የድመትእናያይጥፍቅር

catnmouse

ድመትና ዐይጥ ቢስታኒ በሚባል ቅልጥ ያለ ከተማ ይኖሩ ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ዐይጥ መንገድ ስታቋርጥ ድመት ያያትና በፍቅሯ ይጠመዳል። ተጠግቶ፣ “ምን ያህል እንደምወድሽ ብታውቂ እኮ አብረን እንኑር ስልሽ እሺ ትዪኝ ነበር” አላት። እርሷም በአቀራረቡ ተማርካ ተጋብተው ሊኖሩ ተስማሙ።

እንግዲህ አብረን የምንኖር ከሆነ፣ አለ አቶ ድመት፣ ክረምት ላይ ረሓብ እንዳይጨርሰን ከአሁኑ ቀለባችንን እናዘጋጅ፤ አንቺም ወጥመድ እንዳይዝሽ ከቤት ወጣ ወጣ ማለት አታብዢ፣ እሺ?

እሺ አለች ሙሽሪት።

እንሂድና አንድ ገንቦ ሞራ ገዝተን እንምጣ ተባባሉ። ተያይዘው ወጡ። መንገድ ላይ ያያቸው ሁሉ “ያዝልቅላችሁ፣ ያዝልቅላቸው ... ትፍትፍትፍ” ይል ነበር። ገዝተው ሲመለሱ ግን ሞራውን የት ይደብቁ? አንድ ዘዴ አሰቡ። ሌባ የማይደፍረው ከቤተክርስቲያን የተሻለ አናገኝምና እዚያ ወስደን እንደብቅ አሉ። ረሓብ ዘመን መሻገሪያ ቀለባቸውን ወስደው ከቤተክርስቲያን ካዝና በታች ደበቁ።

የደበቁት ሞራ ከሥራና ከአሳብ ብዛት ሥፍራው እንዳይሳሳተው አቶ ሠጋ፤ ስለዚህ ጧት ማታ ጸሎት ሲያደርስ፣ ጨምሮ “ሞራው፣ ሞራው፣ ሞራው” ይል ጀመር። ሲቆይ ሞራው ባይኑ ፊት እየመጣበት ተቸገረ፤ እንዲያውም በእንቅልፍ ልቡ ሳይቀር ይልስ ጀመረ። በረታበት፣ አንድ ቀን፣

“ዐይጢት” አለ፤

“ወዎይ” አለች፤ (በዐይጦች አፍ “ወይ!” ማለት ነው)

“የአጎቴ ልጅ ጥቊር ጣል ያረገበት ምን የመሰለ ነጭ ወንድ ልጅ ወለደ ብለውኛል፤ እኔም ክርስትናው ላይ እንድገኝለት አደራ አደራ ብሎኛል፣ ደርሼ እስክመለስ አንቺ ቤቱን ትጠብቂ?” አላት።

“ኧረ ሂድ፣ ችግር የለም፤ ብቻ ስትመለስ ለኔም የሚበላ ይዘህልኝ ና” አለችው።

ድመት ሆዬ፣ ግራ ቀኝ ሳይል ቀጥታ ወደ ቤተክርስቲያን ገሠገሠ። ሞራውን ከደበቁበት ከካዝናው በታች መሸፈኛውን ገለጥ አርጎ ቶሎ ቶሎ ካናት ካናቱ ካናት ካናቱ ላስ ላስ ላስ አደረገ። አምሮቱ ጋብ ሲልለት ቤተክርስቲያን ጒልላት ላይ ወጥቶ ከተማውን ቊልቊል ይመለከት ጀመር። “ይኸ ሌላ ከተማ ነው ወይስ እኔው ያለሁበት? እንዴት ያምራል?” አለ። ተንጋልሎ ከንፈሩን እየላላሰ ዐይኑን እየደባበሰ እስኪበቃው ፀሐይ ሞቀ፤ ሲዝናና ሲንሸራሸር ውሎ ሲመሽ ወደ ቤቱ፤

“ደህና ዎዋላችሁ፣ አመሻችሁ?” አለ

“መጣህ? ደስ ብሎክ የዋልክ ትመስላለህ” አለች ዐይጢት፤

“ለመሆኑ ሕጻኑን ማን አሉት?” አለች ጨምራ፤

“ካናቱ” አለ፣

“ካናቱ? እንዲህ ዓይነት ስም ሰምቼ አላውቅም፤ ቤተሰባችሁ ውስጥ ካናቱ የሚባል አለ?”

“ማንስ ቢባል ምን ያረግልሻል? እንዳንቺ ክርስትና ልጆች 'ጥሬ ለቃሚ' ከመባል አይብስ?”

ብዙ አልቆየም፣ ድሙ አምሮቱ አገረሸበት፤

“ዐይጢት” አለ፣

“ወዎይ!”

“ዛሬም ላስቸግርሽ ነው፣ ክርስትና አባት እንድሆን ጠይቀውኝ … እ.እ.እ. እኔ እንኳ እምቢ ልል አስቤ፤ ሕጻኑ አንገቱ ላይ ቀለበት መሳይ ምልክት አለበት፤ ጆሮውም ይንቀሳቀሳል ስላሉኝ የማልቀርበት ሆነ፤ ብቻሽን ትቼሽ ልሄድ ነው” አላት፣

ጥግ ጥጉን አጥሩን ተከትሎ ከጫፍ ሲደርስ በቀዳዳው ሾልኮ ከቤተክርስቲያን ደረሰ፤ ግራ ቀኙን አማትሮ አይቶ፣ ዘው ብሎ ገብቶ የደበቁትን ስንቅ ገሚሱን ላፍ ላፍ፤ ላፍ ላፍ። ላፍ አረገ። አንዴ አስገሳና፣ “ደብቀው እንደያዙት የሚጥም የለም” አለ። እንደ ገና አስገሳና፣ ምላሱና ከንፈሩ ላይ የቀረውን ወዝ እየላላሰ ካፀዳ በኋላ ወደ ቤቱ፤

ሆዱ ሞልቶ ስለነበር ኮቴውን ከሩቅ ሰምታ፣ ከመድረሱ “ስሙን ማን አሉት?” አለች፤ ጮኽ ብላ፣

“ገሚሱ!”

“እየቀለድክ ነው? ገሚሱ ብሎ ስም፤ ቀን መቊጠሪያም ውስጥ እንኳ ቢፈለግ አይገኝም” አለች፤

አልቆየም፣ ድሙ ለሓጩ እየተዝረበረበ ተቸገረ፤ በልቡ፣ “ነገር ሁሉ በሦስት ይጸናል” አለ፤

“ዐይጢት!”

“ወዉይ” አለች፤ (የዚያ ዘመን ዐይጦች ሲሽኮረመሙ ወዎይ እንደማለት ወዉይ ይላሉ)

“ይኸውልሽ እንደገና የክርስትና አባት እንድሆን ጠየቁኝ እኮ” አለ። “ያሁኑ ደግሞ ከእግሩ በተቀር ቀለሙ ጨርሶ ጥቊር ነው፤ ይገርማል። በታሪካችን እንዲህ ዓይነቱ ሕጻን የሚወለደው በአርባ አራት ዓመት አንዴ ብቻ ነው፤ እሺ በይኛ” አላት፤

“ካናቱ! … ገሚሱ! ... ስሞቹ ምነው እንግዳ ሆኑብኝ?” አለች ለራስዋ እንድምታወራ፣

“ምን ይደረግ? የቦነነበት በርኖስ ለብሰሽ፣ ጅራትሽን አስረዝመሽ፣ ቀን ደጅ አትወጪ የሆነ ያልሆነ አሳብ ታጠነጥኚያልሽ” አለ፣

ወጥቶ ሄደ። ዐይጢት ቤቱን አፀዳድታ እቃዎቹን ማስተካከል ጀመረች። አቶ ድመት ለችግር ሰዓት ከደበቁት የቀረውን ቀለባቸውን ደርሶ ከመቸው አጋብቶ። “ካላለቀ ዕረፍት አይሰጥ!” አለ፣ የጥጋብ ግሳት በረጅሙ እያስገሳ። እስኪመሽ ወደ ቤት አልተመለሰም።

ሲደርስ፣ ዐይጢት እንደ ልማዷ የሕጻኑን ስም ጠየቀች።

“ከፊተኞቹ ይልቅ ይኸኛው እንዳስደሰተኝ በምን አወቅሽብኝ? ስሙ ‘ከሥሩ’ ነው” አላት፤

“ከሥሩ? ... ጉዴን!” አለች። “ከሥሩ… ከሥሩ… ምን ማለት ይሆን?” እየገረማት ተጠቅልላ እንቅልፏን መለጠጥ ጀመረች። ከዚያን ቀን በኋላ ድሙ ክርስትናም ሠርግም አልተጠራም፤

ክረምት ጊዜውን ጠብቆ ደረሰ። የሚላስ የሚቀመስ ከቤትም ከደጅም ጠፋ። ይኸኔ ዐይጢት ትዝ አላት፤ ለችግር ቀን የደበቁት ያ ስንቅ ትዝ አላት።

“ድሙ” አለች፤

“ሚያው!” 

“እንሂድና ለክፉ ቀን የደበቅነውን ያን ቀለባችንን አውጥተን እስኪበቃን እንውረድበት፣” 

“እሰይ፣ እሰይ፣ እንዴት ትዝ አለሽ? እኔማ ፈጽሞ ረስቼው!” ተነሥተው ወደ ቤተክርስቲያን አመሩ። ሲደርሱ ገንቦው ከሸሸጉበት ሥፍራ ላይ በኮባ ቅጠል እንደተከደነ ቁጭ ብሎአል። ዐይጢት ኮባውን ገለጥ አረገች። ገንቦው ባ…….ዶ ነው ... ዐይኔ ነው ምንድነው? አለች፤ እንደገና ዞራ አየች ... ባዶ ነው። “ጠርጥሬ እኮ ነበር! ... ዛሬ ግልጽ ሆነልኝ! አንተን ብሎ … ወዳጅ፤ ክርስትና እያልክ ስታጋባው … “ካናቱ” … “ገሚሱ” ... “ከሥርርርርርር …

ዋጥ አረጋት! ቤተክርስቲያን ውስጥ ዋጥ አረጋት!

ምትኩ አዲሱ

© ምትኩ አዲሱ | ጥቅምት 2012 ዓ.ም. | ኦክቶበር 2019 | "አፈ ታሪክ ከእንደገና"

art credit: pinterest.com

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave