ችግሩ አ ል ተ ፈ ታ!
ቤተ መጽሐፍት መረጃና እውቀት አሰባስበው በማደራጀት ለተጠቃሚው ያዳርሳሉ። ያን በማድረጋቸው ማሕበረሰብ ታሪኩን ይማማራል፤ የወደፊቱን ያልማል፣ ይተልማል። በተለያዩ አሳቦች ዙሪያ የመነጋገርን ባህል ያዳብራል። ቤተ መጽሐፍት፣ ደሃውን ከሃብታሙ፣ ወጣቱን ከአዛውንቱ፣ ወንዱን ከሴቱ፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮችን፣ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በአንድ ጣራ ሥር ያሰባስባሉ።
ማንበብ አገር ገንቢና ሰብዓዊ መብት ነው። ቤተ መጽሐፍት ይብዙልን!
መብት ደግሞ ግዴታን ጭኖ ይመጣል። መሸታ ቤት እንደሚኾን ቤተ መጽሐፍት ውስጥ አይኾንም። ሁሉም በየጥጉ ከመረጠው መጽሐፍ ጋር ገጥሞ በተመስጦ አሳቡን ይሞርዳል፤ አሳቡን አስተካክሎ ለብሶ አደባባይ ይወጣል! እንጂ ከወዲህ ወዲያ እየተጠራራ፣ ስልክ እያቃጨለ ታዳሚውን እረፍት አይነሳም። አለዚያ የቤተ መጽሐፍቱ ጌታ፣ ሌባ ጣቷን አፏ ላይ አስጠግታ “እሽሽሽሻ!” ትላለች። ያ ካልሠራ ጠጋ ብላ በጆሮ “እረፍ!” ትላለች። ካስፈለገም በዘብ ታስወጣለች!
ወይም ነበር እንበል፤
ቅርብ ጊዜ በአንድ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት የታዘብኩት። አንደኛው ጫጫታው ሲያውከው የሚሠራውን አቋርጦ ከዚህ ከይሲ ገላግሉኝ ለማለት ቀረበ። የመጽሐፍቱ ጌታ፣ ገና ከመቅረቡ ቃል ሳታሰማ እፊቷ ከተቆለለው ላይ የጆሮ ውታፍ አንስታ አቀበለችው፤ ጩኸት በዛ ካልክ፣ ጆሮህን ወትፍና ሞክረው ነው ነገሩ!
ጠጋ ብዬ፣ ላስተዛዝነው፣ ለጊዜውም ቢሆን ችግርህን ያቃልልልሃል አልኩት። በስጬት ብሎ፣ ምን ያደርጋል ታዲያ አለኝ፣ ችግሩ አልተፈታ!
ሌላም አንባቢ አቤት ካለ፣ ምላሹ ጆሮህን ወትፍ ነው። በጥባጭ ግን አሁንም አልተነካ። ቅድም እንዳልነው፣ ቤተ መጽሐፍት አሳብ መለዋወጫ ነው። ጆሮ ግን ተደፍኖ አሳብ በየት ይግባ?
** **
ችግሩ ቊልጭ ብሎ እየታየ የሌለ መፍትሔ መፍጠር የዘመኑ አካሄድ ሆኗል። እንደ ኢትዮጵያ፣ አሜሪካም ጥቂቶች በልጽገው ብዙኃኑ ኑሮ እያንገላታው ነው።
ሦስት ሚሊዮን የአሜሪካ ሕዝብ ገቢው በ30 ዓመት በ300 እጅ አድጓል። ትረምፕ በፈረንጆች 2017 ያስጸደቁት አዲስ ታክስ ባለጸጋውን በሃብት ላይ ሃብት አከናንቦት፣ ድርጊቱ ብዙ ቊጣና ተቃውሞ ሊያስነሳ ሆነ። ከ 329 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 160 ሚሊዮኑ ግን ገቢው በ30 ዓመት ከነበረበት ፍንክች አላለም። የአሜሪካ ዋነኛ ችግር የገቢ መዛባት ነው፤ የፖለቲካ መሪዎች ግን ገጠሬውን በስደተኛ እያስፈራሩ አረሳስተውታል። የሰውን ቀልብ የሚሠርቅ፣ ወኔ የሚሰልብ እንደ ፍርኃት ምንም የለም። ስደተኛ ሥራህን፣ ሚስትና ሴት ልጅህን ሊነጥቅህ ነው፤ ዘርህን ኃይማኖትህን፣ ቋንቋህን ሊከልስ ነው፤ ስደተኛ መውለድ ስለሚያበዛ ከ25 ዓመት በኋላ አባቶችህ ባቀኑት አገር አናሳ ትሆናለህ! ግንብ አጥር ሠርተን እንድንከላከል ተባበረን! ስደተኛ በገነባው አሜሪካ፣ ታሪኩን የዘነጋውን ኪስ ያወልቃሉ! እንግሊዝ አገርም ታሪኩ ይኸው ነው፤ ሃንጋሪም፣ ሆላንድም፣ ኢትዮጵያም።
የአገራችን ዋነኛ ችግር ጎሳ አይደለም። ድህነት ነው። ዓለም አይቶ የማይለየን አንድ ቀለም ሆነን! መጣላት የጀመርነው ዛሬ አይደለም! ድህነት እንደሚያጣላ ማ ባስታወሰን! አንድ መልክዐ ምድር፣ አንድ የአየር ጠባይ እንጋራለን፤ ከየቀዬአችን የወጣ ውሃ ጠጥተን የቀረውን ለግብፅ አባይ እንገብራለን። የአገራችን ችግር ሥራ ማጣት ነው። ሥራ ፈትነት፣ የሥራ ፈትቶች ፖለቲካ ነው። የሥራ ፈትቶች የፍርኃት ፖለቲካ ችርቻሮ እንጂ ችግራችን ጎሳ አይደለም። ጥቂቶች እጅግ ከብረዋል፣ ዘርፈው ከብረዋል፣ አንዳንዶች ምናልባት በሐቅ! ብዙሃኑ ግን ኑሮ አድቅቆታል። በአገር ውስጥ ስደት፣ ከአገር ውጭ ስደት፣ በአሳብ ስደት ደቅቋል። እስቲ ይብላ ይጠጣ ይረፍበትና ጎሳ ጎሳ ይል እንደሆነ እንይ። እስቲ ይልበስና፤ እስቲ ጤናው እንክብካቤ ያግኝና፤ ልጆቹን አስተምሮ ይዳርና፤ ተስፋ ያግኝና... ጎሳ ከቊጥር ይገባ እንደሆነ ያኔ እናያለን!
የኢትዮጵያ ገበሬ እህሌን ለፉንጋ ወይም ለቁመተ ረጅም አልሸጥም አይልም፤ የምጠይቀውን ከከፈልክ ስለ ዘርማንዘርህ ምን ገዶኝ ነው! የአገራችን ችግር መፍትሔውን ውስጡ ቋጥሯል! ጆሮ ግን በፍርኃት ተደፋፍኖ በምኑ ይስማ?
ጭራቆቻችንን ይመልከቱ