ቤት ያጣው ቤተኛ ወደ ቤት ይመለስ
ሕንጸት/ኪያ “ዘፈን ፓነል ውይይት" ክፍል 1 እና 2 ግምገማ

gorfe4የወንድም ዮናስ ጎርፌ “ቤት ያጣው ቤተኛ” የቀሰቀሰው “ጦርነት” ለጊዜው ጋብ ያለ ይመስላል። “ጦርነቱ” ለመማማር አልጠቀመም አንልም። በቲፎዞ ክስ የቆሰሉ አሉ። በሙገሳ ፍላጻ የቆሰሉ አሉ። ተንዛዛ፣ ተካረረ፣ ተጋነነ ያሉ አሉ። ግራ የተጋቡ አሉ። በእንጥልጥል የተተው ጥያቄዎችስ ይኖሩ ይሆን? የመድረኩ አስተባባሪዎች ለምን ከታዳሚ ቢያንስ ሁለት ጥያቄዎችን ወይም አስተያየቶችን አላስተናገዱም? ወይስ ቅጂው ኤዲት ሲደረግ ከመክፈቻ ጸሎት ጋር ተቆርጦ ወጥቶ ነው?

ሕንጸትና ኪያ ያስተባበሩት የሠለጠነ ዝግጅት አብሮ የመሥራትን ባህል የሚያጎለብት ያማረ ዝግጅት ነበር። ስለዚህ ሊመሰገኑ ይገባል። ወንድም ሚክያስ አበበ በመግቢያው ላይ ያቀረበው ሐተታ ሁለገብ፣ ግልጽና ጉዳዩን መጥኖ በመዳሰስ ፈር ያስያዘ ነበር። እርሱም ይመስገን። በተሳታፊ ወንድሞች ሰለሞን ከበደ፣ ዮናስ ጎርፌ፣ ሰለሞን አበበ፣ ንጉሤ ቡልቻ እና በታዳሚው ዘንድ የታየው ጨዋነት በዓለም ላሉቱ ጭምር ትምህርት ሰጭ ነበር። ይመስገኑ። የሕዝቡ ባለቤት እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን።

ዝግጅቱ እሳት የማዳፈን ዓላማም ነበረው። ርዕሱ “ዘፈን” መባሉ እና በዩቱብ ማስተዋወቂያ “አስከትሎቱ ምንድነው፣ እስካሁንስ አላስከተለም ወይ?” አባባል አዝማሚያውን ከመነሻው ጠቁሞናል። “ቤት ያጣው ቤተኛ” ሳይቆነጸል በምልዓቱ ቢሞገት ኖሮ ምን ልዩነት ያመጣ ነበር? [“ሙዚቃ፣ ሙዚቀኛነትና ኢትዮጵያዊቷ ቤተ ክርስቲያን” የመጽሐፉ ቀጣይ ርዕስ እንደሆነ አንርሳ።] መጽሐፉ ታትሞ አንባቢ እጅ መግባቱ፣ በማኅበራዊ ሚድያ በፍጥነት መሠራጨቱ፣ ብቃት ባላቸው፣ ብዙኃኑ በሚረዳው ቋንቋ በጊዜ አለመገምገሙ ጉዳዩን አወሳስቦታል። ይኸ ሁኔታ ወደፊት እንዳይደገም ምን ጥንቃቄ ይወሰድ?

የ“ቤት ያጣው ቤተኛ” ውይይት ሁለት የተካረሩ ጠቃሚ አመለካከቶችን ሳያገናዝብና ሳያቀራርብ ቀርቷል። የወንድም ዮናስ ሙግት ከሞላ ጎደል ምሑራዊ በመሆኑ። በአንጻሩ፣ በተለይ በወንድም ንጉሤና በአዘጋጆች የተንጸባረቀው “መጋቢያዊ” በመሆኑ። መጋቢያዊነትና ምሑራዊነት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ባንድነት አለመገኘቱ [ኤፌሶን 1፡8፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 14፡20]። “መጋቢያዊ” መንጋውን እያሰበ “አስከትሎቱ ምንድነው?” ይላል። ከመስጋት የተነሳ ይመስላል በዚህ ወቅት ልኩን የማዘግየት ሁኔታ ታይቷል። ለምሳሌ፣ በገላትያ 5፡21፣ ሮሜ 13፡13 እና 1ኛ ጴጥሮስ 4፡3 የተጠቀሱት ቃላት መሠረታዊ ልዩነት የላቸውም። ጳውሎስ በአቴና ውብ ሕንጻዎች ውስጥ የተጎለቱትን ጣዖታት በመንፈሱ ተመልክቶ ተበሳጭቷል [የሐዋ ሥራ17፡16]፤ የሕንጻዎቹን ግዙፍ አዕማድ ጠቅሶ የሕያው እግዚአብሔር ቤት “የእውነት ዓምድና መሠረት” ነው የሚል ትምህርትም አስተምሮበታል [1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15]። “መጋቢያዊ” በተገኘ አጋጣሚ “ቀጥተኛ” ትምህርት መስጠትን ይመርጣል። ምሑራዊነት የተነሳበትን ግብ ብቻ ያስባል፤ መረጃ ይዣለሁ፣ መረጃዬ ወደ መራኝ እሄዳለሁ ይላል። ምሑራዊነት የግለሰብን ውስጣዊ አቋም በሙላት ያንጸባርቃል ማለት አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ የምሑር አቅም በሰበሰባቸው መረጃዎች መጠን፣ ዓይነት፣ አደረጃጀትና አተረጓጎም ይወሰናል፤ የሚገደው የቢጤዎቹ አቅም እንጂ የ “ሰፊው ሕዝብ” አቅም አይደለም። ይኸ መረዳት በሁሉም ዘንድ ግልጽ የሆነ አይመስልም።

ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ጥበብ እና ባህል የሠለጠነ ሆኖ፣ ለተማሩና ላልተማሩ፣ ላመኑና ላላመኑ መልእክቱን አስተካክሎ ያቀርብ ነበር፤ የተሸከመውን መልእክት ክቡርነት ተረድቶ የመግለጥ ጸጋ እንዲሰጠኝ ጸልዩልኝ አለ [ቆላስይስ 4:4]። ተልዕኮውን ለመፈጸም “ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ህግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ” አለ [1ኛ ቆሮንቶስ 9፡19-23]። ወንድም ዮናስ በመጽሐፉ ሁለተኛ ዕትም ላይ አንዳንዶቹን ነጥቦች እንዳያሻሙ አድርጎ እንደሚያቀልልና እንደሚያብራራቸው ቃል የገባው ይህን በማሰብ ይሆን? ለመታረም መፍቀድ ትህትና ብቻ ሳይሆን ምሑራዊ ስነ ምግባርም ነው።

የሙግቶቹ አቅጣጫ ሁለት ነው ብለናል። የመጀመሪያው ሙግት “ያበጠ ይፈንዳ” ሲል፤ ሁለተኛው፣ ፈንጂ የሚያስከትለውን ጉዳት መገመት ስለማይቻል በ “ድጥ ላይ ውኃ እንደማፍሰስ” እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ ይላል። የምንገኝበት ዓለም ድጥ መሆኑ ከታመነ ግን፣ ድጥ ላይ ለመረማመድ ስልቱ ምንድነው የሚለውን አብሮ ማሳሰቡ አይቀርም።

በፈንጂው ጭስና ጭጋግ፣ ሁለቱ ወገኖች የሚጋሩትም እንዳለ ማየትና መተያየት እንዳይዘነጉ። ሁለቱም፣ የሙዚቃ ትምህርት ምሩቃኑ ከቤተክርስቲያን ውጭ መሆን አሳስቧቸዋአል፤ ወደ ቤተክርስቲያን እንመልሳቸው ብለዋል። ቤተክርስቲያንን ስለ ማነጽ እና ሥልጣኗን ይገነዘባሉ። ምሩቃኑ ከቤተክርስቲያን ለወጡበት ምክንያት ግን ሁለቱም የተለያየ መልስ አላቸው። አንደኛው፣ የወንድም ዮናስ ጎርፌ መጽሐፍ ችግሩን እንደቀሰቀሰና እንዳባባሰ ሲመሰክር፣ ሌላኛው፣ ችግሩ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በ “እውነትና በፍቅር” ባልተፈተሸ ትውፊት መታሠር ነው ብሎታል። ሁለቱም ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ የየአገራቱን ትውፊት በማስረጃነት አቅርበዋል፤ ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር መደረግ አለበት ብለዋል። የቤቱ ባለቤት እግዚአብሔር እንደሆነ፣ ግራጫ የሆኑ ጉዳዮችም እንዳሉ አምነዋል። ሙግቱ የተካረረ ቢመስልም፣ ላስተዋለ በብዙ ተስፋ ሰጭ ነው። መድረክ የተጋሩና በማኅበራዊ ሚድያ የተወያዩ መሰጠታቸውና ለጌታ ቤት ያሳዩት ቅንዓት የቤቱን ጌታ ለማመስገን ምክንያት ይሰጠናል።

ውይይቱ አብቅቷል ማለት እንዳይመስል፣ በተስተናገዱ አሳቦች ላይ ትዝብቶቼን ባጭሩ ላስፍርና ልጨርስ፦
1/ ሴኩላርና ኃይማኖታዊ። በምሑራን ዘንድ “ኃይማኖታዊ” በሚለው ቃል አተረጓጎም ላይ እስከ ዛሬ ስምምነት የለም። "ሴኩላርና ኃይማኖታዊ"ን አውሮጳውያን በነሲብ የደነገጉት ምዳቤ እንደሆነ አንርሳ። ለዚያውም አፍሪካን፣ መካከለኛው ምሥራቅን፣ እስያንና ላቲን አሜሪካን አይጨምርም፤ ባጭሩ፣ አብዛኛውን ዓለም ማለት ነው። ሴኩላር አእምሮአዊነትን፣ ሥልጣኔና ሳይንስን አውሮጳን። ኃይማኖታዊ ኋላቀርነትና ስሜታዊነትን አውሬነትን አፍሪቃን ይወክላል ነው ነገሩ።
2/ “እውነት እና ፍቅር” እንጂ ትውፊት መመዘኛ ሊሆን አይገባም ተብለናል። በኬንያ በአውሮጳ በደቡብ አፍሪካና በሰሜን አሜሪካ ትውፊት [ወይም ባህላዊ ክርስትና] የኢትዮጵያን ትውፊት መመዘኑ ተገቢ ነው? ለመሆኑ ትውፊት የሌለበት ምድር አለ? ትውፊት ጠቀሜታ እንደሌለው መታሰቡ ተገቢ ነው? እውነት እና ፍቅር እንዴት ይተረጎማሉ?
3/ "ሴኩላር ሙዚቃ ኃጢአት ነው የተሰኘው በኢትዮጵያ ብቻ ነው" ተብለናል። ደግሞ ሴኩላር ሙዚቃ ጥሩና መጥፎ አለው ተብለናል። “ጥሩ” እና “መጥፎ” መስፈርቱ ምን እንደሆነ አሳማኝ መረጃ አልቀረበም።
4/ “ኃጢአት ነው፣ ኃጢአት አይደለም” ሳይሆን፣ “ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ጥቅም ነው?” እንበል ተብለናል። ልዩነቱ ምንድነው?
5/ “ወንድምህንም በመብል ምክንያት የምታሳዝን ከሆንህ እንግዲህ በፍቅር አልተመላለስህም። ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለትን እርሱን በመብልህ አታጥፋው… መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፥ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም” [ሮሜ 14፡15፣ 1ኛቆሮንቶስ 8፡13] በሚለው ላይ። “ሥጋ መብላት አለመብላት በትምህርት ሊስተካከል የሚችል ነገር ነው እንጂ ዘላለማዊ ዘላቂ ነገር አይደለም፤ መብላት የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን መብላት ችግር እንደሌለው አስተምሬ አብረን እንበላለን” [ደማቅ ጭብጨባ]። እርግጥ አንዳንዱን ነገር በማስተማር ማቃናት ይቻል ይሆናል። ለምሳሌ፣ ለጣዖት የተሠዋውን ከኅሊናና ጣዖቱን ፍራቻ የማይበሉ ይኖራሉ፤ “ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ” ሲያውቁ ግን ጌታን አመስግነው ይበላሉ። ጳውሎስ “አልበላም” ያለው ትምህርት ስለጎደለው ይሆን? 
6/ “ቤት ያጣው ቤተኛ” የቀሰቀሳቸውን ጥያቄዎች በድብቅ ይዘው ሲጓዙ የኖሩ መኖራቸው ግልጽ ነው። ወንድም ዮናስ ርዕሱን ለውይይት በማብቃቱ ሊመሰገን ይገባል። ያሁኑ ትኩረት በ “ዘፈን” ላይ ቢሆንም ወንድም ዮናስ የቤተክርስቲያንን ማኅበራዊ ድርሻ፣ ወዘተ፣ በሚመለከት ያነሳቸው ነጥቦች ምን ምላሽ ይሰጣቸዋል?
7/ “ጥሩ ግጥም፣ ጥሩ ሙዚቃ እንዴት ኃጢአት ሊባል ይችላል?” የተባለውም መልስ ይሻል። ጥያቄው ጥያቄም ያስነሳል፦ “ጥሩ” ምንድነው? ጥሩ ግጥም፣ ጥሩ [ቪዲዮ] ሙዚቃ፣ ጥሩ ዝማሬ ሊወጣው ይችላል? የዝማሬ ተግባሩ ቀልብን በጸሎት ወደ አምላክ ማቅናት ነው ብንል ስንቶች መመዘኛውን ያሟላሉ? [እዚህ እዚህ ይጠቁሙ፤ ድምጹን አጥፍተው ያድምጡ፤ ዐይኖን ጨፍነው ያድምጡ፤ ደግመው ዐይኖን ገልጠው ያድምጡ። እስቲ ምን ተረዱ?]። ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ስለ ኪነጥበብ ያላት አስተምህሮ እንዴት ይብራራ? እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ የኪነ ጥበባትም መገኛ ነው? ይኸ ራሱን የቻለ ጥናት ይሻል። ወንጌላውያን ምንጊዜም እንደ አሜሪካ እንደ ኬንያና እንደ እስራኤል መሆን አይጠበቅባቸውም። ከሌሎች አንማርም ባንልም፣ የእግዚአብሔር ቃል የሚተረጎመው ከምናውቀው ተነስቶ መሆኑን አንዘነጋም።
8/ ሥራ አጥነት ባይኖር የ “ቤት ያጣው ቤተኛ” ይዘትና ሙግት ምን ይመስል ነበር? ለገበያተኛ “መንፈሳዊነት” እና ለተሸቃቀጠ አስተምህሮ፣ የቤተክርስቲያንን ሥልጣን ለሚቀናቀን ግለኛ “ሚኒስትሪ” መበራከት ምክንያቱ ሥራ አጥነት እንደሆነስ? የሙዚቃ ምሩቃን ወደ ዓለም መኮብለል እውን የቤተክርስቲያን ጥፋት ነው? የምሩቁ [የአማኙ] ኃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው? የአመራር መጓደልን በግለሰብ [በወንድም ዮናስ] ማመካኘት ተገቢ ነው? ሥራ አጥነትን አጥብቆ መጠየቅ ማኅበራዊ ምክንያቶችን ማጤን ስለሚያስከትል ከ “ፖለቲካ” ጋር ላለመነካካት ይሆን? በአምልኮ የምናሳብበው ከተጠያቂነት ለመሸሽ ይሆን?
9/ ቤተክርስቲያን ለዘማሪ ቀርቶ ለወንጌላዊ የምትሰጠው ድጎማ ኑሮን ማሸነፍ የማያስችል የጉስቁልና ኑሮ መሆኑ ብዙዎችን ከዓለም ጋር እንዲደራደሩ አስገድዷቸው ይሆን? “ሙሉ ወንጌል” [የሐዋ. ሥራ 20፡27] ከማስተማር ይልቅ መንፈሳዊ ልምምዶች ላይ የማተኮር ውጤት ይሆን? ተከታዩ ትውልድ አመራሩን እንዲረከብ በጊዜ ካለማለማመድ የተነሳ ይሆን? መረሳት የሌለበት አንድ እውነት፦ ለክርስቶስ ተከታዮች በመንፈስ ቅዱስ ከመሞላት፣ ከክርስቲያናዊ ኅብረት፣ ከመጸለይ፣ ቃሉን ከመውደድና ከማጥናት፣ ለቤተክርስቲያን ከመገዛት፣ ጸጋን ለይቶ ከማወቅና ጌታና ሕዝቡን ከማገልገል ውጭ አማራጭ እንደሌለ ነው። ዛሬ የቸገረው ማደበላለቅና መንፈስን አለመለየት ነው።
10/ ሙግቱ እንግዲህ ይህን ይመስላል። አሁን የቀረው፣ የሙዚቃ ምሩቃን ጉዳይ እንዴት ይታይ፣ እንዴት ይተግበር የሚለው ነው።

[ምንጭ፦ በፌስቡክ = ጳውሎስ ፈቃዱ፣ ጌታሁን ሔራሞ፣ ዮናስ ጎርፌ፣ ተስፋዬ ሮበሌ፣ ተካልኝ ዱጉማ፤ ዘላለም መንግሥቱ። ከነ “ወዳጆቻቸው” እና “ተከታዮቻቸው”። ኪያቶክሾው በዩቱብ]

ምትኩ አዲሱ

ተጨማሪ ለማንበብ እዚህ ይጠቁሙ