ሞት እና ፕሮፌሰር
ፕሮፌሰር [መስፍን] ከሞት አፋፍ መትረፋቸውን፣ “ጻዕረ ሞትና መስፍን ወልደ ማርያም” በሚል ርእስ አስነብበዋል። ያለእረፍት ከሞት ጋር ግብግብ ለኢትዮጵያውያን እንግዳ ባይሆንም፣ የፕሮፌሰርን ልዩ የሚያደርገው ሳይቆጠቡና ሳይታክቱ አሳባቸውን ማገናዘብና መግለጽ መቻላቸው ነው። ለአስቸኳይ ህክምና ወደ ህንድ መጓዛቸው፣ ይልቍን መደምደሚያው ላይ “[ሞት] አይቀር! እኔም ማምለጫ የለኝ!” ማለታቸው ለጽሑፋቸው ያልታሰበ ክብደት ሰጥቶታል። በሞት ጉዳይ ላይ መወያየት፣ በነፍስ ወከፍና በአገር ደረጃ ከገባንበት የሞራል ማጥ መውጫ ፍንጭ ይሰጠን ይሆን?
ሰው ድንገት የሚሰናበት ተንቀሳቃሽ ሬሳ ነው። ድንገት ብሰናበት የሚጸጽተኝ አለ? ማለት ብልህነት ነው። ፕሮፌሰር፣ በስድሳ ሰባት “እንጕርጕሮ”ን፤ ከአርባ ዓመት በኋላ ደግሞ “ዛሬም እንጒርጒሮ”፣ “ሞት ማለት” እና “ኑዛዜ” በተሰኙ ግጥሞች ሞት ከእዝነ ልቡናቸው ሩቅ እንዳይደለ ነግረውናል። እንደ ልብ ለመናገር የቆረጠላቸው ለዚህ ይመስላል። ብዙዎቻችን በፍርኃት ተለጕመን ለማሰብ እንኳ ጊዜ አጥተናል። ለማያስተማምን ኋላ ስናቆይ፣ ሞት የጠቆመንን ሂስ ሳንጠቀምበት፣ ለቍምነገርም ሳንበቃ ወደማንመለስበት እንሻገራለን። ፕሮፌሰር [ሞት] አይቀር፣ “እኔም ማምለጫ የለኝ” ማለታቸው፣ ጻዕረ ሞት አምስቴና ስድስቴ ካዋከበኝ [ነቅቼበታለሁ] ለሰባተኛው አይምረኝም ማለታቸው ይመስላል።
ሞት አለመስማት ነው፤ ጆሮ ዳባ ልበስ / ክርስቶስ ሲሰቀል፤ ሲፈታ በርናባስ ["ሞት ማለት"፣ ስንኝ 1]
አእምሮ ፈራርሶ ፣ ኅሊና በስብሶ ... / የሞት ሞት ይኸ ነው፣ ትንሣኤ የሌለው [ስንኝ 6]
በዚህ አስተውሎአቸው፣ እውነቱ [ክርስቶስ] ተትቶ፣ ውሸቱ [በርናባስ (በርባን? ሉቃስ 23፡18-19)] ሲመረጥ፣ “ሞት ማለት” ያ ነው። የሞት ሞት የኅሊናን ዳኝነት መካድ ነው። ኢትዮጵያ ተወልዶ ያደገ መቸም ከኃይማኖት የራቀ ስብእና የለውምና የኢየሱስን መሠቀል መጥቀሱ አይገርምም። የፕሮፌሰርን ልዩ የሚያደርገው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በአደባባይ መወያየት በአገራችን ምሑራን ዘንድ ያልተለመደ መሆኑ ነው። እውቀት የሚሻ እውነትን አይፈራም፤ መረጃን እንጂ መደምደሚያን አያስቀድምም። ፕሮፌሰር በሌላ ሥፍራ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መሠቀል “በድፍን ጨለማ ውስጥ ብልጭታን ያሳየኛል ... ክርስቶስ ተደብድቦና ተገርፎ፣ በምስማር እጆቹና እግሮቹ በእንጨት ላይ ተከርችሞበት፣ በራሱ ላይ የእሾህ አክሊል አስቀምጠውበት ሠቅለው ከሞተ በኋላ ቀበሩት፤ በሞቱም ለሰው ልጆች ኃጢአት ራሱን መስዋእት አደረገ፤ ሞትንም፣ መቃብርንም አሸንፎ ተነሣ፤ ትንሣኤ ይህ ነው” ብለዋል [እዚህ ይጠቁሙ]። ትክክለኛ አባባል ነው።
የኢየሱስን ከሙታን መነሳት ታሪካዊነት መቀበል እና ‘ይኸ ታሪካዊ እውነት ለኔ ሟች ለሆንኩት ፋይዳው ምንድን ነው?’ ማለት ግን ለየቅል ናቸው። ለታመመ፣ የመድኃኒቱን ስምና መድኃኒቱ የሚገኝበትን ሥፍራ ማወቁ ምንም አይጠቅመውም። ብዙዎች የኢየሱስን ስም ሰምተው ያውቃሉ። ሆኖም ህመም እንደሌለባቸው ያስባሉ፣ ህመሙ ከአዳም የተወረሰ፣ በደም ውስጥ የሚተላለፍ መሆኑን ይዘነጋሉ። ‘ቂም አልይዝ፣ እኔ ሆዴ ንጹሕ ነው፤ ገብሬል ያውቅልኛል፤ እመብርሃንን ተማጽኛታለሁ’ እያሉ ራሳቸውን ያባብላሉ። ህመማቸውን ያወቁ ደግሞ ድርሻቸውን ካለመገንዘብ፣ ‘ምን ማድረግ እችላለሁ? እድሌ እንዳደረገኝ እሆናለሁ’ ይላሉ። ማካበድ ማወሳሰብ አያሻም፤ ከህመም ለመገላገል ህመምተኛው ለራሱ መድኃኒቱን ከመውሰድ ውጭ አማራጭ የለም። ወንጌል፣ መድኃኒቱ ኢየሱስ ነው ብሎናል፤ “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ...ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” [ሉቃስ 2:11:: ማቴዎስ 1:21]። “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” [ዮሐንስ 1:12]። ህጻን ለመወለድ የሚያደርገው እንደሌለ ሁሉ፣ ዳግም ከመንፈስ መወለድም እግዚአብሔር በእምነት ለሚቀርቡት የሚያደርግላቸው ነው። “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ[ና]፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል[ና] በአፉም መስክሮ ይድናል[ና]። መጽሐፍ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላል[ና]” [ሮሜ 10:8-11]። ይኸ መዳን የሚሆነው ነገ አይደለም፤ ከሞተ በኋላ አይደለም፤ ዛሬውኑ በዚህ ሕይወት የሚሆን ነው። “ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም” [ዮሐንስ 5:24]። “በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም” [ሮሜ 8:1]። ማንም መዳኑን ዛሬውን በዚህ ሕይወት እያለ እርግጠኛ መሆን ይችላል። "በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው" [1ኛ ዮሐንስ 4፡10]። ኢየሱስ ሕይወት እንጂ ኃይማኖት አይደለም፤ “መዳን[ም] በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለም”[የሐዋ ሥራ4፡12]።
መድኃኒቱን የወሰዱ ፈውሳቸውን ወዲያው ያውቁታል። ከዚህ ቀደም የማያውቁትን፣ ዓለም የማይሰጠውን፣ ሰላም ያገኛሉ፤ ከኅሊና ክስ ነጻ ይወጣሉ። “ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?” [ዕብራውያን 9:14]። የኔ ህመም [በደሌ] ከባድ ስለሆነ እንዲህ በቀላሉ የምገላገለው አይደለም የሚሉ ይኖሩ ይሆናል። እነዚህ የመድኃኒቱን ፍቱንነት ያላወቁ ናቸው። በደላቸው ሲከፋ ቢውል ከዳዊት [ነፍስ ማጥፋትና የሰው ሚስት መቀማት] አይከፋም፤ ከጴጥሮስ ኢየሱስን መካድ አይብስም፤ ከማቴዎስ የሕዝብ ንብረት መዝረፍ አይብስም። ከጳውሎስ ንጹሐንን ማሳደድ፣ ማሳሰርና ማስገደል አይብስም። እነዚህ ሁሉ ወደ ኢየሱስ በንስሓ ቀርበው ይቅር ተብለዋል፤ በንስሓ ኢየሱስ ፊት ቀርቦ ይቅር ያልተባለ አንድም ሰው የለም። በንስሓ ኢየሱስ ፊት ቀርቦ ይቅር ያልተባለ አንድም ሰው የለም [ዮሐንስ 8፡3-11፤ ሉቃስ 19፡1-10፤ 23፡42-43]። ይቅር ተብለዋል ማለት ግን አድራጎታቸው ውጤት አላስከተለም ማለት አይደለም። ገንዘብ የሰረቀ፣ የገደለ ወይም በመግደል የተባበረ በእግዚአብሔር ፊት ንስሓ ቢገባ፣ መስቀል ላይ በፈሰሰው በክርስቶስ ደም ከኅሊና ክስ ነጻ ይወጣል፣ በክርስቶስ ስም ስላመነ፣ አባት ልጁን እንደሚምርና እንደሚቀበል እግዚአብሔር ምሮ ይቀበለዋል፤ ስሙንም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይጽፍለታል። ህግ በሚያዝዘው መሠረት አይቀጣም ማለት ግን አይደለም።
በመረጃ የተረጋገጠ አንድ እውነት እንያዝ። ያም በኢየሱስ ከሙታን መነሳት የሞት ሥልጣን ተሽሯል። ሞት አሁን መደምደሚያ ሳይሆን “ወዲያ” መሻገሪያ ነው፤ “ወዲያ” ደግሞ አሁን በድንግዝግዝ የሚታይ ሁሉ ግልጽ የሚሆንበት ክልል ነው። “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን” [2ኛ ቆሮንቶስ 5:1-4]። “የምንቃትተውና የምንናፍቀው” መልካም ሆኖ የተፈጠረው በኃጢአት በመበላሸቱና፣ የማይሞት አካል ለመጎናጸፍ በመጓጓት ነው። በክርስቶስ ላመኑ የከበረ ሕይወት በዚያ፤ ላላመኑ ግን ፍርድ ይጠብቃቸዋል። “ለሰዎች አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው” ብሎአል [ዕብራውያን 9:27]።
ፕሮፌሰር በ “ኑዛዜ” እንዲህ ብለውናል፣
የሕይወት ጽዋዬ ጥንፍፍ ብሎ ሲያበቃ / ሲቀር ባዶውን፣ የቆየ ባዶ ዕቃ፤
ሲበቃኝ፤ በቃህ ስባል / ትንፋሼ ሲቆም በትግል፣
ስሸነፍ ተሟጦ ኃይል / ሰው መሆኔ ቀርቶ – አስከሬን ስባል፣
ሰው ማንነቱ ከሚታይና ከማይታይ ክፍል የታነጸ ነው፤ ያንን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም። ፕሮፌሰር ሦስት ቀናት ራሳቸውን ስተው ቆይተው መንቃታቸው፣ ስለ ሰው ምን ይነግረናል? ሲታይ በአካል አለ፤ ደግሞ የለም። የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉን መልካም አድርጎ ነው። ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠረ፣ አስከሬኑም እንኳ ክቡር ነው። አንድ ሕዝብ ለሙታኑ የሚያሳየው አክብሮት፣ ለርስበርሱና ለፈጣሪው ያለውን ክብር ይገልጣል።
ኢየሱስ ከሞተ አራት ቀን በሆነው በአልዓዛር መቃብር አጠገብ ቆሞ፣ “አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና” ሲለው አልዓዛር ከነግንዙ ብድግ አለ። ኢየሱስም፣ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” አለ [ዮሐንስ ወንጌል 11:25-26፤32-45]። ይህን ያዩና የሰሙ አንዳንዶች አመኑ፣ አንዳንዶች ግን እያዩ እየሰሙም አላመኑም። ለምን አላመኑም? መረጃ ጠፍቶ ነው? አይደለም። መረጃማ እፊታቸው ቀርቦላቸዋል። ያላመኑት፣ ከያዙት አመለካከት ጋር ስለማይጣጣምና ይህን እውነት ማስተናገድ አኗኗራቸውን ስለሚያስቀይራቸው ነው።
ወደድን ጠላን፣ ትንሣኤ ሙታን የማይቀር ነው። ሰሞኑን ያከበርነው የኢየሱስ ትንሣኤ የሚነግረን ይህንን ነው። የኢየሱስ ከሙታን መነሳት፣ ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ራሱ፣ ስለ ሰው፣ ስለ ፍጥረት ሁሉ፣ ስለ ትናንት-ዛሬ-ነገ የተናገራቸው እውነት ስለ መሆናቸው ማረጋገጫ ነው። “...ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” [ሮሜ 1፡4]። ኢየሱስ ፍጹም አምላክ-ፍጹም ሰው ነው፤ “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራል” [ቆላስይስ 2፡9]። የኃጢአት ሥርየት የሚገኘው በርሱ ብቻ ነው [የሐዋርያት ሥራ 2፡32-38]። ብዙዎች እንዳሰቡትና እንደ ገመቱት ሳይሆን ከሞት በኋላ በእርግጥ ሕይወት አለ! ሰው ሁሉ ስለ ኖረው ኑሮ መልስ የሚሰጥበት፣ ፍርድና ፍትኅ የሚገለጥበት ሕይወት ከፊቱ ይጠብቀዋል [ማቴዎስ 25:31-46፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4:5]። “ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም” [ዮሐንስ 5፡23]። ሕይወትን በሚያክል ጕዳይ ይህን እውነት ችላ ማለት ከኪሳራም ኪሳራ፣ ከሞትም ሞት ነው። ከሞት የማምለጫ ደጅ ተከፍቶ አለማምለጥ ቂልነት ነው።
ሕይወትና ሞት ምርጫ ቀርቦልናል፤ የትኛውን መረጥን? “በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች” [ዮሐንስ 1:4]። "እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም" [1ኛ ዮሐንስ 5፡11-12]። ምርጫችን ክርስቶስ ቢሆን እርስበርስና በአገር ደረጃ ስለምንፋለምባቸው ጉዳዮች መፍትሔና አዲስ እይታ ባገኘን! በተለይ የአገር መሪዎች፣ አዳኝና ይቅር ባይ የሆነውን ኢየሱስን፣ “በድያለሁ፣ ይቅር በለኝ፣ ልቤን ከፍቼልሃለሁና ግባ” ቢሉ ለምድራችን ፈጥኖ ሰላም በወረደ! “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል” [ዮሐንስ 3:16-21]።
ምትኩ አዲሱ
ዳግማዊ ትንሣኤ፤ ሚያዝያ 15/2009 ዓ.ም.
[ስለ ትንሣኤ የዐይን ምስክሮችን ሰነድ እዚህ ያንብቡ]