ኑዛዜው ጥያቄ ነው

mwm tombstone

ፕሮፌሰር መስፍን “ኑዛዜ” በተሰኘ ግጥም ያልተጠበቀ ጥያቄ ትተውልን አልፈዋል። ኑዛዜአቸውን ይፋ ያደረጉት ሰኔ 2005 ዓ.ም. በ “የሚወለዱበት ... መሬት” ጽሑፋቸው ነው። “በራሴ በኩል አውጥቼ አውርጄ ውሳኔ ላይ ከደረስሁ ቆይቻለሁ፤ መቀበር አልፈልግም ... ለህልፈት ስበቃ የሬሳን ፈቃድ የሚፈጽም ከተገኘ … አቃጥሉልኝ ሬሣዬን ..” ብለዋል። ኑዛዜአቸው የምር ነው ወይስ የምሬት? ሬሣ ማቃጠል ምን ማለት ነው? ጠያቂውንና ጥያቄውን ቀጥለን እንመለከታለን።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዓይነተኛ ናቸው። ዓይነተኛ ምሑር አሳቦችን ያስተናግዳል፤ ያለፍርኃት ሳይታክት ይጠይቃል። በአገራችን የከፍተኛ ትምህርት፣ የፖለቲካና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ታሪክ ውስጥ የርሳቸውን ስም አለመጥቀስ ከእንግዲህ አይቻልም። በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያስተማሯቸው (የኢሕአፓ፣ የደርግ፣ የመኢሶን፣ የህወሓት፣ የሻብያ፣ የጀብሃ፣ የኦነግ፣ የቤተ ኃይማኖት መሪዎች) እና የደረሷቸው መጻሕፍት የተጽኖአቸውን መጠን ያበስራሉ። የሚወተውት፣ እውቀትን የሚጠማ፣ እውቀትን የሚያፈልቅና የሚጋራ አእምሮ እነሆ! በዘጠና ዓመታቸው ጽሑፎቻቸውን በፌስቡክ መለጠፍና የመጽሐፎቻቸውን ያለቀ ቅጂ በኮምፕዩተር አዘጋጅተው ለአታሚ መላክ ችለዋል። ዘመናዊነት የእድሜ ሳይሆን የአስተሳሰብ ጒዳይ እንደሆነ እንረዳለን። ከወጣቱ ትውልድ ጋር የመግባባታቸው ምሥጢር ይኸው ነው።

የፕሮፌሰር መስፍን የመሠጠት ልክ በአብዛኞቹ የአገራችን ምሑራን ዘንድ አይታወቅም። አሳብን በአሳብ መታገል እንጂ ዱላ መማዘዝ የማይቀበሉት አቋማቸው ነው። ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን እንዲያውቅ፣ በአገሩ ጒዳይ ከዳር ቆሞ ሳይሆን መሓል ገብቶ እንዲሳተፍ። መሪዎቹ ጦር ሜዳ እንዳይማግዱት፣ ታሪኩንና ቅርሱን እንዳይዘርፉት፣ እርስበርስ እንዳያባሉት፣ ለሥራ አጥነትና ለእስር፣ ለስደት ኑሮ እንዳይዳርጉት መድኃኒቱ ታሪኩን ማወቅና ተግቶ መሳተፍ መሆኑን ታግለው አሳይተዋል። የተሳተፉበት የ97ቱ የቅንጅት ሕዝባዊ ማእበልና በስተእርጅና ከርሸሌ የወረዱበት ይታወሰናል፤ በዚህም የመንግሥት መሪዎችን የሞራል ክሥረት አጋልጠዋል። ከወዳጆቻቸው መሓል እነ ክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ጋዜጠኞች ርእዮት ዓለሙ እና ተመስገን ደሳለኝ፣ ደራሲ በእውቀቱ ስዩም፣ ወዘተ፣ መገኘታቸው የተጽእኖአቸውን ወርድና ስፋት ይጠቊመናል። የፕሮፌሰር መስፍንን ሕይወት በሦስት ቃል ማጠቃለል ቢቻል፣ “ከዳር ቆሜ አላይም!” የሚል ይመስለኛል። ወጣቱ ትውልድ ይህን ብቻ ካስታወሰና ከተተገበረ የኖሩለት ዓላማ ከንቱ አይቀርም!

ፕሮፌሰር መስፍንን የሥልጣን ጥመኛ አድርገው የሚያዩ አሉ። ይህን የሚሉ አንዳንዶች መየቅ የሚያስቆጣቸው፣ መጠየቅ የማይደፍሩ ናቸው። ችግሩ የፖለቲካን መሪ ከሞራል መሪ አለመለየታቸው ነው። ፖለቲካ አንጀኛ ነው፤ በተለይ የአገራችን መሪዎች ጠባብና ርእዮተ ዓለማዊ አጀንዳ ከማራመድ ውጭ አርቀው አያስቡም። የሞራል መሪ በርእዮት ዓለም ሳይታገት፤ ሁሌ ሰብዓዊነትን ያገንናል።

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የጭሰኛ ሥርዓት፣ የሕዝብ መራብ፣ መኃይምነት ዋነኛ ጒዳይ ነበር። በደርግ፣ ጦርነት፣ ርእዮተ ዓለማዊ ክፍፍልና የመጠፋፋት ሽብር ነበር። በህወሓት/ኢሕዴግ ዘረኛ ሽብር፣ የአገርን ቅርስ የመዘበረ ሥርዓት ነበር። ሦስቱም መንግሥታት የዜጋን ተሳትፎና መብት ያስከበሩ አልነበሩም (የዜጋን ጥያቄ የናቊና ያዳፈኑ ነበሩ፤ ያም ለመወገዳቸው ምክንያት ሆነ)። የፕሮፌሰር መስፍን ሕይወትና የዜግነት ድርሻ ከዚህ አኳያ መታየት ይኖርበታል።

ፖለቲካውን ከሞራል ራእይ መነጣጠል ቀላል አይሆንም፤ ሁለቱን አንድነት መያዝም የራሱ ችግር አለበት። ጳጳሱንም ንጉሡንም አንድነት መሆን አይቻልም! ለምሳሌ፣ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱን የፖለቲካና የሞራል መሪነቱን መሳ ለመሳ ለመያዝ የሚያደርጉት ጥረት ወሳኝነትና ተኣማኒነትን እየነሳቸው ነው። ዐቢይ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ መሆናቸው፣ የአገርን ንብረት የሚዘርፉና የሚያዘርፉ አለመሆናቸው ትልቅ ለውጥ ነው። የአመራር መሠረቱ በግለሰብ ላይ ማተኮሩ ሳይሆን፣ የህግ የበላይነትን ማስከበሩ፣ ተቋማትን ማጠናከሩ፣ ዜጋ ተደራጅቶ እንዲሳተፍ ማመቻቸቱ ላይ ነው። ይልቊን መሪው በሌለበት መንግሥት ቀጣይነትን እንዲያገኝ ማዘጋጀት ነው (አፄ ኃይለሥላሴም፣ ኮሎኔል መንግሥቱም፣ መለስ ዜናዊም ያላደረጉት ነው!)።

በጥንት እስራኤል እንጂ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ንጉሥ ዳዊትን መሆን አይቻልም! ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ የቋንቋዎችና የኃይማኖቶች ጥርቅም እንጂ እንደ ጥንት እስራኤል ወጥ አይደለችም! አፄ ኃይለሥላሴ “ስዩመ እግዚአብሔር” የሕዝቡን ጥያቄ በወቅቱ አለመመለሳቸው ለዘውዳቸው መገርሠሥ ምክንያት ሆኗል! ለኮሎኔል መንግሥቱና ለመለስ ዜናዊ (ለኢሕአፓ፣ ለመኢሶን፣ ለኦነግ መሪዎች) በአንጻሩ፣ ‘ሞራላዊነት’ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ያስቻላቸው ብልኃት ሁሉ ነው፤ ሕዝብ ማለቅ ካለበት፣ ያንን ለመጠየፍ የሚበቃ ኅሊና አልነበራቸውም፤ ያልተስማማቸው ሁሉ ጠላት ነው። ስብእናቸው ድርድር የማይፈቅድ ብቸኛ ተዋናይነት ነው! ዛሬ ስም ቀይረው የተኮለኮሉት “ፓርቲዎች” ከዚያው ካደረው ምንጭ የተቀዱ ናቸው! መለስና ጓዶቻቸው በዘፈቀደ ባሠመሩት ድንበር ሳቢያ ሕዝብ ተማግዶ፣ ተተረማምሶ፣ ኑሮውን ካፈቀደበት ሄዶ እንዳይመሠርት ተደርጓል። አገር ወደብ አልባ ተደርጋለች። ነገ ዶ/ር ዐቢይና ፓርቲአቸው (ዶ/ር ብርሃኑና ፓርቲአቸው)፣ እንደ መለስና ኢሳይያስ ሳያስፈቅዱን፣ ኢትዮጵያን ወደ ጥንት ታላቅነቷ መለስናት ብለው ከኤርትራ ጋር ቢቀላቅሉን፤ የአሰብን ወደብ ተከራየንላችሁ ቢሉን ምላሻችን ምንድነው? እንደ ፕሮፌሰር መስፍን አተያይ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ድንገተኛ እንዳይሆንብን ትርኪምርኪውን አቊመን መዘጋጀት ይኖርብናል!

የሞራል መሪ ድርሻው መንግሥት የነፈገውንና የዘነጋውን ክፍተት መሙላት ነው። ሕዝብ ተራበ? ባለሥልጣናት እስኪንቀረፈፉ እጄን አጣምሬ አላይም፤ መረጃ ይዤ እተቻለሁ፤ እደራጃለሁ፤ በምችለው መፍትሔ እሻለሁ ይላል። አገር ከገባችበት የፖለቲካ ዱር ውስጥ መውጫ ማፋለግ በጥልቅ ማሰብን፣ መስዋእትነትን፣ ተግቶ ሕዝቡን ማስተማር ይጠይቃል። “አክቲቪስትነት” ተቧድኖ መናቆር ሳይሆን ወደ ተሻለ ግብ ለመድረስ አስተካክሎ መረጃ መያዝ፣ ድልድዮችን መዘረጋጋትና አብሮ መሥራትን ይጠይቃል። አሁን የምናየው ያረጀ ራእይ ብቸኛ ራእይ ዓላማ ቢስ ራእይ እኲይ ራእይ የሥልጣን ጥመኞች ራእይ ተበራክቶ ጩኸትና ቅዠት መፍጠሩን ነው! በደርግም ይኸው ነው፤ በእነ መለስም ዘመን። በሃምሳ ዓመት አንዴ እንኳ እንዴት የአካሄድ ለውጥ አናደርግም?!

ከአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ እና እስከዚህ ዘመን፣ ገንኖ የምናየው አመለካከት ተመሳሳይ ነው። ‘እውነት፣’ ለብሄሬ ለፓርቲዬ የሚጠቅመው ብቻ ነው። ጥያቄ ማንሳት አይፈቀድም። በመረጃ መርታት አይቻልም፤ ሁሉም የራሱን የመረጃ ፋብሪካ አቋቊሟል! የራሱ እውነት ቸርቻሪ ሆኗል! ህወሓት የብሄርን ፖለቲካ አገነነ እንጂ አልፈጠረም! የፕሮፌሰር መስፍን ጠያቂነት በአንጻሩ፣ በጎሳ ወይም በማይጠየቊ ርእዮቶች አልተገታም። ከዚህ የተነሳ የሚጽፉትና የሚናገሩት ሳያነጋግር ቀርቶ አያውቅም! በስተእርጅና ያከናወኑት ብዙዎቻችን በጒብዝናችን ያልሞከርነው ነው። ንብረት ማፍራት ሲችሉ ለሕዝብ የቀረበ አኗኗር መምረጣቸው፣ ኃይማኖቱንና አገሩን በንዋይ በለወጠ ትውልድ መሓል የማይበገር ተሟጋች አድርጓቸዋል! የሞራል ሰውነት አጎናጽፏቸዋል!

የፕሮፌሰር መስፍን የሞራል መሪነት በተለይ በጻፏቸው ቅኔዎች ውስጥ ይነበባል። እስቲ “ኑዛዜ” ን እንመልከት፦

፩/ ሰው ፍጻሜ አለው፦ የሕይወት ጽዋዬ፣ ጥንፍፍ ብሎ ሲያበቃ፤ | ሲቀር ባዶውን፣ የቆየ ባዶ ዕቃ፤ | ሲበቃኝ፤ በቃህ ስባል፣ | ትንፋሼ ሲቆም በትግል፣  ከራሳቸው ተሞክሮ አልፎ፣ ድርቅና ረሃብ የሰሜኑን ሕዝባችንን ሲረፈርፍ የዐይን እማኝ እንደ ነበሩ ያስታውቃል።

፪/ እያንዳንዱ ሰው ተልእኮ አለው፤ መጠኑ ይለያይ እንጂ አንዳች አስተዋጽዖ ሳያደርግ ሊያልፍ የተፈጠረ አንድም ሰው የለም፤ ይህም የሰውን ክቡርነትና እኲልነት ያስታውቃል። እወቊልኝ ይህን ብቻ፣ | የገባኝን ያህል | ሞክሬ ነበር | ሰው ለመሆን፤ | ሰውነት በከፋበት ዘመን። እግረ መንገድ፣ የጸጋዬ ገብረመድህን ቊጭት ምላሽ አግኝቶ እንመለከታለን፤ ስንቶች “ሞክሬ ነበር” ለማለት በቅተናል? ወይስ ሳንሞክር እጅ ሰጥተናል? ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ | ከሞከርነው ነገር ይልቅ፣ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ። (ጸገመ፣ እሳት ወይ አበባ፤ 1966 ዓ.ም.፣ ገጽ 204)

፫/ ይቅርታ የእግዚአብሔር ነው። ከእግዚአብሔር በቀር ፍጹም የለም። ሰው በንግግሩ፣ በአሳቡና በድርጊቱ ይሳሳታል። ዛሬ በደልን የሚቆጥር እንጂ ይቅር የሚል ጠፍቷል። በዚህ ምክንያት ሁላችንም እረፍት አጥተናል። ፕሮፌሰር መስፍን በ2005 ዓ.ም. ይቅር በሉኝ ብለዋል። የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ግን ገና በደል የሚቆጥሩ መኖራቸው ነው። ከፈርሃ እግዚአብሔር ምን ያህል ብንራራቅ ነው? የበደልኋችሁ ይቅር በሉኝ፤ | ቂም አትያዙብኝ፤ | እንግዲህ መንገዱ አልቆ | የኑሮ ጣጣ፣ | አልወርድ፣ አልወጣ! | አላስቀይም፣ አላስቆጣ!

፬/ ሰው ወደ አፈሩ ይመለሳል። ሬሣ፣ እንደ ኃይማኖቱ ሥርዓት በሣጥን ተደርጎ መሬት ውስጥ ይከተታል። “ኑዛዜ” ማህበረሰብ ልክ ነው ብሎ የተቀበለውን የፍጻሜ ትርክት እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ግጥም ነው። መሬት አልነበረኝም በሕይወቴ | መሬት አልፈልግም፤ አሁን በሞቴ! | አቃጥሉልኝ ሬሣዬን፤ | አመድ እስኪሆን፤ | አዋሽ ውስጥ ጨምሩልኝ አመዴን፤ አመዴ | ከአዋሽ ይቀላቀል ከዘመዴ! | እቺን አትንፈጉኝ አደራ! | አመዴ እንኳን እንዲኮራ!

የቀረበልን ጥያቄ፦ ሬሣን መቅበር ወይስ ማቃጠል? የሚል ነው። ለቤተሰብ “ሥጋን” በዚህ መንገድ መሰናበት የማይታሰብ ነው! እርሳቸውም ይህን ተረድተው፣ “የሬሣን ፈቃድ የሚፈጽም ከተገኘ” ብለዋል። የጥያቄውን አሳሳቢነት ከሁለት አንጻር ማየት ይኖርብናል። ሀ/ ከመንፈሳዊ (ስነ መለኮት) አንጻር፣ ለ/ ከመጤ ባህል አንጻር። በክርስትናም በእስልምናም ሬሣን መቅበር እንጂ ማቃጠል አይታሰብም። ለክርስቲያኖች ሬሣን ስለ ማቃጠል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ አልሠፈረም (ሬሣ የተቃጠለባቸው ጊዜአት በ1ኛ ሳሙኤል 31፡11᎐13፣ ንጉሥ ሳኦልና ልጆቹ በጦርነት ተገድለው ሰውነታቸው ለቀብር ሳይመች ቀርቶ። በሌዋውያን 20፡14 እርግማንን ለማራቅ እርምጃ ተወስዶ)። በሌላ አነጋገር፣ የተለመደው ሬሣን ማቃጠል ሳይሆን መቅበር ነው።

የምእራቡ ዓለም ክርስትና፣ በግልጽ ያልሠፈረን ሁሉ መድፈር ለምዷል። መነሻው ዞሮ ዞሮ ከንግድ ጋር ይያያዛል። የመቀበሪያ መሬት መወደድና ውጣ ውረዱ አንደኛው ምክንያት ነው፤ ቀብር ከስምንት ሺህ እስከ አስር ሺህ ዶላር ያስወጣል፤ ማቃጠል ሁለት ሺህ ያህል ዶላር ነው። አመዱን በሸክላ ወይም በብርጭቆ አድርጎ ማኖር ቦታ ስለማይፈጅ አብያተ ክርስቲያናት ለምእመን የሚሆን የእብነ በረድ ቊም ሳጥን በየቅጥር ግቢአቸው አሠርተው የገቢ ምንጭ አድርገውታል። አስቀድመው ግን የሚደግፋቸውን ስነ መለኮት ማነጽ ነበረባቸው!!

ሬሣ ማቃጠልን ከመጤ ባህልና ንግድ አንጻር ማየት ይቻላል፤ ምክንያቱም ያለንን ጥለን፣ ሳንመረምር የውጭውን መኮረጅ ስለምናበዛ። የቀብር ቦታ መወደድ፣ መካነ መቃብርን በግሬደር አፈራርሶ ለንግድ ቤት መሥሪያ ማዋሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያየናቸውን ባህላዊ ለውጦች ብናጤናቸው፦ በአፄ ኃይለሥላሴ ቀርቶ በደርግ ዘመን የአህያ ልኳንዳ አይታሰብም ነበር፤ ሕጻናትን በነፍስ ወከፍ በሠላሳ ሺህ ዶላር ላሳዳጊ መስጠት አይታሰብም ነበር፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ እህቶቻችንን ለዐረቦች ወሲብና ግርድና በወር ሁለት መቶ ዶላር መዋዋልና መመዝበር አይታሰብም ነበር። ቤተ እምነቶች የክርስቶስን የፍቅር ወንጌል መስበክ ትተው፣ ከመጣው ጋር መዋላቸው፣ በጥላቻና በፍቅረ ንዋይ መጠመዳቸው የሞራል ጒድፍ ጎርፍ ለመመከት የሚያስችል የሞራል አቅም ነስቷቸዋል። ዘረኛ ፖለቲካ ሌላኛው ጒዳይ ነው፤ ሰውን እንደ እግዚአብሔር ፍጡር ሳይሆን በብሄር መነጽር የሚያይ ዐይን ትርፍ ካመጣ ከብሄሩ ውጭ ያለን ሬሣ ከማቃጠል አይመለስም። ባጭሩ፣ አንድ አስተምህሮና ባህል፣ ሰብዓዊነትን ያዋርዳል ወይስ ያንጻል ተብሎ በቅድሚያ ሊመረመር ይገባል።

፭/ በሕይወት ለቀረነው ሌላ ዋነኛ ጥያቄ ቀርቦልናል፤ ሀ/ ሟች እንደሆንን ተዘንግቶን ይሆን? መቊረጫችን እንዴትና መቸ ከተፍ እንደሚል እናውቃለን? ለ/ “የገባኝን ያህል ሞክሬ ነበር” ለማለት እንደፍራለን? ሐ/ ቂም እንደያዝን እናልፋለን ወይስ ይቅር ተባብለን አብረን እንኖራለን? መ/ ሬሣችን በምን አኳኋን ይሸኝ ይሆን? ሠ/ ለህልፈታችን ስድስት ቀን ቢቀረው ምን ዓይነት የአሳብ ለውጥ እናደርጋለን?

፮/ የጸጋዬ ገብረመድኅን ቊጭት፣ በፕሮፌሰር መስፍን “የገባኝን ያህል ሞክሬ ነበር” ጊዜያዊ ምላሽ አግኝቷል ብለናል። በሌላ በኲል፣ ፕሮፌሰር መስፍንና ባለቅኔ ሰሎሞን ዴሬሳ አጋር ሆነው እናገናቸዋለን። መስፍን ፍልስፍና ያጠኑት(?) ህንድ አገር በመነበሩ፣ ከላይ በጠቀስነው ጽሑፍ ላይ ይህንኑ የህንድ ሬሣ የማቃጠል ባህል ጠቅሰዋል። በሂንዱ/ቡዲስት እምነት ሬሣ የሚቃጠለው፣ ነፍስ ቶሎ ከሥጋ እንድትላቀቅ ነው። ሂንዱ እምነት፣ እንደ ክርስቲያን በሙታን ትንሣኤ አያምንም፤ ነፍስ ከሥጋ ተላቅቃ በድመት፣ በአሞራ፣ በዛፍ ወዘተ ተመስላ ትቀጥላለች ይላል፤ ተስፋው ግን የተረጋገጠ አይደለም። የኢየሱስ ከሙታን መነሳት፣ ትንሣኤ አካል ስለ መልበስ፣ ስለ ሞትና ከሞት በኋላ ስለሚሆነው ምን ያስረዳል? (ዮሐንስ ወንጌል 20፡24.2921፡1᎐14)

ሰሎሞን ዴሬሳም (ፍልስፍና አጥንቷል)፤ በ “ቀጠሮ” እና በ “አሟሟት እንደኔ’ናት” ቅኔው እንዲህ ይለናል፦ እመሸበት ታድሮ | ላይቀር መነቃቱ | እንደተቀጠረ ላይቀር መገርጣቱ | የለኰሱት ሻማ | እንዳይሟሟ መወትወቱ (ዘበት እልፊቱ፣ 1991 ዓ.ም.፣ ገጽ 49)። “የለኮሱት ሻማ፣ እንዳይሟሟ መወትወቱ” የሚለው ሐረግ ለረጂም ዘመን የቡዲስት አተያይ ይሆን? ብዬ ስጠይቅ ኖሬ፣ በሰሎሞን ዜና እረፍት ላይ ስለ ቡዲስት እምነት ጥልቅ ፍላጎት እንደነበረው ተጠቅሶ አንብቤ ጥርጣሬዬ ይዞልኛል፤ (በእንግሊዝኛ፣ ኖቬምበር 4/2017፤ ገጽ 5)። በ “አሟሟት”፣ “ካልቀረልኝ ተደናግጦ ተመልሶ መምጣት” ብሎ ይህንኑ አሳብ ደግሞታል። ሰሎሞን ዴሬሳ ሬሣው እንደ ኑዛዜው ተቃጠለ እንጂ አልተቀበረም። ፈር ቀዳጅነቱ በቅኔው ብቻ እንዳልተወሰነ እንመለከታለን!

ተፍጨርጭሬ ፀጥታን መግራቴ | እየፈራሁ ብቻነቴን ማሟላቴ | በምርጫ እንዳልፍ እንደ’ናቴ | እንዲስማማኝ አሟሟቴ | እንደ ህይወቴ እንዲያምርባት ሞቴ | ያለግርግር፣ ያላልቃሽ፣ ጋደም ብዬ መቅረት | አልፌ መረሳት እንዳቻምና ውሃ ሙላት፣ ካልቀረልኝ ተደናግጦ ተመልሶ መምጣት | ልወለድ ጊዜ ካላት አፍሪቃ እናት | ከልጅ፣ አክባሪ ከራስ ወዳድ አባት | ርኅሩኅ፣ ብስል፣ መምህር በተመላለሰበት | ህዝቡ ተከብሮ በተከባበረበት | እውቀት እንደሞት ድርሻ በሆነበት (ዘበት እልፊቱ፣ ገጽ 73)

፯/ ከቡዲስት/ሂንዱ እምነት ባሻገር፣ መስፍንና ሰሎሞን የቀብር ስነ ሥርዓት በቋሚው ላይ የሚያስከትለውን መንገላታት አጥብቀው እንዳሰቡበት ግልጽ ነው። ሬሳዬን ባማረ ሣጥን ውስጥ ከታችሁ፤ | በአበባ አጊጣችሁ፣ | መሬት በሊዝ ገዝታችሁ፣ | ድንጋይ በላዬ ላይ ጭናችሁ፤ | ስራ ፈትታችሁ፣ ተሰብስባችሁ፤ | የባጥ- የቆጡን ቀባጥራችሁ፣ | አትዳርጉኝ ለጭቆና፤ | እንደገና! (መስፍን)። በምርጫ እንዳልፍ እንደ’ናቴ | እንዲስማማኝ አሟሟቴ | እንደ ህይወቴ እንዲያምርባት ሞቴ | ያለግርግር፣ ያላልቃሽ፣ ጋደም ብዬ መቅረት | አልፌ መረሳት እንዳቻምና ውሃ ሙላት (ሰሎሞን)

ለመወያየት፣ ለመታረቅ፣ ለመሞት ተራው አሁን የኛ ነው። የእያንዳንዳችን ኑዛዜ ቢጻፍ ምን ይመስል ይሆን? ዜና እረፍታችን ተገልጦ ሲነበብ፣ ሞክሮ ነበር? ቂመኛ ነበር? ወይስ ለራሱ ብቻ ኖሮ አለፈ ይላል? ምን ቢል እንወዳለን? የኢየሱስን ትንሣኤ ምን እናድርገው?

ምትኩ አዲሱ