ር ዕ ሰ  አ ን ቀ ጽ

ባንተ በኩል ስትቦረቡር ውሃ ገብቶ ልናልቅ አይደል?

sinkingship

በጀልባ ተሳፍሮ እየተጓዘ። ቀጥሎ ካለው ክፍል ውስጥ ኳኳታ ይሰማል። ኳ ኳ ኳ ኳ ኳ ኳ … ኳ ኳ ኳ ኳ ኳ ኳ … ኳኳታው አላቆም ሲል፣ ወጣ ብሎ የጎረቤቱን በር ይመታታል። ኳ ኳ ኳ ሲከፍትለት የጀልባዋን ወለል እየፈለፈለ እንደሆነ ያያል።

“ምን እያረክ ነው!?”

“እየቦረቦርኩ ነው፤ አይታይህም?”

“እየቦረቦር - ኩ? ምን ነካህ? ጤና የለህም?”

“እንዴት ምን ነካህ፣ የቦረቦርኩት በኔ በኩል ስለሆነ አንተን አያገባህም!”

“እንዴት አያገባኝም? ባንተ በኩል ስትቦረቡር ውሃ ገብቶ ልናልቅ አይደል?” አለው ይባላል፤

በዚህ ዘመን ለመብቱ የሚሟገት እንጂ ግዴታውን ጨምሮ የሚያስብ ሰው እየጠፋ ነው። መብቴ ነው፤ በምርጫዬ ምን አገባህ? ይላል። ያም ተቀብሎ፦ በምርጫው ምን አገባኝ፣ ይላል። የጋራ ምርጫ ሲዘነጋ፣ ማኅበረሰብ እንደሚቃወስ፣ ሁሉም እንደሚጎዳ የሚያስብ የለም። እያንዳንዱ እንዳፈቀደው መረን መውጣቱ፣ ነጻነት ነው ተብሏል። እያንዳንዱ በተናጠል፦ መብቴ ነው፤ መብቷ ነው፤ መብቱ ነው፤ መብታችን ነው ይላል። በግልና በጋራ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ግዴታን እንደሚጨምሩ ተዘንግቷል። አንድ ዜጋ ታክስ ካልከፈለ። ባለሥልጣን የሕዝብ ንብረት ከዘረፈ፣ ዘርፎ ካልተቀጣ፣ ድህነት ሊሠለጥን ፍትኅ ሊዛባ ነው። የቤተክርስቲያን መሪ የተጠራበትን ዓላማ ለይቶ ካላወቀ፣ በዓለማዊ ሩጫ ከተጠላለፈ፣ ግዴታውን ዘንግቷልና፣ የሞራል ልቅነት ማኅበረሰቡን ሸርሽሮ ሊያሰጥመው ነው። “በየጎሣህ፣ ለጎሣዬ” ከተባለ፣ ከራስ አልፎ ለሌላው መትረፍ ካቃተ፣ አለመተማመን ሊበራከት፣ የአገር ኅልውና ትርጉም ላይኖረው ነው። ከራሴ ጾታ ጋር ብጋባ፣ ደን ብጨፈጭፍ፣ የባዕድ ባህል ብመርጥ ምን አገባህ ከመጣ፤ ውሃ እያስገባ፣ ጀልባዪቱ አጋድላ ልትሰጥም ነው። ዜጎችና መሪዎች ስለ ጊዜያዊ ምቾት፣ ስለ መብትና ነጻነት ከማውሳታቸው አስቀድሞ፣ ስለ ግዴታቸው በተለይም ስላለባቸው ማኅበራዊ ግዴታና ስለ ትውልድ አደራ ጠንቅቀው ማሰብ የሚኖርባቸው ለዚሁ ነው። ያንዱ ነጻነት ለሌላው እስራት ሊሆን ስለሚችል። ያንዱ ምርጫ ሌላኛውን ምርጫ ሊያሳጣ ስለሚችል። የዛሬ ድል፣ የዛሬ ዝና፣ ነገ ክሥረትና ውርደት ሊሆን ስለሚችል።

የጉዟችን አቅጣጫ አንድ ነው፤ የተሳፈርነው ጀልባ አንድ ነው። የእግዚአብሔር ፍርሃት ካልገዛን ስለ ሌላው ላይገደን ነው፤ አቅጣጫ ልንስት ነው። “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፣ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው” [የሐዋርያት ሥራ 17፡26-27]። የፈጠረን አንድ ነው። ማንም ከማንም አይሻልም ማለት ነው። የሚሻል ከመሰለው ያ ሰው ራሱን እያታለለ ነው፤ ኃያሉን አምላክ እየተቃወመ ነው። የተወሰነልን ዘመን ሰባ ቢበዛ ሰማንያ ዓመት ነው። ለዚያውም መቁረጫውን የሚያውቅ የለም። የተመደበልን ዳርቻ የኢትዮጵያ ምድር ነው። መብት ያለ ግዴታ ትርጉም አይኖረውም። የሌላውን መብት እየገፋን በሰላም እንኑር ማለት ግፍና ሞኝነት ነው። ግፍ፣ ብዙሃኑን ረሐብ ሲሞረሙር፣ ጥቂቶች የጥጋብ ግሳት ሲያሰሙና እንደ ተገባቸው ሲያስቡ፣ ግሳታቸው ሳያሳፍራቸው ሲቀር ነው። ግፍ በተገኘበት የእግዚአብሔርን ፍርድ ይጠራል፤ ፍርዱ ግን እንዴትና መቸ እንደሚመጣ የሚያውቅ የለም። አቅም ላጡ አቅማቸው ከጌታ ፀባዖት ዘንድ ነው [ያዕቆብ 5፡1-5፤ መዝሙር 12፡5]። ቡርቦራውን ማስቆምና ቀዳዳውን መድፈን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ጀልባዪቱ አቅጣጫዋን ስታ፣ ልንሰጥም እያጋደለች፣ ሁሉ ደህና ነው ማለት፣ ስለ ተቦረቦረው ስፋት፣ ስለ ኳኳታውና ስለ ምልልሱ መከራከር ፋይዳ የለውም።

2012-08-05 Photo credits:googleimages