ዐ ብ ይ ን  በ ባ ራ ክ፣  በ ማ ን ዴ ላ  መ ተ ር ጎ ም  ይ ቍ ም !

ከምናውቀው ወደማናውቀው መገሥገሥ፣ የእውቀት በር መክፈቻ ስልቱ ነው። የምናውቀውን ከቅርብ ካላወቅነው ግን እውቀት ይዛባል። እውቀት ሲዛባ ዓላማ ይዘገያል ወይም መንገድ ላይ ይቀራል። ለምሳሌ፣ ማንዴላና ባራክ ዖባማን እንጥቀስ፦ ብርቱካን “ማንዴላ” ተብላለች። አንዳርጋቸውም። ርዕዮት ዓለሙም። ፕሮፌሰር አስራትም። ፕሮፌሰር መስፍንም። ዶ/ር ብርሃኑም። እስክንድርም። በቀለ ገርባም፤ ወዘተ። መለስ ዜናዊ በማንዴላና በታላቁ እስክንድር ተመስለዋል። ዶ/ር ዐብይ፣ ማንዴላ፣ ባራክ ተብለዋል። ሙሴም ተብለዋል። ነገ ሼክስፒር ቢባሉ አይድነቀን። ስያሜው፣ ስለ ግለሰቦቹ፣ ስለ እኛና ስለ መሪዎቻችን ምን ይነግረናል? ለመጣው ሁሉ፣ አንስቶ መለጠፍ የኛን ችኵልነትና አጥርቶ አለማሰብ ያጎላ እንደሆነስ? አድራጎታችን በአስተሳሰባችን ላይ ምን ውጤት እንዳስከተለ በቅጡ ያሰብንበት አይመስልም።

ማንዴላና ባራክ ጥቍርና ታዋቂ ቢሆኑም ኢትዮጵያ ለገባችበት ትግል ባዕድ ናቸው። ባዕዳን ናቸውና ሁሉም የመሰለውን ትርጕም እንዲጭንባቸው ይገደዳል። አስተሳሰብ ሲዛባ፣ ኃላፊነትን አለመውሰድና ማላከክ ይከተላል። ታሪካችንን አጥርተን ስላላወቅን፣ ወቅቱን ከታሪካችን ጋር ስላላዛመድን፣ ውዥንብር ብቻ አተረፍን። የአገራችን ህዝብ በወሬ ከሚሰማው ውጭ የትኞቹንም ግለሰቦች ጠንቅቆ እንደማያውቃቸው አንርሳ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከተሜው ብቻ እንዳይደለ አንዘንጋ።

ከውጭ መዋስ ጨርሶ የለብንም ማለት አይደለም። በሰኔ 16ቱ ህዝባዊ ማዕበል፣ ዐብይ የማንዴላን፣ ህዝቡ የዐብይን ምስል ቲሸርት ለብሰው መታየታቸው፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ፣ ዐብይ በወቅቱ የቆሙለትን ዓላማ ቍልጭ በማድረጉ የሰልፉን አስተባባሪዎች ጕብዝና አስመስክሯል።

* * * *

እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ብቅ ያሉትን ዶ/ር ዐብይን ከባራክ ጋር ብዙዎች አነጻጽረዋቸዋል። በባራክ ዐብይን መተርጎም ግን ኋላ ችግር ያመጣል። በቁመናቸውና በንግግራቸው ብርታት ህዝብ ማነሳሳታቸውና ተስፋ በማጫር ማረጋጋታቸው፣ ካዘነው ጋር ማዘናቸው፣ ብሩህ አእምሮ መለገሳቸው ሁለቱን አመሳስሏቸዋል። ኢትዮጵያዊ አእምሮ ከኃይማኖት ጋር የተቆራኘ ነውና ሲያወድስ ሰማይ አይመልሰውም፤ ሲያዋርድም ሲኦል አይበቃውም። የተስፋ ከፍታ ሲረዝም መንኮታኮቱም እንደሚብስ አንርሳ! በሌላ አነጋገር፣ ይኸ የፈጠርነው ምስል እንዳያስተን፣ ባራክን ጠንቅቆ ማወቅ ለዐብይ አመራር ጠቀሜታ አለው።

የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ከአስር ዓመት በፊት በአሜሪካ የተከሰተውን በከፊል ይመስላል። በሁለቱም የሽግግር ጊዜ ነበር። ከጆርጅ ቡሽ ወደ ባራክ፤ ከመለስ/ኃይለማርያም ወደ ዐብይ አሕመድ። የኤኮኖሚው ዘርፍ አድሎአዊነት፣ ግልጽነት ማጣትና መናጋት። ያለበቂ መረጃ በሽብርተኛነት መታሠር፣ ማቅቆ መለቀቅ። ሰላም አይሉት ጦርነት። ተቃቅሮ መኖር፣ ከሚያስኮበልል ከተዘባረቀ ተስፋ ወደ ብሩህ ተስፋ ሽግግር፣ ወዘተ።

ከአፍሪካዊ አባትና ተጽእኖ ካሳደረችባቸው አውሮጳዊት እናት የተወለዱት ባራክ፣ እ.አ. በ2008 ህዝብ መርጧቸው ፕሬዚደንት ሆኑ። የተባበረች አንዲት አሜሪካ እንጂ፣ ጥቁርና ነጭ፤ ሰማያዊና ቀይ ክልል አሜሪካ ከእንግዲህ አይኖርም አሉ። እስረኛ ይፈታል፣ ጓንታናሞ ይዘጋል። የአሜሪካ ጦር ከኢራቅ ወደ አገሩ ይመለሳል። የአስተማሪና የነርስ፣ የአነስተኛ ነጋዴና የመንግሥት ሠራተኛ ኑሮ ይሻሻላል አሉ። መልከ ቀናና ምሑሩ ፕሮፌሰር፣ በንግግራቸው ማማር በምድሪቱ የተስፋ ችቦ አቀጣጠሉ። ከታሪክ የሚበጃቸውን ጠቃቀሱ፤ አብርሃም ሊንከንን ጠቀሱ፤ ማርቲን ኪንግን፤ ማንዴላን። የህይወት ታሪካቸውን በመጽሐፍ ጻፉ፤ በዩቱብ ለጠፉ። ከ35 ዓመት በፊት ፕሬዚደንት ለመሆን ምኞት እንደ ነበራቸው ገለጹ። መች በአሜሪካ ብቻ፤ ዓለምን አስተሳስራለሁ አሉ። ባመቱ፣ ካይሮ ግብጽ ላይ እስላሙን ዓለም በዲሞክራሲ ተስፋ አስቋመጡ። ጋና ወርደው ለአፍሪካ ተስፋና ነጻነት አበሰሩ። የተቀባ! መሲሕ! ተባሉ። ባራክ የኛ!አለ አፍሪካ። ባራክ ተቀብለው፣ ህዝብ መዝረፍ፣ ማሠቃየት አበቃ አሉ!

ስዊድኖች በቡሽ ትርጕም የለሽና አውዳሚ ጦርነት ቅሬታ ነበራቸው። የሰላም ሰው ባራክ ደረሰልን! አሉ፤ ሥልጣን በያዙ በ11 ቀን የሰላም ጉቦ-ኖቤል ሸለሟቸው። አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ዶላር መረቁላቸው። ጦርነት ግን ተባባሰ፤ ሜዳልያው በሊብያ፣ በየመን፣ በአፍጋኒስታን፣ በሶርያ ሕጻናትና ድኲማን ደም ጎርፍ ተጨማለቀ!

በስምንት ዓመት የፕሬዚደንትነት ዘመናቸው ባራክ ሥፍር ቍጥር የሌለው ማራኪ ንግግሮችን አሰምተዋል። የአባታቸውን አገር ኬንያን ቅኝ በገዙ በእንግሊዞች ንግሥት ፊት። አፄ ኃይለሥላሴ በዋነኛነት ባቋቋሙት በአፍሪካ ማህበር በማንዴላ አዳራሽ። ኢትዮጵያ መሥራች አባል አገር በሆነችበት በተባበሩት መንግሥታት። አሜሪካ ባቶሚክ ቦምብ ባወደመቻቸው በጃፓኖች ንጉሥ ፊት። አሜሪካንን ድል በነሳች በቪዬትናም ሆቺ ሚን አዳራሽ። ስንቱ ይቆጠር?

ለህዝብ ከገቡት ቃል ምን ያህሉን ፈጸሙ? ይህንን ለሌላ ጊዜ እናቆይና አንድ ነገር ግልጽ እናድርግ፦ ባራክ፣ ለድርድር አይቀርቡም ያሏቸውን ዋነኛ ቃሎች አጠፉ። ሶርያን ለስደትና ለውድመት ዳረጉ። የቆሰቆሱት ዲሞክራሲ በምድረ ዐረብ ሲቀጣጠል፣ ሲዝቱ ሲያመነቱ ቆይተው፣ ህዝብ ከበደሉ መሪዎች ጋር ወግነው ተገኙ። የማህበረሰብ ምሰሶ ቤተሰብን የሚያናጋ የተመሳሳይ ጾታን ጋብቻ በህግ አጸደቁ፣ ህጉን ተግባራዊ የማያደርጉ አገሮች እርዳታ አያገኙም አሉ። አሳርፈዋለሁ ያሉትን ስደተኛ ከቡሽ በባሰ ካገር አባረሩ። የሰበኩትን “መቻቻል” ያልተቀበለ፣ በአክራሪነት ተፈረጀ። በጥቍርና በነጭ፣ በሰማያዊና በቀይ ክልል አሜሪካ የነበረው ተቃርኖ ተባብሶ፣ ሃብታሙ በልጽጎ፣ አናሳው አንሶ የሥልጣን ዘመናቸው ተገባደደ። የትረምፕ ብቅ ማለት ከዚህ አንጻር ይታይ። (ዐብይና ትረምፕን ያመሳሰለ ስለሌለ እዚህ አናነሳም።) እንደ ፖለቲከኛ፣ ባራክ የገቡት ቃል ብዛቱ በአንድ ሰው እድሜ የማይተገበር ሆነ። ፖለቲካ እንደ ከበሮ፣ ሲያዩት ያምራል፣ ሲይዙት ያደናግራል። ከሁለት፣ ከአምስት ዓመት በኋላ ስንት ተስፋ ሰጥተው የበነኑ ጉዳዮች ይጠብቁን ይሆን?

ጓንታናሞ ዛሬም አልተዘጋ። የአሜሪካ ጦር ከኢራቅ ወጥቶ አፍጋኒስታን ገባ። እግረኛ ጦር በሰው አልባ “ድሮን” ተተካ፤ ሠርገኛን ከጦረኛ የማይለይ የፈንጅ ጤዛ ከሰማይ ዘነበ። “ድሮን” ድሩን አርባ ምንጭ ድረስ ዘረጋጋ። አፍሪካ፣ የአሜሪካና የሽብርተኞች መፋለሚያ ሜዳ፣ ሥልጣን ላለመልቀቅ የህዝብ ድምጽ በሚሠርቁ፣ህገ መንግሥት በሚደልዙ፣ ዜጋን በቶርች በጥይት በሚቆሉ፣ ከቻይና ጋር የዝርፊያ ውል በሚዋዋሉ መሪዎች ተሞላች። አሜሪካ ከ27 ዓመት በፊት ባገራችን ጉዳይ ጣልቃ ገብታ ካፈጻጸመችው ውል ዛሬ የተለየ ምን አዲስ ነገር ታመጣልናለች? ኢትዮጵያውያንስ ከዳር ቆመው ተስፋ ከማድረግ ውጭ በአገራቸው ህይወት ለመሳተፍ ምን አማራጭ አላቸው?

* * * *

ሰው በሚያሞግሱት አፍ ይፈተናልና፤ ከሦስት ዓመት በፊት ባራክ አዲስ አበባን ሲጎበኙ፣ ቀስተ ደመና መታየቱ የሰላም ሰው ለመሆናቸው ከሰማይ ምልክት ነው ተባለ! ባራክ እጅግ ደስ ተሰኙ። አጸፋውን፣ አገራችን ህግና ዲሞክራሲ የሚገዛት አገር ነች ብለው መሰከሩ! (መሪዎቻችን ህዝቡን በድለናል ያሉትን አልሰሙ!) የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪአቸው ከአራት ቀን አስቀድሞ ስለ ዲሞክራሲው ተጠይቃ ባደባባይ ስታፌዝ ስታስካካ ታይታለች። ባራክ ግን ዛሬም እንኳ ሚሊዮን ባራክዎችን ለማፍራት ዝተዋል!

ሰው ለራሱ በሚሰጠው ግምት ማንነቱ ገሃድ ይወጣል። መሪ በአማካሪዎቹ ብዛትና ዓይነት ይመዘናል፤ ሙገሳ ይጠልፈዋል። ራሱን ሲያገን ይወድቃል፤ ትሑት ሲሆን ይከብራል። ዐብይ ከክልል ክልል የህዝብ ቀልብና ምርቃት ተከትሏቸዋል። የወደፊቱን እግዜር ያውቃል። ለምን በኢትዮጵያ ክልል ብቻ፣ ከኤርትራም ጋር ብለዋል። ለምን ከኤርትራ ብቻ በአፍሪቃም ቀንድ እንጂ። ለምን ቀንድ ብቻ፣ አፍሪቃንም እንጂ። ከብት አርቢው የኡጋንዳ ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ (32 ዓመት እየገዙ ያሉ፣ ራሳቸውን “ሳባጋቤ = የነገሥታት ንጉሥ” ያሰኙ)፣ ዐብይ ሦስት ወር ሳይሞላቸው “የአፍሪካ እጅግ ታላቅ ዕንቍ ጀግና ሜዳልያ” ካምፓላ ድረስ ጋብዘው ሸልመዋቸዋል። ክብሩ ከዐብይ ይልቅ ለሙሴቬኒ ነው እንበል? ከዚህ ቀደም ይህን ሽልማት የተቀበሉ፣ 40 ዓመት ኢኳቶሪያል ጊኒን እየገዙ ያሉ ፕሬዚደንት ቲዮዶሮ ምባሶጎ ብቻ ናቸው። ምባሶጎ፣ “አምላክ እንጂ ሰው አይደለሁም፣ በሰውና በፍጥረት ሁሉ ላይ ሥልጣን አለኝ፣ ብገድል ማንም አይጠይቀኝ፣ ገሃነም አልገባ” ብለው ስለ ራሳቸው በብሔራዊ ራዲዮ ያስነገሩት ናቸው።

ባራክ እጅግ ተወደሱ፤ አወዳሹን ማስቀየም እስኪያቅታቸው ሰማይ ጥግ ተሞገሱ። ሰው ብቻ እንደሆኑ አንርሳ። ለህዝብ የገቧቸው ብዙ ቃሎች ውኃ እንደሌላቸው ደመናዎች ነፈሱ።

* * * *

ዐብይ፣ ባራክ አይደሉም፣ ባራክ መሆን አይጠበቅባቸውም። ዐብይ፣ ዐብይ መሆናቸው ይበቃቸዋል። የዐብይ ቅንነትና አገር ወዳድነት ግን ቀጣይነት እንዲያገኝ፣ በህዝባዊ ሆታና ግለት ብቻ ሳይሆን፣ አገራዊ አደራ በሚጠብቁ ድርጅቶች መታቀፍ አለበት። ቅንና ብቁ ዜጎችን ካላሳተፈ፣ የምንሰማው “ፍቅር” “ሰላም” ፍትህን ካላማከለ፣ አገራችን ከገባችበት የትውልድ አዙሪት አትላቀቅም። ዜጋ ከዳር ቆሞ የመንግሥት እጅ መጠባበቁ መቆም አለበት! “ተደምረን” ያሉት ከደጅ ጠኝነት ወደ ተሳታፊነት ሊያሸጋግረን ይሆን? “ተደምረን” = ጥያቄ ማንሳት አይፈቀድም ማለት ይሆን? እስከ ዛሬ የቸገረው፣ አመራር በአንድና በጥቂቶች እጅ መሆኑ ነው! በትረ ሥልጣን የያዙ ሁሉ፣ ዜጋን እንደ ጕዲፈቻ እንደማያድግ ህጻን እንጂ ሥልጣን ለማጋራት አምነውት አያውቁም። የአገር መሪዎችና ህዝብ በአንድ እውነት ተማምነዋል፦ ሁሉን ዜጋ ሳያሳትፍ አገር መምራት ጭራሽ አቅቷል፤ ለሙስናና ለፍትህ መጓደል ለምሬት ምክንያት ሆኗል፤ ህዝብን በፖለቲካ፣ በዘር፣ በኃይማኖት መከፋፈል ተሞክሮ ከሽፏል።

ውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተመልሰው በአገራቸው ጕዳይ እንዲሳተፉ የተላለፈውን ጥሪ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ተደርጓል? ከምርጫ 97 በኋላ ያለበቂ ምክንያት የታገቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጋዊ የህዝብ ተራድኦ ድርጅቶች ከእስራት ይፈቱ ይሆን? የተሻለ ሆኖ ከተገኘ፣ መንግሥት ከፓርቲው ውጭ ባለሙያዎችን ማሳተፍና ምክራቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ ነው? በደርግም እንኳ ዘመን የፓርቲ አባል ሳይሆኑ፣ ባይነተኛ ችሎታቸው፣ ቁልፍ የኃላፊነት ሥፍራ ላይ የተሰየሙ እንደ ነበሩ አንዘንጋ።

ሁሉም በራሱ ስሌት እንዳይደራደር፣ የመደመር ዝርዝር አሳብ እና አፈጻጸም ሳይዘገይ ይገለጽ!

ምትኩ አዲሱ

ሰኔ 18/2010 ዓ.ም.

ያከበሩኝን አከብራለሁ ያንብቡ