GERBOLEበቋጥኝ ላይ የበቀለች ዋርካ፤ የነቢይ ገርቦሌ ሂርጳ የሕይወትና የአገልግሎት ታሪክ

ደራሲ፦ ደረጀ በቀለ። የታተመው፦ 2003 ዓ.ም። 186 ገጽ።

በጌታ ኃይል ሥራ ደስ ለሚሰኙ፣ ያልተጨማመረ ወሬ መስማትና መነቃቃት ለናፈቃቸው፣ እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ምስክር አጥቶ እንደማያውቅ፣ ዛሬም የተሰጡ በሕይወታቸው የተወራረዱ ባርያዎች እንዳሉት ለተጠራጠሩ ወይም ተስፋ ለቆረጡ የሚያበረታታ መልካም ዜና እነሆ። እግዚአብሔር ዛሬም ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ከሩቅና ከቅርብ ባርያዎች አሉት። በጀርመን አገር “ገርቦሌ ያገር ወይስ የሰው ስም ይሁን አላወቅንም” [ገጽ 102] የሚሉ ቅዱሳን ወ/ዊ ገብሩ ወልዱን አግኝተው እንደ ጠየቁትና የሰው ስም ነው ባላቸው ጊዜ ለገርቦሌ በሰዓቱ የሚያስፈልገውን እንደ ላኩለት መስማት፣ ለካንስ እግዚአብሔር ያለ እኔም ታላቁን ሥራውን ይሠራል “የማልጠቅም ባርያ ነኝ” እንድንል ያስገድደናል።

ወንጌል ደግሞ ለነፍስ ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊ ጉዳዮች መፍትሔ ሰጭ እንደ ሆነ የተለያዩ ሕያው ማስረጃዎች ቀርበውልናል። በአሙሩና በጎጃም መንደሮች በአጋንንት የታሠሩ በኑሮአቸው የከሰሩ፣ ለጣዖታት ለሙታን ይሰግዱ ይሠው የነበሩ፣ በክርስቶስ ስም ኃይል ነጻ ወጥተው ለራሳቸውና ለአገር ታማኞችና ጠቃሚዎች ሆነዋል። የክርስቶስን ወንጌል የተቀበሉ የተለየ ሕዝብ ናቸውና፣ ከበጉ ደምና ከምስክራቸው ቃል የተነሳ ብርሃን ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስና ወደ መንግሥቱ ሌሎችን ያፈልሳሉ።

ከተወለደበት መንደር ከኢበንቱ ጀምሮ ጌታውን በብዙ መስዋእትና በታማኝነት በማገልገል ላይ ስላለ የእግዚአብሔር ሰው ስለ ገርቦሌ ሂርጳ። ጉንዳኖችን ማን ፈጠራቸው? ተራሮችን ማን ሠራቸው? እያለ በልጅ አንደበት እየጠየቀ ጌታ እንዴት ራሱን እንደገለጠለት፤ የአገልግሎት ምሪት ስለ መቀበል፣ ከእህት አዳነች ቶሌራ ጋር እንዴት እንደ ተጋቡና በአገልግሎት ውስጥ ያሳለፉትንና ያዩትን የተአምራት ኑሮ፤ ስለ መንፈሳዊ ውጊያ፣ ከውስጥና ከውጭ ስለ ደረሰበት ተቃውሞና ጌታ ስለ ሰጠው ድል፤ በማጣትና በማግኘት በመራብና በመጦም በስደትና በሐዘን ጌታን በጽናት ስለ ማገልገል። ምንም በሌለበት ሁሉ አለኝ ማለት መቻል፤ ያም የጌታ መገኘት ምሥጢር እንደ ሆነ፤ ያም እንደማያሳፍር የእርግጠኛነትን መንገድ እንደሚያስጉዝ። መስጠት እንደማያጎድል፤ ጥንቃቄ እንደሚጠብቅ፤ እግዚአብሔር የሚሰማው ጸሎት። መታዘዝ፣ መቀደስና ፍሬአማ የኃይል ሥራ፣ ይቅር ማለትና ሌላው ከኔ ይሻላል ማለት እንደማይነጣጠሉ። ሰውን መፍራት ወጥመድ ስለ መሆኑ፤ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሚያድን። የማይመረመረውን የእግዚአብሔርን ሥራ፣ ጥበብና ጥበቃ ከጎጃም ወለጋ፣ ከወለጋ ጎጃም፣ ከወለጋ ሸዋ፣ ከሸዋ ሲዳሞ፣ ወዘተ፤ ከሸዋ አውሮጳና አሜሪካ ወደ ዓለም ሁሉ።

እግዚአብሔር ዛሬም እንደ ሐዋርያት ዘመን ይሠራል። ዛሬም በሚታመኑትና በሚታዘዙት እጅ የኃይል ሥራውን ያከናውናል፤ ዘመናትንና መንግሥታትን ይሽራል፤ እርሱ ብቻ የማይሻር የዘላለም መንግሥት አለው። ሰው ይህን አምላክ በዚህ መልኩ ሲያውቀውና አብዝቶ ሲጠጋጋው በሰዎች መካከል የሚለዩ ሰው-ሠራሽ ድንበሮች እንደ ጭስ በነው ይወገዳሉ። “ለወገኔ ይጠቅማል” ማለት ሥፍራ አይኖረውም፤ ለረብና ለዝና መሮጥ ሥፍራ ይለቃሉ። የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ የዲያብሎስን፣ የኃጢአትንና የሞትን ኃይል ሊያፈርስ ተገለጠ፤ “በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው [አ]ፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ” ነው [1ኛ ዮሐ 3፡9። ኤፌ 2፡14-15]። ይኸን ዓይነት ወንጌል እነ ጳውሎስና ጴጥሮስ ሰብከው አልፈዋል። ዛሬም ለመንፈስ ቅዱስ በተገዙት እጅ የሚሰበከው ይኸው ወንጌል ነው። 

ገርቦሌ፦ “የእግዚአብሔር ሥራ የአንድ ሰው ሥራ አይደለም። የብዙዎች አስተዋጽዖ ውጤት ነው። የእግዚአብሔር ቤት የአስተዋጽዖ ቤት ነው። የእኔ በጌታ መቆምና ማገልገል የእነርሱ ድካም ውጤት ነው። ደግሞም የኔም ብቻ አይደለም። ከዚያ በኋላ ለተገለጠው ታላቅ የእግዚአብሔር ሥራና የአብያተክርስቲያናት ማደግ የዚያን ዘመን ወገኖች እንባ ውጤት ነው። ያን ጊዜ ዋነኛው የጸሎት ርዕስ የሰዎች መዳን የጌታ መንፈስ መፍሰስና ዳግም ምጽኣት ነበሩ። የጌታ መመለስ ትልቅ ናፍቆታችን ነበር። ሰው ሲገናኝ ሰላምታ ከተለዋወጠ በኋላ ‘አይዞህ ጌታ ይመጣል’ በመባባል እርስ በርሱ ይጽናና ነበር። የዚያን ጊዜውን መንፈሳዊ ሕይወት ከዛሬው ጋር ስናስተያይ ያን ጊዜ መታዘዝና መስማማት ተነጋግሮ መግባባት እግዚአብሔርን መፍራት ነበር። ዛሬ እግዚአብሔርን መፍራት የለም። ያኔ ቅርብ የነበረው እግዚአብሔር ዛሬ ርቋል። ክብሩም በመካከላችን የለም። ሰው ቢበዳደል እንኳ ጥፋቱ የኔ ነው በማለት ሰላም ፈላጊው በራሱ ላይ ፈርዶ ይቅርታ ይጠያየቁ ነበር። ዛሬ ድፍረት አለ። እኔ ጥፋተኛ ነኝ የሚል የለም። ቢያጠፋ እንኳ ንስሃ ገብቶ የተበደለውን ይቅርታ ለመጠየቅ ይከራከራል። በደልን ይቆጥራል። ያኔ ሰው በወንድሙ ውድቀት ያዝናል፤ ጌታ ሆይ፣ አስበው ይቅር በለው ወደ ልቡ መልሰው እያለ ይማልዳል፣ ያለቅሳል። ዛሬ ግን ሰው በወንድሙ ውድቀት ይስቃል፤ ወሬውንም በከፍተኛ ፍጥነት ያዳርሳል። ስለ ወንድሙ አይገደውም። እግዚአብሔር ስለ ደከመው [ወንድም] እንደሚገደው ሊገደን ይገባል። ጥንት እርስ በርስ መፈላለግ ነበር። ዛሬ ግን ሰው አንዱ ካንዱ ይሸሻል፤ ፊቱን አዙሮ ያልፋል። አገልግሎትም በምሪት ነበር። አሁን ግን በሥጋ ምርጫ በመሆኑ ኃይል ጠፋ፤ ቃሉና ጸሎት ቁልፍ ሥልጣን ሆነው ሳሉ ወደ ጎን ተትዋል። ንስሃ የማይገባው፣ እርካታ የሌለው ከዓለም ጋር የተዳበለው ብድራቱን የረሳው የጌታን አደራ የናቀው በኃጢአት የተዋጠው የዚህ ዘመን ክርስቲያን ሊመለስ ይገባዋል። አለበለዚያ ግን በፍጻሜው ይጎዳል። ጌታ ይባርካችሁ እምነትንም ይስጣችሁ!” [ከመጽሐፉ፣ ገጽ 184-186]

የቤተክርስቲያን መሪዎች እንዳይያያዙ በታትኖ የያዛቸውን ኃይል ለይቶ ማወቅና አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ጌታን እንድናመሰግንና ራሳችንን እንድናይበት ይህን ጠቃሚ መጽሐፍ ያዘጋጀውን ወንድም ደረጀ በቀለን እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርከው። የገርቦሌን የሕይወትና የአገልግሎት ታሪክ ከማውሳት በተጨማሪ ስለ ገርቦሌ የሌሎችን ምስክርነት ማካተቱ ጥሩ አቀራረብ ሆኖ አግኝተነዋል። ተራኪው በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ሁለት ዋነኛ ጉዳዮችን እንዲህ አስፍሯቸዋል። አንደኛ፣ “በእግዚአብሔር ጸጋ ለቆዳችን ርጥበትና ውበት እንዳንጨምር … ጸጋችንን ለገበያ ላቀረብን ሁሉ ማስጠንቀቂያ” ይሁነን የሚል። ሁለተኛው፣ “እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው ሰዎች ታሪክ የመጻፍ ልምድ ቢዳብር” ለትውልድ ይጠቅማል የሚል። የገርቦሌ ሂርጳ “የሕይወትና የአገልግሎት ታሪክ” በተለይ ላለንበት ዘመን አስቸኳይ መልእክት አለው። የምንጨምረው፣ በሌሎች በረቶች ባሉ ዘንድ የጌታ ኃይል ሥራ እንዲመሰገን መጽሐፉ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲተረጎም የሥራው ባለቤት ይርዳ የሚል ነው። በተረፈ፣ “ታላቅ” መባል በማያሳፍርበትና መኮረጅ በበዛበት ዘመን ጌታ በሠራው ሰው ሲመሰገንና ሲገን እንዳይገኝ እግዚአብሔር ልቡና ይስጥ።