ርዕሰ አንቀጽ

የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ?

matrimonyጋብቻን በተመለከተ፣ ሦስት አሳሳቢ አዝማሚያዎች ይታያሉ። የመጀመሪያው፣ የክርስቲያንና የእስላም ጋብቻ ሲሆን። ቀጥሎ፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ። በመጨረሻም፣ የጅምላ ጋብቻ ነው። ሙስሊም ወንድ፣ ክርስቲያን ሚስት ማግባቱን ቁርዓን አይከለክልም። ሙስሊም ሴት ግን ክርስቲያን ባል ማግባት አትችልም፤ የምትወልዳቸውም ልጆች ክርስቲያን መሆን አይችሉም። በአሁኑ ወቅት ክርስቲያን ነን በሚሉ በአንዳንዶች ዘንድ ከኑሮ ውድነትና እምነትን ካለመረዳት የተነሳ ከሙስሊሞች ጋር የሚጋቡ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል። እምነቱን እንደሚገባ የማያውቅ ምእመን የተጋለጠ ለመሆኑ ይህ አንድ ማስረጃ ነው። “የሰላምና የመቻቻል” አራማጆች የሚሰብኩንን መስማት ትታ ቤተክርስቲያን የክርስቶስን ወንጌል ማስተማር የሚኖርባት ለዚሁ ነው። “[ክርስቶስን] ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ … ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?” [2ኛ ቆሮንቶስ 6፡14-15]። ክርስቶስን ላመኑ፣ እግዚአብሔርን መታዘዝ፣ ሰውን ከመታዘዝ ሊቀድምባቸው ይገባል [የሐዋርያት ሥራ 4፡19]። የክርስቶስን ትምህርት የማይገነዘቡ ያፈቀዳቸውን ያደርጋሉ ማለት፣ ክርስቶስን ለሚከተሉት መመሪያ ይደነግጉላቸዋል ማለት አይደለም።

ሌላኛው፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ጉዳይ ነው። ግብረሰዶማዊነት እንደ ሰብዓዊ መብት ሕጋዊ እውቅናና ድጋፍ እንዲያገኝ ሕዳር ወር 2004 ዓ.ም. በአፍሪካ አዳራሽ የተደረገውን ሙከራ አንዘንጋ። መንግሥት ይህን ተግባራዊ ካላደረገ እርዳታ እንደሚያጣ አሜሪካና አውሮጳ አስታውቀዋል። የፖለቲካና የቤተክርስቲያን መሪዎችም የተባበረ፣ ግልጽና ጠንካራ አቋም እንደ መውሰድ በተናጠል ሲቆሙ፣ ሲያመነቱና ሲያፈገፍጉ ታይተዋል። ዛሬ የመብት ጥያቄ ነው፤ ነገ ግን ጥያቄው የጋብቻ ጥያቄ እንደሚሆን ቤተክርስቲያን መርሣት የለባትም። ቤተሰብ የአገር ህልውና መሠረት እንደ መሆኑ፣ በዚህ አፍራሽ በሆነ ጉዳይ ላይ ተቻችሎ መኖር እንደማይቻል ግልጽ ይመስለናል።

ሦስተኛው፣ የጅምላ ጋብቻ ወይም “የሺህ ጋብቻ” ጉዳይ ነው። በዚህ መሠረት፣ አንድ ሺህ ተጋቢዎች ከየክልሉ መስተዳደሮች ለየብሔሩ በወጣው መመሪያና ኮታ መሠረት እንደሚመለመሉና ጋብቻቸውን በሕዳር ወር በስፖርት ሜዳ ላይ እንደሚፈጽሙ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። ዓላማው፣ ሀ/ ሠርግ እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ ነው ተብሏል። ሪፖርተር ጋዜጣ፣ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ድህነት ስላለ፣ ማግባት እየፈለጉ የተሳናቸው እንዳሉ ጠቅሶ፣ የናጠጠ ሠርግ የሚሠርጉትን ወርፏቸዋል፤ ለ/ የመቻቻልን ባህል ለማዳበር መ/ የአዲስ አበባን መቆርቆር 125ኛ ዓመት ለመዘከር ሠ/ “ሺህ ጋብቻን” ዓመታዊ ክብረ በዓል ለማድረግ ረ/ የአገራችንን መልካም ገጽታ ለዓለም ለማስታወቅና በ“ጊነስ” የዓለም ሪኮርድ ለማስመዝገብ ነው ብለዋል። ተጋቢዎች ማመልከቻ ይሞሉና፣ ለዚሁ የተቋቋመው ኮሚቴ መዝኖ የሚቀበለውን ተቀብሎ ሌላውን ውድቅ ያደርጋል፤ የተመረጡት ተጋቢዎች ወደ መጡበት ክልል ተመልሰው ይህንኑ አዲስ ባህል ያስተዋውቃሉ፤ በጎ ለዋለላቸው መንግሥት ውለታ ከፋዮች ይሆናሉ ማለት ነው።

ዝግጅቱ በንግድ ለተሠማሩ ገቢ ያስገኛል እንበል። በአገር ደረጃ ግን አደገኛ አዝማሚያ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ያልታቀዱ ቆይተው የሚከሰቱ የቀውስ ጽንሶችን እንደቋጠረ ማሰብም ይበጃል። መነሻ አሳቡ፣ ማሕበረሰብን በፈለግነው ሁኔታ እንደ አውራ ጎዳና መቀየስ እንችላለን ከሚል ከ19ኝኛው መቶ ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የተቆነጠረ ይመስላል። ሰው፣ በአምላክ አምሳል የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ሳይሆን በፍጥረት ሂደት የተገኘ ጅምላ አካል ነው ይላል። ባለፈው ትውልድ፣ እግዚአብሔር የሌለበትን ሶሻሊስታዊ ማሕበረሰብ ለመመሥረት፣ የነበረውን እንዳለ መጣልና ማፍረስ እንደ ተጀመረ እናስታውሳለን። በያኔ የአገሬውን ባሕልና የሰውን ተፈጥሮ ካለመረዳት የተነሳ የጠፋውን ሕይወትና የወደመውን ንብረት እንደማስታወስ፣ ያንኑ ስሕተት በሌላ መልኩ ስንደግም እንዳንገኝ ያሠጋል። ሁለተኛ፣ ልዩ ልዩ መሆን ወንጀል እንዳይደለ ሁሉ፣ አንድ ወጥነትም መቻቻል ነው ሊባል አይችልም። ተጋቢዎቹ ብሔራቸውን ይወክሉ ከተባለ፣ ድርጊቱ አንዱ ብሔር ከራሱ ውጭ ከሌላኛው ብሔር ጋር በፈቃዱ፣ የመንግሥት እጅ ሳይኖርበት፣ እንዳይጋባ እንደሚከለክልም አብሮ የታሰበ አይመስልም። ከሺህ ተጋቢዎች ውስጥ ገሚሱ ክርስቲያን [የስም ክርስቲያን ሊሆን ይችላል] ገሚሱም ሌላ ሊሆን ይችላል እየተባልን ነው። ሠርጉ የሚፈጸመው በቤተክርስቲያን ሳይሆን በስፖርት ሜዳ ነው። ዝግጅቱ [ለቱሪስቶች] መዝናኛ እንዲሆን ጭምር ነው። የክርስቲያን ጋብቻ በቤተክርስቲያን መሆን ሲገባው፣ በንግድ፣ በመንግሥታዊ ድርጅቶችና በባለሥልጣናት አቀናባሪነት መሆኑ የእግዚአብሔርን ቤት ሥልጣን መቀናቀን ብቻ ሳይሆን ጋብቻ የሰው ሥራ፣ የፖለቲካ ፕሮግራምና ሸቀጥ መደረጉን ማየት አያዳግትም። የቤተክርስቲያንን ሥልጣንና ተልእኮ በማሕበራዊ ድርጅቶች መተካት ወዴት ያመራል? አውሮጳና ሰሜን አሜሪካ ከደረሰባቸው ማሕበራዊና ሞራላዊ ቀውስ አንጻር ምን ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል?

ጋብቻ በመሠረቱ፣ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ ቃል ኪዳን ነው። ቅዱስ ነው፤ ከማሕበራዊ ግንኙነቶች ሁሉ የተለየና የከበረ ነው። ጋብቻን የመሠረተው፣ ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ ነው። የሁሉ ፈጣሪ የሆነ እግዚአብሔር የደነገገው ሥርዓት ስለሆነ ሰዎች እግዚአብሔርን ይመኑ አይመኑ ለውጥ አያመጣም ማለት ነው። “ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” [ዘፍጥረት 2፡18-25። ማርቆስ 10፡6-9]። “ሺህ ጋብቻ” ይህን አስተምህሮ ይቀናቀናል። የተቀደሰ ሲል፣ ለግለሰቦች የተከለለና በፍቅር ላይ የተመሠረተ መፈቃቀድ መሆኑን ያመለክታል። ሙሽሮች ይቀድማሉ፤ ታዳሚ ይከተላል። ሁለቱ አይነጣጠሉም። ሙሽሮች ይደምቃሉ፤ ታዳሚ ያዳምቃል። የጅምላ ጋብቻ ግን ትኩረቱ “ማሕበራዊው” ላይ ስለሆነ፣ የግለሰብን ሕልውና ይሽራል።

በሥላሴዎች [አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ አምላክ] ለሚያምኑ በ“ሺህ ጋብቻ” መሳተፋቸውን ወንጌል አይደግፍም። ወንጌል፣ ጋብቻን ክቡርና የተቀደሰ እንደሆነና፣ የሰው ሥራ እንዳይደለ ለማስረዳት፣ በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መካከል ባለው ግንኙነት ይመስለዋል። ክርስቶስን ባል፣ ቤተክርስቲያንን ሚስት፤ ወይም ሙሽራና ሙሽራዪቱ ይላቸዋል። ሙሽራዪቱን ፍለጋ ዳግመኛ ሲመለስ የሠርግ ግብዣ እንደሚኖርም ይጠቅሳል፣ “ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነው … ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ” [ኤፌሶን 5፡23-32፤ ራእይ 19፡7-9]።

ጋብቻን በጅምላ በማፈጻጸም በዓለም ዙሪያ የታወቀው ከወር በፊት በ92 ዓመት ዕድሜ የሞተውና መሲሕ ነኝ እያለ ሲያታልል የኖረው ኮርያዊው ሙን ነው። ሙን፣ በአዳምና ሔዋን ኃጢአት ምክንያት የፈረሰውን ቤተሰብ ለማደስና በዓለም ላይ ሰላምን ለማምጣት፣ እኔና ባለቤቴ ተልከናል ብሏል። በዚህ አሳብቦ የተለያዩ ሴቶችን አግብቶ ወልዶ ፈቷል፤ ወጣት ሴቶችን አማግጧል። ያጋባቸው ብዙዎችም እንዳሰቡት አልሆነላቸውም። በሌላ አነጋገር፣ ሙን እንኳንስ የሌሎችን ትዳር ሊመሠርት የራሱንም አልተወጣም! በቻይና ደግሞ፣ የምዕራባውያንን ባሕል ተጽእኖ ለመግታት፣ በጥንታዊ ሃን ስርወ-መንግሥት ባሕል መሠረት የጅምላ ጋብቻ መፈጸም ተጀምሯል። በኢንዶኒዥያም ገቢአቸው ትዳር እንዳይመሠርቱ ላገዳቸው ሺህዎች ዜጎች መንግሥት ነጻ ቲኬት እያደለ ማጋባት ጀምሯል። ናይጄሪያ በካኖ ክፍለ ግዛት ባል ወይም ሚስት የሞቱባቸውና የፈቶች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ መሆኑ ያሳሰበው መንግሥት በጅምላ እየዳረ ይገኛል።

የጅምላ ጋብቻ ከሚመልሰው ይልቅ የሚያስነሳው ጥያቄ ይበዛል። መንግሥትና መንግሥት ፈቃድ የሠጣቸው የንግድ አካላት በትዳር መነገዳቸው ተገቢ ነው? ግለሰቦችን በብሔር ብሔረሰብ አጣምሮ ከመጓጓዣ እስከ ሆቴል እስከ ድግስ ወጪ ሸፍኖ ትዳር እንዲመሠርቱ ማነሳሳት ለምን አስፈለገ? የገንዘብ ጉርሻ በመስጠት ጋብቻን ማካሄድ ስብዕናን ማራከስና የግለሰብን ምርጫ መጫን አይሆንም? ድህነት ትዳር እንዳይመሠርቱ ካገዳቸው፣ ከተጋቡ በኋላ እንዴት ይወጡታል? እያንዳንዱ እንደ አቅሙ እንጂ እንደ ጎረቤቱ [ወይም እንደ ቴዲና ቀነኒሳ] ማግባት አለበት ማን አለ? የአቅም ማነስን ችግር ለመፍታት ከአቅም በላይ የመኖርን ችግር መፍጠር አይሆንም? ሕጋዊ ጋብቻ ሳይፈጽሙ አብረው የሚኖሩትን እንዴት ማገድ ወይም እንዲጋቡ ማስገደድ ይቻላል? ቀዳሚው ማሕበራዊ እንቅፋት ትዳር አለመመሥረት ነው ወይንስ ድህነትና ሥራ አጥነት? በብሔር ማጋባት ለተያዘው ፖለቲካ ምን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ታስቧል? ሃይማኖት ቀይጦ ወይም ጥሎ መጋባት እውን መቻቻልን ያስገኛል?

መቻቻል ጠፍቷል ከተባለ መንስዔው ምንድነው? ሕዝቡስ እስከ ዛሬ እንዴት አብሮ ኖረ? በበለጸጉ አገሮች አለማግባት፣ ዘግይቶ ማግባትና አግብቶ አለመውለድ መስፋፋቱ ለምን ይሆን? መንግሥትና፣ መንግሥት እውቅና የሠጣቸው ድርጅቶች ቤተሰብን በማቋቋም ተግባር መሠማራታቸው ተገቢ ነው? ድህነት ስለ ተባባሰ ነው ጅምላ ጋብቻ የታሰበው? ድህነት ከአርባና ከሃምሳ ዓመት በፊትም የነበረ ነው። ያኔ ትዳር የመሠረቱ እንዴት ተወጡት? የመንግሥትና የንግድ ድርጅቶች ጣልቃ መግባት የግል ጥረትን፣ የጓደኛና የጎረቤትን የመተሳሰብና የመተጋገዝን ባሕል አዳክሞ ተመጽዋችነትን አያስፋፋም?

ያልጸኑ ምእመናን በ“ሺህ ጋብቻ” እንዳይወሰዱ፣ ይህ መጤ ባህል ሥር እንዳይሰድድ፣ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ምን እርምጃ ትውሰድ? ወይስ፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይናና ከናይጄሪያ የተቀዳ የጅምላ ጋብቻ ያዋጣል እንበል?     እአአ በ2012 "ቅዱስ ጋብቻ ወይስ ጅምላ ጋብቻ?" በሚል ርዕስ ታትሞ፤ በ06/25/16 በመጠኑ ታርሞ የቀረበ፤

Copyright © 2012, by Ethiopianchurch.org. All rights reserved. Text, graphics, and HTML code are protected by US and International Copyright Laws, and may not be copied, reprinted, published, translated, hosted, or otherwise distributed by any means without explicit permission. photo credit: google images.