ርዕሰ አንቀጽ

ያከበሩኝን አከብራለሁ

ጠ/ሚንስትር አብይ አህመድ ቀይ ሽብር በተፋፋመበትና ምሕረት በጠፋበት በ68 ተወለዱ፤ ወላጆቻቸው “አብዮት” ብለው ሰየሟቸው። ዛሬ “አብይ” ሆነው በሰላም ቃል ተስፋ በማጣት የላሸቀ መንፈሳችንን እያነሳሱ ይገኛሉ። ያዝልቅልን፣ ያዝልቅላቸው።

ሊቀ መንበር መንግሥቱ ንግግራቸውን በ “ይውደም!” እና በ “እናት አገር ወይም ሞት!” እርግማን ይደመድሙ ነበር። ወዲያው ደግሞ፣ ኢትዮጵያ በነጻነቷ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር! ይሉ ነበር። ድምጻቸው ቍጣን የተመላ ነበር። በአብዮት ጣር እንደ ተያዙ ያህል እጃቸውን እንደ ዛሬ ነብያት ያወራጩ ነበር። መንግሥቱ በ17 ዓመት ንግሣቸው የእግዚአብሔርን ስም በአደባባይ ያነሱት ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር፤ ሥልጣን ላይ ሲወጡ (“በህያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ”) እና ከሥልጣን ሊወርዱ አካባቢ (“ጸልዩ፣ ጸልዩ)። የመሪዎች ሥልጣን ላይ መውጣት እና ከሥልጣን የመውረድ ሁናቴ ብዙ የሚገልጠው ጉዳይ አለ። መለስ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” የምትል መቋጫ አሰምተውን አያውቁም። ንግግራቸው ባጭሩ “አመሰግናለሁ” ነበር። ለእንግሊዟ ጋዜጠኛ “ለእግዚአብሔር ነገር” ጊዜ የለኝም ብለው ነበር። የኃይለማርያም “አመሰግናለሁ” (አንዴ “እመኛለሁ”) ነበር፤ መስከረም 2005 ዓ.ም. የጠ/ሚንስትርነቱን ሹመት ሲቀበሉ “ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለታላቁ መሪያችን ይሁን!” ነበር። እኛም “ወንጌል አማኝ ነኝ” ማለታቸውን አስከትሎ “ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ” ጥያቄ ፈጥሮብን ነበር። ዘመናቸው ብዙ አሣር፣ ብዙ ሞት፣ ብዙ እንግልት የበዛበት ነበር። ከሥልጣን ድንገት የመውረዳቸውን ምሥጢር እግዜር ያውቃል ብለን እንለፈው።

አብይ “ኢትዮጵያ” የሚል ቃል ሰምተን የማናውቅ እስኪመስል ድረስ በአደባባይ ደጋገሙት። ተለይተን የኖርነውን አብሮ አደግ ድንገት መንገድ ላይ እንደ ማግኘት አስመሰሉት። ሰላም በተመላ ቃል “ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!” አሉን። አሜን ብለን ሳናበቃ፣ “ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!” አሉን። እነሆ፣ በ44 ዓመታችን የፈጣሪን ስም ከመሪ አንደበት በአደባባይ ሰማን! “አመሰግናለሁ!” ተመረቀልን።

በምድራችን ላይ ሰላም ሊወርድ ይሆን? ፍትህ ያጓደለ ሰላም እንዳይሆንና፣ በአገር መሪዎች ላይ የደበዘዘብንን ተስፋ ጨርሶ እንዳያጨልመው! ብዙዎች በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ አሉ። የሚፈልጓትን ብቻ መስማት የሚሹ አሉ። አንዳንዶችም ዛሬውን እንዲህና እንዲህ ካልተደረገ ብለዋል። ነገ ዐይንህ ይበራል ቢሉት፣ ዛሬን እንዴት አድሬ ያለው ታሪክ ነው።

የጠንቋይ፣ የተንባይ፣ የኃይማኖተኛ ምድር ጉድ ደግሞ አለ፤ አንድ ኃያል አንድ መሲሕ መጥቶ ሁሉን ከሥር መሠረት ይቀያየራል የሚል ነው። ለመሆኑ፣ ሕዝቡን በትህትናና በአክብሮት ያነጋገረ ስንት መሪ እናስታውሳለን? መንግሥቱ እንደ ኃያል (አብዮተኛ) ታስበው ነበር፤ እርሳቸውም አላስተባበሉም፤ ሁሉን ቻይነታቸውን አየነው። መለስም እንደዚያ ታሰቡ፤ ሞት አሸነፋቸው። የሚጠበቅብንን ጥረትና መስዋእትነት ዘንግተን፣ ከዳር ቆመን ሌላው እንዲጥርልንና መስዋእት እንዲከፍልልን እንሻለን። አብይ “ተደምረን” እንጂ አይሆንም እያሉን ነው። የምንደመረው በመከፋፈል ሊሆን አይችልም። ኃላፊነታችንን በመዘንጋት ወይም መብታችንን በመነፈግም ሊሆን አይችልም።

የሰላም መንገዱ ወጥመድ የበዛበት ነው። ሃያ ሰባት ዓመት ግራ በመጋባትና በሥጋት ተኑሮ ባንድ ጀንበር ያን ልማድ መጣል ቀላል አይሆንም። ልማድ ከኃጢአት ይብሳል ብላለች ይታይሽ። እህተ ማርያም (የማርያም እህት) በበኩሏ፣ አብይ 666 (አውሬው፣ ራእይ 13) ናቸው፤ ወላዲት አምላክ ነገረችኝ እያለችን ነው። ነቢዪት ብርቱካን፣ አብይ እንደሚሾሙ ተናግራ ነበር የሚል ዩቱብ ለጥፏል። “እኔም ብዬ ነበር” የሚሉ በርክተዋል። የፖለቲካ ነቢያትና የኃይማኖት ነቢያትን መለየትና ማመን ቸግሯል። አንድ ስውር ደባ ተደግሶልናል የሚሉ ሞልተዋል። ፈታኝ እና ማስተዋል የሚጠይቅ ዘመን ላይ ነን። ዶ/ር አብይ፣ ጎንደሬውን ቄስ “ጸሎትዎ አይለየኝ” ማለታቸው ጴንጤውን አስቆጥቷል። “አህመድ” ብሎ ... የሚሉ አሉ። የፌስቡክና የዩቱብ ተንታኞች፣ ድንቅ አብሳሪዎች፣ ደጃዝማቾችና ግራዝማቾች ከነደጋፊዎቻቸው የአየር መስመሩን “በሰበር ዜና” በማያልቅ ጉድና ግልብ ገበና ገላጭ ዜና አጨናንቀውታል። ኢትዮጵያዊ አእምሮ ከኃይማኖትና ከስውር ደባ ርቆ አይርቅም።

ሁሉን ጊዜ ይገልጠዋል። የአብይ አብዮት ከሰው ወይስ ከእግዚአብሔር? ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋል፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ማጥፋት አይቻልም። ተስፋ የምናደርገው ሰላም ለምልሞ እንድናይ ድርሻዬ ምንድነው እንበል።

አብይ፣ በአደባባይ የፈጣሪን ስም ጠርተዋል። እግዚአብሔር ደግሞ፣ "ያከበሩኝን አከብራለሁ፣ የናቍኝ ይናቃሉ" ብሏል (1ኛ ሳሙኤል 2:30)። "ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል" (ምሳሌ 29:25) እጃችንን አጣምረን የምንጠብቅበት ጊዜ አይደለም። እንጸልይ።

ይድረስ ለክርስቶስ ደቀመዝሙር

ይህም ደግሞ ያልፋል