ርዕሰ አንቀጽ
ጭ ራ ቆ ቻ ች ን
ጭራቅ ፈርተን አመነታን
ያሰብነውን ስንቴ ጀምረን ተውን
ባንድ ወቅት ሕጻናት ነበርን
ለአቅመ አዳም ደረስን፣ ጃጀን
የሰማነውን እንደ ማጣራት ስናመነታ ዘመን አለፈብን
እኛው የፈጠርነው ጭራቅ መልሶ አስፈራን
የፍርኃት እስረኛ ሆንን፣ ከደስታና ከሰላም ጎደልን፤

ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ ነው። እንደ ማዛጋት፣ አንዱ አፉን ሲከፍት አጠገቡ ያለውም አፉን ይከፍታል። “ተኝቼ አድሬ ምነው አዛጋኝ? ቡና ጠጥቼ ምነው አዛጋኝ?” ይላል። የጭራቅ ኑሮ ይህን ይመስላል።

ከቋጥኝ ጀርባ ቆሟል የተባለው፣ ሲቀርቡት የለም። በከንቱ ፈራን። በቁም ሰልቅጦ ጆሮህን ይተፋል የተባለው ብርሃን ሲበራበት ደብዛው የለም። ስንት ዘመን የፍርኃት እሥረኛ ሆንን? አንዴም አልተረጋጋን። እንጀራችን አፋችን ጋ ሳይደርስ ተፈርፍሮ አለቀ፤ በሰቀቀን ውኃችንን አዝረበረብን። እንቅልፍ ሳናይ ነጋ። ጭራቅ ግን አሁንም የለም።

ስለ ፍርኃት። ፍርኃት ፈሪ ነው። ፍርኃት የሚያስፈራው በአእምሮ ያልተዘጋጁትን፣ አርቆ ማሰብ የማይሆንላቸውን ነው። “ቆይ እስቲ፣ ይኸ ነገር እንዴት ነው?” ለሚሉ ፍርኃት እንደ ጅብ ምልክት አሰምቶ ይፈረጥጣል። ፍርኃት ያለአጀብ አይጓዝም፤ ቁጣ አጀቡ ነው፤ ስድብ፣ ጭለማ፣ መንጋጋት አጀቡ ነው። የአገር መሪዎች ፈርተዋል፤ ዱላ ለማንሳት የሚቸኩሉት ለዚህ ነው። ሕዝብ ፈርቷል፤ የሕዝቡ ፍርኃት ግን እንደ መሪዎች ከሥልጣን የመፈናቀል ፍርኃት ሳይሆን፣ “ምን እበላለሁ? ባለጉልበት ጎጆዬን ያፈርስብኝ ይሆን?” ብሎ ነው።

ጭራቆቻችን ምንና ምንድናቸው? ክልላዊ መንግሥት አንድ ጭራቅ ነው። የክልል አጥር እንደ እስር ቤት ከውስጥ ወደ ውጭ አለማስወጣቱን ያሰበ የለም። በወገን መካከል አጥር ማቆሙን ነቅቶ ያየ ቢኖር ጥቂት ሰው ነው። በሰማንያ ሦስት “ክልል” ሲታወጅ ብዙ ሕዝብ በሥጋት ተፍረከረከ። ከደርግ ብንገላገል የሚበታትን መጣብን ወይ አለ። በረገገ፤ በጩኸት ተደናቆረ። የሕዝብ መሪዎች ስላልተዘጋጁ ተደናገጡ፤ ተንተባተቡ። መሪ ሲንተባተብ ተመሪ ያብዳል፤ ምን ይደንቃል? ደግሞ “ክልል” የኖረን የሕዝብ አሠፋፈር አጎላ እንጂ አዲስ ነገር አላመጣም። አማራ፣ ትግሬው፣ ኦሮሞ፣ ሱማሌው፣ አኝዋው፣ አፋሩ፣ ወላይታው፣ ጉራጌው... ከኖረበት ቀዬው አልተነቃነቀም። ችግሩ ዛሬም እንኳ ሠፈራና ክልል ሳይሆን መሪ ማጣት ነው። ችግሩ፣ በትግራይ የውስጥ ጉዳይ ከትግርኛ ተናጋሪ ውጭ ማንም አያገባውም መባሉ። በአፋር ክልል አማራ፣ በአማራ ኦሮሞ አያገባውም መባሉ። ለ"ማንነት" ክልል የአገር መሪዎችን እንጂ ሌላው ሕዝብ አያገባህም መባሉ ነው። ከዚህ የባሰ ጭራቅ የለም።

“ክልል”፦ “አገር” “መንደር” እንለው የነበረ ነው። ጌታመሳይ “የትም የትም ዞሬ ትዝ አለኝ አገሬ” ሲል “አገር” የሚለው ትውልድ መንደሩን እንጂ ኢትዮጵያን እንዳልሆነ አንርሳ። “የትም የትም ዞሬ” ሲል የዞረው አዲሳባ እንጂ ውጭ አገር እንዳልሆነ አንርሳ። ኢትዮጵያዊ አእምሮ ሲፈጠር መንደርተኛ ነው፤ ጠባብና ወገንተኛ ነው። ተዘግቶ እንደኖረ፣ ነፋስና ፀሐይ እንዳልገባው ደጅ። እንደ ደቡባዊ ዴልታ የአሜሪካ ግዛት። በዓለም ዙሪያ መሰደዱና መበተኑ ከጠባብነት፣ ከሸውራራ አመለካከት ያላቅቀው ይሆን? ከኢንተርኔት ካፌ የሰፋ፣ ሁሉ የሚጋራው ዓለም እንደሚጠብቀው ወደ ማወቅ ይሸጋገር ይሆን? በንግድ፣ በጦርነት፣ በኃይማኖት፣ በባሪያ ፍንገላ፣ በስደት፣ በጠለፋ፣ በጉዲፈቻ፣ ሰርቆ፣ ገድሎ፣ አቁስሎ፣ ዕዳ ሽሽት፣ በጋብቻ በወረርሽኝ በድርቅ ተፈናቅሎ ተዛውሮ ኑሮ ያልመሠረተ ሕዝብ በኢትዮጵያም በዓለምም የለም።

ኦሮሞው ከደቡብ ተነሥቶ ወሎና ጎንደር ሠፍሯል። አማራው ቦረና ጅግጅጋ። ትግሬ ቀብሪ ደሐር ሻሸመኔ። ቃፊሩ። ባህታዊው። አናጢው። አሚናው። ተማሪው። የመንግሥት ሠራተኛው። ሽፍታው። አስተማሪው። ከገጠር ከተማ። ከክርስትና ወደ እስልምና፤ ከእስልምና ወደ ክርስትና። ከክርስትና ወደ ክሕደት። ከክሕደት ክርስትና። ከክሕደት እስልምና። ከእስልምና እስልምና። ከክሕደት ወደ ተፈጥሮ “ባዕድ” አምልኮ። ግማሽ ክርስትና፣ ግማሽ እስልምና። ከቆላ ደጋ፣ ከደጋ ወይናደጋ። ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ ወደ። ወለጋና ጎጃም ድሮም ኩታ ገጠም ነበሩ። ጎጃሜ፣ ጎን[እ]ደሬ፣ ትግሬ፣ ወሎዬ፣ አፋር፣ ሐረሬ፣ ሸዌ ...ኩታ ገጠም፣ ጎረቤት ያልሆኑበት ወቅት የለም። ይኸ ሁሉ ቢያንስ “ሦስት ሺህ” ዓመት ፈጅቶበታል።

በደረሰበት ሁሉም እንግዳ ነው፤ እንግዳ ባዳ ያልሆነ፣ ባዳ ያልተባለ የለም። ዐረብ አገር ቢሆን ፈረንጅ አገር ባዳነት ያልተሰማው የለም። እስኪላመድ በቋንቋ ያልተግባባ፣ በአለባበስ በአበላል፣ በአየር ጠባይ፣ በኃይማኖት ግር ያላለው የለም። ቁምነገሩ መፈራራቱ፣ መለያየቱ ሳይሆን፣ ውሎ አድሮ፣ መዛመዱ መላመዱ ላይ ነው፤ ለኑሮ ብልኃት መፍጠሩ ላይ ነው። ጎረቤት መሆን ሲጀምር። ሚስቱን ሞት ሲቀማበት፤ ለቅሶ ሲደራረስ። የጎረቤቱን ልጅ አፍቅሮ ካላገባኋት ሲል። ጎረቤት ከጎረቤት ጥሬ፣ አብሲት፣ እሳት ሲበዳደርና ገጀራ፣ ሙቀጫ፣ ጨው ሲዋዋስ። ተጣልቶ በሽማግሌ እርቅ ሲፈጥር። ዐመል ላመል ተቻችሎ አብሮ ሲኖር። ታሪኩና ቁምነገሩ ይኸ ነው።

እርግጥ ሁሉ አልጋ በአልጋ ሊሆን አይችልም። ብልጠት፣ ክፋት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ዝርፍያ፣ ውልና ክህደት፣ ድንበር መግፋት፣ ቅጥፈትና ንቀት የሉም ማለት አይደለም። አቅም እንዳገኘ ሁሉም ከበታቹ አርጎ የሚገዛውን ይሻል። አቅም ሲያገኝ በሚገዛው ላይ ገዥ መሆን ይሻል። ይኸ በኢትዮጵያ፣ በምድር ሕዝቦች መሓል፣ በቤተሰብ ውስጥና መሓል፣ በጓደኛ መሓል፣ በብሔር ውስጥና መሓል፣ በቤተ እምነት ውስጥና መሓል፣ በፈረንጅና በጥቁር፣ በከተሜና በገጠሬ መሓል፣ ባስተማሪና በተማሪ መሓል፣ በፍቅረኞች መሓል፣ ባገር መሪና በሕዝብ መሓል፣ በቄስና ምዕመን መሓል፣ በልጆች መሓል፣ በታክሲ ሾፌርና ተሳፋሪ መሓል፣ በሐኪምና በታካሚ መሓል፣ በነጋዴና ነጋዴ መሓል፣ በደገኛና በቆለኛ መሓል፣ በኦሮሞና ኦሮሞ፣ በወላይታና ወላይታ፣ በጋሞና ጋሞ መሓል፣ በክልስና በከሃዲ መሓል፣ ወዘተ፣ የኖረ የሚቀጥል ልማድ ነው።

ሰው የሚያስብ የሚያመዛዝን አእምሮ ተለግሶታል። አንዳንዱ ፈጣን ነው፣ አንዳንዱ ይዘገያል። አንዳንዱም ብኩን ተላላ ስለሆነ ስህተቱን እንደ አቦል ቡና ይደጋግማታል። ሁሉም ግን ያስባል። ለመኖር ይጥራል። ለኑሮው መፍትሔ ይሻል። መሪዎቻችን የሚዘነጉት ይኸንን ነው። ዘውዱ እየገዘተ ከሩቅ እያስፈራ ገዛ። ደርግ በጥይት በእስር እያስፈራራ ገዛ፤ የኋለኛ አስፈሪነታቸው ግን እንደ ነበረው አልቀጠለም። ብዙዎች ይህን ይዘነጋሉ። ደርግ በስድሳ ስድስት ተሰምቶ በማይታወቅና ባልተጠበቀ ስልት መድረኩን ተቆጣጠረ። ስድሳ የአገር አድባር ረሸነ። አድሮ ቁጥር ሥፍር የሌለውን ወጣት ማገደ። በሰማንያ ሦስት ተራ የደረሳቸው በጎሳ ክልል ስልት መድረኩን ተቆጣጠሩት። እነዚህም በያኔ አስፈሪነታቸው ዛሬ የሉም። የደፈረሰው ሲጠራ ነገሮች ኲልል ብለው ወጡ። አማርኛ መናገር ያስጠየፋቸው ዛሬ ተናግረው አላባራ አሉ። ኦሮምኛ ያስጠየፋቸው፣ አማርኛ ከኦሮምኛ ተገኘ ማለት ቀራቸው። ዛሬ የምሩን እንገንጠል የሚል የለም። እንገንጠል ማስፈራሪያ ነበር፣ ነው። ጭራቅ ነበር፣ ነው። እንኳንስ ሌላ ሊያሳምኑ፣ ወዴትና እንዴት እንደሚገነጠሉ ራሳቸውም ጠንቅቀው አያውቁትም፣ በጭፍን እንገንጠል አሉ። ዶሮ በቁሟ ብትዘነጠል ትጮሃለች፣ ደም ይወጣታል። ግለሰብን፣ ቤተሰብን፣ መንደርን እንደ ዶሮ መዘነጣጠል እንደማይቻል አላሰቡም። ራሳቸውን እንደሚዘነጥሉ አልታሰባቸውም። ቁጣ፣ ጥላቻ፣ ድንቁርና አጅቦት ሕዝቡ ከቋጥኙ ጀርባ ማንም እንደሌለ አላስተዋለም። የዕውር መሪ ቢሸፍትና ቢያሸፍት ጓሮ ድረስ ነው። ጓሮ ተቀምጦ ስለ ሽፍትነቱ አገር ተገልብጦ የሚያወራለት መሰለው። ሰው ወሬው ስለ ኑሮው እንጂ ስለ እርሱ አለመሆኑን ሲያውቅ ቀልዴን ነው ማለት ቃጣው።

ሌላም ጭራቅ አለ። ተራ ደርሶት ሥልጣን ሲይዝ ሁሉም የኔ ሥልጣን የማይገረሰስ የማይደፈር ነው አለ። የቀደሙት እንደዚሁ ሲሉ እንደነበሩና እንደተገረሰሱ ዘነጋ። እያንዳንዱ ሥልጣን ሳያጋራ በራሱ ፈቃድ ብቻ በስውር እንደሚንቀሳቀስ አለመ። ሁለት ትውልድ ይህን የመሰለ የውሸት ጡጦ ጠብቶ አደገ። ዘመኑ ግን ምሥጢር የሚደብቁበት አልሆነም።

የታሪክና የአፈታሪክ ደግሞ ጭራቅ አለ። ይኸ ዓይነቱ ግንዛቤ አንዳንዶችን የመቶ ዓመት ግዞተኛ አድርጎአቸዋል። በነዚህ ስሌት አጼ ቴዎድሮስ ዛሬም መቅደላ ላይ መሽገዋል። ምኒልክ ቅኝ ገዥ ናቸው። ዮሐንስ ከኩፊት አልተመለሱም። ቋንቋ፣ የራስ ወይም የቅኝ ገዥ ነው። ማሣው ግን ተዳቅሏል። ዘመን ተለውጧል፤ መርጡለ ማርያም እንኳ የቱሪስት መፈንጫ ሆናለች።

እውነቱን ለማወቅ ለሚሹ፣ እውነቱ በየአደባባዩ ወዳድቆ የሚያነሳውን ይጠብቃል።

እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ፣ የተበደልኩ ደግሞ ጭራቅ አለ፦ ዛሬ በምድራችን እኔ እበልጣለሁ የማይል የለም። እርስበርስ ይሞጋገሳሉ፤ ትርፍ በሌለው ንትርክ ጊዜ ያጠፋሉ። ካለፈው ታሪክ መራርጠው የራሳቸውን አሰማምረው ይተርካሉ። የሌላውን አሳንሰው አጥላልተው ይካሰሳሉ። ጉድፋቸውን በበከተ ጨርቅ ቋጥረዋል፤ ሽቶ አርከፍክፈውበት ግማቱ ብሶበታል። “ለራስህ ቁም፥ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ ይላሉ፤ እነዚህ በአፍንጫዬ ዘንድ ጢስ ቀኑንም ሁሉ የምትነድድ እሳት ናቸው... ኃጢአታችሁና የአባቶቻችሁን ኃጢአት በአንድ ላይ ወደ ብብታቸው ፍዳ አድርጌ እመልሳለሁ እንጂ ዝም አልልም፥ ይላል እግዚአብሔር” [ኢሳይያስ 65፡5-6]። የምሑርነት ጭራቅ፦ ብቃት የተናቀበት ዘመን ላይ ነን። ከቁመታቸው የተለቀ የማዕረግ አገልግል አንግተው ይንገዳገዳሉ፣ ይወላገዳሉ። ግራ ቀኛቸውን የማያውቁትን በማይጨበጥ ተስፋ ያስቋምጣሉ። ጭራቅ፣ ጭራቅ። ተበደልኩ እንጂ በደልኩ የሚል ጠፍቷል። የብልሹ አስተዳደር ጭራቅ አለ፦ አድገህ ራስህን እስክትችል መንግሥት ያውቅልሃል፣ ፊት ፊት እያልክ አታስቸግር ይላል። አድጎ ራሱን እንዳይችል የቀለቡን ገመድ አሳጥሮ ይዞበታል፤ ባወጀው የልማትና የሰላም አልጋ ላይ ተዘርግቶ ለመተኛት አልጋው አጭር ነው፤ ሰውነት ለመሸፈን መጐናጸፊያ ጠባብ ነው [ኢሳይያስ 28:20]። የሙስና ጭራቅ አለ፤ ካዝና እየዘረፈ አገር አደገች ይላል። ሦስት ትውልድ በአዙሪት ጭራቅ ተሽመድምዷል። የብልጽግናና የሰላም ጭራቅ ደግሞ አለ።

ሽሽሽሽ! የሚያጣድፍ ሥራ ይዣለሁ፣ ድምጽ መስማት አልፈልግም
[እኔም እኮ ለአገሬ የሚጠቅም አሳብ አለኝ]
እኔ ከማደርገው የተሻለ ሊሆን አይችልም፤ አታይም? የአገርን ነገር ለኔ ተውልኝ ብያለሁ
[የተጀመረው የተሻለ እንዲሆን ልደመጥ እንጂ፣ ልሳተፍ እንጂ]
አይ እንግዲህ፣ ነገር አታብዛ፣ ዋ ብያለሁ...

“ወንጌላዊው"፣ እግዚአብሔር ድህነትን ይጠላል፣ እንድትበለጽግ እመን ይላል። እኔን አታይም? እንዳንተው ነበርኩ፣ ዛሬ ፊቴ ተወልውሎ የምታየኝ እምነቴ እዚህ አድርሶኝ ነው፣ በመቶ ዶላር የሸመትኩት ጠበል ይህን አረገልኝ ይላል። በልቶ ስላስገሳው አገር ጠግቦ አደረ ይላል። ጥላቻና ንፍገት ቋጥሮ ፍቅርና አንድነትን ይመኛል።

አንተ ግን። "ነቢይ ነኝ" የሚሉ በምድሪቱ ሲበዙ ጠርጥር፤ ለራስህ ፍራ። ሁለት ዓይነት ሰዎች። በህልምና በውናቸው ጭራቅ የሚታያቸው አሉ። የሚሠራጨውን ወሬ ሳይፈትሹ ፍንክች የማይሉ ዓይነተኞች ደግሞ አሉ።

እውነቱ መገለጡ አይቀርም፤ እውነቱ የሚገለጠው ቅንነትና ትጋት ላሳዩ ነው። እውነቱን ለማወቅ ለሚጥሩ ነው። ከርቀት ጋራ ያከለ ጭራቅ፣ ሲቀርቡት ለካንስ የለም። ጭራቅን ጭራቅ ካልሆነው መለየት ዝግታና ምክክር ይሻል፤ ማሰብ፣ ሳይታክቱ መጠየቅን። ነገር ግን “በእነዚያ ወራት ኔፊሊም [ጭራቆች] በምድር ላይ ነበሩ።” ለማሰብ ለማጣራት ጊዜ ያጡ፣ መንታ ጭለማ ልብና መንታ ልስልስ ቆላፋ ምላስ የሆነላቸው አመነቱ፣ ፈሩ ተፈራሩ አስፈራሩ። ሁለት ቅን ልበ ቆራጦች ግን “አየናቸው፣ ጭራቆች ናቸው፣ አስፈሪነታቸው አያስፈራን” አሉ። 1/12/2009 ዓ.ም [9/22/2016]

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave