truework3በጥሩወርቅ መስፍን፤ 2004 ዓ.ም፤ 15ዶላር፤ 232ገጽ፤ ገምጋሚ፦ምትኩ አዲሱ

ግለ ታሪክ በሁለት መንገድ ይጻፋል፦ አንድ፣ ባለ ታሪኩ የሚጽፈው ነው። ሁለት፣ ወክሎ ወይም ሳይወክል ሌላ ሰው የሚጽፈው ነው። መጋቢ ጥሩወርቅ መስፍን “በመሪዬ እጅ” የተሰኘ “በአጠቃላይ ታሪኳን በአጭሩ የሚገልጽ” መጽሐፍ አቅርባልናለች [ገጽ7]። ለመጻፍ የተነሳሳችው “ለምን ስለ ራስሽ አትጽፊም?” የሚሏት ስለ በረከቱና “ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው የምጽፈው? የሚጻፍ ታሪክ ያለኝ መስሎአቸው እኮ ነው!” ስትል ቆይታ ኋላ የእግዚአብሔር ምሪት መሆኑን በመረዳቷ ነው [ገጽ 209-211]።

አንባቢም እንደ ደራሲ ራሱን ይጠይቃል? ለምንድነው ይህን መጽሐፍ ለማንበብ ጊዜና ገንዘብ የማጠፋው? የተራኪውን ሕይወት ልዩ የሚያደርገው ምንድነው? እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በመጠየቁ አንዳች የሚጠቅም ነገር አገኛለሁ ብሎ ተስፋ ያደርጋል። እያንዳንዱ ሰው መጽሐፍ ነው። በአነጋገሩ፣ በአኗኗሩ፣ በሚይዛቸው ባልንጀሮች ዓይነት የሚነበብ ግልጥ መጽሐፍ ነው። ደግሞም የተሰወረ ክፍል አለውና ዝግ መጽሐፍ ነው። የሰው ሕይወትና ጉዞ ይመሳሰላል ብንልም መድገም የማያሻው ፈጣሪ ልዩ ልዩ አድርጎ ፈጥሮናል። የመጋቢ ጥሩወርቅን ታሪክ ልዩ የሚያደርገው በውሳኔ ምርጫዋና በእግዚአብሔር ምሪት ሌላው ሰው ያልተረማመደበትን ጎዳና መጓዟና ይህንኑ በራስዋ ብዕር መግለጧ ነው።

ሌላም ጥያቄ አለ። ሰዎች ለምን የግል ታሪካቸውን ይጽፋሉ? መጋቢ ጥሩወርቅ ‘እጄን ይዞ መራኝ ጌታዬ’ “ታሪኬ እግዚአብሔር የሠራው ታሪክ ነው” ስትል ምክንያቷን ገልጻለች [ገጽ 7]። ሰዎች በአብዛኛው ታሪካቸውን የሚጽፉት ሀ/ የሰው ሕይወት፣ ዘመን በሚያመጣውና በሚያሳልፈው የሚለካ እንደ መሆኑ፣ ቅርስ ለመተው ለ/ ስለ ራሳቸው በሌሎች ዘንድ የታወቀውን ለማጽናት ወይም ለማቃናት መ/ ለሌሎች ትምህርት [ገጽ 8]፤ አንዳንዶችም በታሪክ ውስጥ ቦታ ለማግኘት ይጠቀሙበታል። ባጭሩ፣ ደራሲው አስቦበት ይሁን ሳያስበው ባነሳቸው ጉዳዮች ላይ አንባቢው ለመወያየት ዕድል ያገኛል ማለት ነው።

የመጋቢ ጥሩወርቅ ታሪክ የወላጆቿን ጨምሮ ከመቶ ዓመት ባላነሰ ዘመናዊውን የአገራችንና የወንጌላዉያን አብያተ ክርስቲያናትን ታሪክ ይወክላል ማለት ይቻላል። ኮሰበር እንጅባራ ከመባሉ አስቀድሞ። የጣሊያን ወረራና ነጻነት፤ አፄ ኃይለሥላሴ ከስደት መልስ በትውልድ መንደሯ በኩል ማለፋቸው። የቤተ ክህነት ሰው፣ አርበኛና ገጣሚ አባቷ። ኢትዮጵያዊነትን በልጆቻቸው ውስጥ ተግተው ያሥጸረሱ አባቷ። ሴት ልጅ መማር እንዳለባት የተረዱ ከዘመኑ ቀድመው ያሰቡ እናቷ። 12 ወልደው ለቁምነገር ያበቁ ወላጆቿ። ለክርስቶስ እውነት ልባቸው የተከፈተ ወላጆቿ። [የወንድ አያቶቿ ስም እምሩ መባሉ ፈገግ ያስብላል (ገጽ 9፣10)፦ የአቶ እምሩ ልጅ የአቶ እምሩን ልጅ አገቡ!] የመንፈስ ቅዱስ እሳት በምድራችን ካያያዛቸው የመጀመሪያዎቹ ወጣት አማንያን፤ በእምነት ምክንያት መታሠርና መሰደድ፤ አብዮት፤ በየምድሩ ጥግ የተበተነው የአገራችን ሕዝብ፤ መፈናቀል ያላለዘበው የዕድሜ ልክ ወዳጅነት፤ “በመሪዬ እጅ” ያልነካው የታሪክ ምዕራፍ የለም።

ማኅበራዊ እውነታን ያላገናዘበ፣ ራሱን ያገለለ ወንጌል እውነተኛ ወንጌል ሊሆን አይችልም። አማንያን ከራሳቸው ክልልና “መንፈሳዊ” ቋንቋ ወጣ ማለት ሲያቅታቸው፣ ቋንቋቸው ለዓለም ባእድ ሲሆን ለወንጌል ተልእኮ ዕንቅፋት መፍጠሩ አይቀርም። ይህም ሆኖ፣ ዛሬም መንፈስ ቅዱስ ይሠራል፤ በክርስቶስ ሕጻናት የነበሩ አድገው የቤተክርስቲያን መሪዎች ሆነዋል። በአንጻሩ ዛሬም ሴቶች በስምንት ዓመታቸው ይዳራሉ፣ የአገራችን የትምህርት ፖሊሲ የተዘበራረቀና በሙከራ ላይ የሚገኝ፤ ካለፈው መማር እንዳቃተው ነው፣ ወዘተ። መምህር በተማሪው ላይ የሚያሳድረው ዘላቂ ተጽእኖ። የኦርቶዶክስ እምነትና ወንጌል አማኞች መሠረታቸው አንድ ስለ መሆኑ። ደራሲዋ እደ ማርያም ትምህርት ቤት ሆና ከቤተሰቦቿ ይዛ የመጣችውን የኦርቶዶክስ እምነትና ስነ ምግባር በሚገባ ስለ መጠበቋ። “በመጨረሻ እንደምጸድቅ እንዴት አውቃለሁ? የምከተለው እምነት ትክክለኛው መሆኑንስ እንዴት አውቃለሁ?” ለሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ መሻትና፣ ይበልጥ ለመረዳት በራሷ ወንጌል ማንበብ እንደ ጀመረች [ገጽ 22፣ 24]። ወንጌላዉያን የእምነት መሠረታቸውን አለማወቃቸውና ችላ ማለታቸው። አባቷ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ማልደው ዳዊት መድገማቸው በርሷ ሕይወት ላይ ያሳደረው በጎ ተጽዕኖ [ገጽ 9]። የኦርቶዶክስ አማንያን ወንጌልን ማመን እምነትን ማጽናት እንጂ እምነትን መቀየር አለመሆኑን አለመገንዘባቸው። በክርስቶስ የምንጋራቸውን የሚንዱ አካሄዶችን ከሁለቱም ወገን እንመለከታለን። ባጭሩ፣ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እናት ሆና እንደማቀፍ የገዛ ልጆቿን በማሳደዷ ቅርሷን መበተኗ፣ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የወንጌልን ትምህርት እንደሚገባ አለማወቅ እንደ ሆነ ማየት ይቻላል።   

“በመሪዬ እጅ” በጣም ተነባቢና ትረካው የማይሰለች ሆኖ በሃያ አንድ አጫጭር ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። በሌሎች መጽሐፎች ላይ ያሰለቹ የፊደላት ግድፈትና ያለቦታቸው ሳያስፈልጉ የሚሸነቆሩ የእንግሊዝኛ ቃላት እምብዛም አይታዩም። የመጽሐፉ ይዘት በአንድ ፊት እንግዳ ሲመጣ የሚጋብዙት የቤተሰብ አልበም ይመስላል፦ “ይኸ በሥራ ዓለም የተዋወቅነው ነው፣ ይችን ረስቻታለሁ፤ ይኸ ፊቱ እንጂ ስሙ ተዘንግቶኛል” የሚባልለት አልበም ይመስላል። በአልበሙ ከተካተቱት አብዛኛዎቹ ከአንድ አካባቢና ከአንድ ቤተ ክርስቲያን መሆናቸው የኢትዮጵያዉያንን በቀዬ የመካለል ዝንባሌ አጉልቶታል። የወራሪ ጠላት ስሜትና የሚሲዮናዉያን ተጽእኖ ይሆን? [ከነጸሎቱ፣ “ጠላት አታሳጣኝ” ይላል።] ግለኛነት በበረታበት በዚህ ዘመን ሰው-ሠራሽ ግድግዳዎችን ለማፍረስና አማንያንን ለማቀራረብ ቤተ ክርስቲያን አሠራሯን እንዴት ትቀይስ? የጠራ ምስክርነት፣ ስደትና እስራት ባለበት መካለል እንደሚቀንስ ማሰብ የክርስቲያን ማኅበራትን ለማቀራረብ ጅማሬ ይሆናል እንላለን [የሐዋ ሥራ 8፤ 2ጢሞ 3፡12]። የመጽሐፉ ይዘት የስንብት ወይም የምስጋና ደብዳቤም ይመስላል። በስልክ የሚነጋገሩ ሰዎችንም ይመስላል፤ የአንደኛው ንግግር አጠገቡ ለቆመው ይሰማል፤ የሌላኛውን ግን በግምት ካልሆነ ለይቶ ማወቅ ያዳግታል፤ ወይም በወዲያ በኩል ያለው ጮኽ ስላለ የሚናገረው በከፊል ይሰማል እንበል።

መጋቢ ጥሩወርቅ ገልጻ ካሠፈረቻቸው ሌላ፣ ገልጻ ያላሠፈረቻቸው እንደ ኋለኛው ስልከኛ በከፊል መሰማቱ አልቀረም። ጀምራ እልባት ያልሰጠቻቸው በእንጥልጥል የተወቻቸው አሳቦች አሉ። “ሰው የራሱን ታሪክ ሲጽፍ አስቸጋሪ ሆኖ ያገኘሁት ጉዳይ ታሪካችን ከሌሎች ሰዎች ጋር የተገናኘ ስለሆነ ከሌሎች በኩል ያለውን በትክክል መረዳት አለመቻሉ ነው። ስለሆነም የሰዎችን ስም እየጠቀሱ መጻፍ ደስ የሚያሰኘውን ያህል አስፈሪም ነው” ትላለች [ገጽ 211]። የሰው ታሪክማ በተለይ ባለንበት ዘመን ድንበርና ባሕል ዘለል ሆኗል። ደራሲዋ ታሪኬ “እግዚአብሔር የሠራው ታሪክ” ነው ካለች ግን ከእግዚአብሔር ምሪት ጋር በተገናኘና በቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ የሌሎችን ፈቃድ መጠየቅ ወይም መስጋት ባላስፈለጋት ነበር። መጽሐፍ መጻፍ አድካሚ ብቻ ሳይሆን የሚያስጠይቅም ነው። የሚያስጠይቀው በጽሑፍ የሠፈረው ብቻ ሳይሆን ሊጻፍ ሲገባ ስለ ተተወው ጭምር ነው። በሌላ አነጋገር፣ በይሉኝታ መገታቷን ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም። በተገኘው አጋጣሚ ተጠቅማ በዓይነተኛ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ በግልጽ አለመተረኳ የመጽሐፉ ዋነኛ ድክመት ነው። ለትምህርት እንዲሆን ከተፈለገ፣ “በታማኝነት … ማንንም ዝቅ ለማድረግ ወይም ለማሞገስ” እስካልሆነ [ገጽ 211] በሌላው ወገን ያሉትም የራሳቸውን መረዳት በመግለጻቸው ለመማማር በር በከፈተ ነበር። እስቲ በእንጥልጥል ከተተውት ሦስቱን እንጥቀሳቸው፦   

ሀ/ ሴት መጋቢን በተመለከተ [ገጽ 194-199]። “በእኔ ያለውን የአገልግሎት ጸጋ ቤተ ክርስቲያን መዝናና ፍሬዬንም ተመልክታ በፓስተርነት እንድትሾመኝ ጠየቅሁ” [ገጽ 195]። ቤተ ክርስቲያን እስክትጠየቅ ለምን ተጠበቀ? በወቅቱ የነበሩት መሪዎች ጸጋዋን መለየት ስላልቻሉ ነው? መጋቢ ጥሩወርቅ ጥሪውን በዩኒቨርሲቲ ሳለሁ ተቀበልሁት ማለቷ ሌላውም [ወንድ ይሁን ሴት] እንደዚሁ ጥሪ አለኝ ቢል ማረጋገጫው መንገድ ምን ሊሆን ኖሯል? የእግዚአብሔር ቃል በዚህ ጉዳይ ላይ  ምን ይላል? የሚለው በቂና አሳማኝ ምላሽ አልተሰጠውም።

ለ/ የዶ/ር ኃይሌ ወልደሚካኤል፣ የመጋቢ ባደግ፣ የመጋቢ አሳየኸኝ መልቀቅ ምክንያቱ ሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕይወት ላይ የፈጠረው ጫና ቢኖር፣ በአገልግሎታቸው ወቅት የነበረው ሁኔታና የታየው ውጤት በከፊልም ቢሆን አልተጠቀሰም። መጋቢ ጥሩወርቅ ከላይ ከተጠቀሱት አገልጋዮች ይልቅ ለረጅም ዓመታት [22 ዓመታት] በሎስ አንጀሊስ ቤተ ክርስቲያን በመሪነት እንደ መቆየቷ በአገልግሎቱ ዙሪያ የነበረውን ውጣ ውረድ፣ አስተዳደራዊ አሠራሮችና ልምዶችን በጥንቃቄ ማስፈርና ማስረዳት ነበረባት። የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ታሪኳም ነውና።

ሠ/ ከተለያዩ የአምልኮ ልምዶች [ሙሉ ወንጌል፣ መሠረተ ክርስቶስ፣ መካነ ኢየሱስ፣ ወዘተ] የተሰባሰበን ማኅበር መምራት ያስከተለው ችግር ተጠቅሶአል። ችግሩ የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ችግር ነው ቢባልም በሎስ አንጀሊስ አጥቢያ ለዚህ ያገኙት መፍትሔ እንደሚገባ አልተብራራም። እነዚህ ለናሙና የጠቀስናቸው ነጥቦች በዋነኛነት መወያያ መሆን ሲገባቸው ያመለጡ አጋጣሚዎች ሆነው አግኝተናቸዋል። ደራሲዋ የተነሳችበት ዓላማ ይኸ አልነበረም እንዳንል፣ “ካነሳሁ ዘንድ” “ወደ ቀደመው ሃሳብ ልመለስና” ብላ ከጀመረችው አሳብ በመውጣት ያገናዘበቻቸው ሌሎች ምሳሌዎች ያግዱናል [ለምሳሌ፣ ገጽ 107፣ 109]።

አጠቃላይ ትዝብት። ከግለኛነት ይልቅ ማኅበራዊ ግንኙነቶች እንዲዳብሩና አገራዊነት ባልተገራ ባእድ አመለካከት እንዳይሸረሸር የቤተ ክርስቲያንና የአማንያን ኃላፊነትና ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል? መጋቢ ጥሩወርቅ መስፍን ጀማሪ ክርስቲያን ከነበረችበት ዘመን አንስቶ የወንጌላዉያን አብያተ ክርስቲያናት ዋነኛና ያልረገበ ችግር ከቀዬአቸው አልፈው ግልጽ አቋም የሚወስዱና የሚደመጡ መሪዎች መጥፋት እንደ ሆነ እንገነዘባለን። ግልጽ ከሆነ መተዳደርያ ደንብና መዋቅር ይልቅ ለሥርዓት የማይገዛ የግል አመለካከትና ግብታዊነት ሲሠለጥን ይታያል። ሥርዓት የመንፈሳዊነት መጉደል እንደ ሆነ፤ በአንጻሩ ሥርዓተ አልበኝነትን መንፈሳዊ “ነጻነት” ለማሰኘት የሚደረጉ ሙከራዎች ይታያሉ። ይህ አስተሳሰብና ልምድ ምዕመኑን ተመልካች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ አስተምህሮና ያሳለፈችውን ታሪኳን ባለማሳወቁ በጎ ያልሆነ ተጽእኖ አሳድሯል። በዚሁ ድረ-ገጽ ደጋግመን እንዳሳሰብን የአገልግሎት መልክ ተለውጦ ንግድ መስሏል። “አገልግሎትን በገንዘብ ልክ መዋዋል ተጀምሯል” [ገጽ 144]። “መዋዋል” መግባባትና ማግባባትን ብቻ ሳይሆን ገበያው እንዲደራ ማመቻቸትን ይጨምራል። ማመቻቸት የወንጌልን እውነት ለሰሚው ጆሮ እንዲስማማ መከለስን ይጠቁማል። ዘመደ-ብዙ ወይን ጠጁ ቀጭን ነው። ተዘዋዋሪ አገልጋዮች ያገለገሉበት አጥቢያና ያስተማሩትን ትምህርት ተከታትሎ ሪፖርት ማድረግ  አንዱ ጋ የታየው ችግር እንዳይደገም ይረዳ ይሆን? ሌላው ጉዳይ፣ ወንድ መሆን የማያስጠይቀውን ያህል ሴት ሲኾን አበሳ ማስነሳቱ ለሴቶች የሚሰጠውን ዝቅተኛ አመለካከት እድሜ አራዝሞታል።

በተለይ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ሰዓት አያከብሩም [ገጽ 154-5]። የሥራ ሰዓት ያከብራሉ፤ የቤተክርስቲያን ሰዓት አያከብሩም። ይኸም አማንያን ለእግዚአብሔር ያላቸውን አክብሮትና የሕይወታቸውን ዓይነት የሚያሳይ ነው። የካሊፎርንያ ገዥ ወይም ፍርድ ቤት ወይም ሐኪም ቀጠሮ ቢሰጠን ግን በሰዓት ለመገኘት እንቅልፍ እንዳያሸንፈን የማናደርገው የለም። በሰዓት መገኘትን ለማበረታታት ቤተ ክርስቲያንም ጠንቃቃና መልካም ምስክርነት ያላቸው መሪዎችን የማሠልጠንና መድረኩን የማስከበር ኃላፊነቷን መወጣት ይኖርባታል። የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ በአገራችን በተቀጣጠለበት በደርግ ዘመን በ12 ሰዓት ለሚጀመር ስብሰባ የያዘውን ጥሎ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ሰው መጉረፍ ይጀምር ነበር። ማለዳ ለሚካሄድ ጸሎትና ስብከት ሰዓት እላፊ ሳይፈሩ ከ10 ሰዓት ጀምሮ በእግር ከተማውን አቋርጠው የሚጓዙ አያሌ ነበሩ። መስዋእት ሳይከፈል የሚሆን ነገር የለም። የምንከፍለው መስዋእት ለዚያ ለምንፈልገው ነገር ወይም ለዚያ ሰው የምንሰጠውን አክብሮት ያመለክታል።  

በምዕራፍ 21 “ስለ ወደ ፊቱ ሳስብ” በሚል ርዕስ ሥር ደራሲዋ እግዚአብሔር በሕልም ያሳያትን ጠቅሳለች። የወደ ፊቱ ነገር ሁላችንን የሚያሳስበን፣ በራሳችን ሳይሆን በእግዚአብሔር ተስፋ እንድናደርግና እርስ በርስ እንድንጸልይ የሚጠይቅ ነው። ለእህታችንም መጸለይ አንዱ ግዴታችን ነው። የቃሉ መካከለኛነት በተዛነፈበትና አምልኮ ትርኢት በሆነበት በዚህ ወቅት በግልና በቡድን የቃሉን አጠናን ዘዴ በማስተማር ያካበተችውን ጸጋዋን እንድታካፍል አብያተ ክርስቲያናት የአገልግሎት በር ሊከፍቱላት ይገባል። የመጋቢ ጥሩወርቅ ታሪክ በአንድ መልኩ የሁላችን ታሪክ ነው፤ የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ታሪክ ነው። የቤቱ ጉድለት ለሁላችን ጉድለት ነው፤ የቤቱም ልማት ደስታችን ነው። የያኔ ተማሪዎች ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የአገርም መሪዎች መሆናቸው ጌታን መከተልና ማገልገል ወደ ኋላ እንደማያስቀር ሕያው ምስክር ነው። “እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና” [ዕብራዉያን 6፡10]። ታሪካችንን ማወቅና የማሳወቅ ግዴታ አለብን። እህቶች ይጻፉ። በ “በመሪዬ እጅ” ውስጥ በተካተቱትና በጠቀስናቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቱ ይቀጥል። ሁሉ በፍቅር ይሁን። ሁሉ ለማነጽ ይሁን። ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን።