ሐ ተ ታ  ግ ም ገ ማ

መንበር እርካብ

abiybkcvrየአገር መሪዎች ሥልጣን ላይ ከመውጣቸው በፊት ወይም ከወረዱ በኋላ የራእያቸውንና የታሪካቸውን ሰነድ ይጽፋሉ፣ ያጽፋሉ። ሂትለር “ማይን ካምፍ” (“ትግሌ” የተሰኘ ማኒፌስቶ)፤ ባራክ ኦባማ ፕሬዚደንት ለመሆን ከመወዳደራቸው ከዓመት ተኲል አስቀድሞ (በ1998 ዓ.ም.) “ዘ ኦዳሲቲ ኦፍ ሆፕ”ን አሳትመዋል።

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የጠ/ሚንስትርነቱን እርካብ ረግጠው መንበሩን ከመቆናጠጣቸው ከዓመት ተኲል በፊት (በ2009 ዓ.ም.) “እርካብና መንበር” ን “ዲራአዝ” በሚል የብዕር ስም አሳትመዋል። እርካብ የሚያገለግለው ለመወጣጫ ብቻ አይደለም፤ ላደለው ለመውረጃም ነው። ከቴዎድሮስ እስከ መለስ፣ ሞት ወይም እርካብ ተበጥሶ መሪዎቻችንን አንድባንድ አሰናብቶብናል!

አፄ ኃ/ሥ ከ1923 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ነግሠው፣ ከዙፋን ሊወርዱ ዓመት ሲቀራቸው (በ1965 ዓ.ም.) “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ”ን አሳትመዋል። የርእሱን ቅደም ተከተል ብንመለከት፣ “ሕይወቴ” ከ “ኢትዮጵያ እርምጃ” ይቀድማል፤ ወይም “ሕይወቴ” እና “የኢትዮጵያ እርምጃ” አይነጣጠሉም የሚል ይመስላል። የንግሣቸውም ዘመን ባልተፈጸመ ትንቢታዊ የተስፋ ቃል ተቋጭቷል፦ “ህግ ለሰው ሁሉ የበለጠ የሚጠቅም መሆኑን ማንም አይስተውም። መከበርም መጠቀምም የሚገኙት ከህግ መተካከል የተነሣ ነው። መዋረድም መጎዳትም የሚመጡት ከህግ መጓደል የተነሣ ነው። ግፍና በደልም የሚበዙት ህግ ባለመቆሙ ነው” (ም. 29፣ ገጽ 150፣ አንቀጽ 3)። ፍትሕን በምድሪቱና በሕዝቦቿ መሓል ሳያሰፍኑ፣ ንጉሠ ነገሥቱ እራሳቸው ያለ ፍትሕ ተሰናብተዋል! የፍትሕ ጥያቄ ዛሬም እንኳ የሚያረጋጋ መልስ አላገኘም!

በ1966 ዓ.ም. 120 አባሎች ያሉት የጦር ኃይሎች አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቋመ፤ አባሎቹ አገር ስለመምራት ግራ በተጋቡበት ወቅት “ቆራጡ” መንግሥቱ ኃ/ማ ጠመኔ አንስተው ጥቊር ሰሌዳ ላይ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል ባለ ሁለት ቃል ራእይ ጽፈው፣ በ “ህያው እግዚአብሔር ስም” ተማማሉበት። መንግሥቱ ከተሰደዱበት ምድር “ትግላችንየኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ”ን አሳተሙ፤ እንደ አፄ ኃ/ሥላሴ ከህዝቡ የተለየ ሕይወት አልነበረኝም ብለውናል፤ የትግሉ ነው ሕይወቴ ለማለት እንዳሰቡ ግልጽ ነው። መለስ እና ጓዶቻቸው ደግሞ “የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ማኒፌስቶ” ነበራቸው። መለስ በረቂቅ የቀረ “የአፍሪካ ልማት” ሰነድ ትተውልን አልፈዋል።

ምንሊክ በቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት ይኖሩ በነበረበት ወቅት የቴዎድሮስን አካሄድ ሲያጠኑ ኖረው፣ ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ ወደ ሸዋ ተመልሰው እርሳቸውም የመሪነት ዕድሉ ሲገጥማቸው፣ ቴዎድሮስ በተለይ ከቤተክህነት፣ ከመሳፍንትና ከክልል ንጉሦች ጋር መናቆራቸውና መቆራረጣቸው ያስከተለውን የአመራር ስህተት ላለመድገም ያሳዩትን ብልህነት ከጠ/ሚ ዐቢይ ጒዞ ጋር ማመሳሰል ይቻላል። ለምሳሌ፣ ምንሊክ ኦሮሞ መሪዎችን አጋር ማድረጋቸው ድንበራቸውን ለማስፋትና የአድዋ ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ አስችሏል፤ ተወዳጅነትና ረዥም ንግሥ አቀዳጅቷቸዋል። ዐቢይም በኢሕአዴግ ውስጥ የመለስን አካሄድ ሲያጠኑ መቆየታቸው፣ የመለስን ስህተት ላለመድገም ራሳቸውን ለህዝብ ያቀረቡበትን አካሄድ መመልከት አስረጅ ነው። ቴዎድሮስ እና መለስ ተቀናቃኝ አለመታገሳቸው፣ ከድርድር እና ከመቀባበል ይልቅ ኃይል ለመጠቀም መቻኮላቸው ብዙ ጠላቶችን አፍርቶላቸው ነበር፤ ያ አካሄድ ፍጻሜአቸውን አፋጥኖ፣ በመጨረሻዋ ሰዓት እንደ ኃ/ሥላሴና መንግሥቱ ወዳጅ አልባ አድርጎአቸዋል!

የዐቢይ “እርካብና መንበር” የተጣጣፈ እንጂ ወጥነት ያለው ፕሮግራም አይደለም። መጽሐፉ ስለ ልማት ወይም ስለ ሥልጣን-ኃይል-ታሪክ አሠላለፍ ሲያወሳ፣ ግለሰቡ በወቅቱ የደረሱበትን ማስታወቁ ስለሆነ፤ ሊሞገትና ሊዳብር የሚገባው ሰነድ ነው (ለምሳሌ፣ ኃ/ሥላሴ “ብርሃንና ሰላም”ን ማቋቋማቸው ለጋዜጠኝነት መዳበር ከሌሎች አፍሪካ አገሮች የቀደመ ስለመሆኑ አልተጠቀሰም፣ ገጽ 114-116)። ያም ሆኖ መጽሐፉ የዶ/ር ዐቢይን ማንነትና አካሄድ ለመጠቆም በቂ፣ ጠቃሚና አሳማኝ መረጃ ይዟል። "የኅብረተሰብን ተሳትፎ ማረጋገጥ መቻል ወሳኝ ነው" (ገጽ 15)፤ "ሌሎችን በሃሳብ አሸንፎ ወደራስ አስተሳሰብ ማምጣት ግን የተቃዋሚ ወገኖችን ክንፍ የመነቃቀል ያህል ዋጋ ሊሰጠው ይችላል" (ገጽ 37)፤ "ኮቴን ሳያሰሙ ከጀርባ ቀብ ማድረግና ህልሙን ባንድ ጀንበር ማምከን ... ለዘብተኛ የኃይል አጠቃቀም ዘዴ ሠላም ሳይበጠበጥ ህዝብም ሳያጒረመርም የተደላደለ የሥልጣን ባለቤት ለመሆን ያግዛል" (ገጽ 38)፤ ወዘተ። በተጨማሪ፣ ዶ/ር ዐቢይ ለስነ ጽሑፍ ያላቸውን ፍቅር። ቃል በማሳካት ተጽእኖ የመፍጠር ችሎታቸውን ላፍታ እንመልከት፦

“አስከፊውና አሳዛኙ እውነታ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ታሪክ ተደላድሎ ማረፊያ አፀዳችን ከመሆን ይልቅ የሾህ መንገድነቱ የሚልቅ ይመስላል። ለራሷ ለውዲቷ ሀገራችንም ቢሆን ታሪክ ጌጧ ብቻ ሳይሆን ሸክሟም ጭምር ነው። ጒያዋ ቀዝቅዞ፣ ብርሃኗ ደብዝዞ እንደ ደጋን ጎብጣ ከምናገኛት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጒስቊል ገላ ላይ የምናነበው የቅኔ አሻራ ይኸንኑ መራራ ዕውነት ይመሰክራል። ሀገሪቱ አሁን የምትገኝበት ድንቊርናና ችጋር፣ ሠላም ማጣትና ኋላቀርነት ምክን ያቶች ሁሉ የሚቀዱት ከእርሱ ‘ታሪክ’ ከሚባለው ጥልቅ የትላንት ባህር ውስጥ እንጂ ከሌላ ከየትም ሊሆን አይችልም። ... ከዚያው ነው። በረከታችን ከመሆን ይልቅ መርገምት ሆኖ ከተጣባብን ከእድሜ ጠገቡ የመከራችን ኲሬ፣ በአንድ ቃልም ከታሪካችን ተብሎ ይጠቀለላል። (ገጽ 17-18) 

“ዛሬ ያሏት ዛሬ ከመምሸት ወዲህ የተገኘች ሌላ ቀን ከመሆኗ ባሻገር በሁሉ ነገሯ ቊርጥ ትላንትን መሰለች፤ ትናንትናን ሆነች” (ገጽ 54፣አንቀጽ 1)። ከዚሁ ጋር ለመማር ያላቸውን ጒጒት፣ በመሪነት ላይ ያሳለፉትን ጒዞ (ገጽ 79-81)፤ ማን ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው (በተለይ ኦባማ፣ ከዚያ ማንዴላ፣ ጋንዲ) ማየት ይቻላል።

ዐቢይን ስንሞግታቸው

ሰፋ ያለ የእውቀት አድማስ በስሱ ማሠሣቸው (ከኻያም ኒቸ፣ ከሂትለር ኦባማ፣ ከሼክስፒር ማኪያቬሊ፣ ወዘተ) ዐቢይን ወደ ልሙጥ ድምዳሜ የወሰዳቸው ይመስላል። “ልሙጥ ድምዳሜ” ሀ/ በአንደኛው ዘመን የተፈጸመ በሌላ ዘመን፣ በሌላ ሥፍራና ሁኔታ ሲፈተሽ እውነትነቱ ይምታታል ለ/ መረጃዎችን ከተለያዩ ርእሶች ሲቃርም ምንጮቹን መለየት ያዳግታል ሐ/ ለዓላማው ማሳኪያ ሲመራርጥ መረጃው አውዱን ይስታል፤

የሚከተሉትን ዐቢይ ማስረጃዎች ከመጽሐፉ ጠቅሰን እንሞግት?

1/ [ገጽ 15፣16]። ዐቢይ ኃይልና ሥልጣንን፣ ከመኪና መሪ (ከነጂና) ከሞተር ጋር አመሳስለውታል፤ ነጂው እርሳቸው ናቸው። ካቢኔአቸውን ሰብስበው ሲያስተምሩ፣ አዲስ አበባን ማጽዳት (የማዘጋጃ ቤትን ሥራ)፣ ችግኝ መትከል፣ የምኒልክን ቤተመንግሥት ለጎብኚ ክፍት በማድረግ ገቢ ማሰባሰብ (የቱሪዝም ድርጅትን ሥራ)፣ የኢትዮጵያውያንን ሬሣ ለምድራቸው ማብቃት። ለኤርትራው መሪ ኢሳይያስ እና ኤሚሬቶች ሞሐመድ ቢን ዘይድ ሾፌርነታቸው ይህንኑ የነጂና የሞተርን አስተሳሰብ ያስረዳል።

2/ [ገጽ 17-22]። ዓለምን በመቆጣጠር ረገድ፣ ታላቁ እስክንድርን ከሂትለር ጋር ማስተካከል በፖሊሲ አወጣጥና አተረጓጎም ላይ ትልቅ ስህተት ይፈጥራል። የእስክንድር (ሄለናይዜሽን) ሲሆን የሂትለር (ናትዚፊኬሽን) ነው። ሄለናይዜሽን ብዘሃነትን ይታገሳል፣ ባዕዱን አስተናግዶ በሂደት ውስጥ ወደ ራሱ መንገድ ያገባል። ናትዚፊኬሽን አይታገስም፣ አንድ ወጥነትን በሁሉ መስክ በድንጋጌ ያስፈጽማል፣ ያልተስማማን ያስወግዳል።

3/ [ገጽ 53]። “ይቅርታን በማያውቀው የፖለቲካ ባህላችን” የሚለው ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ጋር በቅሎ በኢሕአዴግ ዘመን ያበበና “የአገር ሽማግሌን” ክብር ያዋረደ የቅርብ ዘመን ባህል ነው። “ይቅር ለእግዚአብሔር” ከቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ አፄ ኃ/ሥላሴ ድረስ የቆየ ባህል መሆኑ ሊታወሰን ይገባል። ለዚህ ምክንያቱ በአመዛኙ እግዚአብሔርን የመፍራት ምሥጢር ነው! በዐቢይ ዘመን መልሶ እያቆጠቆጠ ይሆን?

4/ [ገጽ 162]። ዮሐንስ፣ እንግሊዞችን ከድርብሾች እጅ ለማስጣል ሱዳን ድረስ ሄደው የተዋጉት “ብልጠት የጎደለው ውለታ” ነው ከማለታችን በፊት እነዚህን ጥያቄዎች ግድ ማንሳት ይኖርብናል፣ ሀ/ እንግሊዞች ለዮሐንስ ለምን አስፈለጉ? ለ/ እሰው አገር ሄጄ ምን አዋጋኝ? ለማለት ዮሐንስ አማራጭ ነበራቸው? ሐ/ ይኸስ ዓይነቱ የጂኦፖለቲክ አሠላለፍ በዮሐንስ ብቻ ወይስ በሌሎችም ታይቷል? ከመጨረሻው ብንጀምር፣ ምንሊክ ያለ ጣልያን፣ ኢያሱ ያለ ጀርመን፣ ኃ/ሥላሴ ያለ እንግሊዝ/አሜሪካ፣ መንግሥቱ ያለ ሶቭየት ህብረት፣ መለስ ያለ እንግሊዝ/አሜሪካ፣ ዐቢይ ያለ አሜሪካ የትም ባልደረሱ! መለስ ወደ ሶማልያና ደቡብ ሱዳን የተመላለሱት በቀዳሚነት ለኢትዮጵያ ጥቅም ከመሰለን ተሳስተናል፤ “ብልጠቱ” የሌሎችን ዓላማ በማሳካት ውስጥ የኛንም እናሳካለን ነው! ይኸ አሠራር አንዳንዴ ጒዳት ያስከትላል፤ ዮሐንስ መተማ ላይ ተገደሉ። ኃ/ሥላሴና መለስን አሜሪካኖች ከዷቸው። መንግሥቱን ሶቪየቶች።

5/ [ገጽ 35]። ህዝበ እስራኤል በጎ ተደርጎለት ውለታ ቢስነቱ፣ ከመና ይልቅ የግብጽን ሽንኩርት መመኘቱ ተጠቅሷል። በያኔው የሙሴ አመራር የዛሬዪቱን ኢትዮጵያን መቃኘት ከሚመልሰው ይልቅ የሚፈጥረው ጥያቄ ይበዛል። ህዝብ በመሪ ላይ ማጒረምረም የኖረና የሚቀጥል ነው። ዐቢይ የጠቀሷቸው መሪዎች (ማንዴላ፣ ጋንዲ፣ ሙሴ፣ ኦባማ፣ ጄኔራል ፓርክ) ህዝቦቻቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው። ሙሴ፣ ጋንዲና ፓርክ አሻግረው፣ ባሻገሩት ህዝብ ሰበብ ሳይሻገሩ ቀርተዋል።

ህዝበ እስራኤል፣ በግብጽ ባሮች ሆነው እርግጠኛ የሆነ ኑሮ ይኖሩ ነበር፤ ቀይ ሽንኲርት፣ ዱባ፣ ሥጋ፣ ወዘተ፣ ዕለት ዕለት ይሰጣቸው ነበር (ዘዳ 16፡3፤ ዘኁ 11፡5)። የሚታዩ የሚዳሰሱ ውርስ የግብጽ አማልክት ነበሯቸው። አሁን ሳያዩ እንዲታመኑ ነው ሙሴ እያደረገ ያለው። መና ለዛሬ እንጂ ለነገ ይኑር አይኑር አይታወቅም፤ በእምነት የሚጠበቅ ነው፤ ዛሬ ለቅሞ ለነገ ማሳደር አይቻል! በግብጽ ምድር ምሪታቸው የባርነት ነበር፤ በራስ አነሳሽነት ማሰብና ማከናወን አልነበረም፤ ከማለዳ እስከ ምሽት ጡብ መሥራት፣ ግርፋት በጀርባ ነበር። ከግብጽ ከወጡበት ሌሊት ጀምሮ ሙሴ እየመራቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ተጓዙ፤ የማይታየው አምላክ በልቡናቸው ሠውረው የሚታዘዙትን ህግ በሲና ምድረበዳ በሙሴ እጅ ሰጣቸው። ሙሴ ሲና ተራራ ላይ ወጥቶ ሲዘገይባቸው፣ ወደ አሮን ተሰብስበው። "ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት።" (ዘዳግም 32፡1)

የኢትዮጵያ ህዝብ ከደረሰበት ጒስቊልና የተነሳ መሪዎቹን እንዳያምን ተደርጓል። መሪዎች እግዚአብሔርን የማይፈሩ ጨካኞች ሆነው “የህጋዊነትን ጭንብል ለብሰው ውስጥ ውስጡን ግን ለማመን እንኳን አስቸጋሪ የሆኑ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ” (ገጽ 42፣ አንቀጽ 3)። ህዝብ የሚታይ የሚጨበጥ መልስ አሁኑኑ ቢጠብቅ ለምን ይደንቃል? በሌላ አነጋገር፣ ደሞዝ ጭማሪ ያነሱ ዜጎች ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ባልተገባ! ዐይነ ስውሩ እንኳ፣ ነገ ዐይንህ ይበራል ቢሉት ዛሬን እንዴት አድሬ ብሏል!!

6/ ዐቢይ (እንደ መንግሥቱ እና መለስ)፣ ይልቅ ደግሞ እንደ ኦባማ የንግግር ተሰጥዖ አላቸው፤ ዐቢይ ጅማሬ ላይ ተስፋን በማጫር፣ ህዝብ በማነሳሳትና አመኔታን በመፍጠር ምናልባት ከመንግሥቱና ከመለስ ሳያይሉ አይቀሩም። ሦስቱም መሪዎች በኑሮውና በአስተሳሰቡ የደቀቀን ህዝብ እንደ ተረከቡ አንዘንጋ! መንግሥቱ ከኃ/ሥላሴ ሲረከቡ በህዝብ መሓል መተማመን ጠንካራ ነበር። ከመሪ እጦት ጥቂቶች አይለው እንጂ ዛሬም ቢሆን በሠፊው ህዝብ መሓል እምነት አልተመናመነም። ወቅቱ የሚጠብቀው፣ ለህዝቡ የዕለት ጒርስ ጥያቄ፣ ለወጣቱ ሥራ አጥነት ቅድሚያና ተጨባጭ ምላሽ የሚሰጥ አመራር ነው። ንግግር ማወቅ ደግሞ የራሱን አበሳ ይዞ ብቅ ይላል፤ የቃል ብዛት ጒድለትንም ያጎላልና! ኦባማ ለታሪካቸው ያልበጁ፣ በጅምር ያፈረሷቸውን የቃላት ሃውልቶች ትተውልን ዘመናቸውን አገባድደዋል! ሰጥቶ እንደ መንሳት ልብ የሚሰብር፣ መታመንን የሚያወድም የለም።

7/ [ገጽ 164]። የማይሞቱ ለሚመስላቸው፣ ወይም “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” ለሚሉ ሁሉ፣ “እርካብና መንበር” በ “ስንብት” እንዲህ ይላቸዋል፣

የታሪክ ድርሳንህ ተገልጦ ሲነበብ | አልፈህም የማያልፍ | ልብ ላይ ያተምከው ከታጣበት ቀለም

‘ኖርኩኝ’ ብትል እንኳን | ‘አዎ ኖሯል’ የሚል አንድም ፍጡር የለም

ደግሞ በዚያኛው ገጽ፣ | ‘እሱ ማነው?’ ሲባል... ‘እሱ እኮ...’ ተብሎ...

በበጎ ‘ሚነሳ ... በኲራት ‘ሚወሳ | ካለህ ቅዱስ ተግባር ለሌላው ‘ሚጠቅም

ሞት ስጋህን እንጂ... | ያንተን ህያውነት በፍጹም አይነጥቅም። ~ ዐቢይ አሕመድ

መሪዎቻችን (የአፍሪካን ጨምሮ) ስለ ሞት ማሰብ አይወዱም፤ የሚያልሙት ለዘላለም መግዛትን ነው። ዐቢይ ከጅማሬው ፍጻሜውን እንዳሰቡበት እናያለን። የተቃጡባቸውን ግድያዎች ስናስብ ያልተጠበቁ ጥያቄዎች ይታሰቡናል። ለምሳሌ፣ ከዐቢይ በፊት የነበረው አመራር ህዝቡን ምን ያህል እንዳንገፈገፈው ስናውቅ፣ ዐቢይ በሌሉበት የሚገጥመንን መገመት ከቶ ፍርሓት ይፈጥርብናል። በአንጻሩ፣ በእጃችን ያለውን ዕድል እንደከዚህቀደም እንዳናባክን ምን እናድርግ እንድንል ያስገድደናል። ዐቢይ ስለ ፍጻሜ ከጅምሩ አስበውበታልና ቶሎ ቶሎ ግዳጃቸውን ለመወጣት እየተሯሯጡ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ገጽታቸውም ይመሰክራል። ህዝቦች ሁሌ የተሻለ ይመጣል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ፤ ከኃ/ሥላሴ፣ ከመንግሥቱ፣ ከመለስ በኋላ የተስፋ ጭላንጭል ታይቶ ነበር። እንደታሰበው አልሆነም። በሌላ አነጋገር፣ ዛሬን መጠቀም አማራጭ የለውም። “እርካብና መንበር”ን ያነበበ፣ በእነዚህ 17 የነውጥ ወራት ዐቢይን ያደመጠ፣ ዐቢይ አገር ይዘርፋሉ፣ አገር ይከፋፍላሉ፣ ቅን አይደሉም ወይም ፍጹም ናቸው ብሎ ማሰብ ከእብደት አይሻልም።

8/ [ገጽ 11፣ ወዘተ]። “ያን መሰል ጥንታዊ የነጻነትና የሥልጣኔ ታሪክ የተላበሰች አገር” የሚሉ ሐረጎች ተደጋግመው ይነበባሉ። እርግጥ ነው ጥንታዊ ነን፤ ጥንታዊነታችን ግን አንዳንዴ እንደ ሱስ መጨበጫ ያጣ፣ ወደ ፊት እንዳንራመድ እንቅፋት ሆኖብናል። “በነጻነት” “በሰላም” “በፍቅር” “በአንድነት” “በቅድስት አገር” እንኖር ነበር ማለት በአብዛኛው ታሪካችንን ካለማወቅ፣ በቊንጽል ከማወቅ፣ ዛሬን ለመኮነን፣ የራስን ለማግነን፣ ከገባንበት ምስቅልቅል ቢያላቅቀን ከመመኘት የመነጨ ነው! ይልቅ የሚያዋጣን በወቅቱና በሚጠብቀን ጒዞ ላይ ማተኮራችን ነው። ከ [አፈ] ታሪክ ፖለቲካ ይልቅ በኢኮኖሚ ፍትህ ላይ ማተኮራችን ነው። የክርክር ደጅ ሳይዘጋ፣ የራበው ሆድ ጦም ያድራል፤

abiygursha9/ [ገጽ 149]። “ልማታዊ መንግሥት” ቅድመ ሃሳቡ ምሥጢር አይደለም። በሥልጣን ላይ መቆያ ብልኃት ነው። ከአንድ ጠንካራና ሦስት ተለጣፊ ፓርቲዎች ቅንጅት ውጭ ህዝብ የመረጠው ሌላ ፓርቲ እንዳይኖር ማገጃ ነው። የግል ይዞታዎች መኖር፣ ህዝቡ በፖለቲካና በኢኮኖሚ የሚኖረውን ሚናና የሚያነሳውን ጥያቄ ማገጃ ነው። ባጭሩ፣ “መንግሥት ያውቅልሃል” ነው! ይህም ለዝርፊያ ሰበብ ሆኖ አይተናል። ለበደል። ለጥቂቶች ማየል፣ ለብዙሃኑ መበደል። ፌዴራሊዝም/ራስ አገዝ ልማት እጅግ ጠቃሚ ነው። መንግሥት ከሚያለማው ጋር ተሰባጥሮ የግል ሴክተር መስፋፋት ደግሞ አማራጭ የለውም። የልማት ግብና ድልድይ ህዝቡ ነው! መንግሥት ዋና ድርሻው ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ዜጋን ማሳተፍና መብቶቹን ማስከበር፣ የአገር መከላከያን ማጠናከርና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ማገድ፣ ወዘተ ነው።

10/ ዶ/ር ዐቢይን ጊዜ ልንሰጣቸው ይገባል! ተመልካች መሆን ወይም የወቀሳ ጤዛ ማውረድ ሳይሆን ራእዩ እንዲያብብ ማገዝ ያዘልቀናል! በግለሰብ ደረጃ የአመራራቸውን ስልት ማጥናት፣ በተግባር ከሚታየው ጋር ማመሳከር በጭፍን ከመውቀስ ያድናል! ሁለት ወዶ አይሆንም። ሲዘርፉ፣ በዘር ሲከፋፍሉ የኖሩትን፤ ኢትዮጵያን “የመቶ ዓመት” ወሬ ያስመሰሉትን አይተናል። የመናገር ነጻነታችንን በገፈፉን እጅ ተሠቃይተናል። ለአገር እንቆረቆራለን የሚሉ ሁሉ እንካ ስላንትያና መንደርተኝነትን፣ ጭፍን ጥላቻን አቁመው “እርካብና መንበር”ን ማንበብ፣ በመጽሐፉ ይዘት ላይ መወያየት ይኖርባቸዋል። ከላይ እንዳልነው ዐብይን ፍጹም መሪ እንዲሆኑ አንጠብቅ! “እዚህና እዚህ ላይ እንዲህና እንዲህ ብለው አልነበረ?” እያልን ወቀሳ እናሰማ፤ ወቀሳው ግን የተጀመረውን ለማውደም አይሁን!

ምትኩ አዲሱ

ነሐሴ 7/2011 ዓ.ም.

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | ኑዛዜው ጥያቄም ነው