለች። የሚያስተማምነውን ወንጌል ታውጃለች። ሰውና ማኅበረሰብ በኃጢአት ደዌ ተመትቷል ትላለች። እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ ፈጠረው ብላ ታስተምራለች፤ በርሷ ዘንድ "አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም" ሁሉም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ነው [ዘፍ1፡27፣2፡7፤ገላትያ 3፡28]። ሰውን ካምላኩ ከራሱና ከእርስበርሱ የለየው የኃጢአት ግድግዳ በክርስቶስ ደም ፈርሷል፤ ተስፋና ምህረት ታውጇል ትላለች።

መተማመን ሳይኖር ማኅበራዊነትና ወዳጅነት ሊዳብር አይችልም። ሰውን ማመን ግራ ቀኙን ሳይለዩ መነዳት ማለት ግን አይደለም፤ ለመጠርጠር ከመፍጠን ይልቅ ለማመን የሚፈቅድ ልቡና ሲኖር ማለት እንጂ። ማመን ማመንን ይጠራል፤ ጠርጣራ ሰው ደግሞ ራሱ ይጠረጠራል። ጥርጣሬ በበዛበት ፍርኃት ይነግሳል። ቸኩሎ ከመጠርጠር ማጣራት ሊቀድም ይገባል። ፍርኃትን ለማስወገድ፣ ሳይታክቱና ተስፋ ሳይቆርጡ በግልጥ መነጋገር ያሻል። አለመተማመን ምስጥ ነው። ወዳጅነትን ብቻ ሳይሆን አገርን የሚያፈርስ ምስጥ ነው። አገር አደገች፣ በተሃድሶና በልማት ገሠገሠች ሊባል ይችላል። በሕዝብ መሓል፣ በፖለቲካና በሃይማኖት መሪዎች ላይ፣ በሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ መታመን ሲጠፋ የአገር ህልውና ለአደጋ ተጋልጧል። ተቦርቡሮ ሳይታሰብ ይደረመሳል። ነውጥና ዕልቂት በአንድ ሕዝብ ላይ የሚመጣው ከዚህ የተነሳ ነው። የአገር መሪዎች በሥልጣን ላይ ለመቆየት ብቻ ሲሉ በሕዝብ መሓል አለመተማመንን ይዘራሉ፤ ይህን በማድረጋቸው ሳያስተውሉ የራሳቸውን ውድቀት ያፈጥናሉ። መተማመንን ከኢኮኖሚ ልማት ባልተናነሰ መዝራት ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለአመራራቸው እድሜና በጎ ታሪክ እንደሚያጎናጽፍ ይዘነጋሉ። ሰዎች ከራሳቸው ቤተሰብ፣ ጎሣ፣ ጾታና ሃይማኖት ክልል ውጭ ሌላውን ማመን ሲሳናቸው ማኅበረሰብ መፈረካከስ ጀምሯል። መንግሥታት የሚገዙትን ሕዝብ ሲጠረጥሩ፣ ተሳትፎውን ሲያሳጥሩ፣ የገቡትን ቃል ሲቀያይሩና ፍትኅ ሲነፍጉት ማንም ሳያስገድዳቸው ሊፈናቀሉ ተቃርበዋል። [ይቀጥላል]

ምትኩ አዲሱ