የእግዚአብሔር ስሞችና በእግዚአብሔር ስም የሚመጡ መልእክተኞች

yhwh

እግዚአብሔር ማን ነው? መታወቂያ ስም አለው? ካለው ስሙ ማን ነው? ይኸ የኖረ ጥያቄ ነው። ስሙን የገለጠላቸውና ስሙን ያወቁ በስሙ ይጠሩታል። እውነተኛ ስሙ ከሆነ “አለሁ!” ይላል። “አለሁ!” ካላለ ወይ ስሙ አይደለም ወይም ቀደሞውኑም የፈጠሩት እንጂ እውነተኛው እግዚአብሔር አይደለም።

“እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት …ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ያውቃሉ፤ የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ … ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፥ እኔ ግን አወቅሁህ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤ እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ" [ዮሐ 17: 3፣ 6-8፣ 25-26]።

እግዚአብሔር ማንነቱን፣ ስሙን ካልገለጠ በቀር ማንም ሊያውቀው አይችልም። እርሱ ግን ስሙን ገልጧል። ሊያውቁት ለሚወድዱ ሁሉ ዛሬም ስሙን ይገልጣል። ስሙን ያወቁ የመሰላቸው ሁሉ ስሙን ያውቃሉ ማለት ግን አይደለም። ስሙን ይወቁ አይወቁ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ" [ማቴዎስ 7:20-23]። በስሙ የመጡ ሁሉ እርሱ ልኳቸው ነው ማለት አይደለም። አንዳንዶች ራሳቸው ያወጡለትን ስም ይዘው ሳይልካቸው የወጡ ናቸው። እነዚህም የሐሰት መልእክተኞች፣ አምላካቸውም ጣኦታት ይሰኛሉ።

"በእግዚአብሔር [በጌታ] ስም የሚመጣ ቡሩክ [የተባረከ] ነው [መዝሙር 118:26፤ ማርቆስ 11፤9]። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን" [ገላትያ 1:8፣9]። እንግዲህ፣ እውነተኛ ስሙን ማወቅና አለማወቅ ወይ ለበረከት ወይም ለእርግማን ነው። ስሙን ማወቅ በስሙ የሚመጡትን ማንነት ለመለየት እጅግ አስፈላጊ ነው። ፓስተር ዘላለም መንግሥቱ ስለ እግዚአብሔር ስሞች መጽሐፍ ቅዱሳዊና እጅግ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት አቅርቦልናል። በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሊነበብና ሊወያይበት የተገባ ጽሑፍ ነው፤ ይህን የሚያነብቡ ላላነበቡ ያስነብቡ፦ ኢትዮፕያንቸርች አዘጋጅ።

“… ከባቢሎን ግንብ በፊት የሰዎች መግባቢያ ቋንቋ የትኛው ቋንቋ ስለመሆኑ ማረጋገጫ አናገኝም። ከአዳም እስከ ኖኅና ልጆቹ ቋንቋ ምንመሆን የምናውቀው የለንም። እግዚአብሔር ስሙን የተናገረው ለሙሴ ሲሆን ያ ስም የተነገረበትና የተጻፈበት ቋንቋ ዕብራይስጥ ነው። የዕብራይስጥ ቋንቋም እንደ ሌሎቹ ቋንቋዎች ጅማሬው የባቢሎን ግንብ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ቢያንስ እንዳይደለ ማስተባበል አይቻልም። ይህንን እግዚአብሔር ስሙ ማን መሆኑ ተጠይቆ የስሙን ማንነት የተናገረበትን ስፍራ በማጤን እንጀምር፤ ያም ዘጸ. 3 ነው። ዘጸ. 3፥13-15 እንዲህ ይላል፤ 13፥ ሙሴም እግዚአብሔርን፦ እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፦ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ፦ ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው። 14፥ እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ «ያለና የሚኖር» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው። 15፥ እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፦ የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው። በቁ. 13 ሙሴ ስሙን ቢጠይቁት ማን እንደሚል ነው የጠየቀው። በግብጽ ብዙ አማልክት አሉ። ሁሉም ስም አላቸው። አማልክት በስማቸው ይታወቃሉ። የሙሴ ጥያቄ የሕዝቡን እውቀት የሚወክልና የሚያመለክት ነው። እግዚአብሔር ስሙን፥ 'ያለና የሚኖር' ብሎ ነው የነገረው …” ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ።