ጉዞዬ፣ ዝብርቅርቁ ሕይወቴ እና መለኮታዊው ጸጋ። ጥበበ እሸቴ በእንግሊዝኛ ካሳተመው "ክሬዚ ላይፍ፣ ክሬዚ ግሬስ" በዳግማዊ ውቤ ተተረጎመ፤ አርትዖት፦ በዘነበ ገብረሐና። ኤስ አይ ኤም ማተሚያ፤ አ/አ፤ 2007 ዓ.ም፤ 263 ገጾች። ሐተታና ግምገማ

2roses-covየታሪክ ምሑሩ ዶ/ር ጥበበ እሸቴ የስድሳ ስድስቱ አብዮት ካፈራቸው መካከል ነው። "ጉዞዬ" በሚል ርእስ "ዝብርቅርቅ [የክህደት] ሕይወቱን" በአንድ ጎን፣ በሌላኛው በክርስቶስ አምኖ የተጓዘውን የእምነት ጉዞ ተርኮልናል። ሁለቱ የሕይወት ጎዳናዎች አይገናኙም ማለት አይደለም። ሁለቱም የየራሳቸው ውጣ ውረድ አለባቸው። "ጉዞዬ" ከሞላ ጎደል የአንድ ትውልድ፣ የአንድ አገር፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ታሪክ ነው – ሞት ሁሌ የተጋረጠበት ሕይወት፣ ሬሣ ተረማምዶ መሄድ የለመደ ሕይወት፤ ከሕግ ውጭ እስር ቤት የሚጣል፣ የሚረሸን፣ ስጋትና ስደት፣ ረሐብና እርዛት የሚያውቅ ሕይወት፤ አቅዶ እውን ለማድረግ ደንቃራ እንደ ጤዛ የሚረግፍበት "ዝብርቅርቅ ሕይወት" [ገጽ109-112፣125-126፣129-134]። "ጉዞዬ" የትውልድ ጠር ሰቆቃ በምድራችን እንዳይደገም ለመታገል ያበቃ ይሆን? ወንጌል ለነፍስና ለሥጋ ፍቱን መሆኑን አስተውላ ቤተክርስቲያን ጥረቷን እንድታፋጥን ይረዳ ይሆን? የመጽሐፉ የመጀመሪያዎቹ 154 ገጾች "ዓለማዊ" ጉዞ ላይ ያተኮሩ ሲሆን፤ ቀጣዮቹ ስለ "አዲሱ የአቅጣጫ ቅያሪ – ትልቁ አስደናቂ ክስተት" ይተርካሉ። "ጉዞዬ" የቀሰቀሳቸውን የአብዮት፣ የሃይማኖት፣ የምሑራን ምግባሮችን ትውልዱንና ተረካቢውን በማጣቀስ እንገመግማለን።

የየትውልዱ ፋሽን። እንደ አፍሮና ቤልቦተም፣ አብዮተኛነትና ክህደት የወቅቱ ፋሽን እንደነበረም ባንዘነጋ። ወጣቱ [እሳቱ] በየትኛውም ማኅበረሰብ የቀደመውን ትውልድ መከራከርና የራሱን ፈር መቅደድ እንደሚሻ። የያኔው ትውልድ ላያምን ላይረታ "ወይ አሳምነኝ፣ ወይ ላሳምንህ" ይል እንደነበር [ገጽ 8-9]። ሁለት ገጽ ያነበበ ሁሉ ሌላውን በእውቀቱ ለማስደነቅ፣ በሌላው ላይ ለመኮፈስና በሙግት ለመርታት እንጂ እውቀትን እንደ ጥበብ በነፍስ ፈላልጓት እንዳልሆነ። ዕውር ዕውርን የመራበት፣ የደመነፍስ፣ የቁጣና የጨለማ ጉዞ እንደነበረ። እውቀት፣ አጥንት ለመስበርና ለማዋረድ የተደገነ መትረየስ እንደመሰለ። የዛሬው ትውልድ ፍልሚያ እንዲህ አቅጣጫ-ብዙ፣ ራስ-ተኮርና ባወጣው ይውጣ ሊሆን።

ሰው ሃይማኖተኛ። በዶ/ር ጥበበ መጽሐፍ "ሃይማኖት" ሲል ክርስትናን [የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት] ስለሆነ፣ ይህ ግምገማ በክርስትና ላይ ብቻ ያተኩራል። ዶ/ር ጥበበ "ዓለማዊ" ታሪኩን ሲተርክ "መንፈሳዊነቱ" ጨርሶ እንዳልተወገደ እንታዘብ፤ ድሮውንም ሃይማኖት ያበቀለው ፍሬ ከግንዱ ርቆ አይረግፍም፦ "የተወገድሁና ያላግባብ ከተጣበቀብኝ ['ባንዳ'] ስም የተነሳ የተገለልኩ በመሆኔ ስለምሠቃይ፣ እስከዚህ ጊዜ ድረስ መጽናናትን የማገኘው በጠጪነት ልማዴ ነበር። ከዚህ የተነሳ ራሴን በውኃ ቦይ ውስጥ ለመጣል የፈለግሁባቸው በኋላ ደግሞ ያቅማማሁባቸው ጊዜአት ነበሩ። ወደ ፊት እንድዘል ከውስጤ የሚመጣ የሚመክረኝ ግፊት ይሰማኝና ነገር ግን በድንገት ሐሳቤን ቀይሬ እየተንገዳገድኩኝ ወደ ቤቴ መሄዴን እቀጥላለሁ። የምሄደውም ወደ ብሩህ ጨረቃ እና ከዋክብት እየተመለከትኩ፣ ደግሞም ከጨረቃ፣ ከከዋክብቱና ከአሸዋዎች በምንም የማላንስ 'የአጥናፈ-ዓለም ልጅ' እንደሆንኩ ለራሴ እያወጅኩኝ ነበር ... በእነዚያ መስመሮች አንጻር ማሰቡ የፍንደቃ ስሜትን እና ከመሞት ይልቅ ለመኖር መመኘትን ይሰጠኝ ነበር" [ገጽ122]።

ክህደትና ስካር፣ የአብዮተኞች ሃይማኖት፣ አደንዛዥ ዕጽ እንደነበረ አንርሳ። ሰው ከፍጥረቱ "መንፈሳዊ"ና አምላኪ ነው። በሁሉም ዘንድ የሰነበተ አንድ ችግር፣ "መንፈሳዊ" ምን እንደሆነ በቅጡ አለመረዳት ነው። "መንፈሳዊ" በአብዛኛው የማይታየውን ቁስ ከመጠቆም አልፎ ከቁስ የተለየ እውን ዓለም እንዳለ አይገነዘብም። ዶ/ር ጥበበም "የዚያን ጊዜ መንፈሳዊ ሰው የነበርኩ ባልሆንም" ይለናል [ገጽ 122]። ሁለተኛው ችግር፣ ፓለቲካና ሃይማኖትን መነጣጠል ነው። በክርስቶስ ያመኑ ከዓለም አይሁኑ እንጂ እስከ ዓለም ፍጻሜ በዓለም ናቸው፤ መገኘታቸው በራሱ ፖለቲካዊ ይዘት አለው። ፖለቲካና ሃይማኖት አንዱ በሌላው ላይ ተጽእኖ ያደርጋሉ፤ ሁለቱም የሰው ሁሉ መነኻሪያ እንደመሆናቸው ተነጣጥለው ለየብቻ እንደቆሙ ማሰብ ተሳትፎን የሚገታና የሚያጨናግፍ አደገኛ አመለካከት ነው። እምነት በልብ ብቻ ነው? ክርስቲያን ከፖለቲካ መራቅ አለበት? ክርስቲያን ገዢውን ክፍል መቃወሙ እንጂ መደገፉ ፖለቲካ አይደለም? የደርግ የመደብና የክህደት ርእዮት ፖለቲካ፣ ቤተክርስቲያን አንድ አቋም ይዛ በጥራትና በመከራ እንድታልፍ እንዳደረገ ሁሉ። ዛሬ የጎሳና የ"ነጻነት" ፖለቲካ ለዓለማዊነትና ለግለኛ ፉክክርና ፍርክርክነት ምክንያት ሲሆን እያየን ነው።

አብዮተኛ "መንፈሳዊ"ም ነው፤ እንደሌላው ሁሉ ይጸልያል፤ የሚጸልየው ግን በድብቅ ክህደት ማንም ሳያውቅበት ነው። ዶ/ር ጥበበ ችግር በቀረበ ሰዓት ከሚደጋግማት ጸሎቱ "የለመኑህን የማትነሳ፣ የነገሩህን የማትረሳ አምላክ እርዳኝ" የምትለዋን አካፍሎናል [ገጽ 84]። ደጋግሞ ከሞት አፋፍ በሚያስገርም አኳኋን የታደገውን፣ እርሱና ወላጆቹ በገባቸው መንገድ የለመኑትና የተለመናቸው፣ ኋላ ቻግኒ ጉምላክ ዘመቻ ጣቢያ ተመድቦ ባልጠበቀው መንገድ ካልጠበቀው ሰው ጋር ተዳብሎ በኖረበት ጎጆ ውስጥ፣ ሳያውቀው በልጅነት፣ ባለማወቅ በጎልማሳነት የካደውን በውን ሊያየው በቅቷል። ከዚህ ሁለት ቁምነገሮችን ማየት ይቻላል፤ አንደኛ፣ ሰዎች ጌታን ሳያውቁት፣ እየካዱትም ምሕረቱን እንደማይከለክል፣ የራቀውን ለማቅረብ ፍለጋ እንደሚወጣ፤ "እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና ... የሰው ልጅ [ኢየሱስ ክርስቶስ] የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአል" ማቴዎስ 5፡45፤ ሉቃስ 19፡10። ሁለተኛ፣ ሞት ሲያንዣብብ እንደሚታደግ። የሚገርመው ያኔ በክህደትና በተቃርኖ ከነበሩት መሓል የቀድሞ ጠ/ሚንስትር ታምራት ላይኔ፣ "ሰይፊቲ፣" ሰለሞን፣ ወዘተ፤ ይንቁትና ይጋፉት የነበረውን ወንጌል በኋለኛው ሕይወታቸው አምነው ለማገልገል መብቃታቸው ነው። በአንጻሩ የጌታን ምሕረት ሳይቀበሉ ዘመናቸው የተቆረጠችባቸውን፣ ለፍሬ-አልባ ትግል የብዙዎች ሕይወት መርገፉን ስናስብ ልባችን በፀፀት ይሞላል። አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ከአብዮተኛው ትውልድ ጣቃ ተቀድዶ የወጣ መሆኑንና ዶ/ር ጥበበ ከተረከልን፣ በርዕዮትና በምግባር እምብዛም እንዳልራቀ ስናስብ የያኔው ስህተትና የሥልጣን ጥመኛነት አርቆ ካለማሰብ በሌላ መልኩ እየተደገመ ይሆን? እንዳይደገም የሚፈቅድ ልቡና አይገኝ ይሆን እያልን እንሰጋለን። እነ ዋለልኝ መኮንን "እንደ ቀልድ" ያነሷቸው "እስከመገንጠል" መፈክሮች ዛሬ የዛቻ ይሁን የምር፣ አገራዊ መመሪያ ሆነዋል። በቤተክርስቲያንም ላይ ያልተጠበቁ ጫናዎችን እየፈጠሩ ነው። የተቀጣጠለው አብዮት አገራዊ ራእይ ቢኖርበትም፣ ስውር የሰላ አንደበቱ የአያቶቹን ቂም ለመበቀል ጭምር እንደነበረ። ደም ያፋሰሰ የዘመናት ሰቆቃ "መሬት ላራሹ" በአንጻሩ ከጅምሩ ተቀጭቶ ዛሬ ተገንዞ እናያለን። እርግጥ በሌላ ዘመን አያንሠራራም ማለት አይቻልም፤ ነገር ሁሉ ዛሬ በሚታየው አይጸናምና። የነገርን አካሄድና ፍጻሜ የሚያውቅ አንድ እግዚአብሔርና እግዚአብሔር የመከረው ልብ ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን።

የማኅበራዊ እሴቶችን መሸርሸር እናስባለን። የዶ/ር ጥበበ "ጫታም" ትውልድ አሁን ተንሠራፍቶ ከሚታየው የሐሺሽ የሰዶም፣ ኮብላይና ዘማዊ ባህል አኳያ የባህታውያን ዜና ሊመስል ምንም አልቀረውም። በሌላ አነጋገር፣ የሞራል ውድቀት ሲብስ እንጂ ሲቀንስ አይታይም። ዓላማዬን ብሎ መሞት ጊዜ ያለፈበት ጉዳይ መስሏል፤ ይልቅ ሞት ከፊቱ ተጋርጦበት ተገለባብጦ ራሱን ማዳን በልጦበታል። ይህ በአንድ መልኩ ካልበራለት ግትርነት ቢሻልም፣ ውጤቱ አድሮ የራሱ የሆነ ማኅበራዊ አሳር ማስከተሉ አይቀርም። ለ "እናት አገር ወይም ሞት!" ምላሹ "ሞት!" ነበር። ዛሬ ሳይጠሩት "አቤት!" የሚል "ሞት" በየደጁ ቀርቧል፤ "እናት አገር" መንደርተኝነት እየመሰለ ነው። የያዙትን እውነት መመርመር መልካም ጎን ቢኖረውም የያንዳንዱን "ግለኛ ታሪክ" ማስተናገድ የጋርዮሹን በማዛባቱ የጋራ ጉዳት ማስከተሉ የማይቀር ነው። አርቆ ካለማሰብ መሰዋት ይሻላል ወይስ በሆነ መንገድ ራስን ማኖር? በመደብ ርእዮት መከፋፈል ወይስ በጎሳና በንዋይ ፍቅር? በአብዮት ጫና ከተከፋፈለና በኑሮ ጫና ተሰድዶ ከተበተነ ቤተሰብ የቱ ይመረጣል? በመደብ ጠላትነት ወይስ በጎሳ ተከፋፍሎ በጥርጥር መተያየት ይሻላል? ቁርሾ መቋጠርና መጠፋፋት ወይስ አብሮ ለመኖር መደራደር? የርእዮተ ዓለም ወይስ የኢኮኖሚ ሰለባ መሆን ይከፋል? የኅብረተሰብ አእማድ ተቋማት [ቤተሰብ፣ ቤተ እምነቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና መንግሥት] አለመታመን፣ አለመታመንን ማራባትና መፈረካከስ ውጤቱ መልካም ይሆናል ማለት ከታሪክ አለመማር ነው። አክራሪ ጠርዝ ይዞ ሙጭጭ ከማለት፣ ይልቅ ጠርዙን ከመሓሉ ጋር ማያያዝ እንዴት ይቻላል? ማኅበራዊ ጥያቄዎችን በህጋዊና ባህላዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ማስፈራራት፣ ማባበልና ኃይል መጠቀም ፋይዳው እስከ ምን ድረስ ነው? የሞራል ውድቀት መባባስን በተመለከተ፣ የኢየሱስን ዳግም መምጣት ለምንጠባበቅ፣ "በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች ... ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ...ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ" [2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡1-5] የሚለው ሐዋርያዊ ቃል እንድንጸልይና ማኅበራዊ ተሳትፎ ከማድረግ እንዳንቆጠብ፣ የኢየሱስን አዳኝነት በሕይወት ገጽታዎች ሁሉ ላይ እንድናውጅ ይመክረናል።

ዶ/ር ጥበበ፣ ምሑርም ሃይማኖተኛም መሆን ይቻላል ወይ? የሚል ዋነኛ ጥያቄ ያነሳብናል፦ "ለምሑራን ወይም ከፍተኛ ትምህርት ላላቸው ... በእግዚአብሔር ማመን ፈጽሞ አብሮ የማይሄድ ነገር ነው ብዬ እገምት [ነበር] ... የእኔ ሐሳብ 'ክርስቲያን ነኝ' የሚሉ ምሑራን ከእውነታ ንኪኪ ጨርሰው የሚወጡ ሊሆኑ ግድ ነው የሚል [ነበር]" ገጽ 160። በአንጻሩ፣ ምሑርም ከሃዲም መሆን ይቻላል? የሚለው ያለጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ እንመለከታለን። ለዚህ መፍትሔው የ"ምሑር" እና የ"ሃይማኖት"ን ትርጉም ማጥራት ነው። ስንቱ "ምሑር" ነው ዛሬ ማንኛውንም መጻሕፍት በሚያነብበት ጽሞናና ጥንቃቄ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብብ? የተማረው ክፍል ምንም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ሳይኖረው እንደሚተችና ክህደቱም ከድንቁርና እንደመነጨ እንመለከታለን፤ የያዘውን የሕይወት አቅጣጫ እንዳያስለውጠው "ምሑሩ"ን የእውነት ፍርኃትና ሽሽት ይፈታተኑታል። ክርስትና በ"ምሑራን" መጠርጠሩ ምክንያቱ ለፍትኅ እንዳይቆም ወኔን ይሰልባል መባሉ ነው። ወንጌላዊ ክርስትና ግን በመሠረቱ ፍትኅን ከእግዚአብሔር ማንነት ነጥሎ አይመለከትም [ያዕቆብ 5፡1-6፤ ሚክያስ 6፡8]። ዊልበርፎርስ በባሪያ ንግድ ላይ፣ ማርቲን ኪንግ በዘረኝነት ላይ፣ ሉተር በእግዚአብሔር ስም በሚካሄድ ውስልትና ላይ፣ ኒሬሬ በቅኝ አገዛዝ ላይ፣ ቦንኦፈር በናዚ ግፍ ላይ፣ ወዘተ ያነሳሳቸው ወንጌልን ማመናቸው ነው። አንድን አስተምህሮ ባግባብ ሳይመረምር፣ እውነትን ሸሽቶ "ምሑርነት" መኃይምነት ብቻ ሳይሆን በደል ነው። ሃይማኖት በጭፍን ["በእምነት"] እንጂ መረጃ አይሻም የሚል። "እምነት" መረጃ የማይሻ የጨለማ ጉዞ እንደሆነ ያህል። እምነት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ካለመረዳት ወደ መረዳት ጉዞ መሆኑን አይገነዘብም። እምነት ግን "የዓለም ብርሃን ነኝ" ያለውን፣ በታሪክ የታየውን፣ የማይታይ አምላክ ምሳሌ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ የኖረውንና ያስተማረውን መረጃ አምኖ መከተል ነው [ዮሐንስ 8፡12፤ ቆላስይስ 1፡15፤ ዕብራውያን 1፡3]። ዘመናዊ ትምህርት መረጃ የሚሻ ሳይንሳዊ አመለካከት ስለሆነ ከሃይማኖት ጋር አብሮ አይሄድም ይላል። ምሑር የሌሎችን መብት ያከብራል እንኳ ቢባል በምግባሩና በእውቀቱ ለመታመን ከሃይማኖት ራሱን ማንጻትና ማራቅ፣ እምነቱን በልቡ መያዝ ይገባል ይላል። በልብ ያመኑት በአፍ ካልታወጀና በኑሮ ካልተገለጠ ክርስትናው ምኑ ላይ ነው? "በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። መጽሐፍ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና" [ሮሜ 10፡8-11]። ለአብዮተኛው ጥበበና ለሌሎች ትርጉም ያለው የሕይወት ለውጥ የመጣው የኢየሱስን ማንነትና የማዳን ሥራ በጥሞና በመመዘናቸው ነው።

ከአፄ ኃይለሥላሴ እስከ ደርግ እስከ ኢሕአዴግ "ምሑሩ" በአብዛኛው የተለያዩ አስተሳሰቦችን ለማስተናገድ ባለመቻሉ፣ ድርድር በማያውቅ የአስተሳሰብ ወኅኒ ውስጥ እየማቀቀ ይገኛል። ይህም የአገራችንን ትምህርት ፖሊሲ መሠረታዊ ድክመት ይጠቁማል፤ ትምህርት ቤቶች ትውልዱን እንዳላዘጋጁ፣ ፍርክስክስና ከገዢው ሥልጣን ሥር እንዳልወጡ እንመለከታለን። መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር ትውልዱ ካለፈው ሳይማር እንደ ቄስ ትምህርት ስህተቱን ይደጋግማታል። እያንዳንዱ የራሱን እይታና ጊዜያዊ ፈቃድ በሌላው ላይ ማጽናት ይሻል። የሌላውን፣ የማይደራደርበት ስህተትና ውጉዝ፣ ከግለሰቡና ከቡድኑ ጋር ይወገድ ይላል። መንግሥት ከሰበከው ውጭ መጠየቅና ማሰብ የኖረ ብሔራዊ እርግማን ነው። ገለልተኛነትና ከማንም አለመወገን "በራዥ፣" "ቀልባሽ፣" "ባንዳ"ነት፤ የትምህርት ገበታን ረግጦ አለመውጣት "ሳቦ፣ ሳቦተር፣" ረግጦ መውጣት "ሪቮ"ነት ነው። ለቀናቸው "ከርሸሌ፣ ቶርች፤" ላልቀናቸው፣ "ነጻ እርምጃ፣ መነጠፍ፣ መወገድ፣ መረሸን" ነው። ትግል ጦር ማንሳት ብቻ እንደሆነ ይታሰባል፤ ከትምህርት ገበታ መለየት የትግል ስልት ነው ቢባልም፣ የያዙትን ከዳር ማድረስ እንደ ፀረኛ ማስቆጠሩ። "ዩኒቨርሲቲ" እስከነስሙ መማማርያ፣ መመራመሪያ፣ በተለያዩ በተቃረኑ አሳቦች ዙሪያ መከራከሪያና መግባቢያ፣ የአስተሳሰብ ማበልጸጊያና የሰብዓዊነትና ብሔራዊ ኅልውና ማጎልመሻ ቢሆንም። ወይ አንድ-ወጥነት ወይም ዛሬ እንደምናየው፣ ዩኒቨርሲቲ መረጃ የማይገራው የግለኛ አመለካከት ማጽኛ ማእከል ሆኗል።

ለወንጌል አማንያን ከ"መንፈሳዊ" መጻሕፍት ውጭ ማንበብ "ሥጋዊ"ነት ነው፤ በዓለም ላሉ "ምሑራን" መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ "መርከስ" ነው። የዚህ የተዛባ አመለካከት ምንጩ፣ ሁሉን ወይ ለፖለቲካ ወይም ለምናኔ-መሳይ ፍጆታ ማዋሉ ነው። ወጣቱ አብዮተኛ ጥበበ፣ ድኅረ-ምረቃ እስከገባ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ገልጦ አንብቦ አያውቅም [ገጽ 158-160፣ 163-166፣ 173]። በዶ/ር ጥበበ ጉዞ፣ በክርስትናና በምሑርነት መሓል የተገተረ ግድግዳ የፈረሰው፣ ቻግኒ ጉምላክ አብሮ ዘማቹን ጣዕመን ያገኘ ጊዜ ነበር። አብዮተኛና ዓለማዊ ጓዱ ጥበበ፣ ጊዜ ወስዶ የርሱን ማንነት እንዲያጠናና ከወንጌል ትምህርት ጋር እንዲተዋወቅ ማድረጉ፣ የጣዕመን አምላካዊና ምሑራዊ ምሪት ይጠቁማል። ጣዕመ የምጣኔ-ሃብት ምሑርና የወንጌል አማኝ ነበር [ገጽ 163-165]። ከላይ እንደጠቀስነው፣ ክህደትና ምሑርነት አንድን ሰው እርስበርሱ አያቃርኑትም። ክርስትናና ምሑርነትም ባለሁለት ጓዳ ቤት አይደለም፤ እንደ ዘይትና እንደ ውሃ ሳይሆን እንደ ደምና እንደ ውሃ የተዋሃደ ነው።

ክፉውን ስለመቃወም፣ በጎውን ስለመያዝ። ዘመንና ትውልድ ቢለዋወጥም በአገር ደረጃ ዘለቄታ ያለው አስተማማኝ አካሄድ ገና የያዝን አይመስልም። አጭሩን እንጂ አርቆ አለማየት፣ የአስተሳሰብ ስፋት አለማጎልበት፣ ያላቋረጠ ፈተና ሆኖብናል። የግሪኮቹን ሲሲፈስን አታላይነት ለመቅጣት ቡላድ ድንጋይ ገፍቶ ጋራ ጫፍ እንዲያደርስ እንደተፈረደበት። ገፍቶ ጫፍ ባደረሰ ቁጥር ግን ድንጋዩ ተንከባልሎ ጋራው ግርጌ ሲመለስበት፤ እንደገና "ሀ" ብሎ ሲጀምር። እውነት መነጋገርና አለማታለል ከምንገኝበት ማኅበራዊ ውድቀት ትንሳኤ ያቀዳጀን ይሆን? እውነት መነጋገርስ የእግዚአብሔር ፍርኃት ሳይኖር ይቻላል? ቤተሰብ፣ ቤተ እምነት፣ ትምህርት ቤትና መንግሥት ለዚህ ባህል መፋፋት አስተዋጽዖአቸውን ሳይለግሱ እንዴት ይሆናል? ብሔራዊ የሕዝብ መዝሙር የአምላክን ስም የሚጠቅስ ነበር፤ ቃለ-መሓላ በእግዚአብሔር ስም ይገባ ነበር። ይህ አድራጎት መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ እምነት የሚያንፀባርቅ ቢሆንም በሌሎች የዓለም መንግሥታት ዘንድ እንኳ ከተለመደው በወጣ ጥቂቶች በብዙኃኑ ፈቃድ ላይ ያላግባብ ተጭነው እናያለን። ተማሪዎች ከጅምሩ የአምላክን ህልውና ከአገር፣ ከዜግነት ግዴታና ከአንድነት ጋር ሳያስተያዩ በሁለት ተከታታይ ሥርዓተ መንግሥታት ባእዳን ሆነው እያደጉ ነው። "አብዮታዊ" ወደ "አብዮታዊ ዲሞክራሲ" ተሸጋግሯል። በአብዮት ዘመን፣ በኀሌታ "ሀ" ይጀምር የነበረ ፊደል ተገልብጦ "በ" በሆነ፤ ወደ መሬት እንጂ ወደ ሰማይ መጠቆም፣ የሚጸልዩ እጆችን ማንሳት ተከለከለ። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ፊደል በ"ሀ"ና በ"በ" መሆኑ፤ የቱን መቸና እንዴት እንደሚጠቀም በማድበስበሱ፣ የዜጎችን ተሳትፎ በፍርኃት ገትቶ ይሆን? ሙሉ ተሳትፎ ሳይኖር መተማመንና የተሟላ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ማምጣት ይቻላል? መተማመንን በማጎልበት ወንጌል አማንያን ድርሻቸውን እየተወጡ ነው?

ኋላ "በአብዮት ስም" ሊሆን፤ የደርግ አባሎች መሓላ "በሕያው እግዚአብሔር ስም" እንደነበረ አንርሳ። ከደርግ ጋርና ተቃርነው ለተሰለፉ አንጃዎች ግን "ሕያው እግዚአብሔር" እና "አብዮት" ብዙ አብረው እንደማይጓዙ ገብቶአቸው ነበር። በቅድሚያ "እግዚአብሔር የለም" መባል ነበረበት። ያን በማድረጋቸው "ነጻ የወጡ" ቢመስላቸውም፣ መረን እንደወጡ፣ የራሳቸውን ክብር እንዳጡ፤ በአምሳሉ የተፈጠረውን ሰው ደም በማፍሰስ በራሳቸው ላይ ፍርድ እንዳመጡ በጊዜ ሊገነዘቡ አልቻሉም። ይቅር ባዩ ኢየሱስ በመስቀል እንደሞተላቸው ስላላመኑ፣ እስከዛሬ በኅሊና ክስ ታስረው በነፍስ ጨለማ ውስጥ የሚማቅቁ ስንቶች ናቸው? ዶ/ር ጥበበ ጉዞውን "ግራ በተጋባ ዘመን የሚኖር፣ ግራ የተጋባ ሰው" ሲል ገልጾታል [ገጽ 113]። በሌላ ሥፍራ ደግሞ "ተመሳሳይ ጉዳቶችን በሥቃይ ያስተናገዱትን፣ ነገር ግን ለመቋቋም አቅሙ ያልነበራቸውን የገዛ ራሴን ትውልድ ... በመላው ሕይወቴ ጨለማ የነበሩትን ጊዜአት" [ገጽ 127] ብሎታል። ወይም "ከኃላፊው ጊዜ እንደመታሠርና ጓደኞችን ማጣት ዓይነት ጠባሳ የቀረልን ተስፋ ቆራጮች ነበርን፤ ስለራሳችንም ሆነ በዙሪያችን ስላሉት ነገሮች እፎይ ብለን የተረጋጋን አልነበርንም" [ገጽ 142] ብሎታል። የሞተውም እንኳ አልተረጋጋ፣ የዛሬስ ትውልድ ምን ያህል ተረጋግቷል? የክርስቶስ ወንጌል ካበራለት ውጭ የተስፋ ጭላንጭል ያየ ማን አለ? የአብዮት ፍሬ በአገር ብቻ ሳይሆን በግል ግንኙነቶችም ላይ ታላቅ ተጽእኖ እንዳደረገ እንታዘባለን።

ውጣ ውረድ እስከ ምጽኣት አይቋረጥም። ዶ/ር ጥበበ አምኖም በሕይወቱ ዝብርቅርቅነት ይታይ የለም ወይ? የሚል አይጠፋም። ለምሳሌ፣ ሁለቴ አሜሪካን አገር ለትምህርት መጥቶ ሁለቴ አቋርጦ ወደ አገሩ ተመልሷል [ገጽ 213-236]። "በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ ትልቁን ጥያቄ እንድጠይቅ አደረገኝ፤ የገዛ ራሴን አምሮት እየተከተልኩ ነኝ ወይስ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ፈቃድና በጠላት ሤራ መካከል ትልቅ ጦርነት እየተካሄደ ነው – ወይስ ይሄ በገዛ ፈቃዴ እና በእግዚአብሔር ፈቃድ መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው? ሁሉም ዓይነት ጥያቄዎች ጠንካራ እና የእርግጠኝነት መልስ ልሰጥ በማልችልበት መልኩ በአእምሮዬ ውስጥ ተነሡ። ይሄ በሰውኛ ቃላት ግልጽ አድርጎ ለመግለጽ በጣም የተወሳሰበና ያልተለመደ ታሪክ ነው። የቅርብ ዘመን ኃላፊ ጊዜያትን መለስ ብዬ ስመለከታቸው፣ ሥዕሉ ግልጽ ያልሆነ እና ውስብስብ ነበር" [ገጽ 235]። በመጀመሪያ፣ ወንጌልን ማመን ከዓለም ውጣ ውረድ ነጻ ያረጋል ማለት አይደለም። "በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ" [ዮሐንስ 16፡33]። ወንጌልን ማመን ይልቅ ዓለም የማያውቀውና የማይሰጠው ሰላም አለበት። "ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም" [ዮሐንስ 14፡27]። ጽኑ ተስፋ ያጎናጽፋል። በወንጌል ብርሃን ተስፋ መጓዝ ይቻላል። ዓለም የሚያጎናጽፍው ተስፋ ምንድነው? ተስፋህ፣ ተስፋሽ ምንድነው? ሁለተኛ፣ ዶ/ር ጥበበም እንዳስታወቀን፣ ካመነ በኋላ ላይ ታች ያለበት ምክንያቱ የጌታን ምሪት በእርግጥኛነት ወደማወቅ ባለመድረሱ ይመስላል። ይኸ የሚሆነው አንዳንዴ አስቀድሞ ምሪትን ለራስ ከመቀበል ይልቅ በጣም "መንፈሳዊ" በሆኑ ሌሎች ላይ ከመደገፍ ወይም የግል ልምምድን በቃሉ እውቀት ካለመመርመር ነው።

ነፍሰ ገዳይ ቂመኛ ባህል ደግሞ አለ። ዶ/ር ጥበበ ወላጅ አባቱ ሲሞቱ በያዘው የፖለቲካ አመለካከት ያልተስማሙ አብሮ አደጎቹ "ባንዳ" ብለው ለቅሶ ለመድረስ እንዳልፈቀዱ በልብ ስብራት ተናግሯል [ገጽ 117]። የአብዮት ውጤት ይኸውላችሁ፦ አብዮተኛው ትውልድ ደርግን አብዝቶ ከመጥላቱ የተነሳ ከጠላት ሶማልያ "ዲሞክራሲያዊ ኃይላት" ጋር አብሮ አገሩን ይወጋል [ገጽ 124]። እግዚአብሔርን አለመፍራት ጉዳቱ ምንኛ የከፋ ነው? ይኸው ቂመኛና አርቆ የማያስተውል ባህል ዛሬም ድረስ ይታያል። የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍሬ እነሆላችሁ፦ በጠ/ሚ መለስ ሞት ጮቤ የረገጡትን ማየት ምን ያህል ሰብዓዊነታችን እንደዘቀጠ ያመለክታል። የተያያዘ ነው፦ እግዚአብሔርን መፍራት ራስንና በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው ማክበርን ያስገኛል። ቤተክርስቲያን ሰዎችን በወንጌል ከመድረስ ጋር ማኅበራዊ ተጽእኖ የማድረግ ጥረቷ ምን ያህል ግቡን መትቷል? በክርስቲያኖችስ ዘንድ ነፍሰ ገዳይና ቂመኛ ባህል ይታያል?

የዶ/ር ጥበበ ትውልድ ሠፈርና ቤተሰባዊ ማንነት ሌላ ትምህርት ሰጭ ጉዳይ ነው። በአባቱ በኩል ከ13ኛው ክፍለ ዘመን መነኩሴ ከወንጌላዊ አቡነ ተክለሃይማኖት ጋር መተሳሰሩ፣ በእናቱ ከኦሮሞ ጎሳ መወለዱ [ገጽ 16-18]። ሠፈሩ እስላም፣ ኦርቶዶክስ፣ ሶማሌ፣ ካቶሊክ፣ ጦርነት፣ የፈረንሳይ፣ የጣልያን፣ የእንግሊዝ መንግሥታት ተጽእኖ፣ የነጋዴ የአርሶ አደር፣ ወዘተ፤ የተሰባጠረበት ማኅበር በመሆኑ የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝቦችን አሠፋፈርና አኗኗርን ይወክላል። በሌላ አነጋገር፣ ሕብረብሔርነት በአገራችን ብቻ የተከሠተ ያህል እንደ ድንቅ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ መዋሉ አግባብ አይደለም ማለት ነው።

የመጽሐፉን አተረጓጎም በተመለከተ። የእንግሊዝኛውን ቅጅ ስላላገኘን በትርጉሙ ጥራት ላይ ምንም ማለት አንችልም። ያም ሆኖ መጽሐፉ በጣም ተነባቢና ከግድፈት የነጻ ነው። ግለ-ታሪኩን ለብዙኃን ለመዳረስ ከተፈለገ ግን በሁለተኛው እትም ላይ እነዚህና የመሳሰሉት የእንግሊዝኛ-አማርኛ ሐረጎች ሊብራሩ ይገባል፦
"ክርክሩን ብሸነፍም ቀኑን በማሸነፍ" ገጽ34 / "እንደ ባሪያ ተግቼ መሥራት ነበረብኝ" ገጽ 35 / "መረጃው ቅንድባቸውን አነሳው" ገጽ 109 / "እንደ ጠባቂ መልአክ" ገጽ 130 / "በጉጉት ወደፊት የምንመለከት የተቃጠሉ ተራማጆች ነበርን" ገጽ 135 / "እጅጌዬን ሰብሰብ አድርጌ" ገጽ 151 / "አከርካሪ የሌላቸው ፍጥረቶች" ገጽ 167 / "በአሸዋ ላይ ድንበር እንዳሰመርኩኝ አወቅሁ" ገጽ 177 / "ሌሎች ልጃገረዶች በመንገዴ ላይ አቋርጠዋል" ገጽ 192 / "አረንጓዴውን መብራት በመስጠት" ገጽ 197 / "ቫኒቲ ፌር" መጽሔት "ከንቱ ትርኢት" ሳይሆን "ቫኒቲ ፌር" ነው ገጽ 208 / ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ላለው "የመቃብር ቁልል ዓይነት የለውጥ ባህርያት" ገጽ 209 / "ምቾት የሚሰማኝ ቢሆንም" ገጽ 226 / "በተፈጠረው ክፍተት ውስጥ በመቆም" ገጽ 242 / "ነጥቦቹን ላገናኛቸው ሞከርኩ" ገጽ 254 / "ከንጋቱ 5 ሰዓት" 11 ሰዓት ይባል ገጽ 125 / አነባበብን በተመለከተ። ዊልድ፣ ዋይልድ፤ ዊዘል፣ ቪዜል፤ ኦሲስ፣ ኦኤሲስ ይባል። ይህ ግለ-ታሪክ በአንድ ዘመን በአንድ ሥፍራ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የተፈጸመ እንደመሆኑ በሌሎች በሌላ ዘመን ሲነበብ የተጠቀሱ ሰዎች ስም የተሟላ መረጃ ሊሰጥ ይገባል። ስሞችን ማሳጠር ለእንግሊዝኛ ተናጋሪ ታስቦ ነው ቢባልም ያንኑ ወደ አማርኛ መተርጎም ሌላ ችግር ይፈጥራል። "ሰይፊቲ" ሰይፉ፣ "ጥሌ" ጥላሁን መሆኑ ግልጽ ነው። የትኛውን ጥላሁን? ሙለር? "ሳም" ሳሙኤል ወይስ ሳምሶን? ሳሙኤል ከሆነ ሳሙኤል ማ? የግለሰቦቹን ማንነት ላለመግለጥ ታስቦም ከሆነ መግቢያው ላይ እንዲያ ሊጠቀስ ይገባ ነበር። ከያኔዎቹ የተረፉ የት ደረሱ? ማለት አይቀርምና ከበስተጀርባ ይኸው መጠቀሱ ጥሩ ውሳኔ ነው።

ታሪክ የሚዘነጓትን አትምርም። ግትሮችን እንደ ተንኮለኛ ልጅ አድብታ "አገኘሁህ፣ እስቲ ምን ትሆን?" ብላ ትሳለቅባቸዋለች። የዶ/ር ጥበበ ግለ-ታሪክ ሠፈርና ወቅት እየቀያየረ በስንቶች ሕይወት ተደግሟል? ወጣቱ አብዮተኛ ጥበበ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ ሲመረቅ ዲፕሎማውን የተቀበለው ሲቃወማቸው ከኖረው ከጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም እጅ ነበር [ገጽ 144]። ሊቀመንበሩ የማዕረግ ልብስ ተላብሶ ፊታቸው የቆመው ወጣት በልቡ የቋጠረውን ማየት ቢችሉስ ኖሮ? ውድ እናቱ አዳራሹን በእልልታ ባያቀልጡና ልቡን ባያስፈነድቁ፣ ደስታው ጎድሎ በቀረ። የሰው ሕይወት ምንኛ አሳዛኝ ነው? ምንኛ በምሥጢር የተሞላ ነው? መንግሥታቸው የማይበገር የመሰለ ሊቀመንበር መንግሥቱ ዛሬ በጥገኛነት ዚምባብዌ ይገኛሉ። እርሳቸውንና መንግሥታቸውን ተቃውመው የተነሱ የዶ/ር ጥበበ የትውልድና የትምህርት ቤት አጋሮች ሞተዋል፣ ተሰደዋል ወይም ቤተመንግሥቱን ወርሰዋል። እነዚህንስ "ታሪክ" በምን ትዝብት እየቃኛቸው ይሆን? መንግሥት ግን የእግዚአብሔር ናት፤ "መንግሥትህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን ... መንግሥት ያንተ ናትና፣ ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤" የዶ/ር ጥበበ ጉዞ እንዳስታወቀን ሁሉንም ሕይወት ሰጭው እግዚአብሔር ያውቃል ማለት ይሻላል።

ዶ/ር ጥበበ ለዶክትሬቱ ማሟያ ያካሄደው ጥናት ከስድስት ዓመት በፊት "ዘ ኤቫንጄሊካል ሙቭመንት ኢን ኢትዮፕያ፣ ረዚስተንስ ኤንድ ረዚልየንስ" በሚል ርዕስ በመጽሐፍ ታትሟል። አልተተረጎመ እንደሆነ ይህን ጠቃሚ መጽሐፍ ቀለል ባለ መልኩ በጥንቃቄና በምክክር አርሞ ለብዙኃን ማድረስ የሚቀጥለው የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል። ዳግማዊ ውቤ ውብ ሥራ ሠርቷል፤ በዳግም ሥራው እንደምንገናኝ ተስፋ አለን። ከሃዲ አብዮተኛ የነበረ የደብተራ እሸቴ ኃይሉ እና የወይዘሮ ቦጋለች ዋቅቶላ ልጅ በአገራችን የተቀጣጠለውን የወንጌል እንቅስቃሴ ታሪክ ለመጻፍ መብቃቱ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ጥበብ ያሳያል። እግዚአብሔር ይመስገን።

የመጽሐፉን መንፈስ በተመለከተ። ዶ/ር ጥበበ የታሪክ ምሑር እንደመሆኑ፣ በታወሰው መጠን በሕይወቱ ያሳለፋቸውን ከማስፈር አልፎ የያኔ ባላንጣዎቹን በቂም በቀል ለማሳጣት ወይም ራሱን ከሆነው በላይ አድርጎ ለማሞገስ ሲሞክር አይታይም። ይህ ከለገሰን እሴቶች መካከል የሚደመር ሲሆን ግለ-ታሪካቸውን ለመጻፍ ለሚያስቡ መልካም አርኣያ ነው። ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ በሕይወቱ ያመጣውን ለውጥ "ሊቆም በማይችል የደስታ እና የመደነቅ ሁኔታ ውስጥ ተሞላሁ" ሲል ገልጾታል [ገጽ 186]። ይህም "መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፣ ይህ ማባከን ነውና ... የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና" ከሚለው ሐዋርያዊ ቃል ጋር ይስማማል [ኤፌሶን 5፡18፤ሮሜ 14፡17]። አሜን እንበል።

ምትኩ አዲሱ

Revised 10/6/15